ኢትዮጵያ በታሪኳ የአሳለፈቻቸው መነሣትም ሆነ መውደቅ በቀጥታ ከባሕር ጋር ይያያዛል። በቀይ ባሕር ላይ በነገሠችባቸው ዘመናት ከአራት በላይ ሰፋፊ ወደቦች ነበሯት። የባሕር በሯና ወደቦቿ በአጎናጸፏት ዕድልም ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ በዓለም በኃያልነታቸው እና በዘመኑ ሥልጣኔ ከሚጠቀሱ ጥቂት አገሮች አንዷ ለመሆን የቻለች አገር ነበረች።
በአንጻሩ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ወደብ አልባ ስትሆነ ደግሞ ከሥልጣኔዋ አሽቆልቁላ፤ ብትናገር የማትደመጥ፣አቅሟ የደበዘዘ፣ ኢኮኖሚዋ የተዳከመ፣ ሰላም የራቃት አገር ለመሆን በቅታለች።
ለመሆኑ በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የኃያልነት መድረክ ወርዳ እንዴት ቁልቁል ልትጓዝና የዓለም ጭራ ልትሆን በቃች? ይህ ጽሑፍ እነዚህንና ሌሎች ተጓዳኝ ሐሳቦችን ይመልሳል። የኢትዮጵያ የገናናነት ምንጭ ከሆነው ከቀይ ባሕር እንጀምር።
ቀይ ባሕር
ቀይ ባሕር ከደቡብ ሶርያ ተነሥቶ በእስራኤልና ዮርዳኖስ የሳይናይ በረሓን አቋርጦ ወደ ቃባ ሰላጤ የሚገባና 2ሺሕ 250 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አካባቢ ነው። ከሕንድ ውቅያኖስ፣ ከኤደን ባሕረ ሰላጤና ከዐረብ ባሕር ጋር ይገናኛል።
ቀይ ባሕር በሜዲትራንያን በኩልም ሆነ በሕንድ ውቅያኖስ የነዳጅ ዘይት ለሚጭኑ መርከቦች ዋና የባሕር መንገድ ነው። በዚሁ ባሕር ላይ በዓመት ከ3ሺሕ በላይ መርከቦች የተለያዩ ዕቃዎችን ጭነው ይመላለሳሉ። በአጠቃላይም ቀይ ባሕር ከአለው ስትራቴጂክ ስፍራነት በተጨማሪ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም የንግድ ልውውጥ በዚሁ ባሕር ላይ እንደሚከናወን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአሁኑ ወቅትም ሳዑዲ ዐረቢያ፣ የመን፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ኤርትራና ጅቡቲ በጋራ የቀይ ባሕር ባለቤቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ከዚህ መድረክ ከተገለለች ከ32 ዓመታት በላይ ተቆጠሩ።
ኢትዮጵያ ለሺሕ ኣመታት የቀይ ባሕር ንግሥት ሆና የኖረች አገር ነበረች። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ‹‹አሰብ የማን ናት? በሚለውና ስለ ቀይ ባሕርና የወደብ ጥያቄ በስፋት በተነተኑበት መጽሐፋቸው እንደአሰፈሩት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች በመጀመርያ የታወቀው ከ100 እስከ 150 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።
‹‹ዘ ፐሪፕለስ ኦቭ ዘ ኤርትሪያን ሲ›› በተሰኘው መጽሐፍም የአክሱም መጠነ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ዋነኛ የባሕር በር በነበረው በአዶሊስ ይተላለፍ እንደነበር ያትታል። በወቅቱ የነበረው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ካሌብ እጅግ የዳበረ የባሕር ኃይል እንደነበረውና ቀይ ባሕርንም ተሻግሮ የመንንና ደቡብ ዐረቢያን ይቆጣጠር እንደነበር ይኸው መጽሐፍ ያብራራል።
ጥንታዊው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በሁሉም ዘርፎች ላይ አስደናቂ ለውጥ የታየበት ስለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱት ሐቅ ነው። እነዚህ የአልተቋረጡ የታሪክ አካኼዶች ደግሞ ዛሬም ድረስ የአልደበዘዙ የታሪክ ዐሻራዎች ናቸው። እነዚህ ነባራዊ ሐቆችም ኢትዮጵያን በዓለማች ላይ ከሚገኙ ጥንታዊና የአልተቋረጠ የሥነ መንግሥት ታሪክ ከአላቸው አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።
በተለይም በኢዛና እና በካሌብ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በነበራት ከወርቅ፣ ከብርና ከነሐስ በተሠሩ መገበያያ ገንዘቦች በቀይ ባሕር ላይ እጅግ ብዙ የጦርና የንግድ መርከቦችን ታንቀሳቅስ ነበር። በእነዚያ ከፍተኛ ቁጥር የአላቸው የጦርና የንግድ መርከቦች በመታገዝ ከደቡብ ዐረብ አገሮች እስከ ሕንድ ውቂያኖስና የአሁኗ ቻይና ድረስ በሰፊው የተዘረጋ የግንኙነት መሥመር ነበራት። በዚህ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ በሆነው የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የዲፕሎማሲና የመንግሥታት ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ታካኺድ እንደነበረ ከጥንት ሥልጣኔዋ የከፍታ ልኬት አንጻር የተሰነዱ ነባራዊ የታሪክ ድርሳናት አስረጂዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት ታስተዳድረው በነበረው የቀይ ባሕርና የባሕር በሮቿ ግዛቶችም ከላይ ከተጠቀሱት አገሮች ጋር የዝኆን ጥርስ፣ የቅመማ ቅመም ምርቶችን፣ የሙጫ ተክሎችን እንዲሁም ሌሎች ወጪና ገቢ ሸቀጦችን፣ አልባሳት፣ ሽቶና ጌጣጌጦችን በመላክና ወደአገር ውስጥ በማስገባት የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴ ታካኺድ እንደነበርም ታሪክ ይነግረናል።
ቀይ ባሕርን በሰፊው ትናኝበት በነበረበት ጊዜ ከየመን እስከ ሕንድ፣ ከሶሪያ እስከ እስራኤል፣ ከሳኡዲ ዐረቢያ እስከ ግብጽ፣ ከቻይና እስከ አውሮፓና ኢዤያ ድረስ ጠንካራ የመንግሥታት ግንኙነትን ፈጥራ ቆይታለች። በዚህ የተነሣም የልዕለ ኃያልነት አስፈሪነቷን ለዓመታት እንደቆየችበት የአገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው እውነት ነው።
ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹‹አደጋ የአንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ›› በሚለው መጽሐፋቸው የሚከተለውን አስፍረዋል። ‹‹ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ዘመን በመርከቦቿ ከሕንድ እስከ ኢየሩሳሌም ከነበሩ አጋሮቿ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበራት። አንዳንዴም ጭቆና የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት የጦር ኃይል በመላክ ሁኔታዎችን ትቆጣጠር ነበር።›› ሲሉ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ እንደነበረ ያትታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለረዥም ዘመን የአገለገሉት ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካርያ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን የንግድ እንቅስቃሴ በመቆጣጠሯ ምክንያት በወቅቱ የአክሱም ሥልጣኔ እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል። በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩት ሥልጣኔዎች አንዱ ሆኖ ለመውጣቱም ምክንያቱ የባሕሩ ንግድ ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሥልጣኔና ገናናነት ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው።
ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር የማግለል ሴራዎች ከድሮ እስከ ዘንድሮ
ከአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ የቀይ ባሕር አካባቢ ትኩረት የአገኘ ስፍራ ነው። በየዘመናቱ የነበሩ ኃያላን ቀይ ባሕርን ሳይዙ ኃያልነታቸውን ማረጋገጥ የሚታሰብ አልነበረም።
ቀይ ባሕር በተለይ ከስዊዝ ካናል መከፈት ጋር ተያይዞ የዓለም የንግድ ኮሪደር ለመሆን ችሏል። ቀይ ባሕርን የመቆጣጠር ፍላጎት የዓለም ኃያላን አገሮች ሁሉ ምኞት ነው። እነዚህ አገሮች ኢትዮጵያ እንዳትቀናቀናቸው በየዘመናቱ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ከአካባቢው እንድትርቅ አድርገዋታል።
ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካርያ እንደሚገልጹትም፤ በተለይ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ መቀየር፣ በራሷ በአገሪቱም የመሪዎች መለዋወጥ ምክንያት አገሪቱን ከአለ ወደብ በሚያስቀር ውል ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሆነ። ይህ መሆኑ ደግሞ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች በመቀያየር አገሪቱን ወደብ አልባ ከማድረጉም ባሻገር ከቀይ ባሕርና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቷ ውጪ እንድትሆን አስገድዷታል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር በመሆኗ በወጪ ገቢ ምርቷ ላይ የሌላ አገር ጥገኛ እንድትሆን አስገድዷታል። ይህም ለራሷ ታውለው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማቀጨጭ በኢኮኖሚዋ ላይ ዕድገት እንዳይመዘገብ የፊጥኝ አስሯታል። ከቀይ ባሕር በ 60 ኪሎ ሜትርና ከሕንድ ውቂያኖስ በ ሁለት መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም፤ እነዚህን አካባቢዎች ተጠቅማ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳታደርግ የማግለል ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
‹‹በተለይም ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የሚባለው ግብጻዊ የተባበሩት መንግሥታትን ለአራት ዓመት በመራበት ወቅት ኤርትራም ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ትልቅ ሚናን የተወጣ ነው። እኔም በወቅቱ አብሬያቸው ስለነበርኩ ስለሁኔታው በደንብ ዐውቃለሁ። ይኽንን ተግባሩን ለመፈጸምም ከጅቡቲ እስከ ሱዳን ድረስ በጀት አስሶ አዲስ በምትወለደው የዐረብ ሊግ ላይ ኤርትራን አባል ማድረግ አለብን በማለት ብዙ ሠርቷል።›› ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካርያ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ‹‹አሰብ የማናት?›› በሚለው መጽሐፋቸው፤ ግሬጎሬ ኮፕሌይ የተባለ የአፍሪካ ኤክስፐርት ጋዜጠኛን ጠቅሰው የሚከተለውን አስፍረዋል።
‹‹የግብጽ የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ ፖሊሲ ኢትዮጵያ በአካባቢው የበላይነት እንዳይኖራት ከባሕሩ ዙርያ ማግለል ነው። ግብጽ የኤርትራ ነጻ አውጪዎችን በመርዳት እና የቀይ ባሕርን ደቡብ ክፍል ከኢትዮጵያ እጅ በማውጣት ኤርትራ ነጻ እንድትወጣና ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር አካባቢ ተገልላ በተፈጥሮም ሆነ በባህል መቼም የኤርትራ አካል ሆና የማታውቀው አሰብን እንድታጣ አደረገቻት››
አቶ ሀብተ ሥላሴ የተባሉ ምሁር፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት፣ ኢኮኖሚያዊ ልማትና እንቆቅልሾቹ›› በሚል መጽሐፋቸው ወስጥ የሚከተለውን አስፍረዋል።
‹‹ሕውሐት ሥልጣን ላይ ቂብ እንዳለ የመጀመርያ ሥራው አድርጎ የወሰደው ለኤርትራ መገንጠል ሕጋዊ ዕውቅና መስጠት ነበር። ይህ አቋም ሲፈጸም የኢትዮጵያ ሕዝብን አቋም ሳያካትት ነበር። የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ በነበረው ሄርማን ኮህን ሊቀመንበርነት በ1983 ዓ.ም. ለንደን ላይ ‹‹የለንደን የሰላም ጉባኤ ›› ተካኺዶ ነበር። ምንም እንኳን አቶ ኮህን ኢትዮጵያን ለሕውሐት አሳልፎ በመስጠቱ ቢወቀስም በስብሰባው ሒደት ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋትና አሰብን እንድትወስድ የሻዕቢያን መሪ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂን ጠይቀው ነበር። በሚያስገርም መልኩ በጊዜው ሕወሐትን ወክሎ የቀረበው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጉዳዩን ሳይቀበለው ቀርቷል።›› ሲሉ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትን ምክንያት ያስረዳሉ።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አማረ ቀናው እንደሚሉት፤ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ስለወደብ ማውራት የተወገዘ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ስለወደብ የሚያነሡ ሰዎች እንደጸብ ጫሪና ጦርነት ናፋቂ እየተቆጠሩ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ ላይ ያላት መብት ተድበስብሶ እንዲቀር ተደርጓል። በዚሁ የልብ ልብ የተሰማቸውም የዐረብ እና የቀጠናው ሀገሮች ኢትዮጵያን ከነጭራሹ ከአካባቢው ገሸሽ የሚያደርጉ ስምነቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የቀይ ባሕር ጥምረት (Red sea Alliaince) ወይም ደግሞ የጂቡቲ የሥነ ምግባር ደንብ (Code of conduct) እና የቀይ ባሕር ደኅንነት ተለዋዋጭነት መድረክ (Red sea security dynamics forum) ኢትዮጵያን የአገለሉ ስምምነቶች ተመሥርተዋል።
በተለይም ኢትዮጵያንና እስራኤልን የአገለለ የቀይ ባሕር ደኅንነት ተለዋዋጭነት መድረክ (Red sea security dynamics forum) ተመሥርቷል። ይህ መድረክ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ትስስር የካደና ከነጭራሹም የዘነጋ ነው። ይህ እና ሌሎች ከላይ የተፈረሙት ስምምነቶች ኢትዮጵያውያን በቀይ ባሕር ላይ የአላቸውን መብቶች በአንድነት ለማስከበር እስከአልተነሡ ድረስ አገሪቱን ከቀይ ባሕር የማራቁ ጉዳይ የበለጠ እየተጠናከረ እንደሚሄድ አመላካች ነው፤ ሲሉ ሁኔታውን ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ መሪዎችና የባሕር በር ጥያቄ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ በዝርዝር የጻፉት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም እንደሚተነትኑት፤ በዘመነ መሳፍንት ማዕከላዊ መንግሥት ከመዳከሙ ቀደም ብሎ በዐፄ ፋሲል ሞትና በዐፄ በካፋ መንገሥ መካከል ለ65 ዓመታት የኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ይዞታ እየተዳከመ ቢሔድም በዐፄ በካፋ፣ በዐፄ ኢያሱ ሁለተኛ፣ በዐፄ ኢዮአስ እስከ 1769 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጠረፍ የተጠናከረ ይዞታ እንደነበራት ታሪክ ይገልጻል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከ1769 ዓ.ም. በኋላ የተለያዩ ሴራዎች እየተሠሩባት በቱርኮች፣ በግብጾች፣ በጣልያኖችና በፈረንሳዮች አማካኝነት የሰሜን ግዛቶቿ እና የባሕር ጠረፎቿን የምታጣበት ሁኔታ ተፈጠረ። ዐፄ ቴድሮስ፣ ዐፄ ዮሐንስ፣ ዐፄ ምኒልክ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሁሉም የባሕር በር የማስመለስ ጉዳይን በውጪ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ግዙፍ እና ቀዳሚ ጉዳይ አድርገው ብዙ ጥረት ሲያደርጉ እና ተግተው ሲሠሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ዋቢ ናቸው።
ዐፄ ቴዎድሮስ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 20 ቀን 1855 ለእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር።
‹‹ቱርኮች የአባቶቼን መሬት ልቀቁ ብላቸው እምቢ ብለውኝ በእግዚአብሔር ኃይል ይኸው ልታገለው ነው። ቱርኮች በባሕር ላይ ሆነው መልእክተኛዩን አላሳልፍም ብለው ችግር ፈጥረውብኛል›› ሲሉ ቱርኮችን ከቀይ ባሕር ለማስወጣት መወሰናቸውንና የእንግሊዝ መንግሥትም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያሳይ ደብዳቤ በሰነድ መልክ ይገኛል።
በተመሳሳይም ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ቀይ ባሕርን ከወራሪዎች ለማስለቀቅ ብዙ ደክመዋል። ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ኢትዮጵያ በቱርኮች፣ በግብጾች፣ በጣልያንና በእንግሊዝ ሴራ ከአክሱም ነገሥታት ጀምሮ የነበሯትን የባሕር በሮች ተነጥቃ ሙሉ ለሙሉ ወደብ አልባ የሆነችበት ጊዜ ነበር። ዐፄ ዮሐንስም የተነጠቁትን የባሕር በርና ወደቦች ለማስመለስ ጠንካራ ትግል ያደርጉ ነበር።
ሰኔ 10 ቀን 1872 ለእንግሊዝ ንግስት ቪክቶርያ በጻፉት ደብዳቤም ምጽዋን ለማስመለስ በሚያደርጉት ጦርነት እንዲያግዟቸው መልእክት ልከው ነበር።
‹‹የምጽዋ በር የአባቶቼ የነገሥታት ኢትዮጵያውያን ነው። አሁንም እንበለ በር ቤተ መንግሥት አይቀርምና በእርስዎ ወኪልነት ርዳታ የምጽዋን በር እንድይዝ ያድርጉልኝ ብዬ አምናለሁ።››
ዐፄ ሚኒልክም እንዲሁ የኢትዮጵያን የባሕር በር ለማስጠበቅ ብዙ ደክመዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ስትገለገልበት የነበረውን የዘይላን ወደብ ለማስመለስ በሚያደርጉት ትግል የጣልያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ እንዲያግዛቸው በ1876 ዓ.ም. ደብዳቤ ጽፈው ነበር።
‹‹የዘይላን በር ነገር በሚቻልዎ ነገር ሁሉ ተጣጥረው በእኔ እጅ ቢሆን እንኳን በሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በከንባታ፣ በጅማና በከፋ ያለውን ንግድ ሁሉ በዘይላ አደርገው ነበር። ስለዚህ ጠንቅቀው ቢያስለቅቁልኝ እወዳለሁ…. ››
በዐፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን የዓለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ምሁር በሆኑት ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ እና ሌሎችም በአደረጉት ጥረት በ1952 ዓ.ም. በኤርትራ ሕዝብ ተወካዮች ፍላጎትና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቀለች። ለዘመናት ትግል ሲደረግበት የቆየው የባሕር በር ጥያቄ ከአንድም ሁለት የምፅዋ እና የአሰብ የባሕር በር ባለቤት እንትሆን ማድረግ ተቻለ።
በሒደት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች። ነገር ግን የፌዴሬሽኑ መፍረስ ሻቢያ እና ጀበሃን በኋም ሕውሐትን የመሳሰሉ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ድርጅቶች ተፈጠሩ። በመጨረሻም በድጋሚ ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት የባሕር ጠረፍ አልባ እስረኛ አገር ሆነች።
ከብዙ ወደብ ባለቤትነት ወደ ወደብ አልባነት
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ነግሣ በቆየችባቸው ወቅቶች የበርካታ ወደቦች ባለቤት ነበረች። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኛነት አዶሊስ፣ ምጽዋ፣ አሰብ፣ ዘይላ ተጠቃሾች ናቸው።
ዘይላ ሶማሊያ እንደአገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነበረ። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች።
አሰብ፤ ምጽዋ እና አዶሊስ ኢትዮጵያ በብቸኛነት ስትጠቀምባቸው የነበሩና ኤርትራ ስትገነጠል አብረው የሄዱ ናቸው። በተለይም አሰብ ኢትዮጵያዊ አፋሮችን ጨምሮ ከነወደቡ ኢፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ተላልፈው የተሰጡ የኢትዮጵያ ሃብቶች ናቸው። ይህ ኢፍትሐዊ ውሳኔም ባለብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረችውን አገር ከነጭራሹ ወደብ አልባ አድርጎ አስቀርቷታል።
የባሕር በር ወይም ወደብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ከአራት በላይ ወደቦች አሏት። ይኽች ትንሽ አገር ተፈላጊነቷም ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ እንዲሁም ከአሜሪካ እስከ እስያ ድረስ ደርሷል። የተወሰኑ አገሮች ቻይናን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በዚች ትንሽ አገር ወታደራዊ ቤዝ ገንብተዋል። እነዚህ አገሮች ወደዚች ትንሽ አገር መጥተው ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራቸው ከአስፈለጓቸው ምክንያቶች መካከል የአካባቢው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነም ባለሙያዎች ያብራራሉ ።
በሌላ በኩልም ሳዑዲ ዓረቢያ ከአሰብ ወደብ ከፊሉን ከኤርትራ በሊዝ ገዝታ ለብዙ ዓመታት ለማስተዳደር ፈቃድ አግኝታለች። በአሁኑ ወቅት የአሰብና የምፅዋ ወደቦች የዐረብ አገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ሲሄዱና ወታደራዊ ሠፈር ሲያቋቁሙ ታይቷል። የእነዚህ ወደቦች ታሪካዊ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ወደብ አልባ ሆና የበይ ተመልካች ሆና ቀርታለች።
ወደብ አልባነትና የአለፉት 32 ዓመታት አገራዊ ሸክሞች
በኢትዮጵያና በዐማፅያን መካከል የነበረው የ17 ዓመታቱ ጦርነት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ለዘመናት ትገለገልበት ከነበረው የቀይ ባሕር ይዞታዋ ተነቀለች። ወደብ አልባ አገርም ሆነች።
ባለፉት 32 ዓመታትም ወደብ አልባ አገር ሆና እና ከአክሱም ዘመነ መንገሥት ጀምሮ ይዞታዋ ከነበረው ከቀይ ባሕር ተገልላ ኖራለች። በዚህም ወደብ አልባ አገሮች የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመጋፈጥ ተገዳለች። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ፈተናዎች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የመጀመርያው ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ‹‹አሰብ የማን ናት?›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደአሰፈሩት፤ እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆኑ አገሮች ከዋና ዋና የገበያ ማዕከሎች የተገለሉና ከገበያ ማዕከል የራቁ ሲሆኑ ወደብ አልባነት ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ከፍተኛ ማነቆ ሆኖባቸዋል።
ዶክተር ያዕቆብ፤ ቻውድሪና ኤርዳነቢልግ የተባሉ ምሁር የአደረጉትን ጥናት ጠቅሰው እንደጻፉት፤ ወደብ አልባና ወደብ ያለው በሁሉም ነገር ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት አገሮች በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ሲነጻጸሩ፤ ወደብ አልባው አገር 1 በመቶ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ኋላ ይቀራል። ይህም ማለት ወደብ ያለው አገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 24 ዓመታትን ሲፈጅበት፤ ወደብ አልባው አገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 36 ዓመታት ይፈጅበታል። በሌላም በኩል ወደብ አልባ መሆን ብቻ የአንድ አገር የውጭ ንግድ መጠንን ከ33 በመቶ እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል።
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪም ሆነ የእርሻ ውጤቶች የሚመረቱት ከወደብ በራቀ አካባቢ በአብዛኛው በመሐሉና በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ስለሆነ እነዚህን ምርቶች ወደ ወደቡ ለማዝለቅ ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ስለሆነም ከባድ ዕቃ ለማምረት ለሚፈልግ ኢንቬስተር ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ምርጫ ልትሆን አትችልም።
በዓለም የበለጸጉ ጥቂት ወደብ አልባ ሀገሮች እንዳሉ ይታወቃል። በእነዚህ አካባቢ ያሉ ሰፋፊ ገበያና የዳበረ ኢኮኖሚን በመጠቀም የወደብ አገልገሎት አለመኖር የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ችለዋል። ሆኖም ወደብ አልባ ሆኖ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻለ አንድም አገር እንደሌለ ዶክተር ያዕቆብ ገልጸዋል።
በአገር ደረጃ ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ ወደብ አልባነት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቀን ተቀን ኑሮ ጋር ቁርኝት አለው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለተከሠተውና በየቀኑ እንደ ሮኬት ለሚወነጨፈው የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት የወደብ አለመኖር ነው። በየጊዜው በወደብ ላይ የሚጣለው ታሪፍና ቀረጥ መናር ወደ አገር ውስጥ የሚገባውንና የሚወጣውን ሸቀጥ ዋጋ እንዲንር እያደረገው ይገኛል። በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ በምትጠቀምበት የታጁራ ወደብ ላይ በአንድ ቅጽበት እስከ 25 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስለ ቀይ ባሕርና ስለ ወደብ አስፈላጊነት በሰጡት ማብራርያም ወደብ የሌላቸው አገሮች ዓመታዊ ዕድገታቸው በ 25 በመቶ የተገታ መሆኑን አስረግጠው መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ፖል ኮሊየር የተባሉ ምሁር እንዳሉትም፤ ወደብ አልባ አገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች በአብዛኛው በአንድና ሁለት ምርቶች ላይ ብቻ የተወሰኑ ናቸው። ስለሆነም ከድህነት የመላቀቅ ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። የውጭ ባለሃብቶችም አይመርጧቸውም። በወደብ ኪራይ እና በትራንስፖርት ምልልስ ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳረጉም ለሸቀጦች ዋጋ መናርና ለኑሮ ውድነት የተጋለጡ ናቸው።
የባሕር በር ያለው አገር ከዓለም ጋር ይገበያያል። ወደብ የሌለው አገር ግብይቱ ከጎረቤቱ ጋር ብቻ ነው፤ ሲሉም ፖል ኮሊየር ይገልጻሉ። ስለዚህም ወደብ አልባ አገሮች የጎረቤቶቻቸው እስረኞች ናቸው፤ ሲሉም ጽፈዋል።
በአጠቃላይ የባሕር በር አለመኖር ለኢኮኖሚና ለልማት ዋነኛ ዕንቅፋት መሆኑን ሁሉም ምሁራን ይስማሙበታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮም በየቀኑ ለወደብ ኪራይ ከ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ (በዚያን ጊዜ ስሌት) እንደምታወጣ ዶክተር ያዕቆብ ያስረዳሉ። ይህንኑ ሐቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ለወደብ ኪራይ የሚወጣው ወጪ በርካታ የሕዳሴ ግድቦችን ለመገንባት ያስችለን ነበር፤ ሲሉ በቁጭት መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የወደብ አልባነት ጉዳት ደግሞ ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያያዝ ነው። ወደብ የአላቸውና የሌላቸው አገሮች እኩል ተደማጭነት አይኖራቸውም። ኢትዮጵያም ከቀይ ባሕር ከተወገደች ጀምሮ በዓለም ላይ ያላት ተሰማኒት እየተቀዛቀዘ እንደመጣና በምትኩ ጅቡቲን የመሳሰሉ ትንንሽ አገሮች የበለጠ ተሰሚነትን እያገኙ መምጣታቸውን ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ያስረዳሉ።
ሦስተኛው ችግር ደግሞ፤ ወደብ አልባ አገሮች የሚገጥማቸው የሉዓላዊነት ፈተና ነው። ወደብ አልባ አገሮች ራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ይቸገራሉ። የራሳቸውም ምስጢር አይኖራቸውም። ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር የቀይ ባሕርና ወደብ ጉዳይን በተመለከተ ቆይታ የአደረጉት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዶክተር ዳር እስከ ዳር ታዩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ከአጣችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዋጋ ከፍላለች።
በየዓመቱ ለወደብ ከምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ ለአገር ስትራቴጂክ የሆኑ ዕቃዎችን ለማስገባት ስትፈልግ የግድ ወደብ የሚያከራየው አገር ማወቅና መፍቀድ አለበት። ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ አገር ምስጢር ነው ብላ የምትደብቀው ነገር አይኖራትም ማለት ነው። እንደ አገር የምትይዛቸው ምስጢሮቿ ሁሉ በወደብ ሰጪው አገር ዕውቅና ውስጥ የሚያልፉ ናቸው፤ ብለዋል።
ለምሳሌ አስፈላጊ የጦር መሣሪያዎች ኢትዮጵያ ማስገባት ብትፈልግ ከወደቡ ባለቤት ዕውቅና ማግኘት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ጉዳቱ ከኢኮኖሚ እስከ ሉዓላዊነት ድረስ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፤ ሲሉ ጉዳቱን አብራርተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ እና በየጊዜው እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት አገር እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተሸክሞ እንደአገር ለመቀጠል ትቸገራለች። ልቀጥል ብትልም አትችልም። ባለፉት 30 ዓመታት ስትጓዝበት በነበረው ሁኔታ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መኖር ከማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ስለዚህም መፍትሔ መፈለጉ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አልሆነም። ስለዚህም መፍትሔው ምንድነው? የሚለው ጉዳይም ሁሉንም የሚያሳስብ ጥያቄ መሆ ን ጀምሯል።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና በአጠቃላይ 8 አገሮች አሉ። እነዚህ አገሮችም በሚጠቅማቸውቅና በሚያዋጣቸአው አካሄድ ላይ እየተመካከሩ ያለውን ቸግር ለመፍታት በቂ ዕውቀትም ችሎታም ያላቸው ናቸው። ኢጋድ መጀመሪያ ሲቋቋም ዓላማው ረኃብንና ድርቅን መቋቋም ነበር። ነገር ገን ይህም ሌላኛው ድርቅ በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብታችንን አብረን የምናለማበትን የምንጠቀምበት ሁኔታ ሊመቻች ስለሚገባው ይህንንም አብሮ ማየት ሳያስፈልግ አይቀርም።
ኢትዮጵያም ለጎረቤቶቿ በሙሉ ውሃ ታቀብላለችና ይህንን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ሂደቷን ደግሞ በባሕር ወደቡ በኩልም በማምጣት ከጎረቤቶቿ ጋር ተስማምታ መጠቀምን ማስቀደም ይገባታል።
የለውጡ መንግሥት እና የወደብ አማራጭ ትልሞች
ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፤ ‹‹አሰብ የማናት?›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ከ13 ዓመታት በፊት አንድ ትንቢት የሚመስል ሐሳብ አስፍረው ነበር። ‹‹ኢሕአዴግ የአሰብን ጉዳይ ማንሣት ባይፈልግም ከኢሕአዴግ ቀጥሎ የሚመጣው መንግሥት ይህንን ጥያቄ እንደሚያነሣና ኢሕአዴግንም እንደሚወቅስ አምናለሁ።›› ሲሉ የዛሬውን አገራዊ ሁኔታ አስቀድመው ተንብየው ነበር።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስለቀይ ባሕር እና የወደብ ጉዳይ ገለጻ በማድረግ ኢትዮጵያውያን እንደገና ፊታቸውን ወደ ቀይ ባሕር እንዲያዞሩ ሐሳብ ፈንጥቀዋል። አይነኬ የሚመስለው የቀይ ባሕር እና ወደብ ጉዳይ ቢያንስ የውይይት አጀንዳ እንዲሆን በር ከፍተዋል።
በ2030 ዓ.ም. 150 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በጂኦግራፊ ታሳሪ ሆኖ መኖር የማይችል በመሆኑ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውሃን የማይወስድ ጎረቤት አገር አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ኤርትራ ተከዜን፣ ሱዳን ተከዜን እና ዓባይን፣ ደቡብ ሱዳን ባሮን፣ ኬንያ ኦሞን ጨምሮ፣ ሶማሊያ ዋቢ ሸበሌ እና ገናሌ ዳዋ ወንዞችን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በቀይ ባሕር ጉዳይ የማንወያይ ከሆነ በስንዴም፣ በአረንጓዴ ዐሻራም፣ በገቢው ጉዳይ መወያየት ትርጉም የለውም። እንደ አገር የሚታሰበውን ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና በቀይ ባሕር ምክንያት የሚታጣ ከሆነ ዋጋ እንደሌለው ገልጸዋል።
‹‹ለኢትዮጵያ አንድ ሊትር ውሃ የሚሰጥ አገር የለም። ሁሉም ተቀባይ ነው፤ ይገባቸዋል በደንብ አብዝተን እንሰጣቸዋለን። ግን የእናንተን እንካፈል የእኛን እንዳትጠይቁን ማለት ግን ትክክል አይደለም›› ብለዋል። አብሮ መኖርና ሰላም ከታሰበ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ በመጋራት መኖር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ከአንዱ ወገን ብቻ የሚጠየቅ ከሆነ ፍትሐዊነት የጎደለው ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።
ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት፤ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ከአካባቢው አገሮች ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር እና ፍላጎትን ማጣጣም ከተቻለ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ አማራጮችም አሉ። ወቅቱ የሚጠይቀውም ይህንኑ ትብብር ነው።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት መሪ ተመራማሪና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ዶክተር አማረ ቀናው እንደተናገሩት፤ የባሕር በር ለማግኘት በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል። አንደኛው ሙሉ በሙሉ ከባሕር ጋር የሚያገናኘው ወደብ በባለቤትነት ወይም የራስ የሆነ መሬት ማግኘት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የባሕር በር ተጠቅሞ የአንድን አገር ብሔራዊ ጥቅም ማስጠቅ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ናቸው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ወደብ የላትም። እየተገለገለች የምትገኘው የሌሎችን ወደብ ተከራይታ ነው። በዚህ መልኩ መቀጠል የሚያስከፍለው መሥዋዕትነት ብዙ ነው። ከዚህም የተነሣ አሁን ጉዳዩ ተነሥቷል። ጥያቄው ቀድሞም ቢሆን ተዳፍኖ በእያንዳንዱ ልብ የተቀመጠ ነው፤ ሲሉ ዶክተሩ ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር አማረ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የምትችለው በቀጣናዊ ትብብር ነው። ለዚህ ደግሞ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀትና በጉዳዮች ላይ መነጋገር መልካም ነው። በተለይም ተፈጥሯዊ የሆነው ይህን ሀብት በእኩልነት እንዴት ማስተዳደር እንችላለን? የሚለውን ለማጠናከር ቀጣናዊ ትብብሮችን በአግባቡ ማጠናከር አስፈላጊ ነው።
ለዚህም ኢትዮጵያ ሰሞኑን ቀይ ባሕርን እና ወደብን አስመልክቶ የመጀመርያውን ምክክር መድረክ አዘጋጅታለች። አይነኬ ይመስል ስለነበረው የባሕርና ወደብ ጉዳይ የምሥራቀ አፍሪካ ሀገሮች ጭምር በተገኙበት ግልጽ ውይይት ማድረግ መጀመሩን ዶክተር አማረ ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ እና የኢስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ዳር እስከ ዳር ታዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ ጋር ተያይዞ የባሕር በር ያስፈልጋታል፤ ይላሉ። ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችልም ይናገራሉ።፡
እርሳቸው እንደሚያብራሩትም፤ ኢትዮጵያ ከአለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና ዘልቃለች። ይህ ከነበረው የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር ብዙም ተጽዕኖ ሳያመጣ ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል። አሁን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጨምሯል። ኢኮኖሚዋም በምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ፊተኛውን መሥመር ይዟል። ስለዚህም አሁን ከአለውና በቀጣይ ከሚኖረውም ግዙፍ ኢኮኖሚ አንጻር አንድ ወደብ ብቻ ገቢና ወጪ ዕቃዎችን ሊያስተናግድ አይችልም።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል ሲባል ብዙዎች ጉዳዩን ከጦርነት ጋር ያያይዙታል የሚሉት ዶክተር ዳርእስከዳር፤ እንደዚያ ማሰቡ አግባብነት የሌለው መሆኑን ያመለክታሉ። አማራጮቹ በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ለአብነት ያህል በኪራይ ተጨማሪ ወደቦችን ማግኘት አሊያም ወደብ በጋራ ማልማት ወይም ደግሞ የአካባቢ ልውውጥ በማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ካሉ ልማቶች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት እና በምትኩ ወደብ በማግኘት ማካካስ ይቻላል፤ ሲሉም ይገልጻሉ። እንዲያም ሲባል ከሕዳሴ ግድብ ተርባይኖች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት በምትኩ ወደብ ማግኘት ተጠቃሽ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለአብነትም ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገልግል የሚችል አይደለም። ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች በሚል በርካታ አማራጮች እንዳሉ ዶክተር ዳር እስከ ዳር ያመለክታሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከአሏት የወደብ አማራጮች መካከል በተለይም በቀዳሚነት የአስቀመጡት ዘይላን ሲሆን፤ ዘይላ ወደብ በሶማሌ ላንድ ግዛት በምዕራባዊ አውደል ግዛት ውስጥ የሚገኝ እና የኤደን ባሕረ ሰላጤን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል። በሁለተኛ አማራጭ ነው ያሉት የጂቡቲ ወደብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ የሚገኘው የአዱሊስ ወደብንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውንና የሚያመቻትን የወድብ አማራጮችን ብቻ አልዘረዘሩም። በምትኩ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደብን ለማግኘት በምላሹ ከሕዳሴ ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላትም አብራርተዋል።
ዶክተር ዳር እስከ ዳር ታዬ በአሁኑ ወቅት የቀይ ባሕርና የወደብ ጉዳይ መነሣቱ ወቅታዊ ከመሆኑም ባሻገር የለውጡ መንግሥት አንዱ ገጸ በረከት መሆኑን ያስረዳሉ።
የለውጡ መንግሥት ሠራቸው ብዬ ከማስባቸው ታላላቅ አገራዊ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ተሰሚነት ለማስመለስ እያደረገው ያለው ጥረትን ነው። ኢትዮጵያ ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ተደርጋለች። ይህ ደግሞ እንደ አገር የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ነው።
የለውጡ መንግሥት ይኽንኑ በመረዳት አይነኬ የሚመስለውን የቀይ ባሕር ፖለቲካን ቢያንስ በአሁን ደረጃ የመወያያ አጀንዳ ማድረግ ችሏል። ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠንም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለሷ አይቀርም። ከአምስት ዓመታት በፊት እኮ ስለ ባሕር በር ማውራት እንደተስፋፊነት እና ጠብ ጫሪነት ነበር የሚቆጠረው። ስለቀይ ባሕር ማውራት ራስን ለጦርነት እንደማዘጋጀት፤ ጦርነትን እንደመቆስቆስ ነበር የሚታሰበው።
ዘይላ ሶማሊያ እንደአገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም አገሮች አሸናፊ መሆን ይችላሉ።
በተመሳሳይም ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው መልካም የሰላም አጋጣሚ የአሰብን ወደብ በሰላማዊ አማራጭ ለመጠቀም ውይይት ማድረግ ይቻላል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው አቅርቦቶች ይኖራሉ፤ እነሱን በመስጠት አሰብን መጠቀም ይቻላል።
ወደ ሶማሌ ላንድ ስንመጣ የበርበራ ወደብን በጋራ ማልማትና መጠቀም ይቻላል። ከዚህ ቀደም የኢምሬት መንግሥት 51 በመቶ፣ የሶማሊ ላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግሥት 19 በመቶ ድርሻ ወደቡን በጋራ የማልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችል ነው።
በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ማደግ ለጎረቤት አገሮች ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ሲመጣ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል። ጎረቤት አገሮችም ወደቦችን በማከራየት፣ በጋራ በማልማት ወይም ከኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በእጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባሕር እና ስለ ወደብ ኣታንሣ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም።
ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል። ወደብ ለማግኘትም በርካታ አማራጮች አሏት። በእነዚህ አማራጮች ላይ ግን መነጋገር፣ መወያየትና መግባባት ያስፈልጋል። መፍትሔው ቀጣናዊ ትብብር ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በእኩልነት እንዴት ማስተዳደር እንችላለን? የሚለውን ለማጠናከር ትብብርን በአግባቡ ማጠናከር አስፈላጊ ነው።
በተለይም ዶክተር አማረ እንደሚሉት፤ የትብብር ማሕቀፎችን ዲዛይን ማድረግ ያስፈልጋል። ተጠቃሚነትም መኖር አለበት። ጉዳዩ ገና ሲነሣ ‹‹ውሃችንን ልትወስዱ ነው›› ከመባባል በአለፈ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ማጠናከር አለብን? በሚለው ላይ መወያየት መልካም ነው።
የጋራ ተጠቃሚነት ከሌለ ግጭቶች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ ከቀጣናው ውጭ ያሉትን አካላት ተጠቃሚ ያደርጋል። በውክልናም በመግባት መንግሥት እስከመመሥረት ያደርሳል። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጣር ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው። ከማጠናከር አኳያ ሲታይ ደግሞ ከዚህ በፊት ጠንካራ ሚና ስትጫወት የነበረች ኢትዮጵያ ተነሣሽነቱን ወስዳ ቀጣናዊ ትስስሩ እንዲጎለብት የማድረግ ብቃት ያላት ናት ይላሉ።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የመጀመሪያው የቀይ ባሕር የትብብር መድረክ ነው። ቀጣዩ ኢትዮጵያ ውስጥ አሊያም የተባበሩት ዐረብ ኢመሬቶች ውስጥ አሊያም እስራኤል ወይም ደግሞ ሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ ሊካኼድ ይችላል። ዋናው ነገር ግን ጀማሪዎቹ እኛ ነን። ተነሣሽነቱን ወስደናል፤ መድረኩ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ፖሊሲ አውጪዎች ላይ ጫና ማድረግ አለብን። ወደ ጋራ ተጠቃሚነትና ወደ ጋራ ድል የሚወስደውን መንገድ ለመጓዝ እንሞክራለን።
ለዓመታት ተዳፍኖ የቆየው የባሕር በርና ወደብ ጉዳይ መነሣት መጀመሩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ስሜት መፍጠር ጀምሯል። ከዚህ አልፎም አንዳንድ የውጭ ምሁራንና ፖለቲከኞች ጭምር ኢትዮጵያ የአነሣችውን የፍትሐዊነት ጥያቄ መደገፍ ጀምረዋል። ሰሞኑን አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ ሊያዩት እንደሚገባ መናገራቸው የዚሁ እሳቤ አንዱ መሳያ ነው።
ሎረንስ ፍሪማን የኢትዮጵያ የባሕር በሮችን የመጠቀም ፍላጎትና መሻት ተገቢነት ያለውና የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመጨመር አስተዋፅኦ አለው፤ ሲሉም ገልጸዋል። የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ መገንዘብ አለባቸው፤ ሲሉም ተናግረዋል።
እስማኤል አረቦ
ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2016 ዓ.ም