በአገራችን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተስፋፋ መሄዱ ይነገርለታል። የምዕራባውያኑ ምክንያታዊ አመለካከትና የዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ለድርጊቱ መበራከት ዋቢ ሆኖ ይጠቀሳል፤ ‹‹ግበረሰዶማዊነት››።
ሃይማኖታዊ መዛግብት እንደሚያስረዱት፤ የግብረሰዶም ታሪክ ከ 4 ሺህ ዓመታት በፊት በዮርዳኖስ ሸለቆ ከተቆረቆሩት ከተሞች አንዷ ከሆነችው የሰዶም ከተማ ይነሣል። በአቅራቢያዋ ትገኝ የነበረችው ገሞራም የዚሁ ታሪክ አካል ሆና ትጠቀሳለች።
በቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 19 የሰፈረው ቃልም ስለ ዘመኑ እውነታ በግልጽ ይጠቁማል። በዚህ ዘመን የሰዶምና ገሞራ ሰዎች ተፈጥሮና ሃይማኖት ከሚፈቅዱት የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት የዘለለ ግብር ነበራቸው። በዚህ የኃጢአት ድርጊታቸውም ፈጣሪን በእጅጉ ያስከፉና ያሳዝኑ ነበር። ፈጣሪ ይኸንን ሐዘን ግ ን በዝምታ ብቻ አላለፈም።
ድርጊታቸው የእግዚአብሔርን ትዕግሥት በእጅጉ ተፈታተነ። አምላክ በራሱ ፍጥረታት አንዲያዝንና፣ እንዲቆጭም ምክንያት ሆነ። አብዝቶ የቆየው የእግዚአብሔር ትዕግሥት አንድ ቀን ተቋጨ። ሐዘን ቁጣው በእጅጉ አየለ። ይህ ብቻ አልበቃም። በሁለቱ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን አዝንቦ ሰዎቻቸውን ከምድረ ገጽ አጠፋ።
‹‹ሰዶምና ገሞራ›› ይሏቸው ከተሞች ከጥልቅ የጨው ባሕር ተሸፍነው እስከ ወዲያኛው ጠልቀው ጠፉ። የከፋ ግብራቸው፣ ነውር የሚባል አሻራቸው ግን ዛሬም በስማቸው ታትሞ የዘመናችንና የትውልዱ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል።
አቶ ብርሃኑ ራቦ የሞሽን ማማከርና ሥልጠና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የሕይወት ክህሎት አሠልጣኝ ናቸው። የአፈንጋጭነት ልማዶች በሁለት እንደሚከፈሉ ይገልጻሉ። ‹‹አዎንታዊና አሉታዊ አፈንጋጭነት›› በሚል።
አዎንታዊ አፈንጋጭነት፤ አንድ ሰው በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚያየው እውነታ በመነሣት የራሱን አቋም ይዞ ‹‹እምቢኝ›› ሲል የሚያፈነግጥበት ሂደት ነው። ይህ ሰው እንዲህ ማድረጉ ፋይዳው ለአገርና ለወገን፣ ህልውና ለማኅበራዊ ሕይወትና ቀጣይ ግንኙነት፣ ለሰውልጆች ጤናማ መሠረት የሚረዳ እስከሆነ ማፈንገጡ ጤናማ ነውና አዎንታዊ ይሆናል።
ይህ እውነታ አመለካከትን በመገንባት፣ ሐሳብን በማቃናት፣ መልካምነትን በመዝራት የማኅበረሰቡ ጣራና ግድግዳ የመሆን ጥንካሬ አለው። ከዚህ ባለፈ አንድ ሰው ወይም ቡድን ለሞራልና የኅሊና ፍርድ፣ ለማኅበረሰቡ አኗኗርና ዘይቤ ተቃራኒ ሆኖ ማኅበረሰቡ የተሰፋበትን ድር የሚበጣጥስ፣ የቆመበትን መሠረት የሚንድ ሆኖ ሲገኝ ድርጊቱ በአሉታዊ ማፈንገጥነት ይገለጻል።
ይህ መሰሉ ማፈንገጥ ከማኅበረሰቡ ማንነት ተቆርጦ የመውደቅ ባሕርይ አለው። በአንድም በሌላ የማንነት ህልውናን በግልጽ የመጉዳት ልማድን ይከተላል። ድርጊቱ ከአስተሳሰብ ባለፈ በሰው ልጆች ጤናማ ሕይወት እንደጠንቅ ተፈርጆ የሚታይ ነው።
አቶ ብርሃኑ እንደሚሉትም፤ የዓለም ጤና ድርጅት ‹‹ጤና›› የሚለውን ትርጓሜ የሚያየው በአካል መታመም ላይ ብቻ አይደለም። ማፈንገጥ ይሉትን ልማድ የአንድ ሕመም መገለጫ አድርጎ በማስቀመጥ ጭምር እንጂ።
አንድ ሰው በንግግርና በአስተሳሰብ፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና፣ በሞራላዊ ሁነት ከመደበኛ ማንነቱ አፈንግጦ ሲገኝ የጤናማነት ጸጋ አይኖረውም። በምትኩ ድርጊቱ ከሕመም ተፈርጆ በማፈንገጥ ባሕርይው ይገለጻል።
ይህ ዓይነቱ ልምምድ እንዴት ይመጣል? የሚለው ሲመረመርም ምላሹ ከብዙ አቅጣጫ ያደርሳል። አሁን የአለንበት ዘመን ዓለም በአንድ መስኮት የሚተያይበት፣ ሚስጥርና ገበናውን የማይደባበቅበት ጊዜ ነው። ይህ እውነታም አንዱ ማኅበረሰብ በሌላው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ዕድሉን ያሰፋል።
በምጣኔ ሀብት፣ በፖለቲካና በቴክኖሎጂ ምጥቀት የበላይነት ያለው አካል ምንግዜም ለመደመጥ የበላይነቱን መውሰድ ይፈልጋል። ሁሌም የእሱ በሆነ ጉዳይ ላይ እንዲጨበጨብለት የማድረግ ኃይልም ከእሱጋር ነው። በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተናገረው እንዲጸድቅ፣ የተነፈሰው እንዲታመንለት ይፈልጋል። ማንም ከፊቱ እንዳይቆም የማስገደድ ጉልበቱም ኃያል መሆኑ ግልጽ ነው። አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት ምዕራባውያን ማለት እንደዚህ ናቸው። ብዙዎችን በተለየ ተጽዕኖ ተብትበው የበታቾቻውን በመሸበብ መግዛትና፣ ማሸነፍን ይሻሉ።
ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ለማኅበረሰቡ ሞራል፣ ባህልና ስሜት ያልተመቹና የአልተለመዱ አፈንጋጭ ድርጊቶች እንዲስፋፉ በር ከፋች ይሆናል። የሰው ልጅ እጅግ የተከበረ ፍጥረት ሆኖ ሳለ አፈንጋጭነትን በመለማመዱ ብቻ እንደ ዕቃ ይሸጣል፣ ይሸቀጣል።
ግብረ ሰዶማዊነት በመንፈሳዊና በታሪካዊ ሂደት የራሱ መነሻ አለው። አቶ አበራም ይህንኑ እውነታ በማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። እሳቸው የዘመኑን ግብረሰዶም ሲገልጹት ድርጊቱ ታስቦበትና ታቅዶ በመከወኑ ከጥንቱ እንደሚለይ በማሳየት ነው።
ግብረ ሰዶማዊነት የሰው ልጆች ዘራቸውን እንዳይተኩና ሞራላዊ ማንነታቸውን እንዲጥሉ፣ መንፈሳዊ ኃያልነታቸውን እንዲያጡና ተፈጥሯዊ ጸጋቸውን እንዲነጠቁ ያደርጋል። ከዚሁ ተያይዞም ለአልተገቡ ዓላማዎች ተገዢ እንዲሆኑ የማስገደድ ኃይል አለው።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የበለፀገች አገር ናት። ዓለም የሚያውቃት ግን በኢኮኖሚ ዐቅም ኋላ ከሚባሉት ሀገራት ፊት ተሰልፋ ነው። ምንግዜም በሥልጣኔ የበለጸጉት ኃያላን በድህነት የሚገኙ አገሮችን ሊጠቀሙባቸው ዕድል ያገኛሉ። በዓለም የሚገኙ ክፉ አፈንጋጭ ድርጊቶችን ለመዝራትም በቀላሉ የሚመነዝሩት ዶላር ብዙ ርቀት ያራምዳቸዋል።
በአገራችን ስጋት ሆኖ ለተጋረጠው ግብረሰዶማዊነት አንዱ ምክንያት ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ስለመሆኑ ባለሙያው ይናገራሉ። አንዳንድ ሰዎች የተሻለ ዕውቀት ቢኖራቸው እንኳን በባዕዳን ምርኮ ለመያዝ ቅርብ ናቸው። ለአልተገባ ዘመናዊ እሳቤ መታለላቸውም ራስን ለሚያዋርድ፣ ባህልና እምነትን ለሚጥስ አፈንጋጭነት አሳልፎ ይሰጣቸዋል።
መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊና አነቃቂ መልእክቶችን በማስተማር ይታወቃሉ። የአፈንጋጭነትን ክፉ ባሕርያት በእጅጉ አነውረው፣ በጎ የሚባሉ አፈንጋጮችን ሲጠቅሱ ዛሬ ዓለማችን ለምትገኝበት ታላቅ ለውጥ ምክንያት መሆናቸውን በማስታወስ ነው።
እንዲህ ዓይነቶቹ ከሚሊዮኖች መካከል ተነጥለው በልዩነት ማፈንገጣቸው በርካታ በጎ ለውጦችን ለማምጣት አስችሏል።
የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዘመን አንሥቶ ከሰማያውያን መላእክት፣ ከምድራውያን አራዊትና እንስሳት ተለይቶ አእምሮና ልቦና ተሰጥቶታል። ሰው ማለት ነፍስና ሥጋ ተዋህዶ የተሰጠ የወል ስም ስለ መሆኑ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ይናገራሉ።
ሰው በስጋው ግዙፍ ነው። ይወልዳል ይዋለዳል፣ ይበላል ይጠጣል፣ ያገባል ይፈታል፣ ይታመማል ይሞታል። ከነፍስ አኳያ የሰው ልጅ ማንነት ሲቃኝም ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ይኖሩታል። ሰው በባሕሪው በበጎነት ሲቀረጽ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ይቅርታን ይላበሳል። ይህ ዓይነቱ እውነታ ሁሌም ለነፍስ ምግብ ነው። በመልካም ይመዘገባል።
መጋቤ ሐዲስ እሸቱ እንደሚሉት እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እነዚህን ሁለት ባሕሪያት አስታርቆ እንዲኖር ሕግ ሰጥቷል። ይህ ሕግ ውስጣዊው ከውጫዊው ስሜት ተስማምቶ፣ እንዲጣመር የሆነ ነው። ወንድና ሴት በተፈጥሮ ማንነታቸው ፍጹም ይለያያሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ፍላጎታቸው ጭምር በአንድ አይገለጽም። ይህ የሆነው እግዚአብሔር በሁለቱ መለያየት መሐል ሊፈጥረው የሚሻ ፍላጎት ስለአለ ነው።
አንዲት ሴት ወንድ ስታይ እንድትደነግጥ፣ ወንድም ሴቲቱን ሲመለከት በውበቷ እንዲሳብ የአደረገው የተፈጥሮው እውነታ ነው። እንዲህ መሆኑ ደግሞ በኃጢአትና ኃጢአተኝነት አያስፈርጅም። እንደመጋቤ ሐዲስ ገለጻ ይህ ጉዳይ የመሳሳብ ጸጋ ነው። ኃጢአት ሊሆን የሚችለው ይህን በተፈጥሮ የተሰጠን ጸጋ ያለቦታው ጥቅም ላይ የአዋሉት ከሆነ ነው።
ወንዱ የራሱን ጾታ ሲያይ ከደነገጠ፣ ሴቷም መሰሏን ስትመለከት ልውደድ ላፍቅር፣ ከአለች ድርጊቱ ክፉ አፈንጋጭነት ነው። እንደ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አባባል ሁለቱ ተቃራኒ ጾታዎች በተፈጥሮ ቢለያዩም በአምላክ የተቸራቸው አካል አንዱ ለሌላው እንዲስማማ ሆኖ ተዘጋጅቷል። የዘመናችን ፈተና ግብረ ሰዶማዊነት ግን ይህን ሕግ በእጅጉ የሚጥስ ነው። የጥሰቱ መገለጫም ሰማያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ መሠረትን የሚንድ ሆኖ ይገኛል።
የሴት ተፈጥሯዊ ጸጋ ዘርን መቀበል እንደመሆኑ ወንድም ዘርን እንዲያቀብል ሆኖ ተፈጥሯል። የዚህ ተፈጥሯዊ ሽግግር በተቃራኒው መተግበር ግን በግልጽ ተፈጥሮን መቃረን ነው። መጋቤ ሐዲስ እሸቱ እንደሚሉት ሴት ለወንድ፣ ወንድም ለሴት ብቻ እንዲሆኑ የተፈጠሩ ናቸው።
ተፈጥሮን ተቃርኖ ያለወጉ መገኘት ‹‹ማፈንገጥ›› ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይሆንም። ይህ የነውር ድርጊት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በእጅጉ የከፋ ነው። ሥነልቦናዊ ጉዳቱ የሚኖረው ስብራት ደግሞ በቀላሉ አይጠገንም። የሚያስከትለው ውስጣዊ ጸጸትም እንዲሁ።
መጋቤ ሐዲስ በዚህ ዓይነቱ ሕይወት ወደውና ፈቅደው ከሚያልፉት በርካቶቹ ጉድፈቻ ለመውሰድና ርዳታን ለመለገስ እጆቻቸው ሰፊ ነው። ከዚህ በስተጀርባ ሊኖር የሚችለው ድብቅ ተልእኮ እንዳለ ሆኖ አብዛኞቹ በዕድሜያቸው ማምሻ የሚከሠት ጭንቀትን ለማካካስ ሲሉ በጎነትን የሚከተሉ ናቸው።
ውስጣቸው የሚፈጠረውን ጫጫታ ለማስታገሥ በሚል በሚከፍቷቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ‹‹ግብረ ሠናይ›› መባልን ይሻሉ። መጋቤ ሐዲስ እንደሚሉት ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ጤናማና በጎ የሚባሉ አይደሉም። የፈጣሪን ሕግ በመጣስ የሰውን ምግባር የሚንዱና የሞራል ግጭት የተጠናወታቸው ናቸው።
በሠለጠነው ዓለም የምግብ፣ የልብስ፣ የመጠለያ ችግር የለም። ቴክኖሎጂው በሁሉም ሰው እጅ ለመድረስ ፈጣንና ቀላል የሚባል ነው። ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ግን አብዛኞች በድብርትና ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለዚህ ዋንኛው ምክንያትም በርካቶች በግብረ ሰዶማዊነት ሕይወት የመገኘታቸው ምስጢር ነው።
መጋቤ ሐዲስ በእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ኃጢአት ምድራችን የተፈተነችበትን ክፉ አጋጣሚ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው በምድራችን ታላላቅ የሚባሉ መቅሰፈቶች ወርደዋል። አንደኛው እግዚአብሔር በሰዶምና ገሞራ ሰዎች ተግባር ተቆጥቶ ምድርን በንፍር ውሃ የቀጣበት ነ ው።
ኢትዮጵያውያን ከምንታወቅበት ባህል ሃይማኖትና ነባር ትውፊት አኳያ ማንነታችንን ልንጠብቅ ይገባል የሚሉት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ፤ አገራችን በአሁኑ ጊዜ በሚያስፈልጓት በርካታ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ልናተኩር ግድ እንደሚል ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ዘመን ለትውልዱ ፈተና ሆኖ የተጋረጠውን ግብረ ሰዶማዊነት ለመታገል የሃይማኖት አባቶችና ፖለቲከኞች፣ መንግሥትና ሚዲያ፣ ቤተሰብና ማኅበረሰብ በእኩል ተሳትፎ ሊንቀሳቀስ ይገባል። መጋቤ ሐዲስ እሸቱ በአትኩሮት ያስተላለፉት መልእክት ነው።
እንደ እስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ፤ አላህ የሰው ልጆችን ወደምድር ሲያመጣ ማንነታቸውን በተፈጥሮ ላይ መሥርቶ ነው። የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ እንደሚሉትም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተሰጠው የሕይወት መመሪያና ሕግ ሰዎች በእምነትና ሥነ- ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ ያስገድዳል።
ይህ ይሆን ዘንድም ሃይማኖታዊ መመሪያዎች ተደንግገዋል። መመሪያዎቹ የሰው ልጆች በሁሉም ዘመን፣ ቦታና ወቅት በሁለንተናዊ ማንነታቸው፣ ክብራቸውንና እምነታቸውን እንዲጠብቁ የሚያዙ፣ የሚያስገነዝቡ ናቸው።
እነዚህን እውነታዎች መሠረት የአደረጉ የፈጣሪ ትእዛዛት ደግሞ በሁሉም በኩል ጠቀሜታዎች አላቸው። እንደሕግ የተከለከለው ጉዳይም እንዲሁ ፍጥረቶቹን ከጉዳት የሚጠብቅና የሚታደግ ነው። ኡስታዝ እንደሚሉት፤ በእስልምና ሃይማኖት ሕግ ጋብቻ ከተቀደሱ ተግበራት መካከል አንደኛው ነው። ፈጣሪ በፈቀደው አግባብ የሚደረጉ ግንኙነቶች መልካም ትስስር አላቸው። መውለድ መዋለድ፣ ራስን መተካት ይኖራልና እውነታዎቹ በቅድስና መዝገብ በክብር ተጽፈዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የሚታወቁ ልቅ ግንኙነቶች ነባሩን ማንነት የሚያጠፉ፣ የተወገዙና፣ የተጠሉ ናቸው። በእስልምና ሃይማኖት ሕግ በእንዲህ ዓይነቱ ጸያፍ ድርጊት የሚሳተፉ ቢኖሩ በእምነቱ ከፍተኛ ተብለው ከሚታወቁ ወንጀሎች መሐል አንዱን እንደፈጸሙት ይቆጠራል። እነሱም እንደ ከባድ ወንጀለኞች ይታያሉ።
እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ድርጊታቸው በእነሱ ብቻ አይቆምም። የተወገዘ ተግባራቸውን ወደሌሎች ሊያጋቡ ይፈጥናሉ። ኡስታዝ እንደሚሉት፤ በእምነቱ የተቀመጠው ሕግ ድርጊታቸውን በዝምታ የሚያልፍ አይደለም። ስለ ኃጢአታቸው ዋጋ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያዛል።
በቅዱስ ቁርዓን እንደተገለጸው፤ የሎጥ ዘመን ሕዝቦች የፈጣሪ ቁጣ የወረደባቸው ነበሩ። በዘመኑ የፈጸሙት ጸያፍ ድርጊት ለኃጢአታቸው ማሳያ ለትውልዳቸው መቀጣጫ ሆኗል። በእስልምና አስተምህሮት ይህ ታሪክ ለእምነቱ ተከታዮች ታላቅ ማስተማሪያ ይሆናል። በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚንጸባረቅ አፈንጋጭ ልማድ፣ ተፈጥሮን የሚቃረን ነው። የሰው ልጆችን ጤናማ ግንኙነት የሚሰብር በመሆኑም ተሞክሮው ለማንም ጠንቅ ይሆናል።
ድርጊቱ ተፈጽሞ ሲገኝ የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በቁርአንና የሐዲስ ትውፊት መመሪያ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። በሼርያ ሕግምእስከ መገደል የሚያደርስ የሞት ፍርድ ውሳኔ አለው።
የገደብ አልባ ነጻነቶችን መስፋፋት ከታላቅ ስጋት የሚቆጥሩት ኡስታዝ አቡበከር ለዚህ ስጋት ልጓሙ ሥነ ምግባር መሆኑን ይናገራሉ። እንደ እሳቸው እምነት አፈንጋጭነት ተፈጥሯዊ ባለመሆኑ ለሥነ ምግባር ተገዢ አይደለም። ለማኅበረሰባዊ ግንኙነቶችና ለጤንነትም አደጋ ይሆናል።
በእስልምና ሕግ ራስንም ሆነ ሌሎችን መጉዳት ፈጽሞ የተፈቀደ አይደለም። በተፈጥሮ የተሰጠን ጸጋ አክብሮ መያዝም አንዱ ግዴታ ይሆናል። በአግባቡ ከተቀመጠው እሳቤ መውጣት ደግሞ ሕግን መጣስ፣ መመሪያን መተላለፍ ነው።
ዛሬ ከሌሎች ዓለማት አልፎ በአገራችን ስጋት መሆን የጀመረው ግብረሰዶም ለትውልድ ጠንቅን የሚያወርስ ተግባር ነው። ኡስታዝ እንደሚሉት ከአደጉት አገሮች መውሰድ የሚገባን በርካታ በጎ ተግባራት አሉ። ይህን እውነት ተሻግሮ የማንነትን ዕሴት፣ ትውፊት፣ እምነትና፣ ባህል የሚጋፉትን ክፉ ድርጊቶች እጅ ዘርግቶ መቀበል መልካም አይደለም። ይህ ምርጫ ከሆነ ግን የትውልዱን አደጋ የሰፋ ያደርገዋል።
በእስልምና የሼሪያ ሕጎች መሠረት የሚዳኙ ጥፋተኞች ሁሉ ሌሎችን ለማስተማር ምክንያት ናቸው። ቃሉ የሚያስተምረውም ‹‹እናንተ አስተንታኝ የሆናችሁ የዓዕምሮ ባለቤቶች ተፈጥሮን በሚያዛቡ ሰዎች ላይ በሚወሰዱ ርምጃዎች ሕይወት አላችሁ›› ሲል ነው።
የገደብ አልባ ነጻነቶችን መስፋፋት ከስጋት የሚቆጥሩት ኡስታዝ አቡበከር ለዚህ ስጋት ልጓሙ ሥነ ምግባር መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው ሥነ ምግባር የሌለው ማኅበረሰብ እንደወደቀ ይቆጠራል ባይ ናቸው።
የነብዩ መሐመድ አስተምህሮትና ሁሉም ነብያቶች የሚስማሙበት አንድ መመሪያ አለ። ‹‹የምታፍረው ከሌለ ሁሉንም ነገር ሥራ›› የሚል ቃል። ይህ ቃል በሰው ልጅና በፈጣሪ መካከል ያለውን ግርዶሽ እያሳየ ሥነ ምግባርን የሚያስተምር ነው።
እንደ ኡስታዝ አመለካከት በዓለማዊ ሕግ ላይ የሚኖረው ቅጣት የማያዳግም መሆን አለበት። እንዲህ መሆኑ ትውልድን ለመታደግ፣ ማንነትንም ለማትረፍ ያግዛል።
ከሃይማኖት አስተምህሮቶችና፣ ቤተ እምነቶች ጥረት ባሻገር የትምህርት ሥርዓቱ በወጉ ሊጠናና ሊፈተሽ ይገባል። ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና አካባቢ በትውልድ ሥነ ምግባር ላይ አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የኡስታዝ አቡበከር መሐመድ ምክር ነው።
ፓስተር ቸርነት በላይ የጋብቻ አማካሪና የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መሪ ናቸው። ፓስተር ቸሬ የአፈንጋጭነትን ድርጊት ከሃይማኖትና ባህል አኳያ ሲቃኙት የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ያስቀድማሉ። እሳቸው እንደሚሉት ይህ ዓይነቱ አፈንጋጭነት ከተፈጥሮ ጋር ፍፁም ማመፅን ያመላክታል።
ድርጊቱ ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ ከመሆኑ ባሻገር ራሱን ተፈጥሮ እንደማጥፋት ጭምር ይቆጠራል። እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ሲፈጥር ‹‹ብዙ ተባዙ›› በሚል ዘርን ለማስቀጠል፣ ሕይወትን ሥርዓት ለማስያዝ ነው። የሰው ልጆች ይህን ሕግ መተላለፋቸው ደግሞ በፈጣሪያቸው ላይ እንደማመፅ ይቆጠራል።
ፓስተር ቸሬ አፈንጋጭነትን ከአገራችን ባህል አኳያ ሲያጤኑት ድርጊቱ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌለው በማሳየት ነው። አምላክ በአልፈቀደው ፆታዊ ግንኙነት ያለ ወጉ ሆኖ መገኘት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ጠብ ያሳያል። ይህ እውነት ሲመረመርም ፓስተር ቸሬ ደጋግመው እንደሚሉት የሰው ዘርን እንደ ማጥፋት ነው።
ለዚህ ድርጊት መስፋፋት በዋነኛነት የሚጠቅሱት ምክንያት የመንፈሳዊነት መሰንጠቅን ነው። በእሳቸው እሳቤ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ዝቅጠት ውስጥ በሚገባ ጊዜ ይህ ዓይነቱ ድርጊት አንዱ ማሳያ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 1 ላይ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተጠቅሷል።
እንዲህ ዓይነቶቹ በዋንኛነት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ላሽቀው ከፈጣሪ በሚያጋጭ ሐሳብ ላይ ሲገኙ ለዚህ ዓይነቱ ድርጊት እጅ ይሰጣሉ። የሰው ልጅ አምላኩን የማያውቅ፣ በሥርዓት የማይኖርና ያለገደብ የሚነዳ ከሆነ ክቡር የሚባለው ፍጡር እንደ እንስሳ የሚሆንበት ዕድል ይፈጠራል።
እኛን በመሰሉ የአፍሪካ አገሮች የምዕራባውያንን ሥልጣኔ እንደ ፈጣሪ ስጦታ አምኖ የመቀበሉ ልማድ ተበራክቷል። ይህ ዓይነቱ ተጽዕኖ ውድቀታቸውን ጭምር በእኩል እንድንቀበል እያስገደደን ነው። ፓስተር ቸሬ እንደሚሉት እኛ ከእነሱ እየወሰድን ያለው ሥልጣኔያቸውንብቻ አይደለም። ከዚህ በስተጀርባ እኛነታችንን፣ ነባር ዕሴቶቻችንን፣ እምነት ባህላችንን እየተነጠቅን መሆኑ ጭምር መታወቅ አለበት።
ፓስተር ቸሬ በዘመናችን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የወንድና ሴት ትምህርት ልየታን ፈጽሞ አያምኑበትም። በእሳቸው የሕይወት ተሞክሮም በልጃቸው የትምህርት ቤት ቆይታ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ አግኝቷቸዋል። እሳቸው ወንዶች ከሴቶች፣ ሴቶችም ከወንዶች ተለይተው መማራቸውን አይፈቅዱትም። ይህ ዓይነቱ ልምምድ ልጆች ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ግንኙነት ውስጥ እንዲገቡ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ከሚል ስጋት አድርሷቸዋል።
አንዳንዴ ያለገደብ የሚኖር ቅርበትም ለአልተገባ ግንኙነት አሳልፎ ይሰጣል። በዚህ ጉዳይ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር በግልጽ መሞገታቸውን ጭምር ያስታውሳሉ።
በአፈንጋጭ ባሕሪያት ላይ የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ሰዎች ፈጣሪን እንዲያውቁ ከማድረግ እንደሚጀምር ፓስተር ቸሬ ይገልጻሉ። የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት ማለት የእግዚአብሔርን ሐሳብ በማክበር፣ ዘርን ማስቀጠል ስለመሆኑ ማሳወቅ ግድ ይላል። ትምህርቱ ያለአንዳች መሸፋፈን ግልጽና ቀጥተኛ ሆኖ መድረስ አለበት። ችግሩን እያወገዙ ማስተማርም ጉዳዩ በተከሠተ ጊዜ ከሚኖር መሯሯጥና ግራ መጋባት ይታደጋል።
የአፈንጋጭነት ድርጊት አዲስና አሁን ላይ ብቻ የተከሠተ አይደለም። እስከዛሬም በበርካታ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ስለመኖሩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ጉዳዩን ምስጢር በማድረግ በዝምታ የመሸፋፈኑ ሐቅ ግን ኅብረተሰቡን ዋጋ እያስከፈለው ነው። በአንድም ይሁን በሌላ በዚህ አጋጣሚ ያለፉ በርካቶች ስሜታቸው የተጎዳ፣ ውስጣቸው የተሰበረ ነው። ፓስተር ቸሬ ይህ ዓይነቱን እውነታ በአንድ ማሳያ ያረጋግጡታል።
ጉዳዩ ከአንዲት ወላጅ እናት ጋር ይያያዛል። በቅርቡ ነው። በውጭ አገር የምትኖር ሴት ነች። የዓሥራስድስት ዓመት ልጅ አለቻት። ልጅት ከቀናት በአንዱ ለእናቷ እንደእሷ ሴት የሆነች ባልንጀራዋን የፍቅር ‹‹ጓደኛዬ›› ስትል አስተዋወቀቻት።
ሁሌም ይህ ዓይነቱ እውነት የወላጆችን ቅስም ይሰብራል። በተቃራኒው ደግሞ በዚህ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ‹‹መብታችን›› ነው ሲሉ አደባባይ እንዲወጡ ጉልበት ይሰጣል። ፓስተር ቸሬ ይህ ሁሉ የሆነው እውነታዎች በምስጢርና በማለባበስ መያዛቸውና እንደዋዛ መታለፋቸው ነው ይላሉ።
ለዚህ መሰሉ ነውርነት ምክንያቱ የፈረሰ መንፈሳዊ ማንነት፣ የአልበረታ ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው። ይህ ችግር አንደ ሰደድ እሳት እንዳይስፋፋ የሃይማኖት ተቋማትና ቤተሰብ አበክረው ሊተጉ ይገባል።
ፓስተር ቸሬ በግብረሰዶም የአፈንጋጭ ባሕርይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በመድኃኒትም ይሁን፣ በመንፈሳዊ ሕክምናው መታገዝ እንዳለባቸው ያምናሉ። የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡ ለራሱ ነባር ዕሴት ሊታዘዝ፣ መንግሥትም ተገቢውን ሕግ በአግባቡ ሊያስፈጽም ግድ ይላል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግኑኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ግብረ ሰዶማዊነት ከኢትዮጵያ ሕግ አኳያ ወንጀል መሆኑን ይገልጻሉ። በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 6 ፡ 29 እስከ 31 እንደተደነገገው ድርጊቱ ወንጀል መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለው ተጽዕኖ ጭምር በግልጽ ሰፍሯል። ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ሕጉን አጣቅሰው እንደሚሉት ይህ ተጽዕኖ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ አእምሯዊና ለንጽሕና ክብር ተቃራኒ የሚባል ነው።
