ተስፋ ባለመቁረጥ የተሳኩ ድሎች ይስፉ!

መጋቢት 2010 ዓ.ም እውን የሆነው ለውጥ በርካታ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግቧል። የዲሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ፣ ነጻ እና ጠንካራ ሆነው መንግሥትን ተገዳድረው ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጡ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።

መንግሥት ዲሞክራሲ እንዲያብብ ጠንከር ብለው ተግባራትን ያስፈጽማሉ በሚል ለዲሞክራሲ ተቋማት ዓላማ ተዓማኒ የሆኑ ሰዎችን ኃላፊዎች በማድረግ መድቧል። በሕግ መሠረት ተግባሮቻቸውን ለማከናወን ክፍተት አሉብን ላሉትም ተቋማቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል፤ የማቋቋሚያ ሕጎቻቸውም ተሻሽሎላቸዋል።

የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ እና የምርጫ ሕጉ በአዲስ መልክ መሻሻሉን ተከትሎ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የገለልተኝነትን መርሆ በመከተል እያስፈፀመ ይገኛል። ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕግ ማዕቀፉን ሆነ አደረጃጀቱን እና የሰው ኃይሉን ከመቀየር አንስቶ የጀማመራቸው መልካም አካሄዶች አሉ። ከሞላ ጎደል ትላልቅ የሚባሉ ተዓማኒና ጠንካራ የሆኑ ሪፖርቶች አውጥቷል። መገናኛ ብዙኃን እንዲቀጭጩ፣ ደፋር እንዳይሆኑ፣ ታማኝ ሆነው ሥርዓቱ ብቻ የሚፈቅደውን እንዲናገሩ ያደርጉ የነበሩ ሕጎች እንዲለወጡ ተደርጓል ፡፡

በርካታ በውጪ ሀገር የኖሩና የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው፣ ያላቸውን የፖለቲካ አጀንዳ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲወያዩና እንዲከራከሩ ዕድል መስጠቱ፣ አፋኝ የሆኑና የፖለቲካ ምሕዳሩን የሚያጠቡ የፀረ ሽብር እና የበጎ አድራጎትና የሲቪል ማኅበራት ሕጎች እንዲሻሻሉ መደረጋቸው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተስፋ እየፈነጠቀ መሆኑን ያመላክታሉ። የለውጡ መንግሥት ብዙ ስኬቶች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ፈተናዎችም ገጥመውታል።

ለውጡን በትዕግስት አለማየትና ቅጽበታዊ ለውጥ እንዲመጣ የመፈለግ አዝማሚያ፣ ለውጡ ለገጠሙት ፈተናዎች መባባስ አስተዋፅዖ አድርጓል። በለውጡ ጉዞ፣ የእኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ሕዝቦች ምላሽ ማግኘት ችለዋል። አጋር በሚል ይጠሩ የነበሩ ፓርቲዎችም ወጥ በሆነ ፓርቲ ውስጥ ተደራጅተው በሀገር ዕጣ ፈንታ ላይ ድምጽና ሀሳባቸውን መስጠት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ ነው። ሌሎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች ደግሞ ጊዜን  የሚጠይቁ በመሆናቸው ይህንን ተረድቶ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት።

ሀገር የሚገነባው በሕዝቦች ተሳትፎ ነውና ያለፉ መስዋዕትነቶችን ደግመን እንዳንከፍል የሀሳብ የበላይነትን ማክበር፣ ግልጽ ጥያቄዎችን መመለስ፣ ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ቡድኖችና ግለሰቦችን ሥርዓት በማስያዝ ተጠያቂነትን ማስፈን አሁንም የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። ተስፋ ባለመቁረጥ የተሳኩ ድሎች እያሰፉ የሥርዓት ግንባታ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የለውጡን ስኬት ማፋጠን ነው። የለውጡ አንዱ ዓላማ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትና እኩልነትን ማረጋገጥ ነው። ይህን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት መንግሥት ብዙ የቤት ሥራዎች ይቀሩታል።

እኩልነትን የማይሹ፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይኖራት ሌት ተቀን የሚተጉትን ኃይሎች በአይነቁራኛ መከታተልና መለየት ያስፈልጋል። በመንግሥት መዋቅር የሚገኙ ራስ ተኮር የሆኑና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ለውጡን እንዳያጨናገፉ ብሎም አደጋ ውስጥ እንዳይከቱት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ግድ ይላል። ለውጡን መጠቀሚያ የማድረግ አካሄድ ለማንም ስለማይጠቅም መንግሥት ችግሮችን ለማረም ጨከን ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል።

ዘመን መጽሔት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም  

Recommended For You