ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ጦሯን ብታሰፍር በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ይሰፍናል – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር

ትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ ያለ ባሕር በር መቀጠል ፈተናዋን የማብዛት ያህል የሚቆጠር ነው። በመሆኑም በርቀትም ሆነ በቅርበት ካሉ ጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆን ልማትን የምታመጣበትን መንገድ ማረጋገጥ የግድ ነው። ከዚህ አኳያ ዛሬም የባሕር በርን ማግኘት ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ትናንት ላይነሳ ተቀብሮ የተረሳ የመሰለው የባሕር በር ጉዳይ ዛሬ ከተቀበረበት ወጥቶ የሚመለከታቸው አካላትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲነጋገርበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሠረት ጉዳዩ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል። ከንግግር እና ከውይይት አልፎም ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደስምምነት እንድትመጣ ተደርጓል።

ዘመን መጽሔትም በዚህ ወር እትሟ ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር አያይዛ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን አነጋግራለች። ፕሮፌሰር በየነ፣ ከዛሬ 23 ዓመት በፊት ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዚሁ መጽሔት ላይ “የአሰብ ወደብ ሕጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ማጋራታቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ከዓመት በኋላም በመጽሔቱ “የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት መብት ለድርድር እንዳይቀርብ ታፍኗል” ሲሉም ተናግረዋል። ዘመን መጽሔት ከእኚህ ጉምቱ እና አንጋፋ ፖለቲከኛ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል። መልካም ንባብ።

ዘመን፡- ከዛሬ 23 ዓመት በፊት በዚሁ መጽሔት ላይ ከባሕር በር ጋር በተያያዘ የተናገሩት ነጥብ ነበር፤ በወቅቱ ስለወደብ ሲነሳ “የኤርትራን ሉዓላዊነት መጋፋት ነው” የሚል አካል እንዳለ ሁሉ፤ ዛሬም የሱማሊያን ሉዓላዊነት መጋፋት ነው ያሉ አካላት አሉ፤ እርስዎ ካለፈው ሀሳብዎ ጋር ዛሬ ላይ ያለውን ሲያነጻጽሩት እንዴት ያዛምዱታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አሰብን በሚመለከት ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር እንዲኖራት የማድረጉን ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ብሎ እንደ ቀላል የሚተወው ጉዳይ አይደለም። ከዛሬ 23 ዓመት በፊትም ያልኩት ነገር ቢኖር ይኸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ባለጉዳይ ሆኖ እንዳይነጋገርና መላ እንዳይፈልግ በወቅቱ የነበረውና የበላይነትን የያዘው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት አፍኖት ያስቀረው ነገር ነው። ይህን አባባሌን ዛሬም የምደግመው ጉዳይ ነው። ስለዚህ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኔ እምነትም ሆነ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያሳየው እውነታ ቢኖር የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳለው ነው። መብት አለው ሲባል በጉልበት የሚደረግ ነገር እንዳልሆነ ግን ልብ ይሏል።

በእኔ እምነት የኤርትራ መንግሥትም ቢሆን አሰብንም ሆነ ምፅዋን ከኢትዮጵያ ጋር በሰላምና በጋራ መጠቀም ፋይዳው ብዙ መሆኑን ተገንዝቦ የመፍትሔው አካል መሆን አለበት። የመፍትሔ አካል ቢሆኑ የሚጠቀሙበት እንጂ የሚጎዱበት ነገር የለም። ምክንያቱም ኤርትራውያንን ስናስተውል ልክ የሀገራቸው ያህል ወደኢትዮጵያ ሲጎርፉ ነው የምናየው። የኤርትራ ሕዝብ ሲቸገር ከየትኛውም ሀገር ይልቅ መርጦ ተንደርድሮ የሚመጣው እዚህ ወደ ኢትዮጵያ ነው። ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። ኢትዮጵያ ለኤርትራውያን ሁለተኛ ቤት ያህል መርጠው የሚመጡባት ሀገር ናት።

ይህንን መልካም የሆነ መንፈስ፣ ሥልጣን ላይ ያለ አካል በድሎት መኖር የለበትም፤ ልክ ሥጋ ከሥጋው መለየት እንደማይሆንለት በማሰብ ለመለየት የሚደረግ ጥረት ባይኖር መልካም ነው። ተፈጥሯዊው ሁኔታ ነውና ኢትዮጵያ የባሕር በር ኖሯት ኢኮኖሚዋ አድጎ እና ከራሷ ተርፋ የኤርትራም ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል አቋም አለኝ።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረገው ሁኔታ ሰው ሠራሽ ነው እንጂ ተፈጥሯዊ አይደለም። ኤርትራ በራሷ ለብቻዋ መልማት ቢያቅታት ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ላይ ናትና የኢኮኖሚ ብቃት ስላላት ማልማት ትችላለች። ለመሆኑ አሰብን ማን ነው ያለማው? በምሥራቅ አፍሪካ ታዋቂ የሆነ የቤንዚን ማጣሪያ ፋብሪካ ያቋቋመውስ ማን ነው? የኢትዮጵያ መንግሥት ነበር። የነዳጅ ማጣሪያው በወቅቱ በምሥራቅ አፍሪካ የታወቀ ነበር። ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሀገር የነዳጅ ፍጆታንም የሸፈነ ነበር። በወቅቱ የኤርትራንም የነዳጅ ፍላጎት እየሸፈነ የኖረ ነው። በዚያን ጊዜ ሌላ ማጣሪያ ኤርትራ ውስጥ ስለመኖሩ የማወቀው ነገር የለም።

ዘመን፡- እንደ ኢትዮጵያ ላለ ትልቅ አገር የባሕር በር ማጣት የሚያደርሰው ጉዳት ምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። የባሕር በር በመታጣቱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል። ከዚህ በኋላም ጉዳቱ እየሰፋ ይሄዳል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ባለችበት የባሕር በር እጦት የምትቀጥል ከሆነ ጉዳዩ የከፋ ይሆናል። በጂቡቲ ብቻ በሚገኘው አገልግሎት የኢትዮጵያን ፍላጎት ማርካት አይቻልም። ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እየደረሰባት ይገኛል።

ቀደም ባለው ጊዜ ስለ አሰብ በሚነገርበት ወቅት በወቅቱ “ሰላም እና ዴሞክራሲ” በሚል አዲስ አበባ ውስጥ ሐምሌ 19 ቀን 1983 ዓ.ም በተካሔደው የቻርተሩ ጉባኤ ላይ ተሳትፌ ነበር። በዚያን ጊዜም የባሕር በር ጉዳይ አንዱ የተነሳ ነጥብ ነበር። በወቅቱ የሕወሓት የርዕዮተ ዓለም ኃላፊ የሆኑት አቶ ተወልደ ወልደማሪያም ‹‹ኢትዮጵያን የባሕር በር ማሳጣት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንቁርት መዝጋት ነው። የአሰብን ነገር በአግባቡ ሳንደራደር ኤርትራ ነፃ ትውጣ የሚባለው ነገር አግባብ አይደለም›› ሲሉ ተናግረው ነበር።

አቶ ተወልደ፣ በወቅቱ የኤርትራ ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች በመኖራቸውና በተለይም በአሰብ ላይ የተደረሰ ስምምነት በመኖሩ የጉዳዩን ምንነት በተመለከተ ጉባዔው ያውቀው ዘንድ አቶ መለስን ጥያቄ ሲጠይቋቸው ነበር። ጥያቄው የቀረበላቸው አቶ መለስም፣ የሰጡት ምላሽ “አሰብን በጋራ እንጠቀማለን፤ ደግሞም እናለማለን ተባብለናል። ይህ በሁለት ሀገሮች መካከል የሚሆን ስምምነት ነው። ከዚያ በላይ አልፎ ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ የተለየ ወይም ከዚህ ያለፈ መብት ይኖራታል ብሎ ማሰብ የጦረኞች አመለካከት ነው።” የሚል ነበር። ውይይቱ ቀጣይነት እንዳይኖረውም በማሰብ ሀሳብ እንዳይንሸራሸር የዘጉት ወዲያውኑ ነበር።

እኔም ከዛሬ 23 ዓመት በፊት በዚሁ በዘመን መጽሔት ላይ በሰጠሁት ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉዳዩ እንዳይወያይበት ጉዳዩ የተዘጋና የታፈነ ነው ያልኩት ለዚህ ነው። ከዚህ ባለፈም በአቶ መለስ አማካይነት ስለጉዳዩ ማንሳት የጦረኞች አጀንዳ ነው ተባለ። እንደተፈራውም የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንቁርት የዘጋ ጉዳይ ሆነ። ከዚህ የተነሳ በርካታ ጉዳት ደርሶብናል። መፍትሔ ካላገኘም ጉዳቱ ደግሞ ከዚህ በበለጠ እየሰፋ ይሄዳል።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበትን የታሪክ ሂደት እንዴት ይመለከቱታል? በዚህ ጉዳይ የሚቆጩበትስ ነገር አለ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በወቅቱ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ አሜሪካ የራሷን ሚና ተጫውታለች፤ አቶ መለስን “አንተ አዲስ አበባን፣ አቶ ኢሳያስን ደግሞ አንተ አሥመራን ተቆጣጠር” በሚል ስታስማማ ነበር። በወቅቱ ሲሸመግሉ የነበሩት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ኸርማን ኮኸን የተባሉ ሰው ናቸው። እርሳቸው እንኳ ኢትዮጵያ አሰብ ላይ መብት ሊኖራት ይገባልና በዚህ ጉዳይ ላይ ተስማሙ ሲሉ ነበር። ይህንንም ዕድል ነው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ገፍቶበት መሔድ ያልፈለገው። ሁለቱም ቦታ መንግሥት እንዲቋቋም ያግባባው የአሜሪካ መንግሥት፣ እንደ መልካም ሐሳብ ያቀረበውን ነገር ሕወሓት/ኢሕአዴግ ግን ተቀብሎ መሄድ አልፈለገም።

አሜሪካንን የሚያክል መንግሥት በጉዳዩ ላይ ድጋፍ አሳይቶ እያለ እስከመጨረሻው ገፍቶ መሔድ ይቻል ነበር። እዚህ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ገፍቶ መሔድ ያልፈለገው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነው እንዳልል ከእነሱ መካከል ጉዳዩን የተቃወመ ሰው መኖሩ ግልጽ ነው። የሕወሓት የርዕዮተ ዓለም ኃላፊ ከአቶ መለስ ጋር አንድ አይነት አቋም አልነበራቸውም። ስለሆነም ጉዳዩ የአቶ መለስ አቋም መሆኑ ግልጽ ነበር ማለት ይቻላል። በወቅቱ ኢትዮጵያ አሰብን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ድርድር የማድረግ መብት እንዳላት የገለጹ ናቸው። ይሁንና ውይይት እንዳይካሔድ አቶ መለሱ ጉዳዩን ዘግተውት ነበር።

ይህ በእኔ አመለካከት ያመለጠን ታሪካዊ ስህተት ሆኖ ያለፈ ክስተት ነው። ስለዚህ ይህ የሚያስቆጨኝ ጉዳይ ነው። የመጀመሪው የሽግግር መንግሥት ሲቋቋም ኢትዮጵያ ያመለጣት ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያ በወቅቱ በጉዳዩ ላይ መደራደር የሚያስችላት እድል ብቻ ሳይሆን አቅሙም እያላት ቸል የማለቷ ነገር እኔ ከአቶ መለስ አመራር ትልቁ ችግር የነበረ ጉዳይ ነው። የብዙ ሚሊዮን ሕዝብ መሪ ሆነው ሳለ የአሰብን ጉዳይ እንደ ኢምንት የወሰዱበት ምክንያት ዛሬም ድረስ አልገባ የሚለኝ ነገር ነው። በኋላ ላይ እንደተረዳሁት ከሆነ የግምት ስህተት መኖሩን ነው። ስለዚህ የሚያስቆጨኝ ነገር ቢኖር በአሜሪካኖቹ ዘንድም የተዘጋ እድል ሳይኖር፤ በኢትዮጵያም በኩል የመደራደር ዕድልና አቅም እያለ አጋጣሚውን መጠቀም አለመቻላችን ነው። ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ መብት ሊኖራት ይገባል፤ እናንተ የምትገነጠሉት በዚህ አግባብ ነው የሚለውን በመደራደር ማስኬድ የከለከላቸው ምን እንደሆነ ያስገርማል።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ካጣች ከሦስት አስር ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የግድ የባሕር በር ያስፈልጋታል በሚል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብና ተነሳሽነትን አቅርበዋል፤ ይህንንስ እንዴት ተመለከቱት?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔ አንድ ኃላፊነት ያለበት ሰው ወይም መሪ ማንሳት ያለበትን ጉዳይ እንዳነሱ አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ከዚህ ውጭ ግን ይህ የባሕር በር ጉዳይ በአሁኑ ወቅት የተነሳው፣ አጀንዳ ለማስቀየር ነው፤ እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው እያሉ የሚናገሩ አካላት ሃሳባቸው አልባሌ መሆኑን ነው መናገር የምችለው። ኢትዮጵያን በመምራት ውስጥ ያለው ኃላፊነት እነርሱ እንደሚያዩት ቀላል አይደለም። ኢኮኖሚን ለማንቀሳቀስና ለማሳደግ ተብሎ የሚደረገውን ሩጫ እያየን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም በዚያም ብለው የሚያስጀምሯቸው ሥራዎች ውጤታማ ሲ ሆኑ እያየን ነው።

በዚህ ሁሉ ሩጫ ውስጥ ትልቁ የማይሽር ቁስል ለወደብ የምንገብረው ጉዳይ ነው። ፈረንጅ ሲናገር “ያለህን ሁሉ በአንድ ከረጢት ውስጥ አታድርገው” ይላል። ለምሳሌ በጂቡቲ መስመር ላይ አንድ ከፍተኛ የሆነ ችግር ቢገጥመን ሊመጣ ያለውን ፈተና ማሰቡ ብቻ በቂ ነው። ባለፈው መንግስት ከሕወሓት ጋር ባካሔደው ጦርነት ላይ ይህ መሞከሩ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ የውጭ እቃ የምታስገባበትን መስመር በመዝጋት ማንቁርቷን ለመያዝ ጥረት መደረጉ ይታወቃል።

ነገር ግን የአፋር ልጆች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለው ጉዳዩን ማስቆም ችለዋል። ይህን በምሳሌነት ያመጣሁልሽ የውስጥ ግጭት እንኳን ምን አይነት ሐሳብ ሊያመጣ እንደቻለ ለማስገንዘብ ነው። ከዚያ የበለጠ አቅም ያለው የውጭ ኃይል ቢመጣ ደግሞ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ የሚከብድ አይመስለኝም። የጠላት ችግር የለብንም፤ እዚህም እዚያም ሞልቷል። ስለዚህ ጉዳዩ ዝም ተብሎ የሚተኛበት አይደለም። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተይዞ በአንዲት መስመር ብቻ መተማመን በፍጹም የማይቻል ጉዳይ ነው። ከዚህ የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ሊኖረን ይገባል የሚለውን ጉዳይ በማንሳት ጥረት ማድረጋቸው አግባብነት ያለው ጉዳይ ነው።

ዘመን፡- ብዙ ሀገራት ከሩቅ መጥተው ቀይ ባሕርን እየተጠቀሙ ሳለ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያካሔደችው የባሕር በር ስምምነት አንዳንዶችን የሚያስቆጣቸው ስለምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- የሚያስቆጣቸው ምን ያመጣሉ በሚል ንቀውን ነዋ! ድሃዎች ናቸው በሚል ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከእንዲህ አይነት ፍረጃ መውጣት አለባት። ከዚህ ንቀት ለመውጣት ደግሞ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው። እንዲህ ስል ጦርነት ለማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ሰብሮ ለመውጣት መሥራት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ከባሕር በር ጋር ተያይዞ የጂቡቲ መስመር አንድ ነገር ቢሆን ይህ ብቻውን የማያስተኛ ስጋት መሆኑ ሊታበል አይገባም።

እኛ የባሕር በርን ለ30 ዓመት ያህል አጥተናል፤ ስለሆነም የትኛውንም አካል ቢያስቆጣውም የባሕር በር ለማግኘት ሌላ 30 ዓመት መጠበቅ የለብንም። መንግሥት ለሕዝቡ ኃላፊነት አለበት። እንግሊዞች በፓርላማቸው ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ለሶማሌላንድ እውቅና እንስጥ በሚል ጥብቅና እየቆሙ ናቸው። ከዚህ በላይ የሚጠበቀው ምንድን ነው በማለት ላይም ይገኛሉ።

ሶማሊያ ወይ ራሷን ችላ አልተገለለችም፤ ራሷን በአግባቡ ማስተዳደር አልቻለችም። በዚያድባሬ አገዛዝ ዘመን በሱማሌላንድ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሂዶባቸዋል። በአየር ድብደባ ጭምር ሱማሌላንድን ፈጅቷል። በዚህ መካከል ሱማሌላንዶች ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ ተቃውሞ ጀመሩ። እንዲያም ሆኖ ሶማሊያ ብትንትኗ ሲወጣ ሱማሌላንዶች ግን ጠንካራ ሆነው የራሳቸውን መንግሥት ማቋቋም ቻሉ። ስለዚህ የሞቃዲሾ መንግሥት ከሐርጌሳው መንግሥት ይልቅ ፍርክርኩ የወጣ ነው ማለት ይቻላል። የሶማሊያ መንግሥት ሠላም ማምጣትም ሆነ ራሱን ማረጋጋት ያልቻለ መንግሥት ነው። ቤተ መንግሥቱ ሳይቀር በየቦታው ፍንዳታ ሳይደመጥ የሚውልበት ሀገር ነው። እንዲያውም የሱማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለውለታው መሆኑን ሊገልጽ ሲገባው መልሶ የኢትዮጵያን መንግሥት ወራሪ ሲል መደመጡ የሚያሳዝን ነው።

እንደተባለው ሌሎቹ ሀገራት የተለያየ ድርድር ሲያደርጉ እንደ ጉዳይ አይታይም፤ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ደግሞ ብዙ ያወራሉ። ሶማሊያ ራሷ ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ጊዜያት በዚሁ አይነት ሐሳብ ለምሳሌ በበርበራ ወደብ ድርድር ባደረገችበት ጊዜ የት ነበረች? በወቅቱ የኢትዮጵያ ድርሻ በበርበራ ወደብ ላይ 19 በመቶ ብቻ ስለሆነ ነው? አሁንስ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን አፍሪካ ቀንድ ላይ ስትታይ ከሌሎቹ ጋር የምትነጻጸር ሀገር አይደለችም። በብዙ ትበልጣቸዋለች። ስለሆነም እውነታው ልትበልጥ ትችላለች የሚል አይነት ሳይሆን አሁንም ቢሆን የምትበልጥ ሀገር መሆኗ ነው።

አንድ መታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ድርድር ሶማሊያ ተሳክቶላት ራስ ገዟን ሱማሌላንድ ከራሷ ጋር ብትቀላቅላት ውሉ ቀጣይ መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሳ ተጠቃሚ የምትሆነው ራሷ ሶማሊያም ናት። ስለሆነም ኢትዮጵያ የገባቸው ውል ለእነሱም የሚጠቅም መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ከዚህ ያለፈው ነገር የሚመነጨው ከምቀኝነትና ጥላቻ ነው።

ሌላው መታወቅ ያለበት ሱማሊያና ሱማሌላንድ ቢታረቁ ኢትዮጵያ አትታረቁ አትልም። ኢትዮጵያ የምትፈልገው በትብብር መሥራት ነው። ነገር ግን እነርሱ ተስማምተው እስከሚታረቁ ድረስ ኢትዮጵያ መቆየት አትችልም፤ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት መልማትና በኢኮኖሚ ማደግ ለኢትዮጵያ አጣዳፊ ጉዳይ ነው። የሞቃዲሾ እና የሐርጌሳ ቁርሾን ለመፍታት መቶ ዓመት የሚፈጅ ከሆነ የኢትዮጵያ ችግር ደግሞ የዚያን ያህል ዓመት መጠበቅ አይችልም። ስለሆነም ፈቃደኝነት ካሳየው አካል ጋር በመልካም ጉርብትና እና በሰጥቶ በመቀበል መርሕ መጠቀም እንችላለን። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ አሠራር ነው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ማየት ሲገባቸው እዚህና እዚያ መራወጣቸው ተገቢ አይሆንም።

ባይሆን ሶማሊያን የሚያዋጣት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነቷን ማጠናከር ነው። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ በብዙ ዋጋ የከፈለች ሀገር ናት። አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ወታደር ሶማሊያ ውስጥ ሠላምን በማስከበር ረገድ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው።

ዘመን፡- ግብፅን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት የባሕር በር ስምምነቱን ተከትሎ የሶማሊያን አቋም መደገፋቸው ምክንያቱ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖስ ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር በየነ፡- የግብፅ አቋም ያልሠለጠነና ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት አካሄድ ነው። ግብፅ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጀምሮ ስታካሒድ የነበረው ነገር የሚታወቅ ነው። ከግድቡ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት ብቻ ያደረገላት ድጋፍ ቀላል የሚባል አልነበረም። ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትሠራ ጫና ለማሳደር ያልተኬደበት ርቀት የለም። ከዚያ የበለጠ ድጋፍ መስጠት አይችልም።

ከሱማሌላንድ ጋር የተገባው ውል ከሕዳሴ ግድብ ጋር ሲተያይ ኢምንት ነው። እንዲያውም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ውል የእነ አሜሪካም ጥቅም ያለበት ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ እዚያ አካባቢ ጠንካራ መሠረት ማስቀመጥ የአካባቢውን ሠላም በማስከበሩ በኩል ሚናው የጎላ ነው። ሶማሊያ ያንን ያህል ሠላም ማስከበር አትችልም። የሶማሊያ መንግሥት ጦር ኖሮት አሊያም ደግሞ ባሕር ኃይል ኖሮት የዚያን ያህል ድጋፍ ሊሰጥ አይችልም። ሶማሊያ ለባሕር ላይ ነፃ እንቅስቃሴ ድጋፍ መስጠት የማይችል መንግሥት ነው።

ኢትዮጵያ ግን እዛ አካባቢ የባሕር ኃይሏን ብታሳርፍ ያንን አካባቢ ሠላም ይሆን ዘንድ መቆጣጠር ትችላለች። ያንን ድጋፍ ደግሞ የበለጸጉ ሀገራት ይፈልጉታል። ከበርቴ ሀገራት የንግድ መስመራቸውን የተሳለጠ ለማድረግ የኢትዮጵያን እዚያ መኖር የሚፈልጉት ነገር ነው።

ስለዚህ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ይከበር ይበሉ እንጂ ከዚህ አልፈው ሔደው ኢትዮጵያን ለመኮነን ያደረጉትም የሚያደርጉትም እንቅስቃሴ የለም። እነዚህ ሀገራት ማለት ስላለባቸው ብቻ “የሶማሊያ ሉዓላዊነት ይከበር!” ከማለት በዘለለ የፈጠሩብን ጫና የለም። ሉዓላዊነት ይከበር ማለታቸው ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ስለሆነ እና ማለት የሚገባቸውን ለማለት እንጂ ኢትዮጵያን በመቃወም አይመስለኝም።

እውነት ለመናገር አገራቱ ከሶማሊያ የሚጠቀሙት ምንም ነገር የለም፤ ሶማሊያ ላይ ወጪ የሚያስወጣቸው ነገር እንጂ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነገር እንደሌለ ያውቃሉ። አሜሪካውያኑ አልሸባብን እንወጋለን በሚል የሚያባክኑት ሀብት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። አሜሪካኑ ጂቡቲ ላይ ካላቸው የጦር ቤዝ እየተነሱ አልሻባብን ለመምታት በብዙ ከስረዋል። ኢትዮጵያ ግን በዚያ አካባቢ ብትሆን በብዙ እንደምትደግፋቸው አሳምረው ያውቃሉ። ስለሆነም ይህ ሁሉ ከጂኦፖለቲክሱና ከሀገራቱ ጥቅም አንጻር መታየት ይኖርበታል።

ስለዚህ ግብፅ ገና ለገና ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ትጣላለች፤ አትጣላም በሚል ክፍተት ፍለጋ የምታደርገው ጥረት ነው እንጂ ግብፆች በታሪክም ሆነ ሁሌ ኢትዮጵያን ኃይል ለማሳጣት ያልሞከሩት ነገር የለም። ይህ ሴራቸው የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ከድሮ ጀምሮ ነው። ብዙ ጊዜ የዓባይን ምንጭ እንቆጣጠራለን በሚል ሲባክኑ እንደነበር የሚታወስ ነው። ስለዚህ የግብፅ ጫጫታ የተለመደ በመሆኑ ኢትዮጵያ ሥራዋን እንዳትሠራ የሚግዳት አይደለም።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ እስካሁን የመጣችበት ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ለባሕር በር ስምምነቱ ምን ያህል አግዟል ይላሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በእርግጥ እኛ ዝርዝር ዲፕሎማሲያዊ አካሄዱ ምን እንደሚመስል አናውቅም። ይሁንና እኔ የምረዳው ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት ስትፈጽም ያለምንም ነገር ዘላ ገብታበታለች የሚል እሳቤ የለኝም። ያንን ስምምነት ለመፈጸም ግራ ቀኙን እይታ እንደሆነም አልጠራጠርም። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት የሶማሊያ ሉዓላዊነት ይከበር የሚሉና ያሉ ሀገራት ሁሉ ጉዳዩን እንደሚያወቁ ነው መረጃው ያለኝ። በርግጥም አንድ አስተዋይ መንግሥት ጉዳዩ ምን አይነት ፋይዳ እና ፈተና እንደሚያመጣ ሳይመዝንና ከሚመለከታቸው ጋር ሳይመክር ዝም ብሎ ውሳኔ አይወስንም።

የዲፕሎማሲ አካሄድ ደግሞ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ ነገር አይደለም። ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ብዙ ዘመን የፈጀች እና በዚያም መንገድ ያለፈች አገር ናት። ከዚህ የተነሳ መንግሥት ስምምነትን ሲያደርግ በግብታዊነት አይደለም። አንዳንዶች እንደሚሉት ሳያቅድ እና አጀንዳ ለማስቀየር ሲልም ጉዳዩን አልጀመረም። ኢትዮጵያ ከዓረብ ኢምሬቶችም ጋር የቆየ ግንኙነት ያላት አገር ናት።

እዚህ ላይ አንድ ነገር መጥቀስ እፈልጋለሁ። ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል በማደራጀቱ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳደረገች ይታወቃል። በማሠልጠኑ፣ በማደራጀቱ እና መርከቦችን ዘመናዊ በማድረጉ በኩል ትልቅ ሚና ነበራት። እሷም ብትሆን ይህን ያህል ኢንቨስት ማድረጓ ምንም ጥቅም ሳታገኝበት በባዶ ሜዳ ይሆናል ማለት የዋህነት ነው የሚሆነው።

እነቻይናም ቢሆኑ በመስታወት ውስጥ ያለ ድንጋይ አይወረውርም እንዲሉ ሆኖባቸውና የታይዋን ነገር ስላለ ነው። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ስለዚህ እኔ የተካሄደበትን ዝርዝር ጉዳዩን ባላውቅም፤ ነገር ግን ጉዳዩ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግበት የሚወሰን እንዳልሆነ እገነዘባለሁ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትሠራውን ነገር ጠንቅቃ ታውቃለች፤ ዲፕሎማሲም ለእኛ እንግዳ ነገር አይደለም። ስለሆነም አካሄዱ ዲፕሎማሲያዊ የሆነ መንገድንም የተከተለ ነው ባይ ነኝ።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ከመሆኗ ባሻገር ትልቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንደመያዟ የሚያስፈልጋት አንድ የባሕር በር ብቻ አይደለም የሚሉ አካላት አሉ፤ እርስዎ እዚህ ላይ ያልዎ አመለካከት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ይህ ብዙ ክብደት ያለው ጥያቄ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ያለ የባሕር በር የሌለው ሰፊ ሕዝብ የያዘ ሀገር ወደባሕር የሚገባባቸውንና የሚወጣባቸውን በሮች ማስፋት ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ላይ ችግር የሚፈጠር ከሆነ ወደሌላ ደግሞ መሄድ ይችላል። ምክንያቱም የዛሬ ወዳጅ ነገ ባልተጠበቀ ጊዜ ሊቀየር ይችላል። “ይህ የባሕር በር የራሴ ነው” በሚል እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። በእጅ የተያዘ ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ በርከት ያለ የባሕር በር መኖሩ የግድ ነው።

ሌላው ደግሞ የባሕር በር ያለው ሀገርም ቢሆን ወደቦቹ የተለያዩ የዕቃ አይነቶች የሚመጡባቸውና የሚገቡባቸው እንዲሆኑ ይደረጋል። ለምሳሌ በአንዱ ወደብ ነዳጅ ብቻ የሚገባ ሊሆን ይችላል። ሌላው ወደብ ደግሞ ምግብ ነክን የሚያስገባ ሊሆን ይችላል። ሌላው እንዲሁ የንግድ ሸቀጥ የሚገባበት ሊሆን ይችላል። ከዚህ የተነሳ ወደቦቹ የሎጂስቲክ ፀባያቸው ሊለያይ ይችላል እንጂ እንደ የዕቃዎቹ አይነት ሊለያዩ ይችላሉ። ለምሳሌ ሳዑዲ ወደብ ያላት ብዙ ቦታ ነው። ሌላውም ሀገር እንዲሁ ነው። ስለዚህ ይህ ጥያቄ መነሳቱ ራሱ ይገርመኛል። ኢትዮጵያ ከአንድ በላይ ወደብ የግድ ያስፈልጋታል። እንኳን እኛ የባሕር በር ያላቸውም ብዙ ወደብ አላቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ተግዳሮት ያለባት አገር ብትሆንም ለኢኮኖሚ እድገቱ ዋና ቁልፍ የሆነው የባሕር በር የሚያስፈልጋት ስለመሆኑ አከራካሪ አይሆንም።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ ባደረገችው የባሕር በር ስምምነት በተለያየ ምክንያት ተቃውሞ ያላቸው ኢትዮጵያውን መኖራቸው አይታበልም፤ ለእነዚህ አካላት ያልዎት መልዕክት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እነዚህ አካላት እስከሚገባኝ ድረስ ኢትዮጵያ ያሳደገቻቸው እና ያስተማረቻቸው ናቸው። በተለይም ብቃት አለን ብለው ከኢትዮጵያ ወጥተው በየውጭ ሀገሩ የሚኖሩ ናቸው። በተለያየ የትምህርት ዘርፍም ሙያቸውን ያሳደጉና አንቱ የተባሉ ምሑራን ናቸው። የሕግ ባለሙያ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ በፖለቲካውም ዘርፍ ዕውቀቱ ያላቸው ናቸው። የሚያስገርመው ደግሞ ኢትዮጵያ በድህነቷ ያስተማረቻቸው እና አሁን ላሉበት ማዕረግም ያበቃቻቸው ናቸው።

እኔ በፖለቲካ ሕይወቴ ያየኋቸውና በብዙም የደገፉን አካላትም ያሉበት ነው። በተለይም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሂደት ደግሞ የደርግ ሥርዓት መውደቅ አለበት በሚል አብረውን የቆሙ ሰዎችም ጭምር አሉበት። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ የተፈራረመችውን ሰነድ ሲያጣጥሉ እሰማለሁ። የሰው ልጅ ማሰብ ሲያቅተውና ሲስት ምንም ማድረግ አይቻልም።

ማሰብ ያቃታቸውና ያሳታቸው ጉዳይ እንደሚመስለኝ ምናልባት ይህ ስምምነት በእኛ እጅ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ከእኛ ፈቃድ ውጭ የሆነውን ነገር ሁሉ እንበትነዋለን የሚል የምቀኝነትና የጥላቻ አካሄድ ነው። ይህ ደግሞ የታመመ አይነት አስተሳሰብ ነው ባይ ነኝ፡። ሥልጣን ላይ ማንም ይኑር ማን ኢትዮጵያ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል በሚል የሚደረግን ጥረት መቃወም ከጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ሐሳብ አይደለም።

ዛሬ ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉ ዕድሜ ልካቸውን በቦታው የሚቆዩ አይደለም። የሰው ልጅ የእድሜ ገደብ እንዳለው ሁሉ ሥልጣንም የቆይታ ገደብ አለው። መንግሥት ይሄዳል፤ መንግሥት ይመጣል። ያለፉት መንግሥታት ከነገሥታቱ ጀምሮ አቅማቸው እና ዕውቀታቸው በፈቀደ መጠን በባሕር በር ጉዳይ ሲያሳስባቸው ኖረዋል። በዚህም ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ አሉ።

ቀደም ባለው ጊዜ እነጣሊያን መርከባቸው ቆሞ ቤንዚን የሚቀይሩበትን ትንሽ ቦታ እንድንፈቅድላቸው በወዳጅነት ጠይቀውን ቀስ በቀስ ግዛታቸውን ያስፋፉበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም የሚታወስ ነው። በጂቡቲም በኩል ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። በጂቡቲ ፈረንሳዮች ከ1999 ዓ.ም በኋላ በአፄ ምኒሊክ ጊዜ ተጠቀሙ ተብሎ የተተወ ቦታ ነው። በኋላ ጊዜው ሲደርስ እንደሚመለስ ዓይነት የነበረም ጭምር ነው።

ጂቡቲ መንግሥት ሆና የተቋቋመችው በደርግ ጊዜ ነው። ይህ ደግሞ ፈረንሳዮች ጂቡቲን ትተው ወጥተው የጂቡቲ መንግሥት የተቋቋመው በቅርቡ ነው። እንዲያውም በመሐሉ ፈረንሳይ ወጥቶ ባዶ በሆነበት ጊዜ አሰብ አካባቢ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ወደ ጂቡቲ ሔዶ ተቆጣጥሮ ነበር። ይሁንና የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ፣ “ትታችሁ ውጡ” ብለው ባስተላለፉት መልዕክት ትተው ለመውጣት ተገደዋል። በወቅቱ የጂቡቲ መንግሥት የሚባል ነገር አልነበረም። እርሳቸውም በወቅቱ እንደዚያ ያሉት ከኤርትራ ተቃዋሚዎች ጋር ባላቸው አለመግባባት የተነሳ ሲሆን፣ ጦሩን ወደዚያ እንዲሄድ ለማድረግ አስበው ይመስለኛል። ጂቡቲ መንግሥት ያቋቋመችው ከዚያ በኋላ ነው።

ስለዚህ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ስምምነት የሚያጣጥሉ አካላት እውነት ለመናገር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በማኅበራዊ ትስስር ገጽ የዕለት ጉርሳቸውን የሚጋግሩ ናቸው። ማኅበራዊ ትስስር ገጹን መተዳደሪያቸው ያደረጉ አካላት ናቸው። ነገራቸው ሁሉ አልባሌ በመሆኑ እሱ ሊያሳስበን አይገባም። ከኢትዮጵያ እቅድ ጋር ሲነጻጸሩም ምንም አይነት ለውጥ የማያመጡና ከግምት የሚገቡም አይደለም። በጥቅሉ ጫና መፍጠር የሚችሉ አይደሉም። ስለዚህም የባሕር በርን በተመለከተ የሚንጫጫው አካል ይንጫጫ፤ ኢትዮጵያም ሥራዋን ትቀጥል። ሥራ በመሥራት ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች እና ከስጋት ነፃ የሆነች ሀገርን ለማስረከብ በተነደፈው እቅድ ላይ ጠንክሮ መሥራት ነው። ስለዚህ በየማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ገጼን ውደዱ፤ ሰብስክራይብ አድርጉ እያሉ ወደፊትም ኑሯቸውን በዚህ ሊገፉ በወደዱ አካላት የሚቀለበስ እድገት የለም፤ ሊያሰጋም አይገባም። በተመሳሳይ በፖለቲካ ሕይወቴ እንዲህ አይነት ነገር ደርሶብኝም ስለማውቅ እሱን አካሄድ ንቆ በመተው ቁም ነገሩ ላይ ማተኮር አዋጭ ነው።

ዘመን፡- ፖለቲካንና ብሔራዊ ጥቅምን ያለመለየት ችግር ከምን የመነጨ ነው ይላል? መፍትሔውስ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ይህ አስተሳሰብ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በእኔ እጅ ካልሆነ ሌላው የሚያደርገው ነገር ሁሉ ውድቅ መደረግ አለበት ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። እኔ የሌለሁበት ነገር ጥላሸት መቀባት አለበት የሚል ነው። ከዚህ አልፎ ጠንካራ መረጃ ኖሮት የሚረታ ነገር የላቸውም። ለራሳቸው በተሰደዱበት ሀገር ለራሳቸው አቅም ስላጡ የዕለት ጉርሳቸውን የሚያሳድዱ በመሆናቸው ጭምር ነው። እንዲህ ስል የሰውን ልጅ ጨርሶ ለማጣጣልና ለማንቋሸሽ ፈልጌ አይደለም፤ ይሁንና በአሁኑ ወቅት እያሳዩ ያለው ባሕሪ ግን ከዚህ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ስምምነት ማድረጓ የቀጣናዊ ትስስርን ለማሳለጥ ምን ሚና ይኖረዋል? ይህ ስምምነት ለአፍሪካና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚኖረውን ፋይዳስ እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በመጀመሪያ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋም ሆነ በጦሯ የጎላች ሀገር መሆን ለአካባቢው መረጋጋት ብዙ ጠቀሜታ አለው። እስካሁንም ድሃም እየተባለች በአካባቢዎቹ ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ላይ በሠላም አስከባሪነት እየገባች ብዙ ሚና እየተጫወተች ነው።

ኢትዮጵያን እንደ ጠላት የሚያየው የሞቃዲሾ መንግሥት መቼ አመስጋኝ እንደሚሆን አላወቅም እንጂ ኢትዮጵያን ሲከስ መስማቱ በጣም የሚያሳፍር ነው። በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ሠራዊት ሠላምና መረጋጋት እንዲያመጣ ወደ ሶማሊያ ልናስገባ ነው ባሉበት ጊዜ እኔ የፓርላማ አባል ነበርኩ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት አይግባ፤ ምክንያቱም ከሕዝቡ ጋር ያጣላናል በሚል እና በመቃወም ከረር ያለ ክርክር አስነስተን ነበር። ምክንያቱም ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር ያጣላናል በሚል ነው። ይሁንና “አይሆንም!” ብለው ሠራዊቱን አስገቡ። ይህ ሠራዊት ወደሶማሊያ ገብቶ ሞቃዲሾ ከተማን ነፃ አውጥቷል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር ናት። በቀጣዩም ጥንካሬዋ ይበልጥ እንዲጎላ ወደብ ያስፈልጋታል።

ደቡብ ሱዳን ነፃ ሆና ስትቋቋም የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ነው ድጋፍ ሰጥቶ መንግሥቷ እንዲቋቋም ያበቃው። ስለዚህ ኢትዮጵውያን እስከ ሩዋንዳም ድረስ ለሠላም ማስከበር የሄዱ ናቸው። የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከቀጣናውም ያለፈ ስለመሆኑ ዓለም ያውቀዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የበለጠ ጠንካራ ሀገር መሆን በቀጣናው ላሉ ሀገራት ሁሉ አለኝታ ነው። በእስካሁኑ ሒደትም ዝም ብሎ ሔዶ ለአንዱ ወግኖ ያደረሰው ጥፋትም የለም። አዳዲስ መንግሥታት ሲቋቋሙ ሀገር እንዳይጎዳ ሕዝቡ ላይ መከራ እንዳይደርስ ድጋፍ ከማድረግ ውጭ የሠራው ጥፋት የለም።

ዘመን፡- ከዚሁ ከባሕር በር ጋር አያይዘው ማስተላልፍ የሚሹት መልዕክት ካልዎ ሐሳብዎን ይግለጹልን?

ፕሮፌሰር በየነ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ የውስጥ ችግሮች እንዳሉበት ይታወቃል። በጥቂቱ ለማንሳት ያህል ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ያለ ችግር መጥቀሱ በቂ ነው።

ዝም ብለው በመመኘት ብቻ መንግሥት እንዲፈርስላቸው የሚፈልጉ አካላት አሉ። መንግሥት ፈርሶ ቦታው ላይ ምን ለማስቀመጥ እንደፈለጉ አናውቅም። መንግሥታዊ ሥርዓትን በማጠናከርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድረስ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርጎ እና በሀገር ውስጥም አመራር ሰጥቶ መኖር ብዙ አቅም፣ ጥበብና ብቃትን የሚሻ ጉዳይ እንጂ በምኞት የሚመጣ አይደለም።

ዝም ብሎ ብቻ በወሬ መንግሥት ለመሆን ማሰብ አዋጭም አይደለም። “እነ እንትና እዚህ ደርሰዋል፤ እዚያ ደርሰዋል” እየተባለ የሚባለውን ነገር መስማት ያስገርማል። ይህ አካል ወደየአዕምሮ ቢመለስና ቢያጤነው መልካም ነው እላለሁ። በዚህ አካሄድ ውስጥ በብዙ የተማሩና በሥራቸው አንቱ የተባሉ አካላት በስሜት ተገፍተው ሲገቡ ተስተውለዋል። ሀገር ደግሞ በስሜትና በእልህ ሊመራ አይችልም። አመራር ላይ ያሉ አካላትን ምክንያትና ሰበብ እየፈለጉ ማጥላላት ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባኝም።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትዕግስት ባያጣ መልካም ነው። ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ የዓለም መጨረሻ አድርጎ መቁጠሩም ተገቢ አይሆንም። ያለው ፈተና እንደማይስተካከል አድርጎ በአዕምሮ ውስጥ ማስረጽ አይበጅም። የማይካደው ነገር ችግሮች መኖራቸው ነው፤ እንደሚታወቀውም አንዳንድ መንገዶችም ተዘግተዋል። የሚሰሙ ነገሮች ሁሉ ነውር የሞላባቸውም ጭምር ናቸው። በእያንዳንዳችን ቤተሰብ ላይ የሚደርስ ነገርም አለ።

ይሁንና የብርሃን ፍንጣቂ ሊታየን ይገባል። ሁሉንም ጨለማ አድረገን መሳል የለብንም። እንዲያ ካደረግን ጨለምተኛ እንሆናለን። ተስፋ ማድረግ መልካም ነው። እናም እኔ ተማጽኖዬ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ተረጋጋ የሚል ነው። ስሜታዊ አትሁን፤ አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርገው ማንቋሸሽ ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥን ስላልሆነ ከዚያ ድርጊት ተቆጠብ። በመሰዳደብና አንዱ ሌላውን በመግፋት የሚመጣ ጥቅም የለም። ይልቁኑ ሕዝቡም አገርም ይጎዳል። በሬ ወለደ ወሬም የትም አያደርስም። መንግሥት አንድን ሕዝብ ሆነ ብሎ አይጎዳም። ሠላም ማስፈን ተቀዳሚ ዓላማው ስለሆነ በሚያደርገው እንቅስቃሴም ‹‹አትንኩኝ›› አትበል። እዚህ እና እዚያ ሆኖ የጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ ቢከርምም ሀገር መምራት እና ቡድን መምራት ለየቅል ናቸውና ከስሜታዊነት መውጣት ያሻል። እንዲያ ማድረጉ የሠላማዊውን ሕዝብ ኑሮ እንደመበጥበጥ ይሆናል። መንግሥት ደግሞ እንደእሱ አይነት አካሄድ ሲያጋጥመው ቆሞ የማይመለከት መሆኑን መገንዘብ ያዋጣል። በተለይ ተምሬያለሁ የሚል አካል ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅበታል። እኔ በበኩሌ ግን ኢትዮጵያ በዚህ አይነት ግርግር ትፈርሳለች የሚል እምነት የለኝም። እኛም ባለን አቅም እንንከባለላለን እንጂ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆመን አናይም ባይ ነኝ። ስለዚህ አገራችን በተፈጥሮም ጠንካራ የሆነች አገር አድርጌያት ነው የማሰበውና ስሜታዊ አንሁን መልዕክቴ ነው።

ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዘመን መጽሔት ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2016 ዓ.ም

Recommended For You