‹‹ውብ አገሬ፣ ውብ አገሬ ፤ ውብ አገሬ፤
በአንቺ እኮ ነው መከበሬ፣ መከበሬ፤
እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፤
እህት ወንድም ቢሞት በአገር ይለቀሳል፤
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል።››
ይህን ዝማሬ ከልጅነት ዘመናችን ጀምረን የምንሰማው ነው፤ አገርን ለመውደድና ከመውደድ ባለፈ ተግሳጽና ምክር ሆኖ አስበነው ላናውቅ እንችላለን እንጂ። ዛሬ ላይ ግን የዘመናችን መንፈስ ከላይ እስከ ታች ያሉ ስንኞች ግሩም ትርጉም እንዲኖራቸው አድርጓል። የአንዲት እናት አገር ወንድማማች ልጆች፣ ዓይንና ናጫ ሆነው ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ለጠብና ለክርክር ተፈላልገዋል። አላውቅህም ተባብለው ለመካካድ ጫፍ በደረሱበት ጊዜ፣ በየቤቱ ጭንቅ ገብቶ መልአከ ሞት በየደጁ ገብቶ ዜጎችን ሲያሰቅቅና ሲያስቃዥ፣ ሳናውቀው እንዳይደርስብን ስንዘምረው የነበረው የአገር ሞት ‹‹ይህ ነው እንዴ? ›› ማስባሉ አይቀርም።
‹‹አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ።››
የሚለውንም የባለቅኔውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ታላቅ ምክር እንደዋዛ አንሰማውም ነበር። ለካ አገር ይሞታል፤ ዛሬ ላይ አገሬ ጣር ላይ ሆና አያድርግብንና መርዶ ቢሆንብንስ ብዬ ከሩቅ ሰማሁት። እንዴት ያማል።
አገሬ መታመሟ አይገርምም። ዘመኗን ሁሉ ሕመም አያጣትም። የሞቷን መርዶ ግን እሰማለሁ ብዬ ፈርቼ አላውቅም ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ በዘግናኝ ሁኔታ በከፍተኛ ጥላቻና ጥቃት ሲጠፋፉ ሳስተውል፤ ሴቶች በአደባባይ ሲደፈሩ፣ ወጣቶች በጅምላ ሲገደሉ፣ ጎልማሶች ሀብት ንብረታቸውን በጠራራ ቀን ሲዘረፉ፣ ለአገር መከታ ከለላ ይሆናሉ ተብለው አደራ የተሰጣቸው ወታደሮች በክህደት አብረው በአንድ ዋሻ ያደሩ ጓዶቻቸውን ሲጨፈጭፉ፣ ለአገር መሪ ቢሆኑ ተብለው ሲጎመዥላቸው የነበሩ ሰዎች በጽንፍ ሀሳብ ተመተው ሲውተረተሩ … ሲታዩ ልብ ያርዳል፤ በእጅጉ ያስፈራል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ውስጥ ፈተናዎች ገጥመዋት ነበር። ኢትዮጵያ በጽኑ ታማ ለሞት ደርሳ የነበረው አውሮፓዊው የፋሺስት ኃይል ዳግም በወረራት በ1928 ወረራ ወቅት ነበር። ነገር ግን በከበሩ አርበኞቿ ተጋድሎ ከሞት ጣር ወጥታ ተፈውሳ አዲስ ራዕይ ሰንቃ ተራምዳ ነበር። የታመመ ሁሉ አይሞትም፤ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ታማለች እንጂ ፈርሳ አታውቅም። የሕመሙ ጊዜ ይረዝም፣ የስቃይ ጥግ ይታይ ይሆናል። የሞተች መስላ የታየችበትም ጊዜ ነበር። ሕያው ሆና ግን ስትመላለስ ሲያዩ ለብዙዎች አስገራሚ የታሪክ ክስትት ሆኖ አልፏል።
የአገር መታመም ብርቅም ድንቅም አይደለም። ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈር… የአገር በሽታ ነው። በዚህ ሁሉ አገራችን በጽኑ ታማ ታውቃለች። ነገር ግን ትውልድ ጨክኖ ሳያስታምማት አልተዋትም፤ ስለዚህም እየተፈወሰች ቀጥላለች። ያለንም እኛ፤ የሞትንም እኛው ነንና።
