አዲስ ስፖርት

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በየአከባቢው በማስፋፋት እእምሮው የበለጸገ ጤናው የተጠበቀ ዜጋን ማፍራት ሀገራት የሚጋሩት ዓለም አቀፍ ግብ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ማንኛውም ማኅበረሰብ በሚኖርበት፣ በሚማርበት እና በሚሠራበት አከባቢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናማ እና አምራች ዜጋ እንዲሆን መሥራት እንዳለበት በግልፅ ያስቀምጣል። ይህን ታላቅ ሀገራዊ ፖሊሲ ለማሳካትና ስፖርትን ባህል ለማድረግ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች መካከል ዋነኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ለዜጎቿ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ለረጅም ጊዜ አልነበራትም። በተለይም የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱና የቆዳ ስፋቷ ውስንነት በከተማዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን እንደ ልብ ያለመገኘት ችግር እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከተማዋ ያለባትን ይህን ትልቅ ችግር ለመፍታት የከተማዋን ስታንዳርድ /ደረጃ/ የሚመጥኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን የማዘጋጀት ትልቅ ሐላፊነት ተሰጥቶት እየሠራ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ በአለፉት አራት ዓመታት ከ500 በላይ የሚሆኑ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ ፣የመረብ ኳስ፣ የሕፃናት መጫዎቻዎች እና ቤተመጻሕፍትን ጨምሮ 17 ዓይነት አገልግሎቶችን የሚሰጡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

አቶ ብርሃኑ ባዩ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማዕከላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ቢሯቸው ከተሰጡት ሐላፊነቶች ዋነኞቹ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራዎችን መገንባትና አዳጊ ስፖርተኞችን ማፍራት መሆኑን ይናገራሉ።

ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ስለሚያስፈልጉ ሁለቱ ጉዳዮች ተያያዥ ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራ ትውልድን ከማነጽና አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ከማድረግ አንጻር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ይገልጻሉ። ቢሯቸውም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ለእነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ሲያስረዱም፣ እንደ ቢሮ የዓሥር እና የአምስት ዓመት ዕቅድ አለን። ከእነዚህ ዕቅዶቻችን በመነሣት በየዓመቱ ዝርዝር ዕቅዶችን በማዘጋጀት ከመሬት አስተዳደር፣ ከዲዛይንና ግንባታ እና ከፋይናንስ እንዲሁም ከፕላን ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሥራት ውጤት ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። በየመንገዱ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች ጥርጊያ ሜዳዎች ተሠርተውላቸው የሚገለገሉበትን ሁኔታ መፍጠር መቻሉ ትልቅ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ይላሉ።

“በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሣሽነት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አሉ። የመደመር መጻሕፍት ተሸጠው ለልጆች መጫወቻና ለወጣቶች መዋያ የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ይሄ የሚያሳየው ከላይ እስከታች ያለው አመራር ለስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው።” ብለዋል። አያይዘውም የባለሀብቱና የኅብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በአዲስ አባባ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በ2012 ዓ.ም ከነበሩበት 840 በ2015 ወደ 945 ለማሳደግ ግብ ተቀመጦ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የኅብረተሰቡንና የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ በማሳደግ በተሠራው ሥራ ወደ 1098 ከፍ በማድረግ የዕቅዱን አፈጻጸም 116 በመቶ በማድረስ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። እነዚህ ማዘወተሪያ ሥፍራዎችም ጥርጊያ ሜዳዎች ፣ጅምናዚየሞች፣ መዋኛ ገንዳዎች ፣ ስቴዲየሞችና ፣ 3በ1 ፣ 2በ1፣ ሜዳ ቴኒስ ሲሆኑ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በከተማ ደረጃ ሁሉም ዜጎች በአካል እና በአእምሮ ጎልብተው ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ በማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንዲሳተፉ የስፖርት ሥልጠናዎችና ውድድሮች በአግባቡ እንዲካሄዱ በማድረግ ለስፖርት መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል።

