የትናየት ፈሩ
አቶ አርአያ ተስፋማርያም ጋዜጠኛ ነው። ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ሪፖርተርን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ሰርቷል። ወደ ሙያው የተሳበበትን ሁኔታ ሲገልጽ «በሰማንያዎቹ አጋማሽ ይወጡ ከነበሩ ጋዜጦች ቁጥር አንድ ምርጫዬ ‘ጦማር’ ጋዜጣ ነበረች:: ‘የአራዳ ሹክሹክታ’ የምትለው ቅልብጭ ያለችና አጫጭር መረጃ የምታስኮመኩመው አምድ አትረሴ ናት:: ወደ ጋዜጠኝነት እንዳዘነብል ያደረገችኝ ‘ጦማር’ ጋዜጣ ናት። በተለይ ሳላውቀው ወደ ሙያው የሳበኝ የማከብረው፣ የማደንቀው፣ ልዩ ቦታ የምሰጠው ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ ነው» ይላል። ጋዜጠኛ አርአያ በይበልጥ የሚታወቀው ከ1994 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵ ጋዜጣ ላይ «ከህወሓት መንደር የቃረምኩት» በሚል አምድ ስር ያወጣቸው በነበሩት ጽሑፎቹ ነው። ዘመን መጽሔት ከዚህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ዘመን፡- አንተ ትታወቅ የነበረው «ኢትዮጵ» ጋዜጣ ላይ «ከህወሓት መንደር የቃረምኩት» በሚል አምድ ስትጽፋቸው በነበሩ ጽሑፎች ነው። አምዱን ለመጀመር መነሻህ ምን ነበር?
አቶ አርአያ፡- አምዱን ለመጀመር ያነሳሱኝ በህወሓት ታጋዮች ላይ ይፈጸሙ የነበሩት ግፍና በደሎች ናቸው። ህወሓት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ 1984 ዓ.ም ግምገማ በሚል 36 ሺ ታጋዮችን አባረረ። የዚያን ጊዜ ተማሪ ሆኜ እነዚህን መረጃዎች እሰበስብ ነበር። የህወሓት ክፍፍልን ተከትሎ እሰራበት ከነበረው ከሪፖርተር ጋዜጣ ከለቀቅኩ በኋላ 1994 ዓ.ም መስከረም ሁለት ኢትዮጵ ጋዜጣ ላይ መጻፍ ጀመርኩኝ። በተከታታይ በየሳምንቱ ጽሑፎችን ሳወጣ ነበር። እንደነገርኩህ መነሻዎቹ 36 ሺዎቹ ታጋዮች ናቸው። 1 ሺህ 500 የሚሆኑ ታጋዮች በሆለታ እስር ቤት ውስጥ እንዶድ የተባለ መርዝ ጠጥተው ሞተዋል። በታጠቅ ሁለት ሺህ በሳንባ ተላላፊ አልቀዋል። 14 ሺህ ጎዳና ያድሩ ነበረ። የእነዚህን ታሪክ ከጨረስኩ በኋላ በህወሓት፣ በደህንነት፣ በመከላከያ እና በተለያዩ ተቋማት ይፈጸሙ የነበሩ የወንጀል ድርጊቶችንና ሙስናዎችን ወደ ማጋለጥ ገባሁ። መረጃዎችን አገኝ የነበረው መከላከያ፣ ደህንነት፣ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እና ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ካሉ ሰዎች ነበር።
ዘመን፡- በ «ኢትዮጵ» ላይ በምታወጣቸው ጽሑፎች ካጋለጥካቸው በህወሓት የተፈጸሙ ሴራዎች፣ ግድያዎች እና ዘረፋዎች መካከል ይበልጥ ዋጋ የሰጠኸው የትኛውን ነው?
አቶ አርአያ፡- ብዙ ናቸው በተለይ ግን የታጋዮቹን ስቃይና መከራ ማጋለጤ ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም በድርጅቱ ስም ነበር። ሁለተኛ በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ የነበራቸው ታስረው ብዙ ስቃይ ያዩ ወዳጆች ነበሩኝ። ይሄ ፓርቲ (ህወሓት) ሄዶ፣ ሄዶ ተላትሞ በራሱ ጊዜ እንደሚጠፋ ይነግሩኝ ነበር። ‘ዘንዶ የተራበን ዘንዶ ሲውጠው በጣም ተጠንቅቆ ነው፤ ምክንያቱም ያኛውም ሊበላው ስለሚችል እርምጃ የሚወስድበት ቶሎ ነው። ልክ እንደ ዘንዶዎች ይዋዋጣሉ’ ይሉኝ ነበር። ሀጎስ ገብረሕይወትም በዘፈኖቹ ‘እንደ ትናንቱ ነገም እንፋረዳቸው’ እና ‘በጠዋቱ እረፉ ብለን ነበር’ እያለ ከ18 ዓመታት በፊት ያቀነቀናቸው ሀሳቦች በሙሉ ተፈጽመዋል። ይህ ሲሆን በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ። ሀጎስ ይህን ሳያይ መሞቱ ግን በጣም ያሳዝነኛል።
ዘመን፡- ህወሓት የሚፈጽማቸውን ግፎች ጋዜጣ ላይ በመጻፍህ ምን ዓይነት ችግሮች ደርሰውብሃል?