ዛሬ፣ ዛሬም የመታመሟ ዜና በዘረኝነት ይሰማል፤ በመለያየት ይሰማል፤ በስደት ይሰማል፤ በረሃብ በሰቆቃ ይሰማል። ብዙዎች ቅዥት እንዲሆን የሚሹት መርዶ እንደዋዛ እውን ሲሆንባቸው መድረሻው ይጠፋቸዋል። እጆቻችን ዝለዋል፤ ውዲቷን የተከበረች አገር ልንጥላት የደረስን ይመስላል። አንዳችን በሌላችን ተስፋ የቆረጥን መስለናል። የምንፈልገውን አናውቅም። ከመሻታችን በተቃራኒ እንሮጣለን፤ ከምኞታችን በተጻራሪ እንሠራለን። የምንፈልገው ሰላም ነው፤ ግብራችን ግን ሰላም አይጠራም። የምንሻው ብልጽግና ነው፤ ግብራችን ግን ጉስቁልናን የሚጠራ ነው።
ኢትዮጵያን የሚጎዳት አካልና ሀሳብ ሁሉ እንደ ብርቱ ጉንዳን ገላዋ ላይ ክፉኛ ተጣብቆ ልናላቅቃት ስንሞክር፣ እንዳያደማት እንሰጋለን። ደግሞ እንተወዋለን፤ እየቆየ ይቆነጥጣታል፤ ያሰቃያታል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለሞት ስጋት የጣላትን ጉንዳን ሀሳብና አመለካከት እንዴት እናራግፍ? የሚለው የዜጎች ሁሉ ጭንቅ ነው።
ትውልዳችን መስቀልኛ መንገድ ላይ ነው፤ ከባድ ታሪክ የሚጻፍበት ወቅት ነው። ወይ የክፋት ወይ የመልካምነት ታሪክ ለማስመዝገብ በታሪክ ሚዛን ፊት ቆመናል። የትውልዱ ጥበብ፣ ብቃት፣ የሞራልና የአመለካከት ደረጃ የሚፈተንበት ወሳኝ ጊዜ ነው። የአረጋውያኑ ምክር፣ የወጣቶቻችን ንቃት፣ የሃይማኖተኞች ጸሎት፣ የፖለቲከኞች ታማኝነትና አርቆ አሳቢነት፣ የውጪው ዓለም የወዳጅና የጠላት ሰልፍ በግልጽ የሚታይበት፣ የሚመዘንበት፣ የሚፈተንበት ጊዜ ነው።
አንድ ዕድል በፊታችን ተደቅኗል። እርሱም የታመመች አገራችንን የምንፈውስበት የማይታለፍ አጋጣሚ ነው። የኢትዮጵያ የወቅቱ መንግሥት ለዚህ የሚሆን ብርቱ፣ ውድ እና ታሪካዊ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለ ነው። ኢትዮጵያን ከሞት የሚያድን፣ ከሕመሟ የሚፈውስ ታሪካዊ የምክክር መድረክ ነው። የኢትዮጵያ ፈውስ የሁሉም ዜጋ ፈውስ እንዲሆን ይፈለጋል። የኢትዮጵያ ፈውስ ግማሽ እንዳይሆን፣ አንዱ ብልት ሲድን ሌላው የሚታመም እንዳይሆን አድርጎ የሚፈውስ መድረክ ኢትዮጵያውያን ይሻሉ።
ጋንግሪን ሆኖ ተቆርጦ የሚጣል ብልት እንዳይኖር መትጋት ይገባል። በብዙ ደዌ የተመታች አገር እንደመሆኗ ሁሉም ብልት በአንዴ ይፈወሳል ብለንም ሳንጠብቅ፣ የምንታደምበት ምክክር እንዲሆን ልባውያን የአገር ልጆች እንደሚሹ ይታመናል። መድኃኒትም መወሰድ እንደጀመረ ሕመምን እየቀነሰ ያስኬዳል እንጂ፣ በአንዴ ፈውሶ ታማሚን ከአልጋ ወደ ወንበር እንደማያመጣ ይታወቃል። ማገገሚያ ጊዜ ይፈልጋል። መድኃኒት ኋላ ሊፈውስ ለጊዜው ለምላስ ይመራል። ለጊዜው ሽንፈት የሚመስሉን በኋላ ግን ለሁላችንም ብልቶች መፈወስ ምክንያት የሚሆኑ ስምምነቶች ሊመጡ ይችላሉ። የጎንዮሽ ደዌ እንዳይኖር በጥንቃቄ ሐኪም የሆነውን የውይይት መድረክ ትኩር ብሎ ወደፊትም መያዝ ግድ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግሩበት የሞራል ዝቅጠት ታሪክ የላቸውም፤ ገርና ትሑት ልብ ያላቸው ማኅበረሰቦች መኖሪያ ምድር ባለቤት ናቸው። የደቡብ አፍሪካ መራሩ የአፓርታይድ ሥርዓት በብሔራዊ ምክርና እርቅ ታሪክ ሆኖ አልፏል። የሩዋንዳ ዘግናኝ የዘር ጥላቻና ጭፍጨፋ በብሔራዊ ምክክርና እርቅ ታሪክ ሆኖ አልፏል።
