ኢትዮጵያ በቀጣዮች አስር ዓመታት የምትመራበትን የልማት ዕቅድ አዘጋጅታ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ከጀመረች ሁለተኛ ዓመቷን ይዛለች። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ከ 2013 እስከ 2022 ዓ.ም. የሚተገበረው የልማት ዕቅድ “ኢትዮጵያ ፤ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት!” የሚል መሪ መልዕክት አለው።
ዘመን መጽሔት የአስር ዓመት ዕቅዱ አስኳል በሆነው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ትኩረት በማድረግ የእስካሁን አፈጻጸሙ ምን እንደሚመስል እና ኮቪድ- 19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለው ሁኔታ የሚፈጥሩትን ጫና ለመቋቋም እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ከ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ጋር ቆይታ አድርጋለች። እነሆ።
ዘመን፡- በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብርና ልማት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት የግብርና ምርትን አስተማማኝ በሆነ እና ተከታታይነት ባለው መንገድ ለማሳደግ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዴት ይገመግማቸዋል ?
ዶክተር ፍጹም ፡- ግብርና በሀገራችን አውድ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ እና የድህነት ቅነሳው በጣም ትልቅ ድርሻ ያለው ዘርፍ ነው። በዓለም ተሞክሮም ስንመለከት እነ ቻይናን የመሰሉ ሀገራት ለእድገታቸውና ሽግግራቸው የመጀመሪያው መነሻ ኃይል የሆናቸው የግብርናው ዘርፍ ነው። ባለፉት ዓመታት ግን ግብርና በኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባውን ድርሻ በሚፈለገው መጠን እንዳይጫወት ብዙ ተግዳሮቶች ነበረቡት። እነዛን ተግዳሮቶች በመለየት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን መጨመር እንዲችል ፤ በሀገር ውስጥ የምግብ አቅርቦት ራስን በመቻል ከውጭ የሚገቡ የምግብ ምርቶችን እንዲተካ እና በሚገባው ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆን እንዲችል በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ መልከ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ሲተገበሩ ነበር።
በግብርናው ዘርፍ ሲደረጉ ከነበሩት የሪፎርም ሥራዎች ጥቂቱን ለመጥቀስ የመጀመሪያው በፋይናንስ ፣ በውጭ ምንዛሪ እና በቴክኖሎጂ ግብዓቶች በሚገባው ደረጃ ሳይደገፍ የቆየ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች መሻሻል አለባቸው በሚል በብድር ድልድል ውስጥ በግልጽ በሚታይ መልኩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ለግብርናው ዘርፍ የተሻለ ብድር መሰጠት ተጀምሯል። ይህ የሆነው ደግሞ በመንግሥት በጀት ድጋፍ ነው። በመንግሥት በጀት ድጋፍ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ መጠን ግብርናንም ሆነ ግብርናን ለሚያዘምኑ ሌሎች መስኮች ከፍተኛ በጀት ፈሰስ ተደርጓል። ለምሳሌ ለእርሻና አርብቶ አደር አካባቢዎች ውሃ ልማት ለመስኖ ከብድር በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንትና በጀት በመንግሥት ተግባራዊ ተደርጓል።
ሌላው የግብርናን ዘርፍ ከፋይናንስ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዳይሆን ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ባበዳሪዎች የሚጠየቀው ማስያዣ (ኮላቶራል) ነው። ከተማው ውስጥ አንድ ቤት ማስያዝ የሚገኘውን ብድር ያህል በጣም ትልቅ የእርሻ መሬት ያለው ገበሬው እንኳን የፖሊሲ ድጋፍ ስለሌለ አስይዞ መበደር አይችልም። አርብቶ አደሩም ተንቀሳቃሽ ሀብቶቹን አስይዞ ብድር መበደርና ሥራውን ማስፋት አይችልም ነበር። ይሄ በሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ተንቀሳቃሽ ንብረት አስይዘው መበደር እንዲችሉ በመደረጉ በግብርና ፋይናንስ ትልቅ መሻሻል ታይቷል።
ሌላኛው ድጋፍ የግብርና ማዘመኛ ቴክኖሎጂዎች እና ብዙ የግብርና ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተደረገበት ነው። ትራክተሮች ፣ ኮምባይነሮች ፣ የወተት ማለቢያዎች ፣ ማር የሚያምርቱ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ሌሎችም ግብዓቶች በከፍተኛ ደረጃ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጉ ትልቅ እገዛ አድርጓል።
ግብርና ዘርፉ ራሱ የአሰራር እና የመሬት አስተዳደር ለውጦችን በማድረግ ቀደም ሲል አንዳንድ ወገኖች መሬታችን የተበጣጠሰ በመሆኑ አመቺ አይደለም ግብርናችን ተስፋ የለውም ብለው ያስቡ ነበር። ነገር ግን ይሄን አስተሳሰብ በመቀየር መሬቱ የተበጣጠሰው አእምሯችን ውስጥ እንጂ በእውነታው ዓለም አለመሆኑን በማሳየት አሰራርን በማዘመን የኤክስቴሽን ሥራን በማስፋት ገበሬዎቹ አጠገብ ለአጠገብ ያሉ በመሆናቸው መሬት በኩታ ገጠም እንዲታረስ ማድረግ ተችሏል። በኦሮሚያ አርሲ እና ባሌ እንዲሁም በአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞን እና ሌሎችም አካባቢዎች ሄደን ብንመለከት በጣም በሚገርም ሁኔታ ትልቅ የንግድ እርሻ የሚመስል ነገር ግን በርካታ አርሶ አደሮች መሬታቸውን አቀናጅተው ለቴክኖሎጂና ግብዓት አጠቃቀም ምቹ በማድረግ ኩታ ገጠም የመሬት አጠቃቀምን መተግበር ተችሏል።
ሌላኛው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴ ነው። የሚገርም ለውጥ እየተመዘገበበት ይገኛል። ውጤቱን እንግዲህ በቅርብ ገበያውን ትርጉም ባለው መንገድ እያረጋጋ ሲሄድ እያንዳንዳችን የምንረዳው ይሆናል። ስንዴን ከውጭ መግዛት እንድናቆም የሚያስችለንና የአገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት ካሰብነው ጊዜ ቀድሞ እየተሳካ ያለ ሥራ ነው። በአጠቃላይ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግብርናው ዘርፍ ለውጥ ይሄን ይመስላል።
ዘመን፡- ከ2003 – 2012 ዓ/ም የነበረውን የዘርፎች የወጪ ንግድ አፈፃፀም አማካይ ስንመለከት 73 ነጥብ 8 በመቶን የሚሸፍነው የግብርና ዘርፍ ነው። ማኑፋክቸሪንግ 12 ነጥብ 2 እንዲሁም ማዕድን 11 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ ነበራቸው። የወጪ ምርቶችን ስብጥርና መጠን በማሳደግ እንዲሁም ሀገር ውስጥ ተጨማሪ እሴት ፈጥሮ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለመጨመር የሚያስችሉ ሥራዎች በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አድማስ ልክ እየተተገበሩ ነው ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ፍጹም ፡- የአንድ ኢኮኖሚ ዘመናዊነት ፣ ዘላቂነት እና እድገቱ ሊነቃነቅ የማይችል መሰረት ላይ ተጥሏል የምንለው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ ስንችል ነው። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ስንል የመጀመሪያ ከምንላቸው እንደ ግብርና እና ማዕድን ያሉ ዘርፎች ወደ አምራች ኢንዱስትሪ መሸጋገር ስንችል ነው። ግብርናም ቢሆን ያመረተውን በጥሬው ከመሸጥ ይልቅ አቀናብሮ እሴት ጨምሮ መላክ ሲችል ፤ ማዕድንም ቢሆን በጥሬው ለቅሞ መሸጥ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ግብአትነት መጠቀም ሲችል የሀገር ኢኮኖሚ ዘመነ ተሸጋገረ እንላለን። የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እና የሚመጣው ገቢም በዚያው መጠን በጣም የተሻለ ይሆናል።
በዚህ ዘርፍ በተለይ ባለፉት የልማት እቅዶቻችን በዕቅድ ደረጃ ተቀምጦ የነበር ቢሆንም አልተሳካም። በ 10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ በደምብ አስበንበታል። የተጠኑ ጥናቶች ያሳዩት ነገር የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምርታማነትና የተወዳዳሪነት ችግር እንዳለበት ነው። ምርታማነቱ እና እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ረገድም ያለበት ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ ኢንዱስትሪዎች በኖሩን እንኳን በጣም ብዙ ግብዓቶችን ከውጭ አገር እናመጣና ከሀገር ውስጥ የምንጨምረው እሴት በጣም ትንሽ ነው።
ሌላው ትልቁ ድክመት በትልልቆቹ ኢንዱስትሪዎች እና በመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው የፊትዮሽ እና የኋልዮሽ ትስስር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ይሄም ኢኮኖሚያችንን ተጋላጭ ከማድረጉ በተጨማሪ አጠቃላይ የኢንዱስትሪው ልማት ወደ ኋላ እንዲቀር ካደረጉት ነገሮች ውስጥ የሚካተት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ማስተካከል የሚገባው እጣን ስለሆነ በ 10 ዓመቱ ዕቅድም ሆነ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ልክ እንደ ግብርናው የአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። አንደኛው ተወዳዳሪነቱን እና ምርታማነቱን መጨመር የሚል ነው። ሌላኛው በ10 ዓመቱ ዕቅድ እንደ ትኩረት መስክ ዘርፈ ብዙ እድገት ምንጭ ነው ታሳቢ የተደረገው። አንድ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር በጣም ብዙ እምቅ ሀብት ያላት ሀገር ስለሆነች የአምራች ኢንዱስትሪው አለምንም ጥርጥር በሚመጡት 10 ዓመታት የዕድገት ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።
ይሄን ለመፍታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ከኮቪድ 19 ጀምሮ ከዚያ በሀገር ውስጥ ያጋጠመን ችግር ነበር። ከዚያ ጋር ተያይዞ በጂኦ ፖለቲክሱ እነዚህን ዘርፎች ለማዘመን የሚያስፈልገንን ከልማት አጋሮቻችን ስንጠብቀው የነበረን የፋይናንስ ድጋፍ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በያዙት የተዛባ አስተሳሰብ እና አመለካከት የተነሳ ባለመልቀቃቸው አሉታዊ ተፅእኖ አሳድረውብናል። ቢሆንም ግን ኢንዱስትሪን ማሳደግ እና ማዘመን ካልቻልን ይሄ ሀገር ዘመናዊና ዘላቂነት ያለው ሀገር መሆን አይችልም ፤ ኢኮኖሚውም በዛው መጠን የሥራ ዕድልም ቢሆን ጥራትና ብዛት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው በኢንዱስትሪ ውስጥ በመሆኑ ያለምንም ጥርጥር መሳካት አለበት። ነገር ግን እንደ ሪፎርም በጣም ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዘርፉ እንኳን በኢንዱስትሪ ሚኒስትር አሁን እየተሰሩ ያሉ በጣም ብዙ ሥራዎች አሉ። ይሄ ለወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል የሆናል።
ዘመን፡- በጥቅሉ የወጪ ምርቶችን ስብጥርና መጠን በማሳደግ እና ተጨማሪ እሴት ፈጥሮ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ረገድ በታቀደው ልክ ባይሆንም ለውጦች አሉ ብሎ መጥቀስ ይቻላል ?
ዶክተር ፍጹም ፡- አዎ። ለምሳሌ በኢንዱስትሪ ዘርፉ በዚህ ዘጠኝ ወር ብቻ ከ 80 በመቶ በላይ ያቀደውን ዕቅድ ፈጽሟል። በወጪ ንግድ በዘጠኝ ወሩ ብቻ ወደ 400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል። ይህ ማለት ከነበርንበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር ቀላል ግኝት አይደለም። ኮቪድ 19 ኢትዮጵያን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ዓለም አቀፍ የሆነ ተግዳሮት ነው። ኢንዱስትሪ በኮቪድ 19 ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው የተጎዳው። እዛ ላይ በሀገር ውስጥ የገጠመን ችግር ተጨምሮበት በትልቅ ተግዳሮት ውስጥ እያለፈ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በተለይ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህን ያህል የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ከዓመቱ ዕቅድ 80 በመቶውን ማሳካት ትልቅ ውጤት ነው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል። አንተ እንደጠቀስከው ኢንዱስትሪው ከወጪ ንግድ ያለው ድርሻ ገና 12 ነጥብ 2 በመቶ ስለሆነ ማሳደግ መቻል አለብን።
ዘመን፡- በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የኢንዱስትሪው በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በ2012 ዓ/ም ከነበረበት 6 ነጥብ 9 በመቶ በ2022 ዓ/ም ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ታስቧል። ዘርፉ በሀገሪቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የያዘውን የአምስት በመቶ ድርሻም በ2022 ዓ/ም ወደ 15 በመቶ ለማሳደግ ታልሟል። ሀገራችን እቅዱን ማሳካት የሚያስችል ጉዞ ላይ ናት ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ፍጹም ፡- ኢንዱስትራላይዜሽን ብለን ስናስብ ኢንዱስትሪ ስንል የባህልም ጥያቄ ነው። በጊዜ ብዛት እና ሂደት የሚገነባ ባህል ነው። በ18ኛው እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የምዕራቡን ዓለም የኢንዱስትሪ አብዮት ስንመለከት የባህል ግንባታው እንዴት ባለ ሂደት አሁን የደረሱበት ደረጃ እንዳደረሳቸው እንረዳለን። ዛሬ ተበድረህ አምጥተህ ዛሬውኑ ትርፍ አለማግኘትን ፤ ጥቃቅን ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ በሚባሉት የኢንዱስትሪ ደረጃዎች ሸሚዝህን ሰብስበህ ብረት እየቀጠቀጥክ በጣም ብዙ መስራትን ፤ ፈጠራን ፣ አሻሽሎ መስራትን ፣ ትዕግስትን እና እውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ ኢንዱስትሪን መገንባትና ማዘመን ባህልም ነው። ከዚህ አኳያ አገራችን ኢንዱስትሪ መገንባት የጀመረችው መቼ ነው የሚለውን ስንመለከት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ያለን። ስለዚህ የምንሄድበትን መንገድ እና የምንወስደውን እያንዳንዱን እርምጃ የምንገመግመው መነሻችንን በማሰብ ነው።
ይሄ እንዳለ ሆኖ ይህች አገር በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተወጠነውን ታሳካለች በሚል ለቀረበው ጥያቄ እንግዲህ የመጀመሪያው ነገር የሚሆነው እይታ ፣ ርዕይ እና ፖሊሲ የማስተካከል ጉዳይ ነው። ከዚህ በፊት የነበረን ፖሊሲ ምን ክፍተቶች አሉበት ፣ እቅዳችን ምን ይመስል ነበር እና ስትራቴጂዎቻችን እንዴት ያሉ ነበሩ ብሎ ፈትሾ ማስተካከል ነው። ከዚህ አኳያ የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ተደርጎበታል። ስለዚህ በአሥር ዓመቱ እቅድ ኢንዱስትሪው እንደ አንድ የትኩረት መስክ የእድገት ምንጭ ተወስዶ መቀመጡ አንዱ የእይታ ለውጥ ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን።
ሁለተኛ ከፍተኛ የምንላቸውን ኢንዱስትሪዎች ለብቻቸው ገንጥሎ ከሚያይ እና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ብቻ በማብዛት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ይዘምናል ከሚለው ቁንጽል አረዳድ መተሳሰር ወደ ሚል ከፍ ያለ ሀሳብ መምጣት ተችሏል። ከፍተኛ ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪ የምንለው ቀርቶ እንደ አጠቃላይ ግብርና ፣ ማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች መተሳሰር ካልቻሉ ኢንዱስትሪው ሊሸጋገር አይችልም የሚል እይታ መያዙ ትልቅ ለውጥ ነው። ይህን ስናደርግ ነው ተያይዘው አብረው ሊያድጉ የሚችሉት።
ሌላው አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ቀረጻው ተጠናቆ ብዙ ውይይቶች ተደርገውበት የመጀመሪያው ረቂቅ ተጠናቋል፤ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚጸድቅ ይሆናል። አዲሱ ፖሊሲ ያቀድነውን ግብ እንድናሳካ ትልቅ እገዛ ያደርግልናል። እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል የተገነቡ እና ያልተገነቡ አቅሞች አሉን። የተገነቡ አቅሞች የምንላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን እና ሥራ ላይ ያሉ ፋብሪካዎቻችን ናቸው። አብዛኞቹ አሁን እየሰሩ የሚገኙት በ50 በመቶ እና ከዛ በታች በሆነ የማምረት አቅማቸው ነው። የማምረት አቅማቸውን ወደ 80 ከመቶ ማሳደግ ብንችል ሌላ አዲስ ኢንዱስትሪ መገንባት ሳያስፈልገን ያቀድነውን ማሳካት እንችላለን። አዳዲስ ፋብሪካዎችንና አዲስ ኢንቨስትመንቶችን እንደምንጨምር ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
ያልተገነባ አቅም የምንለው የጥሬ እቃ ሀብታችንን ነው። ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ገና ያልነካነው ብዙ አቅም አለን። ይህን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም አለብን። ሌላው የሰው ሀብት ነው። አነሰም በዛ ከነክፍተቶቹ ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል አለን። ባለፉት ዓመታት ትምህርት ላይ ባደረግነው ኢንቨስትመንት በትንሽ ስልጠና የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ችለናል። ስለዚህ እነዚህን ሀብቶች በጥቂቱ ስናስባቸው የተቀመጠው ግብ ቢያንስ እንጂ ኢትዮጵያ ላላት አቅም የሚበዛ አይሆንም።
ዘመን፡- አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መንገድ ላይ መሆኑን ገልጸውልኛል። ምን ዓይነት ተስፋዎችን መጠበቅ ይቻላል ? በቀረጻ ወቅት የነበረው ተሳትፎስ ምን ይመስላል ?
ዶክተር ፍጹም ፡- አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የእይታ ለውጦች አሉት። አንደኛ ኢንዱስትሪ ተነጥሎ ብቻውን እንዲለማ ሳይሆን ከሌሎቹ ዘርፎች ጋር አብሮ መልማትና መተሳሰር እንዳለበት አምኖ የተነሳ ነው። ግብርና ለኢንዱስትሪው ግብዓት ማቅረብ ካልቻለ አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪውና ሌሎችም ኢንዱስትሪዎች ሊለሙ አይችሉም። የማዕድን ዘርፉ ግብዓት ማቅረብ ካልቻለ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሊለማ አይችልም። ስለዚህ በእነዚህ ዘርፎች መካከል ያለውን ትስስር በከፍተኛ ሁኔታ ያገናዘበ ወይም እውቅና የሰጠ ፖሊሲ ነው።
ሁለተኛው ጉዳዩ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከታች ወደላይና ከላይ ወደታች ሊኖር የሚገባውን ትስስር ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ አሁን በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ውስጥ በፈለግነው መጠን ያልሄደልን ነገር ነው። አንድ ሸሚዝ የሚያመርት ትልቅ ፋብሪካ የሸሚዙን ኮሌታ፣ የሸሚዙን አዝራር እና ለሸሚዙ ግብዓት የሚሆኑ ከጥጥ ጀምሮ ያሉ ግብዓቶችን በትስስር እዚሁ ካሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲቀበልና እንዲሰራ እንፈልጋለን። በተወሰነ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ገና ብዙ ይቀረናል።
ሶስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ይመጣል እያልን ነው፤ ይህ አብዮት ዲጂታል አብዮት ነው። ይህንን የዲጂታል አብዮት ዛሬ ላይ አስበንበት ካልተዘጋጀን ሲመጣ እንደርስበታለን ማለት አንችልም። ኢትዮጵያ ይህንን ማጣት የለባትም። ከዚህ በፊት የነበሩትን የኢንዱስትሪ አብዮቶች አጥታለች። ስለዚህ አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮትም ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ነው።
ፖሊሲው በትንሹ እነዚህን ሶስት እይታዎችን የያዘ ነው። ከመሳተፍና ከውይይት አልፎ በደንብ የተደራጀ ግብዓት የተደረገበትም ነው። በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋና ባለቤትነት እየተመራ ያለና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተውበታል። አሁንም በዛ የመጎልበት ሂደት ውስጥ ያለ ስለሆነ በጣም ጥሩ የሚባል የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በቅርብ እናጸድቃለን ብዬ አስባለሁ።
ዘመን፡- የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በመስከረም ወር 2014 ዓ/ም የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ባለፉት አምስት ዓመታት ከነበሩት ወራት ከፍተኛው እንደሆነ ገልጿል፤ ከዚያ ወዲህ ባለው ጊዜም ግሽበቱ እያየለ ነው። ግሽበቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሰው የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደሆነ አንድ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ያለውን የዋጋ ግሸበት እና ግሸበቱ ያስከተለውን የኑሮ ጫና ለዘለቄታው ለመፍታትስ ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ፍጹም ፡- መጀመሪያው ልገልጽ የምፈልገው ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ተያይዞ የመጣው የኑሮ ውድነት ዜጎቻችንን በከፍተኛ ሁኔታ እያማረረ እና እያስጨነቀ ያለ መሆኑ እውነት ነው። ነገር ግን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን መተግበር የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል የሚለው ሀሳብ ትክክል አይደለም። እኔም የዋጋ ንረቱን እና የኑሮ ውድነቱን ያስከተለው የኢኮኖሚ ማሻሻያው ነው ሲባል ሰምቻለሁ። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ባይተገበር ኖሮ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በዚህ ደረጀ ለማቆየት በጣም እንቸገር ነበር።
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በግብርና በተሰራው ሥራ ዘንድሮ በበጋ ወቅት ከዚህ ቀደም የማይመረትበት 504 ሺ ሄክታር መሬት ታርሶ ወደ 16 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል። ይህ ባይመረት ኖሮ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነበር ? ይሄ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት ነው። ሌላኛው የበጀት አጠቃቀማችን ጉዳይ ነው። እንደ ከዚህ በፊቱ ዓይነት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የበጀት እና የወጪ አስተዳደር ሥርዓት ቢኖርን ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል። የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ደረጃ የአዋጭነት ጥናት ተደርጎባቸው ነው በጀት እየተሰጣቸው ያለው። በተዝረከረከ ሁኔታ የመሰረተ ድንጋይ ጥለን ፕሮጀክቶችን አንጀምርም። ይህ በወጪ አስተዳደር ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሌላው የበጀት ጉድለት ነው። የበጀት ጉድለት ሁሌም ይኖራል። ነገር ግን ቀደም ባለው ጊዜ ጉድለቱ ይሞላ የነበረው የግምጃ ቤት ሰነዶችን በመሸጥ ነበር። ይህ አካሄድ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ገንዘብ ነው ሲጠቀም የነበረው። የኮሜርሻል ብድር ባለፉት አራት ዓመታት አልተበደርንም። ትልቅ ቀይ መስመር ተብለው ከተቀመጡ ነገሮች ውስጥ አንዱ በጣም በትንሽ ወለድ የምንበደረው ብድር ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት የንግድ ብድር አልመበደር ነው ፤ ይሔ ራሱን የቻለ አስተዋጽዖ አለው። ይልቁንም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበሩ የዋጋ ግሽበቱ ከዚህ እንዳይብስ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል። ደግሜ የምለው ግን የኑሮ ውድነቱና ግሽበቱ ህዝባችንን እያስጨነቀ አይደለም ለማለት አይደለም በከፍተኛ ሁኔታ አስጨንቋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዋጋ ግሽበት ፈርጅ ዓለም አቀፋዊ ሆኗል። በጣም ያደጉ ሀገራት ስለ ዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት መጨነቅ ካቆሙ በጣም ብዙ ዘመን ተቆጥሮ ነበር። ከኮቪድ 19 በተለይም ከራሺያና ዩክሬን ጦርነት በኋላ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ሆኗል። በስንዴ ፣ በምግብ ዘይት ፣ ማዳበሪያ ፣ ማዳበሪያ በሚመረትበት ግብዓት እና ነዳጅ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ በሀገራችን ላይም የራሱ አንድምታ አለው። መንግሥት ይሄንን ለመቅረፍ ምን እያረገ ነው ለሚለው በፈለግነው መጠን ባይሆንም ግብርና ላይ የታየው የምርትና ምርታማነት መጨመር ገበያን ለማረጋጋት የራሱ አስተዋጽኦ ያለው አንድ ነገር ነው።
ከውጭ የሚመጣ ስንዴ፣ ዘይት፣ የህጻናት ምግብ፣ ሩዝ እና ስኳር ይጣልበት የነበረው ታክስ መነሳቱም ትልቅ ትርጉም አለው። ሀገርም ከዚህ ብዙ ገቢ አጥታለች። ይህ የሆነው ህዝቡ በታክሱ ምክንያት ይጨመርበት የነበረውን ዋጋ ለመቀነስ ነው። ሌላው በፍራንኮ ቫሉታ የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ማናቸውም ሰዎች የውጭ ምንዛሪያቸውን ማሳወቅ ሳይጠበቅባቸው ሀገር ውስጥ ያለ የምግብና የሸቀጦች አቅርቦት የተሻለ እንዲሆን ወደ ሀገር ውስጥ ዘይት ስንዴ የመሳሰሉትን ሸቀጦች አስገብተው እንዲሸጡ ተደርጓል። እነዚህ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበቱ እንዳይብስ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው። ነገር ግን አሁንም ደግሜ የምለው ህዝባችንን እያስጨነቀ ያለ አሁንም ያልፈታነው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ እና ተያይዞ ያለው የኑሮ ወድነት ግዙፍ የቤት ሥራችን ነው።
ዘመን፡- መነሻዬ ላይ ባለፉት 5 ዓመታት ያልታየ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡን ጠቅሻለሁ፤ እርሶም ህዝቡ የኑሮ ጫና ውስጥ መሆኑን የምናስተባብለው ነገር አይደለም ብለዋል። የዋጋ ግሽበቱን አሁን ባለበት ደረጃ መያዝ የቻልነው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር በመቻሉ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው ?
