ፀሐይና ምድራዊ ኩነቶች

መግቢያ

ፀሐይን በየቀኑ ስለምናያት ስለ እሷ በቂ መረጃ እንዲኖረን ያስፈልጋል የሚል እሳቤ አለን። ፀሐይ የተለያዩ ምድራዊ ተግባራትም አስተናጋጅ፣ ብሎም የኩነቶች መተለሚያ፣ መለኪያ ሆና ታገለግላለች። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንስን ማኸዘብ (የሳይንስን ዘዴ እና ዕውቀት ለሕዝብ እንዲዳረስ ማድረግ) ሲሆን፣ እሳቤው የሚስተናገደው ስለ ፀሐይ እና ምድር ቁርኝት ትንተና በማቅረብ ነው። ሁላችንም ስለፀሐይ የተወሰነ ግንዛቤ አለን፣ ልዩነቱ ግን የግንዛቤው ጥልቀት እና ስፋት ላይ ነው። ፀሐይ የብርሃን እና የሙቀት ምንጭ፣ የጊዜ ልኬት መንስዔ መሆኗን ሁላችንም እናውቃለን። እንዲሁም የዘመን ክፍፍል (በጋ፣ በልግ፣ ክረምት፣ ፀደይ) ከፀሐይ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እንገነዘባለን። በቂ ግንዛቤ የሌለን ስለ አመሠራረቷ እና ስለ ልዩ ባህሪያቷ ነው። ስለ ፀሐይ ያለን ግንዛቤ በዳበረ መጠን፣ በመሬት ዙሪያ ላለው ቁስ አካል፣ እንቅስቃሴ፣ የተሻለ ግንዛቤ እንድናዳብር ይረዳናል።

ፀሐይ የሰው ልጆችን ቀልብ ስባ፣ ከቁሳዊነት ዘልቃ መለኮታዊ ባህርይ እንዳላትም በብዙ አካባቢ ይታመን ነበር፣ አሁንም ቢሆን በተወሰኑ አካባቢዎች ያንን ዓይነት እምነት ያነገቡ አይጠፉም። ለምሳሌ፡- በጥንታዊ ግብጻውያን እምነት “ሪ” (Re)፣ ማለት ፀሐይ፣ የመላእክት የበላይ አካል ነበር፣ እንደ አለቃ ማለት ነው። እንዲሁም በግሪክ አካባቢ “ታይታን” (Titan) መለኮታዊ ፀሐይ ሆኖ ይታይ ነበር። እሱም “የፀሐይ ሰረገላ” በየቀኑ ከምሥራቅ ጀምሮ ወደ ምዕራብ እንደሚጋልብ ይታመን ነበር። ተመሳሳይ እምነቶች፣ በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በሩቅ ምሥራቅ እና በአውስትራሊያም ነበሩ። በተጨማሪ ከሳምንት ቀናት “ሰንደይ” (Sunday/ Sun Day) እና “መንደይ” (Monday/Moon Day) ተብለው፣ ለፀሐይ እና ለጨረቃ፣ አንዳንድ ቀን በስማቸው ተሰይመውላቸዋል።

ፀሐይ በባህላችን በበጎ ሁኔታ ትመሰላለች፣ “እገሌ እኮ ፀሐይ ወጣለት” ሲባል፣ ቀንቶታል፣ የፈለገውን አገኘ እንደማለት ነው።”እነሱማ ጨለመባቸው” ሲባል ደግሞ፣ ጊዜ ከድታቸዋለች፣ አልተመቻቸውም እንደማለት ይቆጠራል። ሌሎች ከፀሐይ ጋር የተዛመዱ አባባሎችንም ማንሳት ይቻላል።

የፀሐይ እና የምድር አመሠራረት

ፀሐይ ከመጠነ ብዙ “ሃይድርጅን” (hydrogen/ H) እና “ሂልየም” (helium/ He) ክምችት የተገነባች “የጋዛዊ አለሎ እሳት” ናት። የፀሐይ የውጭ ገላዋ ሙቀት አምስት ሺ አምስት መቶ ዲግሪ ሴልሲየስ (5,500 0C) ገደማ ሲሆን፣ የውስጥ ሙቀቷ አሥራ አምስት ሺ አምስት መቶ ዲግሪ ሴልሲየስ (15,500 0C) ገደማ ነው።

ፀሐይ የተመሠረተችው ከ4.568 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ያም የዩኒቨርስ ሲሶ እድሜ ማለት ነው። “ሥርዓተ-ፀሐይ” (Solar System) የተመሠረተው በዚያው ወቅት ነው። ፈለኮቹ (Planets)፣ እንዲሁም ሌሎች የሥርዓቱ አባላት ከአንድ ግዙፍ የብርሃን ደመና እንደተገኙ ይገምታል። እሱም ድብዝ ስብስብ ከዋክብት (“ሄቡላ”/ Nebula) ፣ሲባል ከደመናው እምብርት ፀሐይ ታነፀች፣ ፈለኮች (Planets) ከውጭ ካለው ስብስብ ተመሠረቱ። ከበድ ከበድ ያሉት ፈለኮች፣ ለፀሐይ ጠጋ ብለው፣ ይዘታቸው ቀለል ቀለል ያሉት ደግሞ ራቅ ብለው፣ የየራሳቸውን ኳስ መሰል አካላት መሥርተው ፀሐይን መዞር ጀመሩ። ይህ ስብስብ ነው “ሥርዓተ-ፀሐይ” (Solar System) በመባል የሚታወቀው።

“የሥርዓተ-ፀሐይ” (Solar System) አስኳል ፀሐይ ስትሆን፣ ስምንት ፈለኮች በተለያዩ ርቀቶች ፀሐይን ይዞራሉ። በተጨማሪም ሌሎች መጠነ ውስን የሆኑ ፈለኮች፣ እንዲሁም ኮሜቶች (Comets)፣ አስቴሮይድስ (Asteroids)፣ ወፈጥ ድንጋይ (Space rocks) እና ጠጣር በረዶ መሰል አካላት (Space ice) ይገኛሉ። የፈለኮችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ አንዳንዶች ደግሞ ወደ አሥራ አንድ ከፍ የሚያደርጉ ጠበብትም አሉ።

በሰማየ ሰማያት ላይ ሌሊት የምናያቸው አንፀባራቂ አካላት ሁሉ ከዋክብት ሲሆኑ፣ የኛ ፀሐይ የምትገኝበት “ጋላክሲ” በ”ፍኖተ ሃሊብ” (Milky Way) የሚገኙ ሌሎች ፀሐዮች አሉ። እነሱም እያንዳንዳቸው የየግላቸው ሥርዓትን የመሠረቱ ግዙፍ አካላት ናቸው። ዩኒቨርስ ብዙ ቢሊዮን ጋላክሲዎችን ያቀፈ፣ በእያንዳንዱ ጋላክሲም ብዙ ቢሊዮን ፀሐዮች የሰፈሩበት፣ ልክየለሽ ክስትት ነው።

ከሌሎቹ “የፀሐይ ሥርዓት” አባላት ጋር ስትነፃፀር፣ ፀሐይ መጠኗ በጣም ግዙፍ ነው። ጠቅላላ ሥርዓቱ ከተገነባበት መጠነ ቁስ (mass)፣ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስምንት በመቶ (99.8%) የሆነው የፀሐይ ድርሻ ነው፡ ቀሪውን ውስን መጠነ ቁስ ነው ሌሎች አካላት የሚካፈሉት። በተለይ ወደ ፀሐይ ጠጋ ያሉት የምድራዊ ፈለኮች መጠነ ቁስ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ ነው።

ፈለኮች በፀሐይ “ማህለሸሽ ኃይል” (Centrifugal Force) ተወንጭፈው፣ ተስፈንጥረው እንዳይርቁ፣ “በስበ ቁስ” (ግራቪቲ/ Gravity) ተወጥረው ይያዛሉ። ከፀሐይ ቅርብ ከሆነችው ፈለክ ጀመረን ራቅ ራቅ ብለው ወደሚገኙት ፈለኮች በተራ፣ በቅደም ተከተል፣ “ሜርኩሪ” (Mercury)፣ “ቪነስ” (Venus)፣ ምድር (Earth)፣ “ማርስ” (Mars)፣”ጁፒተር”(Jupiter)፣ “ሳተርን”(Saturn)፣ “ዩራነስ” (Uranus) እና “ኔፕቱን” (Neptune) ናቸው። የሥርዓተ-ፀሐይ አባላት የሆኑ፣ ቁጥራቸው የማይታወቅ ብዙ ጥቃቅን ፈለኮች እንዳሉ ይገመታል።

ከፀሐይ ቅርበት ያሉዋቸው ከባድ ከባዶች አራቱ ፈለኮች፣ “ሜርኩሪ፣” “ቪነስ”፣ ምድር፣ እና “ማርስ” “ምድራዊ/ የብሳዊ ፈለኮች” (Terrestrial Planets) ይባላሉ። እነሱም የተገነቡት ከድንጋይእና ከብረት አስተኔዎች (Metals) ሲሆን፣ ከፀሐይ ራቅ ብለው የሚገኙት ሁለቱ ታላላቅ ፈለኮች፣ “ጁፒተር” እና “ሳተርን”፣ “ከሃይድሮጅን” (hydrogen/ H) እና “ከሂልየም” (helium/ He) ነው የታነፁት። ከዚያም ራቅ ብለው የሚገኙት ሁለት ፈለኮች፣ “ዩራነስ” እና “ኔፕቱን” ትናኝ በረዶ መሰል አካል ነው ያላቸው። ሁሉም ፈለኮች ፀሐይን ይዞራሉ። የዙረታቸው አቅጣጫ፣ የራሷ የፀሐይ ሹረት አቅጣጫ ነው። ይህን ዙረት ከሰሜን ዋልታ ላይ ሆነን ስንመለከተው፣ የሰዓት ዙረት ተቃራኒ (anticlockwise) ነው።

“ከየብሳዊ ፈለኮች” (Terrestrial Planets) ምድር ብቻ ናት አጃቢ ጨረቃ ያላት። መሬት ገና ሕፃን በነበረችበት ዘመን፣ ከአንድ ግዙፍ አካል ጋር ተጋጭታ፣ በግጭቱ መንስዔ ጨረቃ ተመሥርታ፣ የምድር አጃቢ ሆነች ተብሎ ይገመታል። ጨረቃ የሰውን ልጅ ቀልብ ከሚስቡት፣ ከምድር ውጭ ከሆኑ ግዙፍ አካላት አንዷ ስትሆን፣ በአንዳንድ የባህል ዘመን መተለሚያ ተደርጋ ተወሰዳለች። ጨረቃ የሰው ልጅ ጎረቤት ስለሆነች፣ ጉርብትናውን ለማጠናከር፣ እሷን መጎብኘት እንደ አንድ ትልቅ የሳይንስ መርሃ ግብር ተደርጎ ከተወሰደ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከምድር የተላከ ቁስ አካል (የሳይንስ መሣሪያ) በጨረቃ ላይ በመጀመሪያ ጊዜ ያረፈው በሶቭየት ሕበረት ተልኮ በግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠር፣ “በሴፕቴምበር” 13 1959 ነበር። ከዚያም ከአስር ዓመት በኋላ “በጁላይ” 1969 አሜሪካ በጨረቃ ላይ ሰው ለማሳረፍ ቻለች፣ እንዲሁም በተከታታይ አሜሪካ ለስድስት ጊዜ ሰዎችን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ በቅታለች።

ሕያው አካላትን የምታስተናግድ የየብሳዊ ፈለኮች አባል የሆነቸው ምድር ብቻ ናት፣ ምክንያቱም “ክበበ ውሃ” (Hydrosphere) በምድር ዙሪያ ብቻ ነው የሚገኝ። ይህም ሁኔታ ምድርን ከሌሎች ጓዶቿ ለየት ያደርጋታል። ኬሚካዊ ውሁድ ያለሆነ ነፃ ኦክስጅን (O2) የሚገኝ ምድር ላይ ብቻ ነው። ም ድር ይህንን ልዩ ተፈጥሮ ያገኘቸው ከፀሐይ የምትገኝበት የርቀት መጠን ለህያው ፍጡር የተመጣጠነ የሙቀት መጠን ማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ነው።

ምድር ስትመሠረት የጋለ ብርት አለሎ መሰል የነበረች ቢሆንም፣ በሂደት የገላዋ የላዩ ሽፋን ቀዝቅዞ፣ ውሃ እንዲጠራቀምበት አስቻለ፣ በሂደት ውቅያኖሶች ተመሠረቱ። ሕይወት በመጀመሪያ የተከሰተው በ ው ቅ ያ ኖ ስ ውስጥ እንደሆነ ብዙ መረጃ ተገኝቷል። የምድር ዘመን በሦስት ግዙፍ የዘመን ክፍሎች ይከፋፈላል። አንደኛው “ዘመነ ጥንተ ሕይወት” (“ፓሊዮዞይክ”/ Paleozoic) ሲባል፣ አከርካሪ የሌላቸው (አከርካሪ አልባ/ የጀርባ አጥንት የሌላቸው) እና በመጀመሪያ ባለአከርካሪ የሆኑት የአሳ ዝርያዎች ዘመን ነው። ከዚያ ቀጥሎ ያለው ማእቀፍ፣ “ዘመነ ማዕከለ ሕይወት (“ሜሶዞይክ”/ Mesozoic) ሲባል፣ ያም የዳይኖሶሮች ዘመን ነበር። የመጨረሻው እና ሦስተኛው ማእቀፍ “ዘመነ ቅርስ ሕይወት” (“ሴኖዞይክ”/ Cenozoic) በመባል ይታወቃል። ያም “አካለ ሰው”፣ የሰው ዘር መሰል የሕያው ሐረግ (ቅርንጫፍ) መታየት የጀመረበት ሲሆን፣ ጊዜውም ከሁለት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ገደማ እንደሆነ ይገመታል። “ቅድመ ሰዎች”፣ እንደ ድንቅነሽ ያሉት፣ ከሦስት ሚሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት ነበር ምድር ላይ የታዩት።

በፀሐይ ኃይል ታግዘው የራሳቸውን ምግብ የሚያመርቱት እፅዋት፣ በምድር ላይ መታየት የጀመሩት ከሦስት ቢሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት እነሱን መሰል ሕያው አካላት በምድር ማንሰራራት በሕዋ ውስጥ የሚገኘውን ኦክሲጅን መጠን በጣም ከፍ አደረገው፣ የዚያም ኩነት ምክንያት እፅዋት “ካርቦን ዳይከሳይድ” (CO2) ምገው ኦክሲጅን (O2) ስለሚተፉ ነው።

ፀሐይ፣ የኢነርጂ ምንጭ

ከላይ እንደተጠቀሰው የእኛ ፀሐይ፣ “የሥርዓተ ፀሐይ” (Solar system) አስኳል (እምብርት) ስትሆን፣ እሷም ለሥርዓተ-ፀሐይ ብቸኛ የኢነርጂ ቋት ናት። የፀሐይ ኢነርጂ የሚገኘው “ኑክሊየር እርስሰት” (Nuclear fusion) በመባል የሚታወቅ የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ ሂደት ነው። በከፍተኛ ግፊት (pressure) እንዲሁም ሙቀት ሃይድርጅንን (hydrogen/ H) ወደ ሂልየም (helium/ He) ሲቀየር (ሁለት የሃይድሮጅን አቶሞች አንድ ሂልየም አቶም ይገነባሉ)። በዚህ ሂደት የተገኘ ከፍተኛ የሆነ ኢነርጂ ይገኛል።

ፀሐይ በየቀኑ የምታመነጨው ኢነርጂ፣ በምድራችን ያሉ ኩነቶች ሁሉ በዓመት ከሚጠቀሙበት ኢነርጂ በጣም የላቀ ነው። ከፀሐይ የሚፈልቀው ኢነርጂ (ብርሃን እና ሙቀት) ሶስት መቶ ሺ ኪሎ ሜትር በሰኮንድ እየተጓዘ፣ አንድ ሞቶ አምሳ ሚሊዮን ኪሎ ሜትርን አቋርጦ፣ ከስምንት ደቂቃ ገደማ በኋላ ምድር ላይ ይደርሳል።

ከፀሐይ በብርሃን ነፀብራቅ (Solar radiation) እና ሙቀት በሚመነጭ ጉልበት (“ሶላር ኢነርጂ” / Solar Energy) የሰው ልጆች መጠቀም ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል። በፀሐይ ኢነርጂ ቀጥታውን ተጠቅሞ የውሃን እና የቤት አካባቢ አየር ሙቀት ከፍ ለማድረግ ይቻላል። በተዘዋዋሪ መንገድ ፀሐይ ከምታስተናግዳቸው ነፋስ እና የባህር ሞገድ የሚገኝ “ሜካኒካል ጉልበት” (mechanical energy) የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ማመነጨት ይቻላል።

በፀሐይ ኢነርጂ በመጠቀም (ሌሎችም የኢነርጂ ምንጮች ለዚህ ተግባር ሊውሉ ይችላሉ) የሃይድሮጂንን አቶም (H) ከውሃ “ሞሊኪውል” (H2O) ነጥሎ በማውጣት እና ያንን ጋዝ ለሞተር ማንቀሳቀሻ ነዳጅ ማድረግ ይቻላል። “በሃይደሮጅን” ነዳጅ የሚንቀሰቀሱ መኪናዎች በሙከራ ደረጃ ፋብሪካ ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳ በሃይደሮጅን ነዳጅ መርከብ፣ አይሮፕላን፣ ወዘተ ማንቀሳቀስ የሚቻል ቢሆንም፣ በዘመናችን ከሃይድሮጅን በተገኘ ኢነርጂ፣ በብዛት፣ በቋሚነት፣ የምንጠቀም ለሮኬቶች ማስወንጨፊያነት ነው። ከሃይድሮጅን በተገኘ ኢነርጂ ስንጠቀም፣ የነዳጁ ዝቃጭ የውሃ እንፋሎት (water vapour) ስለሆነ በካይ አይደለም። ይኸም ምድርን ከአስጊ ሁኔታ ሊታደጋት ይችላል። ከሃይደሮጂን በተገኘ ኢነርጂ የመጠቀሙ ተግባር ዋናው እንቅፋት፣ ነዳጁ በቀላሉ ለአደጋ በመጋለጡ፣ ፍንዳታ እና ቃጠሎ ማስከሰቱ ነው።

ፀሐይ የትየለሌ ኢነርጂ የምታፈልቅበትን መንገድ እንደምሳሌነት ተወስዶ፣ ያንን ዘዴበመከተል፣ ወይም በመኮረጅ፣ ሁለት የሃይደርጅን ኑክሊየሶችን በመቀላቀል፣ “ኑክሊየር እርስሰት” በሚገኝ ኢነርጂ የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ማመንጨት ሲሆን፣ ይህም ስኬታማ መሆኑ በሙከራ ተደርሶበታል። ይህን ሙከራ አዳብሮ ለቀን ተቀን ተግባር ለመጠቀም ዓመታት ይፈጃል፣ ሂደቱ ግን ተጀምሯል።

ፀሐይ ውበትም አስተናጋጅ ናት። የሰው ልጆች ለማየት የሚችሉት ብርሃን (visible light) የተለያዩ ርዝመት (wave length) ያሉዋቸው (spectrum of wavelengths) የብርሃን ሞገዶች ጥምረት ሲሆን፣ ይህ ብርሃን በውሃ ጠብታ ውስጥ ሲያልፍ፣ ጥምረቱ ይበተንና በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቀ ቀስተ ደመና ለማየት እንችላለን። ይኸም ከተፈጥሮ አስደናቂ እና ውብ ስጦታዎች አንዱ ሲሆን፣ ያንን ውበት የም ታበረክትልን ፀሐይ ናት።

የምድራችን ከባቢ አየር (ሕዋ / Atmosphere)

የመሬት ቅርጽ ዱባ መሰል ሲሆን፣ ዙሪያዋን የሚሸፍን አየር እንዲሁም ብናኝ፣ ትናኝ አካላት ይገኛሉ፣ ይህ ስብስብ ነው በጥቅሉ “ከባቢ አየር” (ሕዋ /Atmosphere) የሚባለው። ዋናዎቹ የከባቢ አየር አባላት ናይተሮጅን (Nitrogen/ N2) ሰባ ስምንት በመቶ (78%) እና ኦክስጅን (Oxygen/ O2) ሃያ አንድ በመቶ (21%) የሕዋ ድርሻ አላቸው። በሕያው ገላ ውስጥ እንደ እሳት አቀጣጣይ የሚቆጠረው ኦክስጅን ነው። ኦክስጅን ኢነርጂ በመጠቀም ሂደት ዋና ሚና አለው። ከዚያ በተጨማሪ አስጊ የሆኑ የፀሐይ ጨረሮች ምድር እንዳይደረሱ አንድ የኦክስጅን ዓይነት፣ “ኦዞን” (Ozone/ O3)፣ እንደ መጋረጃ ሆኖ ያገለግላል።

በሕዋ ውስጥ ያለው “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” (CO2) የሕዋ አየር ድርሻ ዜሮ ነጥብ ዜሮ ሦስት በመቶ (0.03%) ብቻ ነው። በመሬት ዙሪያ ባለው አየር ውስጥ የሚገኘው ካርቦን በሁለት ኬሚካላዊ መዋቅር ይከፈላል፣ እነሱም “ሚቴን” (methane- CH4) እና “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” (carbon dioxide/ CO2) ናቸው። ሁለቱም ትናኝ (ጋዞች) ሲሆኑ፣ መሬት ላይ የደረሰው የፀሐይ ሙቀት በቀላሉ ተንፀባርቆ ወደ ሕዋ እንዳይመለስ፣ እንደመጋረጃ ሆነው ያገለግላሉ።

አንዱ አማቂ የጋዝ ዓይነት ኦዞን (O3) ነው። በተጨማሪ “የኦዞን” ሽፋን ሕያውን ከአደገኛ “ልእለ ጨረር” (Ultraviolet radiation-UV) ከመጠቃት ይታደጋል። ጨረሩ በሰው ገላ ላይ ሲያርፍ የሰው ቆዳን ያቃጥላል፣ የቆዳ ካንሰር መንስዔም ይሆናል፣ እንዲሁም ዓይን ላይ ጉዳት ያደርሳል። በመሬት ዙሪያ የሚገኝ፣ “ማግነጢስ ሕዋ”(magnetosphere) በመባል የሚታወቅ ከጨረር መከላከያ ተጨማሪ ሌላ ኃይልም አለ።

መሬት ላይ የደረሰው የፀሐይ ሙቀት በቀላሉ ተንፀባርቆ ወደ ሕዋ እንዳይመለስ፣ እንደመጋረጃ ሆነው የሚያገለግሉ ጋዞች፣ “ዝገ ክበብ አየር” (Greenhouse effect) ተብሎ የሚታወቀውን ሁኔታ ይፈጥራሉ። የመሬት ከባቢ ሙቀት በአማካኝ 14 0C ነው፣ “የሜቴን” እና “የካርቦን ዳይኦክሳይድ” (Carbon dioxide) መጋረጃ ባይኖር ኖሮ፣ ሙቀቱ በአማካኝ በሰላሳ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ (35 0C) ዝቅ ይል ነበር። ይህም ማለት በአማካኝ የመሬት ሙቀት ከዜሮ በታች ሃያ አንድ ዲግሪ ሴልሲየስ (-210C) ሆኖ፣ ውቅያኖሶች በጠቅላላ ወደ ጠጣር በረዶነት ተቀይረው፣ በውስጣቸው ሕያው ነገር ሊኖሩ አይችሉም ነበር፣ ብሎም ምድር ሕይወት አልባ ፣ በጣም ውስን ሕያው አስተናጋጅ ትሆን ነበር።

ከቅርብ ዘመን ጀምሮ፣ የሕያው ቅሬት የሆነ፣ “ካርቦናዊ-ውሁድ” (organic compound) በነዳጅ መልክ፣ የሞተሮች ማንቀሳቀሻ ሲደረግ፤ ከርሰ-ምድር ውስጥ ታምቆ የነበረው ካርቦን፣ አየር ውስጥ ካለው ጋር መቀላቀል ችሏል። በዚህም ምክንያት አየር ውስጥ ያለው የካርቦን መጠን ናረ/ ከፍ አለ፤ ብሎም ለአየር-ቅጥ መለወጥ/ መናወጥ፣ ከዚያም ለምድር ከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፣ ዋናው መንስዔ ሆኗል። ሙቀቱ የጨመረው “ዝገ ክበብ አየር” (Greenhouse effect) ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን፣ የሙቀቱ ዋና ምንጭ ደግሞ ፀሐይ ናት።

የመሬት ሙቀት እንዳይንር የሚያግዙ የመሬት ሽፋኖችም አሉ፣ ያም የጠጠረ ውሃ (በረዶ/ሽኸት/ Ice) ነው። አልቢዶ (Albedo) የሚባለው ክስተት ምድር ላይ የሚደርስን የፀሐይ ብርሃን አንፀባርቆ ወደ ሕዋ ይመልሳል፣ ብሎም የአካባቢው የሙቀት መጠን እንዳይንር ያግዛል። በከፍተኛ ደረጃ የፀሐይን ብርሃን የማንፀባረቅ ባህርይ ሲኖራቸው፣ በበረዶ (ጠጣር ውሃ/ Ice) የተሸፈኑ አካባቢዎችም ናቸው።

እሳተ ገሞራ በሚፈነዳበት ጊዜ ወደ ሕዋ የሚተፋው አቧራ መሰል ብናኝ፣ የፀሐይ ብርሃን እና ሙቀት ወደ መሬት እንዳይደርስ ይጋርዳል፣ ብሎም ለአካባቢ መቀዝቀዝ ምክንያት ሆኖ ለወራት ሊቀጥል ይችላል። በተቃራኒው በጥቁር ቁስ የተሸፈኑ አካባቢዎች፣ ለአካባቢ ሙቀት መናር ምክንያት ይሆናሉ። ስለሆነም በጢስ ጥላሸት የተሸፈነ የበረዶ አካባቢ በቀላሉ በረዶ እንዲሟሟ ያደርጋል። የሟሟው በረዶ ውሃ ስለሚሆን፣ በዚህ መንገድ የተገኘ ውሃ የውቅያኖሶችን ገፅታ ከፍ ያደርገዋል፣ ባህር ዳር የሚገኙ ከተማዎችም በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ።

ፀሐይና በምድራችን ላይ ያሉ ግዙፍ ኩነቶች

በዓለማችን (በምድራችን) ላይ ላሉት ነባራዊ ሂደቶች በሙሉ፣ ለአየር ሙቀት፣ ለነፋስ አቅጣጫ ብሎም እንቅስቃሴ፣ ለውቅያኖስ ሙቀት፣ ለግዙፍ የውሃም ሆነ የአየር ማዕበል፣ ውሽንፍር፣ የፀሐይ እጅ አለበት። ጥቂቶቹን ኩነቶች በምሳሌነትእናንሳ፡ –

የአየር ግፊት (Air pressure)

መሬት ላይ ሆነን ወደ ላይ ብንመለከት፣ የደመና ከለላ ከሌለ፣ ሰማያዊ ሰማይ ብቻ ነው የሚታየን። በሕዋ ውስጥ ያለውን አየር ለማየት ባንችልም፣ ከላያችን ያለው አየር ገላችንን ይጫነዋል። ጭነቱም በእያንዳንዷ ሴንቲሜትር ካሬ ያለው ክብደት አንድ ነጥብ ዜሮ ሦስት ሦስት (1.033) ኪሎ ግራም ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ በመሬትም ላይ ያለው ጭነት (የአየር ግፊት/ Air pressure) ይኸው ክብደት ነው።

ከመሬት ተነስተን ወደ ላይ ወደ ሕዋ ብንዘልቅ፣ ርቀቱ በጨመረ መጠን፣ የአየር ግፊቱ ይቀንሳል። ከመሬት ገጽ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት/ ከፍታ ላይ፣ የአካባቢው አየር መጠን ሳስቶ አየር አልባ እንደሆነ፣ ብሎም የአየር ግፊት እንደሌለ ሊቆጠር ይችላል፤

በመሬት ላይ ያለው የአየር ግፊት በሙቀት መንስዔ ሊቀያየር ይችላል፣ ቀዝቃዛ አየር ከባድ ሲሆን፣ በአንፃሩ ሙቅ አየር ቀላል ነው። በቀዝቃዛ ሕዋ ውስጥ ሰብሰብ ብለው የሚገኙ የአየር ሞሌኩሎች፣ ሙቀት ሲያገኙ ይበታተናሉ። ሲበታተኑ በተወሰነ ቦታ ላይ ያለው የአየር ሞሌኩሎች፣ መጠን ቀንሶ ክብደቱም አብሮ ይቀንሳል። ቀዝቃዛ አየር ያለበት የከፍተኛ ግፊት አካባቢ (High pressure area) በመባል ሲታወቅ፣ በአንፃሩ ሙቅ አየር ያለበት አካባቢ የዝቅተኛ ግፊት አካባቢ (Low pressure area) በመባል ይታወቃሉ። የአየር ግፊት መለዋወጥ መንስዔ ሙቀት ሲሆን፣ የሙቀት ምክንያት ደግሞ ፀሐይ ናት።

በተወሰነ አካባቢ የአየር መታመቅም የአየር ግፊት መናር መንስዔ ይሆናል፣ በፊኛ ውስጥ አየር አምቀን ስናስገባ፣ የአየሩ ግፊት ፊኛውን ይወጥረዋል። ይህም የሆነው በውስን ቦታ ብዙ የአየር ሞሌኩሎች በማመቅ እና ዴንሲቲው (density) እንዲጨመር በመደረጉ ነው። ስለሆነም የዴንሲቲ መጨመርም የአየር ግፊት ንረትን ያስከትላል።

ነፋስ ከፍተኛ የአየር ግፊት ካለበት አካባቢ፣ ወደ ዝቅተኛ ግፊት አካባቢ ነው የሚነፍስ። በዓለማችን የተለያዩ ስሞች የተሰጡዋቸው የነፋስ ዓይነቶች አሉ፣ ከእነኚህ ውስጥ ከሰው ልጆች የባህር ላይ ጉዞ ጋር የተቆራኘው “ምሥራቁ ነፋስ” (ጥብሪት/ Trade winds) ይባላል። “በምሥራቁ ነፋስ” እገዛ፣ መርከቦች በአትላንቲክ፣ በሰላማዊ እና በኢንድያን ውቅያኖሶች፣ በአስተማማኝ ሁኔታ ተንቀሳቅሰው፣ የዓለም ዙሪያን ለማዳረስ ችለዋል። በዘመናችንም መርከቦች በነፋሱ አቅጣጫ የሚጓዙ ከሆኑ ፍጥነታቸው ይጨማራል፣ ከነፋሱ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚጓዙ ከሆኑ ደግሞ ፍጥነታቸው ይቀንሳል። የነፋስ እንቅስቃሴ በየአይሮፕላን ጉዞ ላይም ተመሳሳይ ተፅእኖ ያደርሳል።

በብዙ ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በሚለካ የውቅያኖስ ገፅታ ላይ የሚገኝ ውሃ ሙቀት ሲጨምር፣ ከባህር በላይ ያለው የአየሩ ሽፋን ሙቀት አብሮ ይጨምራል። ሙቁ አየር በቀዝቃዛ አየር ወደ ተሸፈነው አካባቢ ከላይ ሲገሰግስ፣ ከታች ያለውን ውሃ ይጎትተዋል፤ ይስበዋል፤ የውሃው ጉዞ (current) ፍጥነትም እንዲጨምር ያደርገዋል። የውቅያኖስ ውሃ እንቅስቃሴ ከላይ በሚታይ ሁኔታም ሆነ ውስጥ ለውስጥ ይካሄዳል። ቀዝቃዛ ውሃ ከታች ተነስቶ ወደ ባህሩ ገፅታ ሲፈስ፣ ከላይ ያለው ሙቅ ውሃ ደግሞ ቀዝቃዛው ወደነበረበት አካባቢ ይንቀሳቀሳል። በሂደት ቀዝቃዛው ውሃ “ንጥረ ምግብ” ግብዓቶችን ከነበረቡት/ከሚገኙበት ጥልቅ ባህር፣ የፀሐይ ብርሃንና ሙቅት ወደሚደርስበት ወደ ባህሩ ገጽ አካባቢ ያመጣቸዋል።

የእንቅስቃሴው መንስዔ በፀሐይ ኢነርጂ በመሬት ሰቅ አካባቢ ያለው አየር እንዲሁም የውቅያኖስ ውሃ ከሰቁ ራቅ ብሎ ከሚገኝ አካባቢ በበለጠ ሁኔታ ለሙቀት ስለሚዳረግ ነው። ስለሆነም የነፋሱም ብሎም የውሃው እንቅስቃሴ መንስዔ የፀሐይ ኃይል ነው።

ፀሐይ በምድር ላይ ያለው የቀን ተቀን ሙቀት ሚዛናዊ እንዲሆን ታግዛለች። ቀን ፀሐይ በምታበራበት ጊዜ፣ የብስ (በአፈር የተሸፈነው አካል) ሙቀት ከውሃ አካላት (ውቅያኖስ፣ ባህር ሃይቅ) ሙቀት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ ነው። የብስ ላይ ያለው አየር ወደ ላይ ሲንር፣ በውሃ ገፅታ ላይ ያለው አየር ወደ የብስ ይነፍሳል፣ ብሎም የአካባቢውን ሙቀት ዝቅ ያደርገዋል። በተቃራኒው፣ ሌሊት የብስ አካባቢ ያለው የሙቀት መጠን በቶሎ ዝቅ ስለሚል፣ አካባቢው በቶሎ ይቀዘቅዛል፣ ብሎም የብስ ላይ ያለው ቀዝቃዛ አየር በዚያን ጊዜ ወደ ውሃ አካል (ባህር ወዘተ) ይነፍሳል። ውሃ ገፅታ ላይ ያለው ሙቅ አየር ከውሃ አካል ወደ የብስ ይነፍሳል። በዚህ ኩነት የብስ ላይያለው ሙቀት እና ውሃ አካባቢ ያለው ሙቀት ሚዛን እንዲጠብቅ ሂደቱን ፀሐይ ታስተናግዳለች።

ፀሐይ እና ወራት

ምድር አንድ ጊዜ ፀሐይን ስትዞራት አንድ ዓመት ይባላል። ምድር ፀሐይን ስትዞር ገደድ ብላ/ ተንጋዳ ስለሆነ፣ ለፀሐይ ጠጋ ያለው አካባቢ የሙቀት ወቅት (ሳመር/Summer)፣ ራቅ ያለው ደግሞ የቀዝቃዛ ወቅት (ዊንተር/ winter) ይሆናል።

በስእሉ ላይ እንደሚታያው የምድር ሰሜን ዋልታ ከፀሐይ በሚርቅበት ወቅት፣ ከመሬት ሰቅ ሰሜን ያለው ቀዝቃዛ ወቅት፣ ከመሬት ሰቅ በታች ያለው የሙቀት ወቅት ይሆናል። በተቃራኒው የደቡብ የምድር ዋልታ ከፀሐይ በሚርቅበት ወቅት፣ ከመሬት ሰቅ ሰሜን ያለው የሙቀት ወቅት፣ ከሰቅ በታች ያለው ደግሞ ቀዝቃዛ ወቅት ይሆናል።

ከምድር ሰቅ በሰሜን በኩል የሙቀት ወቅት ከግንቦት እስከ ነሐሴ ሲሆን፣ በዚያን ወቅት ከምድር ሰቅ ደቡብ ያለው አካባቢ የብርድ ወቅት ነው። በተቃራኒው ከምድር ሰቅ ደቡብ ያለው አካባቢ የሙቀት ወቅት ከታኅሣሥ እስከ የካቲት ሲሆን፣ በዚያን ወቅት ከምድር ሰቅ በስተሰሜን ያለው አካባቢ የብርድ ወቅት ነው።

በተለምዶ በእንግሊዝኛ “ሳመር” የሚባለው ወቅት በሰኔ፣ በሐምሌ እና በነሐሴ ስለሆነ እኛ ክረምት የምንለው ወቅቱ እነሱ “ሳመር” የሚሉት ነው። ስለሆነም ነው በጋ እና ክረምት የሚለውን ትተን፣ የብርድ ወቅት እና የሙቀት ወቅት ብለን የገለጽነው።

ምድር በራሷ ላይ አንድ ጊዜ ስትዞር፣ በፀሐይ ጎን ያለው ብርሃን፣ በተቃራኒ ጎን ያለው ግማሽ አካል ጨለማ ይሆናል፣ የብርሃኑ እና የጨለማው ጊዜ ድምር አንድ ቀን ይባላል፣ ሃያ አራት ሰዓት። መሬት ሰቅ አካባቢ ያሉ ቦታዎች፣ ተመጣጣኝ የጨለማ እና የብርሃን ጊዜ አላቸው፣ ስለሆነም 12 ሰዓት ጨለማ 12 ሰዓት ብርሃን ያገኛሉ። ከመሬት ሰቅ በራቅን መጠን ብርሃኑ እና የጨለማው የጊዜ መጠን ድርሻ በተመጣጣኝ ሁኔታ እንደርቀቱ ይቀያየራል።

ተፈጥሮያዊ ዑደቶች

ፀሐይ በተፈጥሯዊ ዑደቶች ላይ ወሳኝ ሚና አላት። በፀሐይ መንስዔ ለሚከሰቱት ግዙፍ የቁስ ዑደቶች የውሃ ዑደት እንደምሳሌነት ሊወሰድ ይችላል። ምድራችን ላይ ውሃ ሦሰት ዓይነት ባህርያት አሉት፣ እነሱም ጠጣር (በረዶ/ ሸኸት)፣ ፈሳሽ (ውሃ) እና ጋዝ (የተነነ ውሃ/ እንፋሎት/ ደመና) ናቸው። የውሃ ዑደት የውሃ ባህርያት የመቀያየር ውጤት ነው። ውሃ በፀሐይ ሙቀት መንስዔ ተኖ፣ ፈሳሽ የነበረው ወደ እንፋሎትነት ይቀየራል፣ ያም የሰማይ ዳማና ይሆናል። ደመናው ሲቀዘቅዝ የተሸከመው ውሃ በዝናብ መልክ ወደ መሬት ወርዶ ወንዞችን፣ ሃይቆችን ይሞላል፣ ወንዞችም ወደ ውቅያኖስ ይፈሳሉ። ለፀሐይ የተጋለጠው ውሃ ሙቀቱ ይጨምርና እንደገና ይተናል፣ ከዚያም ደማና፣ ብሎም ዝናብ ይሆናል፣ ዑደቱ ይቀጥላል።

ፀሐይ እና ሕይወት

የጋዝ (gas) ይዘት ያለው “ካርቦን ዳይከሳይድ” (CO2) ምንም መጠኑ ትንሽ ቢሆንም ምድራቸን ሕይወት አልባ እንዳትሆን ዋና ሚና አለው። ይኸውም ከላይ እንደተጠቀሰው የፀሐይ ጨረር ሙቀት ምድር ላይ ከደረሰ በኋላ ተንፃባርቆ ወደ ሕዋ እንዳይመለስ ሽፋን፣ መጋረጃ ሆኖ የፀሐይ ሙቀት ምድር ላይ እና ዙሪያ ታምቆ እንዲቆይ ስለሚያደርግ ነው። መጠኑ እስከተወሰነ ድረስ ሙቀቱ ለሕይወት አስፈላጊ ነው። ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው “ዝገ ክበብ አየር” (green house effect) ይባላል፣ ባህሪዩም መስኮቱ እንደተዘጋ መኪና ሊመሰል ይችላል። መስኮቱ የተዘጋ መኪና ውስጥ ያለው አየር፣ ውጭ ካለው አየር በላቀ ደረጃ ይሞቃል።

የእፅዋት ቅጠሎች በፀሐይ ብርሃን ኃይል ታግዘው “ካርቦን ዳይኦክሳይድን” (CO2) በመማግ ወደራሳቸው አካልነት ይቀይራሉ፣ ይኸን የሚተገብረው የእፅዋት ፋብሪካ “ክሎሮፊል” (Chlorophyll) ሲባል፣ የመፈበረኩ ሂደት “ብርሃን አስተፃምሮ” (ፍቶሲንቴስስ/ photosynthesis) ይባላል። በፀሐይ ኃይል ቀጥተኛ ተጠቃሚው ፋብሪካ “ክሎሮፊል” ካርቦን ዳይኦክሳይድን (CO2) ምጎ፣ በምትኩ ኦክስጅንን (O2) ይተፋል። “ኦክስጅን” (O2) ለሕያው ሕልውና ወሳኝ ሚና አለው፣ ስለሆነም “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” ለሕያው መሠረት ነው። እንስሳት የራሳቸውን ምግብ ስለማያዘጋጁ፣ በእፅዋት የተዘጋጀውን ምግብ ነው የሚመገቡ። በዚህ ሂደት ነው ፀሐይ በሕያው ላይ ያላት ሚና ቁልጭ ብሎ የሚታየው።

እፅዋት ወይም እንስሳት በባህር ውስጥ ሲሞቱ፣ ቅሬቶቻቸው ይበሰብሳል፣ ብስባሹ ለሕያው የምግብ ግብዓት ወደ ሆኑ ንጥረ ነገሮች ይቀየራል። ሆኖም የፀሐይ ብርሃን እና ሙቀት ወደማይደርስበት፣ ብሎም እፅዋት ወደማይኖሩበት ይዘቅጡና፣ ከምግብ ግባትነት ይሰወራሉ። በውቅያኖስ፣ በባህር፣ በሃይቅ፣ የውስጥ የውሃ እንቅስቃሴ (ማዕበል/ current) እነኚህን የዘቀጡ “ንጥረ-ምግብ” እፅዋት ወደሚኖሩበት፣ ጥልቀተ-ውስን ወደሆነ የውሃው አካል ይወሰዳሉ፣ ብሎም “ለውሃ አቅላሚ” (አልጌ/ algae) ለምግብ ግባትንት ያገለግላሉ።

በውሃ ውስጥ፣ “ለቀዳማይ አምራችነት” (Primary productivity)፣ “ለአልጌ” እና ተመሳሳይ ንዑስ እፅዋት የእድገት ግብዓት የሚሆኑ “ንጥረ-ምግብ” (Nutrients) በዚህ ሂደት ነው የሚገኝ። “ውሃ አቅላሚዎችን” የሚመገቡ እንስሳት፣ በተለይ የዓሳ ዝርያዎች ምግብ አግኝተው ለመራባት ይበቃሉ። እነኚህ ዓይነት የውሃ እንቅስቃሴዎች (ከጥልቅ ባህር ወደ ላይ የሚዘልቁ) ባሉበት አካባቢ መጠኑ ጠቀም ያለ አሳ ማምረት ይቻላል።

በአፈር አመሠራረትም የፀሐይ እጅ አለበት። ዝናብ ከሰማይ ሲወርድ አየር ውስጥ ያለውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ አሟምቶ፤ የራሱ አካል አድርጎ ወደ መሬት ይወስዳል (ያዘንበዋል)። ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከውሃ ጋር በመዋሃድ ወደ “ካርቦኒክ አሲድ” (Carbonic acid) ተቀይሮ፣ አለት ይሰነጣጥቃል፣ ይሰባብራል፣ እንዲሁም በሌሎች አካላት ላይ የአሲድነት ተፅዕኖ ያደርጋል። በቀን የፀሐይ ሙቀት በሌሊት ቅዝቃዜ ሲከሰት፣ ድንጋይ (አለት) ይፈረካከሳል፣ ይሰባበራል፣ ብሎም ወደ አፈርነት ይቀየራል። በምድር ላይ የሚበቅሉ እፅዋት የምግብ ፍጆታ የሚያገኙ፣ በ”ብርሃን አስተፃምሮ” ከሚገኘው በተጨማሪ አፈር ነው። ስለሆነም ፀሐይ በእጅ አዙር ለአፈር መገኘትም አንዷ ምክንያት ናት።

ፀሐይን ከብዝሃ ሕይወት አንፃር እንፈትሻት። የመሬት ሰቅ አካባቢ ከሰሜን እና ከደቡብ ዋልታ አካባቢዎች የላቀ የፀሐይ ሙቀት እና ብርሃን ያገኛል። ያም የመሬት ቅርጽ ዱባ መሰል ስለሆነ፣ የመሬት ሰቅ አካባቢ ከሌላው አካባቢ ለፀሐይ የተሻለ ቅርበት አለው። እንዲሁም ሌሎችአካባቢዎች በተወሰኑ ወራት ጠንፍ በረገጠ ብርድ ሲቆፈደዱ፣ የመሬት ሰቅ አካባቢ ሁልጊዜም ከፀሐይ ሙቀት እና ብርሃን አይነፈግም። ኬሚካላዊ ሂደቶች በሙቀት መንስዔ በመሬት ሰቅ አካባቢ ፈጣን ስለሆኑ፣ የረገፉ ቅጠሎችም ሆኑ ሕያው አልባ የሆኑ እፅዋት እና እንስሳት ቅሬቶች ውስጥ ያለው ኬሚካላዊ ውሁድ፣ በቀላሉ ይፈራርስ እና በውስጡ ያለው “ንጥረ-ነገር” (nutrients) ለምግብ ግብዓትነት ያገለግላል።

የዚህ ውጤት የሕያው መራባት እና እድገት ግብዓት የሆኑ ንጥረ-ምግብ በብዛት ይገኛሉ። ስለሆነም በአካባቢው የሕያው እድገት፣ በተለይ እፅዋት በጣም ፈጣን ነው። ለምሳሌ በሰሜን እና በደቡብ ዋልታዎች አጠገብ ያሉ እፅዋት አስረተ-ዓመታት የሚፈጅባቸው የእድገት መጠን፣ በምድር ሰቅ አካባቢ ያሉት ተመጣጣኝ እድገት በጥቂት ዓመታት ሊከናወን ይችላል።

የተለያዩ ኩነቶች ተደምረው፣ በመሬት ሰቅ አካባቢ ያሉ የእርጥበት እጥረት የሌለባቸው ቦታዎች የብዝሃ ሕይወት ባለፀጋዎች ሆነዋል። በዓለማችን ያሉ የተፈጥሮ ግዙፍ ደኖች፣ “የአማዞን” እና “የኮንጎ” ደኖች የሚገኙ በምድር ሰቅ አካባቢ ነው። በእነዚህ ደኖች ውስጥ በጣም ብዙ የእፅዋት እና የእንስሳት፣ ብሎም “የዘረ እንጉዳይ” (fungus) እና የማይክሮቦች “ብቸኛ ዝርያዎች” (species) ይገኛሉ። የብቸኛ ዝርያዎች ቁጥር በጨመረ መጠን፣ የብዝሃ ሕይወት ሃብትም በተመጣጣኝ ሁኔታ ይጨምራል።

ፀሐይ እንዲሁም ከእንስሳት ባህሪዎች ጋር የተዛመደች ናት፣ በእንስሳት ስደት/ ፍልሰትም ወሳኝ ሚና አላት። ለምሳሌ፡- ብዙ የአእዋፍ ዝርያዎች “ከሰሜናዊ ሄሚስፊር” (Northern Hemisphere) ቀዝቃዛ ወራት ሸሽተው ወደ መሬት ሰቅ (equator) አካባቢ ይሰደዳሉ። ወቅቱን ጠብቀው “ሰሜናዊ ሄሚስፊር” ከቆፈድ ሲላቀቅ፣ ቀደሞ ወደ ነበሩበት አካባቢ ይመለሳሉ። በዚህ ተግባር አእዋፍ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ያቋርጣሉ።

በፀሐይ እና በሕያው ግንኙነቶች፣ ብዙ አስደናቂ እና አስገራሚ የሆኑ ኩነቶች ተከስተዋል። ለምሳሌ፡- በቀዝቃዛ ወራት አሸልቦ ወቅቱን በእንቅልፍ መሰል ሁኔታ ማሳለፍ ማለት በ”ሸሸጋ” (hibernation) ሁኔታ የገላ ሙቀት፣ የልብ ትርታ፣ ብሎም አተነፋፈስ እንዲቀንስ ይደረጋል። በዚህ ሂደት ለሕያው አካል የሚያስፈልገው የኢነርጂ መጠን ተቆጥቦ፣ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ይደረጋል። “ሸሸጋ” በብዛት የሚከሰተው በቀዝቃዛ ወራት ሲሆን፣ ከእንቅልፍ በጣም በረዘመ ሁኔታ ተከስቶ፣ ሕልውናን ሳይገዳደር ለወራት ሊዘልቅ ይችላል። ከሌላ አንፃር ድርቅ እና ሙቀቱ የናረባቸውን ወቅቶች “በአህብቦት” estivation) ከተለመዱ የሕያው ተግባራት ተቆጥበው መጥፎ ጊዜን ማሳለፍ የሚችሉ ሕያው አካላት አሉ። እንዲሁም ቀን የብርሃንና የሙቀት ጊዜ ስለሆነ እና ሌሊት በተቃራኒው ጨለማ እና ቀዝቀዝ ያለ ስለሆነ፣ በብዙ እንስሳት ጨለማ የእረፍት ጊዜ (የእንቅልፍ) እና ቀን የእንቅስቃሴ ጊዜ ተደርጎ “በየሕያው ወቅት ልክ” (biological rhythm) ይስተናገዳል።

መደምደሚያ

በምድራዊ ኩነቶች ሁሉ የፀሐይ እጅ አለበት። ካለ ፀሐይ አስተናጋጅነት ሕይወት መኖር ይቅር እና ልትታለምም አትችልም ነበር። ፀሐይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፣ የሕያው ምግብ ፋብሪካ ሞተር ናት። ለሕያው አስፈላጊ የሆኑ እንቃስቃሴዎች ሁሉ በፀሐይ እገዛ ነው የሚተገበሩት።

ፀሐይ ለሰው ልጆች የተስፋም፣ የስጋትም ምንጭ ናት። ስጋቱ ከአየር ቅጥ ለውጥ ጋር የተጓዳኘ ሲሆን፣ ተስፋው ደግሞ ፀሐይ የወደፊት ወሳኝ ብክለት አልባ የኢነርጂ ምንጭ መሆን ስለምትችል ነው። ፀሐይ የምትከስመው ያላትን እምቅ ኢነርጂ ተጠቅማ ስታበቃ ሲሆን፣ ያም አምስት ቢሊዮን ዓመት ገደማ እንደሚፈጅ ይገመታል፣ ስለሆነም ቋቱ በቅርብ ጊዜ አይነጥፍም።

የስጋት ምንጭ የሆነው፣ ቀጥታውን ፀሐይ ሳትሆን፣ ሰበነክ የሆነ ተግባር ከፀሐይ ሙቀት ጋር ተቆራኝቶ የሚከሰት ችግር ነው። የችግሩ መንስዔ የእፅዋት ቅሪት የሆኑ፣ በከርሰ ምድር የሚገኙ የነዳጅ ዘይትን እና የድንጋይ ከሰል ያለአግባብ ከመጠቀም የሚመነጭ ነው። በዚህ ተግባር የሚያመነጨው የጋዝ ዓይነት “ካርቦንዳይኦክሳይድ” (CO2) ነው የአየር ቅጥ ለውጥ (Climate Change) ዋናው መንስዔ የሆነው። በሕዋ ሽፋን ብክለት መንስዔ የምድራችን ሙቀት እየናረ ሄዶ፣ ምድራችን ለሕያው መኖሪያ ምቹ የማትሆንበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች። ይህንን ስጋት ለመቅረፍ ብዙ ዓለም አቀፍ ሰምምነቶች እየተመሠረቱ እና መርሃ ግብሮች እየተተገበሩ ይገኛሉ። በአገራችን የዛፍ ተከላ ፕሮግራምም (የአረንጓዴ አሻራ) የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነው።

የተስፋው ምንጭ በቴክኖሎጂ እገዛ በፀሐይ ኢነርጂ በመጠቀም አላስፈላጊ ብክልትን ማስቀረት ነው። ከድንጋይ ከሰል እና ከፈሳሽ ነዳጅ የሚገኘውን ኢነርጂ ከፀሐይ በሚገኝ ኢነርጂ መተካት ነው። ከተስፋ ጋር ተዛምዶ ስለ ፀሐይ ኃይል ብዙ እየተባለ ነው። በዘመናችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ከፀሐይ የሚገኝ ኢነርጂ ከሌሎች ምንጮች ከሚገኝ ኢነርጂ ቀለል ባለ ወጪ ለማግኘት ተችሏል። ከፀሐይ የሚገኘው ኢነርጅም መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ፀሐይ ተዝቆ የማያልቅ የእምቅ ኢነርጂ ምንጭ ስለሆነች፣ የሰው ልጆች ከተፈጥሮ በዘለለ በቴክኖሎጂ የሚታገዝ የኢነርጂ ማምረቻ በመሆን ታገለግላለች።

የኤሌክትሪክ ኃይል ከፀሐይ ማግኘት የተቻለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን (እንደ ግሪጎሪያን አቆጣጠር በ2021)፣ በዓለማችን ከሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል አራት በመቶ (4%) በቴክኖሎጂ እገዛ ከፀሐይ የሚገኘው ኢነርጂ ነው። ምንም እንኳ ከፀሐይ የሚገኘው ኢነርጂ ብክለት አልባ ቢሆንም፣ በአጠቃቀም ላይ ጥቂት ተግዳሮቶች አሉት። ለጊዜው ዋናው ማነቆ፣ ኢነርጂ ማመንጨቱ ሳይሆን፣ የተገኘውን ኢነርጂ በምን መልክ አቆይቶ ለመጠቀም የመቻልን አቅም ማጎልበቱ ነው። ችግሩ ማከማቻው እንጂ ማምረቱ አይደለም። ዋናው የኢነርጂ ማቆያ ባትሪ ስለሆነ፣ የባትሪ ይዘት ቴክኖሎጂ በማዳበር ችግሩ እንደሚፈታ ይታሰባል።

ለወደፊት ብክለት አልባ የኢነርጂ ምንጭ የሚሆነው፣ ፀሐይ ኢነርጂ የምታመነጭበት ዘዴ በመኮረጅ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። የፀሐይ ኢነርጂ ምንጭ ሁለት የሃይድሮጅን አቶም ኑክሊየሶችን በመቀላቀል (nuclear fusion) የተገኘ ሲሆን፣ በኢነርጂው አጠቃቀም ሂደት አካባቢ የሚበክል ዝቃጭ አይኖርም። የሚገኘውም ኢነርጂ የትየለሌ ነው። ስለሆነም ፀሐይ የብሩህ ተስፋ ፏፏቴ፣ የሕይወት መሠረት፣ ብሎም ተፈጥሮ የለገሰችን ተተኪ የሌላት ስጦታ ናት።

ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ) እና አታላይ አየለ (ፕሮፌሰር)

Recommended For You