እግዜር ነፍስ በሚሏት ብናኝ ሕይወትን ሲሰራ ሃምሳ እጅ ፈተና ሃምሳ እጅ ፍርቱናን ተጠቅሟል እላለሁ፡፡ ብዙ ባልኖርኩት የዘመን ሚዛን ላይ ሕይወትን ስመዝናት ይሄን እውነት ነው ያገኘሁት። ለዛም ነው በሳቃችን ማግስት የምናለቅሰው፡፡ ለዛም ነው የማንሽረው ከሚመስለን መከራ የምንሽረው፡፡
ወደ ታሪኬ ስገባ አደይን ነው የምታገኙት፡፡ አደይ በሕይወቴ የሆነ ቦታ ላይ ድንገት የተከሰተች በምንም የማትደበዝዝ ፈተናና ፍርቱናዬ ናት። በመንገዴ ላይ ብዙ ትዝታዎች ተመላልሰዋል እንደ እሷ ትዝ የሚለኝ ትዝታ ግን የለም፡፡ በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች አሰቃይተውኛል እንደእሷ የተሰቃየሁበት ፈተና ግን የለኝም፡፡ እሷ የነበረችበት ተድላዬም ከኖርኩት አይደለም ወደፊትም ከምኖረው ከማላውቀው የበለጠ ነው። እሷ በማንም ልብ ውስጥ በምንም የማትስተካከል ፈተናና ፍርቱና ናት፡፡ እንዴት ተዋወቃችሁ ላለኝ እንዲህ እለዋለሁ..
የመጀመሪያ ቀን ነው.. ሁለተኛ ዲግሪዬን ልማር ክላስ የገባሁበት ቀን፡፡ ከሁሉም ተማሪ ዘግይቼ ክፍል የተገኘሁት እኔ ነበርኩ፡፡ ቦታ ፈልጎ ማግኘት የማይታሰብ ሆነ፡፡ ከመምህሩ ቀድሞ የተማሪዎቹን ክፍል መገኘት ሳይ ትምህርት እንደ ውሃ ከጠማቸው ተማሪዎች ጋር ቁጭ ብዬ ልማር እንደሆነ ተረዳሁ። ወይም ደግሞ መምህሩ ወግ አጥባቂ የሚሉት አይነት ሆኖ ከኔ ኋላ የመጣን ተማሪ አላስተናግድም የሚል ሕግ የደነገገም መሰለኝ፡፡
የሆነው ሆነና በዛ ቀን ቦታ ሳላገኝ ወንበር ፍለጋ ለአፍታ አይኖቼን ወዲያ ወዲህ አባዘንኩ። በዚህ መሀል ነበር እንደ ጨረቃ የሚያበሩ አይኖች ከዓይኖቼ ጋር ተገጣጥመው በጥቅሻ አፈር ከድሜ የጣሉኝ፡፡ ጥቅሻው ሌላ አይደለም.. መቸገሬን አይተው ና ወዲህ ወንበሬን ላጋራህ ነበር፡፡ እመአምላክን ተደነባብሬ ነበር፡፡ በዓይኖቿ መደነባበሬን አውቃ ይሁን እንጃ ራሷን ሰብራ ና ስትል በምልክት ጠራችኝ፡፡ በዓይኖቿ የራሰ የነፍሴን ላቦት ይዤ በወጉ ባልተሰደረ መቀመጫ መሀል እየተሽሎከሎክ ከፍ ሲልም እግርና ታፋዬን ለወንበሩ እየገበርኩ ወደምትገኝበት የኋላ ስፍራ ሄድኩ፡፡
