- “በሚቀጥለው ዓመት አዲስ ስርዓተ ትምህርት ይተገበራል”
- “ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸው በሰጡት ፈተና ብቻ የሚለኩበት ሁኔታ ከ2015 ዓ.ም ማብቂያ ጀምሮ ያበቃል”
- “በጦርነት ከወደሙት ትምህርት ቤቶች መቶ ያህሉን መልሶ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው
- “የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ከተማሪዎች ክልል ውጪ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት ታቅዷል”
- “ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግስት ጥገኝነት የተላቀቁ ነጻ ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው”
የዘመን መጽሔት የሐምሌ ወር እትም የአብይ ርዕስ አምድ እንግዳ ያደረግናቸው የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩን እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ፓርቲ መሪውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ነው። ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጋር ባደረግነው ቆይታ የትምህርት ዘርፉን ፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን እና የሚመሩትን ፓርቲ የተመለከቱ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸዋል እንደሚከተለው ይቀርባል።
ዘመን፡- በአንድ በኩል ከገዢው ፓርቲ በመቀጠል በርካታ አባላትን ያቀፈ ሀገራዊ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪ በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ነዎት። ሁለቱን ግዙፍ ኃላፊነቶች እንዴት እያስኬዷቸው ነው ያሉት?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፡- በተቻለ መጠን ሁለቱንም መስራት በሚገባኝ ልክ ለመስራት እሞክራለሁ። የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት በጣም ይከብዳል። ትልቅ ተቋም ነው። በተለይም ብዙዎች የሚስማሙባቸውን ችግሮቹን ለመፍታት በጣም ብዙ ነገሮችን መነካካት የሚፈልግ ሆኖ ነው ያገኘነው። በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ስራው ይበዛል ነገር ግን በዛ ምክንያት ሌላውን ኃላፊነቴን ዝም ብዬ አልተውኩትም። ሁለቱንም አንድ ላይ ለማስኬድ ነው የምሞክረው።
ዘመን፡- ሁለቱን ኃላፊነቶች ያለችግር ጎን ለጎን እያስኬዱ እደሚገኙ እየነገሩኝ ነው ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ያለችግር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም። ስራ ስትሰራ ችግሮች ይኖራሉ። ችግሮቹን እየፈታህ መሄድ ነው። ከዛ አንጻር እስካሁን የምሰራውን ስራ የሚያስቆም ነገር አልገጠመኝም።
ዘመን፡- የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ ሆነው የገዢው ፓርቲ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆንዎ ላይ የሚና መደበላለቅ ያመጣል በሚል ጥያቄ የሚያነሱ ወጎኖች አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምድን ነው ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፡- ለዚህ ሀገር አዲስ ሆኖ እንደሆነ አላውቅም፤ ያልተለመደ ነገር አይደለም። በተለይ በአንድ ሀገር ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በአዘቦት ጊዜ ከሚደረገው የፖለቲካ ፉክክር ያለፉ ችግሮች እና አደጋዎች በሚያጋጥሙት ጊዜ ሀገሮች እነዚያን ችግሮች የልዩነት ምክንያት በማድረግ የሚመጡትን አደጋዎች በጋራ ለመቀልበስ የዚህ አይነት ሙከራዎች ያደርጋሉ። በብዙ ሀገሮች የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ለማንም ግልጽ ነው። የሀገሪቱ ህልውና ራሱ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ ተባብሮ ሀገር ለማዳን መስራት ጤነኛ ከሆነ ሰው ይጠበቃል ብዬ ነው የማስበው።
ዘመን፡- የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና መሰረት ለመጣል ያስችላሉ በሚል የተጀመሩት የሪፎርም ስራዎች የእስካሁን ሂደት ምን ይመስላል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ብዙ ነገሮች ስለሆኑ የሚሰሩት ውጤታቸውን በአንድ ጊዜ ለማየትና ለመለካት የሚያስችል ሁኔታ የለም። በተለይ ትምህርትን የመሰለ ትውልድን ለረጅም ጊዜ የሚቀርጽ ነገር በሁለት ሶስት ዓመት ውጤቱ አይታይም። ሲበላሽም ለብዙ ጊዜ ቆይቶ የተበላሸ በመሆኑ ለማስተካከልም የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነገር ነው። እኛ አሁን እያደረግን ያለነው የችግሮቹን ምንነት ለመረዳት አስፈላጊ ሆነው ባገኘናቸው ክፍሎች ላይ ተጨማሪ ጥናቶችን በማጥናት ለችግሮቹ ምክንያት ይሆናሉ የሚባሉትን ነገሮቸ መለየት ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ከትምህርት ማህበረሰብ ፣ ከመምህራን ፣ ከተማሪዎች እና ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በሰፊው በመወያየት ችግሩን በተመለከተ የጋራ ስምምነት አንዲኖር ማድረግ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ለሪፎርሙ አስፈላጊ የሆኑ የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ እና የትምህርት መሰረተ ልማቶችን መቀየር የመሰሉ በአብዛኛው የዝግጀት የሚባሉ ነገር ግን ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ከዝግጅትም ያለፉ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው ያለነው።