እነዚህ ለምሳሌ የተጠቀሱ ታሪካዊ ክስተቶች ዓይነት ችግር ላይ ያሉ ሌሎች አገራት ባይጠቀሙበት የሞኝነት ደረጃን ከፍ አድርጎ ያሳያል። ብልህ ከውድቀት ይማራል። ምናልባት ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካውያን በእነርሱ ላይ የሆነውን ነገር በሌሎች ተደርጎ ታሪክ ሆኖ ተምረውበት ቢሆን፣ በእነርሱ የደረሰው ባልደረሰባቸው ነበር። እኛ ግን ብርቱ መማሪያ አለን፤ የእስከ ዛሬው ይበቃናል። አገር መፈወስ ያለባት ደም አይታ በመደንገጥ አይደለም። የዜጎቿን ደም በማፍሰስ ደንግጣ የምትነቃ አገር ታሳፍር ይሆናል እንጂ አታስከብርም። መረረም ጣፈጠም ልዩ ልዩ መልክ ባለው የታሪክ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈናል፤ ዛሬና ነገ ግን ከትናንት ልዩ ነው። ዛሬ የእኛ ነው፤ ነገ ደግሞ የልጆቻችን ዓለም ነው። የምክክር መድረካችን ከቻልን ዛሬ እኛ ተጠቃሚ ልንሆንበት፣ ካልሆነም ልጆቻችን ከፍሬው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሰላምና ብልጽግናን ችግኝ የምንተክልበት ሊሆን ይገባል። የብልጥነት፣ የቂም በቀል፣ የተላላኪነት እና የክህደት ቆሻሻዎች እንዳይነኩን እንማማል! የግብዝነትና የፖለቲካ ድራማዎች ማብቂያ ይሁን! የኒዎ ኮሎኒያሊስቶች መጠቀሚያ ከመሆን እንጠበቅ! ራሳችንን እንስበክ፤ ለኢትዮጵያ መፈወስ እንጨክን፤ እንስጥ፣ እንቀበል።
‹‹የጎመን ምንቸት ይውጣ! የገንፎ ምንቸት ይግባ›› እንበል። የብርሃን ተስፋ ችቦ እንለኩስ። ጨለማው ይሽሽ! ልጆቻችን ተስፋ ያድርጉ፤ ለነገም ያቅዱ። ልማቶቻችን ይስፋፉ! ይሰንብቱም። ክቦ ማፍረስ ይብቃ። የሚያተሳስረንን ድልድይ እንገንባ፤ የሚያንጹንን እሴቶች እንዲያብቡ እንከባከብ።
ይህ ሁሉ ግን እውን የሚሆነው ሕግን ለመታደግ መንግሥት ያዘጋጀውን የምክክር መድረክ በጥንቃቄ ተጠቅመን ኢትዮጵያን ስንፈውሳት ነው። አገራችን ከሞተች ወዴት እንደርሳለን። እንደ እስራኤላውያን ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት ያህል ያለአገር ተበትኖ መኖር አይገባም። እንደ ሶማሊያ ሰዎች የምንከበርበትን አገር አፍርሰን በሌሎች አገራት ቪዛና ፓስፖርት ለማኝ መሆን የለብንም። አገራችንን የሽብርተኞች መፈንጫ ማድረግ የለብንም። ሳውዲና ኢራን በደማቸውና በምድራቸው እንደሚዋጉባቸው እንደየመን የውጊያ ሜዳ መሆን የለብንም። አገር ኖሮን ተስፋ ማድረግ ይሻላል።
እንደ ከያኒው ‹‹ሁሉም ጥሩ ይሆናል!›› እንበል፤ ‹‹ዛሬ ዓለም ቢላት ኋላ ቀሪ፣ የመጪው ዘመን ፊት ናት መሪ›› ብለን ማሰብና ለዚያ መሥራት ለሁላችን ያዋጣናል። ችግሮቻችንን ሁሉ ለመፍታት ያለን ብቸኛ ምርጫ መወያየት፤ አሁንም መወያየት ነው። ያልተፈቱ ችግሮችን ማሳደር፣ ከዚያም መወያየት ብልህነት ነው። ኢትዮጵያ ስም አጠራሯ እንዲጠፋ በሚሠሩ እልከኞች ላይ ልንነቃባቸው ይገባል። በማያልቅ ጥያቄ እንዳያናውዙን ምክንያታዊ ሆነን እንራመድ። ጊዜ የለንም፤ ዓለም በፍጥነት እየተራመደ ነው። የምንሠራበትን ጊዜ በጭቅጭቅ በማባከን ራሳችንን ለልመና፣ ለስደት፣ ለጉስቁልና እና ለውርደት አናዘጋጅ። ቸር ይግጠመን።
ቶኩማ ሮባ
ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም