ልበ ሰፊነት ያስፈልጋል! 

አገራዊ የምክክር መድረክ ግጭቶችን የመፍቻ ታላቅ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የየበኩላችንን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል። ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ኅብረተሰቡን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ የተወሰኑ አካላት የሚሳተፉ ቢሆንም፣ ህዝቡ የሀገሩን ጉዳይ የእነዚህ ሰዎች ብቻ ጉዳይ ሳያደርግ በየመሥሪያ ቤቱና መሰብሰብ በቻለባቸው ቦታዎች ሁሉ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና ሐሳብ አላቸው ከሚላቸው ሰዎች ጋር እየተቀራረበ፣ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መደማመጥ መቻል አለበት። የማዳመጥ ባህልን ማዳበር ከህዝቡ የሚጠበቅ መሠረታዊ ነገር ነው፤ እኛ ቁጭ ብለን በረጋና በቀና መንፈስ የመነጋገርን ልምድ ባላዳበርንበት ሁኔታ ላይ ያሉ ሰዎች መክረው፣ የሆነ ውጤት ይዘው ቢመጡም ውጤቱን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አንችልም። ስለሆነም፣ሁላችንም ለምክክሩ ስኬት ልባችንን ዝግጁ ማድረግ ይኖርብናል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የመንግሥትን ዝግጁነትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ እየታየ ያለውን ድጋፍ ተስፋ ሰጪ ነው። እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ ቢስተካከሉ የምንላቸውና መንግሥትን የምንተችባቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ገለልተኛ በሆነ አካል ማቋቋሙ፣ የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮችም “በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ጠቁሙ” ብሎ ለህዝቡ እድል መስጠቱና ኮሚሽነሮችን የመሰየምና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ከሥራ አስፈጻሚው ወደ ህግ አውጪው ኃላፊነቱን ማሻገሩ በጣም አበረታችና ዋጋ ልንሰጠው የሚገባ ነው። አሁን ያለው መንግሥት ቀደምት መንግሥታት እንዳደረጉት፣ የጨዋታውን ህግ እኔ ፅፌዋለሁ፤ ይህን የምትከተል ከሆነ “ተከተል” የማትከተል “ሂሳብህን ታገኛለህ” ሳይል፣ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ለሀገራዊ ምክክር መደላድል መፍጠሩን ቀላል ነገር አድርገን ልንቆጥረው አይገባም።

በመንግሥት በኩል ሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ እጁን መዘርጋቱ፤ ቅድመ ዝግጅቶችንም እያካሄደ መሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት ያለውን ፍላጎት ያሳያል። ከዚህ ቀደም የነበሩንን የውይይት እድሎችና የተዘረጉ የሠላም እጆችን በይሁንታ አለመቀበላችን ለበርካታ ችግሮች ዳርጎናል። ዳግመኛ ላለመሳሳት፣ መንግሥት ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ መስመሩን ሲዘረጋ፣ “እንመካከር፤ መፍትሔ እናምጣ” በሚልበት ጊዜ፣ የተዘረጉ የሰላም እጆች እንዳይታጠፉ ሠላም የሚፈልግ ሁሉ ተባባሪ መሆን አለበት።

ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊዎች የሌላውን ፓርቲ አመለካከት ያለ ምንም ብያኔ ቁጭ ብለው በማዳመጥ፣ ለህዝቡ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በምክክሩ የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መምጣታቸው ስለማይቀር የምንሰማቸው ነገሮች የሚቆረቁሩ የጫማ ውስጥ ጠጠር ሊሆኑ ይችላሉና ልበ ሰፊነት ያስፈልጋል። “ፖለቲካ” የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መጥተው የተሻለውን መቀበል በመሆኑ፣ ፖለቲከኞቻችን ሰጥቶ መቀበልን መልመድ አለባቸው።

ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም

Recommended For You