ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እና ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው በዚሁ መጽሔት ቅፅ 20 ቁጥር 97 ታኅሳስ 2014 ዓ.ም. በ”የኔ ዕይታ” ዓምድ ‹‹ለአገር ችግር መፍቻ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ ተሳትፎ›› በሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ ነው። የጽሑፉ ዓላማ በአገራችን ላይ ችግር በተከሰተ ቁጥር መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ በመተባበር ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አዲስ አለመሆኑን ለማመልከት፣ እንዲሁም አሁን ለተከሰተው ችግር ቀራፊ ፕሮግራሞች ለመጠቆም እንደሆነ ተጠቅሷል። ጸሐፊዎቹ በጽሑፋቸው በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ የችግር መፍቻ ጥረቶች ድርጊትን ከታሪክ አንጻር በማንሳት ከገለጹ በኋላ የዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰብ ለወቅታዊ ችግር መፍቻ ጽንስ ሃሳብ በሚል ሦስት ዓይነት አማራጮች አቅርበዋል። በተለይ ሁለተኛውን አማራጭ ዘርዘር አድርገው አሳይተዋል።
ዘርዘር ብሎ የቀረበው ሁለተኛው አማራጭ የዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰብ ራሱን የቻለ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አዋቅሮ፣ በተለያዩ ዘርፎች ቀጥተኛ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚል ነው። ጽሑፉ አመላካች እንጂ፣ የችግር መፍቻ ፕሮግራም አብሳሪ እንዳልሆነ ጸሐፊዎቹ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። እንደእኔ እይታ ግን ጸሐፊዎቹ ምሁራዊ ትህትና ባለው መልኩ ስለገለጹት እንጂ የችግር መፍቻ ፕሮግራም አብሳሪ ለመሆን ብቁ ነው። ቢያንስ ቢያንስ እንኳን የችግር መፍቻ ፕሮግራም አብሳሪ ለመሆን መነሻ ሊሆን የሚችል ነው። የችግር መፍቻ ፕሮግራም አብሳሪ ከመሆን በተጨማሪ በዚህ ሃሳብ መነሻነት ለአንድ ዓላማ ተሰባስቦ ተግባራዊ ሥራ ላይ መሳተፉ በቡድን ተቧድኖ ከመናቆር የሚያርቅ፤ እንዲሁም በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲታይ የቆየውን ከስነምግባር ያፈነገጡ ተግባራትንም ለማረም ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል ባይ ነኝ።
የወደፊቶቹ አገር መሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ደግሞ በፕሮግራሙ በመሳተፋቸው በሳይንሳዊ ትምህርት አዕምሮአቸውን አጎልብተው ከመውጣት በተጨማሪ የአገራቸውን ችግር፣ ችግሩ ባለበት ሥፍራ ተገኝተው ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆናቸው ከሚያገኙት የመንፈስ እርካታ ጎን ለጎን ሌሎችም ጥቅም ያገኛሉ። አንደኛው በሳይንሳዊ ትምህርት ያጎለበቱትን አዕምሮ ለችግር መፍቻነት ለመጠቀም መድረክ ማግኛና መለማመጃ ሊሆናቸው ይችላል። ሁለተኛው አገራቸው የምትገኝበትን ሁኔታ በአካል በቦታው ሄደው በቅጡ ስለሚረዱ ማንም ወደ ፈለገው አቅጣጫ በቀላሉ አይጎትታቸውም። ሦስተኛ ወጣቶቹ ችግርን ለመቅረፍ ከሌሎች መሰል ወንድማቸውና እህታቸው ጋር ስለሚንቀሳቀሱ የበለጠ ለመተዋወቅ እንዲሁም ለመግባባት የሚያስችል ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከተማሪዎች ውጭ ያሉ ማህበረሰቦች ከዚህ ቀደም በሚከናወኑት ተገቢ ያልሆኑ የተማሪዎች ድርጊቶች ሃፍረት የተሰማቸው፤ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚስተካከል እና ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ግራ የገባቸው፤ በዚህ በተነሳው ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ሲሰባሰቡ ለመመካከርና አንድ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ብዬ አስባለሁ። በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉትን ምሁራን ዝምታን በእጅጉ የሚሰብር እንዲሁም ለመመካከር እና ለተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያነሳሳ ተሳትፎ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም።
