
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለዘመናት የተጋረጡባትን ችግሮች በመፍታት አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምር መሰረት የሚጥለውን ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ምሁራን የማይተካ ሚና እንዳላቸው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለንጉሴ ገለጹ ።
አቶ እንዳለ ንጉሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የሀገር ሰላምን ለማስጠበቅ እንዲሁም እንደ ሀገር ለመቀጠል ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያለውን ሀገራዊ ምክክሩን ወደ ተግባር ለመቀየር ምሁራን ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሊሆኑ ይገባል። አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት የስልጡን ዜጎች መለያ እንደሆነ የጠቆሙት መምህር እንዳለ፤ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ምሁራን የግንባር ቀደምትነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
ምክክርና ንግግር የሰው ልጅ የእለት እለት ተግባር መሆኑን የጠቆሙት አቶ እንዳለ፤ ሀገራዊ ምክክሩን ከሌላ ውይይቶች የሚለየው ከውይይቱ በኋላ ህገመንግስት ውስጥ ለሚካተቱ ሃሳቦች መነሻ ሆኖ ማገልገሉና በሀገሪቱም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ንግግር፤ ምሁራን ሀገርን ለሚያሻግሩ ተግባራት ግንባር ቀደም በመሆን ሊሰለፉ ይገባል፤ ብሄራዊ ምክክሩ ደግሞ የጎደለን ለመሙላትና በሰላም ለመኖር ፋይዳው ከፍተኛ ነውና በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳትፎን ማድረግና ሀገር በምትፈልገው ጊዜ ሁሉ ማገልገል ከእያንዳንዱ ምሁር ይጠበቃል።
ምሁሩ ሀገርን በሚመለከቱና የጋራ ጉዳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተግባብቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ያመላከቱት አቶ እንዳለ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ተግባራዊነት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍሎች የየራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ምሁሩ የማነሳሳት ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
በተለይም የሀገርን ሉአላዊነት በሚያስጠብቁ ነገሮች ላይ፣ ድህነትን ለመዋጋት በሚደረጉ ትግሎች ላይ፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን በሚመለከት፣ እንዲሁም የእኩልነት ጉዳዮች ላይ ምሁራን በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ መምህር እንዳለ አብራርተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደተቋቋሙ በመረዳትና ከዓላማቸው ባለማፈንገጥ ሀገራቸው በምትፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
እንዲሁም መገናኛ ብዙሀንም ሀገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ በመንግስትና በህብረተሰቡ መሀል በመቆም የድልድይነት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ እንዳለ አሳስበዋል፡፡
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም