ክረምቱ አንድ ጊዜ ሳሳ፤ ሌላ ጊዜ ወፈር እያለ ጉዞውን ተያይዞታል። ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ፤ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንደሚባለው በተለይም ከቡሄ በኋላ መስከረምን የምታስታውስ ፀሐይ ምድሪቱን ማሞቅ ጀማራለች።አልፎ አልፎም ከየት መጣ ያልተባለ ዝናብ በድንገት ዶፉን ያወርደዋል።
ልክ እንደ ክረምቱ ሁሉ የዘውዴ መታፈርያ ሃሳብም ይዋዥቃል። የኢትዮጵያ ሁኔታ አንድ ጊዜ ተስፋ ሲሰጠው በሌላ ጊዜ ደግሞ ጨለማ መስሎ ይታየዋል። በአንዱ ቀን የኢትዮጵያ ተስፋ ወለል ብሎ ሲታየው በሌላው ቀን የሚሰማውና የሚያየው ነገር ስሜቱን ይረብሸዋል። በዚህ የስሜት መዋዠቅ ውስጥ ሆኖ ሳይረግጣት ወደማያድርባት ማምሻ ጉሮሰሪ ብቅ ማለት ፈለገ።
ማምሻ ጉሮሰሪ ተሰማ መንግስቴን እና ገብረየስ ገብረማርያም የመሳሰሉ ጓደኞቹን ስላስተዋወቀው አጥብቆ ይወደዋል። እንደዛሬው ያለ ስሜት ሲሰማውም የልቡን አውጥቶ በመናገር እፎይታ ስለሚያገኝ ማምሻ ጉሮሰሪን ሳይረግጥ አያደርም።
ዘውዴ ማምሻ ጉሮሰሪ ሲደርስ ተሰማ እና ገብረየስ ቀድመውት ተሰይመዋል። አፍ ለአፍ ገጥመው የሞቀ ወሬ ይዘዋል። ዘውዴ አጠገባቸው መድረሱን እንኳን ልብ አላሉትም። ‹‹ሰላም አመሻችሁ ጓደኞቼ፤እንደዚህ ቀልባችሁን ያጠፋው ወሬ ምንድን ነው ?›› ሲል ጠየቀ በሁኔታቸው ተገርሞ። ‹‹ ሌላ ምን ቀልብ የሚያጠፋ ወሬ አለ ብለህ ነው? ያው የሀገራችን ጉዳይ ነው›› ሲል ገብረየስ መለሰለት።
በልቡ የሚመላለሰውን እና ሰላም የነሳውን ጉዳይ ለማንሳትና እፎይታ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ በማግኘቱ ተደስቶ ወደ ጨዋታው ተቀላቀለ። ግብረየስ ጨዋታውን ቀጥሏል። ‹‹የሀገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢ ነው።ጦርነትና ግጭት እኮ አልለየን አለ። አንዱን ቋጨን ስንል ፤ሌላው ይመጣል። ከአንዱ ተስማማን ስንል፤ ከሌላው ጋር ግጭት እንገባለን። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የሚሆነው በእርሻ ወቅት መሆኑ የነገውን የኑሮ ሁኔታችንን አሳሳቢ ያደርገዋል። ዛሬ ያልዘራነው ነገ ከየት ይመጣል። ስለዚህም በየቦታው ያለው ግጭት እንዲቆም ሁላችንም በየቤተ እምነታችን መጸለይ የሚገባን ይመስለኛል›› ብሎ ሃሳቡን አሳረገ።
‹‹እኔ ግን በምትለው ነገር ለመስማማት እቸገራለሁ›› ብሎ ጉሮሮውን ሞረደና ተሰማ ለቀጣይ ንግግር እራሱን አዘጋጀ። ‹‹ሁላችንም የምናወራውና አልፎ ተርፎም መስማት የምንፈልገው መጥፎ መጥፎውን ካልሆነ በስተቀር ብዙ አስደሳች ጉዳዮችም እኮ አሉ። እንደ በሽታ የተጠናወተን ነገር ቢኖር መጥፎ መጥፎውን እየመረጡ ማውራትና እርሱኑ ለመስማት መሽቀዳደም ነው።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም። የኑሮ ውድነት ፤ግጭትና መፈናቀሎች አሉ። ሆኖም እነዚህ ጉዳዮች የበለጠ ስር የሚሰዱት እኛ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን ስናራግባቸውና ስናጦዛቸው ነው። አንዳችንም ችግሮቹን ከማውራትና ከማራገብ አልፈን የመፍትሄ ሃሳብ እንኳን ስናመነጭ አንደመጥም።
የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨት ቢያቅተን እንኳን ያሉትን መልካም ጎኖች ለማውራት ፍላጎቱም የለንም። የምናወራው ስለ ሀገራችን ከሆነ ጥሩውም መጥፎውም መወራት አለበት። ያለበለዚያ ጨለማውን ብቻ እየተመለከትን ብርሃኑን ሳናይ እንዳንቀር እሰጋለሁ። ›› ብሎ ንግግሩን አሳረገ።
በሁለት ሃሳብ ውስጥ ሆኖ የሚዋልለው ዘውዴ መታፈርያ የሚሰጠው ሃሳብ ተምታታበት። በአንድ በኩል ገብረየስ ያነሳው ሃሳብም ልቡን ገዝቶታል። በየቦታው የሚነሳው ግጭት አሳስቦታል፤በሌላ በኩል ደግሞ ሁልጊዜ መጥፎ መጥፎውን እያሰብንና እያወራን መጓዛቸውን አግባብ አይደለም የሚለው የተሰማ ሃሳብም የሚጣል አይደለም። በዚህ ሃሳብ መሀል ሆኖ አስታራቂ ሃሳብ ለመሰንዘር ወሰነ።
‹‹ እንደተባለው አሁን ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉት ዘመናትም ቢሆን መልካም እና መጥፎ ታሪኮችን ይዛ ስትጓዝ የኖረች ሀገር ነች። አንዳንድ ጊዜ ጥጋብ፤ሌላ ጊዜ ርሃብ ፤በአንድ ወቅት ሰላም፤በሌላ ወቅት ጦርነትና ግጭት የማያጣት ሀገር ነች። ሆኖም ሕዝቡም ሆነ መንግሥታት ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው እየመለሱ ሀገሪቱን ማስቀጠል ችለዋል።ስለዚህም ሊያስጨንቀን የሚገባው እንዴት ከጦርነትና ግጭት አዙሪት እንላቀቅ የሚለው ሊሆን ይገባል።ተሰማ እንዳለው ግጭትን ከማራገብ እንዴት ለመጨረሻ ጊዜ ከዚህ አዙሪት እንገላገል የሚለው ሊሆን ይገባል የሚለው መሆን አለበት። ›› ብሎ ሃሳቡን ገታ።
ተሰማ ቀጠለና ‹‹ይሄውልህ ዘውዴ አንተ እንኳን በዚህ ንግግርህ ችግሩን መፍታት አለብን አልክ እንጂ እንዴት እንደሚፈታ እንኳን የመፍትሄ ሃሳብ አላመነጨህም። በእርግጥ ችግሩን መፍታት አለብን የሚለው በራሱ አንድ በጎ ነገር ነው። ነገር ግን ከነመፍትሄው ቢሆን የተሟላ ይሆን ነበር።›› ብሎ ሃሳቡን አከለ።
በአንክሮ ሲከታተል የነበረው ገብረየስ ሃሳብ ለማዋጣት ተዘጋጀ። ‹‹ እውነት ነው ብዙዎቻችን መፍትሄ እርቆናል፤ አእምሯችን የተያዘው በችግሮች ዙሪያ ስለሆነ መፍትሄ የማመንጨት አቅም አጥሮናል። ሁላችንም የበረታነው ችግሮችን በማጉላቱ ላይ ነው። አትታዘቡኝና ችግሮችን በማወራትና በመተንተን ረገድ ሁላችንም ተክነንበታል፤ መፍትሄ ላይ ግን የለንበትም። ስለዚህም የሀገራችን ችግር እንዴት ይፈታ የሚለው የእያንዳንዳችንን የመፍትሄ ሃሳብ የሚፈልግ እንጂ ለሌላ አካል አሳልፈን የምንሰጠው የቤት ሥራ አይደለም›› በማለት ወደ ጓደኞቹ ተመለከተ።
ዘውዴ ተራውን ወሰደ።‹‹እንዳላችሁት ከእኛ ሌላ ለሀገራችን ማንም ሊመጣላት አይችልም። የችግሩ ባለቤት እኛ እንደሆንን ሁሉ፤ የመፍትሄውም ባለቤት እኛ መሆን አለብን። ለማንም የምንተወው ጉዳይ አይደለም። ችግር ላይ ቢያላዝኑ መፍትሄ አይመጣም። ስለዚህ እንደእኔ እምነት መፍትሄ ነው የምለው መወያየትና መመካከር ነው። ችግሮቻችንን በሙሉ በምክክር ሊፈቱ እንደሚችሉ አምናለሁ።
ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ህልውና ለመጣ ቀልድ አናውቅም ። ቤቴ፤ ዕርስቴ፤ ሚስቴና ልጆቼ ሳንል ሀገራችንን አስቀድመን እራሳችንን ለመስዋዕትነት እናቀርባለን።
በደምና አጥንታችንም ሉዓላዊነትታችን እናስከብራለን፤ ነጻነታችንንም እናረጋግጣለን። አልፎ ተርፎም በኮሪያ፤በኮንጎ፤ በላይቤሪያ፤ በሶማሊያ፤ በሩዋንዳና ብሩንዲ እንዲሁም በሱዳን በመዝመት በግጭትና በጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራትን እናረጋጋለን፤ ወደ ሰላማቸው እንመልሳለን።
ሆኖም የጀግንነታችንና ለሌሎች ሀገራት ጭምር የነጻነት ተምሳሌት የመሆናችን ያህል የውስጥ ሰላማችንን በማረጋገጥ ግን ብዙም አልተሳካልንም። በጀግንነትና በሰላም ማስከበር የገዘፈ ታሪክ ያለንን ያህል በሰላም የመኖር ጥበብ የለንም። የኢትዮጵያን ታሪክ መለስ ብሎ ላየው የውስጥ አለመግባባት፤ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው።በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መግባባት ካለመቻላችንም በላይ የግጭትና የጦርነት መንስኤ እስከ መሆን ደርሰናል።
ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከቷል፤ለበርካታ ሰዋዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል። ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል።ይህ የታሪካችን አንዱ ክፋይ ግን አንድ ቦታ መቆም አለበት። የግጭት፡የጦርነት፤ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ለጋራሀገራችን የምንተጋ፤ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምክክርና በመግባባት ነው።››ብሎ ንግግሩን አሳረገ።
ገብረየስ በበኩሉ ያነሳውን ቢራ አንድ ጊዜ ከተጎነጨ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ።‹‹ዘውዴ እንዳለው ችግሮቻችንን ልንፈታ የምንችለው በውይይትና በምክክር ብቻ ነው።በጦርና በጎራዴ ችግር መፍታት እንደማንችልማ ለዘመናት አየነው እኮ።አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እየሆነ መፍትሄ ማምጣት እንደማንችል ካለፈው ታሪካችን ልንረዳው ይገባል።
እንደ እኔ ጦርነት እና ግጭት ጊዜ ያለፈበትና አሁን ያለችውንም ኢትዮጵያ የማይመጥን ነው።ኢትዮጵያውያን የሚበጃቸው ፍቅር፤አብሮነት፤ትብብር ናቸው። በነፍጥ ማሸነፍና የራስን ወገን መግደልና ማፈናቀል ዘመኑን የሚዋጅ አይደለም። ከዛ ይልቅ ችግሮቻችን ምንድን ናቸው፤የማያግባቡን የታሪክ ክፋዮች የትኞቹ ናቸው፤ እንዴት መፍትሄ እናበጅላቸው ፤ በማያግባቡንስ ላይ እንዴት ተቻችለን እንቀጥል በሚሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን መወያየት አለብን›› ብሎ ጓደኞቹ ሃሳቡን እየተከታተሉት መሆኑን ለመረዳት ፊቱን ወደ እነሱ መለሰ።
ተሰማ በገብረየስ ሃሳብ መስማማቱን ለማሳወቅ አንገቱን ከወዘወዘ በኋላ፤ ሃሳቡን ቀጠለ። ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው። ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግሥታት ጭምር እውቅና አግኝቶ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በሩዋንዳ፤ በቡርንዲ፤በላይቤረያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስመስክሯል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው። በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል።ሰላም የእሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው።
ሆኖም ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል።
እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናንም አደጋ ላይ ወድቋል። ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ። እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል።
እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ። በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዷል።
ከዚህ ድርጊታቸው የሚያስቆማቸው የጸጥታ ኃይል ሲመጣ ደግሞ ግብረ አበሮቻቸውን ሰብስበው በሰፊው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሠራዊታችንንም በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ በጣም ሰላማዊና ለሕግ ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም እንጂ የእነዚህ አካላት ድርጊት ሀገርን የማፍረስ አላማ ጭምር ያለው ነው።
ስለዚህም ሀገር በሰላም ውላ እንድታድርና እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እነዚህን የሰላም ጸሮች በጋራ መመከት ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት አለ። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት አላገገምንም ፤ሥራ አጥነት አሁንም አሳሳቢ ነው፤አሁንም ከድህነት ያልወጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለ፤በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ ደጋግሞ እያጠቃን ነው።
ስለዚህም እነዚህን ችግሮች ለመሻገርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ለማምት ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሳሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመወያየት ባህል ማዳበር ይገባል። ከውይይት ይልቅ ፍላጎታቸውን በመሳሪያ ለማስፈጸም የሚከጅሉ ቡድኖችንም ሕዝቡ ዕውቅና ሊነፍጋቸው ይገባል።›› በማለት ሃሳቡን ቋጨ። አዕምሮውን ሲያስጨንቀው የቆየውን ጉዳይም በመተንፈሱ እፎይ አለ።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015