ምን እንደሆንኩ አላውቅም በአይኗ የሆነ ነገሬን እንዳጣሁ ገብቶኛል፡፡ እንደሳምሶን ከሆነ ነገሬ ላይ የሆነ ነገሬ ሃይል ሲያጣ ታውቆኛል፡፡ እናቴ ልጅ ሆኜ ከሰው ዓይን ልትከልለኝ ስትሸፋፍነኝና ስትደባብቀኝ አስታውሳለው፡፡ አድጌ እንኳን የሰው ዓይን ጥሩ አይደለም ተደብቀህ ብላ፣ ተደብቀህ ልበስ ብላኝ ታውቃለች፡፡ እናቴን እስከዛሬ አምኛት አላውቅም ነበር፡፡ በዚች በማላውቃት ሴት ዓይን የዘመናት እውነት ተገለጠልኝ፡፡ እናቴ ስትደብቀኝና ስታሸሸኝ የነበረችው ከዚች ሴት ይሆን እንዴ? የሚል የትኛውም ቂል ያላሰበው ሃሳብ ተፈጠረብኝ። በዚህ ጊዜ አጠገቧ ደርሼ ነበር፡፡ ምን ልትለኝ ይሆን እያልኩ ለሌላ ግርምት ራሴን ሳዘጋጅ ከተቀመጠችበት ሸርተት እያለች.. ‹ወንበሬን ላጋራህ ብዬ ነው› አለችኝ፡፡ በሚያምር፣ በሚያዝን፣ በሰከነ፣ በሚስረቀረቅ ሁሉንም በሆነ ድምጽ፡፡
መልስ ሳልሰጣት ቆምኩ፡፡ አዎ ነፍሴ የሆነ ነገሯን ተነጥቃለች፡፡ በሴት ድምጽና ውበት ከልዕለሰቤ ላይ የሆነ ነገር ጎሎ በዝምታ ስቆም ያ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ብታምኑኝም ባታምኑኝም እንደዛ ቀን እንደዛች ሴት በደግነት ያስደነቀችኝ ሴት የለችም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ እይታ በሴት ፍቅር እንዳልነበረ ሆንኩ፡፡ እንደእሷ አይነት ሴት ነበር ስፈልግ የነበረው.. ደግ ሆና ቆንጆ የሆነች ሴት፡፡ ልክ እንደዚች ሴት አንዳንድ ነፍሶች ብዙ ውበት፣ ብዙ ማማር ተችሯቸው ደግ ናቸው። ሴት መቼ ነው የምታምረው ላለኝ ደግ ስትሆን እለዋለሁ።
በሕይወቴ ቆንጆ ሆነው ክፉ የሆኑ ብዙ ሴቶችን አውቃለው፡፡ ይቺ ሴት ግን ተለየችብኝ። በልቤ እንዲህ አልኩ.. በስብዕናና በማንነት፣ በሴትነትም ከእብራውያን ሴቶች ከተለየችው የጌታ እናት ቀጥሎ ቅዱስ ሴት፡፡ በወርቅ ጫማዋ ለውሻ ካጠጣችው ከእመብርሃን ቀጥሎ ትሁት›፡፡ ስል ቃሌን ሰጠኋት። ጌታን ከታቀፉ እጆችና ክንዶች ቀጥሎ ለድሃ የተዘረጋ እጅ ያላት ሴት መሰለችኝ። ብዙ እንስቶች እንደእሷ አምረው በውበታቸው ውስጥ ቅድስናን እና ትህትናን አጉድለው ተመልክቻለው፡፡
ዝምታዬ ሳያስቆጣት ቸር በሆነ ፊት አስተዋ ለችኝ፡፡ የተንዠረገገ ዝምታ ዝም ያልኩት በዛ ቀን ይመስለኛል፡፡ ዝንተዓለም በመሰለኝ የጊዜ ርቀት ካለ ድምጽ ፊቷ ቆምኩ፡፡ ኋላ ስለነበርኩ ሁኔታዬን ያጤነ አልነበረም..፡፡ አይደለም ሁለት ሰው ለአንድ ሰው በማትበቃው ወንበር ላይ ከአንዲት ቆንጆና ደግ ከሆነች ሴት ጋር መቀመጥ ገሀድ ሳይሆን ቆይቼ የምባንነው ህልም ነበር የመሰለኝ፡፡ ግብዣዋን ተቀብዬ ወንበሩ ላይ ተቀመጥኩ፡፡
ተቀመጥኩ ልበል እንጂ ከመቆም የከፋ ጉስቁልና ነበር የደረሰብኝ። ብቻዋን ብትቀመጥ በማይበቃት ወንበር ላይ በዓይኗ አደናብራ አብሬአት እንድቀመጥ ማድረጓ ስቃይዋን እያጋራችኝ መሰለኝ፡፡ ገፍታ ልትጥለኝ የጋበዘችኝ እንጂ ራርታ የጠራችኝ አልመስልህ አለኝ፡፡ ወንበሩ ለአርበ ሰፊ ዳሌዋ አልበቃትም፡፡ በዘመኔ ወንበር አጥቶ ሲቁነጠነጥ የእሷን ገላ አየሁ። ከወንበሩ ተርፎ ዳሌና ታፋዋ በተመቸው ቦታ አጮልቋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው አብረኸኝ ተቀመጥ ስትል በጥቅሻ የጠራችኝ፡፡
እንዲመቸኝ ብዙ አይነት መስዋዕት የከፈለች ይመስለኛል፡፡ ወንበሩን ለቆ ከመሄድ ውጪ ያለውን ሁሉንም ሙከራ አድርጋለች፡፡ እግሮቿን በማነባበር፣ በአንድ ጎን ለመቀመጥ በመሞከር በቻለችው ሁሉ እሷ ጠቧት እኔ ሰፍቶኝ ዘና ብዬ እንድቀመጥ ሞክራለች፡፡ ግን አልበቃንም፡፡ አንድ ታፋዬን ወንበሩ ላይ አንዱን ሜዳ ላይ አንጠልጥዬ የስቃይ ቁጭታ ተቀመጥኩ፡፡ እሷም እንዲሰፋኝ በሚል በአንድ ጎኗ ተቀመጠች፡፡ ጡቶቿ ትከሻና ደረቴ ላይ መልህቅ ጣሉ፡፡ ይሄን ሌላ ድካም እለዋለሁ፡፡ እንዴትም ትቀመጥ የጡቶቿ ሰለባ ነበርኩ፡፡
ሳይንስ ብዙ ተመራምሮ ዛሬም ድረስ ያልደረሰበት ሚስጢር ሴቶች ባሉበት በየትኛውም ባረባ ቦታ ላይ ስላለው ምቾት ነው፡፡ እንደዛሬ የተመቸ የሕይወት ከፍታ አልጎበኘኝም፡፡ ብቻዬን ብሆን በምሰቃይበትና ለጠላቴ በማልመኘው ወንበርና ቁጭታ ላይ እንደዛ መደላደሌ ሳስበው ወይጉድ የምልበት ነው፡፡
መጀመሪያ ቀናት ሁሌም ስቃይ ናቸው፡፡ ለየትኛውም ሰው ነገ ሲሆን የሚስቅበት ገጠመኝ አለው፡፡ በባህሪዬ መጀመሪያ ተሰቃይቼ ቀጥዬና ሰልሼ የማሰቃይ ነኝ፡፡ በዛ አቀማመጥ ምድር ላይ ማንም ያልተደሰተውን ደስታ ከማስተናገዴ እኩል ማንም ያላሰበውን ሀጢዐት አሰብኩ፡፡ ጡቶቿ እየተሻሹኝ ነው፣ ጎኗ ከጎኔ ይታከካል፣ ውብ ጠረኗ እድፋም ገላዬን የዘበናይ መቀነት አስመስሎታል፡፡ ነፍሴ አላባት፡፡ ባለፈ ሕይወቴ ከብዙ ቆንጆ ሴቶች ጋር በወንድምነት ተቀምጨ አውቃለሁ ይቺን ሴት ግን እንደእህት ማየት አቃተኝ፡፡ ረመጥ ላይ ወደቅኩ..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015