አዲስ-ጥበብ

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኅብረብሔራዊ ከተማ የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ ከኪነ ጥበብ ጋር ያላት ቁርኝት እጅግ ጥልቅና ትልቅ ነው። በዚህ ጽሑፍ አዲስ አበባን በኪነ-ጥበብ መነጽር እንቃኛታለን።

ቀደም ሲል ዋና ከተማ ከነበረችው እንጦጦ ከተማ ላይ ሆነው የአዲስ አበባን ዕድገት የተመለከቱ ነዋሪዎቿ በከተማዋ ፈጣን ዕድገት ይገረሙ ነበር። በእምነት ገብረአምላክ የተባሉ ገጣሚም በ1950ዎቹ የአዲስ አበባን ውበት በገለጹበት ግጥማቸው የሚከተለውን ብለዋል።

‹‹እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት፣

ባለፈርጥ ኮከብ መስላ አገኘኋት።››

የሥነ ግጥም መምህርና ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ “ አዲስ አበባ በአማርኛ ሥነ ግጥም “ በሚለው መጣጥፋቸው ይህን መንቶ ግጥም እንደሚከተለው ገልጸውታል። ‹‹የዚህ መንቶ ደራሲ፣ የአዲስ አበባ ውበት በድንገት ያነቃው ያነሆለለው ባለቅኔ ነው። ከግጥሙ ዓውደ ንባብ ተነሥተን ስናሰላስል፤ የገጣሚው አድናቆት የመነጨው ከምሽት ትዕይንት ነው ማለት ይቻላል። ለምን ቢሉ ለአድናቆቱ ማንጸሪያ፣ ለአድናቆቱ መያዣ የመረጠው ምስል ባለፈርጥ ኮከብ ነውና፤ አንድም ኮከብ በምናባችን የሚከሠተው የብርሃን ምስል ነውና። አገላለጹ ውብ ነው፤ ምስሉም የተባና የደመቀ። እናም በእነዚህ ስንኞች አዲስ [አዲስ አበባ] ለገጣሚው ብቻ ሳይሆን ለተደራሲውም አዲስ ውበት ትሆናለች።›› (“አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሊኒየም” በተሰኘው መድብል)

ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚዘልቀው አውራ ጎዳና ‹‹እይታን እንደ ቅርስ›› በሚል መርሕ በከተማ አስተዳደሩ የማስፋፋትና የማስዋብ ተግባር ተከናውኖ ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቋል። በአውራ መንገዱ ግራና ቀኝ ለእግረኛ መተላለፊያና ለብስክሌት ጋላቢዎች በሚያመች መልኩ እንዲሰፋ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪበዕፅዋት፣ በአበባ እና በተለያዩ የዛፍ ዘሮች አካባቢው ተውቧል። እግረኞች፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ፒያሳ ሲጓዙ ዐረፍ የሚሉበት፣ ከፈለጉም ቁጭ ብለው የሚያወጉበት መቀመጫዎችም ተበጅተዋል።

በተለይ የቸርችል ጎዳናን የምሽት ገጽታ በኤሌክትሪክ ብርሃን ሕብረ ቀለማት አሸብርቆ ለተመለከተ ሰው የገጣሚ በእምነት ገብረ አምላክ ግጥምን የሚያውቅ ከሆነ ያስታውሳል። የእሳቸውን ግጥም በመዋስም

‹‹ማዘጋጃ ቤት ሆኜ ቸርችልን ሳያት፣

ባለፈርጥ ኮከብ መስላ አገኘኋት።›› ሊል ይችላል። ጎዳናው በጣም በሚያምር ሁኔታ ዐይነ ግቡ በመሆን ለመንፈስ ርካታን በሚሰጥ መልኩ ተውቦ ተሠርቷልና ቢባል ይገባዋል።

አዲስ አበባ በግጥም ስትወሳ አብዛኛውን ጊዜ የሚነገር መንቶ ግጥም አለ። ይኸውም

‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ

ሀገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ››

የሚለው የናፍቆት ግጥም ነው። በዚህ ግጥም ላይ ሐሳባቸውን የሰጡት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ ከላይ በተገለጸው መጣጥፋቸው ላይ የሚከተለውን ብለዋል። ‹‹ በአማርኛ ሥነ ግጥም የአዲስ አበባ ምስል ተደጋግሞና ተዘውትሮ የሚገኘው በትዝታና ናፍቆት ግጥሞች ውስጥ ነው፤ ወይም በስደት ግጥሞች ውስጥ ነው። የሰው ልጅ ገነትም ሆኖ የትውልድ ቀየውን፣ በተራዛሚውም አገሩንና ወንዙን አይረሳም እንዲል ሐዲስ። የአማርኛ ገጣምያን ባሕር ማዶ ለትምህርት ወይ ለሥራ በስደት ሲኖሩ፤ ቃሉ ይለያይ እንጂ የዝማሬያቸው ቃና የቅኔያቸው መንፈስ፤ ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ ሀገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ›› የሚል ነው። ይህ ዓይነቱ የልብና የቀልብ መሸፈት ከአያሌ ስሜቶች ሊቀሰቀስ ይችላል። ከናፍቆትና ከትዝታ፣ ከመከፋትና ከመገፋት፣ ከባይተዋርነትና ከብቸኝነት፣ ከማንሜነትና ከራስ ጥል። በዚህ ረገድ የመንግሥቱ ለማና የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ሁነኛ የዘመናቸው ወኪሎች ናቸው።››

ስለ አራዳ ከተነሣ በቃል ግጥም የተባሉትን አንሥተን እንለፍ።

የአራዳ ዘበኛ ክብሬ ነው ሞገሴ፣

በቸገረኝ ጊዜ የሚደርስ ለነፍሴ።

ይህ መንቶ ግጥም በወቅቱ ከተማዋን እንደ ፖሊስ ሆነው ጥበቃ ያደርጉ ለነበሩ አገልጋዮች የተገጠመ ነው። የአራዳ ዘበኞች ምን ያህል ተግባራቸውን በትጋት እንደሚፈጽሙም የሚያመላክት ነው። በተለይ በምሽት ጊዜ ለሚፈጸም ችግር ለነፍስ የሚደርሱ መሆናቸውን ያሳይል።

ምነው ባደረገኝ ከአራዳ ልጅ መሳ፣

እንኳን ለገንዘቡ ለነፍሱ የማይሳሳ።

አራዳ ሲኒማ አምፔር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ እና ሲኒማ ዓድዋ (ፈርሷል፤ አራዳ ሕንጻ ተሠርቶበታል) የሚገኙበት ቦታ ነው። የአራዳ ልጆች ሲኒማ በመመልከት ለሌሎች አዲስ የሆኑ ድርጊቶችን ማሳየት የተለመደ ነበር። አርቲስት ዓለማየሁ እሸቴ በፊልም የሚያያቸውን ቴክሳሶች በመምሰል በፈረስ አራዳን ይዘዋወር እንደነበረ በመገናኛ ብዙኀን ተናግሯል።

ስለ አራዳ ካነሣን አይቀር አጠገቡ ስላለው ደጃች ውቤ ሠፈር የተባለውን ቃል ግጥም እንመልከት።

ደጃች ውቤ ሠፈር ምን ሠፈር ሆነች፣

ያችም ልጅ አገባች ያችም ልጅ ታጨች።

ደጃች ውቤ ሠፈር ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወደ አፍንጮ በር መሄጃው ላይ ይገኛል። ሠፈሩ በስማቸው የተሰየመላቸው ደጃች ውቤ መኳንንት እና ባለሃብት የነበሩ እንዲሁም ዘውዲቱ ምኒልክን አግብተው የኖሩ ታዋቂ ሰው ናቸው። አዲስ አበባ ሬስቶራንት መኖሪያቸው ነበር። በዚያ አካባቢ ቡና ቤቶችና የጭፈራ ቤቶች ይበዙ ነበር። በእነዚህ ቤቶች ደግሞ የሚሠሩ ሴቶች ደንበኞቻቸውን እንደፍላጎታቸው ያስተናግዳሉ። ከላይ የቀረበው ግጥም ሲታይ ከዚህ በፊት እንደፍላጎቱ ሲስተናገድ የቆየ ደንበኛ፣ አሁን የለመዳቸው አግብተውና ታጭተው በሥፍራው ሲያጣቸው እነሱ የሌሉበት ደጃች ውቤ ሠፈርን እንደሠፈር አለማየቱን የሚያመላክት ነው። የዘመኑ ወጣቶች ሠፈሩን በተለየ ሁኔታ ለጭፈራ ያዘወትሩት ነበር።