አቶ አርአያ፡- በ1995 ዓ.ም ከፖሊስ መረጃዎች ደርሰውኝ የቴሌ ኮሚዩኒኬሽንን መረጃ ማጋለጥ ተያያዝኩኝ። ያንን ይፈጽሙ የነበሩት በሕይወት የሌለው ኢያሱ በርሄ እና አዜብ መስፍን ናቸው። ኢያሱም ራሱ አምኗል። 38 ሰዎች ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ እኔን ማሳደድ ተጀመረ። ቢተው በላይ የሚባል የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም ታስሮ ነበር። ሚስቱ ዝማም ትባላለች፤ ባሏን አሳስራ የደህንነት ሹም ከነበረው ከወልደሥላሴ ጋር ትፈጽማቸው የነበሩ ነውረኛ ድርጊቶች ነበሩ። እሷ ናት የጠቆመችኝ። ‘ኢየሩሳሌም አርአያ ይባል እንጂ ወንድ ነው፤ የሚኖረው ቤላ ነው፤ ቤቱን ግን አላውቅም’ አለቻቸው። ኃይሌ የሚባል ሰው ስድስት ወር ሙሉ አስጨነቀኝ። ‘መረጃዎችን ማነው የሚሰጥህ? ገንዘብ እንስጥህ፤ 400 ሺህ ብር ከዚያ በኋላ ከአገር እንድትወጣ እናደርግሃለን’ የሚሉ መደራደሪያዎች ነበሯቸው፤ እኔ ግን አልተቀበልኩም። አብረዋቸው የታገሉ ታጋዮች ላይ ያንን ሁሉ ግፍ እስር ቤት ውስጥ የፈጸሙ ለእኔ መረጃ የሚሰጡኝን ሰዎች ሲያገኙ ምን ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ አስብ። በገባሁበት፣ በወጣሁበት ጎንበስ እያሉ ሽጉጥ ያሳዩኛል። እኔ ግን እንደዚያም ሆኖ እነሱ ከሚጠረጥሩት ውጪ በተለያየ መንገድ መረጃዎቹን አገኝ ነበር።
ስድስት ወር በጣም አስጨነቀኝ ከዚያ በኋላ ይሄ እንደማይሆን ስነግረው መስከረም ሁለት ቀን ትግራይ ልማት ቢሮ ተጠራሁ። የዚያን ጊዜ የትግራይ ልማት ቢሮ ዳይሬክተሩ ተስፋጽጌ አበራ ይባላል። አባቴና የእሱ አባት ወንድማማቾች ናቸው፤ የአጎቴ ልጅ ማለት ነው። እንግሊዝ አገር ነበር። 1994 ዓ.ም አምጥተው ዳይሬክተር አደረጉት። ከእነሱጋ ሲሰርቅ ሲመዘብር የኖረ ነው። ያው ከወልደሥላሴ ጋር አገናኙኝና ሁለት ሰዓት ሙሉ አስፈራራኝ። እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚሰጡኝና ከአገር ልወጣ እንደምችል ነገረኝ። አንዴ ‘የአድዋ ሰው ነህ’ ይለኛል፤ አንዴ ደግሞ በቤተሰብ ሊያግባባኝ ሞከረ። ከዚያም ‘ፕሮፌሰር መስፍን እና ክፍሌ ሙላት አያድኑህም’ አለኝ። ክፍሌ ሙላት በወቅቱ የኢትዮጵያ ነፃው ፕሬስ ፕሬዚዳንት ነበር። ነፍሳቸውን ይማርና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደግሞ የኢሰመጉ ፕሬዚዳንት ነበሩ። ይሄን ካለ በኋላ ‹‹ብንገልህስ!›› አለኝ። ‹እንግዴህ እኔ ከጀርባዬ መሣሪያ የለም፤ ያለው እስክርቢቶ ነው፤ አሁኑኑ ልታደርገው ትችላለህ፤ 36 ሺህ ታጋዮች እኮ! ለቤተ መንግሥት አብቅተዋችሁ መጨረሻ ላይ ሜዳ ላይ ጥላችኋቸዋል፤ ግማሾቹን እስር ቤት› ስለው ‹‹ምናገባህ!›› ብሎ ጮኸብኝ። ‹አይ! እኔ ያገባኛል፤እንደ ሰው ሳስበው እንደዚያ ተሰቃይተው ሲሞቱ ዝም ማለት አልችልም› አልኩት። ‹‹እንዳንተ እሹሩሩ ያልነው የለም፤ ለማንኛውም 15 ቀን ጊዜ ሰጥተንሃል›› አለኝ። ‹በ15 ዓመትም ሀሳቤን አልቀይርም› አልኩት።
1996 ዓ.ም መስከረም 20 ቀን ረቡዕ ማታ ወደ ቤቴ ስገባ ቤላ ቀበሌ 18 አቦ ድልድዩ ጋር ያደፈጡ ፌዴራል ፖሊሶች ነበሩ። አምስቱ ከኋላ መጥተው አናቴን ፈነክቱኝ ከፊት ያሉት ተቀበሉኝ። ሦስት ጥርሴ ረገፈ። ከዚያ ድልድይ ውስጥ ተወረወርኩ። የፈለጉት ጅብ እንዴበላኝ ነበር፤ ምክንያቱም በአካባቢው ማታ ማታ መንጋ ሆኖ ነበር የሚሄደው። ደሜ ይፈስ ነበር፤ ታፋዬ ተሰነጠቀ፤ መቆም አልቻልኩም። ከዚያ ባትሪ አብርተው አዩኝ። ሞቷል ሲሉ በሰመመን ስማኋቸው። መጨረሻ ላይ በማንም ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥረት ደሜ እየፈሰሰ፣ በዚያ ቆሻሻ የሚጣልበት ዳገት መሬት ለመሬት እየተንፏቀኩ፣ ሄጄ ሰው ቤት ደረስኩ። ከዚያ በኋላ መብራት ሳይ ምን እንደሆንኩኝ አላስታውስም። በእነርሱ እርዳታ ተሰፍቼ፤ ሁሉ አካሌ ሕክምና እየተደረገለት፤ በኋላ ምኒልክ ሆስፒታል ራሴን አገኘሁት። በማግስቱ አስወጡት ተባለ። ለአዘጋጁ ሲሳይ አጌና ደውለው ‘ኢየሩሳሌም አርአያን ፈልገን ነበር’ ሲሉት ለሥራ ወጥቷል ሲላቸው ምኒልክ ሆስፒታል ሄደህ ሬሳውን ውሰድ’ አሉት። ይሄንንም በጋዜጣ ላይ ጽፎት ነበር።
ያው እንግዴህ ስድስት ወር የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ። ሀኪም ቆመህ ትሄዳለህ ያለኝ በሁለት ዓመት ነበር። ታፋዬ ላይ መሰንጠቅ ስለነበረ ስድስት ወር በጀርባዬ ብቻ ተኛሁ። ይህን ያህል ጊዜ ሳትገላበጥ በጣም ይከብዳል፤ ሆኖም በሁለት ዓመት ይወስዳል የተባለው በስድስት ወር ቆሜ ሄድኩኝ። ነገር ግን አሁን እነሱ ባደረሱብኝ ጉዳት ነርቭ ያመኛል።
የእነ ወልደሥላሴ ጭካኔ ከዚህ በላይ ነበር። እኔ የተረፍኩት በእግዚአብሔር ተአምር ነው፤ ዳግም ነው የተወለድኩት።
ዘመን፡- ከዚያ በኋላስ ጋዜጣ ላይ በመጻፉ ቀጥለህ ነበር? ከአገርስ የወጣኸው እንዴት ነው?
