ፈውስ ፈላጊው የትምህርቱ ዘርፍ

መነሻ ሐሳብ

“ትምህርት የዕውቀት መሠረት ነው” ይሉት ተለምዷዊ ብሂል፤ ከይትበሃልነት ባሻገር የትምህርትን የዕውቀት መሠረትነት መግለጥ ከአልቻለ የንግግር ማድመቂያ ከመሆን የዘለለ ረብ አይኖረውም። ለዚህ ማረጋገጫ ሊሆን የሚችል ዐቢይ ማሳያ ከአስፈለገ ደግሞ ተምረው ያወቁ፤ አስተምረውም ያሳወቁ ማኅበረሰቦች እና አገሮች ዛሬ ላይ በዓለማችን በምን መልኩ ተገልጠዋል? ተገኝተዋል? የሚለውን ጠይቆ ለመረዳት መሞከር በቂ ነው።

ትምህርት የዕውቀት መሠረት የሆናቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች/ሀገራት ማወቃቸው ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ጉዳዮቻቸው መፍትሔ የማፍለቅ ልዕልናን ሲያጎናጽፋቸው ተመልክተናል። ስለዐወቁ የሳይንስም፣ የቴክኖሎጂም፣ የሥነ ፈለግም፣ የሥነ ጥበብም፣ የመድኃኒትም፣ የምሕንድስናም፣… ጥበብን መጎናጸፍ ችለው፤ ከራሳቸው የአለፈ ሌሎች የአእምሮ ፍሬያቸው ተቋዳሽ የሚሆኑበትን ዕድል ፈጥረዋል።

በዚህ ረገድ እነ አሜሪካና የአውሮፓ አገሮችን የሥልጣኔና የመበልጸግ ከፍታ መመልከቱ ዕውቀት በሁሉም መስክ ከፊት የሚያሰልፍ መሆኑን ለመገንዘብ ያግዛል። በተመሳሳይ በቅርብ ዓመታት ከነበሩበት የድህነት አረንቋ ወጥተው ከፍተኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ የደረሱ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ እና ሌሎችም በፈጣን የዕድገት መንገዳቸው የሚገለጹ አገሮችን ማየት ጠቃሚ ነው። እነዚህ አገሮች ለትምህርትና ሥልጠና በሰጡት ትኩረት የሰው ሀብታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት የሕዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል እንደቻሉ ለመረዳት ያስችላል።

ቀድመው የበለጸጉትም ሆነ ዘግይተው ወደ ብልጽግናው ጎዳና ገብተው የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ምጣኔያቸውን የአፋጠኑ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው፤ ትምህርት ምን ያህል በማኅበራዊ ጉዳያቸው፤ በፖለቲካ ንቃተ ኅሊናቸው፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መንገዳቸው ዐቅም እንደሆናቸው ነው። ምክንያቱም በተማሩ ዐውቀዋል፤ በዐወቁ ተመራምረዋል፤ በተመራመሩም መፍጠር ችለዋል። ብቁና በቂ የመፍጠር ዐቅም ያለው ዜጋ ማፍራታቸው ሰፊውን ሕዝባዊ እና አገራዊ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ፤ የደኅንነት ስጋታቸውን ለማቃለል፤ የኃይል ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ እና በሁሉም መስክ ቀድመው ለመገኘት አስችሏቸዋል።

አገራችን ኢትዮጵያም የዜጎችን የዕውቀት አድማስ ለማስፋት ዘመናዊውን የትምህርት ሥርዓት ዘርግታ፣ ትምህርት ቤት ገንብታ ማስተማር ከጀመረች ከምዕተ ዓመት የዘለለ ዕድሜን አስቆጥራለች። ቀደም ሲል በቤተ እምነቶች ሲሰጥ የነበረውን የፊደል ቆጠራ ሂደት ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ የተተገበረው ዘመናዊው ትምህርትም አንቱታን የአተረፉ ዐዋቂዎችን ማፍራትም የተቻለበት ዕድል ተፈጥሯል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከትናንት እስከ ዛሬ አንድም ስለ ትምህርት ፍትሐዊነትና ተደራሽነት፤ ሁለተኛም፣ በትምህርት ጥራትና ተገቢነት ላይ የሚሰነዘሩ ስል ትችቶች አልጠፉም። ይኼም በቀደምት ሥርዓቶች በተደራሽነት፣ በቅርቦቹ ሥርዓቶች ደግሞ በጥራት ላይ አመዝነው የሚሰነዘሩ ሐሳቦች የበረቱበት ነው። የእነዚህን ሐሳቦችና ትችቶች ምክንያትም ሆነ ጭብጥ ለመረዳት ታዲያ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከትምህርት ጥራትና ተደራሽነት አኳያ ከየት ተነሥቶ ወደየት የደረሰ ነው? የሚለውን ቀድሞ በወፍ በረር መመልከቱ ተገቢነት ይኖረዋል።

የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ከየት ወደ የት?

በኢትዮጵያ ምንም እንኳን ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ዳምጦ፣ ፊደል ቀርጾ፣ ማስቆጠር የተጀመረበት ዘመን ከሩቅ የሚጠቀስ ቢሆንም፤ “ዘመናዊ ትምህርት” የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ስለመሆኑ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ያስረዳሉ። በወቅቱ የነበረው የትምህርት ዓላማምበጅምር ደረጃ የነበረውን ፊውዳላዊ ቢሮክራሲ የሚያገለግልና በተለይ በአስተርጓሚነት የሚሠራ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፈራት እንደነበርም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

በወቅቱም ሥርዓተ ትምህርቱም ከውጭ የተቀዳ፣ መምህራኑም የውጭ ዜጎች ነበሩ። በሒደትም ሥርዓተ ትምህርቶቹ በአገር ውስጥ እንዲቀረጹ ቢደረግም፣ ከውጭ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ተላቅቀው የሀገሪቱን ችግር የሚፈታ ተደራሽነት፣ ተገቢነት፣ ፍትሐዊነትና ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ሊዘረጋ አልተቻለም። ይኽንንም ለትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሲባል “የትምህርትና ሥልጠና ችግሮቻችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች” በሚል ርእስ በ2010 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ጊዜያዊ የሴክቴሪያት ጽ/ቤት የተከናወነ ጥናት ሰነድ ያመልክታል።

በዚህ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፤ እስከ ንጉሣውያን ዘመን ማብቂያ ድረስ የነበረው የትምህርት ተደራሽነት ውስን ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችም በዋና ዋና ከተማ ብቻ ነበር የሚገኙት። ሴቶች፣ ልዩ ፍላጎት የአላቸውና አርብቶ አደር ዜጎች ደግሞ የዕድሉ ተቋዳሽ አልነበሩም።

ከትምህርት ተገቢነትና ጥራት አኳያ ሲታይም በወቅቱ ከ85 በመቶ በላይ የነበረውና በግብርና የሚተዳደረውን ሕዝብ ግብርናውን በማዘመን የኑሮ ደረጃውን አላሻሻለም። በደርግ ዘመንም ቢሆን ተደራሽነቱ እምብዛም አይደለም። በመሆኑም በእነዚህ ጊዜያት የነበረው የትምህርት ሥርዓት የሀገሪቱን ትምህርት ከተደራሽነት፣ ከፍትሐዊነት፣ ከተገቢነትና ከጥራት ችግሮች ሊያላቅቅ አልቻለም።

