የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በ«አሰብ የማን ናት?» መጽሐፍ

ስለ ባሕር በር የተደረጉ ጥናቶች በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ ከወቅታዊነት፣ አስተማሪነትና አሳዋቂነት፣ መረጃ ሰጪነት፣ ተጨባጭነት፣ ተነባቢነት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ተጠቃሽነት ወዘተ አኳያ ሲፈተሽ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› ን የሚያክል ይህ ጸሐፊ አላጋጠመውም።

እያንዳንዱ መሥመር በመረጃ የተሞላ፣ እያንዳንዱ ገጽና ምዕራፎቹ በዕውቀትና እውነት ላይ የተመሠረቱ፤ ጣፋጭና ድገሙኝ፣ ደጋግሙኝ ∙ ∙ ∙ ከማለቱ አኳያ ከተመለከትነው መጽሐፉ ከምር ከብዙዎቹ ይለያል።

ከአዲስ አበባ 882 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስለሚገኘው፣ 811 ኪ∙ሜ የሚሆነው በኢትዮጵያ በኩል ስለአለው፣ ቀሪው 71 ኪሎ ሜትር ደግሞ በኤርትራ በኩል ስለሆነው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካኼደውን ጦርነት ተከትሎ ለ20 ዓመታት ተዘግቶ ስለነበረው አሰብ ወደብ ለማተት፤ ለኅትመት የበቃው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ከሌሎች ይለያል። ከሚለይበትም አንዱ ዓለም አቀፋዊነቱ ሲሆን ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ መርሖዎችን፣ ልምዶችን፣ ስምምነቶችን ወዘተ በርከት አድርጎ ይዞ መቅረቡ ነው።

መታሰቢያነቱን ለዲሞክራሲ፣ ለፍትሕና ለአንድነት ሲታገሉ ለወደቁ ኢትዮጵያውያን የአደረገው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› የብዙ ሕዝብ የታፈኑ ድምፆች መተንፈሻ፣ የበርካቶችን ቁጭት ማሳያ በመሆኑ ከሌሎች ይለያል።

ለተደጋጋሚ ኅትመት በመብቃቱ ብቻ ሳይሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ በመነበቡ፣ እጅጉን በማከራከሩ፣ ብዙዎችን ያነቃቃ መሆኑ፣ ለብዙዎች የመረጃ ምንጭ በመሆን ማገልገሉ፣ የበርካቶች ብዕር ከአፎቱ እንዲመዘዝና በአሰብ ጉዳይ በስፋት እንዲጻፍ ምክንያት መሆኑ ከመጽሐፉ ጠንካራ ጎን የሚመዘዙ እውነታዎች ናቸው።

ተሸጦ የሚገኘው ገቢ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚውለው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ 216 ያህል ዋቢ ሥራዎችን፣ ማጣቀሻዎችን (ቃለመጠይቆችን፣ ጥናታዊ ሥራዎችን፣ ታሪካዊና ሕጋዊ ሰነዶችን ወዘተ) በመያዝና በመረጃና ማስረጃነት በመጠቀሙ፤ ለአንባብያንም በራስ መተማመን እንዲፈጠር በማድረጉ ከብዙዎቹ መሰል ሥራዎች ይለያል።

የግርጌ ማስታወሻዎች ያሉትና በተለያዩ ሰንጠረዦች የተደገፈው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ከርእሱ ጀምሮ ቀልብ ሳቢና ለውይይትና ክርክር ጋባዥ፣ በራሱ የሚተማመን ተከራካሪ ካለ ወደ አደባባይ እንዲመጣና አሰብ የማን እንደሆነች በአደባባይ መረጃና ማስረጃውን ይዞ እንዲከራከር የሚጋብዝ ወዘተ መሆኑም ለልዩነቱ ተጨማሪ ማሳያ ነው።

‹‹አሰብ የማን ናት?›› (የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ) በደፋርነቱ ከሁሉም ይለያል። ደራሲው “ተዘግቷል የተባለውን ዶሴ ዳግም ወደ አጀንዳነት በመቀየራቸው፣ የተከደነውን በመከፋፈታቸው፣ የተደበቀውን በመገላለጣቸው፤ ከሁሉም በላይ የማናውቃቸውን ገመናዎች በመዘርገፋቸው እርሳቸውና ‹‹አሰብ የማን ናት?›› ሥራቸው ደንቅ ናቸው ማለት ይቻላል።