ሁለቱ ምሁራን በ1967 ዓ.ም. «የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ» ወቅት ዶክተሩ በዘመቻው ጠቅላይ መምሪያ በጤና ዘርፍ ኃላፊነት፣ ፕሮፌሰሩ የእንዳ ሥላሴ/ትግራይ/ ምድብ ጣቢያ የአስተዳደር ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ፕሮፌሰሩ ከዚህ ዘመቻ በተጨማሪ በ1977 ዓ.ም. ክረምት ላይ ለሁለት ወራት በመንግሥት አስተባባሪነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠራተኞች፣ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በጋምቤላ(በባሮ ግብረ ኃይል)፣ በመተከል(የዓባይ ግብረ ኃይል) የጎጆ ቅለሳ ዘመቻ በተሰማሩበት ጊዜ የዓባይ ግብረ ኃይል ሥራ አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ። በዚህ ተፈጥሮ ያስከተለውን ጉዳት ለመቋቋም በተደረገ ዘመቻ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተሳትፎውን ሲያጠናቅቅ የዓባይ ግብረ ኃይል ዘማቾች ብቻ ሠርተው ያስረከቡት 18,372(አስራ ስምንት ሺህ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት) ጎጆዎች ናቸው። ስለሆነም ጸሐፊዎቹ የዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰብ ተሳትፎ ለአገር ችግር መፍቻነት ሲውል በተግባር ተሳትፈው በመመልከት፣ ልምዳቸውን ተጠቅመው ያቀረቡት ሃሳብ ነው። ይህም በመሆኑ ያነሱትን አማራጮች በተለያዩ ጥናቶች እና ትችቶች በማዳበር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል እላለሁ።
እነዚህ ምሁራን ያነሱት ጽንሰ ሃሳብ በተግባር ከተሞከረ እንዲሁም ጠንካራ ጎን እና ውስንነቶችን በአካል ተገኝተው ከሚያውቁትና ከተገነዘቡት ተነስተው ያቀረቡት ስለሆነ፣ ሌሎችም ቢተቹትና ቢያዳብሩት እንዲሁም ወደ ተግባር ቢገባ አዲስ ጽንሰ ሀሳብ አንስቶ እንደመተግበር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥር አይመስለኝም። ይህ ጽንሰ ሃሳብ ብዙ ድካምና ጥረት ተደርጎባቸው ለአገር እድገት በጣም ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ጥናቶች በሼልፍ ውስጥ ብቻ የመቀመጥ ዕጣ ፈንታ እንደደረሰባቸው፣ ፖሊሲ አመንጪዎችና ቀራጮች እንዲሁም ሥራ አስፈጻሚዎች ሳይመለከቱት ተሸፋፍኖ ሊቀርና ሊቀመጥ አይገባውም።
ምሁራኖቹ ያነሱት ጽንሰ ሀሳብ ለሚመለከታቸው አካላት ሊቀርብና ሊተች ይገባዋል። የደርግ አባል የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ከታናሽ ወንድማቸው ፍስሃ ባይህ የሰሙትን «የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ» ጽንሰ ሃሳብን ለደርግ አባላት ካቀረቡ በኋላ ወደ ተግባር ለመቀየር የፈጀው ጊዜ በወራት የሚቆጠር ነው (“ያልታሰበው፤የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዪ” ከሚል መጽሐፍ የተወሰደ)። የዘመቻው ጽንሰ ሃሳብ በ1966 ዓ.ም. ክረምት ላይ ተጸነሰ። ከዚያም ዘመቻው እንዴት እንደሚካሄድ ምን ዓይነት ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚኖረው እንዲሁም ምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚሳተፍ ተጠና። በመቀጠልም የዘማቾችን ኃላፊነትንና ተግባር የሚጠቁም ኮሚቴ በመስከረም ወር አጋማሽ 1967 ዓ.ም. ተመሠረተ። ጥቅምት 16 ቀን 1967 ዓ.ም. የእድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ጠቅላይ መምሪያ በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራውን በይፋ ጀመረ። ታኅሣሥ 12 ቀን 1967 ዓ.ም. የዘመቻው የክተት በዓል በመላው አገሪቱ ተከበረ። በዚህ ዘመቻ ከአስረኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎችና መምህራን የገጠሩን ሕዝብ ለማስተማር፣ ለማንቃት እና ለማደራጀት «ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
እንደነሆቺ ሚኒ እንደነቼ ኩቬራ
በወንዝ በተራራ ታሪክ ልትሠራ
ሕዝብን ልትመራ» የሚል መዝሙር እየዘመሩ ዳር እስከ ዳር ነቅለው ተንቀሳቅሰዋል።
ስለሆነም ሁለቱ ምሁራን ያነሱት ይህን ዘርዘር ብሎ የቀረበ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ ለወቅታዊ ችግር መፍቻ ጽንሰ ሃሳብ የሚያነብ ማንኛውም ዜጋ ለስትራቴጂ ቀራጮች፣ ለፖሊሲ አመንጪዎች እንዲሁም ለሥራ አስፈጻሚዎች ማመላከት ይገባዋል። የሚመለከታቸው አካላት ደግሞ ጽንሰ ሃሳቡን ወስደው ጥናት ተደርጎ፣ ተተችቶ፣ ዳብሮ ወደ ተግባር እንዲገባ ቢያደርጉ ለአገር የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው እላለሁ።
ስሜነህ ደስታ
ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም