አገራዊ የምክክር መድረክ ግጭቶችን የመፍቻ ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የየበኩላችንን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል። አገራዊ ምክክሩ ላይ ኅብረተሰቡን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ የተወሰኑ አካላት የሚሳተፉ ቢሆንም፣ ሕዝቡ የአገሩን ጉዳይ የእነዚህ ሰዎች ብቻ ጉዳይ ሳያደርግ በየመሥሪያ ቤቱና መሰብሰብ በቻለባቸው ቦታዎች ሁሉ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና ሐሳብ አላቸው ከሚላቸው ሰዎች ጋር እየተቀራረበ፣ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መደማመጥ መቻል አለበት። የማዳመጥ ባህልን ማዳበር ከሕዝቡ የሚጠበቅ መሠረታዊ ነገር ነው፤ ቁጭ ብለን በረጋና በቀና መንፈስ የመነጋገርን ልምድ በአዳበርንበት ሁኔታ፤ ሌሎች ሰዎች መክረው፣ የሆነ ውጤት ይዘው ቢመጡም ውጤቱን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አንችልም። ስለሆነም ሁላችንም ለምክክሩ ስኬት ልባችንን ዝግጁ ማድረግ ይኖርብናል።
ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የመንግሥትን ዝግጁነትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ እየታየ ያለው ድጋፍ ተስፋ ሰጪ ነው። እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ ቢስተካከለሉ የምንላቸውና መንግሥትን የምንተችባቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ገለልተኛ በሆነ አካል ማቋቋሙ፣ የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮችም “በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ጠቁሙ” ብሎ ለህዝቡ እድል መስጠቱና ኮሚሽነሮችን የመሰየምና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ከሥራ አስፈጻሚው ወደ ሕግ አውጪው ሐላፊነቱን ማሻገሩ በጣም አበረታችና ዋጋ ልንሰጠው የሚገባ ነው። አሁን ያለው መንግሥት ቀደምት መንግሥታት እንደአደረጉት፣ የጨዋታውን ሕግ እኔ ጽፌዋለሁ፤ ይህን የምትከተል ከሆነ “ተከተል” የማትከተል “ሒሳብህን ታገኛለህ” ሳይል፣ ሐላፊነት በተሞላው መንገድ ለአገራዊ ምክክር መደላድል መፍጠሩን ቀላል ነገር አድርገን ልንቆጥረው አይገባም።
በመንግሥት በኩል አገራዊ ምክክርን ለማካሄድ እጁን መዘርጋቱ፤ ቅድመ ዝግጅቶችንም እያካሄደ መሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት ያለውን ፍላጎት ያሳያል። ከዚህ ቀደም የነበሩንን የውይይት ዕድሎችና የተዘረጉ የሰላም እጆችን በይሁንታ አለመቀበላችን ለበርካታ ችግሮች ዳርጎናል። መንግሥት አገራዊ ምክክር እንዲደረግ መሥመሩን ሲዘረጋ፣ “እንመካከር፤ መፍትሔ እናምጣ” በሚልበት ጊዜ፣ የተዘረጉ የሰላም እጆች እንዳይታጠፉ ሰላም የሚፈልግ ሁሉ ተባባሪ መሆን አለበት።
ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊዎች የሌላውን ፓርቲ አመለካከት ያለ ምንም ብያኔ ቁጭ ብለው በማዳመጥ፣ ለሕዝቡ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በምክክሩ የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መምጣታቸው ስለማይቀር የምንሰማቸው ነገሮች የሚቆረቁሩ የጫማ ውስጥ ጠጠር ሊሆኑ ይችላሉና ልበ ሰፊነት ያስፈልጋል። “ፖለቲካ” የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መጥተው የተሻለውን መቀበል በመሆኑ፣ ፖለቲከኞቻችን ሰጥቶ መቀበልን መልመድ አለባቸው።
ዘመን መጽሄት ሚያዝያ 2016 ዓ.ም