የተሻለ ሥራ፣ ትምህርት፣ ኑሮ፣ ህክምና፣ … ወዘተ ፍለጋ በአራቱም አቅጣጫ ወደ መዲናዋ ሰዎች ይጎርፋሉ። በዚህ የተነሳ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክፉና ደጉን በውል ያልለዩ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ታዳጊዎችን ጭምር በከተማዋ ጎዳናዎች ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ታዳጊዎች የሚጠጉበት ዘመድ፣ አይዟችህ የሚላቸው ወገን ከአጠገባቸው ባለመኖሩ ውሎ አዳራቸው ጎዳና ላይ ነው። ከጎዳና ሕይወት ወጥተው የተሻለ ኑሮ ለመምራት የቀን ሥራ በመሥራት፣ ጫማ በመጥረግ፣ ቆሎ፣ ማስቲካ፣ ሎተሪ … ወዘተ እያዞሩ በመሸጥ፣ የሚዛን አገልግሎት መስጠት የመሳሰሉ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው እራሳቸውን ለመቀየር ሲታትሩ ይስተዋላሉ።
በአንጻሩ በልጅነታቸው ከቤተሰብ ተለይተው ጎዳና ላይ የወደቁ አብዛኞቹ ታዳጊዎች ገና በለጋ እድሜያቸው የሱስ ምርኮኛ ሆነው፣ ነገ ላይ ሠርቶ የተሻለ ሕይወት የመምራት ህልም ሆነ ሞራል አጥተው ይታያሉ። ታዳጊዎቹ ተሯሩጠው ሠርተው በሚያተርፉበት የወጣትነት እድሜያቸው በተለይ በከተማዋ የትራፊክ መብራት ያለባቸው አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች መብራት ይዟቸው ሲቆሙ እጃቸውን ለምጽዋት ሲዘረጉ በየጎዳናው ማየት የተለመደ ነው። ከዚህ ባለፈም ሱሳቸውን የሚያስታግሱበት ገንዘብ በቀላሉ ለማግኘት ሲሉ የተለያየ የወንጀል አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀው የሚዳክሩም ብዙዎች ናቸው።
በተመሳሳይ ወጣት ተስፋዬ መሃመድ (በቅጽል ስሙ ፋራው) እና አማኑኤል መሰለ (በቅጽል ስሙ ባሪያው) ገና በታዳጊነት እድሜያቸው ከደቡብ ክልል የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። እንደመጡም የሚያርፉበት ዘመድ ስለሌላቸው ኑሯቸውን ጎዳና ላይ አድርገው በወዛደርነትና ያገኙትን የቀን ሥራ በመሥራት ሕይወታቸውን መግፋት ጀመሩ። እንዲህ ዓመታትን በጎዳና ሕይወት ያሳለፉት ወጣቶቹ፤ ቀስ በቀስ ሱስ ተለማመዱ። ይህኔ የቀን ሥራ ሠርተው የሚያገኙት ገቢ ጉሮሮን ከመሸፈን አልፎ ሱሳቸውን ሊያረካላቸው አልቻለም። በዚህም ሳይወጡ፣ ሳይወርዱ በቀላሉ ገንዘብ አግኝተው ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት እንዲሁም ሱሳቸውን የሚያረኩበት ሌብነት ውስጥ ለመግባት ይወስናሉ።
ይህን ከጀመሩ በኋላ ሌሎች ጓደኞቻቸው በጠዋት ተነስተው ወደ ሥራ ሲያመሩ፤ እነሱ ግን ተኝተው ያረፍዳሉ። ከመኝታቸው አርፍደው ከተነሱ በኋለ ቀን ላይ ጫት ሲቅሙና ሲጠጡ ይውላሉ። ማታ ማታ የሌብነት ወንጀል ለመፈጸም ይሠማራሉ። እንዲህ የሰዎችን ላብ እየነጠቁና የሰው ደም እያፈሰሱ ባገኙት ገንዘብ ዛሬን ሱሳቸውን አርክተው፣ ያማራቸውን በልተው፣ ጠጥተው ተደስተው ይውላሉ። ነገን አያስቡም። ምን ይገጥመናል? ምን ላይ እንወድቃለን? ብለው አይጨነቁም።
እንዲህ እንደወትሮው ሁሉ ጓደኛማቾቹ ሦስት ሆነው (ተስፋዬ፣ አማኑኤል እና በረከት) በቀን 15/06/2011 ዓ.ም የሌብነት ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ ቀን ጫት ሲቅሙ፣ ሲያጨሱ፣ ሲጠጡ ውለዋል። በዚሁ ዕለት ማታ በፕላስቲክ የውሃ መያዣ (ሀይላንድ) አረቄ ገዝተው ይዘው እየጠጡ የሌብነት ወንጀል ለመፈጸም በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ጀሞ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ገብተው ይዘዋወራሉ።
ከምሽቱ በግምት ሶስት ስዓት ከ15 ደቂቃ አካባቢ ሲሆን፤ እሰይ ገ/ሕይወት የተባለ ግለሰብ ብቻውን ስልክ እያወራ ከዋናው አስፓልት ወደ ጀሞ የጋራ መኖሪያ ቤት አንደኛ በር በኩል እየሄደ ይመለከቱታል። ከሶስቱ ጓደኛማቾች አንደኛው ተስፋዬ የተባለው ቀስ ብሎ መንገደኛ መስሎ ወደ ግለሰቡ ተጠግቶ በጠረባ ሲመታው የእግረኛ መንገድ ጠርዝ ላይ ይወድቃል። ይህኔ ሰውየው ለብቻ፣ ስልኩ ለብቻ ይወድቃል። ሰውየው እያወራበት የነበረውን ቴክኖ ተች እስክሪን የእጅ ስልክ አማኑኤል እንዳነሳው፤ ሰው ሲመጣባቸው ሶስቱ ጓደኛማቾች ስልኩን ይዘው በተለያየ አቅጣጫ እሮጠው ይሠወራሉ።
እግር ጥሏቸው በአካባቢው የደረሱ ሰዎችም “እዚህ አካባቢ ሰው ወድቋል” ብለው ጀሞ አንድ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ያመለክታሉ። በወቅቱ ተረኛ የነበረው ፖሊስም ወደ ስፍራው አቅንቶ ተጠግቶ ሲመለከት ፈርጠም ያለ፣ የሱፍ ልብስ የለበሰ ሰው በፊት ለፊቱ በአፉ ተደፍቶ ወድቆ፤ በጀርባው፣ በአፍና በአፍንጫው ከፍተኛ ደም እየፈሰሰው ሕይወቱ አልፎ ይመለከታል። ፖሊስም በወቅቱ በቅርብ እርቀት የነበሩ የተከፈቱ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች ባለቤቶችን ስለሁኔታው እንዲያስረዱት ቢጠይቅም ይሄነው የሚል ፍንጭ ያጣል።
በኋላም በአካባቢው የተሰበሰቡ ሲቪል ሰዎች “የሟች ኪስ ውስጥ መታወቂያ ካለ ለቅርብ ተጠሪው እንደውል” ብለው አንድ ሰው ከሟች ኪስ ዋሌት ቦርሳ አውጥቶ ለቅርብ ተጠሪው “እሰይ እንደዚህ ያለአካባቢ ታሞ ወድቋል” ብሎ በስልክ ደውሎ ይነግራል። ሟች የቅርብ ተጠሪዬ ብሎ መታወቂያው ላይ አስመዝግቦ የነበረው የባለቤቱ የወይዘሮ እሌኒ ከፍቶ ስልክ ቁጥር ነበር። ወይዘሮ እሌኒም በስልክ ተደውሎ ባለቤቷ ታሞ ወድቋል ተብሎ የተነገራት ቦታ በራ ደረሰች። እንደዋዛ የልጆቿ አባት አውላላ አስፓልት ላይ ወድቆ ሕይወቱ አልፎ ስታገኝ፣ ቦታ አልበቃት ብሎ መሬት ላይ እየተንከባለለች ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ልክ ሰውን ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቅስ በድኑን በእጇ እየነካች በስሙ ብትጠራ አቤት የሚላት የለም። ባለቤቷ ላይመለስ አሸልቧል። በመጨረሻም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አምቡላንስ መጥቶ አስከሬኑን ከስፍራው አንስቶ ለምርመራ ይዞ ይሄዳል።
ባልንጀራአማቾቹ ወዴት ተሰወሩ
ባልንጀራአማቾቹ ይህንን ወንጀል ሲፈጽሙ ሰው መጥቶባቸው በየፊናቸው ተበታትነው ነበር። በኋላ ከየአቅጣጫቸው ወጥተው ጀሞ 67 የአውቶብስ ማዞሪያ አካባቢ ሶስቱም ጓደኛማቾች ተገናኝተው በእግራቸው ወደ ዘነበወርቅ አካባቢ አመሩ። በዚያም ሁሌ ወደ ሚጠጡበት ታዬ ግሮሰሪ ቤት ጎራ ብለው ቢራ አዘው መጠጣት ጀመሩ። አማኑኤል የተባለው ከሟች የቀማውን ስልክ አውጥቶ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ እየጠጣ እያለ፤ የግሮሰሪውን ባለቤት አቶ ታዬ ለምለምን ጠርቶ “ይህንን ስልክ ትገዛለህ?” ብሎ ይጠይቀዋል። የግሮሰሪው ባለቤትም ስልኩን አገላብጦ ካየ በኋላ “አልገዛም” ብሎ መልሶ ጠረጴዛው ላይ ያስቀምጣል።
አማኑኤልና የግሮሰሪው ባለቤት እንዲህ እየተነጋገሩ እያለ በዚህ መሀል ተስፋዬ ከተቀመጠበት ተነስቶ እየጠጡበት ካለው ግሮሰሪ ጎን ወደ ሚገኘው በላይ ግሮሰሪ በመሄድ አንዲት ሴተኛ አዳሪ ይዞ ይመጣል። እሷም ከነሱ ጋር ቁጭ ብላ ቢራ አዛ አንድ ቢራ ከጠጣች በኋላ ተነስታ ቀድማ ወደ ነበረችበት በላይ ግሮሰሪ አመራች። ይህኔ ተስፋዬ ሴተኛ አዳሪዋን እግር በእግር ተከታትሏት ወደ በላይ ግሮሰሪ ይሄዳል። በዚያ ሲጠጣ ከነበረ አንድ ግለሰብ ጋር በሴቷ የተነሳ ተጣልቶ ሰውየውን በቢራ ጠርሙስ ፈንክቶ ወደ ታዬ ግሮሰሪ ይመለሳል። ተስፋዬን ብዛት ያላቸው ሰዎች ተከታትለውት ታዬ ግሮሰሪ ውስጥ ገብተው ሊመቱት ሲሉ፤ የግሮሰሪው ባለቤት “አትመቱትም፣ ለሕግ አሳልፌ ነው የምሰጠው” ብሎ እንዳይመቱት ተከላከለለት።
የግሮሰሪው ባለቤት ታዬ ፀቡን ለማብረድና ሰዎቹን ለመገላገል እንዲያመቸው ሲል በእጁ ቆጥሮ የያዘውን አንድ ሺ ስድስት መቶ (1,600) ብር ሶስቱ ጓደኛማቾች ተቀምጠው ይጠጡበት የነበረው ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ለመገላገል ከግሮሰሪው ወጥቶ ነበር። ፖሊስም ተደውሎለት በቦታው ላይ እንደደረሰ ተስፋዬና ተጎጂውን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞ ይሄዳል። ይህኔ ታዬ ወደ ቤቱ ገብቶ ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠውን ገንዘብ ለማንሳት ሲሄድ ብሩ ካስቀመጠበት ቦታ የለም። ነገር ግን “ትገዛዋለህ ወይ?” ብለው ያሳዩት ስልክ እዛው ጠረጴዛው ላይ ተቀምጧል። አማኑኤልም ከተቀመጠበት ስላልተነሳ “ብሩስ?” ብሎ አቶ ታዬ ሲጠይቀው፤ “እኔ አላየሁም” ብሎ ይመልስለታል።
“እንግዳውስ ካንተውጭ እዚህ ቦታ የተቀመጠ ሰው የለም፤ ገንዘቡን አንተነህ የወሰድኸው፤ ገንዘቡን ካልሰጠኸኝ ይሄን ስልክ አልሰጥኽም” ብሎ አቶ ታዬ ከሟች የነጠቁትን ስልክ ከጠረጴዛው ላይ አፈፍ አድርጎ አንስቶ ያዘ። አማኑኤልና በረከት የተባሉት ጓደኛማቾች ደጋግመው “ስልኩን ስጠን” ብለው አቶ ታዬን ሲጠይቁት፤ እሱም በምላሹ “ቆሜ ውዬ የሠራሁት ብር ነው። መጀመሪያ ገንዘቤን መልሱልኝና ስልካችሁን ልመልስላችሁ” ሲላቸው ጥለውት ሄዱ። በነጋታው አማኑኤልና በረከት ደግመው “ስልኩን መልስልን” ብለው ሲጠይቁት በተመሳሳይ “ብሬን መልሱልኝና ስልካችሁን ልመልስላችህ” ሲላቸው፤ “እኛ ያንተን ብር አልወሰድንም፤ ከወሰድከው ውሰደው” ብለው ስልኩን ለታዬ ትተውለት ሄዱ። ከዛ በኋላም ተስፋዬ ከፖሊስ ጣቢያ ተፈትቶ ሶስቱ ጓደኛማቾች አንድ ላይ መጥተው በእሱ ግሮሰሪ ውስጥ እየተጠቀሙ አይቷቸዋል። ነገር ግን ስልኩን ስጠን ብለው ግን ታዬን አልጠየቁትም።
