የብርሃን መንገድ

አዲስ አበባ አዲስ መልክ በመላበስ ላይ ትገኛለች። ለዓሥርት ዓመታት ከአሸለባት፣ በየመሐሉ እየባነነች መልሳ ከምትወሰድበት እንቅልፍ እየነቃችም ነው።

በለውጡ ዘመን አዲስን የሚመጥን ዘላቂ ልማት ታቅዶላታል። የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ላይ የሚገኙ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ነው። በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙና በውጥን የተያዙ ማርሽ ቀያሪ ፕሮጀክቶችም ብዙ ናቸው። ለነዋሪዎቿ የምትመችና የአፍሪካ መዲናነቷን እንድትመጥን በሚያስችል መልኩ የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ‘ሰርክ አዲስ’ የሚለውን ስያሜ እንድትመጥንም እያገዘ ነው።

በለውጡ ዘመን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ግንባር ቀደም መሪነት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት፣ በተለያዩ የልማት ድርጅቶች፣ በመንግሥት እና በግል ባለሀብቶች ጥምረት እንዲሁም በግሉ ዘርፍ በከተማዋ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል። የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነላቸው ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችም አሉ። እነዚህ በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት የሚፈስባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አዲሲቷን፣ አዲስ አበባን እየፈጠሩ ነው። በዚህ ጽሑፍ ለአዲስ አበባ አዲስ መልክ እየሰጧትና እንደ ስሟ ውብ እያደረጓት ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዳስሳለን።

የአንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ አመንጪነት ግንባታው የተጀመረው የአንድነት ፓርክ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቆ ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት ሆኗል። የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን ያቀፈ ነው። ፓርኩ የሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት በ1887 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ቤተ መንግሥቱ የስምንት ኢትዮጵያውያን መሪዎች የመኖሪያና የሥራ ቦታ ሆኖ ዘልቋል። በ40 ሄክታር መሬት ላይ ከዐረፈው ቤተ መንግሥት 13 ሄክታር ያህሉ ላይ የዐረፈው አንድነት ፓርክ የሀገር በቀል ዕፅዋትና እንስሳት መገኛ፣ የነገሥታቱ እልፍኞች፣ ሙዚየምና ታሪክ ነጋሪ ክፍሎችን ይዟል።

የወዳጅነት ፓርክ የባህል ማዕከላትን፣ የሥነ ጥበብ ጋለሪ እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቦታዎችን የአካተተ 58 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእንጦጦ-አቃቂ የወንዝ ዳር (ሪቨር ሳይድ) ውበት ፕሮጀክት አካል ነው። የእግር ኳስ እና የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችን ጨምሮ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመዝናኛ መገልገያዎችን እና የመጫወቻ ሜዳዎችን የአካተተ ነው።

በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ግንባታ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ የወሰደ ነው። የእንጦጦ ፓርክ በአምስት የግንባታ ሳይቶች ላይ በርካታ መዝናኛዎችን ይዟል። ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘልቀው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ከ2 መቶ ዓመታት በላይ የቆዩ ታሪካዊ ቅርሶችና የኢትዮጵያ ትልቁ የአርት ጋለሪ የሚገኝበት ነው። በአምስት ሳይቶች ተከፋፍሎ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ፣ በውስጡ የፈረስ መጋለቢያ ሜዳ እስከነ ፈረሶቹ ጋጣ፤ ባህላዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና በቀድሞ ነገሥታት የግብር አዳራሽ አምሳል የተሠሩ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን፤ ዘመናዊ ካፍቴሪያዎችን፤ ለጥንዶችና በቡድን ለሚዝናኑ የተዘጋጁ መናፈሻዎችን፤ የህዋ መመልከቻ ማማ፤ የብስክሌት መጓጓዣና ሌሎችንም ይዟል።

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት

ግንባታው በሰኔ 2012 ዓ.ም የተጀመረው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለግንባታ ሥራው 2 ቢሊዮን 589 ሚሊዮን 800 ብር በጀት ወጪ ተደርጎበታል። ከቸርችል ጎዳና እስከ መስቀል አደባባይ ልዩ ገጽታን ያላበሰው ይህ ፕሮጀክት መስቀል አደባባይ የቀድሞ ይዘቱን ሳይቀይር ከመሬት ሥር ሁለት ወለል ወደ ውስጥ በመግባት የመኪና ማቆሚያ እንዲሁም አደባባዩንና ጎዳናዎችን የማስዋብ ሥራ ተሠርቷል። አደባባዩ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረውን ሃይማኖታዊ፣ ሕዝባዊ እና ሌሎች ማኅበራዊ ዝግጅቶች በተለይ በከተማዋ ብዙኃኑን ታሳቢ ያደረጉ ኹነቶችን በተሻለ እና ምቹ በሆነ መልኩ ለማዘጋጀት በሚያስችል መልኩ የተገነባ ነው።

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት በአካባቢው የሚስተዋለውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራ ጥበትን ከመቅረፍ አንጻር እስከ 1ሺህ 400 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን የሚያስቆሙ ባለሁለት ወለል የመሬት ውስጥ ስማርት ፓርኪንግ የያዘ ነው። በተጨማሪም 35 ሱቆች፣ 140 መጸዳጃና 20 መታጠቢያ ቤቶች፣ እንዲሁም ሌሎች የቢሮ መገልገያ ክፍሎች አሉት። ሱቆቹ የኢትዮጵያን ባህል እና ቅርሶች የሚያሳዩ እና ለጎብኚዎች እንዲሸጡ በሚያመች ሁኔታ የተገነቡ ናቸው። ስድስት ዘመናዊ ሊፍቶች፣ ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ የደኅንነት ካሜራዎች፣ ዘመናዊ ዲጂታል ስክሪኖች እና የእሳት መከላከያ ተገጥሞለታል። በመስቀል አደባባይ እና አካባቢው ነጻ የWiFI ኢንተርኔት አገልግሎትም እንዲሰጥ ተደርጎ የተሠራ ነው።

አብርሆት ቤተመጻሕፍት

የነገዋን ሀገር ተረካቢዎች ለማፍራት ትምህርት ተኪ እንደሌለው ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ትምህርት ደግሞ ያ ለንባብ የሚታሰብ አይደለም። ከዚህ መሠረታዊ እውነት የተነሣውና ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአዲስ አበባ 4 ኪሎ በዘመናዊ መልኩየተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተመጻሕፍት ታኅሣሥ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል። በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የዐረፈው ቤተመጻሕፍቱ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ቤተመጻሕፍት መካከል አንዱ መሆኑ ተነግሮለታል። ቤተመጻሕፍቱ በ4 ወለሎቹ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን መያዝ የሚችል 1 ነጥብ 5 ኪ.ሜ መደርደሪያ ይዟል። ተመርቆ በተከፈተበት ወቅት ከ240 ሺህ በላይ መጻሕፍትና 300 ሺህ ጥናታዊ ጽሑፎችን መያዙ ተገልጿል። የሕፃናት ማንበቢያ እንዲሁም ለዐይነ ስውራን አንባቢዎች በቂ የብሬይል መጻሕፍት አቅርቦት ያለው መሆኑም ልዩ ያደርገዋል። ዘመናዊ ካፍቴሪያ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ስምንት የመጻሕፍት መሸጫ ሱቆች፣ አምፊ ቴአትር እና መጫወቻ ቦታዎችንም የአካተተ ነው። በተጨማሪም ደኅንነቱ የተጠበቀ በአንድ ጊዜ 115 መኪኖችን ማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ የያዘው ይህ ቤተመጻሕፍት ግንባታው የተጠናቀቀው በ18 ወራት ነው።

የሳይንስ ሙዚየም

በኢትዮጵያ በዓይነቱ የተለየ ነው የተባለ የሳይንስና ሥነ ጥበብ ሙዚየም በታላቁ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ተገንብቶ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ተመርቆ ተከፍቷል። ሕንጻው በቀለበት ቅርጽ እና በጉልላት መልክ የተሠራ መሆኑ ምሉዕነትን፣ የማያቋርጥ የከፍታ ጥረትንና ምኞትን ማሳያ፣ ረቂቅ የሆነውን የኢትዮጵያዊ ጥበብ እንዲሁም ኢትዮጵያ የወደፊቱን ቴክኖሎጂ ለመጨበጥ ያላትን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ተብሏል። የሙዚየሙ ውስጣዊ ክፍል ወደ 1400 ሜትር ስኩየር ስፋት ያለው ድምፅ የማያስተላልፍ ቋሚ እና ጊዜያዊ የዐውደ ርእይ ቦታዎችን የያዘ ነው። ሙዚየሙ ከዐረፈበት ቦታ 80 በመቶ የሚሆነው መሬትም ከአራት ሺህ በላይ በሆኑ ሀገር በቀል ዕፅዋትና ውብ አበቦች የተሸፈነ ነው፤ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራም አለው። ሙዚየሙ ከተፈጥሮ ጋር በማይቃረን መልኩ የታነጸ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይልም ከፀሐይ ብርሃን ያገኛል።የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እድሳት

የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሕንጻው ከ57 ዓመታት በኋላ ነባር ገጽታውን ሳይለቅ እድሳት ተደርጎለት ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመርቋል። የከተማ አስተዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዘጋጃ ቤቱን ዋና መሥሪያ ቤት ለማደስ በአጠቃላይ 2.2 ቢሊዮን ብር ፈሰስ አድርጓል። የእድሳት ሥራው የመሬት አቀማመጥ፣ ቢሮዎችን እና ባለ 850 መቀመጫዎች ያሉት የቴአትር አዳራሽ ማደስ እንዲሁም በማዘጋጃ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አዳዲስ መገልገያዎችን የአካተተ ነው። እድሳቱ የተጠናቀቀው የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ የሕፃናት መዋያ፣ ቤተመጻሕፍት፣ የሥልጠናና የምርምር ክፍሎች፣ ክሊኒክ፣ የቴአትር አዳራሽ፣ ስብሰባ አዳራሾች፣ የሠራተኞች እና የባለጉዳዮች መመገቢያ አዳራሽና የተለያዩ ቢሮዎችን ያቀፈ ሲሆን፤ በቂ የመኪና ማቆሚያ፣ አረንጓዴ ሥፍራዎችንና የከተማ ግብርናን አካቶ የያዘ ነው።

ቤተ መንግሥት-ስማርት የመኪና ማቆሚያ

ዓለም አቀፍ የግንባታ ጥራቱን ጠብቆ የተገነባው ግራንድ የመኪና ማቆሚያ በቀን 1000 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ ዐቅም አለው። ወደ ታች አራት የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች የያዘውና 9000 ካሬ ሜትር ላይ የዐረፈው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ግንባታው ሦስት ዓመታት ያህል ወስዷል። ከግል ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የአንበሳና የሸገር ባስ ማቆሚያ ቦታ ያለው ሲሆን፤ በውስጡም የተለያዩ ሱቆች፣ አምፊ ቴአትር ቤትና ቢሮዎችን አካቶ ይዟል። ዘመናዊነትን የተላበሰና ከታች ግራውንድ እስከ ላይ ድረስ የሚያወጣ የራሱ የሆነ የመኪና ማጓጓዣ አሳንሰር አለው። ጎብኚዎችን ከአንድነት ፓርክ ጋር ቀጥታ የሚያገናኝ ድንቅ ዋሻም በማዕከሉ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ግራንድ የመኪና ማቆሚያ አምፊ ቴአያትር፣ ባህላዊ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆች እና ሌሎች መስኅቦችን የአካተተ ነው። የፓርኪንግ ሕንጻው ለብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ ለሳይንስ ሙዚየም፣ ለወዳጅነት አደባባይ ምዕራፍ ሁለት እና ለሌሎችም የፓርክ መዳረሻዎች ከመስቀል አደባባይ እስከ አብርሆት ቤተመጻሕፍት የጎብኚዎች ማዕከል ሆኖም ያገለግላል።

የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር

በ18 ወራት ውስጥ በሦስት ቢሊዮን ብር በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተገነባው የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር ቴክኖሎጂ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ፕሮጀክት መሆኑ የተመሰከረለት ነው። የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር ፕሮጀክት በዓይነቱ ልዩ የሆነና እንደ ሀገር በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘመኑን የዋጀ አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ይዞ የመጣ ነው። የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ የደኅንነት ጥበቃ ሥርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና ማቆም የሚያስችል ሥፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ስፖርት መሥሪያ ቦታዎች፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ መናፈሻ፣ አምፊ ቴአትር፣ የልጆች መጫወቻና መዋኛ ገንዳን የአካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት

ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ሞገስ የሆነውና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአስገነባው አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ምድር ውስጥ ያለውን ጨምሮ ባለ 53 ወለል ነው። 5 ዓመታት ከ11 ወራት የወሰደው ግንባታው 303 ሚሊዮን 500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበት የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቋል። ሕንጻው በውስጡ የቢሮ አገልግሎት ከሚሰጡ ክፍሎች በተጨማሪ እጅግ ግዙፍ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሙዚየም፣ ሱፐርማርኬት እና ሲኒማ ቤትን አካቷል። እስከ 1 ሺህ 500 መኪናዎችን መያዝ የሚችል ማቆሚያም አለው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአስገነባው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ በቁመቱ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንዲሁም በአፍሪካ 7ኛው ግዙፍ ሕንጻ እንደሆነ ተነግሮለታል። ሌሎች ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማትም ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታን ያላበሱ ረጃጅም ሕንጻዎችን ገንብተዋል። አሁንም እየተገነቡ ያሉ በርካቶች ናቸው።

የመንገድ ፕሮጀክቶች

የከተማ ዘመናዊነት አንዱ መገለጫ የመንገድ መሠረተ ልማት ነው። ዘመናዊቷ አዲስም በተለይም በለውጡ ዘመን እጀግ ውብና ዘመናዊ መንገዶች ባለቤት በመሆን ላይ ትገኛለች። በዓይነቱ ልዩ የሆነው የሳር ቤት ጎፋ ማዞርያ የፑሽኪን ጎተራ ማሳለጫ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። የማሳለጫ መንገዱ የአዲስ አበባን ስምና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን በሚመጥን መልኩ ዘምኖ የተገነባ ነው። የፑሽኪን አደባባይ ጎፋ ማዞሪያ- ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፤ የግንባታ ወጪው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በሁለት በኩል 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ፣ የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መሥመርና ተሽከርካሪዎችን ከሥርና ከላይ የሚያሳልፍ ዘመናዊ መንገድ ያቀፈ ነው።

የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት

የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታው ተጠናቆ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቋል። የሚኒስቴሩ ዋና መሥሪያ ቤት ጦር ኃይሎች በሚገኘው የቀድሞ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥፍራ ላይ የተገነባ ነው። ሕንጻው በ13 ሺህ ካሬ ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ባለ 5 ወለል እና ከ700 በላይ ቢሮዎች ያሉት ነው። በውስጡም የተለያየ ደረጃ ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ ቤተመጻሕፍት፣ የምርምር ማዕከላትና የተደራጀ የመረጃ ማዕከልን አካቷል። የሕንጻው ኪነ ሕንጻ ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና እና ፍልስፍና ተቀድቶ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከላይ ጦር እና ጋሻ ሆኖ ይታያል፤ ይህም የመከላከያ ሠራዊት ሀገር የመጠበቅ ሚናውን የሚያንጸባርቅ ነው። በአረንጓዴ ልማት የታጀበው ይህ ዘመናዊና ኢትዮጵያን የሚመጥነው ሕንጻ ሰው ሠራሽ ፏፏቴም አለው።

ዓድዋ ሙዚየም

የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት በአዲስ አበባ መሐል ፒያሳ ላይ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ግንባታ ነው። የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን አባቶቻቸውን ዘክረውና አንድነታቸውን አጽንተው ለትውልድ የሚያስተላልፉበት የጥንካሬ፣ የጀግንነት እና የነጻነት ማሳያ ነው። 4.6 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለትና በ12 ሔክታር መሬት ላይ የዐረፈው ይህ ፕሮጀክት ግንባታው በመገባደድ ላይይገኛል። የመዋቅር ግንባታ ሥራው መጠናቀቅን ተከትሎ የማጠቃለያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በዚህም የኤሌክትሪክና የውሃ መሥመር ዝርጋታ፣ የወለል ንጣፍ፣ የጅብሰም እና ሌሎች መሰል የማጠቃለያ ተግባራት በሕንጻው ውስጣዊ ክፍሎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። ሙዚየሙን ለአገልግሎት ለማብቃት ሥራዎች እየተፋጠኑ ሲሆን የፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀም 80 ከመቶ በላይ ደርሷል።

የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ከ2,000 እስከ 4,000 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት፣ የተለያዩ ቢሮዎች፣ ካፍቴሪያና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች፣ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የአውቶቡስና የታክሲ ተርሚናል፣ እንዲሁም ከሕንጻው ውጪ የቴአትርና የኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታዎች የሚይዝ ነው።

የላጋር የተቀናጀ መንደር

በአዲስ አበባ የድሮው ባቡር ጣቢያ ለገሐር አካባቢ በ360 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ የሚያርፈው የለገሐር የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ማዕከል እየተገነባ ያለና በውስጡ ከ4000 በላይ መኖሪያ ቤቶች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ግዙፍ የንግድ ማእከላት፣ መጋቢና ዋና መንገዶች እና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎችን የያዘ ግዙፍ መንደር ነው።

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቅርብ ርቀት የሚሠራው

ይህ ሁለገብ መንደር ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ አረንጓዴ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እና የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በበቂ ሁኔታ በውስጡ እንዳካተተ ማስተር ፕላኑ ያመለክታል። ከለገሐር በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ እየተገነባ ያለው ይህ መንደር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዱባዩ ኤግል ሒልስ ትብብር እየተሠራ የሚገኝ ነው።

የካ – 2 መኪና ማቆሚያ

ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የካ-2 መኪና ማቆሚያ ግንባታ ፕሮጀክት ከመሬት ውስጥ እና ከመሬት በላይ እየተሠሩ ባሉ ወለሎች 900 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዐቅም ያለው ነው። የከተማው አስተዳደር የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ አካል የሆነው የካ-2 መኪና ማቆሚያ (ሾላ ፓርኪንግ) ግንባታ የተወሰኑ ሱቆችና መኪና ማጠቢያን የአካተተ የመኪና ማቆሚያ ሕንጻ ነው። የግንባታ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከዘጠኝ መቶ በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚያስችል ምቹና አስተማማኝ ጥበቃ ያለው ቦታን በማቅረብ በሾላ ገበያ አካባቢ ያለውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጥረት በመቅረፍ የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት ያሳልጣል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 42 በመቶ ደረጃ ደርሷል።

የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል አምራችን ከሸማች በቀጥታ ማገናኘት የሚያስችል የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ግንባታ በማከናወን ላይ ነው። በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት አያት እና ወረዳ አምስት ሰሚት አካባቢ እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦላቸዋል። ማዕከላቱ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ አሁን ላይ ያለውን ሕገወጥ የገበያ ትስሥር ሰንሰለትን በማስቀረት እና የነዋሪውን ኅብረተሰብ የኑሮ ጫና በማቅለል ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። የሦስቱ የገበያ ማዕከላት ግንባታ በአራትና አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ45 እስከ 65 በመቶ መድረስ ችሏል።

ትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል

የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 አካባቢ በመገንባት ላይ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ሕንጻው በ7,507,175 ካሬ ሜትር ላይ ዐርፏል። ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ አንሥቶ 831,842,924.43 ብር ፈሰስ ተደርጎበታል። ሕንጻው በመጀመሪያ ወለሉ ላይ የደኅንነት መጠበቂያ ክፍል፣ ፓርኪንግ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የፋይናንስ ክፍል፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ የአደጋ መውጫና ሌሎች ክፍሎችን አካቶ ይዟል። በሁለተኛ፣ በሦስተኛና በአራተኛ ወለል ላይ ደግሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል። ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ እውን ሲሆን ለአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊና ቴክኖሎጂን የተላበሰ የትራፊክ አገልግሎትን ለመስጠት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 54 በመቶ ተጠናቋል።

የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት

የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ኮዬ ፈቼ ኮንዶሚኒየም አካባቢ የሚገኝና 14 ሔክታር መሬት ላይ የዐረፈ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ እስካሁን 811,683,914,94 ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ ከ91 በመቶ በላይ ተጠናቋል። በልማት ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑበት ታስቦ እየተገነባ ያለው ይህ ፕሮጀክት በውስጡ 300 ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ ዐቅም ያለው ማጠራቀሚያ፤ ለወተት ላሞች እርባታ ዓሥር ብሎኮች፣ ለሥጋ ከብቶች ማደለቢያ ዓሥር ብሎኮች፣ ለምርት መሸጫና ማሳያ 32 ሼዶች እንዲሁም አንድ የከብቶች መኖ ማከማቻና ሌላ የዶሮ መኖ ማከማቻና መጋዘኖችን ከተጨማሪ ሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ጋር አጣምሮ የያዘ ነው።

ለሚ አደባባይ

በ1.3 ቢሊዮን ብር በጀት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እየተገነባ ያለው ለሚ አደባባይ ለአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ አደባባይ ነው። ግንባታው በይፋ ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተጀመረው አደባባይ 14,400 ካሬ ሜትር ላይ ያርፋል። የሕዝብ ሥፍራ አደባባይ (ፐብሊክ ስፔስ)፣ የመኪና ማቆምያ፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ጂምናዝየሞች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ የሰርግና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ፣ ሱፐርማርኬት፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች፣ መጻሕፍት የማንበቢያ ሥፍራና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ይኖሩታል። አካባቢውንም በማስዋብ ከመንገድ አካፋዮች፤ አደባባዮችንና የእግረኛ መንገዶች ጋር ተናቦ የሚሠራ ሁለንተናዊ ፕሮጀክትም ነው። ፕሮጀክቶች በመሐል ከተማ ብቻ ሳይሆኑ በዳር አካባቢዎችም ማዳረስን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የተነገረለት የለሚ አደባባይ አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚገኝበት አካባቢ እየተገነባ ያለ ነው።

አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል

አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሴኤምሲ አካባቢ እየተገነባ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። የኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከሉ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ እየተገነባ የሚገኝ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች፣ ኮንቬንሽኖችና ዐውደ ርእዮች ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የአዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተኛ ባለአክስዮን ነው።

የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ

የአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለት ጥቅምት 2015 ዓ.ም ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ ለአዳዲስ ኢንዱስትሪያሊስቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች መተካት፣ የውጭ ምንዛሪ ችግርን መቅረፍ ታሳቢ አድርጎ እየተካሄደ ያለ ነው።

አደይ አበባ ስታዲየም

በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እየተገነባ ያለው አደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም 62 ሺህ ሰዎችን የመያዝ ዐቅም ያለው ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ የሕንጻውን መዋቅር ጨምሮ የስፖርተኞች ማረፊያ፣ ቢሮዎች፣ የጋዜጠኞች ማስተናገጃ ወዘተ ያካትታል። ለመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከ2.47 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል። በሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየሙ ፕሮጀክት ከሚካተቱት ሥራዎች መካከል የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም ይገኙበታል። በተጨማሪም ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራ መግጠምና ሌሎች በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የዘውዲቱ መታሳቢያ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ

በ1 ሺ 800 ካሬ ሜትር መሬት ቦታ ላይ የማስፋፊያ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሰፋፊ መታከሚያ ክፍሎች አሉት። ተኝቶ መታከሚያ 200 አልጋ፣ ለተመላላሽ ታካሚ 26 ክፍሎች፣ ለሕፃናትና ፅኑ ሕሙማን የሚሆን 50 አልጋ እንዲሁም የኦፕራሲዮን ማድረጊያ 6 አልጋ መያዝ የሚያስችል ዐቅም አለው። በተጨማሪም ራሱን የቻለ የኤክስ ሬይ (X ray)፣ ሲቲ ስካን (city scan ) ክፍል፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች ማካሄጃ ክፍሎች፣ 300 ሰዎችን ማስተናገድ የሚያስችል መሰብሰቢያ አዳራሽ እና ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት ማከማቻ ክፍል ያለው ግዙፍ የልማት ሥራ ነው። በአዲስ አበባ ከሚገኙት ሆስፒታሎች መካከል ተጠቃሽ የሆነውና ለዘጠና ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ይህ አንጋፋ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ በሆስፒታሉ ያለውን የሕሙማን አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታል።

“አዲስ ቱሞሮ”

ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ጎተራ አካባቢ ለባለሀብቶችና ዲፕሎማቶች የቤት ፍላጎት የሚሆን “አዲስ ቱሞሮ” የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ከቻይና መንግሥት ኩባንያ ጋር ሊፈራረሙ መሆኑን ገልጸው ነበር። ይሄው ዕቅድ ጎልምሶና ፍሬ አፍርቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ እና በቻይናው አምባሳደር ዚንዣዎ አማካኝነት የትግበራ ስምምነት ተፈርሟል።

ከላይ የተዘረዘሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን መሆን የአዲስ አበባ ብሩህ ዘመን እውነትም መቃረቡን አመላካች ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደምብ ቁጥር 110/2012 ዓ.ም. ተቋቁሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ያላቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከውሃ፣ መብራትና መንገድ መሠረተ ልማቶች ውጪ ግንባታዎችን እንዲያሠራ ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ምሬሳ ልኬሳ አስተያየት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

ጽሕፈት ቤታቸው በሚያሠራቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለ24 ሰዓታት ያለመቋረጥ የግንባታ ሥራዎች ይከናወናሉ። ከታች እስከ ላይኛው አመራር ድረስ በተዘረጋ የክትትልና ድጋፍ መስጫ ሥርዓት በመታገዝ ለግንባታ ሥራዎቹ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ችግሮች ከሥር ከሥር እየተቀረፉ ግዙፍ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው። በቀጣይ መሰል ግንባታዎችን በራስ ዐቅም ማካሄድ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰው ኃይል የማብቃት ሥራም እየተሠራ ነው። ውብ-አዲስ አበባ በአስገራሚ ፍጥነትና ዘመን ተሻጋሪ በሆነ የጥራት ደረጃ እየተገነባችና እያበበች በብርሃን ፍኖት የትንሳኤ ጉዞዋን ቀጥላለች።

ተስፋ ፈሩ

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You