የወቅቱ መሪዎች “∙ ∙ ∙ ኢትዮጵያ ያለወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም። ∙ ∙ ∙፤ “ተቃዋሚዎች የሚያነት የአሰብ ይገባኛል ጥያቄ፣ ኢሕአዴግ አያምንበትም”፤ “አሰብን ካልያዝን የሚሉ ዘውዳዊ ትምክህተኞች ናቸው”፤ “አሰብ ኢትዮጵያ ከአልተጠቀመችበት የግመል መፈንጫ ይሆናል” (ደራሲው በገጽ 189 ላይ “በአንድ ወቅት የተነሣውን የአቶ መለስ ዜናዊ “አሰብ ኢትዮጵያ ከአልተጠቀመችበት የግመል መፈንጫ ይሆናል” የሚል አቋም ተከትሎ፣ የአካባቢውን ስትራቴጂክነትና ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳ የተረዱ ኢትዮጵያውያን፤ የአቶ መለስን ሐሳብ ተቃውመው፣ አሰብ ለኢትዮጵያ በጎ በማይመኙ ኃይሎች እጅ ትወድቃለች በማለት አስጠንቅቀው ነበር።” ማለታቸውን ልብ ይሏል።)፤ ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት ከአደረጓት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1434 − 1468) ጀምሮ፣ የቀድሞዎቹ “ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነትዋን አስከብረው ቢያልፉም፤ ይኽ ትውልድ ግን የተረከበውን አደራ መጠበቅ አልቻለም።” የሚሉ ትውልድ ወቃሽ አስተያየቶች በበዙበትና ስለ አሰብ ያነሣ ሁሉ በሚዘለፍበት በዛ ክፉ ጊዜ፤ “ለኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ተጠያቂው ኢሕአዴግ ነው“ በማለትና ራሱን፣ ኢሕአዴግን ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ ያለ ምንም ፍርኀት ለአደባባይ የበቃ መጽሐፍ በመሆኑ ሁለቱም (መጽሐፉና ደራሲው) ከሌሎች ይለያሉ።

የወቅቱ መሪዎች፣ “ወደብ አለመኖሩ ረኃብ አያመጣም። በጎረቤት አገር ወደብ በመጠቀም መሥራት ይቻላል። ያለ ነገር ነው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ያለ ወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም። ወደብ አለመኖሩ አይጎዳንም፣ ሊጎዳንም አይችልም። ወደብ በነበረን ጊዜ ኢትዮጵያ ደሀ ነበረች። አሁን ወደብ የለንም። ዕድገት ግን እያስመዘገብን ነው፤ በማለት አሰብን ለተመለከቱ የሕዝብ ጥያቄዎች የሰጡትን አስገራሚ መልስ ሁሉ ሳይቀር፤ “ያለ ምንም መሸማቀቅ (ያኔ በየስብሰባው ላይ እንዲህ ይባል ነበርና ነው) ለንባብ የበቃ ታሪካዊ መጽሐፍ በመሆኑ፣ ወቅቱንና የወቅቱን መሪዎች ልክ እንደ መስተዋት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ በመሆኑ፣ ከእስከ ዛሬዎቹና በርካታ ቁም ነገሮችን ሲያስጨብጡን ከኖሩት አሰብን የተመለከቱ ሥራዎች እጅጉን ይለያል የአልኩት።

እስቲ ስለ አዘጋጁ ጥቂት እንበል፤

መጽሐፉ በመግቢያው ላይ ዓላማው “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሰብ የኢትዮጵያ መሆኗን ዐውቆ የባሕር በራችንን ማስመለስ ብሔራዊ ግዴታችን እንደሆነ ለማስታወስ መጣር መሆኑን አስፍሯል። በመጨረሻው ምዕራፍ “አሰብን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ ለእነዚህ ሰዎች መጠነኛ ግንዛቤ እንዲሰጥ የተዘጋጀ” እንግሊዝኛ ጽሑፍን አካትቷል። የ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ደራሲ የሕግ ባለሙያ፣ መምህርና ጠበቃ ናቸው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ጉዳይ አስመልክቶ በዐቃቤ ሕግነት ሠርተዋል። በናይጄሪያና በካሜሩን መካከል ተከሥቶ የነበረውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት በሥፍራው

ከተሰማሩ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ። የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ተከትሎ በተቋቋመው ችሎት ውስጥ በዳኝነት ከተሳተፉ ባለሙያዎች አንዱ የነበሩ እና ለጉዳዩ ቅርበትና ዕውቀት የአላቸው ምሁር ናቸው። መጽሐፉ በእኒህ ደራሲ መዘጋጀቱ ጸሐፊው ለጉዳዩ ስለአላቸው ብቃት ይመሰክራል። የመጽሐፉ ዝግጅት በስሜት ሳይሆን በዕውቀት፣ በዐይን ምስክርነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ጠቀሜታው የላቀ ነውና ይለያል ስንል በምክንያት እንጂ ያለ አመክንዮ አይደለም።

የ“አሰብ የማን ናት?ን መጽሐፍ ለአደባባይ መብቃት ተከትሎ ከሸገር ታይምስ ጋር ቆይታ የአደረጉትና ‹‹አሰብ የኤርትራ ግዛት፣ የኤርትራ አካል አልነበረም። ወደ ኢትዮጵያ መቅረት ነበረበት። ግን ጠያቂ አልነበረም።›› የአሉት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ፖለቲከኛም ናቸው። ሪፖርተር ጋዜጣ “ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ የመጠፋፋትና የእልኸኝነት መንገድ መከተል በተመረጠበት የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳታፊ መሆን ተጨማሪ ጥፋት ከመሥራት ውጪ ሌላ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ ራሳቸውን ከፖለቲካ አመራር ሰጪነት “በቃኝ” በማለት መወሰናቸውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የውጪ ግንኙነት ሐላፊ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ይፋ” አድርገዋል” ሲል እስከ አስነበበት ጊዜ ድረስ በጠንካራ ፖለቲካ ተሳትፏቸው ይታወቁ እንደ ነበር ይታወሳል። በቅንጅት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥም አባል፣ በጉራጌ ዞን ችሃ ምርጫ ክልል ተወዳድረው አሸንፈው እንደነበርም ይታወቃል።