አቶ አርኣያ፡- አዎ! የ1997ን ምርጫ ተከትሎ ጋዜጣው እስከተዘጋ እስከ ጥቅምት 1998 ዓ.ም ድረስ እጽፍ ነበር። ከዚያ በኋላም የተባለው ‘ቀጥቅጣችሁ ጣሉት’ ነበር። እኔ ግን ወደ ሐረር ሄጄ ተደበቅኩኝ። ከዚያ በኋላ ልጄ ታመመች። ኢየሩሳሌም የምትባል ታዳጊ ልጅ አለችኝ። ‘የውጭ ሕክምና ያስፈልጋታል፤ ካልታከመች ፓራላይዝድ ትሆናለች’ ተባለ። ብዙ ጥረት ካደረግኩ በኋላ በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እገዛ 10 ሺ ዶላር ድጋፍ ተገኝቶ፤ ወደ ሕንድ ሄድን። ሁለት ጊዜ ቀዶ ጥገና አድርጋ በዚያ ከቆየን በኋላ ወደ አሜሪካን ሄድን። ዶክተር ነጋሶ በጣም ባለውለታዬ ናቸው፤ በጣም ጥሩ ሰው ናቸው። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው እንደዚህ ነበሩ። ባለፈው ዓመት ልናመሰግናቸው ወደዚህ አገር ስንመጣ በስልክ ተገናኝተን ‘ወደ አያቶቼ አገር ደርሼ እመጣለሁ’ ብለው ሄዱ፤ ያው ሬሳቸው መጣና ሳናገኛቸው፣ ሳናመሰግናቸው ቀረን። እኔ ብወልዳትም ኢየሩስን ሕይወት የዘሩባት እሳቸው ናቸው፤ ከአገር አወጣጣችን እንደዚህ ነው።
ዘመን፡- ህወሓት ሲነሳ የማፈኛ ፣ ማሰቃያ እና መግደያ ቦታዎች አብረው ይነሳሉ። አንተም እነዚህን ቦታዎች ታነሳቸዋለህ። እንደ ምርመራ ጋዜጠኛ አንተ የደረስክባቸው መሰል ቦታዎች የት አካባቢ ይገኛሉ? በእነዚህ ቦታዎች ግፍ የሚፈጸመውስ በእነማን ላይ ነበር?
አቶ አርአያ፡- በጣም ብዙ ናቸው። ዝዋይ ለምሳሌ ካምፕ አለ፤ የወታደር ካምፕ ነው የሚባለው፤ ግን ወደ ሦስት፣ አራት ጉድጓዶች አሉ። እዚያ ውስጥ የራሳቸው ታጋዮች አብዛኞቹ ደግሞ የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ ኦነግ ተብለው ገብተው ታስረዋል። ለመጸዳዳት የሚወጡት ጠዋት ብቻ ነው። ቀኑን ሙሉ አይወጡም። ስለዚህ ይንጋ ይምሽ አያውቁም። ወደ ሰላሳ የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው። ምርጫ 97ን ተከትሎ ቅንጅት ናችሁ ተብለው ከአየር ኃይል ተወስደው እዚያ የታሰሩ ሁለት ልጆች አውቃለሁ፤ አንዱ አሁን ካናዳ ነው። እዚያ ገብተው ጠዋት ሲነሱ ‘እንደምን አደራችሁ’ ሲሏቸው ‘እኛ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሰምተን አናውቅም፤ ይምሽ ይንጋ ሳናውቅ እንደምን አደራችሁ አትበሉን’ ብለው በድንጋይ ሊፈነክቷቸው ነበር። ሰዎቹ ገርጥተው ነጭ ሆነዋል። ሌላው እዚህ ማዕከላዊም ግፍ ይፈጸም ነበር።
ካዛንችስ የነበረው ማሰቃያ ቦታው ደግሞ ነዳጅ ማደያ የነበረ የደህንነት ግቢ ነው። በካዛንችስ ሱፐር ማርኬት በኩል ነበር፤ አሁን ሕንፃዎች ተሰርተውበታል። በእሱ በኩል ስትወርድ በስተቀኝ በኩል የሚገኝ ነው። የሚገርምህ ይህን ማሰቃያ እዚያው እየሰሩ ያሉ ደህንነቶችም አያውቁትም። ማደያ የነበረውን አፍርሰው፣ በቆርቆሮ ከልለውት ነው፤ በዚያ በብሎኬት የተሰራ ጉድጓድ ነገር አለ። እዚያ ውስጥ ያስገባሉ፤ ብዙዎቹ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፤ አንድ ጊዜ በ1995 ወይም 96 ዓ.ም ይመስለኛል ሙቀት ስለነበር እነ ወልደሥላሴ ደህንነቶቹን ግቢው ውስጥ ያለ ትልቅ ዛፍ ስር ሰበሰቧቸው። ደህንነቶቹ ያ፤ የታጠረ ቦታ ምን እንደሆነ አያውቁም። አንድ አሞራ ዝቅ ይልና ስጋ መስሎት ያነሳው ነገር በደም የተለወሰ ፋሻ ሲሆንበት የተሰበሰቡት ደህንነቶች ላይ ጣለው፣ በዚህ ጊዜ ደህንነቶቹ ደነግጡ።
ሌላው ደህንነት ቢሮ ውስጥም የእነ ጌታቸው አሰፋ ማሰቃያ ነበረ። እነ ረታ፣ ኢሳያስ እና ተክላይ ፀሐዬ የሚባሉሰው የሚደበድቡት ሰክረው ገብተው ነው። አሁን ተክላይ ፀሐዬ አሜሪካን ነው። የሚያደርጉትን ልንገርህ፤ ሽሮ ሜዳ ማታ፣ ማታ የወረዳ 11 ፖሊስ ለጥበቃ ወደዚያ እንዳያልፍ ተደርጎ ወስደው ድምጽ በሌለውና ባለው መሣሪያ ይገድላሉ። ብዙ ጊዜ በዚያ ጥፍርና ጸጉር ደም ይገኛል። የወረዳው ፖሊስ አዛዦች ምንም ማድረግ አይችሉም። በጣም ብዙ ሰው ተገድሏል።