ስለአዲስ አበባ ከአነሣን መርካቶን አለማንሣት ከባድ ነው። ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በ1966 ዓ.ም. በአሳተሙት ‹‹እሳት ወይ አበባ›› በሚለው የግጥም መድብላቸው ላይ “አይ መርካቶ” የሚል ርእስ ያለው ግጥም መጻፋቸውን ብናነሣ ጥሩ ነው። ከዚህ ግጥም የመጀመሪያውን አንጓ ወስደን እንመልከት

አገር ከየጎራው ወጥቶ

አንቺን ብሎ ነቅሎ ወጥቶ

ግሣንግሡን ጓዙን ሞልቶ

ኊልቆ መሣፍርትሽ ፈልቶ

ባንቺ ባዝኖ ተንከራትቶ

እንደባዘቶ ተባዝቶ

ተንጠራውዞ ዋትቶ ዋትቶ

አይ መርካቶ……

በአንዳንድ አካባቢዎች ቀንን መሠረት በማድረግ የሰኞ፣ የማክሰኞ፣ የረቡዕ፣ ወዘተ. ተብሎ ስያሜ ወጥቶላቸው በዕለቱ ገበያ ቆሞ ከፍተኛ ግብይት ይከናወናል። መርካቶ ግን ሁሌም ገበያ አለ። ግብይቱ ቀዝቀዝ ብሎ የሚታይበት ቀን ቢኖር እሑድ ብቻ ነው። መርካቶ ለመገበያየት የሚመጣው ሕዝብ ከሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው ገጣሚው በ1965 ዓ.ም. ያዩትን ሲጽፉ “አገር ከየጎራው ወጥቶ፣ አንቺን ብሎ ነቅሎ ወጥቶ” ያሉት። ለመሸጥ ወይም ለመግዛት የሚመጣውን ሰውና ጓዝ በመመልከት ደግሞ ኊልቆ መሣፍርትሽ ፈልቶ” በማለት ገልጸውታል። መርካቶ በውስጧ ምናለሽ፣ ቆርቆሮ፣ ጋዝ፣ ዶሮ፣ ቦንብ፣ አውቶቢስ፣ ጭድ፣ ጫት፣ ቆጮ፣ ብረት፣ ቡና፣ ሶማሌ፣ ሳጥን፣ ጠረጴዛ፣ ሸክላ፣ ፎዴ፣ ሚሊቴሪ፣ ድር፣ ሚስማር፣ ሸማ፣ ሸራ፣ ወዘተ. ተራ በሚል የተሰየሙ መገበያያ ሥፍራዎች አሏት። ሎሬትም በዚህ ሥፍራ የተመለከቱትን ነው በግጥም የገለጹት።

ሎሬት ስለ መርካቶ ይህን ሲሉ ጌታቸው ካሳ ደግሞ ስለመርካቶ የሚከተለውን አዚሟል።

ውብ አዲስ አበባ የትውልድ ሀገሬ

ያደኩብሽ መንደር መርካቶ ሰፈሬ

ከልጅነት እስከዕውቀት ያየሁት ኑሮዬ

ከልቤ ተጽፎ ተሥሎ ከላዬ…

ከግጥም መምህሩና ተመራማሪው እይታ በመቀጠል ስለ አዲስ አበባ ከተማ የተዘፈኑ የተወሰኑ ዘፈኖችን እንመልከት።

አዲስ አበባ ቤቴ አዲስ አበባ ቤቴ

ሸጋ ልጅ ቆንጆ ልጅ አለች ጎረቤቴ

ኧረ እንዲያው ይመኙሻል ኧረ እንዲያው ይመኙሻል

ኧረ እንዲያው ይመኙሻል ኧረ እንዲያው ይመኙሻል

በምኞት ቢጓጉ ወዴት ያገኙሻል። …

(ዓለማየሁ እሸቴ)

ይህን የዓለማየሁ እሸቴ ዘፈን ትዝታ ቀስቃሽ ነው።

ኤሌ ኤሌ አባ – አዲስ አበባ

ኤሌ ኤሌ አባ – አዲስ አበባ

መዓዛዋ ጠራኝ – አዲስ አበባስሟ ሲነሣ – አዲስ አበባ

በንጋት ተኩላ- አዲስ አበባ

በአበባው ሞይሳ – አዲስ አበባ

ዐይኗም ይናጋራል – አዲስ አበባ

ፍቅሯ እያደራ – አዲስ አበባ

ውበት አልብሷታል – አዲስ አበባ

አቤት የእሱ ሥራ – አዲስ አበባ …

ብርሃኑ ተዘራ እና ዮሐንስ በቀለ (ቶኪቻው)

ይህ የብርሃኑ ተዘራ ዘፈን አዲስ አበባ ከተማ ስሟ ሲነሣ መዓዛዋ ያውደኛል ይለናል፤ መልካም ገጽታዋን ለማድነቅ የተባለ ነው። ከተማዋ በንጋት ተጣጥባ ተኳኩላ በለጋነቷ (በአበባነቷ) ለአሸናፊነት በተዘጋጀች እንስት ተመስላ ቀርባለች (ሞይሳ በኦሮሚኛ አሸናፊ ማለት ነው)። በተጨማሪም ከተማዋ ውበቷ (መልካምነቷ) አማሎት አምላኩን ያደንቃል፤ ያሞግሳል።

ታምራት ደስታም ስለ አዲስ አበባ ሲዘፍን ተመሳሳይ ይዘት ያለው ከተማዋ የፍቅርና የጥቁር ሕዝብ መሰብሰቢያ እንደሆነች፣ በክፉ ቀን ሳትነፍግና ሳትሰስት አምኗት ለመጣ ለአዳም ዘር ሁሉ መጠለያ ሆና ያላትን የቸረች መሆኗን እንደሚከተለው አቅርቧል።

አንቺ የፍቅር አንባ የአፍሪካ መዲና

አንቺ የፍቅር አንባ ሀገሬ አዲስ አበባ

የጥቁር ሕዝብ መናኸሪያ

የፍቅር መጀመሪያ

ተወልጄ ያደኩብሽ

ብዙ ብዙ ያዩብሽ …

አንቺን አምኖ ተጠግቶ…

አዲስ አበባ ከተማን በተመለከተ የተዘፈኑ ዘፈኖች ይዘት ስንመለከት ከተማዋ በጠዋት ተኳኩላ ለአሸናፊነት ብቅ እንዳለች ወጣት እንስት ተመስላ ታይታለች። ከዚህ በተጨማሪ እንደስሟ የፈካች አዲስ አበባ መሆኗ እና ኅብረ ብሔራዊነት ያላት የኢትዮጵያ ተምሳሌትነቷ ተጠቅሷል። ውበቷ በውስጧ ካላት ሰላምና ከኢትዮጵያ ስመ ገናናነት የመነጨ መሆኑም ተወስቷል። ከተማዋ የጥቁር ሕዝቦች መዲና እና መመኪያ ከመሆኗ በተጨማሪ በተለይ ክፉ ቀን ላጋጠማቸው የአዳም ዘር ለሆኑ በሙሉ ሳትነፍግና ሳትሰስት መጠለያ ሆና ያላትን የቸረች መሆኗ በሚያምር ድምፅና ጆሮ ገብ በሆነ ሙዚቃ ቀርቧል።

ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ከተማ በኪነጥበብ በምን መልኩ ቀርባለች ለሚለው ዳሰሳ ለማድረግ የተሞከረበት ነው።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You