በፈተና የአልተበገሩ ወርቃማ እግሮች!

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተወዳደሩባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ታሪክ ሲሠሩ ኖረዋል፣ ዛሬም እየሠሩ ይገኛሉ። የቀደመን ታሪክ የሚቀይር ትልቅ ታሪክ በወርቅ ቀለም የሚጽፉም ጥቂት አይደሉም። የዘመናችን አዲሲቷ አንጸባራቂ ኮከብ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ከእነዚህ አንዷ ነች። ከጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ማራቶን የዓለምን ክብረወሰን ደጋግመው አንሥተዋል። በሴቶች ግን ይህን ታሪክ መሥራት የቻለች አትሌት ከወር በፊት ፈልጎ ማግኘት አይቻልም ነበር። ይህ ታሪክ ከወር በፊት በበርሊን ማራቶን በአዲስ ታሪክ ተተክቷል። ትዕግሥት አሰፋ ፈታኙን ርቀት ለማመን በሚከብድ ብቃት በ2:11:53 ሰዓት አጠናቃ አዲሲቷ የማራቶን ንግሥት በመሆን ዘውዱን ደፍታለች። የሠራችው አዲስ ታሪክ አሁንም ድረስ የስፖርቱን ባለሙያዎችና የዓለም መገናኛ ብዙኃን እያነጋገረ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ይኽንን ታሪክ የሠራችበት መንገድና የተጓዘችበት ረጅም የሕይወት ውጣ ውረድ ለበርካቶች የጽናት ተምሳሌት፣ የአልሸነፍ ባይነት ጥግ ሆኖ ዓለም ተደንቆበታል።

የትናንቷ ትዕግሥት

ሙሉ ስሟ ትዕግሥት አሰፋ ተሰማ ይባላል። የተወለደችው እኤአ በ1994 መጋቢት ወር ሱሉልታ ነው። ከአምስት ወንድምና እኅቶቿ ለቤተሰቧ ታናሽ ልጅ ናት። ሩጫን የጀመረችው ገና ዕድሜዋ ሳይጠና አፈር ፈጭታ በአደገችባት ሆለታ ነው። ረጅሙ የአትሌቲክስ መንገድ የጀመረውም በአራዳ ምሥራቅ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ውድድር ላይ ነው። ‹‹በስፖርት የትምህርት ክፍለ ጊዜ ስሮጥ የተመለከተኝ መምህር ነው አትሌቲክስ እንድጀምር የመከረኝ›› ትላለች ወደ ስፖርቱ የገባችበትን አጋጣሚ ስታስታውስ። የመምህሯን ምክር የተቀበለችው አዳጊ በክለብ ታቅፋ የአትሌቲክስ ጉዞዋን ስትጀምር ጊዜ አልፈጀባትም። ሩጫ ተፈጥሮ የአደለቻት መክሊቷ መሆኑን መረዳት የጀመረችውም በጊዜ ነበር። ‹‹ልጅ እያለሁ የትም ቦታ ስሄድ በሩጫ ነው፣ ሱቅ ዕቃ ለመግዛት ስላክ እንኳን በሩጫ ነው፣ በእርምጃ መጓዝ አልወድም። በአገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መሮጥ ይቀናኛል›› ትላለች የያኔዋ አዳጊ ወጣት የአሁኗ የማራቶን ንግሥት። በሆለታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ100 እና በ200 ሜትር የተጀመረው የትዕግሥት የአትሌቲክስ ሕይወት ጎለበተ። በአገር አቀፍ ውድድሮች መሳተፍም ቀጣዩ ርምጃዋ ሆነ።

በ2001 ዓ.ም. በተካኼደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ200፣ በ400 እና በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ትዕግሥት ጅማሬዋ በወርቅ የደመቀ ነበር። በዚህ ውጤቷ የግላቸው ለማድረግ የቋመጡ ክለቦች ጥቂት አልነበሩም። እሷ ግን አሻፈረኝ ብለ ወደ ሆለታ መመለስን መረጠች። በ2003 ዓ.ም. ዳግም በኢትዮጵያ ሻምፒዮናም በአጭር ርቀት መድመቋን ቀጠለች። አሁን ግን የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌትክስ ክለብ የአቀረበላትን ጥያቄ መግፋት አልፈለገችም፣ ክለቡን መቀላቀሏ እውን ሆነ።

የዓለም አቀፍ ውድድሮች ጅማሬ

ወጣቷ የአጭር ርቀት ተስፈኛ አትሌት ከክለቧ ጋር በሒደት ብቃቷን እያሳደገች እኤአ 2012 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሯን ወክላ የምትሳተፍበት ዕድል አገኘች። ይህም በሱዳን የተካኼደው የምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና ሲሆን በ400 ሜትር ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ነበር የተቋጨው። ትዕግሥት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማይደፍሩት በአጭር ርቀት  ሱዳን ላይ የአጠለቀችው የብር ሜዳሊያ በዚያው ዓመት ወደ አፍሪካ ሻምፒዮና መድረክ አሸጋግሯታል። በቤኒን ላይ በተካኼደው ሻምፒዮና በ400 እና በ4 በ400 ሜትር ምርጥ ተፎካካሪ መሆኗን አስመሰከረች። ይህም አገሯን ደጋግማ የመወከል ዕድሏ እያደገ እኤአ በ2013 በሞርሺየስ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና በ800 እና በ 4 በ400 ሜትር 2ኛና 3ኛ ሆና ልታጠናቅቅ አስቻላት። በማራቶን ታላቅ ስኬት ከአስመዘገበችበት በርሊን ከተማ ጋር የተዋወቀችውም ከዘጠኝ ዓመት በፊት የአጭር ርቀት ራጭ እያለች ነበር። ይህም በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4ኛ ሆና በአጠናቀቀችበት ተመሳሳይ ወር በርሊን ላይ በ8 መቶ ሜትር የአሸነፈችበት አጋጣሚ ነው።

እኤአ በ2016 የፖርትላንድ ኦሪገን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በ8 መቶ ሜትር አገሯን ወክላ ተወዳድራለች። ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ውድድር ማለፍ አልቻለችም። በተመሳሳይ ዓመት በሪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ ኢትዮጵያን ወክላ ለመወዳደር ብትበቃም ከመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ማለፍ አልቻለችም። ይሁን እንጂ በማጣሪያው የውድድር ዓመቱን የራሷን ፈጣን ሰዓት በ2:00:21 አስመዝግባለች። እኤአ እስከ 2016ቱ ሪዮ ኦሊምፒክ ድረስም ኢትዮጵያን ወክላ በተሳተፈችባቸው ውድድሮች የጎላ ባይሆንም ውጤታማ ነበረች።

ከባዱ ፈተና

ትዕግሥት ከሪዮ ኦሊምፒክ በኋላ በትልልቅ ውድድሮች አልታየችም። የአሁኗ የማራቶን ንግሥት ከባድ ፈተናም ከዚህ ይጀምራል። እኤአ ከ2014 ጀምሮ በገጠማት የእግር ሕመም በተለይም የተረከዝ ጅማት ሕመም ምክንያት እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ድረስ ከጉዳት ጋር በመታገል ነበር ስትወዳደር የቆየችው። ትዕግሥት የገጠማት ሕመም እየጠነከረ በመምጣቱም እኤአ 2017 ሙሉ በሙሉ ከውድድር ለመራቅ አስገድዷታል። በ2018 መጨረሻ ወር ግን ከሕመሟ ጋር እየታገለች በቅጡ እንኳን ሳታገግም አንድ ውድድር ብቻ በ10 ኪሎ ሜትር ሮጣ ሁለተኛ ሆና ነበር የአጠናቀቀችው።

እኤአ በ2019ም የእግሯን ሕመም እያስታገሠች ከመወዳደር ወደኋላ አላለችም። ሦስት ውድድር አድርጋ በዓመቱ መጨረሻ በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሕመሙ እየተሰማት ርቀቱን 68:24 በሆነ ሰዓት ሮጣ እንደጨረሰች ባሰባትና በሸክም ወጣች። እዚያው ስፔን ወደሕክምና በተወሰደችበት ወቅት ነበር ሐኪሞች በአትሌቲክስ ሕይወቷ ላይ ተስፋን እንድትቆርጥ የሚያደርጋትን ሐሳብ ያረዷት። በወቅቱ ሐኪሞች ‹‹ከአሁን በኋላ የትራክ (መም) ሩጫ በስፓይክ ጫማ መሮጥ አትችይም›› ሲሉ ለዓመታት በተጋችበት የአትሌቲክስ ጉዞዋ ብሩህ ተስፋ ላይ ውሃ የቸለሱት። ትዕግሥት ተስፋ ሳትቆርጥ በሌሎች የአውሮፓ አገራት በተለይም በጣልያን በአደረገችው ሕክምና ተመሳሳይ ምክር ነበር የተሰጣት። ይባስ ብለው የተረከዝ ጅማቷ በመበጠሱ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ስለማትችል ሩጫን እርግፍ አድርጋ ትታ በሌላ የሥራ ዘርፍ እንድትሰማራ ሐኪሞች ደግመው ነግረዋታል። በሰላም ለውድድር ከቤት የወጣችው አትሌትም በሁለት ክራንች ተደግፋ ወደ ሀገሯ ለመመለስ ተገደደች። በዚህ ሁኔታ ጥቂት የማይባሉ ወራት ነጎዱ። ትዕግሥት እነዚህን የፈተና ወራት እንደ ስሟ ታግሣ አሳለፈች። ተስፋ ግን አልቆረጠችም ‹‹ዳግም እችላለሁ እሮጣለሁ›› በማለት በእምነት በጽናት ቆመች። ‹‹ሐኪሞች ያሉኝን ደግሜ ለአእምሮዬ አልነግረውም፣ ሩጫ ፈጣሪ የሰጠኝ ስጦታ ነው አልተውም›› በማለት መንፈሷን አጠንክራ ታገለች። ለ4 ወር በሁለት ክራች ተደግፋ ለመንቀሳቀስ ከተገደደች በኋላ ቀስ በቀስ ለውጥ እያሳየች መጣች። ለሁለት ወር በአንድ ክራች መጓዝ ጀመረች። እሱንም አሽቀንጥራ ጥላ ሙሉ በሙሉ መራመድ ጀመረች። በክራንች እየሄደች ግን ዋናና፣ ጂምናዚየም እየሠራች በጠንካራ ሥነ ልቦና መታገሏን አላቆመችም ነበር። ከባዱ ፈተና የአትሌቲክስ ሕይወቷን ተስፋ እንዲያጨልምባት አልፈቀደችም። ቀላል ልምምዶችን እየሠራች ቀስ በቀስ እስክትጠነክር መታገሥ ነበረባት። በዚህ ሁኔታ እኤአ 2020 የውድድር ዓመት ሙሉ በሙሉ ሕመምን ለማሸነፍ በሚደረግ ትግል አለፈ። እኤአ በ2021 ከግማሽ ዓመት በኋላ ልምምድ ተጀመረ።

የትዕግሥት ትንሣኤ

ታጋሿ አትሌት ለሰባት ዓመታት ከሕመሟ ጋር ታግላ የተስፋ ጮራ መመልከት ጀምረች። ይህ ወቅት ለእሷ እንደ ትንሣኤ ነው። ለአንድ አትሌት ያን ያህል ዓመት ከውድድር ርቆ መቆየት ቀላል አልነበረም። ሕመሙ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊም ጭምር ነው። ያም ሆኖ ብርቱዋ አትሌት ፈታኙን ጊዜ ድል አድርጋእኤአ ከ2021 አጋማሽ በኋላ ወደ ውድድር ተመልሳለች። ትዕግሥት ወደ ውድድር ስትመልስ ፊቷን ሩጫን ከጀመረችበት አጭርና መካከለኛ ርቀት ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች አዙራ ነው።

ከረጅሙ የጉዳት ዘመን ተመልሳ በአደረገቻቸው ሦስት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮችም ሦስቱንም በማሸነፍ ይበልጥ በራስ መተማመኗን አሳደገች። የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሯ ዱባይ ላይ ሲሆን 34:35 ሰዓት ነበር የሮጠችው። ሁለተኛ ውድድሯን ጀርመን ላይ አድርጋም 31:45 በመሮጥ ሦስት ደቂቃ ገደማ አሻሽላለች። ከዚህ በኋላ ትዕግሥትን የሚያቆማት አልተገኘም። በሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ድል ቀናት።

ዛሬ ላይ በማራቶን ገናና ስም የአተረፈችበትን የማራቶን ውድድር ግን መሮጥ የጀመረችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። በሳኡዲ ዐረቢያ መዲና ሪያድ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የ42 ኪሎ ሜትር ውድድሯን የአደረገችው ትዕግሥት በ2:34:01 ሰዓት ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ነበር የአጠናቀቀችው።

ከመጀመሪያው የማራቶን ውድድር ውጤቷ በኋላ ድምፅዋን አጥፍታ ስትዘጋጅ የቆየችው ይህች ድንቅ አትሌት እኤአ በ2022 በርሊን ማራቶን ሦስተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት አስመዝግባ ታሸንፋለች ብሎ የጠበቀ አልነበረም። በተለይም የበርሊን ማራቶን በርቀቱ ገና ሁለተኛ ውድድሯ እንደመሆኑ ከአላት ትንሽ ልምድና በመጀመሪያ ውድድሯ ከአስመዘገበችው ደካማ ሰዓት አኳያ እንኳን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ለጠንካራ ተፎካካሪነትም ያጫት አልነበረም።

በዓለም ታላላቅ ከሚባሉ የማራቶን ውድድሮች አንዱና ዋነኛው በሆነው የበርሊን ማራቶን በወንዶች በርካታ የዓለም ክብረ ወሰኖች ቢሰበሩም በሴቶች ረገድ ያለው ታሪክ ተቃራኒ ነው። ማንም ያልጠበቃት ኢትዮጵያዊት አትሌት ግን 2:15:37 ሰዓት በማጠናቀቅ በአንድ ውድድር ሦስት የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን መጨበጥ ቻለች። አንዱ የውድድሩን ክብረ ወሰን የሆነውን ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ የአሻሻለችበት ሲሆን፣ ሌላኛው የኢትዮጵያ የማራቶን ክብረ ወሰን የጨበጠችበት ነው። ቀሪው ደግሞ በታሪክ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት የአስመዘገበችበት ነው።

ትዕግሥት በዚህ ውድድር ቀድሞ በማራቶን ከአስመዘገበችው ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ያላነሰ መሻሻል ማሳየቷ ለማመን የሚከብድ ነበር። ይህም በማራቶን ታሪክ ከኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌ እና ከእንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ቀጥላ ስሟ በክብረ ወሰን ማኅደር እንዲሰፍር አድርጓታል። በኢትዮጵያ የሴቶች ማራቶን ታሪክ ከአንድ ደቂቃ በላይ ክብረ ወሰኑን የአሻሻለች የመጀመሪያዋ አትሌትም ሆናለች። ይህ ከዓመታት በፊት ‹‹ከዚህ በኋላ አትሌቲክስ ይቅርብሽ›› ተብላ ለነበረች አትሌት ትልቅ ስኬት ቢሆንም የትዕግሥት የሩጫው ዓለም ታምራቶች በዚህ አላበቃም።

የስኬት ማማ

ትዕግሥት እኤአ በ2022ቱ የበርሊን ማራቶን 2:15:37 በመግባት የቦታውን ክብረ ወሰን ሰብራ ሶስተኛውን የርቀቱ ፈጣን ሰኣት ስታዝመዘግብ ዳግም ያንን ብቃቷን ትደግማለች ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። ብርቱዋ አትሌት በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ተመልሳ የሠራችው ታሪክ ግን ለራሷም ቢሆን አስገርሟታል። ‹‹እውነት ለመናገር በተወሰነ መልኩ ክብረ ወሰኑን የማሻሻል ፍላጎት ነበረኝ፤ ከአሠልጣኜ ጋርም ክብረ ወሰኑን ለመስበር ዐቅደን ነው የተዘጋጀነው። ጥሩ አቋም ላይ ብገኝም በዚህ ደረጃ አሻሽላለሁ ብዬ ግን አልጠበኩም፤ ዕቅዴ 2:12:13 ሰዓት ለመሮጥ ነበር›› ትላለች።