በማኅበራዊ ድረ ገፆች ሳይቀር:-

“ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ምሁር ሁሉ ራሱን ሸብቦ፣ የሕዝብ ጉዳይ አያገባኝም ባለበት ወቅት ሐሳባቸውን በአደባባይ ሲናገሩ ከነበሩት ጥቂት ምሁራን መካከል ግንባር ቀደሙ፤ ዜጎች ሲፈናቀሉ ጉዳያቸውን በነፃ ለፍርድ ቤትና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሲያቀርቡ የኖሩ ዕውቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ናቸው። እንደ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ መኢአድ የመሳሰሉ ፓርቲዎች (ሁሉም ምርጫ ቦርድ ሳያፈርሳቸው) በጭቆናው ዘመን ሲንቀሳቀሱ ዶ/ር ያዕቆብ መካሪ ሆነው አገልግለዋል። የኢትዮ ኤርትራውን ጦርነት ተከትሎ በነበረው የአልጀርስ ክርክር በወቅቱ ገዥዎቹ የውጭ አገር ጠበቃ በውድ እንቅጠር ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ በነፃ ልከራከር ብለው አገር ወዳድነታቸውን ያሳዩ ሰው ናቸው።

“ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ስለ ዜጎች በነፃ ተከራክረዋል። ሌሎች ዝም በአለቡት ወቅት እሳቸው ስለ አገር ብዙ ብለዋል። ስለ ሕዝብ ስቃይ ተናግረዋል። ስለ ሕዝብ አብሮነት ሰብከዋል። “አሰብ የማን ናት?“ ከእኝህ ሰው አእምሮ የተወለደች በመሆኗ፤ ጉዳዩን በቅርብና በጥልቀት በሚያውቅ ሰው ለመዘጋጀቷ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

ወደ «አሰብ የማን ናት?» (የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ) እንመለስ

አገራዊና ሕዝባዊ ጉዳትን፣ ከመጠቀም የአለፈ የባለቤትነት መብትን፣ ታሪክን ከሁሉም በላይ የሕግ ፅንሰ ሐሳብንና ሕጋዊ መደላድልን ተንተርሶ ለንባብ የበቃው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ፤ “የአሰብ ጉዳይ የፈሰሰ ውሃ ሳይሆን የተዳፈነ እሳት ነው፤» የሚል ትንቢታዊ ሐሳብ የሰፈረበት መጽሐፍ በመሆኑ በመሰል ርእሰ ጉዳይ ላይ ከተዘጋጁ መጻሕፍት እጅጉን ይለያል።

አሰብን ማጣትና የባሕር በር ተጠቃሚ አለመሆን በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በፖለቲካው ዘርፍ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ዐይን ከሰበከት እያገላበጠ የአሳየ፤ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የፈተሸ መጽሐፍ በመሆኑ ከእስከ ዛሬዎቹ፣ ኢትዮጵያን ከተመለከቱና አሰብን አሳልፎ የሰጠውን ቡድን ከኮነኑ ሥራዎች ይለያል።

ከኤርትራ ጋር በታሪክም ሆነ በሕግ አግባብ የማትገናኘው አሰብ በስጦታነት የቀረበችው ኢፍትሐዊ በሆነ አግባብ ነው። በተለይም አቶ መለስ በ1979 ዓ.ም. ኤርትራን አስመልክቶ በጻፉት መጽሐፍ፤ ‹‹ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች ማለት ትክክለኛና ሳይንሳዊ ነው ∙ ∙ ∙ ኢትዮጵያ የ3 ሺሕ ዓመት ታሪክ የላትም›› ማለታቸውን በግልጽ የሚናገረው፤ የዶ/ር ያዕቆብ “አሰብ የማን ናት? መጽሐፍ እውነት እውነቱን እንድናውቅና ለታሪክ ፍርድም ይመች ዘንድ ፍንትው አድርጎ በማስቀመጡ ይለያል።

በአልጀርስ ስምምነት ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ዕድሏ ሰፊ የነበረ ቢሆንም ፍላጎት በአለማሳየቷ እንዳማረን የቀረ መሆኑን የሚነግረን ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ በተዋቀረባቸው 13 ምዕራፎች በሙሉ ሞጋች ሆኖ በመቅረቡም ከጥንካሬዎቹ የሚደመር ነው።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት (መጽሐፉን ጨምሮ ብዙዎች ትርጉም የለሽና አሳዛኝ ጦርነት ይሉታል) አድርጋ ከአሸነፈች በኋላ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች ይዛ እንደ ነበር “አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ያስታውሳል። ያንን ከፍተኛ ወታደራዊ ድል እና የማይገኝ ዕድል ጨብጦ አሰብን ለማስመለስ መጠቀም ሲገባ በአንድ ሰው ትእዛዝ መሠረት ያ ሊሆን እንዳልቻለ እና አገርና ሕዝብን ለከፋ ሐዘንና ኪሳራ የዳረገ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ያሳጣ መሆኑን መጽሐፉ በማስረጃ ያቀርባል።

ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የነበራትን የባሕር በር ባለቤትነት መነሻ የአደረገ፤ ኢትዮጵያውያን በባሕር በር ባለቤትነታቸው ላይ የገጠማቸውን ተግዳሮትና የአደረጉትን መራር ትግል የዘከረ፤ የባሕር በር መኖርና አለመኖር በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያስከትለውን ጥቅምና ጉዳት፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የአለውን ሚናና ሌሎችንም የዳሰሰ፣ የኤርትራ መገንጠልን ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር የመሆኗን ጉዳይ በስፋት የቃኘ፣ የኢትዮኤርትራን ጦርነት እና የአልጀርሱን የድንበር አከላለል ስምምነት ∙ ∙ ∙ ወዘተ በጥልቀት በመመርመር እውነቱን ይዞ የቀረበም መጽሐፍ ነው።

በአሰብ ወደብ ጉዳይ ላይ በተለየ መልኩ የተለየ አጽንዖትን በመስጠት የአብራራ፤ በመግቢያው እ.አ.አ በታኅሣሥ 2000 ዓ.ም. በአልጀርስ የተፈረመው የወሰን መካለል ስምምነት አገራችን አሰብን የራሷ ግዛት የማድረግ ዕድል እንደነበራትና በኢትዮጵያ ድክመት ዕድሉ እንደአመለጠ በመግለፅ፤ በገጽ 9 ላይ “የኢትዮጵያን የባሕር በር ማስመለስ የሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን በማስረጽ፤ ይህም እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ ዐቅሙ የሚፈቅደውንና የሚችለውን እንዲያደርግ፤ የሚል አገራዊ ጥሪን የአቀረበ ነው።

“በስምምነቱ ወቅት ኢትዮጵያን ከወከሉት ተደራዳሪዎች መካከል በሕግ አማካሪነትና በጥብቅና ዘርፍ የተሰማራ ኢትዮጵያዊ ሰው አልነበረም።“ በማለት የዐይን ምስክርነታቸውን የሚሰጡት ደራሲው ዶ/ር ያዕቆብ ‹‹የድርድሩ ዋና አጋፋሪ ሚስተር አብዱል አዚዝ ቡተፍሊካ አልጄሪያ ከሻዕቢያና ከጀብሃ ጋር ለነበራት ግንኙነት ፓሊሲ ቀራጺና ለኤርትራ መገንጠል ሌት ተቀን የሠሩ ሰው መሆናቸው እየታወቀ በዝምታ ታልፏል›› በማለትም ይገልጹታል።

የአልጀርሱን ውል ከወቅቱ የተዋዋዮቹ ዐቅም ልዩነት፣ ከውሉ ኢፍትሐዊነትና ሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች አንጻር ውድቅ የሚያደርገው ይህ የዶ/ር ያዕቆብ መጽሐፍ፤ በድርድሩ ኢትዮጵያ 9 ሚሊዮን ዶላር መከስከሷንም በስላቅ እያነሣ ‹‹ወደው አይስቁ›› እንል ዘንድ ያደርገናል፤ “አሰብ የማን ናት?“ መጽሐፍ።

“ኢትዮጽያ የባሕር በሯ አሰብ እስከአልተመለሰላት ድረስ ኢሕአዴግ ከየትኛውም በጎም ይሁን መጥፎ ሥራዎች የባሕር በር ማዘጋቱ ከሁሉም በላይ ጎልቶ ይወጣል። አሰብ ለኢትዮጽያ እስከአልተመለሰ ድረስ ዘመናት አልፈው ዘመናት ሲተኩ በጊዜው ኢሕአዴግ ማን ነበር ሲባል መልሱ መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ወይንም ሐኪም ቤቶችን የአነጸው አይሆንም። መልሱ ‹‹የኢትዮጵያን የባሕር በር የአዘጋው መንግሥት ነው የሚሆነው።›› በማለትም መጸሐፉ ትንቢት ይነግረናል።

በመጀመሪያው አንቀጽ “ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች በአገር ውስጥ ብቅ ያሉ አምባገነን መሪዎች የጫኑባቸውን በደሎች ሰው ሠራሽም ሆኑ ተፈጥሯዊ ችግሮች በትዕግሥት ያስተናገዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን በትዕግሥት የማይመለከቱት ነገር ቢኖር የድንበር መደፈርን ነው ማለት ይቻላል። የሚለው ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ፤ እንዳለው ሁሉ ዛሬ ላይ ስለ አሰብ ጉዳይ ዳግም ምናልባትም ከፍ ለአለና ለተጋጋለ የውይይት ዐውድ ቆስቋሽ ሆኗል።

በወቅቱ በመጽሐፉ ላይ አስተያየታቸውን ይሰጡ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት በርካቶች ነበሩ። የወርልድ ፕሬሱ ጸሐፊ “የዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ ማርያም ‹አሰብ የማን ናት?› መጽሐፍ ዶክተሩን የሚያስመሰግን፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያነቃቃ ነው። መጽሐፉን እያነበብኩ እያለሁ ይሰማኝ የነበረው ስሜት በመዳን ላይ ያለ ቁስል ዳር ዳሩን ሲያኩት የሚሰጠውን ዓይነት ስሜት ነበር። (የምታውቁት ካላችሁ) በማለት የመሰከሩለት ከመሆኑም አኳያ እንመልከተው ካልን፤ አሁንም “አሰብ የማን ናት?“ መጽሐፍን የተለየ ብቻ ሳይሆን፣ የሥነልቦና ሕክምና (ሳይኮቴራፒ) ሆኖ ሁሉ እናገኘዋለን።

“የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ማካለልን በተመለከተ ብያኔ የተካኼደበት የአልጀርሱ ስምምነት መሠረት የአደረገው የኢትዮ ጣልያን የቅኝ ግዛትን ስምምነት ነው” እንደሚሉት፤ እንደ ዶ/ር ያዕቆብ አገላለጽ በቀይ ባሕር፣ በተለይ በአሰብ የኑክሌር መሣሪያ ቢጠመድበትና የጠላት ጦር ቢሰፍርበት፣ ለህልውናችን ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ ቢጠነሰስ ኢትዮጵያ ልታደርገው የምትችለው ምንም ነገር አይኖርም። ዐረቦች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ብቸኛ የቀይ ባሕር ተቀናቃኛቸው የነበረችውን ኢትዮጵያ ከባሕሩ አካባቢ አግልለው ቀይ ባሕርን የዐረብ ባሕር ለማድረግ ሲታገሉለት የነበረውን ዓላማቸውን አሳክተዋል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ደረቅ እውነቶችና በወቅቱ ኢትዮጵያ በገዛ ልጆቿ የተፈፀመባትን ደባና ክህደት ለትውልድ ግንዛቤ በሚያመች መልኩ ማቅረቡ ደራሲውን ከማስመስገንም ባለፈ ሥራቸውን ይበል ያሰኘዋል።

በኢትዮጵያ ላይ በፍጥነት የተሠራውን ሸፍጥም “የባሕር በርን የሚዘጋ፣ ባድመን፣ ኢሮብን፣ ጾረናን፣ ከፊል አፋርንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ ውዝግብ በ285 ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ የጊዜ ሰሌዳውን አጠያያቂ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ድርድሩ የተካኼደባት አገር አልጀርስ (አልጄሪያ) የኤርትራን መገንጠል ከጥንስሱ ጀምሮ ትደግፍ የነበረች ከመሆኗም ባሻገር የድርድሩ አጋፋሪ የነበሩት ሚስተር አብዱል አዚዝ ቡተፍሊካ (የወቅቱ የአ.አ.ድ ሊቀመንበር) ለኤርትራ መገንጠል የሃገራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የሠሩ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ እንዲነሣ ጥረው አልተሳካላቸውም።” በማለት በ“አሰብ የማን ናት? ምዕራፍ ስድስት ሥር አስፍረውት፣ ለትዝብትም አብቅተውት እናገኛለን።

የ “አሰብ የማን ናት?” መጽሐፍ አዘጋጅ ዶ/ር ያዕቆብ “አሰብ ኢትዮጵያ ከአልተጠቀመችበት የግመል ውሃ ማጠጫ ይሆናል” የሚለውን የወቅቱ ባለሥልጣናት ሁኔታዎችን የአላገናዘበ አባባልም በአሁኑ ሰዓት የኤርትራ መንግሥት ወደቡን ለሳኡዲና ሌሎችም አገሮች አከራይቶት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ይኽ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነት ስጋት ውስጥ እንዳስገባውም ይገልፃሉ። ይህ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ሊያሳስብና ወደ መፍትሔም ሊሄዱ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ጸሐፊው ከሸገር ታይምስ ጋር ቆይታ በአደረጉበት ወቅት፤ ‹‹በቀጣናው ኃያላን አገሮች የጦር ሰፈር እየገነቡ ናቸው። አገሮቹ የጦር ሰፈር እየገነቡ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቼ በምትላቸው አካባቢዎች ነው። ይኼ የኃያላን አገሮች እንቅስቃሴና ከበባ ኢትዮጵያን የት ድረስ ያሰጋታል?›› ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ:- “ምንም አያጠራጥርም፣ አሰብ ላይ ሳኡዲ ዐረቢያና ኢሚሬትስ የጦር ሰፈር ሠርተዋል። ከዚያም ግብጽ አሁን ሱማሌ ላንድ ላይ እንደዚሁ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ውይይት እያደረገች ነው። ግብጽም ሆነ ሌሎቹ የዐረብ አገሮች ጅቡቲ ዉስጥ ብዙ እንቅስቃሴ አላቸው።

አንዳንድ ሰፈሮችንም ሠርተዋል። ከዚያም አልፎ ግብጽ ቀጣናውን አልፎ እንዲያውም ከደቡብ ሱዳን አንድ ስምምነት ተደርጓል። ስምምነቱ ምን እንደሆነ ብዙ ሰው አያውቅም። ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ቀለበት ውስጥ ገብታለች። ተከባለች ማለት ነው። ስለዚህ በተከበበችበት ሁኔታ ከእነዚህ የጦር ሰፈሮች መሠራት በተጨማሪም ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ግብጽ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ገዝታለች። እና ይኼ ሁሉ ለምንድነው ግብጽ የአስፈለጋት? የሚለው ጥያቄ ሲነሣ የኢትዮጵያ ሁኔታ እዚያ ውሰጥ መግባቱ የሚያጠራጥር አይደለም። በማለት መመለሳቸውን ስናስተውል በጉዳዩ ላይ የጸና አቋም የያዙ ከመሆናቸው ባሻገር፤ ችግሩን በውል ከመረዳት አኳያ ከብዙዎች የተሻለ ዐቅም ያላቸው ምሁር መሆናቸውን እንገነዘባለን።

በምዕራፍ ሰባት ሥር ደግሞ በአልጀርሱ ድርድር ወቅት ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን በአብዛኛው ይከራከር የነበረው ለኤርትራ ነበር። የኢትዮጵያ ድንበር በተሰረዘው “ውል መሠ ረት ከምሥራቅ 60 ኪ∙ሜ ገባ ብሎ ስለነበረ የምሥራቅ ጠረፍ የሚባለውን ከደሴቶቹ ሳይሆን ባሕሩ ከሚያልቅበት የየብሱ ጫፍ እንዲጀምር ተከራክረዋል። ከዚህም በላይ ቡሬን ድንበር አድርጎ በማካለል ከ60 ኪ∙ሜ በላይ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዋል። ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን ጾረና የኤርትራ ነች ብሎ ድርቅ በማለቱ ካርታው ልዩ ቅርጽ ሠርቶ ጾረና ወደ ኤርትራ መከለሏ በካርታ ሳይቀር በመጽሐፉ ላይ ተመላክቷል።

በዚህ መንገድ ከጣልያን የተቀላቀለችው ኤርትራ ‹‹የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት›› ተብላ ስትገነጠል “ባለህበት እርጋ የተባለው የድኅረ ቅኝ ግዛት መርሕም አልተከበረም። የድንበር ኮሚሽኑ መሬቱን ሲያከፋፍል የተለያዩ የሰብአዊ መብቶችን (የዜግነት መብቶችን) እንዳሻው በመከፋፈል ጥሷል። የኢትዮጵያ ሰራዊትም በጦርነቱ ወቅት የአሰብ ወደብን መቆጣጠር ሲችል በገዢዎቻችን ትእዛዝ ወደ ኋላ አፈግፍጓል።

በአልጀርሱ የድርድር ሂደት የኢትዮጵያን ሽንፈት ዕውቁ ምሁር ፕሮፌሰር ክላፋም ‹‹ኢትዮጵያ ሽንፈትን ከድል መንጋጋ ፈልቅቃ አወጣች›› በማለት የገለፁት መሆኑን በዚሁ መጽሐፍና በዚሁ ምዕራፍ ላይ አስፍረውት ይገኛል።

ግራና ቀኝ በጠላት የተከበበቸው ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሣሪያ ከውጭ በባሕር ማስገባት የግድ ይላታል። ይሁን እንጂ፣ ባለ ወደቡ አገር ከፈለገ ይህን ያህል ብቻ ይበቃሃል ብሎ ማስተላለፍ ላይ ገደብ ሊጥልበት ይችላል። እናም የሉዓላዊነት ገዳይ ዘወትር በቋፍ ላይ ይንጠለጠላል ማለት ይሆናልና ልብ ያለው ልብ ይበል፤ አእምሮ ያለውም ያስብ ዘንድ አጥብቃ አሳስባለች፤ “አሰብ የማን ናት? መጽሐፍ።

እንደ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ከሆነ ወረራም ሌላው ስጋት ነው። ጄኔራል ናፒየር ዐፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት ወደ አገራችን የገባው በቀይ ባሕር ወደብ ነው። ወራሪዎች ከስትራቴጂክ አንጻር ከየብሱ ባሕሩን ይመርጣሉ። ምክንያቱ ደግሞ የቀለለ መሆኑ ሲሆን፤ መጽሐፉ ይህንንም እንድናስብ ማድረጉ ለየት የሚያደርገው ሆኖ፣ ስለ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነቱ ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ ቆም ብሎ ያስብ ዘንድ የሚያስገድድ ነጥብ በመሆኑ ሌላው የ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› ጥንካሬና ብቃት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

“∙ ∙ ∙ ኢትዮጵያ ያለወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም፤ ከአሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በ1983 ዓ.ም. “የአሰብ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ መካለል እንዳለበት ታሪክም፣ ሕግም ያስገድዳል” (ምዕራፍ አራትን ይመለከቷል) ለሚለው ለፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስ አስተያየት “ታሪክና ሕግ የሚሉትን ዝባዝንኬ ለትምህርት ቤት ይተዉት፤ ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ በጦር ሜዳ ተፈትቷል።›› በማለት መልስ ከሰጡት ኢሳያስ አፈወርቂ በተቃራኒ የቆሙትና “በአንድ ሰው (የመለስ) የዐይን ጥቅሻ ኢትዮጵያ በ60 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀይ ባሕረ ሰላጤ ሙሉ ለሙሉ ተገለለች ከሚሉት (በ“አሰብ የማን ናት? ላይ እንደ ተጠቀሰው) ፕሮፌሰር ፀጋዬ መብራሕቱ ጋር የሚስማሙት ዶ/ር ያዕቆብ፤ የአልጀርሱን ጉድ (ስምምነት የሚሉትን) በተመለከተም “የድንበር ውዝግብ በሚፈጠር ጊዜ አገሮች ጉዳያቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ይወስዳሉ። ይህ ፍርድ ቤት የቅኝ ግዛት ውሎችን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ የተደረጉ ውሎችን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን፣ የሕግ ልሂቃን የጻፏቸውን ጽሑፎች በሙሉ ይመለከታል። ሂደቱ ባለቀ ጊዜ ያልቃል እንጂ አያጣድፍም። (ከላይ “በ285 ቀናት ውስጥ ∙ ∙ ∙” ያልነውን ያስታውሷል) በማለት ያሰፍሩና የእኛኑ ጉድ አስመልክተውም፤ ‹‹ወደዚህ ፍ/ቤት መሄድ አልተፈለገም።›› ሲሉ እውነቱን ወድደን ሳይሆን ተገድደን እንድንውጠው ያደርጉናል።

በተለይ በመጽሐፉ ምዕራፍ አምስት ሥር “እነዚህ [በ1900፣ በ1902 እና በ1908 በተፈራረሟቸው የኢትዮ-ጣልያን የቅኝ ግዛትን ስምምነቶች] ጥንታዊ ውሎች ኢትዮጵያ ላይ በጣልያን በግድ በመጣላቸው፣ ጣልያን ውሉን ጥሳ ኢትዮጵያን በመውረሯ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣልያን ቅኝ ግዛቷን በመነጠቋ እና ኢትዮጵያና ኤርትራ የኋላ ኋላ በመዋሐዳቸው በተደጋጋሚ የተሰረዙ ውሎች ናቸው። የኢሕአዴግ መንግሥት ግን ይህንን እውነታ ሽሮ በአልጀርሱ ስምምነት በኢትዮ-ጣልያን በተሻሩ ውሎች ለመቀጠል መስማማቱ በድንበር ማካለሉ ሥራ የወደብ ባለቤትነታችን ሊረጋገጥ ቀርቶ ቤተክርስቲያንና የመቃብር ቦታው፣ ከዚያም በላይ አንድ ትምህርት ቤት ለሁለት እንዲከፋፈሉ ሆነዋል።” የሚል ሰፍሮ መገኘቱ የ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍን ዘመን አይሽሬነት ከወዲሁ ይናገራልና የደራሲው ሥራ ይለያል ስንል ያለ ምክንያት አይደለም።

ለባሕር በርና የባሕር በርን ለማስከበር ሲባል በዐፄ ዮሐንስ፣ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ ዐፄ ምኒልክ የተከፈለውን መሥዋዕትነት ብቻ ሳይሆን፣ በንግሥት ዘውዲቱ፣ በዐፄ ኃይለ ሥላሴና በመንግሥቱ ኃ/ማርያም ሥርዓትም የባሕር በርን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ይተርካል። ከቅርብ ጊዜው ኢሕአዴግ በስተቀር የእስከ ዛሬዎቹ የአገሪቱ መሪዎች የአሰብ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ሲከፍሉ የኖሩትን መሥዋዕትነት የሚዘረዝረው ይህ መጽሐፍ ተግባሩን፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ‹‹አንድም ስሕተት፥ ሲከፋም ክህደት›› በማለት ያስቀምጠዋል።

ከርቀትና ቅርበት አኳያ አሰብን የመጠቀም ፋይዳን በተመለከተም “ኢትዮጵያ የምትከራያቸው የጎረቤት አገር ወደቦች ርቀታቸው ከአዲስ አበባ፣ ከ910 ኪ.ሜ. (ጅቡቲ) እስከ 1804 ኪ.ሜ. (ሞምባሳ) ይደርሳሉ። የአሰብ ወደብን ብንጠቀም ግን 640 ኪ.ሜ. ብቻ (ከኢትዮጵያ የአሁኑ ክልል ደግሞ 60 ኪ.ሜ. /የእግር መንገድ ርቀት/) ወይም ከጅቡቲ አንፃር የአንድ ቀን የመኪና ጉዞ መቅረብ ትችላለች” በማለት በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ሥር ሰፍሮ ይገኛል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡ “∙ ∙ ∙ ኢትዮጵያ ያለወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም። ∙ ∙ ∙” ሲሉ የተናገሩትን ከሥሩ በመናድ “ወደብ የሌላቸው ድሃ ሃገራት የውጭ ንግዳቸው ከ33 እሰከ 43 በመቶ ሊቀንስ ይችላል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በየቀኑ ከ 3 ሚሊዮን ዶላር (በዚያ ጊዜ ስሌት፤) ይህ የዶላር ቁጥር ዛሬ ስንት እንደሆነ ባናውቅም ከእጥፍ በላይ እንደሚሆን ግን መጠራጠር አይቻልም) ታወጣለች። ከዚህም በከፋ መንገድ በኢኮኖሚ ዕድገት አንድ ወደብ ያለው አገር በ24 ዓመት ኢኮኖሚው እጥፍ ማደግ ሲችል፣ ወደብ የሌለው ግን 36 ዓመት ይፈጅበታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆኑ አገሮች መካከል በሕዝብ ብዛት አንደኛዋ ስትሆን ብሔራዊ ደኅንነቷ በዚሁ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቋል።” በማለት ገና በጠዋቱ፣ በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ በማስፈር ተቆጭተው ያስቆጫሉ።

በአንድ ወቅት ዶ/ር ያዕቆብ ከቢቢሲ አማርኛው ፕሮግራም ጋር በአደረጉት ቆይታ፤ “ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሶማሌላንድ የዐረብ ሊግ አባል አገሮች ናቸው። እነዚህ አገሮች እርስ በእርስም ቅርበት አላቸው። እንዲሁም ጅቡቲ ከበርካታ አገሮች ጋር ስትራቴጂካዊ ትስስርን ፈጥራለች።

“ወደቦቿን ቻይናዎች፣ እንግሊዞች፣ ፈረንሳዮች እና ግብጾች ይጠቀሙታል። ግብጽም ብትሆን ወታደራዊ ማዕከል በኤርትራ መሥርታለች። ይህ ብቻ ሳይሆን ግብጽ በደቡብ ሱዳንም ወታደራዊ ማዕከል አላት’’ በማለት መግለፃቸው የአሰብ ወደብን መጠቀም አለመቻል ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ መጣል መሆኑን ከፍ አድርገው ማሳየታቸው እንደሆነ በወቅቱ ተነግሯል። ኢትዮጵያ እያንዳንዱ ውሳኔዋን ከጂኦፖለቲካዊ ጥቅም አንጻር መፈተሽ ያለባት መሆኑም እንደዛው።

ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፤

«ነገር በሆድ ማመቅ፣

ለትውልድ መርዝ መጥመቅ፤»

እንዳለው፤ ወይም ደበበ ሰይፉ:-

በትን ያሻራህን ዘር፣

ይዘኸው እንዳትቀበር።

ሲል እንደአሳሰበው፤ ዶ/ር ያዕቆብም የሚያውቁትን በሆዳቸው መቋጠርና ለትውልድ መርዝ ማስቀመጥን ባለመፈለጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ሥራቸውም ዐይን ገላጭ፣ ልብ አስደንጋጭ፤ ጊዜ ከማይሽረው (timeless/ ሊሆን መቻሉ ላይ መጠራጠር አይቻልም) ነውና ከሌሎቹ መለየቱ ላይ አጽንዖት ቢሰጠው ቢያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይሆንም። በመሆኑም የአገር ባለውለታ ናቸው ብሎ መደምደም ያስችላል።

በመጨረሻም ወደ ተሰነዘረው አስተያየት እንምጣ።

“በዓለም 44 ወደብ የሌላቸው ሀገሮች አሉ። ከ 44 ቱ የድሃ ድሃ የሚባሉት 13 ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። በመሆኑም ለኢትዮጵያ የወደብ አስፈላጊነት በጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። እንደሚሉት፤ እንደ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ደራሲ አስተያየትና የመፍትሔ ሐሳብ አሰብን ሁለቱም አገሮች በጋራ ይዘውት ሁለቱም ጣምራ ሉዓላዊነት (joint sovereignty) እንዲኖራቸው ሊስማሙ ይችላሉ። ለዚህም ሕንድና ፓኪስታን የሚፋጠጡበት የካሽሚር ግዛት፣ ፈረንሳይና ስፔን ለ700 ዓመታት የሚያስተዳድሯትን አንዶራ የተባለች አገር በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

ሌላው የዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም የመፍትሔ ሐሳብ፤ “ከኤርትራ ጋር ሰላም መሥርቶ መደራደር ነው። ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር በ1952 በፌዴሬሽን ስትቀላቀል “የኢትዮጵያ ሕጋዊ የሆነ ወደ ባሕር የመዝለቅ መብቷ እንዲጠበቅ ኤርትራ በፌዴሬሽን ተቀላቅላለች” ይላል የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ። ኢትዮጵያ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ከኤርትራ ጋር ተደራድራ አሰብ ወደብ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋታል“ የሚል ነው።

በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የሚፈጠር አለመግባባትም፤ ልክ እንደ እስከ ዛሬው ሁሉ በመነጋገር የሚፈታ እንደሆነ፤ የወደብ አጠቃቀምን በተመለከተ ሊከሠቱ የሚችሉ አለመግባባቶች ወቅታዊ ሁኔታን የሚከተሉ በመሆናቸው ጥርስ የሚያናክስ እንደማይሆን የሚያሳዩ ጥናቶችና የባለሙያዎች አስተያየቶች መኖራቸውን በመጥቀስ በ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ላይ ያለንን አስተያየት እናጠቃልላለን።

ግርማ መንግሥቴ

ዘመን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም

Recommended For You