የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ፣ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ፣ የበርካታ ውብና ድንቅ ባህሎች መገኛ፣ የኅብረ ብሔራዊነት ማሳያና የኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት የእኛዋ አዲስ አበባ።
የተስማሚ አየር ንብረት ባለቤትና የታታሪ ሕዝቦች መገኛ የሆነችው የኢትዮጵያዋ መዲና የዕድሜዋን ያህል ዕድገት ሳታሳይ መኖሯ በብዙ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሐቅ ነው። የፍትሐዊነት መጓደል፣ በፕላንና በዕቅድ አለመመራት፣ ሕዝብን አሳትፎ ልማትን በማረጋገጥ በኩል የታዩ ክፍተቶች ወዘተ አዲስ አበባን እንደ ሰሟ አዲስ እንዳትሆን አድርገዋት የቆዩ ትልልቅ የዕድገት እንቅፋቶቿ ነበሩ።
በ132 ዓመት ዕድሜዋ በ32 ከንቲባዎች የመመራት ዕድል የገጠማት አዲስ አበባ መንግስታዊ አመራሮችዋና ከንቲባዎቿ የቻሉትን ያህል ሠርተው ዐሻራቸውን በዘመን ጅረት ውስጥ አሳርፈዋል።
በኢትዮጵያ የለውጥ ዘመን መከሠት ለአዲስ አበባ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞላት መጥቷል። በዚህም አዲስ አበባን እንደገጠር ማስተዳደርና ቅድሚያ ለገጠሩ የሚሉ የተሳሳቱ ፖሊሲዎችና አካሄዶች ተቀልብሰው፤ አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ተምሳሌትና የልማት ሞተር የማድረግ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም እመርታዊ የሚባሉ ለውጦች ተመዝግበዋል።
አብርሆት ቤተመጻሕፍት፣ የቸርችል – መስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ ዓድዋ መዚየም፣ አንድነት፣ ወዳጅነት፣ እንጦጦ ፓርኮች፣ የንግድ ባንክና የመከላከያ ግዙፍ ሕንጻዎች በለውጡ ዘመን ተወጥነው የተተገበሩና የአዲስ አበባን የዕድገት ግስጋሴ አፍ አውጥተው የሚመሰክሩ ታላላቅ መገለጫዎች ናቸው።
ዕድገት በሕንጻና በቁስ ሳይሆን በሰብዓዊ ልማት ነው መመዘን አለበት የሚለው የለውጥ አመራር እሳቤም አዲስ አበባ ከሁሉ ነገር አስቀድማ ለዜጎቿ ትኩረት ሠጥታ እንድትሠራ አድርጓታል።
የወላጆችን ሸክም የአቀለለውና የነገዋን ኢትዮጵያ ተረካቢ ዜጎችን በብቃት ማፍራትን ታሳቢ ያደረገው የተማሪዎች ምገባና የደንብ ልብስ ድጋፍ፤ የአረጋውያን ምገባ፣ የዐቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ ማዕድ ማጋራትን የመሳሰሉ የተቀደሱ ተግባራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቀይረዋል፡፡ የመኖር ተስፋቸውንም ያለመለሙ የአዲሲቷ አዲስ አበባ መገለጫ ባሕርያት ሆነዋል። አዲስ አበባ የዜጎቿን የኑሮ ጫና በማቃልልም በዓመት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በጅታ እየሠራች ትገኛለች።
አርሶ አደሮችን ከሚያፈናቅልና ከሚገፉ ሥርዓት የተላቀቀችው አዲስ አበባ እነዚህኑ የልማት ኃይሎች ደግፋና አቅፋ ትራክተር ጄኔሬተር፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፕና አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን አቅርባ የዕድገቷና የውበቷ አካላት አድርጋቸው እየተጓዘች ትገኛለች።
ከጄኔቭ በመቀጠል የዓለም የዲፕሎማቲክ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ አህጉራዊና ቀጣናዊ ድርጅቶች መቀመጫ ናት። ይኸም ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት ድምቀትና ጥቅም ሆኗታል። በመዲናዋ የሚከናወኑ ዓለም አቀፍ ሁነቶቸም ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ደምቀትና ገቢ ሆነውላታል።
የአዲስ አበባ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮቿ የሥራ ሰዓትንና ቀንን ቆጥሮ በመሥራት ብቻ የማይመለሱ መሆናቸውን የተገነዘበው የከተማዋ አስተዳደርም ከችግሯ አላቆ ለዜጎቿ የተመቸች መዲናን እውን ለማድረግ ለዕድገቷና ስኬቷ ሌት ተቀን መትጋቱን ቀጥሏል።
ዊንዶው ኦፍ አፍሪካ፣ የኦቪድ ግሩፕ መኖሪያ ቤቶች፣ ግዙፉ የኢኮኖሚ ዞን ወዘተ ለነገዋ አዲስ አበባ ሰርግ በዝግጅት ላይ ያሉ አጓጊ መሠረተ ልማቶች ናቸው። ሕዝቦቿን አሳትፋና አወዳጅታ በልማት ሩጫ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ጅምሯ ሠምሮ ራእይዋ ተሳክቶ የሚታይበት ዘመን እውነትም መቃረቡን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያስችላል!
ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015