ተደጋግሞ የማይሰበረውን የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን 2:11:53 በማጠናቀቅ አንክታዋለች። ቀደም ሲል የርቀቱ ክብረ ወሰን እኤአ በ2019 የቺካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ 2:14:04 የተያዘ ነው። ትዕግሥት ይህን ክብረ ወሰን ብዙዎች ለማመን በከበዳቸው ድንቅ ብቃት ከ2:11 ደቂቃ በላይ አሻሽላዋለች። በማራቶን ታሪክ በዚህ ያህል ልዩነት ክብረ ወሰን ማሻሻል የማይታሰብ ነው። በሴቶች ማራቶን በሰፊ ልዩነት ክብረ ወሰን የተሻሻለው ከአርባ ዓመታት በፊት ነው። ይህም እኤአ በ1988 አሜሪካዊቷ አትሌት ጆአን ቤኖይት 2:25:29 የነበረውን ክብረወሰን ወደ 2:22:43 ያወረደችበት ነው። ትዕግሥት ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ማንም ሳያስበው የተከሠተች ኮከብ ነች። በእነዚህ ዓመታት በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ቁንጮ አትሌቶች የብቃታቸው ጥግ ላይ ደርሰው ይህን ማሳካት አልቻሉም። እሷ ግን በርቀቱ ያውም ገና በሦስተኛ ውድድሯ አሳክታዋለች። እኤአ በ1981 መጨረሻ ላይ በአሠልጣኝ ንጉሤ ሮባና አትሌት አዲስ ገዛኸኝ የተጀመረው የኢትዮጵያ የሴቶች ማራቶን ታሪክ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀው ጊዜ 3:00 ነበረ። አሁን ላይ ትዕግሥት ምናልባትም ለበርካታ ዓመታት እንዳይደፈር አድርጋ ሰቅላዋለች። እሷ ግን በዚህ ብቻ የምትቆም አይደለችም፤ ከዚህም በላይ የብቃቷን ጥግ ለዓለም የማሳየት ህልም አላት። ይህንንም በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ስታልፍ ተስፋ ሳይቆርጥ ከጎኗ ከነበረው አሠልጣኟ ገመዶ ደደፎ ጋር እንደምታሳካው አትጠራጠርም። የራሷን የዓለም ክብረ ወሰን ‹‹በእርግጠኝኛት አሻሽለዋለሁ›› ትላለች። 42 ኪሎ ሜትሩን ከ2:10 በታች ማጠናቀቅ ይቻላል በማለትም በቀጣይ ዓመታት የማይደፈረውን ለመድፈር ዕቅድ አላት።

የፓሪስ ኦሊምፒክ ተስፋ

ትዕግሥት የአስመዘገበችው የዓለም ክብረ ወሰን ሌላ የጤና እክል ከአልገጠማት ከዓመት በኋላ በሚካሄደው የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን እንድትወክል የሚያስችላት ነው። ‹‹ይህ ስኬት በኦሊምፒክ ቡድኑ እንደሚያካትተኝ አምናለሁ›› ስትልም ከፊት ስለሚጠብቃት ታላቁ የውድድር መድረክ ትናገራለች። ከዚያም በላይ ግን የእሷ የዓለም ክብረ ወሰን በርካታ ሴት ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶችን ተነሣሽነት እንደሚጨምር ታምናለች። ‹‹በርሊን ላይ የአሳየሁት ብቃት ለበርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተነሣሽነት ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ አገራችን በቀጣይ ለሚኖራት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ትልቅ ዐቅም ይሆናል›› ብላ እንድታምንም አድርጓታል።

ብርቱዋ አትሌት ከወደቀችበት ተነሥታ በአስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለብዙዎች የተስፋ ስንቅ ሆናለች። በሕይወት ጉዞ የቱንም ያህል የከበደ ፈተና ቢገጥም ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግ ሁነኛ ምሳሌ ሆናለች። ለዚህም በክለቧ የምክትል ኢንስፔክተርነት መዓርግ ተሰጥቷታል።

ቦጋለ አበበ

ዘመን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You