በአንጻሩ ከ1983ቱ የሥርዓት ለውጥ በኋላ፣ በ1986 ዓ.ም. የተቀረጸው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መነሻ በማድረግ በተሠሩ ሥራዎችም ውጤት ማግኘት እንደተቻለ መረጃው አመላክቷል። ለዚህም የትምህርት ተሳትፎን፣ ፍትሐዊነትና ጥራትን በማስጠበቅ በኩል የትምህርት አመራሩንና አደረጃጀቱን በወሳኝነት በሕዝብ ተሳትፎ እንዲመራ ሥርዓት በመዘርጋት እንዲለወጥ መደረጉን ይጠቅሳል።

ከሥርዓት ለውጡ በፊት በመላው አገሪቱ አራት ሺሕ በሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃና 278 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፤ በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዩን የአልበለጡ ተማሪዎች ብቻ ይማሩ እንደነበር ሰነዱ በአብነት ጠቅሷል። ይኼም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በዝቅተኛ የትምህርት ተሳትፎ ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የአደረጋት እንደነበር ያትታል።

ሆኖም ከሥርዓት ለውጡ ማግስት በተሠሩ ሥራዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ለማዳረስ መቻሉን፤ በዚህም ከ28 ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችን እያስተማሩ ያሉ ከ39 ሺሕ በላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ሦስት ሺሕ 300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመንግሥት ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ በሰነዱ ተገልጿል።

በተመሳሳይ መልኩ በጥቂት ተቋማትና የትምህርት ፕሮግራሞች ተወሰኖ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ከሁለት ወደ 46 ማሳደግ ተችሏል። ወደ 130 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ይሄም ከፍተኛ የሆነ የሠለጠነ የሰው ሀብት በማፍራት ለአገራዊ ዕድገቱ መሣለጥ ጉልህ ድርሻ አድርጓል።

የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በተመለከተ ከዚህ ሰነድ በተጨማሪ፣ በትምህርት ሚኒስቴር ከ2008 – 2012 ዓ.ም. እንዲተገበር በተዘጋጀው አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሐ ግብር ሰነድ፤ ከ2013 – 2022 ዓ.ም. እንዲተገበር በተዘጋጀው የዓሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ሰነድ፤ እንዲሁም በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ሰነድ ላይም ተመሳሳይ ሐሳቦች ናቸው የተጠቀሱት።

ሁሉም ሰነዶች ላይ ከ1983 ዓ.ም. የሥርዓት ለውጥ በፊት የትምህርት ተደራሽነት እምብዛም አለመሆኑን፤ ከ1986ቱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መቀረጽ በኋላ በተሠራው ሥራ ግን የትምህርት ተደራሽነትን እና ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ ውጤት የተገኘበት ስለመሆኑ ያብራራሉ።

በዚህ መልኩ የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ላይ አበረታች ሥራ የተሠራ መሆኑን የሚጠቅሱት እነዚህ ሰነዶች፤ ከዚህ በተቃራኒው ግን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብዙ ችግር የአለበት ስለመሆኑ ነው የሚያትቱት። ለምሳሌ፣ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፤ በ1986 ዓ.ም. ተቀርጾ ሲተገበር የቆየው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የትምህርት ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ በኩል ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ የትምህርት ጥራትን ግን ማረጋገጥ አልቻለም።

ይልቁንም በእነዚህ ዓመታት የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ የመጣ ሲሆን፤ በየደረጃው ያለው አብዛኛው ተማሪ የትምህርት ውጤት በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን 50 በመቶና በላይ ውጤት መሆን አለመቻሉ ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል እንደ ማሳያ ተደርጎ ነው በሰነዶቹ የተጠቀሰው።

በዚህ መልኩ ለትምህርት ጥራት መውረድ እና ውጤት ማሽቆልቆል እንደ ምክንያት ሆነው በሰነዱ ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል፤ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ በንድፈ ሐሳብ የታጨቀ እና ለተግባር ትምህርት ተገቢውን ትኩረት የአልሰጠ መሆኑ አንዱ ነው። በቴክኖሎጂ የተደገፈ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርትም ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ በሰነዶቹ ቀርቧል። ይኼም ከውጤት ማሽቆልቆል በተጓዳኝ ከኢንዱስትሪው ጋር የተሳሰረና የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ የአገናዘበ ትምህርትና ሥልጠና አለመተግበሩ፤ ሠልጥነውና ተመርቀው የወጡ ዜጎች የሥራ ፈጣሪ መሆን አለመቻላቸውም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ፣ ከትምህርት ጥራትም ተደራሽነትም አኳያ በሰነዶቹ የተመላከቱትን ሐሳቦች ይጋራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ባሉት ሥርዓቶች የትምህርት ተቋማት ቁጥርም፤ ተደራሽነታቸውም ትንሽ ነው፤ የቅበላ ዐቅማቸው እና ተሳታፊዎችም ትንሽ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የትምህርት ተቋማት ቁጥር በእጅጉ አድጓል። የተማሪዎች ቁጥምር ሆነ የመምህራን ብዛት ጨምሯል። ከዚህ አኳያ ሲታይ ተደራሽነቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው። ይሄ ተደራሽነት ደግሞ ከፍትሐዊነት አኳያም የሚታይ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በተወሰኑ ቦታዎች ተገድቦ የነበረው ትምህርት አሁን ወደ ሕብረተሰቡ ሁሉ ደርሷል። በአንደኛ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃ እና በየኒቨርሲቲም ደረጃ ተደራሽነቱ በጥሩ ሁኔታ ነው ያለው።

ይሁን እንጂ፣ በዚህ መልኩ ተደራሽነቱ እያደገ ሲሄድ፤ ይሄንን ተደራሽነት የመጠነ/ ማዕከል ያደረገ ለትምህርት አስፈላጊ የሆነ ግብዓት(ሪሶርስ)ን ከማሟላት አኳያ እጥረት አለ። ትምህርት ደግሞ ግብዓት ይፈልጋል። ግብዓት ሲያጥር ደግሞ የትምህርት ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ያሳድራል። ከዚህ አኳያ የተሠራው ሥራ በተደራሽነት ጥሩ ቢሆንም፤ በጥራት ግን ተጎድቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻያ ዴስክ ሐላፊ አቶ ታዬ ግርማ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። አቶ ታዬ እንደሚሉት፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዐሥርት ዓመታት፣ ለትምህርት ተደራሽነትም ሆነ ጥራት በተሠሩ ሰፋፊ ሥራዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም ቦታ ማዳረስ፤ በዚህ ደረጃ ያለው ጥቅል ተሳትፎም ወደ 98 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። በዚህ ረገድ በአለፉት ዓመታት ሲሠራ የነበረው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ማምጣት ላይ ነው። በዚህም ብዙ የተሠራ ሲሆን፤ ከቁጥር አኳያም ትምህርት ቤቶች የመንግሥትና የግሉን ጨምሮ ከ56 ሺሕ በላይ ደርሰዋል።

በዚህ መልኩ በጥቅል ተደራሽነቱ ሲታይ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ቢባልም፤ ተደራሽነቱ ጥራትን በሚያረጋግጥ መልኩ ነው ወይ? የሚለው ሲታይ፤ መልሱ አይደለም ነው። አንድ ትምህርት ቤት ሲገነባ/ሲከፈት ምን ምን ነገሮችን ማሟላት አለበት? የሚለው ታሳቢ አልተደረገም። ተደራሽነቱ ላይ ሲሠራ፤ አንደኛ፣ ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን (ስታንዳርዳቸውን) ጠብቀው አይደለም የተሠሩት። ምክንያቱም በወቅቱ በሕብረተሰቡ ፍላጎት እንዲሁም በፖለቲካው ጫና የተነሣ ብቻ ደረጃውን በአልጠበቀ ሁኔታ በዘፈቀደ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች ብዙ ናቸው።

