ጉዞ ወደ ትምህርት ቤት

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? እንኳን ለ2016 ዓ.ም በሠላምና በጤና አደረሳችሁ? “እንኳን አብሮ አደረሰን” አላችሁ አይደል? ልጆች ጎበዞች። የአዲስ ዓመት በዓል እንዴት አለፈ? ደስ በሚል መንገድ እንዳሳለፋችሁት፤ ምንም ጥርጥር የለኝም። ክረምቱንም የተለያዩ መጻሕፍትን ስታነቡ፣ ወላጆቻችሁን ስታግዙ፣ እንዴት ማቀድ እንዳለባችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር ስትመካከሩ እና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት እንዳሳለፋችሁ እምነቴ ነው። ልጆችዬ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ አልናፈቋችሁም? መምህራኖቻችሁስ? መልሳችሁ ‹‹በጣም ናፍቀውናል፡፡›› የሚል እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

ከመስከረም 07 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት እንደሚጀመር በመንግስት በኩል ተገልጿል። ስለዚህም ከዚህ በኋላ ጉዟችሁ ወደ ትምህርት ቤት ነው። ለትምህርት ቤት የሚሆኗችሁን ቁሳቁሶች በሚገባ እንዳዘጋጃችሁ ሙሉ እምነት አለኝ። የናፈቃችኋችሁንም ልታገኟቸው ነው።

ልጆች መልካም እውቀትን ለመገብየት ወደ ትምህርት ቤት ማቅናት ከተማሪዎች የሚጠበቅ የእለት ተእለት ተግባር ነው። ነገ ሕይወታችሁ ተቀይሮ እንዲሁም ትልቅ ደረጃ ደርሳችሁ፤ ከራሳችሁ አልፋችሁ እና ተርፋችሁ ለወገን እንዲሁም ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ እንድትሆኑ ትምህርት ቤት ገብታችሁ መማር ይኖርባችኋል። ማንበብ እና መጻፍ ከመቻል በዘለለም ምርምሮችን፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን፣ ችግር ፈቺ ሃሳቦችን ለማመንጨት፣ እና በሌሎች ሥራዎች ወገናችሁን ለመጥቀም በትምህርት ቤት ሕይወት ማለፍ ጠቃሚው ነገር ነው። ለዚህም ነው ወላጆቻችሁ እና አሳዳጊዎቻችሁ እናንተን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት። ለዚህም ነው፣ መምህራንም እናተን ለማስተማር ‹‹ደከምኝ፤ ሰለቸኝ፡፡›› ሳይሉ ብዙ እውቀት እንድትጨብጡ ያላቸውን እውቀት በማካፈል ዘወትር እናንተን የሚረዷችሁ።

ልጆች ባለፈው ዓመት ምን አይነት ተማሪዎች ነበራችሁ? ጎበዝ፣ መካከለኛ ወይስ ዝቅተኛ ደረጃ፣ ረባሽ ወይስ ጨዋ ተማሪ ነበራችሁ? ይህንን የምጠይቃችሁ ለምን መሰላችሁ? የእናንተ ጸባይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በትምህርታችሁ ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ነው። ከዚህ አንጻር በጥንካሬያችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል። ደካማ ጎናችሁም ምን እንደሆነ በመለየት ብታሻሽሉ በትምህርታችሁ ውጤታማ እንድትሆኑ ያግዛችኋል። ከዚህ በተጨማሪም ያልገባችሁን ትምህርት መምህሮቻችሁን በመጠየቅ፤ እንዲሁም፣ ከጓደኞቻችሁ ጋር በጋራ በማጥናት እና በመረዳዳት ብታሳልፉ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት እንድታመጡ ይረዳችኋል፡፡

በመምህራኖቹ የሚሰጣችሁን የክፍል እና የቤት ሥራም በሚገባ በመሥራት ጎበዝ ተማሪዎች መሆን ይጠበቅባችኋል። ወላጆቻችሁ እና መምህራኖቻችሁ በጣም ደስ ስለሚሰኙባችሁ በርትታችሁ አጥኑ እሺ ልጆች። ሌላው ማወቅ ያለባችሁ ነገር የተማራችሁትን ትምህርት በፈተና ወቅት ብቻ ማጥናት ተገቢ አይደለም። የጥናት ሰዓት በማውጣት በፕሮግራማችሁ መሠረት ማጥናት ይኖርባችኋል። ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ ልብስ ስትቀይሩ ቦርሳችሁን እና የደንብ ልብሳችሁን (ዩኒፎርማችሁን) ለቀጣዩ ቀን በቀላሉ እንድታገኙ አጣጥፋችሁ ማስቀመጥ ይኖርባችኋል። እንዲሁም ትምህርት ቤት ውስጥ ስትጫወቱ ይሁን ምግብ በምትመገቡበት ሰዓት እንዳይቆሽሽባችሁ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል፡፡

የሚከብዳችሁ የትምህርት ዓይነት ካሉም እርሱን ለይቶ ለመምህራን፣ ለአስጠኚዎቻችሁ፣ ለታላላቅ ወንድም ወይም እህት እና ወላጆቻችሁ በመንገር እገዛን መጠየቅ ይኖርባችኋል፡፡

ወላጆችም ልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት ልካችሁ ጥሩ እውቀት ገብይተው የነገ ሀገር ተረካቢ ይሆኑ ዘንድ በሚደረገው ሂደት ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን በሚገባ እየተጠባበቃችሁ እንደሆነ እተማመናለሁ። ስለዚህ እንደ ወላጅ፤ ለተማሪ ልጆቻችሁ የትምህርት ግብአት (ደብተር፣ ቦርሳ፣ እርሳስ፣ ስክሪቢቶ፣ የደንብ ልብስ እና የመሳሰሉትን) ከማዘጋጀት በተጨማሪ ልጆቻችሁ ምን እንደተማሩ እና ውሏቸው ምንም እንደሚመስል በመጠየቅ የልጆቻችሁን የትምህርት ቤት ውሎ በሚገባ መረዳት ይኖርባችኋል። በተጨማሪም የጥናት ሰዓት በማውጣት ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ማገዝ ይጠበቅባችኋል፡፡

በተለይም የባለፈው የትምህርት ዘመን ለልጆቻችሁ ምን ዓይነት እንደነበር ከመምህራን በመቀጠል እናንተም በሚገባ ታውቁታላችሁ ተብሎ ይታመናል። እናም ወላጆች የልጆቻችሁን ጥንካሬ እንዲቀጥሉበት፤ ደከም ያሉበትን ደግሞ በማስጠናት ብሎም ክትትል በማድረግ ማበረታታት ይጠበቅባችኋል። ልጆቻችሁንም ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ በራሳቸው መንገድ ነገሮችን እንዲረዱ ማገዝ ተገቢ ይሆናል።

ከምንም በላይ ደግሞ ልጆች፤ ዘወትር ወደ ትምህርት ቤት ስትሄዱ የግል ንጽህና (ጠዋት ጥርስ መቦረሽ፣ ፊት መታጠብ፣ ጥፍር አለማሳደግ፣ ጸጉር መታጠብ …) መጠበቅ የሚኖርባችሁ ሲሆን፤ እናንተ ማድረግ የማትችሏቸው ለምሳሌ ሴቶች ከሆናችሁ ጸጉራችሁን መሥራት፤ ወንዶች ደግሞ ጸጉር መቁረጥ እና መሰል ነገሮች ሲያጋጥማችሁ የወላጆቻቸሁን፤ ወይም፣ የሌላ ሰው እርዳታ እንድታገኙ ከወላጆቻችሁ ጋር መነጋገር ይኖርባችኋል።

ልጆችዬ ትምህርታችሁን በሚገባ ከተከታተላችሁ፣ ያልገባችሁን ከጠየቃችሁ፣ የጥናት ሰዓታችሁን በሚገባ ከተጠቀማችሁ፤ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት ከሚያመጡት ተማሪዎች መካከል በቀዳሚነት ትቀመጣላችሁ፡፡

በሉ ልጆችዬ፣ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስከምንገኛኝ ድረስ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላችሁ በመመኘት ለዛሬ በዚሁ እንሰነባበት፡፡

ደህና ሁኑ ልጆች፣ ደህና ሁኑ!!!

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You