በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 የሚገኙ ወጣቶች ዘወትር እሁድ እሁድ ጠዋት ከአስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ከኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪ ወደ አፍሪካ ህብረት የሚወስደውን ባለሁለት መስመር ዋና አስፋልት መንገድ አንደኛውን በመዝጋት እግር ኳስ ይጫወቱበታል፡፡ የመኪና መንገድ ዘግተው ለመጫወት የተገደዱበትን ምክንያት ወጣቶቹ ሲገልጹ በወረዳው በተዘጋጀው ሜዳ ላይ ለመጫወት በሚፈልጉበት ቀን ሜዳው ከፍለው በሚጫወቱ እንደሚያዝባቸው፣ ቀደም ሲል ሲጫወቱበት የነበረው ፈረስ ሜዳ ተብሎ የሚጠራው መጫወቻ ሜዳቸው ደግሞ ያለ አገልግሎት ለዓመታት በመታጠሩ የሚጫወቱበት ቦታ በማጣታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡ ፡ ስለሆነም ወጣቶቹ መንገድ ሳይዘጉ መጫወት እንዲችሉ ቀደም ሲል ሲጫወቱበት የነበረው ሜዳ ክፍት እንዲሆንላቸው በመጠየቅ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
ለዚህ ቅሬታ ምላሽ የሰጡን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የስፖርት ተሳትፎ፣ አካል ብቃትና ፋሲሊቲ ቡድን አስተባባሪ አቶ ስማቸው ይዘንጋው እና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጠብቀው አመሸ ናቸው፡፡
አቶ ስማቸው ይዘንጋው፡- በ2013 ዓ.ም. ወደ 42 የሚጠጉ ወጣቶች ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት የነበረው ፈረስ ሜዳ ተብሎ የሚታወቀው የመጫወቻ ሜዳቸው ያለጥቅም የታጠረባቸው መሆኑን በመግለጽ ክፍት እንዲሆንላቸው በፊርማ የተደገፈ ደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከጽ/ቤቱ አቅም በላይ ስለሆነ በወቅቱ ለክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት በደብዳቤ ጠይቀናል፡፡ የደብዳቤው ይዘትም በአጥር ታጥሮ የሚገኘው ወጣቶቹ ቅሬታ ያቀረቡበት ፈረስ ሜዳ ተብሎ የሚታወቀው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ከተቻለ ቦታው በወረዳው ስፖርት ማዘውተሪያነት ተይዞ ህብረተሰቡ እንዲጠቀምበት፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ለተፈለገው ተግባር እስኪውል ድረስ በጊዚያዊነት ወጣቶቹ መገልገል እንዲችሉበት ክፍት እንዲሆን የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ምላሽ አልተገኘም፡፡ በወረዳው የተዘጋጀውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ በተመለከተ ግን ህብረተሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል በክፍያም ሆነ በነጻ ትብብር የሚደረጉባቸው የቀናት እና የሰዓታት ፕሮግራሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ በፕሮግራም ከተያዙት ጊዜያት ውጪ ደግሞ ማንኛውም አካል የትብብር ጥያቄ ካቀረበ በመግባባት በነጻም ሆነ በክፍያ በሜዳው እንዲጠቀሙ ፕሮግራም ማስያዝ እንደሚቻል ወረዳው ዝግጁ ነው፡፡
አቶ ጠብቀው አመሸ፡- ወጣቶቹ ያቀረቡትን የፈረስ ሜዳን በስፖርት ማዘውተሪያነት እንጠቀምበት ጥያቄ ተይዞ ከክፍለ ከተማው መሬትና ልማት ማኔጅመንት ኃላፊዋ ጋር ተነጋግረንበታል፡፡ ቦታው ግን ለሆስፒታልነት መያዙንና በጊዚያዊነት ለስፖርት ማዘውተሪያነት ለመፍቀድ ደግሞ መሬትን በጊዚያዊነት ለማስጠቀም የሚያስችል መመሪያ ባለመኖሩ ለመፍቀድ እንደሚቸገሩ ተገልፆልናል፡፡ የወጣቶቹን ችግር ለመቅረፍ ግን በክፍለ ከተማ ደረጃ 17 የሚደርሱ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የሚገኙት በት/ቤቶች ውስጥ ስለሆነ በቅርቡ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከትምህርት ቢሮ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ከስምምነቶቹ መካከል አንዱ በት/ቤቶች ሜዳዎች ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ስለሆነም ወጣቶች አጠገባቸው በሚገኘው የእውቀት ምንጭ ት/ቤት ሜዳ በሚፈልጉበት ቀንና ሰዓት መጫወት እንዲችሉ ከት/ቤቱ ርዕሰ-መምህር ጋር በመነጋገር ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ በክፍለ ከተማው አስፋልት ላይ የሚጫወቱ ወጣቶችን በመለየት በሚቀርባቸው ሜዳ በፕሮግራም እንዲጠቀሙ በማድረግ ለትራፊክ አደጋ የማይጋለጡበት ሥራ ይሠራል፡፡
ስሜነህ ደስታ
ዘመን መጽሄት ግንቦት 2014 ዓ.ም