በ2013 በጀት ዓመት ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን 51 የስፖርት መዘውተሪያ ሥፍራዎችን ግንባታቸውን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርጓል። ከእነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መካከል 45ቱግንባታቸው በ2013 ዓ.ም. የተጀመሩና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር ባደረገው ክትትልና ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ ናቸው። ግንባታቸዉ በ2013ዓ.ም ተጀምሮ በአጭር ጊዜ ከተጠናቀቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መካከል የአፍንጮ በር ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ አንዱ ሲሆን ግንባታው በሦስት ወር ከ15 ቀን የተጠናቀቀ እና የቅርጫት ኳስ፤ የቮሊቦልና የእጅ ኳስ ስፖርት መጫወቻ 3 በ1 ሜዳ፣ የእግር ኳስ ሜዳ እና የቤት ውስጥ ጫዋታዎችን ማጫወት የሚችል አዳራሽ እንዲሁም ካፍቴሪያ ያለው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው። ለግንባታውም 14 ሚሊዮን ብር ከተማ አስተዳደሩ ወጭ አድርጎበታል። የፈረንሳይ ጨፌ ሜዳ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ሌላዉ በከተማ አስተዳደሩ በ3 ወር 15 ቀን ግንባታው የተጠናቀቀ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው። ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ፤ 3 በ 1 ሜዳ፤ የእግር ኳስ ሜዳ እንዲሁም የቤት ውስጥ ስፖርቶች ማወዳደሪያ አዳራሽና የሻወር ቤቶችን አካቶ የተገነባ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው። ለግንባታውም 25 ሚሊዮን ብር ከተማ አስተዳደሩ ፈሰስ አድርጎበታል።

የራስ ኃይሉ ዘመናዊ የውሀ ገንዳ ግንባታው በ2005 ዓ.ም. የተጀመረና በችግር ምክንያት የዘገየ ነበር። የነበረበትን የተለያዩ ችግሮች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን በመለየትና በመፍታት በ2013 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቋል። ለግንባታው በአጠቃላይ አንድ መቶ ዓሥር ሚሊዮን ብር ወጭ ሆኖበታል። የሕፃናት እና የዐዋቂዎች መዋኛ ገንዳን አካቶ የተገነባ ዘመናዊ የውሃ መዋኛ ገንዳ ነው።

በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ብቻ ከ24 በላይ የማዘውተርያ ሥፍራዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የማድረግ ሥራ በመሠራቱ ስፓርቱ መነቃቃትን አግኝቷል። ቢሮው የከተማዋን ነዋሪ ማኅበረሰብ ቁጥር ያማከለና የከተማዋን ስታንዳርድ /ደረጃ/ የሚመጥን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ለማዘጋጀት ያደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በስኬት እንዲጠናቀቅ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ምርቃት የአንበሳውን ድርሻ ይዟል።

በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት በሦስት ወራት ውስጥ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ስታንዳርዶችን የጠበቁ እና ወቅቱን የሚዋጁ ሆነው ተሠርተዋል። 12 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በመደመር ትውልድ የመጽሐፍ ሽያጭ የተገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ 12 ከተማ አስተዳደሩ በመደበው በጀት ግንባታቸው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ናቸው። ማዘውተሪያዎቹ የቅርጫት ኳስ፤ የመረብ ኳስና የእጅ ኳስ ስፖርት መጫዎቻ፣ 3 በ1 ሜዳ፣ የእግር ኳስ ሜዳ እና የቤት ውስጥ ጫዋታዎችን ማጫወት እንዲችሉ ተደርገው የተገነቡ እና አዳራሽ እንዲሁም ካፍቴሪያ አላቸው።

የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሀገር አቀፍ ስታንዳርድ እንዲያሟሉ ለማድረግ በተሠራውም ሥራ 10 ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ደረጃ (ስታንዳርድ) እንዲያሟሉ የተያዘው ዕቅድ ግቡን መቷል። የአበበ ቢቂላ ስቴድየም እና የራስ ኃይሉ መዋኛ ገንዳ ዓለም አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድ) ያሟሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሆኑ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል። የአቃቂ ቃሊቲ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን የመለየት ሥራ ከመሥራት ጎን ለጎን የCAF እና FIFA ስታንዳርድ እንዲያሟላ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ለስታዲየሙ ማስፋፊያ የተጠየቀው ቦታ ተፈቅዶ ግንባታው በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማዕከላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ ለዘመን መጽሔት እንደተናገሩት፤ በሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደታየው የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራዎች በመንግሥት ብቻ ተገንብተው ተደራሽ ማድረግ አይቻልም። ባለሀብቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማልማት እንዲችሉ አንድ ደምብ አዘጋጅተን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ አቅርበን እየታየ ይገኛል። ደምቡ ሲጸድቅ እስከዛሬ ባለሀብቱ ጥያቄ እያቀረበ የሕግ ማሕቀፍ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይስተናገድ የቀረበት ሁኔታ ተቀይሮ የግል ዘርፉ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ ላይ መሠማራት ይችላል። በአለፉት ጥቂት ዓመታት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለማስፋፋት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በዚህ የሕግ ማሕቀፍ ሲደገፍ በአዲስ አባባ ከተማ የፈነጠቀው የስፖርት ማዘወተሪያ ቦታዎች ትንሣኤ ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል።

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You