ለምሳሌ፣ ትምህርት ቤቶቹ ሲሠሩ የግብዓት ደረጃ (ስታንዳርድ) አሟልተው አይደለም። ተማሪዎች የሚማሩበት ክፍል ብቻ በመገንባት የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች አሉ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ግን በቂ መቀመጫ እንኳን የሌላቸው፤ ጥቁር ሰሌዳ የሌላቸው፤ ቤተ ሙከራ እና ቤተ መጻሕፍት የሌላቸው፤ ውሃ እና መጸዳጅ ቤት የሌላቸው፤ የልጆች መጫወቻ ሜዳ የሌላቸው ናቸው።

በዚህ በኩል፣ በተደረገ የፍተሻ ሥራ ከአሉት ከ56 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ86 በመቶ በላዩ ከደረጃ በታች ናቸው። ይሄ ማለት ደግሞ ለመማር ማስተማር ሥራ ብቁ አይደሉም። በዚህ መልኩ ደረጃውን በአልጠበቀ ሁኔታ (ያለ ስታንዳርድ) ለማዳረስ ሲባል የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት ሳያገኙ እንዲቀሩ ስለሚያደርጉ ለትምህርት ጥራት መጓደል የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ታዲያ በኢትዮጵያ ትምህርት ወድቋል?

በትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ላይ ታየ የተባለው ውጤት ከጥራት አኳያ በተቃርኖ መንገድ መገለጹ፣ እንደ አገር የትምህርት ጥራት እንዲወርድ ማድረጉን መረጃዎችም፣ የዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ። ይኼ የትምህርት ጥራት ችግር ከፍ ብሎ መታየት ደግሞ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሚገባቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ይዘው እንዲወጡ እያደረጋቸው አይደለም።

ይሄ ያለመሆኑ ማሳያ ደግሞ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል፤ እንዲሁም ሠልጥነውና ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ ያለመሆን፤ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ያለማፍለቅ ችግር አሳድሮባቸዋል። አሁን በአለው ሁኔታም ትምህርት የሚጠበቅበትን ግብ መምታት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፤ ወይንም ወድቋል። ይኼም የትምህርት ጥራት ችግሩም ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት መሸጋገሩን ማሳያ ነው፤ ሲሉ የሚከራከሩ አካላትም ተፈጥረዋል።

በእርግጥ የትምህርትና ሥልጠና ሂደቱ በርካታ የሰው ኃይል አስተምሮ ማስመረቅ የተቻለበት ቢሆንም፤ ተምረውና ሠልጥነው የሚወጡ ዜጎች የሚፈለገውን ዐቅም መፍጠር አልቻሉም። ይሄ በመሆኑም በቂና ተገቢ የሰው ኃይል ለገበያው ማቅረብ አለመቻሉን፤ ሰልጥነውና ተመርቀው የወጡ ዜጎችም ቢሆኑ ሥራ ፈጣሪ መሆን አለመቻላቸውን በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ላይም በግልጽ ተመላክቷል። ትልቁ ጉዳይ ግን በዚህ መልኩ የሚገለጸው የትምህርት ጥራት ችግር በኢትዮጵያ ትምህርት ወድቋል በሚያስብል ደረጃ ላይ ነውን? የሚለው ጉዳይ ነው።

ይኽንን በተመለከተ አቶ ታዬ እንደሚናገሩት፤ ለትምህርት ጥራት መጓደል ብዙ ማሳያዎች አሉ። ዋናው ጉዳይ ግን አንድ ተማሪ ከትምህርት ቤት የሚያገኛቸው ነገሮች በዕውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከትና አስተሳሰቡ ምን ለውጥ አመጡለት? የሚለው ነው። ምክንያቱም ይኼ ተማሪ በትምህርት ቤት ቆይታው በዚህ ረገድ ማግኘት የሚገባውን ነገር ከአልተሰጠው ትምህርት ወድቋል ማለት ነው።

ሆኖም ትምህርት ወድቋል ወይም የትምህርት ጥራት ችግር አጋጥሟል ስንል በደፈናው ሳይሆን፤ የቱጋ ነው ችግሩ የተፈጠረው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል። አንዱ መለኪያው፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ (ስታንዳርድ) ነው። በዚህ በኩል፣ ከ86 በመቶ በላይ ትምህርት ቤቶቻችን ከደረጃ በታች ናቸው።

ከትምህርት ቤቶች ደረጃ (ስታንዳርድ) ችግር ባለፈ፤ በቂ ዝግጅት ያላቸው በቂ መምህራን ሳይኖራቸው የተከፈቱ በርካታ ትምህርት ቤቶች አሉ። በተመሳሳይ በአንድ ክፍል ውስጥ ከደረጃው (ስታንዳርዱ) በላይ የተማሪ ቁጥር እንዲማር ይደረጋል። ለምሳሌ፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስታንዳርዱ በክፍል 40 ተማሪ ቢሆንም፤ እስከ 120 ተማሪ ተቀምጦ ይማራል። ይሄ ደግሞ መምህራን እንደየተማሪዎቹ የትምህርት አቀባበል ችሎታ ተማሪዎችን እንዳያግዙና እንዳያበቁ ያደርጋል።

የመጻሕፍት አቅርቦት ችግር፤ መምህራንም የትምህርት ካሪኩለሙን ተረድቶ ከማስተማር አኳያ ያለ ክፍተት፤ የትምህርት አመራሩ በአግባቡ ሥራው ላይ ያለማተኮር ድክመት፤ ወላጆች ከትምህርት ቤቶች ጋር ያላቸው ቁርኝትና ልጆቻቸውን የመከታተል ጉዳይ፤ የትምህርት አመራሩ ኢንስትራክሽናል ሊደር ሺፕ ያለመሆን፤ የተማሪዎች ለመማር ፍላጎት ማጣት፤ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የሰላምና ጸጥታ ችግር፤ በትምህርት ቤቶች የሚንጸባረቀው የፖለቲካ አመለካከት፤… የመሳሰሉ ጉዳዮች ለትምህርት ጥራት መጓደል የየራሳቸው አበርክቶ አላቸው።

እንደ አቶ ታዬ ማብራሪያ፤ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች የትምህርት ጥራት ችግር ተፈጥሯል፤ የተማሪዎች ውጤት አሸቆልቁሏል። ይሄ ማለት ግን ትምህርት ፈጽሞ ወድቋል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም፣ ዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ሰዎችን ማፍራትም፤ ማግኘትም ተችሏል። እነዚህን የፈጠረው ደግሞ ይኼው የትምህርት ሥርዓት ነው። ይሄ የሚያሳየው ደግሞ መሥራት የሚገባውን ባለመሥራት የተፈጠረ የትምህርት ጥራት መጓደሉን እንጂ ትምህርትም ሆነ የትምህርት ሥርዓቱ መውደቁን አይደለም።

ይኼው የአቶ ታዬ ገለጻ በዶክተር ፍርዲሳ ማብራሪያም ተቀባይነት አለው። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ትምህርት ለአንድ ዓላማ፣ ግብና ራእይ ነው የሚሰጠው። ይኼም ተማሪዎች ሠልጥነው ለአገር አገልግሎት እንዲበቁ ማስቻል ነው። ሆኖም ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ለዚህ ደረጃ ካልበቁ (በዕውቀታቸው፣ በክህሎትና በአመለካከታቸው) እና የታሰበው ቦታ ሳይውሉ ሲቀር ትምህርት ወድቋል ማለት ይቻላል።

በዚህ ረገድ ትምህርት በሚባለው ልክ አልወደቀም ሊያስብሉ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ምክንያቱም ዜጎች የመማርና ራሳቸውን የማብቃት፣ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት የማግኘት፣ ራሳቸውንም ለሥራ የማዘጋጀት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ስለዚህ እስከአሁን ካለው ሁኔታ አኳያ በትምህርት ሙሉ በሙሉ ወድቀናል ለማለት አይቻልም።

ይህ ሲባል ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም። ክፍተቶቹ ደግሞ ከሥርዓተ ትምህርቱ ብቻ የመነጩ አይደሉም። ይልቁንም ከአተገባበር የሚመነጩ ክፍተቶች ናቸው። እስከአሁንም ድረስ የአልተፈታ የትምህርት አመራር ክፍተት አለ። ምክንያቱም የትምህርት አመራር በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ለፖለቲካዊ አስተዳደሩ ነው። ሙያው ላይ አተኩሮ የሚሠራ አመራር (ኢንስትራክሽናል ሊደርሺፕ) አልተተገበረም።

እንደ ዶክተር ፍርዲሳ ገለጻ፤ ጥራት አመራር ይጠይቃል። በየደረጃው (ከትምህርት ቤት እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት) ያለው መሪ ጥራትን ከአልመራ ለጉዳዩ ማንም ትኩረት አይሰጠውም። ሥራው ሪፖርት ብቻ ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ ለትምህርት ጥራት ችግር መፈጠር አንዱና ትልቁ ክፍተት እዚህ ላይ ነው። በምርምር እንደታየውም 85 ከመቶው የአመራሩ ጊዜ እሳት በማጥፋት ላይ ነው የሚባክነው። ስብሰባዎች ላይ፣ ሪፖርቶች ላይ፣ ዕቅዶች ላይ ነው የሚያተኩረው እንጂ ጥራትን መምራት ላይ አይደ ለም።

ኢንስትራክሽናል ሊደርሺፕ ሲባል፤ በትምህርት ይዘቶች ላይ ዕውቀት ያለው፣ሐሳብና አስተያየት የሚሰጥ፤ ድጋፍ የሚሰጥ፣ ስሕተት ካለም የሚተችና የሚያርም ማለት ነው። ምክንያቱም የትምህርቱ ሂደት ድጋፍ የሚሰጥ፤ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ፤ ሂደትን የሚገመግምና ገንቢ ኂስ የሚሰጥ መሪ ይፈልጋል።

ይኽ ባለመሆኑ ነው አሁን ሆነ እየተባለው የትምህርት ጥራት ችግር የተፈጠረው፤ የትምህርት ውድቀትም አለ ለማለት ዕድል የፈጠረው። እንዲህ ዓይነት መሪ ቢኖር ኖሮ ችግሮቹን በሂደት እያየና እየገመገመ አስፈላጊውን የእርምትና ማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ስለሚያስተካክል ጥራቱ በዚህ መልኩ አይወርድም፤ አደጋውም አይፈጠርም ነበር።

ነገር ግን አሁን ያለበት ሁኔታ ሲታይ፣ ሰዎችን ከማብቃት፣ በገበያው ላይ ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጠሩ ከማብቃት፣ የራሳቸውን የፈጠራ ዐቅም እንዲያዳብሩ ከማድረግ አኳያ ሙሉ በሙሉ ውጤት የለውም የሚባል አይደለም። በተወሰነ ውጤትም አምጥቷል። ለምሳሌ፣ በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች መፍጠር ተችሏል። ድሮን እስከመፍጠር ደረጃ የደረሰ ወጣት ትውልድን ማፍራት ተችሏል። ሆኖም ግን ጥራትን በዓለም መመዘኛ መሠረት ከታየ ተጎድቷል።

የውድቀቱ ተጽዕኖ እና ተጠያቂነት

የትምህርት ጥራት ችግር ላይ ሲወድቅ እና ትውልድ ከትምህርት ገበታ ማግኘት የሚገባውን ነገር ማግኘት ሳይችል ሲቀር፤ በምላሹ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የሚፈጠር ማኅበራዊም፣ ኢኮኖሚያዊም፣ ፖለቲካዊም፣ አጠቃላይ ከሰላምና ደኅንነት እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ከፍ ያለ ዋጋን የሚያስከፍል ነው። በኢትዮጵያም በትምህርት ጥራት ችግር ምክንያት ይኽን ያህል ተብሎ የሚገለጽ መጠን ጉዳትና ተጽዕኖ አይጠቀስ እንጂ፤ በኢኮኖሚውም፣ በማኅበራዊ መስተጋብሩም፣ በሰላምና ደኅንነቱም፣ በፖለቲካውም፣… ዘርፎች ለሚታዩ ችግሮች አንዱና ቀዳሚው ምክንያት ይኸው የትምህርት ጥራት ችግር ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሰነዶች የተመላከተውም ይሄው እውነታ ነው። ምክንያቱም ያላወቀ ተማሪ በተሰማራበት መስክ ውጤታማ አይሆንም፤ ክህሎት ያልጨበጠ ተማሪ የፈጠራ ዐቅምም ተነሣሽነትም አይኖረውም፤ በአመለካከቱ መልካም ሰብእናን የአልተላበሰ ትውልድ ለሀገሩም ለሕዝቡም የሚሆን የሞራል ልዕልናን ገንዘቡ አያደርግም። የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ሕዝብን እንደ ሕዝብ፤ አገርንም እንደ አገር ለፍቶ መና የሚያደርግ ነው።

ይኽ እንዲሆን ደግሞ የትምህርት ዘርፉን የሚመራው አካል ሐላፊነቱ የጎላ ሊሆን ቢችልም፤ በርካታ አካላት ግን ድርሻ አላቸው። ወላጆች፣ የየአከባቢው ማኅበረሰቦች፣ ቤተ እምነቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን፣ ተማሪዎች፣… ሁሉም ድርሻቸው ይለያይ እንጂ ለችግሩ መፈጠር፤ ለአገራዊም ሆነ ማኅበረሰባዊ ተጽዕኖው መከሠት የየራሳቸው አበርክቶም፣ ተጠያቂነትም አለባቸው።

“አሁን ላይ የትምህርት ጥራት በመውረዱ፤ ችግሩም ወደ ትምህርት ውድቀት እያመራ በመሄዱ ምክንያት አገርም ሆነች ሕዝብ ከትምህርቱ መስክ ማግኘት የአለባቸውን ጥቅም አግኝተዋል ማለት አይቻልም፤” የሚሉት ዶክተር ፍርዲሳ፤ ምናልባት የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት እና የተማረ የሰው ኃይል በመፍጠር/በማብቃት ረገድ ጥሩ ነገር ተገኝቷል ለማለት ቢያስችልም፤ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ከትምህርት ዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ከማግኘት አኳያ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ዶክተር ፍርዲሳ ገለጻ፤ በአለፉት ዓመታት የትምህርት ዘርፉ ዕውቀትን፣ ክህሎትንና አመለካከትን በተማሪዎች ከማሥረጽ አኳያ የሚጠበቀውን ያህል አልሄደም። ለምሳሌ፣ ቀጣሪ ድርጅቶች ተመራቂ ተማሪዎችን መልምለው ያሠለጥናሉ። ይኽን የሚያደርጉትም በትምህርት ተቋማት የሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት የሥራ ቦታው ከሚፈልገው ዕውቀትና ክህሎት ጋር የሚጣጣም በአለመሆኑ ነው።

ይኼ ደግሞ ባለድርሻ አካላት ተናብበው አገር ከዘርፉ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ምን ትፈልጋለች ብሎ የመምራትም፣ የመሥራትም ባህሉ ያለመዳበሩ ማሳያ ነው። ከዚህ ባሻገር ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ሥራ አይገቡም። ይኽም ስናስተምር ለምን እንደምናስተምር ዐውቀን ስለማናስተምር ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ የግብር ከፋዩ ገንዘብ ነው የሚባክነው፤ የአገር ኢኮኖሚ ነው የሚጎዳው፤ ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው የሚናጉት።

ለዚህ የአንድና ሁለት አካላት ብቻ ሐላፊነትን ያለመወጣት ችግር አይደለም። በዚህ ረገድ እንደ አገርም እንደ አንድ ዜጋም ሁሉም ተጠያቂነት አለበት። ምክንያቱም በአመራሩ (ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከላይኛው ድረስ) ክፍተት አለ። ቁልፍ ክፍተትና ችግሮችን ለይቶ ከማረም ይልቅ፤ በስብሰባ፣ በዕቅድና ሪፖርት ላይ ነው ጊዜውን የሚያሳልፈው። የትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ በዛው ልክ ክፍተት ያለባቸው ናቸው።

ይዘቱም ተመሳሳይ ክፍተት አለው። በመማር ማስተማሩም ሂደት የተማሪ ሰዓት ይባክናል። የተማሪዎችም ለትምህርት በልኩ ትኩረት የአለመስጠት ችግር አለ። ሆኖም ተማሪ ድጋፍና ማበረታቻ ያስፈልገዋል። ተምሮ ብቁና ምርታማ ዜጋ የመሆን ተነሣሽነቱ ሊፈጠርለት፤ ለዚህ የሚሆን ከባቢም ሊመቻችለት ይገባል። መምህራንን ያለማብቃት ጉዳይም አለ። መምህራን ላይ ከሕይወታቸው ጋር የተገናኘ፤ ከራእይያቸው ጋር የተገናኘ፤ ከተነሣሽነት /ሞቲቬሽን/ ጋር የተገናኘ፤… በአለመሠራቱ የሚጠበቅባቸውን ያህል ምሳሌ/ ሞዴል/ ሆነው እንዳይገኙ ያደርጋል።

በጥቅሉ አካሄዱ ከሕገ መንግሥቱ አንጻር የሰው ኃይሉን ስናስተምር ከዚህ ተነሥተን እነዚህ እንደርሳለን፤ እናደርሳለንም ተብሎ ሊተገበር ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የፈተና ውጤት የተማሪዎች ውድቀት ሊመስል ይችላል። ሆኖም የተማሪው ውድቀት ብቻ አይደለም፤ ተማሪ የወደቀው በሁሉም አካል ውድቀት ነው። በፈተና 97 በመቶው ተማሪ ወደቀ ሲባል፤ ውድቀቱ የተማሪው ብቻ ነው ሊባል አይገባውም። አጠቃላይ ውድቀቱም፣ ተጠያቂነቱም የጋራ ነው።

አቶ ታዬም፣ በዶክተር ፍርዲሳ ሐሳብ ይስማማሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፈተና አንዱ የችግሮች መመልከቻ መንገድ እንጂ ብቸኛ የጥራት ጉድለትን መለያ መሣሪያ አይደለም። በመሆኑም በፈተና የተገለጠው ችግር፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲፈተሽ ታይቷል። ውጤቱም የሂደቱ ፍሬ መሆኑን መመልከት ተችሏል። ሆኖም ችግሩ በአንድ ጀንበር የመጣ እንደአልሆነ ሁሉ በአንድ ጀንበር ሊፈታ አይችልም፤ ሂደት የሚጠይቅ፣ ሥራና ጊዜም የሚፈልግ ነው።

የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተማሪ የመማር ፍላጎት ወሳኝ ነው። ለመማር ዝግጁ የሆነ ተማሪ በሌለበት ይኼን ማሰብ አይቻልም። ይኽንን ዓይነት ተማሪ ለመፍጠር ደግሞ ወላጆች፣ የየአከባቢው ማኅበረሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት አመራሩ፣… ድርሻው የጎላ ነው። ወላጅና የየአከባቢው ማኅበረሰብ ለትምህርት ፍላጎት ያለው ተማሪን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ፤ ትምህርት ቤቶችና የትምህርት አመራሩ ደግሞ ለመማር የተዘጋጀውን ተማሪ በፍላጎቱ ልክ የሆነ ዝግጅት አድርገው ሊያስተምሩት፤ በዕውቀት፣ ክህሎትናአመለካከትም ሊያበቁት ይገባል። የእነዚህ አካላት ሥራ ድምር ውጤት የሚመዘነው ደግሞ በፈተና እንደመሆኑ፤ በፈተናው የታየው ውድቀትም የተማሪውን ችግር ብቻ ሳይሆን፤ የእነዚህን ሁሉ አካላት ችግር አጋልጦ የአሳየ ነው።

በመሆኑም ሂደቱ በዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የበቃ ሰው ማፍራት እንዳይቻል አድርጓል። በዚህም ሀገሩንም፣ ራሱንም በጥቅሉ ሁሉን ነገር ለመለወጥ የሚቸገር ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው። ይሄ ደግሞ አንድን ሴክተር ብቻ የሚጎዳ አይደለም። የጤናውን ዘርፍ ይጎዳል፤ የግንባታውን ዘርፍ ይጎዳል፤ የፍትሕን ዘርፍ ጎዳል። ስለዚህ ትምህርት ላይ በጋራ ባለመሠራቱ እንደ አገርም፣ እንደ ሕዝብም ብዙ ዋጋ እየተከፈለበት ነው። በመሆኑም ለትምህርት ጥራት ችግር መፈጠርም፤ ጥራቱ በመውደቁ ምክንያትም እንደ አገርም፣ እንደ ማኅበረሰብም ለተፈጠረው ችግር ሁሉም ድርሻ አለው።

ከውድቀቱ እንዲነሣ ምን እየተሠራ ነው?

በአንድ አገር ትምህርት የሚጠበቅበትን ሚና የሚወጣው፤ በጥራትም፣ በተደራሽነትና ፍትሐዊነትም በኩል የተመጣጠነ ሥራ መሥራት ሲቻል ነው። የእስከ አሁኑ ሂደት ደግሞ ይኼ ባለመሆኑ ምክንያት በተደራሽነት ላይ ውጤት ቢታይም፤ ከጥራት አኳያ የተፈጠረው ስብራት ብዙ ዋጋ የአስከፈለ ስለመሆኑ ከሰነድም፣ ከዘርፉ ባለድርሻዎችም፣ ከሪፖርትም መረዳት ተችሏል።

በመሆኑም ችግሩን እና አደጋውን ከመገንዘብ ባሻገርም፤ ለችግሩ መሻገሪያ፣ ከአደጋውም መውጫ የሚሆን መፍትሔን ማቅረብ፤ በመፍትሔው መነሻነትም በዕቅድ ታግዞ ወደ ተግባር መግባት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ የትምህርት ዘርፉ የሚመራበት አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የተቀረጸ ሲሆን፤ ይሄ ፖሊሲ የሚመራበትም፣ ውጤቱ የሚገመገምበትም አገራዊ የዐሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለአለፉት ሦስት ዓመታት እየተተገበረ ይገኛል።

ለምሳሌ፣ ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም. እንዲተገበር በተዘጋጀው የዐሥር ዓመት የልማት ዕቅድ፤ ከላይ የተጠቀሱትን የትምህርቱ ዘርፍ ክፍተቶችን በአገናዘበ መልኩ ትምህርት አንዱ ቁልፍ የትኩረት መስክ ተደርጎ ተወስዷል። በዚህም የትምህርት ፍትሐዊ ተደራሽነትን እንዲሁም ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ ከዕቅዱ ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በተለይ ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የማስተማር ሥነ ዘዴው፣ የማስተማሪያና የመማሪያ ቁሳቁሶችና የግምገማ ሥርዓቶቹ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆን ማድረግን ታላሚ አድርጓል። ጥያቄው ታዲያ ይኼንን ዕቅድ ከመተግበር እና የወደቀውት የትምህርት ሂደት ከማንሣት አኳያ ምን ያህል ተጉዘናል? የሚለው ነው።

አሁን ላይ በትምህርት አሰጣጡ ሂደት መገኘት የሚገባቸው የዕውቀት፣ የክህሎትና የአመለካከት ጉዳዮች ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ፍርዲሳ፤ ለዚህም የተማሪ ጊዜ መባከን፣ የመደገፍ ዐቅም አለመኖር፣ አመራሩ ለሪፖርት እንጂ ለይዘት ትኩረት አለመስጠት፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴው እና ሌሎችም ምክንያቶች ችግሩ የተፈጠረ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ዶክተር ፍርዲሳ ገለጻ፤ የትምህርት ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በተለያዩ ፈተናዎች የተማሪው መውደቅም የሁሉም ባለድርሻ ውድቀት ውጤት ነው። በመሆኑም ከዚህ ችግር ለመውጣት መሥራት ይገባል። ይኼን ለማድረግ ግን ትምህርት የአንድ ግለሰብ ወይንም የተወሰነ ቡድን ወይም ፓርቲ ብቻ አለመሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም መሥራት ይኖርበታል።

በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ሥራ የትምህርት አስተዳደሩን ማስተካከል ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ለትውልዱ አሳቢ፣ ተቆርቋሪ፣ ዕውቀትና ክህሎት ያለው፤ አመለካከቱ ሰፋ ያለ አመራር መመደብ አለበት። ምክንያቱም በዚህ ቦታ ትውልድን እየተገነባ እንደመሆኑ በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ ሊሰየም የሚገባው አመራር ሊኖር አያስፈልግም።

ከስምንት ዓመት በፊት እርሳቸውም በነበሩበት ከጂ.አይ.ዜድ ጋር በመሆን ብዙ ሥራ መሠራቱን የጠቆሙት ዶክተር ፍርዲሳ፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ተብሎ መጀመሩን፤ ይኼም አዲስ ነገር ይዞ የመጣ እና ቀደም ሲል በሰዎች ልብና ሐሳብ ውስጥ የነበረውን ነገር ለማካተት የሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰነዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርት በሦስት ዓመት መሆን የለበትም፤ የመጀመሪያ ዓመት (ፍረሽማን) ኮርስ መቅረት የለበትም፤ ቢያንስ አራት ዓመት መሆን አለበት፤ የሚለውን ለመመለስ ማስቻሉን በምሳሌነት አንሥተዋል። ሆኖም ሁሉንም ነገር በትክክል ለመሥራት መሞከር እና ትክክለኛውን ሥራ በትክክል መሥራት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል፤ ሲሉ አሁንም በአተገባበር በኩል ያሉክፍተቶች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።

አሁን እየተሰጡ ያሉ ፈተናዎች መልካም ቢሆኑም፤ ከፈተና በፊት መሠራት የሚገባቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ለዚህ በማሳያ በማንሣት፤ በዚህም በትምህርት ቤት፣ በመምህራን ላይ፣ ጊዜ ላይ፣ የማስተማር ሥነ ዘዴ (ሜተዶሎጂ) ላይ መሠራት እንዳለበት አብራርተዋል። በዚህ ረገድ አሁን ላይ ጥረቶችና መነሣሣቶች አሉ፤ ነገር ግን ትክክለኛ ሥራን በትክክለኛ መንገድ ነው እየተሠራ ያለው? ወይስ ማንኛውንም ሥራ ነው በትክክል ለመሥራት እየሞከርን ያለነው? የሚለው ትኩረት ሊሰጠውና ተፈትሾ ሊመለስ ይገባዋል፤ ብለዋል።

አቶ ታዬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ 12ኛ ክፍል ተፈትነው የወደቁ ተማሪዎች በ2012 ዓ.ም. ላይ ዘጠነኛ ክፍል የነበሩ፤ በኮሮና ምክንያት አንድ ሴሚስተር ተምረው ወደሚቀጥለው ክፍል አለፉ ናቸው። በወቅቱ የማካካሻ ትምህርት ይሰጥ የተባለ ቢሆንም፤ ምን ያህሉ ተሰጥቷል? የሚለው ግን የራሱ ችግር የነበረበት፤ ሁሉም ራሱን ፈትሾ የሚመልሰው ነው። በ2013 ዓ.ም. ም ቢሆን፤ በፈረቃ በሳምንት ሦስት ቀን እንዲማሩ ሆነው ያለፉ ናቸው። ይሄ ከክፍለ ጊዜና መሰል የትምህርት ሰዓትን ከመሸራረፍ ባሻገር ያለ ጉዳይ ነው። ስለዚህ እነዚህ ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን ሳያገኙ ያለፉ ናቸው።

ሌለው ችግር መምህርነት ተወድዶና ተከብሮ የሚገባበት ሙያ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ያለው ክፍተት ለትምህርት ጥራት መጓደል ተጠቃሽ ነው። ምክንያቱም ሁኔታው በመምህራን ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ስለአለ እና የተሻሉ ሰዎች እንዳይገቡበት ስለሚያደርግም ጭምር ነው። የኢንስትራክሽናል ሊደርሺፕ ጉዳይ ደግሞ፣ ከመምህራን ምልመላ ይጀምራል። እነዚህ መምህራን እንዴትና ከየት ተመልምለው መጡ? የሚለው አንዱ ጉዳይ ነው። ሥልጠናውና ስምሪቱም ይሄንኑ የሚገድብ ነው።

የፖለቲካ ጉዳይ አስፈጻሚ በሚመስል መልኩ ተመልምሎና ሠልጥኖ ስምሪት የሚሰጠው ከሆነ፤ ይሄ አካል ኢንስትራክሽናል ሊደርሺፕ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም በምልመላ፣ በሥልጠና እና ስምሪት ላይ ያለው ክፍተት ተለይቶ እየተሠራበት ይገኛል። ይኼም አመራሩ የመማር ማስተማሩን ሥራ ብቻ ይዞ እንዲሄድ ያስችለዋል። ይሄ ሲሆን ደግሞ የዕውቀትም፣ የክህሎትም፣ የአመለካከትም ውጤት የሚገኝ ይሆናል።

ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤት ሊኖር የሚገባው የክትትልና ድጋፍ ሥርዓትም ችግር የነበረበት ነው። አሁን ይኼንን ለመቀየርና ችግሩን ለማረምም የክትትልና ድጋፍ ሥርዓቱ የሚመራበት አሠራር መመሪያ እየተዘጋጀ ሲሆን፤ በቅርቡም ወደሥራ ይገባል። ምክንያቱም ጥሩ ጥሩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደታች የወረዱ ቢሆንም፤ አብዛኛው ችግር ከአተገባበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ እንደመሆኑ ይኼን ለመተግበር የሚሆን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትን መላበስ ይጠይቃል።

እንደ አቶ ታዬ ማብራሪያ፤ የትምህርት ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን ጥራትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተለይቷል። ለዚህም ከቅድመ አንደኛ ትምህርት ጀምሮ ጥራትን ማዕከል ያደረገ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ለምሳሌ፣ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን ከጤና፣ ከሴቶችና ሕፃናት ጋር በመሆን የሚሠራበት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። ይኼም ሕፃናቱ በጤናም፣ በማኅበራዊ መስተጋብርም፣ በተግባቦትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ብቁ ሆነው እንዲያድጉም ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው በአካልም በአእምሮም እንዲጎለብቱ ያስችላቸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተሳትፎን ከማሳደግም ሆነ፣ በሂደቱ የሚፈጠር የትምህርት ጥራት ችግርን ከመፍታት አኳያ አንድ ሕፃን ቢያንስ የሁለት ዓመት፣ ከተቻለም የሦስት ዓመት ትምህርት ማግኘት አለበት፤ በሚል መንግሥት ሐላፊነትን ወስዶ እየሠራ ይገኛል።

ከዚህ በተጓዳኝ የትምህርት ፕሮግራም ክለሳ ተደርጓል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ከማድረግ በተጓዳኝ፤ የሚገባቸውን ትምህርት እንዲያገኙ አስፈላጊው ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ለዚህም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በዚህ በኩል ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በክረምቱ ብቻ 12 ቢሊዬን ብር ኅብረተሰቡ አዋጥቶ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል፤ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተዋል።

የትምህርት ቤቶች ማሻሻል ሥራው ደግሞ አራት መሠረታዊ ነገሮችን ይዞ የሚተገበር ነው። አንደኛው፣ አመራሩ ኢንስትራክሽናል አመራር እንዲሆን ማስቻል ነው። መምህሩም ርእሰ መምህሩንም ለትምህርት ሥራው በአግባቡ መጠቀም፤ ሁለተኛው፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲመራና እንዲከወን ማስቻል፤ ሦስተኛው፣ ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢን የመፍጠር (ምገባ ማከናወንን ጨምሮ ተማሪዎችን የሚያውኩ በትምህርት ቤቶችና ከባቢያቸው እንዳይኖር ማስቻል)፤ አራተኛው፣ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ (ወላጆች ገንዘብ አዋጥቶ ትምህርት ቤት ከመገንባት ባሻገር ስለ ልጆቻቸው ውሎና የትምህትር ቤት ቆይታ ግድ የሚላቸው እንዲሆኑ ማስቻል) ናቸው።

በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው። ከተሠራ ደግሞ ለውጥ የማይመጣበት ምክንያት የለም። ሠርተውም ለውጥ ያመጡ ትምህርት ቤቶች አሉ። በሪሚዲያል መርሐ ግብርም ራሳቸውን አዘጋጅተውና አብቅተው ጥሩ የፈተና ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ተማሪዎችም አሉ። ትልቁ ጉዳይ ሥራው የእኔም ነው የሚል የባለቤትነት መንፈስ እና ለሥራው ትልቅ ተነሳሽነትና ቁርጠኛነት ይጠይቃል።

ሆኖም አሁንም ድረስ በአንድኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት የታየው ውጤት በሁለተኛ ደረጃ እና በቅድመ አንደኛ ትምህርት ባለመምጣቱ የሁለተኛ ደረጃ ከ44 በመቶ፤ የቅድመ አንደኛም ከ39 በመቶ የዘለለ ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም። በዚህም የሁለተኛ ደረጃ እና የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ መመልከት ተችሏል።

በአጠቃላይም ተገቢውን ሰው በተገቢው ቦታ አስቀምጦ ውጤት እንዲመጣ ከማስቻል አኳያ የሁሉም አካል ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ተምሮና ተመርቆ መሥራት የማይችል ተማሪን መፍጠር ለማኅበረሰብም፣ ለአገርም ተጨማሪ ሸክም መፍጠር ማለት ነው። አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲም ይኼንን ችግር በሚቀርፍ መልኩ የተቀረጸና እየተተገበረ ያለ ነው።

የመውጫ ሐሳብና መልእክት

ትምህርት የአንድ አገር የዕድገት ብቻ ሳይሆን የሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት መሆኑ የታመነ ነው። በኢትዮጵያም ትምህርት ይኼንን ሚናውን እንዲወጣ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ላይ የተገኘ ውጤት ቢኖርም፤ በጥራት አኳያ ግን እጅጉን ችግር የታየበት ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል፤ ይኼው እውነትም በተለያየ አግባብ ተረጋግጧል።

በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሪፖርቶችም ሆኑ በጥናት የተደገፉ ሰነዶች እንደሚያሳዩትም፤ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትም እያሽቆለቆለ ሲሆን፣ በዚህም በየደረጃው ያለው አብዛኛው ተማሪ የትምህርት ውጤቱ ከ50 በመቶ በታች ነው። ሌላው ቀርቶ የከፍተኛ ትምህርትን የተቀላቀሉ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ከመግቢያ ፈተናው ዝቅተኛውን የመግቢያ ነጥብ (50 በመቶ) በታች የአገኙ ናቸው። ይኼ ደግሞችግሩ ከመሰረቱ የተበላሸ እና ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ አመላካች ነው።

ለምሳሌ፣ በ2002 ዓ.ም. በሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ በተካኼደ የዝቅተኛ ክፍል ደረጃ የንባብ ዳሰሳ ጥናት፤ በመጀመሪያ ደረጃ አንደኛ ሳይክል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በቀጣይ ክፍሎች በአግባቡ ለመማር የሚያስችሏቸውን መሠረታዊ ክህሎቶች ያላዳበሩ መሆናቸው ታይቷል። በወቅቱም፣ ሁለተኛ ክፍል ከሚማሩት ተማሪዎች 34 በመቶ ለደረጃው ከተዘጋጀው ምንባብ ውስጥ አንድም ቃል ማንበብ አልቻሉም፤ 48 በመቶው ደግሞ ከተዘጋጀው አንብቦ የመረዳት ፈተና አንዱንም መመለስ አልቻሉም።

በተመሳሳይ፣ በ2006 ዓ.ም. በተደረገው ዳሰሳ በሒሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ ትምህርቶች አማካይ ውጤታቸው 50 በመቶ የደረሰ ዐሥረኛ ክፍል ተማሪዎች ቁጥር 23 በመቶ ነው። ይሄም ተማሪዎች በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃዎች መሠረታዊ ክህሎቶች ከአላዳበሩ፣ በተከታታይ ደረጃዎች ባሉት ክፍሎች በሚማሯቸው የትምህርት ዓይነቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አረጋገጠ ሆኗል። በመሆኑም ይኼንን መቀየር እና ትምህርት በአገር ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ መሥራት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው።

ዶክተር ፍርዲሳ ይኼንን በተመለከተ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራት ወረደ፤ ትምህርትም ችግር ውስጥ ገባ ማለት፤ ትውልድ ወደቀ፤ አገርም ችግር ውስጥ ገባች፤ ማለት ነው። ነገ አመራሩን የሚተካ፤ አገር የሚረከብ ትውልድ መፍጠር ከአልተቻለ ደግሞ አገር አትቀጥልም። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ተጠያቂነት አለበት። አሁን የታየው የትምህርት ጥራት ውድቀትም የማይቀረፍ፣ ሙሉ ለሙሉም ጨለማ ነው ብሎ መውሰድ አይገባም። ከዚህ ችግር መውጫ ብዙ አስቻይ ሁኔታዎች እና መልካም ዕድሎች አሉ። ለምሳሌ፣ መንግሥት ትምህርት ላይ ኢንቨስት ያደርጋል። ትኩረት ሰጥቶም መሥራት ጀምሯል። ማገዝ ለሚፈልጉም በሩ ክፍት ነው።

እናም ሁሉም ዜጋ ትምህርት የጋራ ሥራን የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት አለበት። ተባብሮ አለመሥራት ለውድቀት እንደሚዳርግ ሁሉ፤ ተባብሮ መሥራትም ከውድቀት መነሻ ዐቅም እንደሚፈጥር መገንዘብ ይገባል። ለምሳሌ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በትምህርት ጉዳይ ላይ ገለልተኛነት ሊኖራቸው አይገባም። ምክንያቱም ትምህርት ትውልድ መፍጠሪያ ዐቅም ነው። ትውልድ መፍጠር ደግሞ የእኔ ነው፤ የአንተ ነው፤ የሚባል አይደለም። ስለዚህ በትምህርት ጉዳይ አብረው መሥራት ይኖርባቸዋል። ተማሪ የሚኮርጀው በአግባቡ የሚገባውን ነገር ማግኘት ባለመቻሉ ስለሆነ፣ በራሱ የሚተማመንና ስርቆትን የሚጠየፍ ተማሪ፤ ለራሱም ለሥራውም የሚታመን ማኅበረሰብ መፍጠር ከሁሉም ይጠበቃል።

ምክንያቱም ዓለም በዕውቀት፣ በክህሎትና አመለካከት በኩል የደረሰችበት ደረጃ፣ ጊዜው የውድድር እንዲሆን አድርጎታል። ይሄ ትውልድ ደግሞ በዚህ ውድድር ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ከዓለም ጋር መዋሐድ አለበት። ስለዚህ ወጣቶችን በጥቅሉም ትውልዱን የዚህ ዕድል ተቋዳሽ እንዲሆነ መሥራት ይገባል።

ከዚህ በተጓዳኝ ተማሪ ሊማርም ሆነ የተማረውን ዐውቆ ሊተገብር የሚችለው፣ ሰላም ሲኖር እንደመሆኑ ሰላሙ ላይ መሥራት ይገባል። እነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ደግሞ የትውልዱ የነገ ዕጣ ፈንታ ላይ መወሰን መሆኑን ዐውቆ ሁሉም ሊረባረብ ይገባዋል።

አቶ ታዬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ትምህርት የአገር ዕድገት መሠረት እንዲሆን፣ አገር ያለችበትን ቦታ ማወቅን፣ የት ለመድረስ ዐቅዳ እየሠራች እንደሆነም መረዳትን ይጠይቃል። እዚህ ለመድረስም የተማረ የሰው ኃይል፣ የተማረ ማኅበረሰብ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል። ለምሳሌ፣ በመንግሥት ተቋማት ውጤት ለማምጣት የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፤ በንግድ ውጤታማ ለመሆንም ትምህርት ያስፈልጋል፤ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዕውቀት ያስፈልጋል፤ የሰከነ ፖለቲካ ለማራመድም ከፍ ያለ ዕውቀትና አመለካከት ይጠይቃል፤ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅም የሥነ ምግባር ከፍታን ይጠይቃል።

በዚህ መልኩ ከታየም የትምህርት ተጽዕኖ የሴክተር ድንበር የለውም። ችግሩ ግን እነዚህ ተቋማት (ግብርናውም፣ ንግዱም፣ ደኅንነቱም፣ ባንኩም፣…) ከትምህርት የሚፈልገውን ያህል ለትምህርት ጥራት መሻሻል እየሠሩ አለመሆናቸው ነው። ለምሳሌ፣ ባንኮች አሠራሮቻቸውን ለማሳለጥ ደንበኞቻቸው ሞባይል ባንኪንግና ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ይገፋፋሉ። ሆኖም ይሄን መጠቀም የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሚናቸው ይሄ ነው የሚባል አይደለም። በመሆኑም እያንዳንዱ አካል ከትምህርት ሴክተሩ የተሻለ ሰው መጠበቅን እንጂ የተሻለ ሰው በማፍራት ሂደቱ ላይ ሚናው እምብዛም አይደለም። በመሆኑም ይኼ መታረም እና ሁሉም ለትምህርት ጥራት መሻሻል የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

ከዚህ ባሻገር አንድ ልጅ ብዙ ቦታ ይቀረጻል። ይኼም ከቤተሰብ ይጀምራል፤ በማኅበረሰብ ይገነባል፤ በእምነት ተቋማት ይታነጻል፤ በትምህርት ቤት ይቀረጻል። እነዚህ የሚሰጡት መልካም ነገር ካለ መልካም ፍሬን ይዘራል፤ ከአልሆነም ውጤቱ በተቃራኒው ይሆናል። ወጣቶች መልካም ሰብዕናንም፣ መጥፎ ሰውነትንም የሚያገኙት ከእነዚሁ አካላት ነው። ስለዚህ ሁሉም በዚሁ ቅኝት የትውልዱን ሰብእና በዕውቀትም፣ በክህሎትም፣ በአመለካከትም ቀርጸው ማነጽ ይጠበቅባቸዋል።

እንደ አቶ ታዬ ማብራሪያ የትምህርት ጥራት ሂደት ነው። የትምህርት ጥራት ችግር አንጻራዊ ነው እንጂ በአደጉት ሀገራትም አለ። ቁርጠኛነቱ እና መተባበሩም ካለ በአጭር ጊዜ ከችግሩ መውጣት ይቻላል። ከከፋ የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ የወጡ ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ከሠሩ ከችግሩ መውጣት እንደሚቻል ነው። በኢትዮጵያም ከችግሩ ለመውጣት የተጀማመሩ ሥራዎችን አጠንክሮ መሄድ ያስፈልጋል።

ለዚህ የሚሆን ተነሣሽነትና ቁርጠኛነትን ለመያዝ ደግሞ፣ አሁን ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችም ሆኑ አገራዊ ችግሮቻችን የትምህርቱ ዘርፍ ውድቀት ውጤቶች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም የትምህርት ውድቀት የማኅበረሰብም፣ የአገርም ውድቀት ነው። ለምሳሌ፣ አምና ያ ሁሉ ተማሪ ሲወድቅ ሁሉም ቆም ብሎ ወደራሱ ማየት ይገባ ነበር። ይሄ ባለመሆኑ በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ችግር ታየ።

በዚህ ረገድ ተማሪው ድርሻውን ወስዷል። ይኼ ግን የችግሩ ትንሹ ክፍል ነው። አብዛኛው በሌሎች ባለድርሻዎች ላይ የሚወድቅ ሐላፊነት ነው። በተለይ የትምህርት ሴክተሩ በዋናነት ወስዶ ሐላፊነቱን በሚገባ መወጣት ይኖርበታል። በተመሳሳይም ወላጅ፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህሩ፣ የትምህርት አመራሩ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣… ሁሉም የየራሱን ወስዶ መስራት ይኖርበታል።

ምክንያቱም ሀገራት በተማሩ፣ በተመራመሩና ቴክኖሎጂን በፈጠሩ ዜጎቻቸው ነው እየተለወጡና እያደጉ ያሉት። እኛም ይሄንኑ ተገንዝበን ከሠራን እንደምንለወጥ፤ ከአልሠራን አሁን በአለንበት ችግር ቀጥለን ለባሰ ችግር እንደምንዳረግ መረዳት ይገባል። ሁሉም ሐላፊነቱን ወስዶ እንዲሠራ ያይጠበቃል። ያሉንን ብዙ ፀጋዎች ማልማት፣ መጠቀምና መለወጥ የምንችለውም ይኼንን ስናደርግ ነው።

ወንድወሰን ሽመልስ

ዘመን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም

Recommended For You