መመካከር እያለ መነካከስ አይበጅም!

አገራዊ ውይይቶች የአንዲት ሃገር ህልውና በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አደጋ ላይ ሲወድቅ አሊያም ዜጎችና ይመለከተናል የሚሉ አካላት የሃገሪቱ ቀጣይነትና የዜጎች የወደፊት ኑሮ ሲያሳስባቸው የሆነ አይነት የመውጫ ብልሃት ለመሻት የአኗኗር ዘይቤያቸውን፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አወቃቀራቸውን ያሉበትን ክፍለአለም ታሳቢ ያደረገ አካታች የንግግር የውይይት ወይም የድርድር መንገዶች ስለመፈለጋቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም ሲባል የተመሰረተው አገራዊ የምክክር መድረኩ ቀደምሲል የነበሩና አሁንም ፈተና ሆነው የተገኙ የአገራችንን ችግሮችን ተነጋግሮ ከመፍታት አካያ የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው፡፡ ምንም እንኳን ብዙ የሚያግባቡ ነገሮች ቢኖሩንም ከጊዜ ወደጊዜ ግን አንዳንድ መሰረታዊ የሆኑ የማያግባቡን ነገሮች በመኖራቸውና እነኚያም ለግጭትና አልፎም ለጦርነት ስለዳረጉን ህዝቦቻችን በማያግባቡን ነገሮች ላይ ተወያይተው ወደፊት ሀገራችን ሰላማዊ የምትሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡

ውይይት ተወያዮችን መግባባት ላይ ያደርሳል፡፡ መግባባት ላይ እንኳን ባይደረስ ከነ አለመግባባታችን ተግባብተን እንድንቀጥል ያስችላል፡፡ ከነ አለመግባባታችን ተግባብተን እንቀጥል ማለት አንድ ቀን ያላግባቡን ነገሮች ይፈታሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ውይይት እንጂ ጦርነት እና መሳሪያ ጥቅም የለውም፡፡ ማንኛውም ችግር የተፈጠረው ሰዎች በሃሳብ ባለመግባባታቸው በመሆኑ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ችግራቸው እንዲወገድ በቅድሚያ መነጋገር አለባቸው፡፡ ውይይት መግባባትን ያመጣል፡፡ በብዛትና በሀይል ልዩነቶቻችን ላይ ስለሰራን አሁን የደረስንበት ላይ ደርሰናል፡ የጦርነትን አስከፊነት አይተናል፡፡ በጦርነት ሰላም አይመጣም፡፡

ዘላቂ የሆነ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ሊመጣ የሚችለው ቁጭ ብሎ መሳሪያን አስቀምጦ መወያየት ሲቻል ነው፡ ፡ ወደ ውይይት ሲመጣ መጀመሪያ መቀመጥ ያለበት መሳሪያ ነው፡፡ ውይይት ሁላችንም የምናሸንፍበት እስከሆነ ድረስ ሁላችንም መሳሪያችንን አስቀምጠን ሰላምን አንግበን መምጣት አለብን፡፡ ስለሰላም እስከተመጣ ድረስ ለሰላም የማይከፈል መስዋዕትነት የለም፡ ፡ ለሰላም በሚከፈል መስዋዕትነት ውስጥ ደግሞ ህይወት አይጠፋም፡፡

በጦርነት ያየነው አሳርና መከራ ነው፡ ፡ መመካከር እያለ መነካከስ አይበጅም። ሰላም በአገራችን በመኖሩ የሚቀኑ አሉ። እርስ በእርሳችን እንድንቀያየም፣ እንዳንረዳዳ፣ እንዳንተማመን ሠላም የሌለባት ረብሻና መከራ የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትሆን ሌት ከቀን የሚሰሩ አካላት እንዳሉ መረዳት ያሥፈልጋል።

Recommended For You