አቶ ታዬም፤ አቶ መዝገቡ ይልቃል ለተባለ ግለሰብ በሁለት ሺ ሶስት መቶ (2,300) ብር ስልኩን በመሸጥ የጠፋበትን ብር ይተካል። አቶ መዝገቡ ይልቃል ደግሞ የቤት ኪራይ የሚከፍለው ገንዘብ ሲቸግረው የገዛውን ስልክ ለአቶ ሰለሞን ጌታነህ በሶስት ሺ (3,000) ብር ይሸጥለታል። አቶ ሰለሞንም ከቴሌ ያወጣውን የራሱን የስልክ መስመር (ሲም) የገዛው የስልክ ቀፎ ላይ አስገብቶ መገልገል ጀመረ።
በመዲናዋ የብዙዎች ደም በከንቱ ፈሶ ደመ ክልብ ሆኖ እንዳይቀር ጠዋት ማታ ሳይታክት የሚሠራው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ አቶ እሰይ ገ/ሕይወት ሞቶ ከተገኘበት ቀን ጀምሮ ገዳዩን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ የገዳዩን ዱካ መከታተሉን ተያይዟል። በዚህም ፖሊስ የሟችን ስልክ ማን ይዞ እየተገለገለበት እንደሚገኝ ባደረገው ሙያዊ ክትትል፤ በቀን 04/07/2011 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 1:00 ስዓት አካባቢ የሟችን ስልክ ይዞ እየተገለገለ የሚገኘውን ተጠርጣሪ አቶ ሰለሞንን በቁጥጥር ስር አዋለ።
ፖሊስም ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ “ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ስትል ሟችን ገድለሃል” በሚል ፖሊስ ክስ ሲያቀርብበት፤ አቶ ሰለሞን በምላሹ “እኔ ስልኩን ያገኘሁት ወንጀል ሰርቼ ሳይሆን በገንዘቤ ገዝቼ ነው” በማለት ለሱ የሸጠለትን ሰው አቶ መዝገቡ ይልቃልን ለፖሊስ መርቶ ያስይዛል። አቶ መዝገቡም በተመሳሳይ የሸጠለትን አቶ ታዬን ለፖሊስ መርቶ ያስይዛል። አቶ ታዬም ከላይ በተገለጸው መሰረት እንዴት ስልኩን ከወንጀሉ ፈጻሚዎች እንደተቀበለ ለፖሊስ በማስረዳቱ፤ የወንጀሉ ፈጻሚ የሆኑትን አማኑኤልና ተስፋዬን ፖሊስ አድኖ በቁጥጥር ሥር ሊያውል ችሏል።
የገዳዮች ቃል
ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ከላይ ታሪኩ በተገለጸው መሰረት የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸውንና በፈጸሙት ወንጀል መጸጸታቸውን ለፖሊስ ገልጸዋል። ተጠርጣሪ አማኑኤል መሠለ “ጓደኛው ተስፋዬ ሟችን እግሩን በጠረባ በመምታት ገፍትሮ እንዲወድቅ እንዳደረገ ጠቁሞ፤ የእርሱ ድርሻ ሟች ሲወድቅ ስልኩን አንስቶ መውሰድ እንደሆነ ለፖሊስ አስረድቷል። ተስፋዬ መሃመድ በበኩሉ ሟችን በጠረባ በመምታት መሬት ላይ እንዲወድቅ ማድረጉን አምኖ ለፖሊስ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ተጠርጣሪዎቹን ከ05/07/2011 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪዋን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟች አስከሬን የህክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሰርትባቸው መረጃውን አቅርቧል።
የሚስት የምስክርነት ቃል
ወይዘሮ እሌኒ ከፍቶ፤ ከሟች ባለቤቷ እሰይ ገ/ሕይወት ጋር ለሰባት ዓመት ያህል በትዳር አብረው ሲኖሩ ምንም አይነት መጠጥ ጠጥቶ እንደማያውቅ እንዲሁም ከሰው ጋርም ጸብ እንደሌለው ገልፃ፤ በትዳር ሕይወታቸው ልጆች ማፍራታቸውንም ትናገራለች።
ወንጀሉ በተፈጸመበት ቀን ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ቤተሰብ ቤት ሂዳ ቤት እንዳልነበረች ወይዘሮ እሌኒ ጠቁማ፤ ወንጀሉ በተፈጸመበት ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት ባለቤቷ ወደ እሷ ስልክ ቁጥር ይደውልላታል። እሷም ባለቤቷን “ለምን እስካሁን ወደ ቤትህ አልገባህም?” ስትለው፤ ጀሞ አንደኛ በር አካባቢ ከወላጅ አባቱ ጋር በስልክ እያወራ ቆይቶ ወደ ቤቱ እየገባ እንደሆነ ይገልጽላታል። እሱም “ልጆቼን አገናኚኝ” ብሎ ሁለቱንም ልጆቹን አገናኝቼው። ልጆቹን አውርቶ ከጨረሰ በኋላ ሰልኩን ከልጆቿ ተቀብላ እያዋራችው እያለ ድንገት ስልኩ ተቋረጠ። እሷም “ሳንቲም አልቆበት ይሆናል ቆይቶ ይደውላል” ብላ እየተጠባበቀች እያለ፤ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ከዚህ ቀደም ተደውሎላት በማያውቅ ስልክ ቁጥር ወደ ስልኳ ተደውሎ ኤልያስ ገ/ሕይወት ጀሞ አካባቢ ወድቋል ይሏታል።
እሷም የባለቤቷ ስም በትክክል ስላልተገለጸላት፤ ተሳስተሃል ብላ መለሰችለት። ከዛም በድንጋጤ መልሳ በደወለላት ሰው ስልክ ስትደውል፤ “እሰይ ገ/ሕይወት” በሚል የባለቤቷን ስም አስተካክሎ ጠርቶ ጀሞ አንድ አካባቢ ወድቋል ብሎ ይነግራታል። እሷም “ምንሆኖ ነው?” ብላ ስትጠይቅ ታሞ ወድቆ ይሏታል። ወይዘሮ እሌኒ እየበረረች የተባለው አካባቢ ስትደርስ ሰዎች ተሰብስበው አይታ ወደ ተሰበሰቡበት ስትሄድ፤ ባለቤቷ አስፓልት ዳር የእግረኛ መንገድ ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፤ በጆሮው፣ በአፉና በአፍንጫው በብዛት ደም እየፈሰሰው ባልታወቁ ወንጀል ፈጻሚ ጉዳት ደርሶበት ሕይወቱ አልፎ እንዳገኝችና የእጅ ስልኩ እንደተወሰደ ለፖሊስ ቃሏን ሰጥታለች።
ዐቃቤ ሕግ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና 671/2/ ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ከላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ቦታ እና ጊዜ ሟች እሰይ ገ/ሕይወትን 1ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ መሀመድ በጠረባ በመምታት የእግረኛ መንገድ ጠርዝ ላይ እንዲወድቅ ሲያደርግ፤ 2ኛ ተከሳሽ አማኑኤል መሠለ በበኩሉ እያወራበት የነበረውን ቴክኖ ተች እስክሪን የእጅ ስልክ የዋጋ ግምቱ 3,800/ ሶስት ሺ ስምንት መቶ ብር የሆነውን አንስቶ በመውሰዱ፤ እንዲሁም ሟች 1ኛ ተከሳሽ ሟችን እግሩን ጠልፎ ሲጥሉት ራሱ ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት ሕይወታቸው ያልፍ ሆኗል። በመሆኑም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ ክስ መስርቶባቸዋል።
ውሳኔ
ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ 1ኛ ተከሳሽ በ18 (በአሥራ ስምንት) ዓመት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በሀያ (20) ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2015