በዚሁ አንቀጽ ላይ በአጽንዖት እንደተጠቀሰው ግብረ ሰዶም ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ መሆኑ በተለይ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ሕፃናት ላይ ውጤቱን የከፋ ያደርገዋል። በአገራችን የግብረ ሰዶማዊነት ወንጀል እየተስፋፋ መሆኑ በማስረጃ መረጋገጡን የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ ለድርጊቱ መበራከት ምክንያት ናቸው የሚባሉትን እውነታዎችን ጭምር ይጠቁማሉ።
እንደ ኮማንደር ማርቆስ እሳቤ ይህ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ያፈነገጠ፣ በነውርነት የሚፈረጅ ድርጊት እንዲስፋፋ ሰበቡ የባዕዳን ተጽዕኖ ነው። ከዚሁ ተያይዞ ትውልዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥገኛ የመሆኑ አጋጣሚ ለሁኔታዎች መመቸት ዕድል ፈጥሯል።
ይህን በኢትዮጵያ ሕግ በወንጀልነት የሚፈረጅ ድርጊት ብዙኃኑ እንደ ቀልድ በማየት በምንቸገረኝነት ማለፉ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። የዚህ ግዴለሽነት መደጋገም ለወንጀሉ መበራከት ዋነኛ ምክንያት ስለመሆኑም ኮማንደሩ ያስረዳሉ። በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ ድርጊቱን የዘመናዊነት መገለጫ አድርጎ የመውሰድ እሳቤ አለ።
ኮማንደር ማርቆስ ግብረ ሰዶም ወንጀል በመሆኑ በድርጊቱ የተጠረጠሩትን በሕግ አግባብ መያዝ የፖሊስ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ፖሊስ በወንጀሉ ድርጊት የተፈረደባቸውን ሰዎች አስተማሪ የሕግ ውሳኔ ይፋ የማድረግ ሐላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ለፖሊስ ከሚደርሰው መረጃ ለማወቅ እንደሚቻለው በአብዛኛው የግብረ ሰዶም ወንጀል የሚፈጸመው በሕፃናት ላይ ነው። ድርጊቱ በዐዋቂዎችም ላይ ይፈጸማል። ኮማንደሩ እንደጠቆሙት በከተማዋ በድብቅ የተከፈቱ አንዳንድ ቤቶች የግብረ ሰዶም ማካሄጃ መሆናቸው ተደርሶበት ሕጋዊ ርምጃ ተወስዷል።
ኮማንደር ማርቆስ ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ተቃራኒ በሆነ ድርጊት መገኘት ወንጀል እንደመሆኑ በሕግ አግባብ ሊዳኝ እንደሚገባ ያሠምሩበታል። በዚህ ነውርነት የሚገኙ ሰዎች ሲያጋጥሙም ኅብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ ለፖሊስ ማድረስ ይጠበቅበታል።
ወላጆች፣ መምህራንና መላው ኅብረተሰብ የወንጀሉን መስፋፋት ለማስቆም እጁ ሊተባበር ግድ ነው። ይህ የወንጀል ድርጊት በዝምታና ቸልተኝነት ሲታለፍ ችግሩ የሁሉንም በር ያንኳኳልና። የኮማንደር ማርቆስ ታደሰ መልእክት ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
ዘመን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም