ባዶ የምሳ እቃ እና ሌሎች ተረቶች

እውነተኛ ታሪክ ነው። በብዙዎች ጓዳ፣ በሕፃናት እና አዳጊዎች፣ በደጋግ እናቶች አእምሮ ውስጥ ትዝታው ተቀርጾ የሚኖር ታሪክ። የንጋት ሰቆቃዎች፣ የኑሮ ዘባተሎ፣ የድህነት ታሪክ….የባዶ የምሳ እቃ እና የባዶ ሆድ የድብብቆሽ ሰቀቀናም “ጨዋታ”፣ የባዶ የምሳ እቃ እና ሌሎች ተረቶች እውነተኛ ታሪክ። ልብ ወለድ ያልሆነ የተኖረ የአዳጊዎች እና የወላጆች ትዝታ።

የአውራ ዶሮው ጩኸት፣ የወፎች ጫጫታ የመንጋቱ ዜና አብሳሪ ድምፆች ናቸው። አዲስ አበባ ላይ የመኪናው፣ የወያላው፣ የአዛን፣ የቅዳሴው፣ የሰው ግርግር እንደየአካባቢው መንጋቱን ያበሥራሉ። ገጠር ይሁን ከተማ የማይለወጠው ጎሕ ይቀዳል፤ ጨለማ ለብርሃን ቦታውን ይተካል። ንጋት፣ ተስፋ፣ አዲስ ቀን ይሆናል።

አዳጊዋ መክሊት [ስሟ የተቀየረ] መሽቶ በነጋ ቁጥር በትናንሽ፣ ብሩህ ዐይኖቿ ተስፋ የቆረጠ የእናቷን ፊት፣ እንጀራ አልባውን ሞሰብ ማየት የዘወትር የንጋት ተግባሯ እንደነበር ትናገራለች። በነጋ ቁጥር የእሷ እና የችግረኛ እናቷ የትምህርት ፍላጎት እየገፋት ታስሮ ያልተፈታውን የምሳ እቃ አንጠልጥላ ለብዙ ቀናት እንደጓደኞቿ አስመስላለች። ቀኑ ሲገፋ ርኃቡ ሲጠናባት በሚታይባት ድካም እና እንቅልፍ ይታወቅባታል። በዚህ ጉዞ እያለፈች እሷ የትምህርት ቤት ምገባ መጀመሩ የባዶ የምሳ እቃ ሸክሙ እና የባዶ ሆድ የትምህርት ቤት ውሎዋ ተረት ሊሆን በቅቷል። መሰሎቿ ድካሙ አሸንፏቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተገድደዋል።

አዲስ አበባ በጉያዋ የደበቀችው፣ ደብቃ ያኖረችው ሰው የሚሻ የሰው ችግር ብዙ ነው። ይህንን የተረዳው ከተማ አስተዳደሩ ከተማዋ የምታመነጨውን የኢኮኖሚ ዐቅም የተቸገሩትን ለመርዳት እንዲያስችል በዕቅድ ተሠርቷል። ያ በመሆኑ የታወቁት ችግሮች ተፈትተዋል። የብዙ ወላጆችን እና አዳጊዎችን ሥነልቦና ከርኃብ በላይ የጎዱት የባዶ የምሳ እቃ ታሪኮች ተረት ሆነዋል። ከተማው ከሚያመነጨው ገቢ ውስጥ እስከ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ተማሪ ተስፋ ካሳሁን (ስሙ የተቀየረ) የሐምሌ 1967 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ስለ ምገባው ለመናገር ምገባው ሳይመጣ በተማሪዎች ላይ ምን ያስከተለው ጉዳትና ተጽዕኖ ነበረ? ምገባው ከመጣ በኋላስ የተገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ብሎ መናገር ያስፈልጋል በሚል ይጀምራል። የሱሉልታ ተማሪ ስለሆንኩኝ የኢኮኖሚውን ትቼው ጊዜና ጉልበት ላይ ያለውን ስናገር ቤተሰብ ቁርስና ምሳ አዘጋጅቶ ምሳ ቋጥሮ ከሰጠኝ በኋላ ትራንስፖርት ይዤ እስክመጣ የነበረው መሯሯጥ አድካሚና ጊዜ የሚፈጅ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ምሳው ከታሰረ የቆየ በመሆኑ ስበላው ለጤና ጥሩ አልነበረም። ሐምሌ 1967 ትምህርት ቤት ያለነው ተማሪዎች አብዛኞቻችን በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቤተሰብ የመጣን ስለሆንን ጠዋት ምግብ ሳንበላ የምንመጣ፣ አንዳንዴም ምሳ ላይቋጠርልን ስለሚችል በተዳከመሁኔታ ነበር ትምህርት የምንማረው። ምግብ የምንበላ እንኳን ቢሆን የተመጣጣነ ስላልሆነ ይደክመናል።

ይህም ስለሆነ ትምህርት በአግባቡ ስለማንከታተል የትምህርታችን ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድር ነበር። አሁን ግን ምገባው ከመጣ በኋላ ቀጥታ ከአልጋችን እንደተነሣን ተጣጥበን ተዘገጃጅተን ከቤት እንወጣለን። ከዚያም ወደ ትምህርት ቤት ጉዞ በማድረግ እናቶች ያዘጋጁልንን ምግብ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በመመገብ በንቁ ተሳትፎ ወደ መማሪያ ክፍላችን በመሄድ ትምህርታችንን እንከታተላን በማለት ለውጡን ያስረዳል።

ተማሪ ተስፋ ከምገባው ስለተገኘው ጥቅም ሲያስረዳ፤ በሳምንቱ ውስጥ አምስቱንም ቀን ንጽሕናው የተጠበቀ የተለያዩ የተመጣጠኑ ምግቦች ተዘጋጅተው ስለሚቀርቡልን፤ የድካም ሁኔታ የለብንም። ይህም ስለሆነ ትምህርታችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ እንማራለን። ከምገባው በኋላ ብዙ ተማሪዎች በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ምገባው የቤተሰብን የኢኮኖሚ ጫናም መቀነስ ችሏል። የምገባ መርሐ ግብሩ መጀመር ቤተሰብ ለእኔ ለምግብ የሚያወጣው ስለቀነሰለት እንዲሁም ዩኒፎርም፣ ቦርሳ፣ ደብተር እና እስኪሪብቶ የመሳሰሉት በመንግሥት በኩል ስለሚቀርቡ ቤተሰብ ለእኔ ለትምህርት አጋዥ ለሆኑ ሌሎች ነገሮች ወጪ በማውጣት የበለጠ በትምህርቴ ላይ እንድተጋ አድርጎኝ ከበፊቱ በተሻለ ውጤት ያለው ተማሪ እንድሆን አድርጎኛል ብሏል።

የዚሁ መርሐ ግብር ተጠቃሚ የሆነቸው ተማሪ ዝናሽ ቻሌ ድካም ቀርቶ ንቃት፣ የውጤት ማሽቆልቆል ቀርቶ ጉብዝና፣ መራራቅ ቀርቶ መቀራረብ፣ አብሮ መመገብ፣ የፈጠረው አንድነት በትምህርታቸው ውጤታማ መሆናቸውን ትናገራለች። ዝናሽ የምገባ መርሐግብር ለተማሪዎች የሰጠውን ጠቀሜታ ስታስረዳ “አንደኛ ትምህርታችንን በንቃት እንድንከታተል አድርጎናል። ሁለተኛ ከግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ አድርጎናል።

በግል ትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ዘወትር የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ተመግበው ይቀርባሉ። ስለዚህ ትምህርታቸውን በሥርዓት መከታተል ይችላሉ። እኛ ደግሞ የምገባ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ሳንመገብ የምንመጣ ተማሪዎች ነበርን። ያ ድካም እንዲሰማን ስለሚያደረግ ክፍል ውስጥ እንተኛ ነበር። በትምህርት ቤታችን ምገባ ከተጀመረ በኋላ ትምህርታችንን በንቃት መከታተል ችለኛናል። በውጤት ደረጃም የተሻለ ውጤት እያስመዘገብን ነው።” ትላለች።

በሌላ በኩል በመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወላጆች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት ይፈጥር የነበረው የሥነልቦና ጫና መቀረፉንም ትገልጻለች። ሁኔታውን የምታስረዳው፣ የምገባ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የተሻለ ገቢ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ምሳ ቋጥረው ሲልኩ ሌሎቻችን ባዶ እጃችንን መጥተን እነሱን ነበር የምናየው። አሁን ግን የምገባ ፕሮግራም መጀመሩ በመካከላችን ልዩነት እንዳይኖር አድርጓል። በአንድ መሶብ የቀረበ እንጀራ እና አንድ ድስት ውስጥ የተሠራ ወጥ ጓደኝነት ፈጥረን በአንድነት ነው የምንበላው። ይሄ ትንሿ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ውስጥ እንድትፈጠር ያደርጋል። የተቀበልነውን ለየብቻ ሳይሆን በጋራ አድርገን አንድ ላይ መመገባችን ይበልጥ ወንድምና እኅትማማችነታችን እንዲጠናከርና እንድንዋደድ እያደረገን ነው ብላለች።

ከምገባ ባለፈ የትምህርት ቁሳቁሶች እና የደምብ ልብስ ይቀርብልናል የምትለው ዝናሽ፣ የሚያስፈልገን እስክሪቢቶ ይሰጠናል። ደብተርና በተለይ በተመሳሳይ የጨርቅ ዓይነት አንድ ዓይነት የደምብ ልብስ ተዘጋጅቶልን መምጣቱ ትለቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው። መንግሥት ይህን የደምብ ልብስ ማቅረብ ከመጀመሩ በፊት አንዱ ተማሪ አዲስ ሌላው ደግሞ አሮጌና የተቀዳደደ የደምብ ልብስ ለብሶ መምጣቱ ሰፊ ልዩነት ያመጣ ስለነበር የሥነልቦና እና የአእምሮ ጉዳት ያደርስብን ነበር። አሁን ግን በየዓመቱ አዲስ ዩኒፎርም ተቀይሮ ስለሚሰጠን በመካከላችን ምንም ዓይነት ልዩነት የለም ትላለች።

ዝናሽ ሐሳቧን የምትቋጨው ለሴት ተማሪዎች ስለሚሰጠው ልዩ ድጋፍ “እኔ ሴት ተማሪ ነኝና በሴትነቴ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ይሰጠኛል። ከዚህ በፊት የንጽሕና መጠበቂያ የምናገኘበት ዕድል ስላልነበረን ተፈጥሯዊ የሆነው ወርኃዊ ዑደት ሲመጣ በጣም እንቸገር ነበር። አሁን ግን ከአምስተኛ ክፍል በላይ ላለን ሴት ተማሪዎች በሙሉ የንጽሕና መጠበቂያ ይቀርብልናል። በተጨማሪም ዘንድሮ ባይቀርብልንም ከዚህ በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታት ጫማና ቦርሳ ይመጣልን ነበር።” ስትል ምስክርነቷን በመስጠት ነው።

ከሦስት ዓመት በፊት መቶ ሺዎች የነበሩት ተማሪዎች ዛሬ ቁጥራቸው ከ700ሺህ በላይ አልፏል። ቁጥሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ስለሚጨምር ዘጠኝ መቶ ሺህ ተጠግቷል። አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ቁጥራቸው የአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ሕዝብ ቁጥር የሚያክሉ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ ትመግባለች።

የምግብ ዝግጅት ሂደቱም አብዛኛው የተማሪ ወላጆች እናቶች በብዛት የሚሳተፉባቸው ናቸው። ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች በትምህርት ቤት ምገባው ብቻ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

በማምሻ ዕድሜ ያሉ አረጋውያን፣ ስለኢትዮጵያ ታላላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ማኅበራዊ ጫና ለችግር ያጋለጣቸው ሰዎችም በሰው ተኮር ልማቱ የተረሱ አይደሉም። ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጃቸው 19 የምገባ ማዕከላት ምግብ የሻተ እጁን ታጥቦ የሚመገብባቸው ማዕከላት ተሰናድተዋል። ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ይባላሉ_ለብዙ ሺዎች የተስፋ ብርሃን ሆነዋልና።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ አዲስ አበባ ለሰው ተኮር የበጎ አገልግሎት ሥራዎች ቢሮ ከፍታ፣ አመራር መድባ፣ ሠራተኛ ቀጥራ እና በጀት መድባ ሰው ላይ ሠርታለች። ከ14 በላይ በሆኑ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተለይተው ውጤታማ ሥራዎችም ተሠርተዋል። ይህም በማኅበረሰባችን ውስጥ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጋራ የመረዳዳት፣ ደስታን ብቻ ሳይሆን ችግርን የመካፈል እሴቶቻችንን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ዐሻራ ነው።

ክረምት ይጠብቅ የነበረው የበጎ አገልግሎት ተግባር ዓመቱን ሙሉ እንዲሠራ ሆኗል። በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም ዕውቀትን መሠረት ያደረጉ መጻሕፍትን በመሰብሰብ፣ በሆስፒታል የሚገኙ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ፣ የደከሙ ቤቶችን በማደስ፣ በበዓላት ማዕድ በማጋራት፣ ለአካል ጉዳተኞች አጋዥ ተሽከርካሪዎች በመስጠት፣ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ሂደት መላውን የኅብረተሰብ ክፍል የማንቀሳቀስ ሥራ ተሠርቷል። ተማሪዎችም ትርፍ ጊዜያቸውን ለበጎ ዓላማ እንዲያውሉ ሆኗል።

በተቋሙ አማካኝነት ትብብርን፣ ደግነትን፣ መተጋገዝን ያጎለበቱ ዐቅሞችን በማስተባበር ከ20 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ ቤቶች ታድሰውና ተሠርተው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። የገንዘብ፣ የዕውቀት እና የጉልበት ትብብሩ በገንዘብ ሲገመት ወደ 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ሥራ ላይ ውሏል። በዚህ በየአመቱ እያደገ በመጣ ሰውኛ ተግባር በ2015 ዓ.ም ብቻ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ተሰባስቦ ለዚህ ሥራ ውሏል።

ደግነትን በተቋም እና በአሠራር ማስተባበር በመቻሉ የአዲስ አበባ አብነት ወደሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም ሰፍቷል ይላሉ አቶ አብርሃም። ይህ በማኅበረሰባችን ውስጥ የነበረውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ዕሴት እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ ባደረገው የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ለተሠሩ ሥራዎች በሙሉ የሀብት ምንጩ ሕዝብ ነው።

ባለሀብቶች እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ድረስ ለበጎ ዓላማ ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ ርኃብን የሻረ፣ ያፈሰሰ ቤት፣ የተቦደሰ ግድግዳ፣ የላስቲክ ጣራ የቀየረ ሆኗል። የአረጋውያንን ድካም፣ የእርጅና ዘመን ችግር ያስወገደ ሆኗል። ወጣቶችን ያሳተፈው የበጎ ፈቃደኝነቱ ሥራ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ያለውን ችግር ለይተው ትናንት ላሳደጓቸው ጎረቤቶቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ቤት በማደስ፣ አካባቢ በማጽዳትና በመንከባከብ፣ ብርድ ፀሐይ ሳይሉ በትራፊክ ደኅንነት ላይ በመሠማራትና ለሌሎችም በጎ ተግባራት ጊዜና ጉልበታቸውንም ሰጥተዋል፤ በዚህም የብዙዎችን ሕይወት መቀየር ተችሏል።

“አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ”

“ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” የሚለውን አባባል ከተማዋ ለበጎነት ሥራ ተጠቅማዋለች። ኮሚሽኑ ካሉት የበጎነት ማስፈጸሚያ መርሐ ግብሮች አንዱ “አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ” የሚለው ይገኝበታል። ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እስከ ክብርት ከንቲባዋ፣ ከከንቲባዋ እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሩ ድረስ ያለው አመራር ይህንን የደግነት ሥራ በተግባር ገልጧል። ይህ ከላይ የጀመረው የአመራሩ ተግባር ሌሎችን ለማነሣሣት እንደረዳቸው አቶ አብርሃም ይናገራሉ። የተቸገሩ ሕፃናትን ማሳደግ፣ ገንዘብ በቋሚነት በማዋጣት አንድ ሰው አንድ ቤተሰብ መደገፍ፣ ማዕድ ማጋራት ባህል እየሆነ መጥቷል።

ትኩረቱን ሰው ላይ አድርጎ፣ በሰዎች ስለሰዎች አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ያለው ተግባር ለትውልድ የሚሻገር ነው። ከሚመለከተው በላይ ተጠቃሚዎች ይናገሩታል። የባዶ የምሳ እቃ እና ሌሎች የሰቀቀን ታሪኮችን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተረት ያደረገ ሰውኛ ተግባር ሆኗል!

ዘመን መፅሄት ነሃሴ 2015

Recommended For You