ብዙ የማሰቃያ እስር ቤቶች ነበሩ። ማዕከላዊም አንደኛው ነው። በጣም የሚዘገንኑ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው ነበር። የአእምሮ በሽተኛ የሆኑ ሴቶች እንኳን በአስር ወንዶች ይደፈሩ ነበር። አንድ በሕይወት የሚኖር ጀነራልን ጨምሮ የህወሓት መኮንኖች የነበሩ ወንዶች እንዴደፈሩ ተደርጓል። ትግራይ ውስጥ ያለው በጣም ብዙ እስር ቤት ነው። ሰዎቹ አሁን ወጥተው ይሆናል። ባዶ ስድስት የሚባለው ወደ መሬት የሚቆፈር ነው። አሁን እነ ስብሃት የተያዙበት ቦታ ባዶ ስድስት ነው። እነሱ እዚያ ቦታ ላይ ብዙ ሰው ገድለዋል። የኢሃፓ፣ የኢዴዩ ፊውዳል ምናምን እያሉ በጣም ብዙ ሰው ያሰቃዩበት ነበር። እነዚህ ቦታዎች የራሳቸውን ታጋዮች የገደሉባቸውም ነበሩ። የምትቀበርበትን ጉድጓድ ‘አልቆፍርም’ ስትል ሌሎች ቆፍረውልህ አንተ እጅና እግርህ ታስሮ ከእነ ሕይወትህ የምትቀበርባቸው ቦታዎች ነበሩ። እነስብሃት እዚያ ቦታ ላይ ከእነ ሕይወታቸው የቀበሯቸው ብዙ ናቸው፤ እንግዴህ ስብሃትን የጠራው ደም ነው ማለት ነው።
ዘመን፡- ህወሓት የራሱን ሰዎች ደብዛ የሚያጠፋው እና እንዴወገዱ የሚያደርገው በምን ዓይነት መንገድ ነበር?
አቶ አርአያ፡- በተለያየ መንገድ ነው፤ ለምሳሌ ትግሉ ሃዋዜን የገደሉት ከእስር ቤት አመለጠ ብለው ነው። አጋዚን የመቱት ሆነ ብለው ከኋላ ነው፤ ግን ‘ከኢዴዩ ጋር ሲዋጋ ምናምን’ ይሉሃል። ስሁልንም የገደሉት እንዴሁ ሆነ ብለው ነው። ቤተሰቡን ሳይቀር ማጥፋት ስለፈለጉ ወንድሙን ለስለላ ብለው ልከውት ወደ ደርግ እየተመላለሰ መረጃ ይሰጣቸው ነበር። ከዚያ እነ መለስ ለደርግ ሊሰልላችሁ መጣ ብለው መረጃ እንዴደርሳቸው አደረጉ፤ ከዚያ ይሄ ሰውዬ ታስሮ ተሰቃይቶ ተገደለ ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ነበር የሚፈጸሙት። ሁለተኛ በመርዝ ይድሉሃል፤ ምን ዓይነት መርዝ እንደሆነና ከየት እንደሚያመጡት አላውቅም። ለምሳሌ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የሚባል አለ አይደል? ዋልታ ማለት የክንፈ ወንድም ነው፤ ዮሐንስ ይባላል። ዮሐንስንም የገደሉት ሆነ ብለው ነው፤ ድርጅቱ እንደዚህ ነው። እነ ኢያሱ በርሄ ብዙ ሰው ሲያጠፉ ከርመው ራሱ ኢያሱ በርሄም መጨረሻ ላይ በመርዝ ነው የተገደለው።
ስዬ አብርሃም በወቅቱ ሆነ ተብሎ ነው ከጨዋታ ውጪ እንዴሆን የተደረገው። ግን ያው ስዬ አብርሃ የአቋም ሰው አይደለም። እንደምታውቀው በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጦርነት እንዴከፈት ካደረጉትና ስብሃት ጣት ከቀሰረባቸው አንዱ እሱ ነው። ዛሬም እንግዴህ ቦስተን ሸሽቶ ሄዶ የራሱን ሦስት ልጆች እዚያ በተቀማጠለ ሕይወት በሰረቀው ገንዘብ እያኖረ፣ ውድ ትምህርት ቤት እያስተማረ የድሃውን የትግራይን ልጅ እንዴህ እንዴያልቅ ያደረገ ነው፤ ነገ ጠዋት በጦር ወንጀለኝነት የሚፈለግ አንድ ወንጀለኛ ነው። የትም አይደርስም እንጂ አሁንም ቅስቀሳ ላይ ነው። አሜሪካን አገር ግሪን ካርድም ምንም ስትሞላ የምትፈርመው ወንጀል አልፈጸምኩም፤ ሰው አላስገደልኩምና ትዕዛዝ አልሰጠሁም ብለህ ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት የቀይ ሽብር ወንጀለኛን ይዘው ለፍርድ አቅርበዋል። መንግሥት የቀይ ሽብር ወንጀለኞችን ታሪክ እየወሰደ እዚያ በአቃቢ ሕግ በኩል ለፍርድ ያቀርባቸው ነበር። አሁንም ልክ እንደዛ እነስዬ አብርሃም በሕግ መጠየቅ አለባቸው።
ዘመን፡- የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ቤተ ሰቦች የዝርፊያ ሰንሰለትና አኗኗር ከትግራይ ሕዝብ ኑሮ ጋር ሲነጻጸር ምን መልክ አለው ?
አቶ አርአያ፡- እየሁልህ ጥቂት የህወሓት አመራሮች አልፎላቸዋል። አንደኛው እንግዴህ ጥገት ላም የሚባለው ትእምት-ትግራይ እግሪ ምትካል/ ነው። የስብሃት ዘርማንዘር ከነቤተሰቡ ጠቅላላ ትእምት ሀብት ሆኖለታል። ከሱር ኮንስትራክሽን ብቻ በፓኪስታን ዜጎች በኩል ወደ ሲቲ ባንክ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ከአገር ያስወጣ ነበር። እነዚያ ፓኪስታኖች የመጡት ኮንሰልታንት ተብለው ነው። ምንም ሥራ የላቸውም ግን ለእነሱ ይከፈላል በሚል በዶላር 100 ሚሊዮን ይወጣ ነበር። ቀጥሎ ትእምትን የያዘችው አዜብ መስፍን ነች። አንድ ነገር ልንገርህ! ልጇ ሥራ ሰርታ አታውቅም፤ ነገር ግን የአምስትና ስምንት ሚሊዮን ብር መኪና ትነዳለች፤ በጣም ትልቅ ትምህርት ቤት ትማራለች። ከየት ነው ያመጣችው? የትእምት ገንዘብ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ። ኢፈርት አሁን 30 ዓመት ሆነው! እስካሁን አንድም ኦዴት አያውቀውም። እነሱ አማካሪ ብለው የሚጠሯቸው አንዳንድ ድርጅቶች አሉ። ይሄንን በዚህ፣ በዚህ ጥቅም ብትሰራ ብለው ምክር ይሰጡሃል እንጂ ኦዴት አያደርጉም። አዜብ ስትጠየቅ የቻይና እና የኮሪያ ኦዴተሮችን አስመጥተን ኦዴት አስደርገናል፤ እጄ ላይ ወረቀት አለ ብላለች። የዚህ አገር ኦዴተር ጠፍቶ ነው ከዚያ የሚያመጡት? ኦዴት አያውቀውም። እዚያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ተጠቅመውበት የቪላ ቤት ባለቤት ሆነዋል። ነገር ግን ብርሃነ ጋኖ ማለት በዘፈን 98 በመቶ የሚሆነውን ታጋይ በርሃ የወሰደ ነው። ሱዳን ላይ ተቸግሮ፣ ደሃ ሆኖ፣ በመኪና አደጋ ነው የሞተው። እሱን ጨምሮ አምስት ልጆቻቸውን ያጡት የብርሃነ ጋኖ እናት መቀሌ አደባባይ ቁጭ ብለው ይለምናሉ። አሁንም በሕይወት አሉ፤ ባለፈው ዓመት እንዴያውም በፌስ ቡክ ታሪካቸውን አንስቼ ከአሜሪካና ከተለያየ አካባቢ ሰዎች ረድተዋቸዋል። የብርሃነ እናት ዓይነት ታሪክ ያላቸው በጣም ብዙ ናቸው። የትግራይን ሕዝብ የያዙት በሴፍቲኔት ነው። ከበላና ከጠጣ ሌላ ጥያቄ ሊያመጣ ነው፤ ስለዚህ አፍነው ነው የያዙት።
ዘመን፡- በትግራይ የተካሄደውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ የእስካሁን ሂደት እንዴት አገኘኸው?