ዶክተር ፍጹም፡- ባለበት እንዲያዝ ተደርጓል ስል አንድ ቦታ ቆሟል እያልኩ አይደለም። ግጨት ፣ ኮሮና እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ነበሩ። የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ ነው እንዳይብስ ለማድረግ ግን የሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን መተግበራችን የራሱ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ 60 እና 70 ላይ ተደርሶ ያውቃል።
ዘመን፡- ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ የማድረግ ሂደቱ እንደታቀደው በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ያለው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ፍጹም፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። ፍጥነት እንግዲህ አንጻራዊ ነው። ለምሳሌ የዱላ ቅብብል ላይ ትፈጥናለህ ቀጣዩ ጓደኛህ አቀብሎህ ይሮጣል የምታሸንፈውም ሆነ የተሻለ ውጤት የምታስመዘግበው ዱላ ቅብብሉ በሁለቱም ወገን በተከናወነበት ፍጥነት ነው። ዱላውን ተቀብለህ የምትሮጥ ከሆነ ካንተ በፊት የነበረው ሯጭ የሮጠበት መንገድና የወሰደው ሰዓት በጣም ወሳኝ ይሆናል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበሩበት ሁኔታ አንዳንዶቹ ገቢና ወጪያቸው የማይታወቅ የግለሰቦች ንብረት የሚመስሉ ነበሩ።
ለምሳሌ አንተ አንድ የመንግሥት ልማታዊ ድርጅት ግዛ ብትባል እሺ ብለህ ዝም ብለህ አትገዛም። የምታየው ነገር አለ። ሀብትና እዳው ምን ይመስላል? አያያዙ እንዴት ነው? ትርፋማ ነው ወይ? የሚለውን ማየት ትፈልጋለህ። ማን ገዢ ነው የተዝረከረከን ድርጅት ሳታስተካክለው መጥቶ የሚገዛው ? መንግሥትስ ጥሩ ገንዘብ ያገኝበታል ? ልሽጥ እንኳን ብትል የመጣል ያክል ነው የሚሆነው። ስለዚህ የመንግሥት የመጀመሪያ ሥራ የነበረው በአገር በቀል ሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ እነዚህ የልማት ድርጅቶች የተሻለ ይዞታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ ትርፋማ እንዲሆኑ፤ የተዝረከረከው አሠራር እንዲሻሻል እና እንደቢዝነስ መመራት እንዲችሉ ካደረጃጀታቸውና ከአሠራራቸው ጀምሮ ጥረት ተደርጓል። ከነበረባቸው እዳ ወደ ሰባት መቶ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ነው የተነሳላቸው። ይህ ትልቅ ርምጃ ነው። ስለዚህ ጭራሽ መሸጥ የማይችሉት የነበሩትን ለመሸጥ ወደሚችሉበት ደረጃ ማድረስ የራሱ ጊዜ የሚወስድ ነበርና ያ ሲደረግ ነበር የቆየው።
በዚህ ሂደት ውስጥ በአመራራቸው ምክንያት ፈጥነው ለመሻሻል የቻሉ የልማት ድርጅቶች አሉ። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም በጣም በፍጥነት ለውጥ ያሳየ ለአገር ኢኮኖሚም ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ተቋም ነው። ውስጡ የተሠራው ሪፎርም በፍጥነት የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት በመቻሉ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ዝግጁ የሆነ ተቋም በመሆኑ አሁን አትራፊና ሳቢ ሆኗል።
ኢትዮ ቴሌኮም የህዝብ ተቋም ነው። ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሰዎችን ወይም የአገራትን የኢንቨስትመንት ውሳኔ በጣም ይወስናሉ። በጣም ጥሩ የሆነ ዓመትና ጥሩ ያልሆነ ዓመት ላይ የአንድ ግለሰብ ኢንቨስትመንት ውሳኔ ይለያያል። በዓለም ላይ አሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ዓመት የምንለው አይነት አይደለም። ዓለማችን ፐርፌክት ስቶርም የምንለው አይነት ችግር አጋጥሟታል። የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ አለ፤ ዓለማአቀፋዊ ሁኔታም አለ፤ ለዘመናት የተገነባን የሕዝብና የሀገር ሀብት በዚህ አይነት ጊዜ ለመሸጥ ብታወጣ ጥሩ ዋጋ አያስገኝልህም። የገዢው ሀሳብም ውሳኔም ስለሚወስን ያለው ሁኔታ እስኪሻሻል መጠበቁ የተሻለ ስለሆነ የተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።
ሌሎቹንም በቅድሚያ ውስጣቸውን ሙልጭ አድርጎ ማጽዳት ያስፈልጋል። የተቀበለው ዱላ በጣም ብዙ ችግር ያለበት በመሆኑ መንግሥት ያንን ሥራ እየሠራ ነው። ለዘመናት ኪሳራ ሲያስመዘግቡ የነበሩ ከአርባ በላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ነበሩ። አሁን ከሁለት የልማት ድርጅቶች በስተቀር ሁሉም ድርጅቶች ትርፍ ማስመዝገብ ጀምረዋል። ይሄ ነው የሚበልጠው ፤ ሪፎርማቸው ውጤታማ ሆኗል ማለት ነው።
ዘመን፡- የመንግሥት የካፒታል በጀት በእቅድ በተያዙ እና አዋጪነታቸው በታመነባቸው የመንግሥት ኢንቨስትመንቶች ላይ ብቻ መዋል እንዳለበት፣ ተፈፃሚነቱንም ለማረጋገጥ ጥብቅ የሆነ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ በሕግ ተደንግጓል። የካፒታል በጀት በታሰበው ልክ ለተፈለገው ዓላማ ብቻ መዋሉን ለማረጋገጥ ተቋማዊ አሠራር እንዲኖር በማድረግ ደረጃ እርሶ በኃላፊነት የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያቤት ምን ያህል ርቀት መጓዝ ችሏል?
ዶክተር ፍጹም ፡- በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ውስጥ ከተሠሩ ትልቅ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር አዋጅን ማጽደቅ ነበር። ይህ አዋጅ ከጸደቀ በኋላ አንድም ፕሮጀክት ዝም ብሎ ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ ሄዶ የመሠረት ድንጋይ የጣለባቸው ፕሮጀክቶች የሉም። እያንዳንዱ ፕሮጀክት ከጽንሰ ሐሳብ ጀምሮ እስከ ሙሉ አዋጭነት ጥናት ሂደት ስድስት ደረጃዎች ያሉት ስለሆነ እነዚህን ደረጃዎች ማለፍ አለበት።
እነዚህን ደረጃዎች ካለፈ በኋላም አንደኛ ከሀገር የልማት እቅድ ጋራ የሚሄድ መሆኑ፤ ሁለተኛ በመንግሥት መሠራት ያለበት በግሉ ዘርፍ ሊሠራው የማይችል መሆኑ ፤ ሶስተኛ ባለን ውስን ሀብት አሁን ቢሠራ ይሻላል ወይስ በሚቀጥለው ዓመትና በቀጣዮቹ ዓመታት መሰራት መቻሉ እንዲሁም በአዋጪነቱ ጥናት ረገድ ደግሞ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ አዋጭነቱ በአካባቢው ማህበረሰብ እና አካባቢ ላይ ያለው ተጽዕኖ ይፈተሻል። ይሄን ሁሉ የሚያሟላ ፕሮጀክት መቀጠል ይችላል ብለን ከዚህ አረንጓዴ ካርድ ስንሰጠው ገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ገንዘብ ይመድብለታል። ስለዚህ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ አንድም ፕሮጀክት በዚህ ስርዓት ውስጥ ሳያለፍ የገንዘብ ምደባ የተደረገለት የለም።
በዚህ የአሰራር ስርዓት አንደኛ የማያዋጡ ፕሮጀክቶች ማስቀረት ተችሏል። ሁለተኛው የሚያዋጡም ሆነው የግሉ ዘርፍ መሥራት የሚችለው ከሆነ ለምን መንግሥት ይሠራዋል በሚል የቀሩ አሉ። ሌሎች ደግሞ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አንድ አይነት ይዘት ያላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ጋር ሰብሰብ ብለው መሠራት ሲችሉ ተበጣጥሰው ይሠሩ የነበሩ ፕሮጀክቶች ሰብሰብ ተደርገው እንዲሠሩና ውጤታማ እንዲሆኑ የራሱን ሚና ተጫውቷል። ሌላኛው ደግሞ ማንም ሀገር ላይ ሪሶርስ ውስን ነው፤ ካለን ሪሶርስ ውስንነት አንጻር ፕሮጀክትን ቅደም ተከተል ለማስያዝ ይሄ ከዚህ ቀጥሎ ይሄኛው በዚህ ዓመት ሌላኛው በዚያ ዓመት የሚለውን ለመሥራት የራሱን ሚና ተጫውቷል። ከዚህ አኳያ በጣም ስኬታማ ሪፎርም ከምንለው ውስጥ ይሄኛው ነው ብዬ አስባለሁ።
ዘመን፡- ሥራ ላይ ከዋለው አዲስ አዋጅ በኋላ የማያዋጡ ናቸው በሚል የተሰረዙትን ፕሮጀክቶች በቁጥር ወይም በአይነት መጥቀስ ይችላሉ ?
ዶክተር ፍጹም፡- ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ። በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 130 ፕሮጀክቶች አይተናል። ወደ 30 በመቶ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች መንግሥት ጭራሽ መሥራት የለበትም የግሉ ዘርፍ ሊሠራው የሚችል ፕሮጀክት ነው በሚል ውድቅ ሆነዋል። ይሄ አዋጅ ባይኖርና ይሄ አሠራር ባይዘረጋ ኖሮ እነዚህ ሰላሳ ፐርሰንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ይገቡ ነበር። አንድ ፕሮጀክት ውድቅ ተደረገ ማለት ተመልሶ አይመጣም ማለት ነው። ውድቅ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ውድቅ ባይሆኑ ኖሮ ገንዘብ ያለአግባብ ያስወጡ ነበር።
ዘመን፡-30 በመቶዎቹ ፕሮጀክቶች ከአዋጁ በፊት በመንግሥት ይከወኑ የነበሩ ናቸው?
ዶክተር ፍጹም፡- አዎ በመንግሥት ይከወኑ የነበሩ ናቸው። ቀደም ሲል አሁን የያዝነውን አይነት አሠራር ስለሌለ ማንኛውንም ፕሮጀክት ማሳመን እስከቻልክ ድረስ ገንዘብ ታገኛለህ። እኔለዚህ ተቋም አንድ ፕሮጀክት ሳስብ ገንዘብ ሚኒስቴር ሄጄ ማሳመን ከቻልኩኝ ገንዘብ አገኛለሁ። ያ ፕሮጀክት አዋጪ መሆኑ እና መንግሥት መሥራት ነበረበት ወይ ወዘተ. የሚሉ ነገሮች አይታዩም ነበር። ስለዚህ ይህ ነበር ትልቁ ችግር የነበረው። አዲስ የዘረጋነው የአሠራር ስርዓት ባይኖር ኖሮ በእርግጠኝነት ብዙዎቹ ወደ ሥራ ይገቡና አሁን ያየናቸውን አይነት የሀገርና የሕዝብ እዳ ፕሮጀክቶች አካል ይሆኑ ነበር።
ዘመን፡- ቀደም ሲል በነበረው የካፒታል በጀት አጠቃቀም ምክንያት ኢትዮጵያ የተሸከመችው እዳ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈላት ነው ?
ዶክተር ፍጹም፡- የስኳር ፕሮጀክቶችን ብቻ ብንወስድ አስር የሚሆኑት አዲስ ፕሮጀክቶች ናቸው። አስሩም ፕሮጀክቶች አንድ ላይ ሲጀመሩ በጣም ብዙ ብር ነው የተበደርንባቸው፤ በኮሜርሻል ብድር አምጥተን። የነበረው እቅድ ያንን ብድር አምጥተን ቶሎ ወደ ሥራ ተገብቶ ስኳር ሸጠን እንከፍላለን፤ የስኳር ፍላጎትም በአገር ምርት እናሟላለን የሚል ነው። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች አምርተው ሸጠው ብድራቸውን መክፈል አይደለም ማለቅ እንኳን አልቻሉም። እዳ ነው የተረከብነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ስነጋገር ያነሳው አባባል በጣም ነው የገረመኝ። ካፒታል ኢንቨስት ከተደረገ ሞቷል ነው የሚባለው። ሰው ከሆነ ከሞተ አስከሬን ነው ትቀብረዋለህ። ከዚያ በኋላ ከዚያ አስከሬን ጋር በተያያዘ ምንም ችግር የለብህም። በፕሮጀክት ወይም በኢንቨስትመንት ግን የሞተ ካፒታል ብድር አስከሬኑ እየተንቀሳቀሰ እንደሚያስቸግርህ አይነት ማለት ነው ብሎ ነው የገለጸው። ምክንያቱም ብድር መክፈል አለብህ። የሞተው አስከሬን ሞቶ ቢቀር ኖሮ ጥሩ ነበር፤ ብድር ስላለበት መከፈል አለበት። እዚህ ጋ ገንዘብ የለም ብድር ብቻ መክፈል ነው የሚሆነው።
ዘመን፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውና በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አተገባበር ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎች እንዴት እየተስተናገዱ ነው ?
ዶክተር ፍጹም፡- እንደሚታወቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው። ስለሆነም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ በአገራችን ላይም በዚያው መጠን ማለት ነው። በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከህልውና ዘመቻውም ጋር ተያይዞ የነበረው ሁኔታ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱ አንድምታ፣ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ምንም የማይካድ ነው። እንግዲህ በዚህ አሉታዊ ተጽዕኖ ውስጥ ሁሉ ሆኖ ኢኮኖሚው እንዴት አለፈ? እንዴት ተመራ? የሚለውን ለማየት ውጤቶቹን መዳሰስ በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ።
ጥያቄውን በአጭሩ ለመመለስ የወጪ ንግዳችንን ስንመለከተው በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከፍተኛ መጠን ተመዝግቦ የሚያውቀው ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እንደ አይ ኤም ኤፍ እና ወርልድ ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የዓለም አገራት በኢኮኖሚያቸው ላይ ሊያጋጥማቸው ይችላሉ ካሏቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ የውጪ ንግድ ገቢያቸው ይቀንሳል የሚል ነው።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና አሁን ያለው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ግጭት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ እና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች ጭምር አጋጥመውናል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነን አምና 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግበናል። ዘንድሮም በዘጠኝ ወር ውስጥ ከአምናው ዘጠኝ ወር በከፍተኛ ደረጃ የሚበልጥ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ የወጪ ንግድ ተመዝግቧል። ይህ አፈጻጸም በራሱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው ግጭት ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳይጎዳው አድርጓል። ይህ በአንድ እጅ የአገር ሉአላዊነትን ለማስከበር የህልውና ዘመቻውን በመወጣት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ የታቀዱ ተግባራትን ለማሳካት የተደረገውን ጥረት ውጤታማነት አመላካች ናቸው።
በጦርነቱ ምክንያት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ አካባቢዎች ምርት ማምረት እንደማይችሉ ይታወቃል። ሊፈጠር የሚችለውን እጥረት ለማካካስ በሌሎች አካባቢዎች ለግብርና ምርት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። የተሰጠው ትኩረት እና የተገኘው ውጤት ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን ዘርፉ በአግባቡ የተመራበትን ሁኔታን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ በግብርና ምርት የተገኘው ትልቅ ዕምርታ ኢኮኖሚው በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተጎዳ ቢሆንም፣ ጉዳቱ ከዚህ የባሰ እንዳይሆን በአንዱ አካባቢ የታጣው የግብርና ምርት በሌላ አካባቢ እንዲተካ የራሱን ሚና ተጫውቷል።
በሌላ በኩል ማዕድንን ብንመለከት ማዕድን በታሪኩ ተመዝግቦ የማያውቀውን ገቢ አስገኝቷል። አምና ብቻ በወር ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ችሏል። ማዕድን ማለት ከግጭት ጋር በጣም የሚዋደድ ነገር ነው፤ ግጭት ካለ ማዕድን የለም። የትም አገር ብትሄድ ግጭት የሚኖረው ማዕድን ያለበት አካባቢ ነው። በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆነን በጣም በከፍተኛ ጥረት ከክልሎችም ሆነ ከአካባቢ ማህበረሰብም ጋር ተባብሮ በመስራት በዚህ ዓመት የተጠበቀውን ያህል እንኳ ባይሆን ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ካመጡት የውጭ ንግዶች ውስጥ አንዱ የማዕድን ምርት ነው።
ይህንን ሁሉ ችግር ለመቋቋም ኢኮኖሚው ሳይረሳ ፤ ጦርነት ስላለ በጦርነቱ ላይ ብቻ አተኩረን ሁሉን ነገር ወደ ጦር ግንባር ሳንል፣ የሚያመርተው እንዲያመርት ኢኮኖሚው እንዳይወድቅና ከከፍተኛ የዕድገት ምህዋር እንዳይንሸራተት ለማድረግ ትልቅ ሥራ ለመስራት ጥረት ተደርጓል። በፋይናንስ ዘርፍ የተከናወኑ ሁሉንም ተግባራት ለመዘርዘር ስለሚከብድ ነው እንጂ በዚህ ግጭት ውስጥ በጣም የሚገርሙ እና የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ነገር ግን ግጭቱ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው አይካድም። ይሁን እንጂ ኢኮኖሚው ያንን አሉታዊ ተጽዕኖ መቋቋም እንዲችል ተደርጎ በስርዓት ተመርቷል።
ዘመን፡- በተለይ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በደረሰው ጉዳት ምክንያት የተፈጠረው ፈርጀ ብዙ ችግር ራሱን እየገለጸ የሚሄደው በቀጣይ ጊዜያት እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህን ከግንዛቤ ያስገቡ ዝግጅቶች አሉ ?
ዶክተር ፍጹም፡- በትክክል! በችግሩ ልክ ዝግጅቶች ተደርገዋል። እንዲያውም ከዚህ አኳያ ለመጥቀስ የምፈልገው ነገር የተከናወኑ ተግባራት እንደሀገር ጠቅለል ያለ የኢኮኖሚ ጫናውን በደንብ ጎልቶ እንዳናየው ሊያደርጉን ይችላሉ። በሌላ አካባቢ የተሰራው ሥራና የተደረገው ጥረት ችግሩን እንዳይሸፍነው መግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ጦርነቱ በነበረበት አካባቢ ያሉ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ በዜጋ ደረጃ ሲታይ ተጎድተዋል።
እኛ የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ የልማት ግቦችን ተቀብለን እንደራሳችን ዕቅድ አድርገንም በዕቅዳችን ውስጥ አካተን አቅደናል። የዘላቂ የልማት ግቦች ዋና መርህ ደግሞ ማንም ወደ ኋላ መቅረት የለበትም (living no one behind) የሚል ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ እንደሀገር በኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ሁሉም ዜጋ ይገነዘበዋል ብዬ አስባለሁ። በዋናነት መረሳት የሌለበት ነገር ጦርነቱ በነበረባቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች በእያንዳንዳቸው ሕይዎት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል
አለመሆኑን ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ገንዘብ ሚኒስቴር ራሱን የቻለ የመልሶ ማቋቋምና መገንባት (rehabilitation and construction) ሴክሬታሪያት አደረጃጀት ፈጥሮለታል። ከልማት አጋሮችም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ተገኝቷል፤ መንግሥትም በጀት መድቦለታል። በመሆኑም ወደ መልሶ መቋቋምና ግንባታ ተግባር የምንገባ ይሆናል፤ ዕቅዱም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ዘመን፡- በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በዓለም ላይ በታየው የኢኮኖሚና ንግድ ስርዓት መረበሽ እንዲሁም አሁን ስናነሳቸው በነበሩት አገር በቀል በሆኑ ችግሮች ምክንያት የተፈጥሮ ችግሮችም ጭምር ስለስተዋሉ ጫናዎች አሉ። እነዚህን ጫናዎች ለመሻገር እንደሀገር ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ፍጹም፡- እርግጥ ነው የራሺያና ዩክሬንን ጦርነት ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዲባባሱ ሊያደርጋቸው ስለሚችል የሚያደርሰው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናየው ራሺያና ዩክሬን ለዓለም የምግብ እህል በተለይም ስንዴ በማቅረብ ትልቅ ድርሻ አላቸው። ማዳበሪያን ራሳቸው አምርተው ከማቅረብ በተጨማሪ ለሌሎች ማዳበሪያ ለሚያመርቱ አገራት ፖታሺየም እና አሞኒያ የተባሉትን ጥሬ ዕቃ ግብዓቶች ብቻቸውን 80 በመቶ የሚያመርቱት ዩክሬንና ራሺያ ናቸው።
ዩክሬንና ራሺያ ራሳቸው አምርተው የሚያቀርቡት ማዳበሪያ ብዙ ባይሆንም፣ የማዳበሪያ ግብዓቶችን ከእነሱ ገዝተው ማዳበሪያ ለሚያቀርቡ አገራት ግን በዚህ ጦርነት ምክንያት ትልቅ ተግዳሮት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ዩክሬን የምግብ ዘይት በተለይም የሱፍ (sunflower) የምግብ ዘይት ትልቅ አቅራቢ አገር ናት። ራሺያ ደግሞ ለብቻዋ የዓለምን ወደ 11 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ አቅርቦት ትሸፍናለች። በመሆኑም በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በጣም ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለዚህም ነው ሁሉም እንደሚገነዘበው የዓለም የገበያ ዋጋ በመናጋት ላይ የሚገኘው። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የምግብ ዋጋን በተለይም የስንዴን እና የማዳበሪያን ዋጋ ብንመለከት በሚገርም ሁኔታ ጨምሯል። የነዳጅ ዋጋም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ ንሯል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነዳጅ ለማያመርቱና ከውጪ ገዥ ለሆኑ አገራት ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ነው።
ስለዚህ መንግሥት ከዚህ አኳያ በሀገራችን ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መስራት ያለበት ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ታሪክ እንደሚያስረዳን በዓለም ላይ ያሉ አገራት የዚህ ዓይነት በዓለምም በአገር ውስጥም በጣም ከባድ ጋሬጣና ተግዳሮት ሲያጋጥማቸው ችግሩን ለመሻገር ከህዝባቸው ጋር ተነጋግረው፣ ተመካክረው እና ተባብረው የሚያልፉባቸውን ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ግብር ነው። ህብረተሰቡ ግብርን በተመለከተ የሚጠበቅበትን ግዴታ ለመወጣት በፍጹም ወደ ኋላ ማለት የለበትም። በተለይም ደግሞ ከንግድ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ትልቁ ጉዳይ ነው። ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ሌላው ተግባር በህገ- ወጥ ንግድ ውስጥ አለመሳተፍ፣ የሚሳተፉትንም ማጋለጥ ያስፈልጋል።
የዩክሬንና የራሺያ ጦርነት መቼ እንደሚያቆም አናውቅም፣ እርግጠኛ ሆኖ መናገርም በፍጹም አይቻልም። እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ እውነታዎች በጣም ተቀይረዋል። ድሮ ግሎባላይዜሽን በምንለው የትም አገር ቢመረት ገዝቶ መጠቀም ይቻላል። የካፒታልና የሰው ኃይል ፍሰቱም በጣም ቀላል ነበር፣ ምርቶች የግድ ከእኔ ሀገር ካልተመረቱ የሚል ነገርም አልነበረም። አሁን ላይ ግን ሀገራት ከኮቢድ 19 መከሰት ወዲህ በተለይም የዓለም የሎጂስቲክስ ሰንሰለት ሲቋረጥ፣ በሚመጣው ወር እገዛዋለሁ የምትለውን ዕቃ ገንዘብ ቢኖርህ እንኳ የማትገዛበት ሁኔታ ያጋጥምሃል። ስለሆነም አገራት ወደ ውስጥ እንዲያዩ እና በተለይም ወሳኝ የሆኑ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ እንዲያመርቷቸው አድርጓቸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ብድርና ዕርዳታ፣ለድሃ ሀገራት ይሰጡ የነበሩት ዕገዛዎች፣የሰብዓዊ እና የልማት ድጋፍ እንኳ ማድረግ በዚህ በጂኦ ፖለቲክሱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። የራሺያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ዓለም ሁሉ ፊቱን ወደ ጦርነቱ አዙሯል። መድኃኒት ለማግኘት እንኳን በጣም ከባድ ሆኗል። እንደ ስንዴ የመሳሰሉት በሙሉ ከዩክሬን ለተፈናቀሉት ቅድሚያ እየተሰጡ ነው።
በመሆኑም አሁን ላይ እኛ ወደ ውስጥ ማየት መጀመር ያለብን ይመስለኛል። ሁኔታውን እኛ ኢትዮጵያውያን ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። የአመጋገብ፣ የአኗኗር፣ የቁጠባ፣ የነዳጅ አጠቃቀምን ባህላችንን መፈተሽ ይገባል። በተለይም የነዳጅ አጠቃቀማችንን እያንዳንዳችን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት መፈተሽ የምንጀምርበት ወቅት ነው። ያለንን የውጭ ምንዛሪ ከፍለን ነው ነዳጅ ከውጭ የምናስመጣው። ችግሩን እንድትሻገር እያንዳንዱ ዜጋ እኔ ምን ልወጣ ብሎ የሚያስብበት ወቅት ላይ እንገኛለን። መንግሥት ችግሩን ለመቋቋም የሚያወጣቸውን ህጎች እና የሚወስዳቸውን እርምጃዎችም መደገፍና መተባበር ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ።
ዘመን፡- የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ፍጹም ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ
ዘመን መጽሄት ግንቦት 2014 ዓ.ም