“ኢትዮጵያ ችግሮቿን የምትፈታው በአንድነቷ ላይ ቆማ ነው” – ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የዘመን መጽሔት የህዳር ወር እትም አብይ ርዕስ አምድ እንግዳችን ናቸው።ዘመን ከፕሮፌሰር ያዕቆብ ጋር ባደረገችው ቆይታ ወቅታዊውን የኮፕ 27 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን፣ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እና ሌሎች ጉዳያችን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርባ የተብራሩ ምላሾችን አግኝታለች።መልካም ቆይታ!

ዘመን፡- በቅርቡ በአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረቱን ያደረገው 27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በግብፅ ሻርም አል ሼክ ተካሂዷል።መድረኩን እና የኢትዮጵያን ተሳትፎ እንዴት አገኙት?

ዶክተር ያዕቆብ፡- የዚህ ኮፕ 27 የተባለውና በግብጽ የመዝናኛ ከተማ ሻርማ አል ሼክ የተካሄደው ጉባዔ ብዙ ትዝብትን ያዘለና ያሳየ ነው ማለት ይቻላል።ከአሁን በፊት በተደረጉት ጉባኤዎች አውሮፓና አሜሪካ በጠቅላላው ምዕራባውያን ሀብታም ሀገሮች የዓለም አየር ለውጥ ትልቁ ችግር መንሰኤው እነሱ መሆናቸውን ሌሎች ሀገራት ነግረዋቸው እነሱም የተቀበሉ መስለው ነበር።ለዚህም ማካካሻ እንዲሆን ተገቢ የሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እጽዋትን ፣ ውሃን ፣ አሰፋፈርን እንደሁም የኢንዱስትሪ ተቋመትን እና የከርሰ ምድር ሀብትን በተሻለ እና በተቆጠበ ሁኔታ በመጠቀም በተለይም ለድርቅ ተጋላጭነት ያለቸው ሀገሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊ የሆነው ድጋፍ ተሰጥቶ በሀገር ፣ በአህጉርና በዓለም ደረጃ የአየር ንብረት ሁኔታ እንዲስተካከል ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

የበለጸጉ ሀገሮች የለሙት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ባስቀደመ እና ሌሎች ሀገራት ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ከግምት ባላስገባ መንገድ በመሆኑ፣ በተለይም ከኢንዱስትሪዎች ኬሚካል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚመነጨው የአየርም ሆነ የሌላ ዝቃጭ የዓለም አየር ንብረትን እንደሚበክል በግድም ቢሆን አምነው የልማት አቅጣጫቸውን በተቻለ መጠን ለአየር ንብረት ተስማሚ በሆነ አካሄድ በመምራት በካይ አካሄዶችን ለመቀነስ ብሎም ለሦስተኛው ዓለም ሀገራት ለደረሰባቸው ጉዳት ማካካሻ እንዲሆን የተሻለ የልማት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር፤ ይህን ቃላቸውን አልጠበቁም።በዘንድሮ ጉባኤ የተነሳው ዋናው ነገር ሀብታም ሀገሮች ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ጉዳቱ እየቀጠለ መሆኑን የሚገልጽ ነው።

በኢትዮጵያ በኩል የተገለጸው በጣም ጥሩ ነገር ይመስለኛል።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ባለፉት ቅርብ አመታት በተለይም የአየር ንብረትን በሚያሻሻልና የኢትዮጵያንም ልማት እጅግ በጣም ተስፋ ባለው መሰረት ላይ የሚያኖር ስራ እየተሰራ መሆኑን፤ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ የውሃ ትነትን የሚቀንሱ እና የውሃ ግኝቱን ከፍ የሚያደርጉ ተክሎችን ኢትዮጵያ በሰፊው መትከሏን በዚህም ሂደት 25 ቢሊየን ተክሎች መተከላቸውን ፤ ይሄንኑ አብነትም ለጎረቤት ሀገሮች ኢትዮጵያ በትሩፋትነት እንዳስተላለፈች ገልጸዋል።ይሄም ከአሁን በፊት ሀገራት በየሪፖርቶቻቸውና መገናኛ ብዙሀኖቻቸው ኢትዮጵያን ካመሰገኑትና ካሞካሹት ባሻገር ይህን በመሰለ የዓለም መድረክ በአደባባይ ይሄ ውጤት መተረኩ፣ ለሌሎች አብነት በሚሆን መንገድ ማንሳቱ፣ ሀገሪቱ በዚህ አቅጣጫ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ፈርጠም ባለ መንገድ መገለጹ በጣም ጥሩ ነገር ይመስለኛል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የራሷን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እየቀጠለች እንደምትሄድ ተገልጿል።ከአካባቢ ጋር ተስማሚነት ያላቸውን የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቿን በሚገባ እንደቀጠለች ይሄም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካበቢው አስተዋጽኦ ያለው ትልቅ ስጦታ እንደሚሆን ተነግሯል።ኢትዮጵያ የተያያዘችው ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ ትክክለኛ የእድገት አቅጣጫ መሆኑ በሚገባ እንደተገለጸ ነው ያስተዋልኩት።በተለይ በታዳሽ ኃይል በኩል የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ከራሷ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን የሚጠቅም መሆኑ በደንብ አጽዕኖት የተሰጠበት ነው።የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በህዳሴ ግድብ እና ለወደፊትም በሚሰሩ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ትብብር እንዲያደርጉና በቀና መንፈስ እንዲመለከቱ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ የሚያደርግ መሆኑንን እንዲረዱ፤ ሁልጊዜ የኢትዮጵያን አካሄድ በክፉ እያዩ እንደ ባላንጣ ማየት እንደማይገባቸው መልዕክት የሚያስተላልፍ አይነት ንግግርና መግለጫ ስለሆነ በኢትዮጵያ በኩል የተተላለፈው አወንታዊ ነው ብዬ አስባለው።

ዘመን፡-ከአመታት በፊት አንድ የዘርፉ ባለሙያ “እኛ መሬት ላራሹ ስንል ነው የከረምነው፤ ይህ ደግሞ መሬትን ካራሹ ጋር ማገናኘት ብቻ ሆነ።መሬትን ከውሃ ጋር ማገናኘት ቀዳሚ ቢሆንም በኢትዮያ ተረስቷል” ብለው ነበር።እርስዎም እንደ ዘርፉ ባለሙያነትዎ የኢትዮጵያ የውሃ ፖሊሲ ከመሬት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- መሬት ላራሹ የፖለቲካ መፈክር ነው።መሬት የሚገባው ለሚያርስ ወገን ነው እንጂ ከተማ ላይ ቁጭ ብሎ በጭሰኛ ጉልበት ለሚጠቀም አይገባም የሚል ነበር።ይሄ መፈክር ውሎ አድሮ መሬት የህዝብና የመንግስት እንዲሆን አድርጎታል፤ ይሄ እንግዲህ ከአርባ አመት በላይ ሆኖታል።ውሃና መሬት ቢገናኙ የሚባለው ትክክለኛ ነገር ነው።የአየር ንብረትንም የሚመለከት፣ ሰው ከአካባቢው ጋር ታርቆ አካባቢውን በሚገባ በተገቢው መንገድ መጠቀም እንዲችል ማሰብ ያለበት መንገድ ነው።ውሃ መቼም ለእርሻ፣ ለእጽዋት፣ ለእንስሳት፣ ለሰው ልጅ እና ለአካባቢው አየር ንብረት ሁሉ ጠቃሚ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሄ የተመሰከረለት ነገር ነው።

የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ ውሃውን እንዴት አድርገን ነው ጥቅም ላይ የምናውለውን ይመለከታል።ለእርሻ፣ ለእፀዋት፣ ለእንስሳት እንዲሁም ለሰው ልጅ ጤና እና ለተስተካከለ ኑሮ ውሃን እንዴት እንጠቀምበት የሚለው በሚገባ መጤን እና ስራ ላይ መዋል ያለበት ነገር ነው።የኢትዮጵያ መንግስት በየጊዜው የውሃ ፖሊሲ እያወጣ መመሪያዎችንም እያዘጋጀ የውሃ ልማትም እያካሄደ በሚኒስቴር መስሪያቤት ደረጃ የውሃ ጉዳይ ሲሰራበት ቆይቷል።በእኔ አስተሳሰብ የውሃ ልማት ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ገና በቂ የሆነ ትኩረት ያላገኘ መሆኑን አስተውያለሁ።ለምን በበርካታ አካባቢዎች ምንጮች እና ጨፌዎች እየደረቁ እንዲሁም ወንዞች የፍሰት መጠናቸውን እየቀነሱ ናቸው።ይህ የሆነበት ምክንያት የውሃው አጠቃቀምና ውሃን በመሬት ላይ የማስተዳደር ስራው በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ነው ማለት ይቻላል።ጨፌዎች የሚደርቁበት ምክንያት ገበሬዎች መሬት እየጠበባቸው ወይም ደግሞ በኢትዮጵያ በትክክለኛ መንገድ የመሬት አጠባበቅ ፖሊሲ ስላልወጣ፣ የመሬት አስተዳደሩ በትክክለኛ መንገድ ስላልተመራና ስራ ላይ ስላልዋለ እንዲሁም የተፈጥሮ አጠባበቅ ጠበቅ ባለ መንገድ ሳይሰራ ስለቆየ ገበሬውም አልሚውም ሁሉም መሬትን በዘፈቀደ ስለሚጠቀም መሬትና ውሃ ያላቸው ግንኙነት በአግባቡ ስለማይመዘን ነው።በዚህ ምክንያት ውሃ ባነሰባቸው አካባቢዎች ሰፊ የግብርና ስራዎች እየተሰሩ በአንጻሩ ውሃ በሚመነጭበት ማማ ላይ ውሃ መጣጭ ዛፍ እየተተከለ እና ሰፈራ እየተካሄደ ይገኛል።በቂ ውሃ በሌለበት ቦታ ከተሞች እየተቆረቆሩና እየተስፋፉ በሄዱ መጠን ውሀ ላይ ያለው ሽሚያ ያይላል።በመሆኑም ውሃን ለተገቢው ልማት ማዋል መቻል በጣም እየተወዛገበ ከልማቱ ጋር አብሮ ሳይስተጋበር እየቀረ የውሃ እጥረት በየቦታው ሲያጋጥም ይታያል።በአንዳንድ አካባቢዎች የከፋ የውሃ እጥረትም ብክለትም ይስተወዋላል።

የጉድጓድ ውሃም (በባለሙያ ብቻ ሳይሆን በተመልካች አይን ጭምር) ከድሮው ወደታች እየራቀ፤ ከጉድጓድ የሚገኝ ውሃ ከተገኘ በኋላ ቶሎ እያለቀና እየነጠፈ በዚህም የተነሳ የአዳዲስ ጉድጓዶች ቁፋሮ ዋጋ በጣም እየጨመረ ውሃ የማግኛ መንገድ ሁሉ ከበፊቱ እየቀነሰ እንደመጣ የሚያሳይ ነው።ስለዚህ የውሃ አጠቃቀም ከውሃ አስተዳደር ጋር አብሮ ተስተጋብሮ ካልሄደ፤ ያለንን ውሃ በሚገባ ለመጠቀም ካልተቻለና የውሃ አጠቃቀም በዘፈቀደ ሆኖ ከእርሻ ልማት ጋር፤ በገጠርም ሆነ በከተማ ከሰዎች አሰፋፈርና ከከተማ ልማትና ስፋት ጋር አብሮ በሚገባ ካልተያያዘ የውሃ እጥረት ማጋጠሙ የታወቀ ነው።ይህ ሲባል ደግሞ በየአመቱ ከሰማይ የሚወርድልን ውሃ እያነሰ መጣ ማለት አይደለም።የሜትሮሎጂ ሰዎች እንደሚናገሩት የዝናብ መጠን እየቀነሰ አይደልም።ነገር ግን የወረደው ውሃ በወንዝነት፣ በጨፌነትና በምንጭነት በሚገባ አስተዳደር ውስጥ ካልገባ የውሃ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልና አሁንም በየቦታው እያጋጠመ መሆኑ በጣም ግልጽ ነው።ውሃ በመኖሩ ብቻ የውሃ ጥቅም ይገኛል ማለት አይደለም።በውሃ ለመጠቀም ከፖሊሲ አንስቶ የአስተዳደር ሁኔታና ዕለት ከዕለት የሚደረገውን የአካባቢ ጥበቃ አስተጋብሮ ማየት ያስፈልጋል።

ዘመን፡- የግብጹ ፕሬዚደንት በቅርቡ በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት ለመፈረም ተአማኒነቷን እንድታሳይ ጠይቀዋል።ግብጾች ደጋግመው የሚያነሱት “አስገዳጅ ስምምነት” ለሁለቱ ሀገራት የሚኖረው ትርጉም ምንድን ነው ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- የግብጽ ፖለቲከኞች ፕሬዚደንቱንና ሌሎች የፖለቲካ እና የአካዳሚክ ሰዎች ተጠቃለው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር አንዳንዴም ከግብጽና ሱዳን ጋር አስገዳጅ ስምምነት ትፈርም እያሉ የሚያነሱት ነገር አለ።ይሄም በአረብ ሊግ ጉባዔ ላይ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በነበሩት ድርድሮች ላይም ግብጽ ኢትዮጵያ በውሃ አጠቃቀሟ አስገዳጅ ሰምምነት ታድርግ ስትል ቆይታለች።በህዳሴ ግድብ ድርድር ጊዜ ትልቁ ማፋረሻ የነበረው ይሄው ግብጽ ይዛው የደረቀችበት አስገዳጅ ስምምነት የሚል ሀሳብ ነው።ግብጾች አስገዳጅ ስምምነት የሚሉትን ጉዳይ በደምብ ብናጤን አንደኛ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሞላው ግብጽ በምትፈልገው የጊዜ ቀመር እንዲሆን የሚጠይቅ ነው።ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰራ ያለ ቢሆንምትልቅ ግድብ ስለሆነ የጋራ ጽህፈት ቤታችንን አዲስ አበባ ወይም ግድቡ የሚሰራበት ቦታ ጉባ አድርገን በጋራ እናስተዳደረው የሚል ጥያቄ ነው።ከዚህ ሁሉ ደግሞ የከፋው የኢትዮጵያ መንግስት ከህዳሴ ግድብ ከፍ ብሎ የአባይን ውሃ ማልማት በሚፈልግበት ጊዜ አስቀድሞ ከእኛ ጋር ስምምነት ያድርግ ወይም ደግሞ ያስፈቅድ የሚል ሀሳብ የያዘ ነው።በእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ አስገዳጅ የሚሉትን ስምምነት እንድትፈርም ነው ግብፆች የሚፈልጉት።

የግድቡ አሞላል በግብጽ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ በታወቁ የዘርፉ ሳይንቲስቶች አንደላይ በመሆን ባጠኑት ቀመር መሰረት በሰባት አመታት እንዲሞላ ስምምነት ተደርጓል።ይሄ የህዳሴ ግድብ አሞላል የጊዜ ቀመር ሳይንሳዊ የሆነና የዘርፉ አዋቂዎች መርምረው ተነጋግረው የተስማሙበት ነው።ኢትዮጵያ ግድቡን እየሞላች ያለችው በዚህ መንገድ ነው።ግብጽ በምትፈልገው ረጅም አመታት በሚወስድ አሞላል ላይ ኢትዮጵያ እንደማትስማማ ተነግሯቸዋል።ኢትዮጵያ ጥቅሟ በማይጎድልበትና ሱዳንና ግብጽ በውሃ እጥረት በማይቸገሩበት መንገድ ታስቦ የተነደፈና እየተሰራ ያለ ግድብ ነው።ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለግብጽና ሱዳን ለመስጠት ፈቃደኛ ነች።ይሄ የመልካም ጉርብትና አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ግድቡን ማስተዳደርን በተመለከተም ኃላፊነቱ የግድቡ ባለቤት ሀገር እንጂ የሱዳንም ሆነ የግብጽ አለመሆኑ ግልጽ ነው።ኢትዮጵያ በራሷ መሬት ላይ በአንጡራ ሀብቷ የገነባችውን ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው እንዲያስተዳደድሩ አልፈቀደችላቸውም።ያንን ያልተፈቀደላቸውን እና ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ በአስገዳጅነት ኢትዮጵያ ትፈርምልን ነው የሚሉት፤ ይሄ የማይቻል ነገር ነው።የበለጠ የከፋው ኢትዮጵያ ወደፊት መቶም ሆነ ሺ ግድብ በምትሰራበት ጊዜ አስቀድማ ከግብጽ ፈቃድ ትውሰድ የሚለው ነው።ግብጽ እኔ እስካልተስማማሁ ድረስ ኢትዮጵያ የውሃ ልማት ማካሄድ አትችልም የሚል ሀሳብ አላት።ይሄን ኢትዮጵያ በፊርማ እንድታጸድቅላት ትፈልጋለች።ይህ ማለት ኢትዮጵያ ወንዞቿን ከማልማት ተቆጥባ እጅ እግሯን አጣጥፋ በመቀመጥ የግብጽን ይሁንታ ትጠብቅ ማለት ነው።ግብጽ እነዚህን አስገዳጅ ስምምነት ብላ የምታቀርባቸውን ሀሳቦች በአረብ ሊግ፣ በአፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በሚገናኙበት መድረክ ስትናገር ነው የምትውለው።በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት እንደሌላቸው ተነግሯታል።

ዘመን፡- የአባይ ግድብ እየተጠናቀቀ መምጣቱ በአባይ ወንዝ ላይ ለሚነሳው የፍትሃዊ አጠቃቀም ጥያቄ ይበልጥ ጉልበት ይሰጠዋል ወይስ የግብጽን የቅኝ ግዛት ስምምነት መሰረት የሚያደርግ የውሃ ድርሻዬ ይከበርልኝ ጥያቄን ያከረዋል ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- አሁን ግድቡ ለሦስት ዙር ተሞልቷል።በሦስቱም ሙሌት ግብጽም ሱዳንም ተጠቅመውበታል እንጂ አልተጎዱበትም።እንዳልተጎዱ ደግሞ በራሳቸውም አንደበት ተገልጿል።ሱዳን ከሞላ ጎደል ከአመታዊ የጎርፍ አደጋ ስጋት ድናለች።የሱዳንን መንደርና ከተማ የሚያጥለቀልቀው ውሃ በሚያመጠው ደለል ከመሞላትም ተርፋለች (ቀንሶላታል)። ውሃም ደግሞ በተመጠነ መንገድ እየሄደላት ስለሆነ የደረሰባት ጉዳት የለም።ግብጾችም ቢሆኑ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት እኛን አይጎዳንም አስቀድመን ተዘጋጅተንበታል ብለዋል።ግብጽ ተጎዳች ማለት አስዋን ግድብ ላይ ውሃ አነሰ ማለት ነው።አስዋን ግድብ ላይ ውሃ የሚቀንስበት ምንም ምክንያት የለም።ኢትዮጵያ ውሃ የምትሞላው ዝናብ በብዛት በሚዘንብበትና ጎርፍ በብዛት በሚገባበት የክረምት ወቅት እንጂ አመቱን ሙሉ ስላልሆነ ግብጽም ሆነች ሱዳን አይጎዱበትም።ከአሁን በፊት እነሱ ለመጠቀም የሚያስቡበት ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገሮች ውሃ እንዳይጠቀሙ የሚያግድና የሚያቅብ መንገድ እንደማይሰራ በተለይም አሁን ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ አንጻር ያደረገችው ነገር ትምህርት ሰጪ ስለሆነ በአባይ ወንዝ ላይ ለሚነሳው የፍትሃዊ አጠቃቀም ጥያቄ ተግባረዊ ምላሽ የሚሰጥ ነው።ወደፊት በሚሰሩት ግድቦችም ከዚህ የተለየ ነገር አይኖርም።

ዘምን፡- የግብጽ ፖለቲከኞች በሚዲያዎቻቸው የባህር ውሃን ማጣራትን ጨምሮ ለጉድጓድ ቁፋሮ ሰፊ ትኩረት መስጠታቸውን ሲገልጹ እና ዜጎቻቸው ውሃ እንዳያባክኑ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ሲያወጡ ይታያል።ግብጽ በዚህ ደረጃ የውሃ እጥረት ስጋት የደቀነባት ሀገር ነች ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ውሃ እንቆጥባለን፣ አዳዲስ ውሃ የማጣራትና የማበራከት ዘዴ እንከተላለን ሲሉ እኔ ራሴ ስሰማ ከሰላሳ አመታት በላይ ሆኖኛል።በየጊዜው ነው እንዲህ የሚሉት።ከውሃ አመንጪ ሀገሮች ከሚመጣ ውሃ አጠቃቀም ጋር አያይዘው መልካም አሰራርና መግባባትን ይፈጥራል ብለው የምር ቢያደርጉት ጥሩ ነበር።ግብጾች በዕቅዳቸው፣ በየጉባኤውና በየአደባባዩ የሚገልጹት ነገር ከሚሰሩት ተቃራኒውን ነው።እርግጥ ውሃ ከባህር አጣርተው ከጨው ለይተው መጠቀም የሚችሉበት ቴክኖሎጂ አለ።ይጎድለናል የሚሉትን ውሃ በዚህ ሊያሟሉ ይችሉ ነበር።ነገር ግን እስካሁን በበቂ እንዳላደረጉት የተረጋገጠ ነው።ጉድጓዶችን እንቆፍራለን የሚሉትንም ቢያደርጉት ጥሩ ነው።በመሰረቱ ከጉድጓድ ውሃ የሚገኘው ከኢትዮጵያ እና ከሌሎቹ አመንጪ ሀገሮች የሄደው ውሃ ወደመሬት ሰርጎ ከመሬት የሚያወጡት ውሃ ስለሆነ መልካም ነው።በብዙ ሺ ሜትሪክ ኪብ ውሃ ከግብጽ ከርሰ ምድር ስር እንደሚገኝም ይታወቃል።ይህን ሁሉ በአማራጭ ሊያለሙት ይችላሉ።

ከሁሉም በላይ የውሃ ብክነትን እንቀንሳለን የሚሉት ውሸት ነው።ግብጽ ውስጥ ውሃ ያለቅጥ ይባክናል።በርሃ ላይ በተሰራው አስዋን ግድብ ብቻ ከ10 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ይባክናል።ሁለተኛ ግብጽ ውስጥ የሚሰራበት የውሃ አጠቃቀም የጎርፍ መስኖ ጥንታዊ የሆነ የመስኖ አሰራር ነው።ውሃውን በቦይ እየወሰዱ ከትልቁ ቦይ በትንሹ ቦይ እያደረጉ ከዚያ ደግሞ በቀጭኑ ቦይ እያደረጉ እጽዋትና አትክልት ውስጥ ውሃ በጎርፍ ያሰራጫሉ።ይሄ በርሃ ውስጥ የሚሰራውን እርሻ ቢያለማም በእርሻ ቦታ ላይ የሚፈሰውና የሚንጣለለው ውሃ እጀግ በከፋ መንገድ ለትነት የተጋለጠ ነው።እዚያም ላይ ከ10 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ይባክናል።ይሄ ብቻ አይደለም አሁን ግብጾች የናይልን ውሃ ከተፈጥሮ ተፋሰሱ ውጭ በብዙአቅጣጫ እየወሰዱ እያባከኑት ነው።አንደኛ በርሃ ውስጥ በሰሩት ቶሽካ በሚባለው ትልቅ የእርሻ ልማት ከአምስት ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ያለ ውሃ ወስደው ያባክናሉ።ይሄ አንድ ትልቅ የማባከኛ መንገድ ነው።የናይልን ውሃ እንደገና በቀይ ባህር ከታች በመሬት ስር በቱቦ ወስደው በሲናበርሃ ላይ ሻርም አል ሼክ የሚባለውን አሁን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔው የተካሄደበትን ከተማ አልምተውበታል።በከተማው የሚገኘው የውሃ አገልግሎት የእርሻን ስራና ሌሎች የመንደር ልማቶችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ከናይል ወንዝ የሚገኝ ነው።ይሄም ትልቅ ብክነት ነው ማለት ይቻላል።አሁን ፕሬዚደንት አልሲሲ በቀይ ባህር ጫፍ ላይ በስዊዝ ካናል አጠገብ በጣም ትልቅ ዘመናዊ ከተማ እየገነቡ ነው።ይሄ በዓለም ላይ አዲስ ፕሮጀክት ተብሎ በእነሱ በኩል ትልቅ አድናቆት የሚቸሩት ነው።በርሃ ላይ ያንን ህንጻና መንገድ ለመገንባት የናይልን ውሃ ከተፈጥሯዊ ተፋሰሱ ውጪ ቆልምመው ወስደው ነው የሚጠቀሙበት።ስለዚህ ብዙ አይነት የውሃ ማባከን ስራዎች እያካሄዱ ስለሆነ ውሃ እየቆጠብን ነው ወይም ልንቆጥብ ነው የሚሉት ነገር ትክክለኛ አይደለም።ሌሎች ውሃ እየከለከሉን እኛ ግን ውሃ ቆጣቢ ነን ብለው ለዓለም ለማሳየት በአብዛኛው ለፕሮፖጋንዳ እና ሌሎችን ለመወንጀል የሚጠቀሙበት እንጂ ከባህር ውሃ ጨው ለይተው ለመጠቀም ከሚያደርጉት ሙከራ ውጪ የተቀሩት ጉዳዮች ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው።

ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ድርድር ስታራምደው በነበረው ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ ውስጣዊ ችግሯን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መፍታት መቻሏ ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ ይፈታል የተባለው በኢትዮጵያ በኩል በደምብ በትክክለኛው መንግድ የተቀየሰ ይመስለኛል።የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብጽ አማካኝነት እንዲሁም ምዕራባዊያን በደገፉት አቅጣጫ ባልተገባ መልኩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ተወስዶ ሁለት ጊዜ ክርክር ተካሂዶበታል።በሁለቱም ጊዜ የውሃ ጉዳይ የልማት ጉዳይ እንጂ የደህንነት ጉዳይ አይደለም በሚል በኢትዮጵያ በኩል በቀረበው ጠንካራ ክርክር ከዚያ ተመልሷል።ከዚያስ ምን ይደረግ ሲባል እንደችግር ከታየ በአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ መድረክ ይታይና መፍትሄ ይፈለግለት ተብሎ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት እየታየ ነው ያለው።ነገር ግን ግብጽና ሱዳን የያዙት ጉዳይ ውሃ የማይቋጥር ስለሆነና የአፍሪካ ህብረት ይህን በደምብ ስለሚረዳ ግብጾች በአፍሪከ ህብረት ጥላ ስር በሚመቻቸው መድረክ ላይ ለቀጠል አፍረው እስካሁን ድረስ እግራቸውን እየጎተቱ ያሉ ይመስለኛል።የአፍሪካ ህብረት ሊቃነ መናብርት ከአንድም ሁለት ሦስቴ ጉዳዩን ተከታትለዋል፣ ግብጾች ግን ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ ከመድረኩ እየሸሹ ነው የሚገኙት።የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን ይፈታ የሚለውን መርህ ኢትዮጵያ በሙሉ ልቦና የተቀበለችውና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከጸጥታው ምክር ቤት ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ያደረገችበት መንገድ ነው።

አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭትም የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሃት ጉዳይ ከጦርነት ይልቅ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት እንዲታይ ኢትዮጵያ ፈቃደኛ በመሆኗ ህብረቱ ሁለቱንም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረጉን አስተውለናል።ስለዚህ በኢትዮጵያ በኩል የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ መድረክ እንዲቃና የህዳሴ ግድብ ወይም የድንበሮች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአንድ ሀገር የውስጥ ግጭት ጉዳይም በህብረቱ ስር ቢታይ ዘላቂ ሰላም ይገኛል የሚል እምነት በሚገባ አጽንታ የያዘች ሀገር መሆኗን ነው የሚያሳየው።ይሄንን ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም እንደ አብነት ቢወስዱት አንደኛ አላስፈላጊ ካልሆነ ግጭትና ጉዳት ይተርፋሉ።ሁለተኛ የአፍሪካን ጉዳይ እያባባሱ በሚነሱ ቁስሎች ላይ ዘይት እየጨመሩ ጉዳዮችን በማይገባ ደረጃ እያከረሩ የራሳቸውን ዘላቂ ጥቅም በመፈለግ የሚማስኑትን አውሮፓዊያን እና ሌሎች የውጭ ኃይሎች መከልከያና ማገጃ ለእነሱ አመቺ አለመሆንን የሚያረጋግጥ መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ ይሄንን ከአንድም ሁለት ጊዜ አሳይታለች።ከአሁን ቀደምም የአፍሪካን ጉዳይ በሽምግልና እና በማመቻቸት ሰርታ ታውቃለች።በአልጄሪያና በሞሮኮ መካከል የነበረውን ግጭት እንዲሁም በናይጄሪያ ፌዴራል መንግስትና በቢያፍራ አማጽያን መካከል የነበረውን እጅግ የከፋ ግጭት በሽምግልና እንዲያልቅ እንዳመቻቸች ይታወቃል።አሁን ደግሞ በራሷ ጉዳይ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና የአፍሪካ ህብረት ጭምር ገብተው ሲያስማሙ መድረኩን መጠቀሙ ተገቢ መሆኑን ኢትዮጵያ አሳይታለች፤ በራሷም ሆነ በሌሎች ጉዳይ። ስለዚህ ይሄ በአፍሪካ መለመድ ያለበት ነገር ነው።ሌሎች ሀገሮችም ሁኔታቸውን ለማስተካከልና ለማሻሻል፤ ሰላም ለማስፈን ፤ ልማትን ወደፊት ለማራመድ ፤ ነጻነታቸውና ሉዋላዊነታቸው እንዲጸና እንዲሁም ሀገሮች በመካከላቸው ያለውንም ችግር ከጦርነት ውጭ በአፍሪካ ህብረት መድረክ መፍታት እንደሚችሉ ኢትዮጵያ በሚገባ ያሳየች ሀገር ናት።

ዘመን፡- ኃያላን ሀገራት እና የአህጉራት ተቋማት በአባይ ግድብ ድርድርም ሆነ በቅርብ በተካሄደው የሰላም ውይይት በታዛቢነት መግኘት የሚፈልጉት ለምንድን ነው ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው።ይህንን ለመገመት እንደሚቻለው እነሱ በተቻለ መጠን በተለይም በአፍሪካና በሌሎች ባልለሙት ሀገሮች ጥቅማቸው እንዲከበር ግጭት ባለበት ቦታ ሁሉ ከአንዱ ወይም ከሌላው ወገን ጋር የማበር ባህሪ አላቸው። እስካሁን ባለው ልምድ እንደምናስተውለው እነሱ የሚፈልጉት በድርድርም ሆነ በውይይት ሂደት የእነሱ ጥቅም መስመር እንዲይዝላቸው ለማመቻቸት ነው መገኘት የሚፈልጉት።የሚገኙት ፍታዊ በመሆን ነገሮች እንዳይበላሹ ለመከላከልና ሀገሮች ሰላማቸውን መልሰው እንዲያገኙ ለማድረግ ቅን ፍላጎትን ይዘው የሚሰሩ አይመስለኝም።ችግር በሚኖርበት ጊዜ እኛ ምን ትርፍ እናገኛለን፤ እኛን የሚያግዝ ነገርን እንዴት አድርገን እናመቻች ወይም እኛን በሚያግዝ መንገድ የተባለው ግጭት እንዴት መስመር ይያዝ ብለው በስሌት የሚያደርጉት ነገር ነው።ስለዚህ ለፍትህ፣ ለሌሎች ጥቅምና ለዓለም ሰላም በመቆም የሚያደርጉት ነገር እንዳልሆነ እስካሁን ድረስ ባለን ልምድና በተለያየ ሁኔታ በወሰድነው ግምገማ እንረዳለን።

ዘመን፡- የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አንድ በር ሲዘጋባቸው ሌላውን ማንኳኳታቸው አይቀሬ ነውና ቀጣይ አጀንዳቸው ሊያደርጉት ከአሁን እንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመሩበት የአባይ ግድብ ጉዳይ ዲፕሎማሲ ከዚህ በኋላ እንዴት ባለ አቅጣጫ መመራት አለበት ይላሉ ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ዛሬ ላይ ግድቡ 86 በመቶ ተጠናቋል።ሦስት ሙሌት ተካሂዶ ኤሌክትሪክማመንጨት ጀምሯል።ሌሎች ማመንጫዎችም እየተተከሉ ነው ያሉት።ስለዚህ ግድቡ ወደ መጠናቀቅ እየደረሰ ነው።ይሄን ግድብ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከሊቅ እስከደቂቅ በመሳተፍ ነው እየገነባ የሚገኘው።ስለሆነም ኢትዮጵያ ግድቡን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ቁርጠኝነት አሳይታለች። በግድቡ ላይ አልፎ አልፎ የተነሱና የተካሄዱ ሳንካዎችም እየተቀረፉ ግድቡ አሁን በጥሩ መንገድ ላይ ነው ያለው። አሰራሩ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ለሌሎች ደግሞ ጎጂ አለመሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነ ይሄንኑ በመግለጽ በዛ አቅጣጫ መቀጠል ትልቅ የዲፕሎማሲ መሳሪያ ይመስለኛል።ስለዚህ አዲስ ዲፕሎማሲ፣ አዲስ አይነት መንገድ፣ አዲስ አይነት አገላለጽ እና አዲስ አይነት ብልሃት የሚያስፈልግ አይመስለኝም።ይሄንኑ በሚገባ አጽንቶ በተግባር እያሳዩ መሄድ ያስፈልጋል።

ምናልባት እንደጉድለት ሊነሳ የሚችለውና ኢትዮጵያ ማሻሻል የሚገባት ነገር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ የምትሰራውን ስራ በሚገባ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳትታክት መግለጽ አለባት።በዲፕሎማቶቿ ፣ በየጊዜው ወደተለያዩ ሀገራት በሚላኩ ወኪሎቿ፣ በምሁራኖቿ ፣ በጋዜጠኞቿ እንዲሁም ደግሞ በተለያዩ መድረኮች አቋሟን ህዝቧና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቅላት የማድረግ፣ የማስተዋወቅና የማስረዳት ስራ በሰፊው መስራት ይኖርባታል።

ዘመን፡- በዓባይ ወንዝ ላይ ግብጾች የሚነዟቸውን የተዛቡ ትርክቶች ለማረም በኢትዮጵያ በኩል ምን መሰራት አለበት ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ግብጾች በአባይ ውሃ ላይ ብዙ የተዛቡ ትርክቶችን እንደሚያራምዱ ይታወቃል።አብዛኛው ስራቸው ደግሞ የተዛባና ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ትክክለኛ ያልሆነ እውቀት ለመፍጠር በማሰብ የሚፈጸም መሆኑ የታወቀ ነው።ኢትዮጵያ ግብጾች የሚሰሩትን መልካም ያልሆነ ነገር ተሻምታ እንደዚሁ ተመሳሳይ ነገር መስራት ያለባት አይመስለኝም።በኢትዮጵያ በኩል እየተሰራ ያለው ግብጽ በሰፊው ከምትሰራው የተሻለ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው።ኢትዮጵያ ስለ ድንበር ተሸጋሪ ውሃዎቿ፣ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ስላላት ትብብር እና ትብብሩን እንዴት አድርጋ እንደምታጎለብት ለአሁኑም ለሚመጣውም ትውልድ ማሳየትና ማስተማር አለባት፤ ይሄ በጣም ተገቢ ነገር በመሆኑ በዚህ መበርታት በጣም አስፈላጊ ነው።ነገር ግን ግብጽ የሄደችበትን መልካም ያልሆነ እርምጃ ሁሉ ኢትዮጵያ እግር በእግር እየተከተለች በመቃወም ጊዜዋን ማጥፋት ያለባት አይመስለኝም።ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የምትሰራው ጥሩ ነገር ይመስለኛል።ይሄ በትምህርት፣ በተግባቦት መረብና እና በሌሎች መንገዶች አንጻር በበቂ ስላልተገለጸ እዛ ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው።ዋናው ጉዳይ በኢትዮጵያ በኩል የውሃ ሀብቱን በተመለከተ በመደበኛ ትምህርት፣ በምርምር፣ በስልጠና እና በቀጥታ ልማት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።

ዘመን፡- ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት ጦርነት ውስጥ በመቆየቷ በብዙ ተጎድታለች።አሁን ደግሞ ሰላም ወርዷል።ቀጣዮቹ አመታት ለኢትዮጵያ እንዴት ያሉ ይሆናሉ ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ችግር አጋጥሟት ያውቃል።እነዚያን ችግሮች እንደየሁኔታው በስቃይም በመሰዋትነትም በብልሃትም ፈትታ አሳይታለች።ከአድዋ ጀምሮ የጣሊያን ፋሺስት ወረራ አምስቱ አመታት ፣ የሶማሌና የባድሜ ጦርነቶችና ሌሎችም በየመሃሉ የተነሱ ግጭቶችና የርስበርስ ጦርነቶች ሁሉ አሉ።ነገር ግን ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት በየጊዜው ችግሯን የፈታችው በአንድነቷ ላይ ተመስርታ ነው።ለወደፊትም ችግሯን ልትፈታ የምትችለው በአንድነቷ ላይ ቆማ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያ መንግስትነቷ የቆየ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትነት የኢትዮጵያን ህብረተሰብ በአንድ መቆምን፤ በአንድ ተስፋ መንቀሳቀስን እና ጠላት በመጣ ቁጥር በአንድ ልቦና ቆሞ በአርበኝነት መመከትን እንዲሁም የውስጥ ችግሮችን በህዝቧ አንድነትና ትብብር መፍታትን ነው ያሳየው።

አሁንም ቢሆን ችግሮቿ የሚፈቱት የኢትዮጵያን አንድነት በጠበቀ መንገድ መሆን አለበት።ወደፊትም ቢሆን በአንድነትና በአንድ መንፈስ፤ በአንድ መድረክና በአንድ ሀገራዊነት እንዲሁም በእኩል የዜግነት መብት ላይ ቆማ ማናቸውንም ችግሮቿን ልትፈታ ትችላለች።ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን አንድነት በጠበቀ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ነው የኢትዮጵያ ልዕልና፣ ነጻነት፣ አንድነትና ሰላም የሚገኘው፤ ይሄ በጥቅሉ ነው።ኢትዮጵያን በተሸረፈ መንገድ ከተመለከትናት ፤ በመንደር ከመዘንናት፤ ኢትዮጵያን በሃይማኖት ብቻ ከመዘንናት፤ ኢትዮጵያን በቋንቋ ብቻ ከመዘንናት፤ ኢትዮጵያን በደጋ ወይም በቆላ ብቻ ከመዘንናት፤ ኢትዮጵያን በዚህ ባህል ወይም በዛ ባህል አንጻር ብቻ ከመዘንካት በተሸራረፈ መንገድ ችግሯ ሊፈታ አይችልም።

የኢትዮጵያ አንድነት ማለት የኢትዮጵያውያንን መብት የሚያጎድል ሳይሆን የሚያሟላ ነው መሆን ያለበት። እስካሁን የኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቆ የቆየው በአንድነቷ ነው።አንድነቷ ካለ ሰላም ይሰፍናል፤ ከፍ ያለ የወደፊት ብልጽግና ይገኛል፤ ጠላቶቿንም ማሸነፍ ትችላለች። አንድነቱ ከሌለ ግን እዚህም እዚያም ጦርነት፣ መጨፋጨፍ፣ መናናቅ፤ መጎነታተልና በሆነ ባልሆነ ግጭት ወስጥ መግባት ይከተላል።ስለዚህ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እና ከታሪክ አንጻር ስለወደፊቱ በእኔ በኩል የሚታየኝ የህብረተሰቡ ዕኩልነት፤ በፍትህ መተዳደር፤ በልማት ጎዳና መጓዝ፤ የሚሰራ የሚተጋ መንግስት ማበጀት እና የዜጎች ክብር መረጋገጥን ጨምሮ ነባራዊ ልዩነቶችን በሚገባ ያጤነ ለሁሉም የሚሆን የአንድነት ንጣፍ ካለ ለሁሉም ነገር መፍትሄ የሚገኝ ይመስለኛል።

ለአንዳንድ ሰው አንድነት ጨቋኝነትና ጨፍላቂነት ሊመስለው ይችላል።አንድነት ጨፍላቂና ጨቋኝ መሆን የለበትም።አንድነት የሚያስተሳስር፤ የሚያስተባብርና በተቻለ መጠን የሚያስተጋግዝ ሆኖ ማህበረሰቡ በፍትህ አንገቱን ቀና አድርጎ ደረቱን ገልብጦ በየቦታው በዜግነቱ ተከብሮ ንብረቱን፣ ነጻነቱን እና ክብሩን ጠብቆ ያልተጨፈለቀ መብት ኖሮት ሲኖር ነው ኢትዮጵያ የምትጸናውና የምትለማው።ነገር ግን አንድነት በሌለበት መድረክ፣ አንድነት ባልሰፈነበት መንፈስ፣ አንድነት ዋና የሀገር መቆሚያ ባልሆነበት ሁኔታ እንዲሁም አንድነት የኢትዮጵያን መንግስትነት በማያጸናበት ሁኔታ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋን ማየት በጣም አዳጋች ይመስለኛል።

ዘመን፡- ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ለጥያቄዎቻችን የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን፡፡

ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ተስፋ ፈሩ

Recommended For You