አዕምሮ በሥራ ሲጨናነቅ አልያም በሃሳብ ሲወጠር ለአፍታ ዘና የሚያደርገውን ቢያገኝ አይጠላም። እንዲህ በሆነ ጊዜ የምርጫው ጉዳይ እንደየ ሰው ፍላጎትና አቅም ሊለያይ ይችላል። አንዳንዱ ከከተማ ወጣ ብሎ ከባህር ዳርቻው አሸዋ ጋደም ማለት ፍላጎቱ ነው። ለእሱ መዝናናት ማለት ንጹህ አየር እየሳቡ ተፈጥሮን ማድነቅ ሊሆን ይችላል።
ሌላው ደግሞ አውሮፓ አሜሪካ ወጣ ብሎ፤ ከሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ፣ ከታዋቂ የገበያ ማዕከላት መገኘቱን እንደ መዝናናት ይቆጥረዋል። ራስን ከስፖርት ማዘውተሪያዎች አስተዋውቆ ጤና እየጠበቁ መንፈስን ማርካትም አንዱ የመዝናናት መገለጫ ነው ሊባል ይችላል።
መዝናናት እንግዲህ ሰፊና መልከ ብዙ ነው። እንደየሰው አቅምና ፍላጎት ቢለያይም ከሰው ልጆች የዕለት እንቅስቃሴዎች ጋር በእኩል ይራመዳል። ወደ እኛ ማህበረሰብ መለስ ስንል ግን የመዝናናት ሁኔታ ሊዥጎረጎር ይችላል። ይህ እንግዲህ እንደየሰው አቅምና ፍላጎት ብለን ከለየነው ነው።
አብዛኛው ግን ከቤቱ ተቀምጦ የሚዝናናበት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሊኖረው እንደሚችል ያስማማናል። አይነት ደረጃው ይለያይ እንጂ አሁን ላይ በየቤቱ ቴሌቪዥን የሌለው ሰው ይኖራል ለማለት አያስደፍርም።
የዛሬን አያድርገውና ቴሌቪዥን ብርቅ ሆኖ በጥቂት ሰዎች ቤት በነበረ ጊዜ ራስን ለማዝናናት ወደጎረቤት ጎራ የሚለው ተመልካች ጥቂት አልነበረም። እንዲህ ሲሆን ግን ሁሉም እንዳሻው የፈለገውን መርጦ ያያል ማለት አልነበረም። ምንጊዜም ይህ አይነቱ ፍላጎት የሚወሰነው በቴሌቪዥን ባለቤቶች ምርጫ ብቻ ይሆናል። በተለይ በዘመኑ የነበሩ ህጻናት ቴሌቪዥን ለማየት ነጻነታቸው በገደብ እንደነበር የሚያውቅ ያውቀዋል።
የዛኔ በእነሱ ዕድሜ ተመራጭ የነበረው ፕሮግራም በልጆች ክፍለ ጊዜ የሚተላለፈው የ‹‹አባባ ተስፋዬ የተረት ወግ ነበር። ከዚህ በዘለለ ከወላጆቻቸው ጠጋ ብለው የሚያዩት የ ‹‹ሕብረትርዒት›› የሙዚቃ ምርጫ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ተወዳጅ ፕሮግራሞች ታዲያ ከሰው ቤት ገብቶ ደልቀቅ ብሎ ማየት ክልክል ነበር።
የዛን ዘመን ህጻናት ቴሌቪዥን ከማየታቸው አስድቀሞ በአቅማቸው ለቤቱ ባለቤቶች የጉልበት ግብር ሊከፍሉ ግድ ነው። በትንሹ በእነሱ አቅም የሚጸዳ ቤት፣ አልያም የሚታጠብ ዕቃ ካለ እንደሚሆን ማድረግ ግዴታቸው ይሆናል ። ይህ ሁሉ ዋጋ የሚከፈለው ታዲያ ራስን ለማዝናናትና ደስታን ለመፍጠር ሲባል ነው ።
በወቅቱ ዘመኑ የሚፈቅደው የመዝናኛ አማራጭ ከዚህ የዘለለ አልነበረም። ሁሉም አካባቢውን ተጠቅሞ አእምሮውን ዘና ፈታ ለማድረግ የቴሌቪዥን መስኮት ላይ ማተኮር ነበረበት ። ይህ ዘመን ጥቂት ፈቀቅ ብሎ አንድ ርምጃ እንዳለፈ ፣ የቪዲዮ ፊልሞች ለመዝናኛነት ይመረጡ ያዙ።
በዘመኑ ሁሉም ዘንድ ይህ አማራጭ ነበር ባይባልም ቪዲዮ ይሉት ማጫወቻ በየቤቱ መዘውተሩ በርካታ ተመልካቾችን አላሳጣም። በጊዜው በየቦታው በገንዘብ የሚከራዩ ምርጥ የውጭ ሀገራት ፊልሞች ተወዳጅነት ነበራቸው ።
ወቅትና ጊዜ ሲለወጥ ደግሞ ቀን ቆጥሮ አሮጌው በአዲስ ተተካ። የቴክኖሎጂው ጫፍ ከብዙዎች ሲደርስም ትናንት ያልነበሩ መገልገያዎች ከብዙዎች ዘንድ ተገኙ ። የሲዲ ፊልሞች ፣ሙዚቃዎችና አልበሞች ለብዘኃኑ ተደራሽ መሆን ያዙ።
ውሎ አድሮ ደግሞ ዓለምን በአንድ የሚያገናኘው የማህበራዊ ሚዲያ መረብ በሁሉም ሰው መዳፍ አረፈ። የቴክኖሎጂው መፍጠን ጥቅም ጉዳቱ፣ ትርፍ ኪሳራው ከትውልድ ተጠጋ። ይህን ተከትሎ መዝናናት ፣ መደሰት ይሏቸው እውነታዎች በቀላል ዘዴና መንገድ ተተግብረው ለብዙዎች ዕውን ሆኑ ።
ወዳጆቼ መነሻዬን አልዘነጋሁም። አስቀድሜ እንዳልኳችሁ ለማውሳት የፈለግሁት የመዝናኛውን ነገር ነው ። ‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› ሆኖብኝ እኛንና የቴሌቪዥንን ነገር መለስ ብዬ አስታወስኩ። ይህ አጋጣሚ የዘመንኛውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና የአስተዋዋቂዎቹን ጉዳይ እንድታዘበው አስገደደኝ።
ለጊዜ ምስጋና ይግባወና ዛሬ ላይ ሁሉም ቤት በሚያስብል ሁኔታ ቴሌቪዥን ይሉት ነገር አይጠፋም። የምልከታው ጉዳይ እንደየፍላጎት ቢሆንም በተለያዩ ጣቢያዎች የመዝናኛ ዝግጅቶች ይተላለፋሉ። ‹‹መዝናኛ›› የሚለው ሃሳብ በብዙዎች ዘንድ የሚኖረውን ትርጉም መለየት ባይቻልም ተመልካቹ ግን ይህን ቃል በሚሸከም አግባብ ለዓይኑ የሚጠብቀው ነገር መመኘቱ ዕሙን ነው ።
ብዙዎቻችን እንደምንታዘበው ግን በየቴሌቪዥን መስኮቶች የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የልብ አድራሽ የሚባሉ አልሆኑም። በአንድ ትዕዛዝ አንድ አይነት ጉዳይ አስተላልፉ የተባሉ ይመስል አብዛኞቹ በተመሳሳይ ይዘት መገለጥ ልምዳቸው ሆኗል ። በርካቶች በእረፍት ሰአታቸው ቤት በተገኙ ጊዜ ከቴሌቪዥን መስኮት ማተኮራቸው አይቀሬ ነው።
በእነዚህ ቀናት ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች ሰአት ለይተው ፣ ጣቢያ መርጠው እንዳያተኩሩ ግን ምርጫው ጠባብ ይሆናል ። ብዙዎች እንደሚሉት አንዱ ጣቢያ ሲታይ ወንድና ሴት አስተዋዋቂዎች ከስቱዲዮ ተቀምጠው ያለመታከት የሚያወሩት የተለመደ ወሬ ያሰለቻል።
እሱን ለውጠው ወደሌላው ሲሻገሩም ጉዳዩ ተመሳሳይ ነው። የሰዎቹ መቀየር እንጂ የሚነሳው ርዕሰ ጉዳይ እምብዛም ለውጥ የለውም። አሁንም ጥቂት አየት አድርገው ሪሞቱን ወደሌላ ያዞሩታል። በዚህም ጣቢያ በሌሎቹ አይተው ካለፉት አይነት ይዘት ጋር ይፋጠጣሉ። ይህ የሚሆነው በእረፍት ቀናት በተመሳሳይ ሰአትና ጊዜ በሚተላለፉ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ነው።
በጣም አስገራሚው ጉዳይ በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች የሚታዩ አቅራቢዎች ተመሳስሎ ነው። አሁን ላይ ሁሉም በሚባል መልኩ በተጋነነ የሜካፕ ገጽታ ብቅ የሚሉ የስቱዲዮ ጋዜጠኞች በእጅጉ በርክተዋል። ሁሉም የአንድ እናት ልጆች እስኪመስሉ የሚጠቀሙት ሜካፕም ኢትዮጵያዊ ማንነትን እያስረሳ ነው። ይህ እውነታ ደግሞ በእንግድነት የሚቀርቡት ላይ ጭምር ከማን አንሼነትን እያሳየ መሆኑን ልብ ይሏል። እርግጥ ነው ራስን አሳምሮና በተገቢው ተውቦ መታየት የግድ ይላል። አሁን ላይ ግን ይህ አይቱ ሀገርኛ ምግባር ሙሉ ለሙሉ እየጠፋ ነው ለማለት ያስደፍራል ።
በዘመኑ ደጋግመን እንደምናስተውለው በቴሌቪዥን የመዝናኛ ጣቢያዎች የሚቀርቡ በርካታ እንግዶች የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች እየሆኑ ነው። ኩሽና መግባቱ ግድ የሆነ ይመስል በአንዱ ጣቢያ የታየው ጥቂት ለወጥ ብሎ በሌላው መደገሙ ተለምዷል። ይህ ደግሞ በትክክል የተመልካቾችን ዓይን ማረፊያ የሚያሳጣ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ እንግዶች ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች የመናገር ፍላጎት በግልጽ ሲገደብ ይስተዋላል። ምናአልባትም የጠያቂዎቹ ፍላጎት ብቻ በሚመስል አቅጣጫ ቃላቸው ሲገራ ማየት ያስተዛዝባል። ከዚሁ ተያይዞ በቡድን ጨዋታ ለመዝናኛ ተብለው የሚቀርቡ አንዳንድ ጥያቄዎች የሚያሸማቅቁ ናቸው። በተለይ የጥንዶችን ግንኙነት በሚመለከት የሚጠየቁ ከሆነ ከማስፈገግ ባለፈ አስደንጋጭና ያልታረሙ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል።
ማዝናናት ሲባል ማሳቅ ብቻ ሊሆን አይገባም። በዋዘኛ ንግግሮች መሀል የሚያስተምሩ፣ ቁምነገር የሚያስጨብጡ ይዘቶች ቢቀርቡ ነውርነት የለውም ። የእኛዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ግን ማዝናናትን በሳቅና ፈንጠዝያ ብቻ ከበው አሰልቺ የሚባል ይዘቶችን ‹‹እንካችሁ›› ይላሉ።
አንዳንዶቹን በጥልቅ ካስተዋልናቸው ፕሮግራሞቻቸው በቀጥታ የተቀዱት ከውጭው ዓለም የመዝናኛ ፕሮግራም ነው። ይህ ሲደረግ ግን በሁለቱ መሀል የሚኖረውን የባህል፣ የኑሮና የአስተሳሰብ ግጭቶችን ልብ ያሏቸው አይመስልም ። ይዘቶቹ እንደወረዱ መተግበራቸው ቀለማቱ በአንድ ሳይዋሀዱ የባዕድነት ስሜት እንዲንጸባረቅ አስገድዷል። መዝናናት አሰልቺ ሆኖም ሪሞት ያስወረውራል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016