ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የውጭ አገር ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ማብራሪያቸው «ተጨማሪ ሀብት፣ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ስላለብን የውጭ ባንኮች እናመጣለን። የአገር ውስጥ ባንኮች ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል» ሲሉ አሳስበው ነበር።
ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያን የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶችና ተቋማት ክፍት የሚያደርገው ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውሳኔውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ መንግሥት ፖሊሲው ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው የፋይናንስ ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ ውጤታማነትና ቀልጣፋነት በመጨመር፤ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲሳለጥ ለማድረግ መሆኑን ጠቁሞ፤ አዲሱ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል። ፖሊሲው ከዚህ በተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲጎለብት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነትን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ያስችላል። የዘርፉን አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያግዛል ሲል ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሎ ነበር።
ዘመን መፅሔት መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ክፍት ማድረጉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና በባንክ አገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚኖረውን አጠቃላይ አንድምታ አስመልክታ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ቀደምት ተዋናይ ከሆኑት የህብረት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዛፉ ጋር ቆይታ አድርጋለች፤ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ዘመን፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዴት አገኙት ?
አቶ ዛፉ፡- ዘገየ እንጂ አዲስ ነገር ሆኖ አይደለም ያገኘሁት። እኔ ወደአገር ቤት ከመመለሴ በፊት ለ 18 አመታት ያህል ከአገር ውጪ ነበርኩ። የመጨረሻዎቹን ዘጠኝ አመታት የመላው አፍሪካ ጠለፋ ዋስትና ድርጅት (African reinshurans corporation) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበርኩ። ኢትዮጵያም ከዚህ ድርጅት መሥራች አገሮች አንዷ ናት። ዋና መስሪያቤቱ ናይጄሪያ ሌጎስ ሆኖ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ቅርንጫፎች አሉት። የዛሬ 30 አመት እዚያ እየሠራሁ እያለ የአፍሪካ የፋይናንስ ገበያዎች ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት መሆናቸው አይቀርም ጥያቄው መቼ እና እንዴት ይከፈቱ የሚለው ነው ብዬ ተናግሬ ነበር። እኔ ይህን ስናገር አገራችን ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት እና አንድ የቁጠባና ቤቶች ባንክ ብቻ ነበር የነበሩት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበኩሌ የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ተወዳዳሪዎች ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ዝግ ሆኖ ይቆያል እንጂ ለዘለቄታው ዝግ እንደማይሆን እናገር ነበረ።
መከፈቱ የማይቀር መሆኑን የሚያመላክቱ ነገሮች ነበሩ። አንደኛ ከ18 አመታት በፊት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን አመልክታ ነበር፤ እስካሁን ድረስ ድርድር እየተደረገ ነው የሚገኘው። የአገር ውስጥ ገበያውን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ ድርጅቱን ለመቀላቀል እንደ አንድ መስፈርት የሚወሰድ ነገር ነው። ይሄ ባልተቋጨበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ተወካዮች በተገኙበት መድረክ ኪጋሊ ላይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት የሚሆንበት ጊዜ በቶሎ እንዲሆን ተጽዕኖ አሳዳሪ ናቸው። ገበያውን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረጋችን ጥሩ ነገር ነው።
እኛ ችግራችን ገና የግል ባንኮችና ኢንሹራንሶች እንዲመሠረቱ ሲፈቀድ ጀምሮ ሌላ ተወዳዳሪ እንደማይገባበት አድርገን ማስብ ጀመርን። አንዱ በሃይማኖት ሌላው በብሔር እየሔደ በጎጥ ነው ገበያ የፈለግነው፤ በመሠረቱ ይሄ ጥፋት ነው። አስቀድመን ገበያው ለውጭ ባንኮች ክፍት መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ መገንዘብ ነበረብን።
ዘመን፡- ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት የተደረገበት ጊዜ ላይ የሚስተጋቡ ሀሳቦች አሉ። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ባንኮች ራሳቸውን ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ለሚኖር ውድድር ዝግጁ ባላደረጉበት ሁኔታ ገበያው ክፍት መደረጉ ባልተረጋጋውየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ ፈተና ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው የሚሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ባንኮች አቅም እንዲያዳብሩ መንግሥት የተከተለው አካሔድ ከ20 አመታት በላይ እንዳስቆጠረ በመጥቀስ ውሳኔው ተገቢ ነው የሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ። እነዚህን ሁለት አቋሞች እንዴት ይመለከቷቸዋል?
አቶ ዛፉ፡- እዚህ አገር የተቋቋምን ኩባንያዎች ስለውድድር ብዙ ልምድ የለንም። ልክ እንደ ፖለቲካችን ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ነው የምናውቀው። በአንድ ወቅት አቶ ሌንጮ ለታ ይመስሉኛል ስለፖለቲካው ሲያወሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር አድርገው ሁለቱም ወገን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ነገር ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንብንና የማናውቀው ነገር ነው፤ ልምድ የለንም። ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ነው የምናውቀው ይሄ ልምድ መለወጥ አለበት ብለው ነበር።
ባንክና ኢንሹራንስ ማቋቋም ከጀመርን ወደ 30 አመታት ግድም ሆነን። አሁን ጊዜው እየተለወጠ መጥቷል። ኢትዮጵያ ብቻዋን ጥርቅም አድርጋ በሯን ዘግታ መኖር አትችልም። ከሌሎች አገሮች ጋራ መራመድ ይኖርባታል። ከሌሎች አገሮች ጋር መገበያየት ይኖርባታል። የኢትዮጵያ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ከጎረቤት አገራት አቻዎቻቸው ጋር መወዳደር፤ አንዳንድ ጊዜም መዋሃድና አብረው መሥራትም ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ጊዜው ላይ እኔ እንዲያውም ዘግይተናል ነው የምለው።
ዘመን፡- ባለፈው አመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚሆነው ቅድመ ሁኔታዎች ሲጠናቀቁ እና ባንኮች ሲዘጋጁ እንደሆነ ገልጸው ነበር። አሁን በመንግሥት በኩል ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቀዋል፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ተዘጋጅተዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ዛፉ፡- እስኪዘጋጁ እንጠብቅ ከተባለ ምንጊዜም አንዘጋጅም። ምክንያቱም 30 አመታት ተሰጡን፣ ምንም ያህል ወደፊት አልተንቀሳቀስንም። እሺ ስንት አመት ነው የሚበቃን 50 ወይስ 60 አመታት? በመሠረቱ 30 አመታት ብዙ ነበሩ ነገር ግን አልሠራንባቸውም።
ዘመን፡- የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ሊያበረክቱ የሚችሉት አወንታዊ አስተዋጽኦ ምንድን ነው ?
አቶ ዛፉ፡- በአሁኑ ሰዓት አገራችን ችግር አለብን። አገራችን በጣም ብዙ የውጭ እና የውስጥ እዳ አለባት። የውጭ ምንዛሬ እጥረት እጅግ አድርጎ ጠርንፎ ይዟታል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በሚመጣበት ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ኢንቨስትመንት ይመጣል። ይሄ ብቻ አይደለም የውጭ ባንኮች በአንድ ወይም በሌላ መልክ እኛ ገበያ ውስጥ ሲገቡ፤ ለምሳሌ የኬንያና ናይጄሪያ ባንኮች ቢመጡ እዚያ አገር ያሉ ወደ አገራችን መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ፈራ ተባ ሲሉ የነበሩ ተቋሞች ባንካቸው እዚህ ሲገባላቸው ይበረታታሉ። ነገር ግን የውጭ ባንኮች ወደ አገራችን እንዲገቡ መፍቀድ ብቻውን የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ዘላቂ መፍትሄ መሆን አይችልም። ዘላቂ መፍትሄ የወጪ ንግዳችንን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ገቢያችንን ከፍ ማድረግ ነው።
ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ በአገር በቀል ባንኮች፣ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ በኢንሹራንሶችና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደርና አለማሳደራቸው መንግሥት በሚፈቅዳቸው የአገልግሎት ዓይነቶች እንደሚወሰን የፋይናንስ ዘርፍ ሰዎች ይናገራሉ። መንግሥት ምን ዓይነት ማዕቀፎችን በአማራጭነት ማቅረብ አለበት ይላሉ?
አቶ ዛፉ፡- የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ይገቡበታል ተብሎ በፖሊሲ ደረጃ የቀረበው አራት መንገድ ነው። አንዱ መንገድ ቀድሞም የነበረ ገበያውን ለመከታተል እንዲችሉ ቢሮ እንዲከፍቱ መፍቀድ ነው። ሌላኛው መንገድ እንደ ውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተቆጥረውየራሳቸውን ባንክ አቋቁመው ወደ ሥራ መግባት ነው። በዚህ መንገድ ገብተው ተቀማጭ ገንዘብ ይቀበላሉ ሁሉንም ነገር እንደሌሎች ባንኮች ይሠራሉ ማለት ነው። ይህ ማለት የውጪ ባንክ ከኢትዮጵያውያን አክሲዮን መግዛት ሳያስፈልገው ራሱን እዚህ አገር እንዲፈጥር መፍቀድ ነው። ተጨማሪ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ሌላ መንገድ ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ ዕድል የሚሰጥ ነው። ኬንያ፣ ናይጄሪያ ወይም ሎንደን ያለ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ተደራሽ የሚሆንበት ነው። ሦስተኛው መንገድ የውጭ ባንኮች ከዚህ አገር ባንኮች ጋር ተቀናጅተው አዲስ ኩባንያ ማቋቋም ወይም ካሉት ባንኮች ውስጥ የባለቤትነት ድርሻን መግዛት ነው። ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ በበኩሌ የተሻለ ነው የምለው ይሄኛውን ነው።
የውጭ ባንኮች ወደአገራችን መግባታቸው በአንዳንድ ሁኔታዎች ችግር እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረጋል። እንዲሁ ዝም ብሎ ፈረንጆች “fly by night” እንደሚሉት አንድ ጊዜ ቦጭቀው የሚሄዱ ኢንቨስተሮች አይደለም የምንፈልገውና የምንጠብቀው። አገራችን ውስጥ ገብተው ተቀናጅተው ጥሩ ሥራ ሠርተው ውጤት አምጥተው እነርሱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እኛም እንድንጠቀም ነው የምንፈልገው። በተለይ ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት የውጭ ባንኮች እዚህ መጥተው ራሳቸውን ችለው ቢሯቸውን ከፍተው የሚቋቋሙ ከሆነ አንዳንድ ዋስትናዎች ያስፈልጉናል። እዚህ መጥተው የሚቋቋሙት ባንኮች በአገራቸው በምን ዓይነት ቁጥጥር ስር እንዳሉ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም እዚያ ያለ ኪሳራ እዚህ ሊመጣ ይችላል። በእርግጥ እዚህ አገር መጥተው ሲቋቋሙ በአገራቸው ሕግ ሳይሆን በአገራችን ሕግ ነው የሚተዳደሩት። ብሔራዊ ባንክ ነው የሚቆጣጠራቸው፤ ስለዚህ የሚቀመጡ መስፈርቶች ይኖራሉ እነሱን ማሟላት አለባቸው። በአጭሩ ጥንቃቄ የሚወሰድባቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው።
ባንኮቹ አገር ውስጥ ካሉ ባንኮች የባለቤትነት ድርሻ ሲገዙ እስከ ምንያህል በመቶ ነው የሚወስዱት የሚለው በእጅጉ ወሳኝ ነገር ነው። ለምሳሌ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ድርሻ እንዲወስዱ ማድረግ ይጎዳናል። አሁን በብሔራዊ ባንክ የቀረበው ሀሳብ 30 በመቶ የውጭ ባንክ፣ አምስት በመቶ የውጭ ድርጅት ወይም ዜጋ እንዲሁም አምስት በመቶ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ በውጭ ሰዎች እና ድርጅቶች እስከ 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ መያዝ ይችላል የሚል ነው። ይሄ ብዙ ጥናት ተደርጎበት የቀረበ ነው። ለምን ያህል ጊዜ በዚህ ደረጃ እንደሚቆይ ገና አልተወሰነም። እኔ በበኩሌ ቀደም ሲል ጀምሮ ከ15 እስከ 30 በመቶ፣ ቢበዛ እስከ 35 በመቶ የሚል ሀሳብ ነበረኝ አሁን በብሔራዊ ባንክ የቀረበው ሀሳብ ከዚህ ብዙም የራቀ አይደለም።
በዚህ የባለቤትነት ድርሻ ይዞታቸው እስከ ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ የሚለው መወሰን አለበት። ምናልባት ሦስት አመት ሊሆን ይችላል፣ ከዚያ በኋላ ግን እንደሚታወቀው አሁን የሼር ገበያ ከአመትና ሁለት አመት በኋላ ስለሚከፈት ሼሮች እዚያ ላይ ሲሸጡ እነዚህ 30 በመቶ ድርሻ የነበራቸው የውጭ ባንኮች 70 እና 80 በመቶ አልፈውም መቶ በመቶ የባለቤትነት ድርሻዎችን ሊይዙ ይችላሉ። ቀደም አድርገን ብንጀምረው ኖሮ ለመጀመሪያ ሦስት አመት ይህን ያህል፣ ለተከታዮቹ አምስት አመታት ድግሞ የዚህን ያህል እያልን ረዘም ያሉ አመታት ልንወስድ እንችል ነበር። አሁን እየተጣደፍን ነው የምናደርገው፣ ምክንያቱም ከሚያስፈልገው በላይ ዳተኞች ሆነን ብዙ ቆየን። ነገር ግን ትክክለኛ ነገር እስከሆነ ድረስ ዘግይተናል በማለት ነገሩን ልናኮስሰው ስለማይገባ በአሁኑ ሰዓት ውሳኔ ላይ መደረሱ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።
ዘመን፡- ዘርፉን የሚመራው ብሔራዊ ባንክ የተሻለ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል ይዘው የሚመጡትን የውጭ ባንኮች ለመምራትና መቆጣጠር አቅም ገንብቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ ዛፉ፡- ብሔራዊ ባንክ ራሱ ባወጣው አንድ ሰነድ ላይ ራሱን እንደገና ማደራጀትና ማጠናከር እንዳለበት ይገልጻል። ቢያንስ ብሔራዊ ባንክ አሁን ባለበት ሁኔታ መቶ በመቶ ዝግጁ አለመሆኑን ማወቁና መገንዘቡ መልካም ነገር ነው። ይሄ ማለት አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋል ማለት ነው። ገበያው ለውጭ ባንኮች ይከፈታል ሲባል አሁንም ቢሆን የአመታት ዕድሜ ባይሆንም የወራት የዝግጅት ጊዜያት አሉ። ምክንያቱም ባንኮችም ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፣ ብሔራዊ ባንክም ራሱን ማዘጋጀት አለበት። እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ ዛሬ ተወስኖ ከነገ ጀምሮ ባንኮች መግባት ትችላላችሁ የሚባልበት ሁኔታ አይደለም።
ዘመን፡- የፋይናንሱ ዘርፍ ለውጭ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ክፍት ሲደረግ የኢትዮጵያ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ተወዳዳሪ ለመሆን የሚቸገሩበት አንዱ ጉዳይ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት ነው። ይህን ነባር ችግር ለመቅረፍ የፋይናንስ የስልጠና ተቋም ለማቋቋም ረዘም ላለ ጊዜ ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደገኛል?
አቶ ዛፉ፡- በአገር ደረጃ ከ25 አመታት በፊት ለፋይናንስ ተቋማት የሰው ኃይል ለማፍራት በደምብ ታስቦበት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በደብረዘይት መንገድ ከአቃቂ ከተማ መውጫ ላይ በስተግራ በኩል የሚገኝ አንድ ትልቅ ግቢ በኮንትራክተር ተሠርቶ እዚህ የኢትዮጵያ የባንክና ኢንሹራንስ ስልጠና ኢንስቱቲዩት ይቋቋማል ተብሎ ነበር። በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ለአዲስ አበባ ለዩኒቨርሲቲ ተሰጠ። ከጊዜ በኋላ በምዕጻረ ቃል ዩኒሳ ተብሎ ለሚጠራው የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተሰጠ። እባካችሁ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው የሰለጠነ የሰው ኃይልን ከየት ያግኝ? እያልን ስንወተውት ቆይተናል። አሁን እንደማውቀው ለብሔራዊ ባንክ ተመልሷል። ብሔራዊ ባንክ ይሄን ተቋም ሥራ ለማስጀመር ጥናት እያደረገ እና አንዳንድ ሥራዎችን እየሠራ ያለ ይመስለኛል ነው።
አንዳንዶቻችን ይህንን ተቋም ሥራ ለማስጀመር የሚደረገውን እንቅስቃሴ በበላይነት መምራት ያለባቸው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ናቸው ብለን እናምናለን። ብሔራዊ ባንክ ከ10 አመታት በፊት የውጭ ባንኮች ሲገቡ እነርሱን በደንብ ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንድንፈጥር በሚል ከዓለም ባንክ ከ13 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድር ወስዷል። አቅም ገንብተውበታል አልገነቡበትም የሚለውን እኔ አላውቅም። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ተቋሙ ለብሔራዊ ባንክ ስለተመለሰ ቢቋቋም ጥሩ ነው። እንዲያውም ኢንስቱቲዩቱ የምሥራቅ አፍሪካ የልዕቀት ማዕከል ሆኖ ቢቋቋም ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶች መናኸሪያነት ከዓለም ሦስተኛዋ አገር ስለሆነች ለእንዲህ ዓይነት የልዕቀት ማዕከል አመቺ ቦታ ናት። በአገር ውስጥ ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ከማሟላት አልፈን ከሌሎች አገራት ሰልጣኞች እየመጡ የሚሰለጥኑበት ተቋም እንዲሆን ማድረግ እንችላለን።
ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት በሙሉ ይህንን ተቋም ለመፍጠር የሚያስፈልገውን መዋዕለነዋይ ለማፍሰስ ዝግጁ ስለሆኑ የገንዘብ ችግር የለብንም። እኔ እንግዲህ ምን ችግር እንደያዘን አሁን ለጊዜው አልገባኝም። ከሁለት አመት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዢው ክቡር ዶክተር ይናገር ደሴ ኢንስቱቲዩቱስለሚቋቋምበት ሁኔታ ሀሳብ አምጡ ብለውን አንድ ስድስት ሆነን ጥናት አድርገን ኢንስቱቲዩቱ ባንኮችን፣ ኢንሹራንሶችን፣ ማይክሮ ፋይናንስን፣ ሊዝ ፋይናንስን እና ዩኒቨርሲቲን ያሳተፈ ሆኖ እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበን ነበር። ዩኒቨርሲቲዎች ያስፈለጉት ስልጠና ስለሆነና ወደፊት ሙያዊ የሆነ ዕውቅና ሊሰጥበት ስለሚችል ነው። ምክንያቱም ይሄ ተቋም ቢፈጠር መጀመሪያ ማድረግ ያለበት መካከለኛ አመራር ለሚባሉት በሥራ ላይ ላሉት በፋይናንሱ ዘርፍ ላሉት ሠራተኞች አሁኑኑ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠናዎች መስጠት ነው። ወደፊት ግን ጥናትና ምርምሮች ይደረጉበታል፤ ከዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶም ለድህረ ምረቃና ከዚያም በላይ ትምህርት ሊሰጠበት ይችላል። ይህን ጥናት አቅርበን የብሔራዊ ባንክ ገዢውን አነጋግረናል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቱን ፕሮፌሰር ጣሰውን ቀጠሮ ተቀብዬ አነጋግሬያለሁ፤ ለመሳተፍ ዝግጁ እንደሆኑ ነግረውኛል። ይሄ ነገ ዛሬ ሳይባል አሁኑኑ መደረግ ያለበት ነገር ነው። አሁን እንደምሰማው ደግሞ ይህንኑ ሥራ ለመሥራት በንግድ መልክ ተቋም ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ። በእኔ እይታ በአሁኑ ጊዜ አቅማችንን በያለበት ከመበታተን አንድ ላይ ሆነን ሙያተኞችና ተቋማት ተሳትፈውበት ሕዝብና መንግሥት በጋራ አንድ ተቋም በቶሎ ብናቋቁም በጣም ይጠቅማል።
ዘመን፡- በመንግሥት በኩል የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ ያስፈለገው «ተጨማሪ ሐብት፤ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ» ማግኘት መሆኑን ጠቅሰው ነበር። በአንጻሩ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር ከመቶ ብር በላይ እየተመነዘረ ይገኛል። ይህ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ምን ዓይነት ጫና ይፈጥራል ? መንግሥት ሁኔታውን ለዘለቄታው ለመቆጣጠር ምን ዓይነት እርምጃዎችን መውሰድ አለበት?
አቶ ዛፉ፡- መንግሥት ጥቁር ገበያውን በተመለከተ በቅርቡ እርምጃዎችን ወስዷል። እንዲህ ያለ ተጨማሪ እርምጃ ይውሰድ ለማለት እቸገራለሁ። ነገር ግን ምንድን ነው አስቀድሞ ማሰብና ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በተወሰነ ደረጃ ተንብዮ እንዳይሆኑ ዝግጅት ማድረግ ላይ አገራችን ውስጥ ችግር አለብን። የፋይናንስ ዘርፉ አንዱ የዚህ ችግር ሰለባ ነው። የተናጠል እርምጃዎች ይወሰዳሉ። እኔ እንደሚገባኝ ይህ ከግንዛቤ ማጠር እንጂ ሆነኝ ተብሎ ለተንኮል የሚደረግ አይመስለኝም። ምክንያቱም በሙያው ውስጥ ብዙ ያልቆዩ ሰዎች የሥራው ጫና ተጣደባቸው፤ ምን ያድርጉ? የሚችሉትን ያህል ይሞክራሉ።
አንዳንድ የተወሰዱ እርምጃዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኗል። ለምሳሌ ፍራንኮ ቫሎታ ሲፈቀድ ሌሎች ብዙ ቀዳዳዎች ይከፈቱ ነበር። ይህንን ለማወቅ ኒውክሬል ሳይንስ መማር አያስፈልግም ነበር። ፍራንኮ ቫሎታ ሲፈቀድ ምንድን ነው የሆነው? በቀጥታ ላኪዎች አስመጪ ነው የሆኑት። ቡና ወደ ውጭ ይልኩና የውጭ ምንዛሬውን ወደ አገራችን በማምጣት ፈንታ ሌላ ዕቃ ማስገባት ጀመሩ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ የውጭ ምንዛሬው ላይ የሚያገኙት ትርፍ ያንን ኪሳራ ሸፍኖ ሌላ ገቢ ስለሚያስገኝላቸው ቡናውን ከተገዛበት ባነሰ ዋጋ በኪሳራ ለውጭ አገራት መሸጥ ጀመሩ። ቆይቶ ብሔራዊ ባንክ ሲነቃ ዋጋ ቆርጦ ወደ ውጭ አገር የሚላክ ቡና ከዚህ ዋጋ በታች መሸጥ አይቻልም የሚል ሕግ አወጣ።
ዘመን፡- ገንዘብ ሚኒስቴር የውጭ ምንዛሬን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የምግብ ሸቀጦች፣ መድኃኒቶችና የሕክምና ቁሳቁሶች ለማዋል በሚል ከውጭ የሚገቡ 38 ዓይነት ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት ታግደዋል። ክልከላውን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ዛፉ፡- ይሄ ብዙ ጊዜ የምንጠይቀው ነገር ነበረ። ሰው በልቶ ማደር እያቃተው ግብስብስ ነገር በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ መግባት የለበትም። ያለችንን የውጭ ምንዛሬ በትክክለኛ ቦታ ላይ ማዋል እንዲሁም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድሞ በመተንበይ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ተቸግረን ነው ምን እናድርግ? አገር የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ የላትም። ዕዳ መክፈልም አለባት። ተጽዕኖ የሚያደርጉብን አገራት ስላሉ ብድር ደግሞ እንደ ድሮ አይደለም። የተበደርነውን እንኳን ክፍያ ለማራዘም በዓለም ባንክ በኩል ጥያቄ አቅርበን እስካሁን ድረስ አበዳሪዎቻችን አንድ ላይ ቁጭ ብለው ተነጋግረው እንዲህ ያለ አስተያየት እናድርግላቸው አላሉም። አገራችን ጦርነት ውስጥ በመክረሟ በተለያየ መልኩ ጫናዎች እየመጡብን ነው። ሁሉነገር የተሳሰረ ነው። እኔ እንዲያውም አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ከዚህ የባሰ ነገር ውስጥም ልንገባ እንችል ስለነበር ተመስገን ነው የምለው። ችግር አለ ነገር ግን ጠንክረን መታገልና ማለፍ አለብን፤ እኔ እናልፋለን ብዬ ነው የማምነው።
ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
አቶ ዛፉ፡- እሺ እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