ምን እንጠይቅልዎ?

ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ:- ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት ወደ ቄራ የሚወስደው ባለ ሁለት መስመር መንገድ ዘወትር በመንገደኛ፣ በታክሲ ተሳፋሪ ሰልፈኛ እና በመኪና የተጨናነቀ ነው። አሁን ደግሞ በቅርቡ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ህንጻ አጠገብ አዲስ ለሚሠራው የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማህበር ህንጻ ሲባል አንደኛው የአስፋልት መስመር እስከ እግረኛው መንገድ በብሎኬት ታጥሮ ወደሚሠራው ህንጻ ተካቷል። ከመታጠር በተረፈው አንደኛው የአስፋልት መስመር ሚኒባስ ታክሲዎች ደርበው ወረፋ በመያዝ ተሳፋሪዎችን ይጭናሉ። በቀረው የአስፋልት መንገድ ተሽከርካሪዎችና እግረኞች ተገፋፍተው በጋራ ይንቀሳቀሳሉ። ይህ በመሆኑም በተለይ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት እጅግ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ ስለሚከሰት፣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እንዲሁም ግጭት የሚከሰትበት ቦታ እየሆነ መምጣቱን በመጥቀስ የመንገዱ ተጠቃሚ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ቅሬታቸውን በምሬት ያቀርባሉ። ይህን ቅሬታ በመያዝ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጄንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኩማን በማናገር ምላሹን አቅርበናል።

የአቶ ብርሃኑ ኩማ ምላሽ :- ኤጀንሲው በከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ ደህንነት ሰላማዊ እና ተቀባይነት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴዎች ለሁሉም መንገድ ተጠቃሚዎች ለማረጋገጥ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሚያሠራውን ባለ 35 ወለል ህንጻ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው አካላት የተጻፈ ደብዳቤ ይዞ እንደተንቀሳቀሰ በመግለጽ ይ ጀምራሉ።

እንደሳቸው ገለጻ በመጀመሪያ ኩባንያው ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ህንጻውን ለመሥራት ያጋጠመውን ችግር በመግለጽ ይጠይቃል። የከንቲባው ጽ/ቤት ግንባታው እጅግ ውስብስብ እና ከመሬት በታች ከ20 ሜትር በላይ ቁመት ያለው የመሠረት ቁፋሮ የሚቆፈር ስለሆነ፣ በህንጻው ግንባታ አጠገብ ከፍተኛ ክብደት ያላቸውና ከፍተኛ ጭነት የተጫኑ ተሽከርካሪዎች የሚያልፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በህንጻው አቅራቢያ የታክሲ ፓርኪንግና የህዝብ መመላለሻ መንገድ ስለሚገኝ ያለውን ችግር በመመልከት ባለው አሰራርና መመሪያ መሰረት ምላሽ እንዲሰጥበት ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ደብዳቤ ጽፏል።

በዚህ ደብዳቤ መነሻነት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ባለሙያ በቦታው ልኳል። በቀረበው ሪፖርት መሰረት የህንጻው ግንባታ ከመሬት በታች ጥልቀት ያለው መሆኑ እና ከእግረኛ መንገድ ጠርዝ ላይ የሚገነባ ስለሆነ ታክሲና አውቶቡስ ሲጭኑ እንዲሁም ሲያወርዱ ለግንባታ ስጋት እንደሚፈጥር ታይቷል። ስለሆነም ኩባንያው በመንገዱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርስ፣ የህንጻ ግንባታው ባልተጓተተ የግንባታ ጊዜ፣ የአካባቢውን ሁኔታ በማይረብሽና በማያውክ ሁኔታ እንዲሁም የግንባታ ተረፈ ምርቶችንም አግባብ ባለው መንገድ በማስወገድ የግንባታ ሥራውን እንዲያከናውን የአንዱን አቅጣጫ መንገድ ዘግቶ እንዲጠቀም፤ የኩባንያውን ኃላፊ ውል በማስገባት ፈቅዷል።

ምላሻቸውን ሲያጠቃልሉ ኩባንያው የገባውን ውልና የአንዱን አቅጣጫ መንገድ ዘግቶ እንዲጠቀም የተፈቀደለትን ደብዳቤ በመያዝ ለአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጥያቄውን አቅርቧል። ህንጻው ሲሠራ በጥልቀት ስለሚቆፈር የአፈር መደርመስ ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች ደህንነት በማሰብ እንዲሁም ሊደርስ ከሚችል አደጋ ለመከላከል ሲባል የህንጻው ቁፋሮ ተጀምሮ መሰረቱ ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ አንዱ አስፋልት እስከ እግረኛ መንገዱ አገልግሎት እንዳይሰጥ ወደሚሠራው ህንጻ እንዲካተት በኤጀንሴው ተፈቅዷል። መንገዱ አገልግሎት ባለመስጠቱ መጨናነቅን ለመቀነስ አስፈላጊ የሆኑ ምልክቶች በኤጀንሲው በኩል እንዲተከሉ ተደርጓል። እነዚህ ምልክቶችን አክብረው የማይንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች የመንገዱን መጨናነቅ ለመቀነስ ተገቢውን ምክርና ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በቀጣይም የሚከሰቱ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ይሰጣል ብለዋል።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም

Recommended For You