በሰላም ይሁን በጦርነት ጊዜ አላግባብ ሰብዓዊ መብታቸውን የተገፈፉ፣ ፍትሕ ያጡ፣ የአካል እና የሞራል ውድቀት የደረሳባቸው ዜጎች የሽግግር ፍትህ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ችግር ለመፍታታ በርካታ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በመቅረጽ ተግባራዊ አድርገው መፍትሄ አግኝተውበታል። ኢትዮጵያም የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን ለመዘረጋት እና ተግባራዊ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ይህም ያለፈውንም ቁስል ለማከም ዛሬም ያለውን አዳዲስ ቁስሎች ለማስቆም እና ወደ ተረጋጋ፣ ሠላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቅናት መልካሙ መንገድ ነው።
የሽግግር ፍትህ ሂደት ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተገቢውን ክስ በማቅረብና በማስቀጣት፣ ሁለንተናዊ የሆነ እርቅን በማጠከር፣ ምህረትን በመስጠት፣ እውነትን በማፈላለግ፣ ማካካሻን በመስጠት፣ተቋማዊ ማሻሻያን እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው ጉዳዮችን በአንድነትና በተመጋጋቢነት ያካተተ ሁለንተናዊ አካሄድ ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ለተጀመረው የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጭ ስኬታማነት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ መወጣት የዜግነት ኃላፊነታችን ነው። ሂደቱ ቀና እንዲሆን ጥላቻና ቂም በቀልን በመተው ለፍቅር ልዩ ቦታ መስጠት ይጠበቅብናል።
ሀገራችን ያለችበትን የፖለቲካ ትኩሳት በመረዳት፤ካለፉት የጠላትነት ስሜት የጎደፈ ፖለቲካ ታሪካችን በመማር፤የዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ግሎባላይዜሽንን በማገናዘብ፤በተለይም ልዩ መታወቂያችን የሆነውን ‘እርስበርስ የመጠፋፋት ፖሊሲያችን’ የሚመስለውን በማስወገድ ብሄራዊ መግባባት ላይ በመድረስ ሀገራዊ እድገትን በጋራ የሚያራምድ የጋራ ብሄራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ እራሳችንን እናዘጋጅ። በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ ባለፈው ሰሞን ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁትም፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን አብዝቶ የሚፈልግ፣ከበቀል ይልቅ ይቅርታን የሚያስብ፣ ከግጭት ይልቅ ዕርቅን የሚፈልግ ካለ የስኬት መንገድ ተጀምሯል። ሰላም መተጋገዝን፣መተባበርን፣ አንዱ ላንዱ መተውንም ይፈልጋል። ባለፉት በርካታ አመታት በቂ ጦርነቶችን አድርገናል፤ አሁን ግን ኢትዮጵያ የእፎይታ ጊዜ ያስፈልጋታል። ይህም በፍቅር ከሆነ በደንብ ይቻላል።
በዓለም ላይ ለጠላቶቻቸው ምህረትና ይቅርታ በማድረግ ያለጠላትነት በሰላም በጋራ የመኖር ጥበብ ሞዴሎች ከሆኑት የሀገር መሪዎች ውስጥ ኒልሰን ማንዴላና ማህተመ ጋንዲ ምንጊዜም ተጠቃሽ ናቸው። ማንዴላ “ጠላትህን ውደድ” “ወንድምህ ሰባት ጊዜ ቢበድልህ ሰባ ጊዜ ይቅር በለው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሰረት፤ለግፈኞቹ ህዳጣን ነጮች ገዢዎች ታላቅ ምህረትና ይቅርታ አድርገው ደቡብ አፍሪካን የሁሉም እኩል መኖሪያ በማድረግ ዴሞክራሲና ሰላምን አስፍነዋል። ኒልሰን ማንዴላና ማህተመ ጋንዲ በሀገራቸው አስተማማኝ ሰላምና እድገት ለማምጣት የመረጡት ይቅርታና ምህረት ያለበትን የፍቅር ጎዳና ሲሆን፤ እንዳዋጣቸው የምናውቀው ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲ በማስፈን በብልጽግና ጎዳና ላይ መሆናቸው ነው።
ጋንዲም ይሁኑ ኒልሰን ማንዴላ የበርካታ ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች ሀገሮቻቸውን ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ ያፀዱት በሁለት ነገሮች ብቻ ነው። በምህረትና ይቅርታ እንዲሁም ገደብ በሌለበት ፍቅር ነው። እኛስ? ዘረኛ፣ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ተለጣፊ፣ ባንዳ ወዘተ በመባባል አንዳችን አንዳችንን ለማጥፋት ስለት ከመሳል፤ ጦር ከመስበቅ ይልቅ፤ በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ጥላቻ-አልባ የፖለቲካ ህይወትን እንከተል። በምህረትና በይቅርታ ታድሰን፣ በመቻቻል ተደራድረን፣ ፍትህና ነጻነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማምጣት ግድ የሚለን ጊዜ አሁን ነው። ዘላቂና እውነተኛ ሰላም፣ልማት፣ ነፃነትና እኩልነት የሚኖሩት ፍቅር ሁሉን ሲያሸንፍ ብቻ ነው። በመሆኑም ለሀገራችን የምናስብ፣ለህዝብ የምንቆረቆር፣ዘላቂ ሰላምና ልማት የምንሻ ከሆነ ይቅርታና ምህረት ያለበትን የፍቅር ጎዳና እንም ረጥ !