እነዚህ ስራዎች ብዙ ጊዜ የሚወስዱ እና በቶሎ ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገሮች አሉባቸው። ስለዚህ አስቸኳይ ብለን የለየናቸውን ስራዎች በአንድ በኩል እንሰራለን፣ በመካከለኛ ጊዜ የሚሰሩ ስራዎችን በሚመለከት ዝግጅት እናደርጋለን እንዲሁም ረጅም ጊዜ ለሚወስዱ ስራዎች ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ጥናቶችን ከማከናወን ጀምሮ ስራዎቹን እንዴት ባለ መዋቅርና መንገድ ብንሰራ ውጤት ማምጣት እንችላለን በሚል ዝግጅት እናደርጋለን። በረጅም ጊዜ የምንከውነው አንዱ ስራችን ማህበረሰቡ በትምህርት ዙሪያ ያለው የሞራል ክስረት በምን መልኩ እንደገና ይጠገናል የሚለው ነው። እንዲህ ያሉ ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚቀየሩ ስላልሆኑ የረጅም ጊዜ ስራ የሚፈልጉ ናቸው።
ዘመን፡- በ 2015 ዓ.ም. አዲስ ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሚመለከት ባለፈው ዓመት በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የተጀመረው አዲስ የስርዓተ ትምህርት ሙከራ ስለተጠናቀቀ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ይተገበራል። ክልሎች ለትግበራው የሚያስፈልጉትን መጽሐፎች ቋንቋ የመተርጎም ስራዎች እየሰሩ ነው። ከዚያ የሱሪ ባንገት ነገር እንዳይሆን ጊዜው ሲደርስ መጽሐፍ ወደ ማሳተም ስራ እንገባለን። በተመሳሳይ መልኩ የሁለተኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ተሰርቶ አልቋል ነገር ግን መፈተሽ ስላለበት በቀጣዩ ዓመት በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ ይሞከራል፤ ከዚያም በ2016 ዓ.ም. በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።
ዘመን፡- የመጀመሪያ ደረጃ ስርዓተ ትምህርቱ በሙከራ ትግበራ ወቅት ያጋጠሙት ችግሮች ነበሩ ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እንዲህ ያለ ስርዓት ሁለት ሶስት አራት ጊዜ የሚኬድበትና በየጊዜው እየተሻሻለ መጨረሻ ደረጃ ላይ ደረሰ እስከሚባል ድረስ ችግሮችን አጥርቶ ለመሄድ የሚጣርበት ነው። በዚህ ደረጃ ስለሆነ ሙከራው የሚካሄደው እስካሁን መሰረታዊ ነገሩን የሚቀይሩ ችግሮች ማጋጠማቸውን አልሰማሁም።
ዘመን፡- በቀጣይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሲተገበር ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ክፍተቶች አሉ ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ልንገምት እንችላለን። እንዲህ አይነት አዲስ ፕሮጀክት ሲዘረጋ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ በሚደረጉ ሙከራዎች ቆንጆ ሆኖ ቢወጣም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። ስርዓተ ትምህርትን የምናየው በወርቅ እንደተጻፈ የማይቀየር ነገር አድርገን አይደለም። በየጊዜው የዓለም እና የሀገራችን ሁኔታ እየተቀየረ ሲሄድ እየተሻሻለ የሚሄድ፣ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግል ሆኖ የሚዘጋጅ ሰነድ ነው። እስካሁን ካየነው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር ባለሙያዎችም ተገምግሞ ያሉበት ችግሮች በደምብ ጠርተው እንዲሰሩ ተደርጓል። ስለዚህ ከሞላ ጎደል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የትምህርቱን ስርዓት ያሻሽለዋል ብለን ተስፋ እያደረግን ነው።
ዘመን፡- በአዲሱ የሁለተኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት የስፖርት ትምህርት እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተሰጥቶ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ይቋረጣል። 9ኛ እና 10ኛ ክፍሎችም የትምህርት አይነቱ ክፍለ ጊዜ እንዲቀንስ ይደረጋል። በአንጻሩ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በኮመን ኮርስነት ይሰጣል። ይህ ለምን ሆነ ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የሁለተኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ገና በሂደት ላይ ያለ ነው። ከስፖርት ትምህርት ጋር በተያያዘ 11ኛ እና 12ኛ የክፍል ደረጃዎች ላይ ይቆማል የሚል ነገር ከኤክስፐርቶቹ ጋር በነበረኝ ቆይታ አልሰማሁም። ነገር ግን ያለቀ ነገር ባለመሆኑ የምንከታተለው ነገር ነው። በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የያዝነው አንድ ነገር ግን አጠቃላይ የስፖርት ትምህርትን በሚመለከት ዝም ብሎ በክፍል ውስጥ መስጠት ብቻ ሳይሆን በየትምህርት ቤቱ ጠንካራ የሆነ የስፖርት እንቅስቃሴ መኖር አለበት ብለን በትኩረት እየሰራን ነው። አሁን በአዲስ መልክ በምንሰራቸው ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ላይ ለምሳሌ በቂ የሆኑ የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች እንዲኖሩ እያደረግን ነው። የአእምሮ ብቃትና ቅልጥፍና ከሰውነት ብቃትና ቅልጥፍና ጋር አብሮ መሄድ አለበት።
እኛ ሀገር ትምህርት ቤቶች በስፖርት ዙሪያ ብዙ ነገር መስራት ሲችሉ ለዚያ የተመቻቸ ሁኔታ ስላልነበር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ አይደለም። በትምህርት ቤቶች መካከል የሚኖሩ ስፖርታዊ ውድድሮች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማበረታት ባለፈ ብዙ ተያያዥ ጥቅሞች አሏቸው። ለምሳሌ ማህበረሰቡን እና ትምህርት ቤቶቹን ያገናኛሉ። ወላጆች ልጆቻቸው በስፖርት እንቅስቃሴዎች ሲሳተፉ ሄደው ስለሚያዩ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጠንካራ ያደርገዋል። በስፖርት ብቻ ሳይሆን ከሙዚቃ ጀምሮ ስነጥበብ እና የእጅ ስራዎችን የመሰሉ ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ስርዓቱ የወጡትን ለመመለስ ነው እኛ የምናስበው። በስፖርትም በኩል የሚሰጠው ትኩርት ይጨምራል እንጂ ይቀንሳል የሚል እምነት የለኝም።
ዘመን፡- በቀጣዩ ዓመት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መውጫ ፈተና ለመስጠት እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በሙሉ አቅማችን እየተዘጋጀን ነው። የሚቀር ነገር አይደለም 2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ማብቂያ ላይ ይጀመራል። ከዚህ በፊት እንደነበረው ዲግሪ ዝም ብሎ የሚሰጥበት ነገር ሀገሪቱን አጅግ በጣም ክፉኛ ጎድቷታል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶች ፣ ከግል ኮሌጅ አመራሮችና ባለቤቶች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት ያደረግንበት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አዲስ ሀሳብ አይደለም ከዚህ በፊት ተሞክሮ ብዙ ተቃውሞ ስለገጠመው የሕግ እና ህክምና ትምህርቶች ላይ ብቻ ፈተናው እንዲሰጥ ተደርጎ ሌሎቹ ላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ተደርጎ ነበር። አሁን ግን በአጠቃላይ ከከፍተኛ የትምህርት ጥራት ችግር ጋር በተገናኘ ምንም ልንወጣው የማንችልበት ደረጃ ላይ በመድረሳችን ሁኔታውን ለማስተካከል ዩኒቨርሲቲዎቹ ራሳቸው በሰጡት ፈተና ብቻ የሚለኩበት ሁኔታ ከጀርባው ያለ ጠንካራ የሞራል መሰረት ይጠይቃል።
ከዚህ በፊት የነበረው አንዱ ችግር ዝም ብሎ ማሳለፍ የሚባል ነገር አለ። ተማሪዎች ከወደቁ የትምህርት ክፍሉን ድክመት ያሳያል እየተባለ የተመጣበት መንገድ ምን ያህል ሀገሪቱን እንደጎዳት ለውይይት የሚቀርብ አይደለም። እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ላለፉት ሰባት ወራት በትምህርት ዙሪያ ከሚሰሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶች እና የግል ኮሌጆች ባለቤቶች የለም መሆን የለበትም የሚል አይን ያወጣ ክርክር አልገጠመኝም። ሁልጊዜ የሚሰማው ለምን በእኛ ጊዜ የሚባል ነገር አለ ፤ ይሄ ደረቅ ክርክር ነው የሚሆነው። በአንድ በሆነ ጊዜ መጀመር አለበት ምክንያቱም በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ሀገሪቱን ክፉኛ ዋጋ እያስከፈላት ነው።
ለዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪዎችም ለወላጆችም የአንድ ዓመት የዝግጅት ጊዜ ሰጥተናል። ይህንን ጊዜ ተጠቅመው ስራቸውን ሰርተው መጠበቅ አለባቸው። እንደሚታወቀው ይሄ የመውጫ ፈተና የተማሪዎች ፈተና አይደለም። ከተማሪዎቹ በላይ የትምህርት ክፍሎችና የኮሌጆች/የዩኒቨርሲቲዎች ፈተና ነው። እኛ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ከመውጫ ፈተናው የምናገኘው ዩኒቨርሲቲዎቹ ምን እያደረጉ ነው ለሚለው ጥያቄ መልሰ የሚሆን ነገር ነው። ዩኒቨርሲቲዎቻችን በእርግጥም ተማሪዎችን እያበቁ ነው ወይስ የዲግሪ ወፍጮ ቤት እንደሚሏቸው ጊዜ እያስቆጠሩ የትምህርት ማስረጃ የሚሰጡ ናቸው የሚለውን የምንለይበት ነው።
ዘመን፡- እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአካባቢ ተወላጅነት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ለመሆን እንደ ዋነኛ መስፈረት ይወሰድ ነበር። ከፖለቲካ ተልዕኮ እና ትምህርትን ንግድ ከማድረግ ጋር በተያያዘም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ነጻነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ አካሄዶች ሲታዩ ቆይተዋል። ትምህርት ሚንስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ነጻነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለው ስራ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ደጅ ሊደርስ ይችላል?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፡- በየክልሉና በየዞኑ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል መንግስቱ ተቋማት መሆናቸው እንኳን ተረስቶ የዞኖች ተቋማት የሚመስሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚል ቅሬታ በማህበረሰቡ ውስጥ ስንሰማ ነው የቆየነው። በመጀመሪያ ለሁሉም ግልጽ ያደረግነው እነዚህ ዩነቨርሲቲዎች የክልል ንብረቶች አለመሆናቸውን እና የፌዴራል መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ነው። የፌዴራል መንግስቱ ናቸው ስንል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚከፍለው ታክስ የተቋቋሙ ናቸው። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎችን የተወሰነ አካባቢ የሚጠቀምባቸው አድርጎ ማየት በጣም የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በግልጽ ስንናገር ቆይተናል።
የዩኒቨርሲቲዎች ነጻነት ግን ከዚህ ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም። ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጥሯቸው ሰብዓዊ ፣ ዓለም አቀፋዊ እና ዕውቀትን የምንሻባቸው ቦታዎች ናቸው። እውቀት ዘር እና ሃይማኖት ስለሌለው አለም አቀፋዊ የሆነ እውቀት መማሪያ ቦታዎች ናቸው። ስለዚህ እውቀትን መሻትን ዋናው ስራው አድርጎ የተፈጠረ ተቋም በመንገዱ ላይ እንቅፋት እንዳያጋጥመው ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ምክንያት ነው ነጻነት ባለባቸው ሀገሮች ዩኒቨርሲቲዎች ከዕለት ተዕለት አሰራራቸው ጀምሮ ስርዓተ ትምህርታቸውን እስከመቅረጽ ፣ ተማሪዎችን ራሳቸው በሚሰጧቸው ፈተናዎች ለይተው ምን ያህሉን እንደሚቀበሉ እስከ መወሰን ፣ ያላቸውን ገቢና ወጪ አስተካክለው ለማንም ግልጽ በሆነ መልኩ እስከመስራት እንዲሁም ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት ደግሞ መንግስት እንዲያስተምሩለት በሚፈልጋቸው ተማሪዎች በሚሰጠው የትምህርት ዕድል ቁጥር በስምምነት ተቀብለው እስከ ማስተናገድ የሚደርስ ነጻነት ያላቸው።
አሁን በእኛ ሀገርም አንድ የመንግስት ካድሬ እናንተን የሚቆጣጠርበት ምንም ምክንያት ስለሌለ በሁለት እግራችሁ ቆማችሁ መስራት የምትችሉ ተቋሞች መሆን አለባችሁ በሚል ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግስት ጥገንኝት እንዲላቀቁ በአጠቃላይ በመንግስት ደረጃ ስምምነት አለ። እንዲህ አይነት እርምጃዎች ሲወሰዱ በመንግስት እጁን ተይዞ ሲራመድ የነበረን ተቋም በአንድ ጊዜ ራሱን ችሎ እንዲሄድ ብትለቀው እናዳይሳካለት ነው የምታደርገው። እኛ ይሄ ነገር በደምብ ተሳክቶ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ሆነው መንግስት ምንም አይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው ለማድረግ እንፈልጋለን። ዕድሉን አበላሽተውት እንደገና በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ ይግቡ እንዳይባል በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል።
የረጅም ጊዜ ተቋም የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ነጻ እንዲሆን በማድረግ ሂደቱን እንጀምራለን። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስፈልጉ ሪፎርሞችን የሚሰሩ ከ80 በላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚሳተፉበት የለውጥ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው። እነዚህን እንቅስቃሴዎች ሲጨርሱ እኛም የቻርተር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን እያደረግን ያለነውን ዝግጅት አጠናቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንጀምርና በቀጣይ የበቁትን እና የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኙትን እየለየን ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ እያደረግን እንሄዳለን። የመንግስት ፍላጎት ቢቻል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሁሉንም ነጻ ዩኒቨርሲቲዎች ለማድረግ ነው።
ዘመን፡- በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ለማስተካከል ምን ምን ነገሮችን ነው ማድረግ ያለብን በሚል ከዚህ በፊት በትምህርት ሚኒስቴር የተሰሩ ጥናቶች አሉ። ለምሳሌ የመምህራን ብቃት ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ፣ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ፣ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን የብቃት ደረጃ ምን ይመስላል እያልን የተሰሩ ስራዎችን በሙሉ ነበር የፈተሽነው። በዚህ ሂደት አንዱ ያየነው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የመንግስት ትምህርት ቤቶች 99 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን አራት ደረጃ ያለው የብቃት ማዕቀፍ የማያሟሉ መሆናቸውን ነው። ከ 47 ሺ አካባቢ ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛ የሆነውን አራተኛ ደረጃ አሟልተው ተማሪዎችን ተቀበሎ ለማስተማርና ጥሩ የትምህርት ከባቢ ለመፍጠር የሚችሉ ናቸው ተብለው የተለዩት ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው።
ከታች ጀምሮ ልጆች መጥተው ትምህርት ለመማር የሚያስችል አከባቢ ውስጥ ነው ወይ የሚገቡት ብለን ስናስብ ጉዳዩ ለትምህርት ጥራት አንዱ ችግር መሆኑን እንረዳለን። ልጆች ሀሁ ብላችሁ ቁጠሩ ስለተባሉ ብቻ አይደለም ትምህርት የሚያገኙት፣ በአጠቃላይ ያለው ከባቢ ሁኔታ ለትምህርት የሚስብ እና ንጽህና ያለው መሆኑ በመሰረታዊነት አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን ከጎበኘን በኋላ በእርግጥም ዕድሉ ካለ አቅሙ በሚፈቅድ ጊዜ አንዱ መደረግ ያለበት ነገር የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ማሻሻል ነው የሚል ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር።
ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ደግሞ ወያኔዎች በእልህና ነውር በሚያሰኝ መንገድ ትምህርት ቤቶችን ማፍረስ እንደ ቁም ነገር አድርገው በመያዛቸው ወደ አንድ ሺህ 300 ያህል ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ፈርሰውብናል ፤ ሶስት ሺህ ገደማ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በጣም ተጎድተዋል። በተለይም ሙሉ ለሙሉ የፈረሱትን ትምህርት ቤቶች በአዲስ መልክ መገንባት አለብን። ስለዚህ በአዲስ መልክ መገንባት ያለብንን ትምህርት ቤቶች ለምንድን ነው እኛ በምናስበው ጥሩ ትምህርት ቤት በሚያሰኝ ደረጃ ለመስራት የማንሞክረው የሚል ጥያቄ አነሳን። ከባድ ይሆናል፤ የገንዘብ ችግር ይኖራል ነገር ግን ማህበረሰቡን እና ውጪ ሀገር ያሉትን ኢትዮጵያውያን አሰባስበን ከሄድንበት አያቅተንም በሚል ወደ እንቅስቃሴ ገባን።
መጀመሪያ ያደረግነው የወደፊቶቹ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ምን መምሰል አለባቸው በሚል ዲዛይን ማዘጋጀት ነበር። ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቹ የተከለሉ ቦታዎች ፣ ትምህርት ቤቱና ማህበረሰቡ የሚገናኙባቸው ቦታዎች እና ውጪ ከአጥሩ ጋር ተያይዘው ተማሪዎቹ የሰሩትን የአካባቢ ሰውም ያመረተውን ይዞ መጥቶ የሚገባያዩባቸው ቦታዎች እንዲኖራቸው ተደርገው ይሰሩ ተብሎ የትምህርት ዘርፍ ሰዎች ፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ፣ ከዚህ በፊት የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የገነቡ አካላት እና ሌሎችም በጋራ የተሳተፉበትን ዲዛይን አሰርተናል። ዲዛይኑን ለማዘጋጀት ሶስትና አራት ወራት ጊዜ ወስደናል። የተዘጋጀው ዲዛይን እንዲገመገም ተደርጎ ተወያይተንበት ይህ ይጨመር ያ ይቀነስ ካልን በኋላ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ የወደፊት ትምህርት ቤቶች ይሄን መምሰል አለባቸው የሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል። ሙሉ ለሙሉ አንድ አይነት ይሆናሉ ማለት ሳይሆን ቢያንስ ማዕቀፉ ወጥነት ሊኖረው ይገባል ነው ያልነው።
እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ግን ከአካባቢው ጋር በተያያዘ ሞቃታማ ወይም ቀዝቃዛ አሊያም ተራራማ ቦታ መሆኑን ከግምት ባስገባ መልኩ ዲዛይን ሊሰራለት ይገባል ብለን ከኢትዮጵያ የአርክቴክቶች ማህበር ጋር ተስማምተን እነሱም ለሀገር እንደሚደረግ አስተዋጽኦ ዲዛይኖቹን በነጻ ሊሰሩልን ተስማምተው አሁን ከመቶ በላይ ዲዛይኖች ተሰርተው እያለቁ ነው። የሚቀጥለው ዓመት መጠናቀቂያ ድረስ እስከ ሁለት መቶ እንደርሳለን ብለን እየሰራን ነው የምንገኘው። በቅርብ ጊዜ ይህ ክረምት ከመውጣቱ በፊት በሙከራ ደረጃ ሶስት አራት ትምህርት ቤቶች መገንባት እንጀምራለን። በፍጥነት ወደ ግንባታ መግባት የፈለግነው ትምህርት ቤቶቹ ምን ይመስላሉ የሚለውን በማየት ከክረምት በኋላ በስፋት ግንባታዎችን ለማከናወን ነው። መጀመሪያ ሙሉ ለሙሉ የፈረሱትን እና የተጎዱትን ትምህርት ቤቶች ከሰራን በኋላ ምንም ወዳልሆኑት ነገር ግን ደረጃቸውን ወዳልጠበቁት ውስጥ ገብተን ቀስ በቀስ አስርም ሃያም ዓመት ይፍጅ 47 ሺዎቹን ትምህርት ቤቶች መቀየር አለብን የሚል አቅጣጫ አስቀምጠናል።
በዚህ ብቻ አያበቃም አንዱ የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር ምንድን ነው ብለን ስንወያይ በጣም ግልጽ ሆኖ የወጣልን የኢትዮጵያ የወደፊት መሪዎች ከየት ነው የሚወጡት የሚለው ጥያቄ ነው። በሳይንስ ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በስነ ጥብብ ፣ በፍልስፍና ፣ በፖለቲካ እና በሌሎችም መስኮች ወደፊት ማህበረሰባችንን እንደ ማህበረሰብ ሊመሩ የሚችሉ ልጆችን የት ላይ ነው ብቁ የሆነ ትምህርት የምናስተምራቸው ብለን መመርመር ይዘን ነበር። በጣም የሚገርም አይነት የትምህርት ቤቶች ልዩነት ነው ያገኘነው።
በጣም ጥቂት የሚባሉ ብዙ ገንዝብ የሚያስከፍሉ ከውጪ ሀገር ኮሚዩኒቲ ጋር የተገናኙ ትምህርት ቤቶች አሉ። በቁጥር ስድስት እና ሰባት ናቸው። እንዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው ወይም ደግሞ በጣም ብዙ ብር መክፈል የሚችሉ ወላጆች ያሏቸው ናቸው። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ሀገር ውስጥ ቆይተው ማትሪክ እንኳን አይወስዱም። ጠቅላላ ትምህርታቸው ወደ ውጭ ሀገር ነው የሚሄደው። እነዚህ ሰዎች ተመልሰው ሀገራቸውን ያገለግላሉ ብሎ መጠበቅ በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም ከትምህርቱ ጋር የሚያገኙት የህይወት ዘይቤም የውጪው ስለሆነ እትብታቸው ከዚህ ሀገር ጋር የተያያዘ አይደለም። ስለዚህ እነሱ የወደፊት የሀገር መሪዎች ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ የሚቻል አይደለም።
በሁለተኛ ደረጃ መካከለኛ ገቢ አለው የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ልጆቹን የሚልክባቸው በተለይ ባለፈው ዓመትና እያገባደድን ባለነው ዓመት ለቅሶ ቤት እስኪመስሉ ድረስ ወላጆች የሚያለቅሱባቸው የግል ትምህርት ቤቶች አሉ። በእነዚህ ትምህርትቤቶችም በአብዛኛው ያየነው እንግሊዝኛ ቋንቋን ከማስተማር ባሻገር ይዘትን መሰረት ባደረገ የትምህርት አሰጣጥ ረገድ በወላጆች ዘንድ ያን ያህል እርካታ የለም። ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሙሉ ለሙሉ ችላ የተባሉት የመንግስት ትምህርት ቤቶች ናቸው። ጉዳዩን ይበልጥ መጥፎ የሚያደርገው ነገር ደግሞ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ትምህርት ቤቶቹን ማሻሻል የሚችለው የመካከለኛ መደብ ሰው ጥሏቸው ሄዶ የግል ትምህርት ቤቶች ጋር ከትሟል። በዚህ ምክንያት የመንግስት ትምህርት ቤቶች በቂ ባጀት አለመኖርና የአስተማሪዎች ችግር ብቻ ሳይሆን ያለባቸው የሚከታተሏቸው ወላጆች እንኳን የሉም። ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነጻጸር ምንም እንኳን ጥሩ የሚባል የተሻለ መሰረተ ልማት ቢኖራቸውም ክትትል በማድረግ ጥሩ ትምህርት እንዲሰጡ የሚያደርግ የወላጅ አካል ስለሌለ ከመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጡ የማህበረሰብ መሪዎች አሉ ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። የዚህ ሀገር መሪዎች ከየት ነው የሚመጡት ብለን ስንጠይቅ ይሄ ነው ያስደነገጠን ነገር።
በዚህ ምክንያት ቢያንስ በተወሰነ መንገድ ዘር ሃይማኖት እና አካባቢ ሳንለይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ስምንተኛ ክፍል የሚጨርሱ ጥሩ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በማዕከል የሚሰጥ ፈተና ፈትነን አዳሪ ትምህርት ቤቶች ገንብተን የወደፊት ሀገር መሪዎች መሆን እንዲችሉ እናዘጋጃቸው ብለን 50 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት አቅደናል። በ2015 ዓ.ም. በሁሉም ክልሎች አንድ አንድ በመገንባት በድምሩ 15 ትምህርት ቤቶችን እንሰራለን። የሚሰሩት ትምህርት ቤቶች ግን የሚገኙበትን ክልል ተማሪዎች ብቻ አይደለም የሚቀበሉት። ከየትኛውም ክልል የሚመጡ የሀገራችን ልጆች በዚያ የዕድሜ ክልል አብረው በመማር እርስ በእርስ መተዋወቅ መጀመር አለባቸው።
ዘመን፡- በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። በገንዘብ እና በአይነት ምን ያህል ድጋፍ እንደተደረገ የሚያሳይ መረጃ አለ ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በሙሉ ደምሬ ይሄ ነው የምልህ ነገር አይደለም። ነገር ግን ለምሳሌ ከዲያስፖራ ፈንድ ጋር አራት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ተስማምተን ኮንትራት ተፈራርመናል። እንደውም አሁን መጀመሪያ የሚሰሩት ትምህርት ቤቶች በጀታቸው ከዚያ የሚገኝ ነው። የካርል ፋውንዴሽን ከስድስት እስከ አስር ትምህርት ቤቶች እሰራለሁ ብሏል፤ ለእነሱም ዲዛይን እያዘጋጀን ነው። ራሳችን በትምህርት ሚንስቴር ደረጃ ከተለያዩ ስራዎች በፕሮጀክቶች ከምናገኘው ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት አለብን ብለን የያዝነው የተወሰነ ገንዘብ አለ። ህዝቡን በቴሌ እና በተለያዩ መንገዶች እንዲያዋጣ ጠይቀን አምስት ሚሊየን ብር አካባቢ አግኝተናል። የተገኘው ገንዘብ አነስተኛ ስለሆነ በአዲስ መልክ ገንዝበ የማሰባሰብ ዘመቻ እንዳርጋለን ብለናል። አሁን ቢያንስ መቶ ትምህርት ቤቶች ለመስራት የሚያስችል አቅም አለን። ህብረተሰቡን ዝም ብለን ገንዘብ ስጥ ብቻ ከማለት በተወሰነ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹን ሰርተን በማሳየት ምን ያህል ጥቅም ያለው ነገር እንደሆነ ሲመለከት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለን ተስፋ አድርገናል።
ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ክልሎች ያልተገባ ፉክክር ውስጥ ገብተው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ስርቆት መበራከቱን ገልጸው ነበር። ክልሎች እንዲህ ባለ ተግባር ላይ የተገኙት ምን ትርፍ ለማግኘት ነው ? ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ስርቆትን ለመቀነስ ዘንድሮ ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመስጠት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በሀገር ደረጃ የፈተና ስርቆትን መፈጸም ፓለቲካዊ ጥቅም ይሰጠናል ብሎ የሚያይ ሀገራዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አለ ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል። በዋናነት እብደቱ ያለው በክልሎች መካካል በሚደረግ ውድድር ላይ ነው። የኔ ክልል ልጆች በይበልጥ ዩኒቨርሲቲ መግባት ቻሉ ፤ እታች ያሉ ትምህርት ቢሮዎች ደግሞ እኛ ጥሩ እየሰራን ነው ብዙ ተማሪ አሳለፍን ለማለት እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ገንዘብ እያሰባሰቡ ለፈታኞች ጉቦ በመስጠት በርካታ ተማሪ ለማሳለፍ የሚፈጽሙት ነገር ነው። በአጠቃላይ በስራና በትምህርት ሳይሆን በአቋራጭ ውጤት ማግኘት እንችላለን ብሎ በማሰብ ትምህርት ከሚፈልገው ንጽህና አንጻር አዋቂ ቀርቶ ልጆች እንኳን የሚጸየፉት ነገር ነው በሀገራችን እየሆነ ያለው። ይሄ በፍጹም ሊቀጥል አይችልም። የሚያመጣው የሞራል ክስረት በጣም በብዙ መልኩ ነው የሚጎዳን። ዛሬ በዚህ መልኩ ያሳለፍነው ተማሪ ኮሌጅ ገብቶ እንደመጣበት መንገድ ሰርቆ ዲግሪ ከያዘ በኋላ የክልል ፋይናንስ ቢሮ እና ፍርድ ቤት ሄዶ እንዲሰራና ፍትህ እንዲሰጥ አይጠበቅም። ስራው ከህዝቡ ጉቦ መብላት እና ማጭበርበር ነው የሚሆነው። በትምህርት ላይ የምትፈጠረው ያልተገባ ነገር እያደር ስርዓቱን በሙሉ ነው እንደ ብል የሚበላው። ማንም ክልል ከዚህ ሊጠቀም እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል።
በመንግስት በኩል ችግሩ መቆም በሚችልበት መንገድ እንዲቆም ለማድረግ ቆራጥነት አለ። ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ፈተናውን በዲጅታል መንገድ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። ችግሩ አንድ ሚሊየን አካባቢ ለሚደርስ ተማሪ ፈተና ለመስጠት አንድ ሚሊየን ታብሌት ያስፈልጋል። ይህ 500 ሚሊየን ዶላር ይጠይቃል። ገንዘቡ ከቻይና በሚገኝ እርዳታ ይሟላል ተብሎ ነበር ያ አልተሳካም። አቅም ፈጥሮ ስርቆቱን ለማስቀረት እኛ ወደ ኃላፊነት ቦታው ከመምጣታችን በፊት ሙከራዎች ሲደረጉ ነበር። እኛ ከመጣን በኋላ ያሳለፍነው ውሳኔ በሁለት መንገድ መዘጋጀት አለብን የሚል ነው። ቴክኖሎጂውን ሀገር ውስጥ ማስገባት ከቻልን እሰየው በዲጂታል መልኩ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ፈተናውን እንሰጣለን። ያ ላይሆን የሚችል ከሆነ እና እንደ ከዚህ ቀደሙ ፈተናውን በወረቀት የምንሰጥ ከሆነ ከስርቆት መቶ በመቶ ነጻ ማውጣት እንኳን ባንችል በተቻለ መጠን ማንም ሰው በመስረቅ አልፋለሁ ብሎ አምኖ ሊሄድ የማይችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን በሚል አማራጮችን አይተናል። አንዱ ፈተናው ለስርቆት የሚጋለጥበት መንገድ ከመጓጓዙ ጋር የሚያያዝ ነው። ፈተናው ከማዕከል ገጠር ድረስ ስለሚሰራጭ በሚጓጓዝበት ወቅት ለስርቆት ምቹ ይሆናል። ባለፈው ዓመት የፈተና ስርቆት ለመፈጸም ሲባል በተከፈተ ተኩስ ፈተናውን አጅበው ሲሄዱ የነበሩ ሶስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተገድለውብናል። የፈተና ስርቆት የሰው ህይወት የሚጠፋበት ነገር ሆኗል።
ችግሩን ለመቀነስ የክልል ኃላፊዎችን ከሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናው እንለያቸውና ፈተናው ራሱ የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፈተና ስለሆነ በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ብቻ እንዲሰጥ እናድርግ ብለን አሁን ቢቻል ሁሉንም ተፈታኝ ተማሪዎች አጓጉዘን ከክልላቸው ውጪ ባሉ የኒኒቨርሲቲዎችና የፌዴራል ተቋማት ውስጥ ፈተናውን ለመስጠት ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው። ይሄ ሁለት ነገሮችን ያስቀራል። አንደኛ በመንገድ ላይ የሚኖረውን የመሰረቅ አደጋ ይቀንሰዋል። ሁለተኛ ክፍል ውስጥ ከተገባ በኋላ ደግሞ ለመስረቅ የሚቻልበትን ዕድል ይቀንሰዋል።
ፈተናዎችን በማዘጋጀት ደረጃም ከዚህ በፊት አራት የተለያየ ኮድ ያላቸውን ፈተናዎች ነበር የምናዘጋጀው አሁን እስከ አስራ ሁለት አድርሰናቸው ፍጹም የተለያዩ እንዲሆኑ አድርገን ጎን ለጎን የሚቀመጡ ተማሪዎች ፈተና በቅደም ተከተሉ በፍጹም ያልተገናኘ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራን ነው። እነዚህ ጥረቶች የፈተና ስርቆቱን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሱታል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው።
ዘመን፡- ወቅታዊውን የሀገራችንን ሁኔታ ስንመለከት ስልቱን እየቀያየረ በየጊዜው በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እና ማፈናቀል እየተበራከተ መጥቷል። ችግሩን እንዴት ማስቆም ይቻላል ብለው ያምናሉ ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ይሄ ለእኔ ሰዎች ወደ አውሬነት ተቀይረው የሞራል ስብዕናቸውን ሙሉ ለሙሉ አጥተው ህጻን ልጅ እና አዛውንት የሚገድሉበት ደረጃ ላይ ሲደርስ የፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ ይቆምና እብደት ነው የሚሆነው። እንዲህ አይነት ነገር በምንም አይነት መንገድ ማህበረሰቡ ውስጥ ስር እንዲሰድ ሊፈቀድለት አይገባም። የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ በደምብ አይቶ ያንን የችግር ምንጭ ለማድረቅ የሚያስችል ጠንካራ እንቅስቃሴ ከመንግስትም በአጠቃላይ ከህብረተሰቡም ሊኖር ይገባል። እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች በተፈጥሯቸው ኢመደበኛ እንቅስቃሴዎች ስለሆኑ ከአንድ አገር ወይም ከቋሚ ጦር ጋር እንደሚደረግ አይነት ጦርነት የሚደረግባቸው አይደሉም።
እንደ ታጣቂ ቡድን ውጊያ አካሄድክ የሚባለው ከመንግሥት ወታደሮች ወይም ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር ስትገጥም ነው። መሳሪያ ያልታጠቀ ሰላማዊ ህዝብ ዘንድ እየሄድክ መግደል አሸባሪነት ነው። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ለምንድን ነው ይሄንን የሚያደርጉት እና ማነው የሚጠቀመው የሚለው ነው። ምክንያቱም አንዳቸውም በዚያ የሚመጣ የፖለቲካ ጥቅም ያገኛሉ ብዬ አላስብም። የሚዘልቁበትም አይነት አይደለም። ህብረተሰቡ ተስፋ እየቆረጠ ሲሄድና መንግሥትም ህብረተሰቡን ለመከላከል በፀጥታ ኃይሎች ከሚወስደው እርምጃ ባሻገር የአካባቢው ህብረተሰብ ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ሲጀመር በተወሰነ ደረጃ እየቀነሰ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። በመንግሥት ደረጃ መወሰድ ያለበት የዚህ አይነት እርምጃ ነው።
ይሄ ነገር ከዚህ ቀደም እንዴት ነው ጋብ ብሎ የነበረው፣ አሁን ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሶስት ሳምንቶች ሊባባስ የቻለው በምን ምክንያት ነው ? እኔ እንደሚገባኝ ህወሃት መጀመሪያ ራሱ በየክልሉ የሚደረጉ ጦርነቶችን በፋይናንስ ሲያግዝ እንደነበር ስንሰማ ነበር። በዚያ በኩል ሀገርን ለማፍረስ ሞክረው ሞክረው አልሆን ሲላቸው በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ገቡ። ሠራዊታችንን ገደሉ፤ ደብረሲና ድረስ መጡ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ህልውና ላይ እንደማይደራደርና ተሰባስቦ የሀገሩን ደህንነት ለማስጠበቅ ምን አይነት ጥረት እንደሚያደርግ አዩ። መከላከያው፣ ፌዴራል ፖሊሱ፣ ልዩ ኃይሉ፣ ፋኖው፣ ወዘተ. ተሰብስቦ ሀገራችንን አናስደፍርም ብሎ ተዋግቶ ትግራይ ድንበር ድረስ መለሳቸው። አደብ ገዝተው በሰላማዊ መንገድ እንዴት አብሮ እንደሚኖር መንገድ እንደመፈለግ ከዚያ በኋላም የያዙት፣ እኛ በቀጥታ ጦርነት ልናገኘው ያልቻልነውን ነገር ማህበረሰቡን እርስ በእርሱ አባልተን ልናገኘው እንችላለን የሚል ስትራቴጂ ነው ብዬ ነው የማስበው። በዋነኛነት አማራንና ኦሮሞን አባልተን ይህን ሀገር ለእኛ እንደሚመች አድርገን እንቀይረዋለን የሚል እምነት ይዘው የሚንቀሳቀሱ ይመስለኛል።
በአገር ውስጥ ለዚህ መሳሪያ የሚሆኑ ደካማ ሰዎች አሉ። በፕሮፓጋንዳውም በምኑም እያደረጉ የህብረተሰቡን መንፈስ መረበሽና እንደ አንድ ሀገር የቆምን አይደለንም የሚል እሳቤ ውስጥ ለመክተት የሚደረግ ሙከራ ነው የሚመስለኝ። ይሄን ደግሞ ቁጭ ብሎ በደንብ ለሚያስበው ለአማራውም፣ ለኦሮሞውም ሆነ ለሀገሪቱ በፍጹም የማይበጅ አካሄድ ነው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ሰዎች ዝግ ብለው ተረጋግተው ቁጭ ብለው ማሰብ አለባቸው። ዝም ብለን በስሜት እየተነዳን እርስ በእርሳችን ከምንቦጫጨቅ፣ ጠላት ማን ነው? ይሄን ማን ነው የሚፈልገው? እንዴት አድርገን ይሄንን ኃይል ነቅተን በመጠበቅ መምታት አለብን የሚለው ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
አሸባሪው ሸኔ በሲቪል ማህበረሰብ ላይ የሚወስደውን እርምጃ ለማስቆም የመንግስት፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ፣ የአካባቢው ሚሊሻ፣ የአማራው ማህበረሰብ፣ የአፋሩ ማህበረሰብ፣ ወዘተ… የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ ነው አንድነት የሚያስፈልገው። እንደዚህ አይነት ለሰውነት የሚሰቀጥጥ ግፍ መፈጸም የሚችሉ ኃይሎች ሲመጡብህ አጠገብ ካሉት ጋር አይደለም መባላት ያለብህ ተሰባስበህ ጠንከር ብለህ የመጡትን ኃይሎች ማስቆም ነው ያለብህ። ይሄ እንዳይሆን ነው እየሠሩት ያሉት። ቢያንስ ሥራዬ ብለው በያዙት በሶሻል ሚዲያው የተወሰነ ያህል የተሳካላቸው ይመስላል፤ ለረጅም ጊዜ ግን በፍጹም ይሳካል ብዬ አላምንም። በተጨማሪም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ችግር ያለባቸው አንዳንድ አካላት ካሉ መንግስት ውስጡን በአግባቡ ፈትሾ ከእነዚህ የጥፋት ሃይሎች ራሱን ማጽዳት ይጠበቅበታል ።
ዘመን፡- ብሔራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የኢትዮጵያ ሀገር መንግስትን ከመገንባት አኳያ ብዙ ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው በዚህ ቦታ የሚነሱት። ከህገ መንግስት ጋር የተያያዙ እና ሌሎችንም ጉዳዮችማንሳት ይቻላል። አንድ ፓርቲ ጂኦ ፖለቲካን ታሳቢ አድርጎ ያወጣው ህገ መንግስት ጭምር አለ። በመሆኑም የሀገራችንን አንድነት እና የህብረተሰቡን ሰላም ችግሮች ውስጥ የከተቱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው ብሎ ቁጭ ብሎ በደንብ ፈትሾ በመወያየት ልብ ለልብ መገናኘት ይገባል። በውይይቱ የምንሳተፈው የፖለቲካ ዲስኩር ለማካሄድ ብቻ ሳይሆን አብረን እንደምንኖርና የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችንን አስበን መሆን አለበት። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በደንብ አስበውበት ያላቸውን አመለካከት ከነምክንያታቸው ለህብረተሰቡ አስረድተው ልዩነቶቻችን ምን ምን ላይ ናቸው የምንስማማባቸውስ የትኞቹ ናቸው ብለው ለመግባባት መቅረብ ይኖርባቸዋል። በሚካሄደው ውይይት ልዩነቶቹን መፍታት የማይቻል ከሆነ ደግሞ ለህብረተሰቡ አቅርቦ እንዲወስንበት ማድረግ ተገቢ ይሆናል። በዚህም ሲቪል ማህበረሰቡ በሰላም የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ምንም ጥያቄ ውስጥ በማይገባበት ሁኔታ ኢዜማ፣ ብልጽግና፣ አብን፣ ወዘተ ማንም ቢመረጥ ልዩነት ስለማያመጣ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።
ዘመን፡- ከሁለት ሳምንት በፊት ኢዜማ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ በተካሄደ ምርጫ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ፓርቲውን በመሪነት እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የታየውን ፉክክር በመመልከት ኢዜማ በምርጫው ማግስት ለሁለት ሊሰነጠቅ ይችላል በሚል ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች ነበሩ። አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት እና ስጋቱን እንዴት ይገልጹታል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ጉባዔው መደበኛ እና አመራር የሚመረጥበት ነበር። ለእኔ ትልቅ መድረክ ቢሆንም በሂደቱ ግን አንዳንድ ትንሽ መስመር ያለፉ ነገሮች ታይተውበታል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር የሚፈልግ ፓርቲ መጀመሪያ ራሱ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት። መሪዎቹን በፓርቲው ውስጥ በሚካሄድ ውይይትና ክርክር ፍጹም ነጻ በሆነ መልኩ የሚመርጥበት ሁኔታ ከሌለ በስተቀር ስልጣን ሲይዝ ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ እኛ እንደ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር እንፈልጋለን። ዴሞክራሲ እንዲፈጠር ከፈለግን ደግሞ ከፓርቲያችን አወቃቀርና አደረጃጀት ጀምሮ እስከ ጉባዔዎቻችን የምናደርጋቸው መድረኮች እና አሰራሮች ፍጹም ዲሞክራሲያዊ መሆን አለባቸው የሚል አቋም ይዘናል። ይህ አሰራር በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ አይደለም።
የኢዜማ አደረጃጀት ለየት ይላል። አንድ ፓርቲ ተወዳድሮ ሲያሸንፍ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ ብቻ መሆን የለበትም። ፓርቲው የመንግስት ስልጣን ሲይዝ የሚያገለግለው ፓርቲውን ወይም የመረጠውን ሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሀገሪቱን ህዝብ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ በተቻለ መጠን የመንግስት ስልጣን ከፓርቲው በተወሰነ ደረጃ መራቅ አለበት። በሀገራችን የተለመደው ግን የአውራ ፓርቲ ሞዴል አደረጃጀት ነው። ፓርቲው ሁሉን ነገር ይቆጣጠረዋል። በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ያለው ባለሙያ የሚያድገው በፓርቲ አባልነቱ ነው። በመንግስት መስሪያ ቤት መደበኛ በጀት የፓርቲ ስራ ይሰራል። ሰዎች የሚመድቡት በፓርቲ ሃላፊነታቸው ነው። የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በፓርቲ አሰራር ይመራል። ይህ አሠራር ከበፊት ጀምሮ ብዙ ችግሮች ውስጥ ከቶናል። ከቀይ ሽብር ጀምሮ የወያኔ አሰራር አሁን ላይ እርስ በእርሳችን እንድንባላ አድርጎናል። እኛ እንደ ፓርቲ ከዚያ ትርምስ ውስጥ ወጥተን እውነተኛ ዴሞክራሲ መፍጠር አለብን ብለን ነው ያንን ልምምድ በማድረግ ላይ የምንገኘው።
ይሁን እንጂ ሂደቱን ብዙ ሰው ስላለመደው በአንድ ፓርቲ ውስጥ በሚደረግ ውድድር እንደዚህ ዓይነት እሰጥ አገባና ክርክር ካለ የፓርቲው የወደፊት ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮበታል። በመሆኑም እኛ በፓርቲያችን ውስጥ ጠንካራ ክርክርና ውይይት የምናካሂደው ዴሞክራሲን ለመለማመድና ለመገነባት ነው። በሂደቱ ብታሽንፍ የተሸነፉ ግለሰቦችን ሃሳብ ከግምት ውስጥ የምታስገባበት፣ ከተሸነፍክም በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ፓርቲው የሚሰጣቸውን ተግባራት አክብረህ የምትሰራበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው።
ዘመን፡- ኢዜማን በሚመሩባቸው ቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ምን ለመስራት አቅደዋል ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በጣም ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ዕቅድ ይዘናል። ከእነዚህ መካከል በርካታ መሪዎችን ለማብቃት የስልጠና ስራ እንሰራለን። አደረጃጀታችንን እንደገና ፈትሸን በሁሉም የሀገሪቱ ቦታዎች ጠንካራ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖረን እናደርጋለን። በፖለቲካው ዙሪያ ከፊታችን ባሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከብሔራዊ የምክክር ጉባዔ ጋር በተያያዘ የሚሰራ አንድ ኮሜቴ አዋቅረናል። በውይይት መድረኩ እንደ ድርጅት አባልነታችን ምን አጀንዳ ይዘን እንደምንነጋገር እና በምን ጉዳዮች ላይ የሰከነ ጽሁፍ ማዘጋጀት እንዳለብን እናስብበታለን። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ሃሳብ አቅርበን ለመወያየት እንሞክራለን። እነዚህን ተግባራት የሚከታተሉ ሰዎች እንዲመደቡ ተደርጓል። በአጠቃላይ የተደላደለ የፖለቲካ ስርዓት በመፍጠር ሀገራችን ከገባችበት ችግር የምትወጣበትን ሁኔታ ለማገዝ እንሰራለን።
ዘመን፡- የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ
ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ.ም