አቶ አርአያ፡- መጀመሪያ እነዚህ ሰዎች በጥጋብ፣ በስካር፣ በእብሪት ተነሳስተው ነው ይሄንን ወንጀል በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የፈጸሙት። እነሱ እንግዴህ በጎሬላ ውጊያ ዘመን ነው የሚያስቡት ያ፤ ደግሞ አያስኬድም አሁን ዓለም ሰልጥኗል። መንግሥትም በተደጋጋሚ በጣም በትዕግስት አልፏቸዋል። በትጥቅ ጊዜ እንደነበረው ሕዝቡም ያግዘናል ብለው በሽሬና በተለያዩ ቦታዎች መሣሪያ ሲያድሉ ነበር። እነሱ መሣሪያ የሚዋጋ ነው የሚመስላቸው፤ ሰዉ ግን ጀርባውን ነው የሰጠው። እነሱ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተወገዱት ያለምክንያት አይደለም፤ ትግራይ ውስጥ 40 ሺ ሰው ገድለዋል፤ ይሄ አረጋዊ በርሔም ያመነው ነው። ፊውዳል እያሉ የጨፈጨፏቸው 40 ሺ የትግራይ ተወላጆችን ማለቴ ነው። ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች ደም፣ የተሰዉት እምባ እና ጎዳና የሚለምኑት ተበዳዮች ግፍ ተደራረበና ሰው ጀርባውን ሰጣቸው። ስለዚህ መከላከያ መቀሌ የገባው ሰተት ብሎ ነው። ከዚህ ቀደም በሚዴያዎች ላይ እንደ ሳዳምሁሴንና ጋዳፊ ተጎትተው ከዋሻ ውስጥ ይወጣሉ ብዬ ነበር፤ ያው እንግዴህ እነ ስብሃት እንደዛ ወጡ። እና ሕግ የማስከበሩ ዘመቻ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ በጣም ጥሩ ነው።
ዘመን፡- ሕግ የማስከበር ዘመቻው በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ያሉት መረጃዎች እንዴህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የሚያደርሱ ናቸው?
አቶ አርአያ፡- እነዚህ ሰዎች ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቁረው አይደለም፤ እኔ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ከማጋለጥ እውነትን ከመያዝ ወደ ኋላ አልልም። አንድ ነገር ሲነሳ ምክንያት ይኖረዋል፤ እሳት ዝም ብሎ ሊፈጠር አይችልም ወይ በክብሪት ነው ወይ በሲጋራ ነው ወይ ደግሞ በአንዳች ነገር ነው። እንዴህ የሚሉትን ሰዎች ‘ይሄንን ትንኮሳ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ማን ነው?’ ብትላቸው የሚመልሱት መልስ የላቸውም። እዚያ የነበረው መከላከያ ሰራዊት እኮ! አግብቶ ተዋልዶ መንገድ እየሰራ፣ ክሊኒክ እየገነባና እህል እያጨደ 21 ዓመት ከሕዝብ ጋር የኖረ ነው። ዛሬ የታሰሩት እነ አባይ ወልዱ እና የስብሃት እህት ቅዱሳን ነጋ ይሄን ይመሰክሩ ነበር። ይሄን የሚያወሩ ሰዎች ሀቁን ለመደፍጠጥ እየሞከሩ ነው። እውነታው በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተወሰደው እርምጃ ነው።
ዘመን፡- ህወሓት የተከተለው ይዞ የመሞት ፖለቲካ ያስከተለው ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዴሁም የመሰረተ ልማት ውድመት በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው?
አቶ አርአያ፡- ልክ የመከላከያ ሰራዊት ሕግ ለማስከበር አጸፋዊ እርምጃ ጀምሮ በቀላሉ ከተሞችን መቆጣጠር ሲጀምር መጀመሪያ አሮጌውን ብር ለመቀየር በአንቶኖቭ የገባውን ገንዘብ ወሰዱ። ባንኮችም በጠቅላላ እንዴዘረፉ ተደረገ፤ ሲስተማቸውንም አበላሹት። ያ፤ ገንዘብ ተከማችቶ ‘ማን ነው የማይከዳን?’ ሲባል የስብሃት እህት ተመርጣ ቅዱሳን ነጋ ቤት ተቀመጠ። ከዚያ በኋላ አዴግራት ፋብሪካ የነበረውን መድኃኒት እንዳለ ወስደው ፋብሪካውን አወደሙት። ከተከዜ የነበረውን መብራት ጠቅላላ አቋረጡት። ኢንተርኔት እንዳይሰራ አደረጉ። በኋላም መቀሌ የሚገኘውን ድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሙሉ ለሙሉ አወደሙት። ቀጥሎም መረጃ የሚያቀብሉ ተቃዋሚዎች እና ብልጽግና ብለው የእነ አብርሃ ደስታን አሁን የመቀሌ ከንቲባ የሆነውን የእነ አትክልትን ስም ዝርዝር አውጥተው መግደል ሊጀምሩ ነበረ ፤ የገደሏቸውም አሉ። ከዚያ በኋላ ነው እንግዴህ የሚጭኑትን ጭነው በተለያየ አቅጣጫ ያመለጡት። ሞንጆሪኖ እና ደብረጽዮን በሬዴዮ ያደረጉትን የተጠለፈ ንግግር ሰምቼ ነበር። እሷ ‘በቃ ከእንግዴህ አብይ እግር ስር ወድቀንም ቢሆንም እርቅና ሰላም እንፍጠር’ ትላለች፣ እሱ ደግሞ ‘እርቅና ሰላም የምንፈጥርበት ጊዜ አሁን ዘግይቷል፤ ስለዚህ በየአቅጣጫው ሕይወታችንን ማዳን ነው ያለብን’ ይላል። የሄዱት በጣም ብዙ መሰረተ ልማት አውድመው ነው።
ዛሬ ግን ጣትን ወደ ሌላ ይቀስራሉ፤ እውነታው ግን ይሄ ነው፤ ያረጋገጥኩትም ነገር ነው። ‘የኤርትራ ወታደር ገባ’ ይላሉ። የአንድን አገር መከላከያ ሰራዊት ካረድክ በኋላ ማን ሊጠብቅልህ ነው ድንበሩን? ሌላም ኃይል ሱዳንም ግብጽም ሊገባ ይችላል እኮ! ምክንያቱም መጀመሪያ መከ ላከያው ላይ እርምጃ ወሰዱ። እነሱ ያደረሱት ከፍተኛ ውድመት ነው።
አሁን ትግራይ ውስጥ ረሃብ አለ። መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ በቶሎ ደርሷል። ሰዎች በረሃብ አልሞቱም። ይሄ ጥሩ ነገር ነው። ትግራይን መልሶ ለመገንባት በጣም ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል። መንግሥት ይሄን እንደሚያደርግ አልጠራጠርም። ብዙ ባለሀብቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ዝም እንዳሉ ግን ሊገባኝ አልቻልም። ያንን ሁሉ ሚሊዮን ብር ሲረጩ የነበሩ ሰዎች የትግራይ ልማት ሲባል ዝም ማለታቸው ይገርማል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት መቶ ሺህ ብር ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ ፣ የአንድ ወር ደመወዛቸውን እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስም ሦስት የውሃ ቦቴ መኪኖችን ሰጥተዋል። ይሄ ጥሩ ነገር ነው። ሌሎቹም ቢቀጥሉበት መልካም ነው። አንዳንድ ክልሎችም እያደረጉት ያለው ድጋፍ ጥሩ ነው፤ ግን ከፍተኛ ሀብት ማሰባሰብን የሚጠይቅ ነው።
ዘመን፡- ሕግ የማስከበር ዘመቻው ለትግራይ ምን ዓይነት መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል ማለት ይቻላል?
አቶ አርአያ፡- ትግራይ ከእንግዴህ በኋላ በአንድ ህወሓት እየተጠመዘዘ፣ መቶ በመቶ ምረጥ እየተባለ የሚገደድበትና ስንዴ የሚከለከልበት ዘመን አብቅቷል። ካንሰር የነበረው የነስብሃት የሴራ መንገድ ተበጥሶ ተጥሏል። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ነፃነቱን አግኝቷል።
ዘመን፡- መከላከያ ሚኒስቴር የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚሸልም ማሳወቁ ይታወሳል። አንተ ደግሞ አራት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ቦታ ጠቁመህ እንዴያዙ አድርገሃል። ቃል የተገባውን የገንዘብ ሽልማት አግኝተሃል?
አቶ አርአያ፡- አላገኘሁም፤ ባገኝም ለሕዝቡ ስንዴ የምገዛበት ነው። በትክክል ገልጸኸዋል፤ አራት ባለሥልጣናት ተንቤን ውስጥ ተደብቀው ነበር። ከአንድ ሰው ጋር ሆነን የተደበቁበትን ቦታ ለመከላከያ የመረጃ ክፍል ኃላፊዎች ጠቁመን እንዴያዙ አድርገናል። ነገር ግን የገንዘብ ሽልማት የተባለው አልተሰጠንም። እኔ እንደገለጽኩልህ ቢሰጠንም የማውለው ለሕዝቡ ነው።
ዘመን፡- ህወሓት ወታደራዊ ሽንፈት መከናነቡን ተከትሎ በውጭ አገራት የሚ ገኙ ደጋፊዎቹ የትግራይ ሕዝብ አድማ እንዴመታና ራሱን ከኢትዮጵያዊ እህትና ወንድሞቹ እንዴነጥል እያቀረቡ ያሉትን ጥሪ እንዴት ታየዋለህ?
አቶ አርአያ፡- እነሱ እንግዴህ በጣም ከፍተኛ የሀብት ትስስር የነበራቸውና ብዙ ጥቅም የቀረባቸው ናቸው። በደንብ አውቃቸዋለሁ። ዝም ብሎ ስም ማጥፋትና እንደ እነሱ ፍረጃ አልገባሁም። ከኤምባሲ ውስጥ ያገኘሁት ደብዳቤ ነበር። አሁን የተለያየ ጥሪ የሚያስተላልፉት ሚዴያዎች በወር እስከ ሰባት ሺህ ዶላር ድረስ ይወስዱ ነበር። ምን እንደሚሰሩ ግን አይታወቅም። በአንድ ወቅት የተከሰተውን ልንገርህ፤ የባለሥልጣናት ልጆች በሰባት ሺህ ዶላር አንድ ዕቃ በካሽ ይገዛሉ፤ እዚያ እንዴህ ዓይነት ባህል ስለሌለ የገቡበት እስቶር/የዕቃ ማከማቻ/ ሰዎች 911 ደውለው ነበር። እነሱ እንዴህ ናቸው። የችግሩ ሰለባ ግን የሆነው የትግራይ ሕዝብ ነው። የእነ ስብሃት ዕድሜ እንዴቀጥል ስንት ትውልድ መሞት አለበት? እዚህ ያሉት ሚዴያዎች ግን መጫወት የሚገባቸውን ሚና እየተጫወቱ አይደለም። ትግራይ ቲቪም እያስተላለፈ ያለው አንጻራዊ ነገር ነው። በተደጋጋሚ በየሚዴያዎቹ ብናገርም እርማት ሊደረግበት አልቻለም። እየሠሩ ያሉት የካድሬ ሥራ ነው። በፊትም ጋዜጠኞች ሳይሆኑ ካድሬ ነበሩ። የተሓድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው የገቡ ቢሆኑም እየሠሩ አይደለም። የችግሩ ሰለባ ሕዝብ እዚህ ስላለ እነዚያ ውጭ ያሉትን ከምንም አልቆጥራቸውም።
ዘመን፡- በትግራይ የሆነው ነገር ነው እየተነገረ ያለው? አንዳንድ ወገኖች «የተነገረው ጥቂቱ ነው፤ የከፋው ነገር ገና አልተገለጸም» ሲሉ ይደመጣሉ ፤ ሌሎች ደግሞ «ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል መረጃዎች ተጋነው እየቀረቡ ነው» ሲሉ ይከሳሉ። አንተ ባለህ መረጃ እውነታው የቱ ነው ?
አቶ አርአያ፡- በቅርቡ ቢቢሲ በትግርኛ ያወጣው ዘገባ ነበረ። ቢቢሲ ማለት ደንበኛ ድምጸ ወያኔ ማለት ነው። ኅዳር ሦስት ቀን ‹አብይ አዴ ተንቤን ከአያቷ ጋር የምትኖር አንድ ወጣት ሴት አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሄዶ አያቷን ይችን ልጃገረድ አብራው እንድትተኛ ሲጠይቀው፣ እምቢ ብሎት ሲታገሉ ወደ ውጪ አውጥቶ ገደለው› ብሎ የተቆረጠ እጅም በምስል አስደግፎ ዘግቧል። የዚህ ሁሉ ድራማ ማብቂያውና ምላሹ ምን መሰለህ!? ኅዳር ሦስት ቀን መከላከያ አብይ አዴ አልገባም። ጦርነቱ የተለኮሰው ጥቅምት 24 ነው። ኅዳር ሦስት ቀን አልገባም። እነ ቢቢሲ እያቀረቡ ያሉት እንዴህ ጽንፍ የያዘ፣ ሕዝብን የሚያነሳሳ፣ በጣም የተንሸዋረረ ዘገባ ነው።
ሚዴያው ላይ አልተሰራም የምልህ ይሄንን ነው።
ሁለተኛ ደግሞ ጦርነት ሲፈጠር ብዙ ነገሮች መከተላቸው ግድ ነው። ሰዎች ይሞታሉ፤ ይፈናቀላሉ፤ እነዚህ ሰዎች እኮ! የለኮሱት እርችት አይደለም ወይም ነገሩ ሰርግ አይደለም። መከላከያ ሰራዊት ላይ እርድ ሲፈጽሙ ተከታዩ ነገር ምን እንደሚሆን ግልጽ ነው። ስለዚህ ጥፋቶች አይደርሱም ማለት አይደለም፤ ይደርሳሉ። ለዚህ ሁሉ ግን መንስኤዎቹ እነ ስብሃት ናቸው።
ዘመን፡- የዓለም የጤና ድርጅትን እየመሩ ያሉት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ፣ በተለይም በወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያንጸባረቁ ስላለው አቋም ምን ትላለህ?
አቶ አርአያ፡- እርቀ ሰላም ይውረድ ማለቱ እንዳለ ሆኖ፤ ግን እነዛን ሰዎች/የህወሓትም አመራሮችን/ ያውቃቸዋል ለምን ‹ተዉ! ይሄ ነገር አያዋጣም።› አይላቸውም ነበር። ልጆቹ ራሳው በፌስቡክ እየጻፉ ያሉት ነገር መታዘብ ይቻላል። ‹ተነስ! ታጠቅ!› እያሉ በመንግሥት ላይ እየቀሰቀሱ ነው። ፈረንሳይ ውስጥ በተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ በፌስቡካቸው እየጻፉ ያሉት ነገር ግን የትግራይ ወጣት እንዴነሳሳ ነው። ልጆቹንም ‹ተዉ! ማን እንዴሞት ነው ይሄን ቅስቀሳ የምታደርጉት?› አይልም። በየቀኑ እየተፉ ያሉት ከባድ መርዝ ነው። ይሄ መንገድ እንደማያዋጣ መንገር ነበረበት። ይሄ ነገር ከተከሰተ በኋላ ግን መጮኹ ምንም ተቀባይነት የለውም።
ዘመን፡- በቅርቡ በውጭ አገር በሚገኘው «ትግራይ ሚዴያ ሀውስ» በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል የአቶ ጌታቸው ረዳ ነው በተባለ ድምጽ «ጦርነቱ አላለቀም። በየቀኑ እየተዋጋን ነው፤ መቶ ሺ ሰራዊት ደምስሰናል» የሚል መልዕክት ተላልፏል። መረጃውን እንዴት አገኘኸው?
አቶ አርአያ፡- ውሸታቸውና ፕሮፓጋዳንቸው የተለመደ ነው። በዚህ የተካኑ ናቸው። ስለጌታቸው እህቱም ተናግራለች፤ ‹ጌታቸው ጥይት ተኩሶም አያውቅም› ብላ በደንብ አድርጋ ነግራዋለች። ‹አሁን እያወራን ከፊት ለፊቴ መአት ወጣት ያልቃል› ይላል፣ የሚሰማው ግን የንፋስ ድምጽ ነው። አንድም የጥይት ድምጽ አይሰማም። ሁለተኛ መቶ ሺህ ከገደለ ታዴያ እነሱ ዋሻ ለዋሻ ምን ያደርጋሉ? እንደ በፊታቸው አፍነው እረግጠው እየገዙ ሥልጣን ላይ መሆን ነበረባቸው። ከተሞቻችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አጸፋዊ መልስ የምንሰጠው በጥንቃቄ ነው ይላሉ። ያደረጉት ግን መብራት እንዴቋረጥ አድርገው ትግራይ በጭለማ እንድትዋጥ ነው። ሕዝቡ ደግሞ አንቅሮ እንደተፋቸው ሁሉ አሳልፎ ሊሰጣቸው ይገባል። እነሱ የፈለጉትን ቢሉ አይድነቅህ።
ዘመን፡- መጽሐፍ ለማሳተም ዝግጅትህን አጠናቀሃል። መቼ ለንባብ ይበቃል?
አቶ አርአያ፡- በዚህ አንድ ወር ውስጥ መጽሐፌን አወጣለሁ። ከዚያ በኋላም የሚቀጠል መጽሐፍ ነው። ሁለት ሦስት ተከታታይ መጽሐፍቶችን ለማውጣት ዝግጅት ላይ እገኛለሁ።
ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
አቶ አርአያ፡- እኔም አመሰግናለሁ።