ሳሙኤል ይትባረክ

ሕወሓት ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በርካታ የደርግ ባለሥልጣናት በየፊናቸው ተበተኑ። ከእነዚህ ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት የተወሰኑት አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው ጣሊያን ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቀው ገቡ። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ባለሥልጣናት መካከል ሌተናል ጄነራል አዲስ ተድላ አንዱ ናቸው። ጄነራሉ በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢሰፓ የፖሊት ቢሮ አባል፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው አገልግለዋል። በዘመነ ሕወሓት ኢህአዴግ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቶ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል። ከሰላሳ ዓመታት የጣሊያን ኤምባሲ ተወስኖ መቆየት በኋላ የሞት ፍርዳቸው ወደ እድሜ ልክ ከተቀየረ በኋላ እሱም ቢሆን ወደ ምህረት ተቀይሮ ሰላሳ ዓመታት እድሜአቸውን ከፈጁበት የጣሊያን ኤምባሲ ቅጥር ጊቢ ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ብሎም ቀሪ ዘመናቸውንም በነፃነት እንዲኖሩ አሁን ባለው መንግሥት በኩል ውሳኔ ተሰጥቶበታል። በቅርቡም ‹‹በገጠመኞች የታጀበ የሕይወት ጉዞ›› በሚል ርዕስ መጽሃፍ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል። እኚህን ጉምቱ ወታደራዊ አመራር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ጄነራል ዘመን መጽሄት የአብይ ርእስ ጉዳይ አድርጋቸዋለች።

ዘመን ፡- ሌተናል ጄነራል አዲስ ተድላ ማን ናቸው ብለው ለሚጠይቁ ወጣቶች እራስዎን እንደምን ያስተዋውቃሉ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕጻንነት ጀምሮ በትምህርት ቤት ዓለም ውስጥ አልፌ እስከ ዘጠኛ ክፍል ድረስ አስፋው ወሰን ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በአየር ኃይል ስር በነበረ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የአገር ውስጥና ከለንደን ስኩል ሰርቲፍኬት የሚባል አለ ሁለቱን በአንድ ላይ ወሰድኩ። ፈተናውን ካለፍኩ በኋላ በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ነበረኝ። በወቅቱ ወደ በረራ ኮሌጅ ወይስ ወደ ማህንዲስ ኮሌጅ ልግባ የሚለው ነገር ትንሽ ለመምረጥ አስቸግሮኝ ነበር። በኋላ ግን አየር ኃይል ውስጥ ወደ ሚገኘው የበረራ ትምህርት ቤት ገባው። በሂደቱም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስጄ በተለያዩ ተልዕኮ ውስጥ አልፌያለሁ። በመሃል የጀት ኳሊፊኬሽን ትምህርት የሚባል አለ እሱን እንደጨረስን እንደገና ዩኒቨርሲቲ ዕድል ተሰጠን። የዛን ጊዜ ከሌሎች የአየር ኃይል መኮንኖች ጓደኞቻችን ጋር እኔ መሃንዲስ ኮሌጅ ገብቼ በመካኒካል ምህንድስና የመጀመሪያ ቢ ኤስ ሲ ዲግሪዬን አግኝቼ ወደ አየር ኃይል ተመለስኩ። ከዚያ እንደገና በበራራ ስራ ላይ ተሰማራሁ። በወቅቱ ዋና ተዋጊ ስኳድርል በነበረው በኤፍ አይ ስኳድርል ውስጥ በረራ ላይ እያለን የ1966 አብዮት መጣ። ከዛ ተመርጬ ወደ ደርግ መጣሁ።

 ዘመን ፡- ሰሞኑን “በገጠመኞች የታጀበ የሕይወት ጉዞ” በሚል ርዕስ ባስመረቁት መጽሐፍዎ ላይ የአየር ኃይል የስራ ስምሪት በሚል ንኡስ ርዕስ ስር መሳጭ ታሪኮችን አስነብበዋል። የአየር ኃይል ቆይታዎ ምን ይመስል ነበር ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ፡- የአየር ኃይል ቆይታዬን ያሳለፍኩት ብዙውን ጊዜ የበረራ ልምድን በማዳበር ተልዕኮ ሲኖር ደግሞ ወደዚያ ግዳጅ በመሄድና በመፈጸም ነበረ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የነበርኩበት ሶስተኛ አጥቂ ስኳድርል ይባላል። ወደ ታንዛኒያ ለሚሽን ሔደን ነበር። ወደዚያ የሄድነው የመጀመሪያው የታዛኒያ ፕሬዚደንት ነጻነታቸውን እንዳገኙ በአካባቢያቸው ሞዛምቢክን የሚገዙት ፖርቹጋሎች ስለነበሩ ስጋት አድሮባቸው ንጉሠ ነገስቱን የአየር ኃይል ድጋፍ ይሰጠን ብለው ስለጠየቁ ነው። በአየር በኩል ስጋት ተፈጥሮብናል በሚል ለቀረበው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የእኛ ስኳድርል ወደዚያ እንዲሄድ ታዝዞ ወደዛ አመራን። ከዚህ ተነስተን ናይሮቢ አንድ ቀን አድረን ከዚያ ዳሬሰላም ሄድን። ከዚያ ወደ ወሰኑ ሄደን በረራ በማካሄዳችን ፖርቺጊሶቹ ስጋት ገባቸው። ስለዚህ አንደኛ የነበረው ወቅታዊ ስጋ ተቀነሰላቸው ሁለተኛውና ትልቁ ነገር ታንዛኒያ ነጻነቷን ባገኘችበት ወቅት አብዛኛው ነገር የተያዘው በውጭ አገር ዜጎች ነበር። በእንግሊዞች ነው ወይም በህንድ ስለነበር ሕዝቡ ጥቁር ምን መስራት እንደሚችል ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ስለነበረ ጥቁሮች አውሮፕላን አስነስተው በርረው ሲመለሱ ማየት ለእነሱ ትልቅ ነገር ነበር። ፕሬዚዳንቱም ደግሞ በጣም ኮርተው ስለነበር ደስ ብሏቸው በደንብ አስተናግደውን ከስድስት ወራት በኋላ ተመለስን። የኢትዮጵያ አየር ኃይል በተለያየ ቦታ ግዳጅ ፈጽሟል ፤ በአንድ ወቅት ኮንጎም ሄዶ ተልዕኮ ፈጽሟል።

ዘመን ፡- በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አጠቃላይ ቁመና ምን ይመስል ነበረ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡– አየር ኃይል በደንብ የተደራጀ ቴክኒካሊ በጣም በቴክኖሎጂ የገፋ ራሱን የቻለ የጥገና ክፍል የነበረውና ይህ ክፍል ደረጃ በደረጃ እያደገ ብዙ ነገሮችን እዚሁ የመስራት ችሎታን አዳብሮ ነበር። በአካባቢው የኢትዮጵያን አየር ክልል ከመጠበቅ አንጻር ይሄ ነው የሚባል የሚገዳደረው ሌላ ኃይል አልነበረም። ይሄን ሁኔታ ደግሞ በሶማሌ ጦርነት ጊዜ አረጋግጧል። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የአየር የበላይነት አግኝቶ በዚያን ጊዜ ዓለም መስክሮለታል። የሶማሌን አየር ኃይል ድምጥማጡን አጠፋው፤ ከዚያ በኋላ ማንም ሳይገዳደረው አለተቀናቃኝ የሚበር ኃይል ነበር። ይሄ የሚያሳየው በወቅቱ አየር ኃይል የነበረበትን ደረጃ ነው።

ዘመን ፡- ደርግ ሲቋቋም አንዱ አባል እርሶ ነበሩ። ከነበሩበት የጦር ክፍል በምን መስፈርት ተመረጡ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ፡- ይሄን መጽሐፌ ላይም ገልጬዋለሁ። እኔ ምንም አይነት ሃሳብ አልነበረኝም። መጀመሪያ ደርግ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲቋቋም እኔ ቅዳሜና እሁድን ለእረፍት አዲስ አበባ መጥቼ ነበር። የዚያን ጊዜ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከጓደኞቼ ጋር እያለሁ የሰዓት እላፊ ታወጀ ተባለ። የሰዓት እላፊውን ያወጁት እነ ኮሎኔል አጥናፉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ሁላችንም ወታደሩ ክፍል ይሄን ነገር ለምን በሥርዓት አይዘውም እያልን እያማረርን አደርን። ቅዳሜ ይህንን ሰምተን እሁድ ደብረዘይት ተመለስን።

ሰኞ ክፍል ስንገባ ከየክፍሉ አንድ መኮንን አንድ የበታች ሹም መርጣችሀ ላኩ በተባለው መሰረት በወቅቱ ሻንበል የነበረው ሲሳይ ሀብቴ እና እንድ ሌላ ሊዲንግ ኤርፖርት ማን ደምሰው ካሳዬ የሚባሉ ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ ሄደው ነበር። በዚህ ጊዜ አየር ኃይል ዋናው ተዋጊ ክፍል እንዴት አይወከልም፤ አየር ኃይል በአየር ላይ ግዳጅ የሚፈጽም ስለሆነ መወከል አለበት ተብሎ ፓይለቶች ተሰበሰብን። እንግዲህ ፓይለቶች ስል የተዋጊ ፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የኤሊኮፍተር ክፍል አለ። ሁላችንም ተሰብስበን ማንን እንወከል በሚል ውይይት ሲደረግ እያንዳንዱ አስተያየት ሰጠ። እኔም የራሴን አስተያየት ሰጠሁ። ከዚያ ምርጫ ይካሄድ ሲባል እኔ ላይ ተጠቆመ። ለምን እኔ እንደተጠቆምኩ አልገባኝም። በእርግጥ እኔ ቀደም ብዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለነበርኩና የተማሪውንም እንቅስቃሴ ስለማውቅ ምናልባት በተሻለ ሁኔታ እኛን ይወክለናል በሚል ሊሆን ይችላል። ከዛው ክፍል ደግሞ የቴክኒካል ክፍሉ ማስተር ቴክኒሺያን ገሰሰ ተመረጠ። ከዚያ ሁለታችን ማክሰኞ ወደዚያ ሄድን። እንግዲህ ባላሰብኩትና ባልጠበኩት ሁኔታ ወደ ደርግ መጣሁ።

ዘመን ፡- መጽሐፍዎት ላይ እንዳሰፈሩት ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በ60ዎች የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ የፖለቲካ ውሳኔ ተሰጠ። ይህ መሆኑ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ፈጥርብዎት እንደነበረ ጠቅሰዋል። ምኑ ነው የመንፈስ ጭንቀት የፈጠረብዎት?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- በሁለት ነገር ነው። አንደኛ የእነዚህ ሰዎች የመጨረሻ ውሳኔ በፍርድ ይሰጣል ተብሎ ነበር የፍርድ ሂደት ውስጥ የተገባው። ያ ነገር ተቀይሮ በእነሱ ላይ ውሳኔ ይሰጥ ተባለ። ይሄ ራሱ በጣም የመንፈስ ጭንቀት የሚፈጥር ነገር ነው። ሁለተኛ ከታሰሩት ውስጥ ስለያንዳንዱ ሰው ከስም በቀር ምን አደረጉ ምን አጠፉ የሚለውን ነገር በተመለከተ እኔ ብዙም እውቀት አልነበረኝም። አሁን ለምሳሌ ከታወቁት ውስጥ አክሊሉ ሀብተወለድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን ሌሎቹም ሌሎቹም በነበራቸው ሥልጣን በዜና የምሰማው ነው እንጂ ከኋላቸው ምን እንዳደረጉ እና እንደሰሩ እኔ በቂ ግንዛቤ አልነበረኝም። የሚገርመው ግን እዛ መሃላችን የነበሩ የምድር ጦር አባላትና የበታች ሹሞች ስለእያንዳንዱ በዝርዝር የሚናገሩት ነገር አለ። እኔ ግንኙነት የነበረኝና በቅርብ የማውቃቸው የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩትንና ሌሎች መኮንኖችን ስለነበር በድንገት ተነስቶ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ይሰጥ ሲባል የመንፈስ ጭንቀት የሚያሳድር ነው።

በሌላ በኩል በዛው ስብሰባ ላይ ኮሎኔል ብርሃኑም ተቃውሞ ይሄ ነገር በሕግ ነው መፈጸም ያለበት ብሎ ነበር። ይህንን ሃሳብ የሚደግፉም የማይደግፉም ነበሩ ህዳር 14 የነበረው ሂደት ድንገት የመጣ ነው።

ዘመን ፡- የአየር ኃይል የቅርብ ባልደረባዎትና መንግሥቱ ኃይለማርያምን በብዙ ነገር ይገዳደራቸዋል ተብሎ ይታሰብ የነበረው ሻምበል ሲሳይ ሀብቴ አሟሟትን እስኪ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይንገሩኝ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ፡- ሻምበል ሲሳይ ሀብቴ በጣም ጎበዝ ኦፊሰር ነው ፤ በትምህርትም። መጀመሪያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በገባው ጊዜ ከእኔ በአንድ አመት ቀድሞ ይማር ነበር። በፊት ኤልክትሮኒክስ ትምህርት ቤት ሆኖ አውቀው ነበረ። ጎበዝ ከሚባሉት መኮንኖች አንዱ ነው። እዚህ ያለውን ትምህርት ሳይጨርስ ወደ አሜሪካ ሄዶ ማስተርሱን ይዞ መጣ። ደርግ እንደተመሰረተ እነ ጄነራል አማንም ሆነ ሌሎች ግለሰቦች ሄደው ሲያነጋግሩት በሱ ብስለትና ብልህነት ተደንቀዋል። የውጭ ሰዎች ሁሉ ያደንቁታል። በሌላ በኩል ልዩ የመናገርና የማሳመን ችሎታ ያለው መንግሥቱ ኃይለማሪያምም አለ። እንግዲህ እዚያ ውስጥ መከፋፈል ቢኖር ምናልባት የእሱን ሥልጣን ሊቀናቀን ይችላል ብሎ የሚገምተው ሲሳይን ሊሆን ይችላል። ተቀናቃኝ ያልከው ነገር ይሄ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የምገምተው።

እንዴት ተወገደ ለሚለው በመንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ቅሬታ ያደረባቸው ከሲሳይ ጋር የሚሰሩ አንድ ሁለት ሶስት መኮንኖች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች አንድ ለውጥ ይምጣ እንጂ በሚል ገፋፍተውት ወደ አንድ ያልተፈለገ እቅጣጫ የሄደ ይመስለኛል። እርግጥ ይሄን ነገር ያሳወቀንና ሁኔታውን የገለጸልን የደርግ ደህንነት ክፍል ነው። ሲከታተሏቸው ከደርግ ውጪ ራሳቸው ሰዎች ሰብስበው እያነጋገሩ አንድ አይነት ለውጥ ለማምጣት መፈንቅለ አመራር ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው ያስረዳን። በመጨረሻ ይሄንን ተጨባጭ መረጃ ይዘው ነው ከእሱ ጋር የነበሩት መቶ አለቃ በእውቀቱ ካሳ እና መቶ አለቃ ስለሺ በየነ የሚባሉ የአካዳሚ ኦፊሰሮች ሁለት መኮንኖች አዲስ አበባን ጥለው ወደ ጎጃም ሄደው ስለነበር እሱን እዚህ ያዙት። ከዚያ በኋላ የሆነው ነገር ታሪክ ነው።

ዘመን፡-የወቅቱ የደርግ ሊቀመንበር ጄነራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ ሌሎች በኢህአፓነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሲገደሉ በምን ሁኔታ ሰሙ ? አቋሞ ምን ነበረ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- የእነ ጄነራል ተፈሪ ደግሞ ከብዙ ጊዜ ሂደት በኋላ የሆነ ነው። መጀመሪያ እኛ ንጉሱን እንዳወረድን እና ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መቋቋሙን ስናውጅ በህቡ የነበሩ ድርጅቶች የሚታወቁ አልነበሩም። የሚታወቁት በሚበትኑት ጽሁፍ ነው። ለምሳሌ ኢህአፓ ዴሞክራሲያ የሚል መጽሔት ይበትን ነበር። እነ መኢሶን ደግሞ ሰፊው ሕዝብ የሚል ነበራቸው። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የኋላ ታሪካቸው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተመሰረቱ ግማሾቹም አውሮፓ ያሉ ተማሪዎች የመሰረቷቸው ናቸው። አሁን እያደገ ሲሄድ ሕዝብ ድርጅት ጽህፈት ቤትም ከተቋቋመ በኋላ በድርጅቶች መሃል ቅራኔ ተፈጠረ። ያው እንደሚታወቀው የተወሰኑት ሂሳዊ ድጋፍ እየሰጠን ከደርግ ጋር እንስራ አሉ።

መኢሶን፣ ወዝ ሊግ እና ሌሎች ድርጅቶች በአብዛኛው ከደርግ ጋር መስራት ጀመሩ። ኢህአፓ ግን አልሰራም አለ። በዚህ ሂደት ውስጥ ሥነ ሥርዓቱ ካለቀ በኋላ ተነስቼ ወደ ቢሮ ሄድኩ። ወደ ቢሮ ስሄድ በሚያሳዝን ሁኔታ የአየር ሃይል ጀቶች ከደቡብ ወደ ሰሜን ይበራሉ፤ በዝቅተኛ ከፍታ ላይ ሆነው ማለት ነው። እና እኔ በዚያን ጊዜ የመጣብኝ አስመራ ወይም ባህር ዳር አንድ ችግር ተፈጥሯል ወደዛ እየሄዱ ነው ብዬ አሰብኩ። ከዛ ስልክ ተደወለና በአስቸኳይ መንግሥት ምክር ቤት ትፈለጋለህ አሉኝ። ስደርስ እነ ሻምበል ፍቅረ ስላሴና ጥቂት ሰዎች ነበሩ። መፈንቅለ መንግሥት እየተካሄደ ነው አሉኝ። ይሄንን አላስብኩም፣ አልጠበቀኩም። በወቅቱ ከጀቶቹ ሌላ ሄሊኮፕተሮች ከተማው ውስጥ ይበሩ ነበር።

ፍቅረ ስላሴ ኮሎኔል አዲስና ኮሎኔል ደበላ ሂዱና አነጋግሯቸው፤ ምን እየሰሩ እንደሆነ ቼክ አድርጉ ብሎ ላከን። እኛ ራሱ ያልጠበቅነውና ያልተዘጋጀንበት ነው። ምን ለማድረግ ነው ምንሄደው ብለን ጥያቄ አልጠየቅንም፤ ምንድነው የምንለው፣ እነማንን ነው የምናገኘው ምንም አላሰብንበትም። ፍቅረስላሴ እኔን የላከኝ ከብዙዎቹ መኮንኖች ጋር ስለምገናኝ ስለእኔም መጥፎ አስተያየት ስለሌላቸው እሱ ቢሄድ ምንም አይሆንም ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ ሕዝብ በማነጋገር ልምድ ስላለው ብሎ ሊሆን ይችላል። ብቻ ሄድን፣ እዛ ስንሄድ መከላከያ ሚኒስቴር ተከቧል፤ ሻምበል መንግሥቱ ገመቹን አገኘነው እና እነርሱን ለማነጋገር መጥተናል አልነው። እሺ ግቡ አለንና ስንገባ የፖሊስ አዛዡን አገኘናቸው። እኔ ሳላስበው እዚህ መጥቼ ተይዣለሁና እንድወጣ አስፈቅዱልኝ አሉ። እኛ እዚህ የመጣነው ለሌላ ዓላማ ስለሆነ መጀመሪያ ሄደን ጀነራል መርዕድን ማነጋገር አለብን አልን። ጀነራል መርዕድ ቢሮ ስንደርስ የመፈንቅለ መንግሥት አባላቶቹ ተሰብስበዋል። ለማነጋገር እንደምንፈልግ ንገሯቸው አልን። ነገሯቸው ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። እንዲያውም እኛን ወደ ስብሰባ አዳራሽ ኑ አሉን። አይ ስብሰባው አንገባም አልናቸው። በኋላ እሺ አሉና መጡ። ሜጀር ጄነራል መርዕድ ንጉሴ፣ ጄነራል ኃይሉ፣ የአየር ኃይሉ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል አምሃ ደስታ፣ አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ መጡ። ርቀት ለርቀት ቆመን ነበር። በኋላ እየተጠጋጋን መጣንና ምንድነው እየተደረገ ያለው አልን። ጄነራል መርዕድም መንግሥቱን ሕዝቡ አይወደውም፣ ሕዝቡ ጠልቶታል፣ ሠራዊቱም ጠልቶታል እና እንዲነሳ ይፈልጋል። እኛ የሕዝቡንና የሠራዊቱን ድምጽ ፍላጎቱን ለማስፈጸም ነው። ከእናንተ ጋር ጠብ የለንም አሉን።

እንዴት ይሆናል መጀመሪያ ነገር እኛ አድርጉ ብለን ውሳኔ ለመስጠትም አይደለም የመጣነው፤ ሁኔታውን ተረድተን እንናገራለን አልናቸው። እና የተወሰነ ሰዓት ነው የምንሰጣችሁ አሉን፤ ጀነራል አምሃ ከእኔም ጋር በጣም ቅርብ ሰው ስለነበረ ይህ የተከበበ ታንክና መሳሪያ ካልተነሳ በአየር እንዲደበደብ አስደርጋለሁ አለኝ፣ አይ እንዴት ይሆናል፣ ከእነርሱ ይልቅ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው። በኢትዮጵያ ሆቴል፣ በብሄራዊ ቲያትር ሕዝብ ተሰልፎ ድራማውን እንደሚከታተል አይነት ነገር ነው። እርምጃ ከተወሰደ ሕዝብ ነው የሚያልቀው ይህን ነገር አታደርጉ። ለማንኛውም እኛ ሄደን የእናንተን ሐሳብ እንነግራልን አልን። በዚህ ተነስተን ሄድን ያለውን ሁኔታ ገለጽን እና ደረጃ በደረጃ ነገሩ እየሟሸሸ፣ እየሟሸሸ ሄደ። በመጨረሻ ሌሎቹ እጃቸውን ሰጡ። ሁለቱ ግን ራሳቸውን አጠፉ ጀነራል መርዕድና ጀነራል አምሃ።

ዘመን ፡- ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ እርሶ የመከላከያ ሚኒስትር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ተሸሙ፣ ተቋሙን ለማስተካከል የወሰዱት እርምጃ አለ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- ይህንን ኃላፊነት መንግሥቱ ውሰድ ያለኝ ድንገት ነው። እኔ በጭራሽ አልጠበኩም። አንደኛ ለረጅም ጊዜ ከሠራዊቱ ተለይቻለሁ፣ ሁለተኛ እኔ የአየር ሃይል ሰራተኞችን እንጂ የምድር ጦር ሠራተኞችን አላውቅም። በሥራ ምክንያት ከማውቃቸው ውጪ እና ይህንን አድርግ ከእኔ ጋር አብረን እንስራ አለኝ፣ እንዴት ከእኔ የተሻሉ ሌሎች ሰራተኞች አሉ አይደለም ወይ የምድር ጦር ሰዎች፣ እነ ጄነራል ተስፋዬ /የተነሳም ቢሆን/ እሱም አለ፣ ኮሎኔል ብርሃኑም አለ፣ ሌሎችም አሉ አልኩት። የለም አንተ እንድትሆን ነው የምፈልገው አንተ ሁን አለኝ። ይህን ያለበት የራሱ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። አየር ኃይል ከመንግሥት ጋር አብሮ እንዲሰራ ፈልጎም ሊሆን ይችላል።

በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ብዙ የቀደሙ ሠራተኞች ተገልለዋል፤ የሞቱም፣ የታሰሩም አሉ። እና ይሄንን ነገር እንደገና ወደ ተዋጊ ኃይል የተደራጀና ውጤታማ ኃይል ለማድረግ ብዙ ጥረት ነበር። ሰዎች ተመርጠው ከእኔ ጋር የነበሩ እንደ ጄነራል መስፍን ገብረ ቃል፣ እነ ጄነራል ስዩም፣ ሌሎችም ነበሩ። አብረን ሆነን ይሔንን ሰራዊት እንዴት ውጤታማ አድርገን አጠናክረን እናዋቅረው። ሁለተኛ በሠራዊቱ ውስጥ ያለውን ሙስና ለማጥፋት፣ ብዙ ስማቸው በሙስና የሚነሳ ሰራተኞችን መጀመሪያ ማግለል አለብን፤ ጥሩ ጥሩ እና ሀቀኛ ሠራተኞችን ወደ ላይ አምጥተን ማዋቀር አለብን ብለን በአዲስ መልክ ለማደራጀት ሞከርን። ከዛ ደግሞ ግንባር ያሉትን ሠራተኞች ሄደን ለመጎብኘት ወሰንን። በተለይ የሰሜን እዝ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባህር ኃይል ያሉበት ከመሆኑ ባለፈ ዋናው ውጊያም እዛ ነው ያለው። ይሄን ማየት፣ እንደገና ደግሞ በዋናው መሥሪያ ቤት ያሉትን ነገሮች ለማስተካከል ሞከርን። ልምድ የነበራቸው ውጤታማ የነበሩ ሠራተኞች ብዙዎቹ በመፈንቅለ መንግሥቱ ስለተጠረጠሩ ከቦታቸው ተነስተው ነበርና በጣም ከባድ የሆነ ነገር ነበር። ለዛም ነው ጄነራል እምቢ በል ከማዕከላዊ ኮሚቴ ተነስቶ የምድር ጦርን እንዲመራ የተደረገው። በተቻለ መጠን ያሉት መኮንኖች እንዲሰሩ በማድረግ፤ በዚህ መሠረት ነው ለማስተካከል የተሞከረው።

ዘመን ፡- የ1982ቱ የምጽዋ ጦርነት ከሌሎች ጦርነቶች ልዩ የሚያደርገው ምን ነበረ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- በወቅቱ ዋና የኢትዮጵያ ወደብ አንዱ ምጽዋ ነው። ሌላው አሰብ ነው። ምጽዋ ግን ለሰሜን እዝ ዋና የሎጅስቲክስ ማቅረቢያ ቦታ ነው። ሁለተኛ አንዱ ኃይላችን ዋናው መሥሪያ ቤት ያለው እዛ ነው። የባሀር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የሎጅስቲክስ ድጋፍ የሚጠይቅ የሠራዊት ክምችት ያለውም እዛ ነው። ስለዚህ ምጽዋ በጣም በጣም ወሳኝ ክፍል ነው፣ እሱን ማዳን እሱን በደንብ መጠበቅ ወሳኝ ነበር።

ዘመን ፡- በወቅቱ እነማን ከዱ እነማንስ በጀግንነት ተሰዉ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፡- ምጽዋ ሲመታ ራሱን በደንብ እንዲከላከል ተብሎ፣ አንድ ታንከኛ ክፍለ ጦር ነበር፣ አካባቢው ሜዳ ነው፣ አሸዋ ነው። በዛ ሜዳ ላይ ማንም እርሱን ሊገዳደረው የሚችል ኃይል ሊኖር አይችልም። ሻዕቢያም ቢመጣ የእግረኛና የተወሰነ የጦር መሳሪያ ይዞ ነው እንጂ ታንክ እንደኛ አይኖረውም። ሌሎችም ልዩ ልዩ ኃይሎች ነበሩን። የባህር ኃይል አለ፣ የአየር ኃይል ደግሞ አስመራ አለ። ከዚህ በፊትም ብዙ ጊዜ ሞክሮ ከሽፎበታል። አሁን ይሔ ድንገት ሲጠቃና ሲፈርስ ያለምክንያት አልነበረም። የታንኩ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበረው እና ምጽዋ አካባቢ የነበረው የኮር አዛዥ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እጃቸውን ለሻዕቢያ ሰጥተው ነበር። እነ ብርጋዲየር ጀነራል ክፍሌ ጥላሁን እና ጀነራል አሊ ሀጂ እጃቸውን ከመስጠት ባለፈ ሌሎች እጅ እንዲሰጡ ይቀሰቅሱ ነበር። በሕይወትም ኖሩ አልኖሩ ታሪክ ሲወቅሳቸው ይኖራል። በተቃራኒው ደግሞ በአገር ፍቅር ያበዱ፣ ሕይወታቸውን ለአገር መስዋዕትነት ያዋሉ፣ ዝንተ ዓለም በበጎ ተግባራቸው ሲወሱ የሚኖሩ ጀግኖች የታዩበት ውጊያ ነበር። እነ ጄነራል ተሾመ ተሰማ፣ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ፣ ሻምበል ሸዋንታዪ አለሙ ሀብቴ፣ ክብር ኮሞዶር በለገ በለጠና ክብር ኮሞዶር ጌታቸው ስዩም እጃችንን አንሰጥም ብለው እስከ መጨረሻው ተዋግተው በጀግንነት የተሰው ናቸው። ይሄ እንግዲህ የፈጠረው ክፍተትና ውድቀት በጣም ከፍተኛ ነበር።

ዘመን ፦ በርካቶች ምጽዋ ላይ ሲወድቁ በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው ስሜት ምን ነበር? እርስዎስ ምን ተሰማዎት?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ እንዴ! በጣም ነው የተሰማኝ። አንደኛ የባህር ኃይሉ ምክትል አዛዥ የነበረው ኮሞዶር በለገ በዚህ ጦርነት ተሰውቷል። ባህር ኃይሎች ያላቸውን ቤዝ አጥተዋል። ከፍተኛ የአገሪቷ የመከላከያ ኃይል እና መሳሪያ፣ ያ ሁሉ ሲወድም ከፍተኛ ውድቀት ነው። በጣም የሚያሳዝን ነው። ምክንያቱም ከእንግዲህ ወዲያ ሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊትን መደገፍ በመሬት አይቻልም፤ በአየር ብቻ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም በትግራይ በኩልም አማራጭ አልነበረንም።

ዘመን፦ ሕውሓት እያደረገ ያለውን አገር የማፍረስ እንቅስቃሴን እንዴት አዩት?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ ይሄን ሁሉም የሚያውቀው ነው! መጀመሪያውኑ ሲቋቋም ትግራይን ነጻ ለማውጣት በሚል እስከ አሁን ድረስ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ተብሎ ትግራይን ሪፐብሊክ አድርጎ ለማውጣት እና ኢትዮጵያን ለማውደም ነው የተነሳው። ይሄንኑ ነው ሲቀጥልበት የነበረው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የድርጅቱ አመራሮች የአገሪቱን ሀብትና የሀብት ምንጭ ለራሳቸው አድርገዋል፤ ወደ ውጭ አሽሽተዋል። መከላከያውን ከላይ እስከ ታች ተቆጣጥረው፤ ደህንነቱን ሙሉ በሙሉ ይዘው፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር ሰርተዋል። ይሄ በጣም በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው።

ዘመን፦ ሕውሓት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሮ፣ ኢትዮጵያ ጠል የሆነ ድርጅት ለምን ሆነ ብለው ያስባሉ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ ከድርጅቱ አፈጣጠር ይመስለኛል። እንደሚባለው ከሆነ ወያኔ ቅሬታ ያለው የአገሪቱን አመራር ያለ አግባብ እነ አፄ ምንሊክ፣ የሸዋ ነገስታት ወሰዱት፤ የእኛ ነበረ። ከአጼ ቴዎድሮስ ቀጥሎ ተክለ ጊዮርጊስ ነግሰው ነበር፤ በመቀጠል ሥልጣን የተረከቡቱ አጼ ዮሃንስ ናቸው። አጼ ዮሃንስ በሚገርም ሁኔታ ስለኢትዮጵያ አንድነት ከፍተኛ ስሜት የነበራቸው ንጉስ ነበሩ። መተማ ላይ እሳቸው ሲሰዉ፣ የእሳቸው ልጅ መንገስ ነበረበት የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው ሰዎች ይናገራሉ። አፄ ምኒልክ አላግባብ ነው ንግስናውን የወሰዱት ይላሉ። በዚህ ሁኔታ ነው የተነሱት ወይም ይሄን ትረካ ይዘው ነው እንዲህ የሚያደርጉት የሚል አለ።

ሁለተኛ ብዙዎቹ የሕወሓት አመራሮች የባንዳነት ፀባይ ያላቸው ወይም ዘመዶቻቸው ባንዳ በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተመሳጥረው፣ ከኢትዮጵያውያን በተቃራኒ የመስራት ልምድ አላቸው። የመለስ ሁኔታ የታወቀ ነው፤ አባቱ ባንዳ ነበሩ። ስለዚህ ሥልጣን አላግባብ ተነጠቅን በሚል ከቻሉ ሥልጣኑን ለመውሰድ ካልሆነ አገር ለማፍረስ እየሰሩ ነው። ይሄ አሁን በግልጽ እየታየ ነው። ሕወሓት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትጥፋ ብሎ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።

ዘመን፦ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በማንኛውም የአገራችን ጉዳይ ላይ ውይይት የማድረግ ሀሳብን እንዴት አዩት?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ መልካም ነገር ነው። ከተሳካ ጥሩ ነው። በመሀል ጭቅጭቅ እንዳለ ነው የምንሰማው። ከብልጽግና ውጭ ያሉት የተወሰኑ ፓርቲዎች ይህንን ሂደት የሚደግፉ አሉ። አካሄዱ ትክክል አይደለም ብለው የሚቃወሙም ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ እንዴት ማቀራረብ ይቻላል? አንዳንድ ፓርቲዎች ብሄርን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት የብሄር ማንነት መቅደም አለበት ሲሉ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ብሄረ ኢትዮጵያን ሲያስቀድሙ ይታያሉ። የምክክር መድረኩ ጫፍና ጫፍ ሆነው የሚሳሳቡ አካላትን ማቀራረብ የሚያስችል መድረክ ከሆነ ጥሩ ውጤት ይገኛል። እነዚህን አቀራርቦ ለአንድ አገር የሚሠሩ ከሆነ ጥሩ ነው።

ዘመን፦ ከጓድ መንግሥቱ ሃይለማሪያም ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩት መቼ ነበር ? በምን ጉዳይ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ እሱ የሄደው ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም. ነው። ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም. ማታ በስልክ ተነጋግረናል። እኔ ዘመቻ መምሪያ ነበርኩኝ፤ እሱ ደግሞ ቤቱ ነበር። የተነጋገርነው አሰብ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብታ ስለነበረ አንስተን ተወያይተናል። ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ያሉትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለምንድነው ወደ አሰብ የማትልኳቸው አለ። እንዴ! እነሱማ ገና ሥልጠና ወስደው አላጠናቀቁም፤ አሰብ ሄደው ምን ጥቅም ይሰጣሉ በሚል ሊሆን አይችልም ብዬ ተነጋገርን።

ዘመን፦ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ እንዴት ገቡ? ወደ ኤምባሲው ከመግባትዎ በፊት የት ነበሩ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ ማታ ቤቴ ነበርኩኝ። ወደ ጣሊያን ኤምባሲ ለመግባት ምንም ሃሳቡ አልነበረኝም። ድንገት ማታ ወደ አንድ ሰዓት ላይ ጄነራል ተስፋዬ ስልክ ይደውልና ጣሊያን ኤምባሲ እንሂድ፤ ሰዎቹ እኛን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው ብሎ ነገረኝ። በኋላ አንዳንድ ሰዎች ሳነጋግር አሁን ያለውን ጊዜ፣ ይቺን ጥቂት ቀናት ዞር ማለት ይጠቅማል አሉኝ። እኔም እሺ ብዬ ከጄነራል ተስፋዬ ጋር ሄድኩኝ፤ ማታ ወደ ሁለት ሰዓት ላይ ገባን። ተስፋዬ ከአምባሰደሩ ጋር ትውውቅ ነበረው። እኔም ከዚህ በፊት ዘመቻ መምሪያ በነበርኩበት ጊዜ መጥቶ ጎብኝቶኛል፤ አውቀዋለሁ። እነሱ ግን የተሻለ ግንኙነት ነበራቸው። አምባሳደሩ እሺ ብሎ እሱን ለማስተናገድ ዝግጁ ነበረ፤ እኔንም ይዞኝ ለመምጣት ነግሮት ለሁለታችንም አዘጋጀልን። ሁለታችንም ከአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ነበር ለብዙ ጊዜ የምንኖረው።

ዘመን፦ የሌተናል ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን አሟሟት እንዴት ነበር ?

ሌተናል ጀነራል አዲስ ፦ ለነገሩ በጻፍኩት መጽሐፍ ላይ ጽፌዋለሁ። ከበፊትም ጀምሮ ቅራኔ ነበራቸው። ጦር ሠራዊት ውስጥ ችግር ነበር። የሐረር የጦር አካዳሚ ምሩቆች መኮንኖች አሉ፤ የሆለታ የጦር አካዳሚ ምሩቆች አሉ። በእነሱ መካከል ከፍተኛ ፍትጊያ ነበር። ሐረር አካዳሚ ገብተው የሰለጠኑት ከፍተኛ ትምህርት ተምረው የጨረሱና አንዳንዶቹ ዩኒቨርሲቲ አንድ ዓመት ጨርሰው በግድ ገብተው ነው እዚያ የተማሩት። የሆለታው ደግሞ ከስምንተኛ ክፍልም ከአስረኛ ክፍልም ገብተው ነው የተማሩት። በሚሊቴሪ ከሰለጠኑ በኋላ የሆለታዎቹ መብታችን አልተከበረም፤ እኛ ዩኒቨርሲቲ ከገቡት እኩል ማግኘት አለብን፤ በደሞዝም ሆነ በሌላ ነገር የሚል ቅራኔ ነበራቸው። ይሄ ቅራኔ ቆይቷል። ክቡር ዘበኛም የራሱ ጥያቄ አለው፤ እኛ የተለየ ሥልጠና የወስደን ነን ይላሉ። በመካከላቸው ብዙ ችግሮች ነበሩ። በአጋጣሚ ደግሞ ከፍተኛ ተሰሚ ድምጽ ያላቸው ኮሎኔል መንግሥቱን ጨምሮ ጄነራል ተስፋዬ ሌሎችም የሆለታ ምሩቆች ናቸው። የአካዳሚው ሰዎችም ጄነራል ደረጃ የደረሱ አሉ። ዋናውን ቦታ የያዙት እነ መንግሥቱ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የሐረር አካዳሚ ደረጃ በደረጃ እንዲዘጋ ተደረገ። ምክንያት ነበረው፤ ሆን ተብሎ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በሱማሌ ጦርነት ምክንያት አካዳሚው ሊቀጥል አልቻለም ነበር። ይሄ ሁሉ ቅራኔ ስላለ ሁለቱም የተለያየ አተያይ አላቸው። በዚህ በዚህ ምክንያት በሁለቱ መካከል ቅራኔ ነበር። የብርሃኑ እና የተስፋዬን ብንመለከት ብርሃኑ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የሕግ ምሩቅ ነው። ተስፋዬ በዛው በፊልዱ የተማረ እና ሁለት ጊዜ አሜሪካ ሄዶ የሰለጠነ ነው። መንግስቱም እንደዚሁ። ይሄ ሁኔታና ሌሎች ትናንሽ ነገሮች ናቸው ወደ ግጭት ያስገባቸው።

ዘመን፦ በዕለቱ ግን መነሻ የነበረው ጸብ ምን ነበር ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ በየቀኑ ማታ ማታ ወክ እናደርጋለን። ከአስር እስከ አስራ አንድ ሰዓት ወክ አድርገን ከተመለስን በኋላ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ እራት እንበላለን። በዕለቱ ተስፋዬ መጀመሪያ ወክ አድርጎ ጨረሰና ወደ ክፍሉ ገባ። እኔና ብርሃኑ ከጣሊያኑ ፖሊስ ጋር አብረን ወክ አድርገን ስንገባ አብሮን የነበረው ፖሊስ ነገ የእኛ የሕዝብ በዓል ስለሆነ ይሄን በዓል ለማክበር ከውጭ የሚመጡ ብዙ እንግዶች ስላሉ፣ እባካችሁ ከግቢያችሁ አትውጡ አለን። ለራሳችን ለብቻችን ግቢ አዘጋጅተውልናል። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነስተን ተስፋዬ በቅድሚያ ቁርስ በላና ወደ ውጭ ሲወጣ፣ እዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጥበቃዎች ዛሬ መውጣት አይቻልም እንግዶች ስለሚመጡ፤ ትናንት እኮ ተነግሯል ሲሉት ተበሳጨና መጣ። ዛሬ መውጣት እንደማይቻል ታውቁ ነበር? ብሎ እኔን ጠየቀኝ። አዎ አልኩት፤ ብርሃኑንም ጠየቀው አዎ አለው። እንደቀልድ ነው የነገረን አለው። በጣም ታሳዝናለችሁ እንዴት አልነገራችሁኝም አለን፤ ዝም አልነው።

እንደገና ተነስቶ ወጣ። በመቀጠል ተመልሶ መጣና ለምን አልነገርከኝም ብሎ ብርሃኑ ላይ ቦክስ ሰነዘረ። የዚያን ጊዜ ተቃቀፉ። በዚያን ጊዜ እኔ ያለሁበት ጠረጴዛ ተንሸራተተና ጥግ ውስጥ ገባሁ። እነሱ ተያይዘው ወደቁ። ዞሬ እነሱን ለማላቀቅ ሞከርኩኝ። ከዚያ በኋላ ሠራተኛችን ሰምታ ስትጮህ ፖሊሶች መጡ፤ ለያዩዋቸው። በመቀጠል ቆመን ሳለን እንደገና ደግሞ ጄነራል ተስፋዬ እልሁ አልበረደለትም። በእርግጫ ለመማታት ሲሞክር ብርሃኑ አቀፈው። ሲታገሉ መስኮት አካባቢ ነበሩ። ጠረጴዛ ላይ ሲወድቅ መስኮቷ ተሰበረችና የተስፋዬን የጭንቅላቱን የኋላ ክፍል ቀረደደችው።

በነገራችን ላይ ጄነራል ተስፋዬ የስኳር በሽተኛ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ በመርፌ በሚወጋ መድኃኒት ነው የነበረው፡፡ ጭንቅላቱን በፎጣ ጠቅልሎ ወደ መኝታ ቤት ሲሄድ በአስቸኳይ ሀኪም እንዲመጣ ተደረገ። የመጣው ሀኪም እዛው ግብዣ ላይ የነበረ የኤምባሲው ሀኪም ነበር። ሀኪሙ መጥቶ አይቶ ምንም አይደለም፤ በወታደሮች መካከል ግጭት ያለ ነው አለና ፋሻ ጠቀለለት፤ አንዳንድ መድኃኒትም ሰጠው፤ በቃ ደህና ነው አለ።

መሆን የነበረበት የተቀረደደው መሰፋት ነበረበት፤ ደም እንዲቆም። በአገራችን ባህል እንኳን ደም የሚፈስ ከሆነ በማሰሻ ተደርጎ ድም ድም ይደረጋል፤ ደሙ እንዲቆም። ሀኪሙ በፋሻ ብቻ ጠምጥሞት ሄደ። በጣም የሚያሳዝን ነው። መድኃኒት ይሄን ስጠው አሉኝ። በኋላ ከሰባትና ስምንት ሰአት በኋላ ቆይቶ ለሠራተኛዋ ለእሱ እራት አቅርቢለት አልናት። እኛ እየበላን ሳለን እሱ መኝታ ቤት ድምጽ ሰማሁ። መኝታ ቤቱ ሄጄ ስመለከት ነጭ ፋሻው በሙሉ ደም ሆኗል። በጣም በጣም አዝኜ በአስቸኳይ ፖሊስ ጠራሁ፤ ሀኪሙም ተጠራ። እንግዲህ ለስድስትና ለሰባት ሰዓት ያህል ደም ሲፈሰው ነው የቆየው። መወሰን አቃታቸው። ወይ ሆስፒታል ወስደው ወይም ባለሙያ አምጥተው መሰፋት ነበረበት። ሌተናል ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን የሞተው በሀኪሙ ጥፋት ደም ፈሶት ነው። በእንደዚህ አይነት ሕይወቱ አላግባብ ጠፋ።

ዘመን፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ?

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ በጣም አስቸጋሪ ነው። የእኛ ጊዜ እና የአሁን ጊዜ በጣም የተለያየ ነው። አንደኛ በእኛ ዘመን በዘር የተከፋፈለ አልነበረም። ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ ያምናል። ወጣቱ ስለኢትዮጵያ አንድነት ግንዛቤ ነበረው። ሲመለመልም የትም ሲሄድ አንተ ኢትዮጵያዊ ነህ እንጂ ኦሮሞ ነህ፣ ትግሬ ነህ፣ ወይ ሌላ ብሄር ነህ የሚባልበት ነገር አልነበረም። አሁን ያ ሁሉ ተቀይሮ ያለፈው ሰላሳ ዓመታት በዘር ተከፋፍሏል።

ሁለተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት እንዳይሰጥ ተደርጎ ወጣቱ ምንም እሳቤ የለውም። ኢትዮጵያ አንድ ሆና የስንትና ስንት ዘመን ታሪክ ያላትና የነጻነት ተምሳሌት አገር ነች። ስለዚህ ሁሉ የሚያቀው ነገር የለም። ሁሉም በየክልሉ መቧደኑ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። የታሪክ ትምህርት እንዳይሰጥ የተደረገው ሆን ተብሎ በየጎሳው እንዲኖር ታልሞ ነው። እኔ የነበርኩበት ሁኔታ በጣም የተለየ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ይዘቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጧል። ለምሳሌ ዶክተር ዐቢይ መጥቶ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለታላቅነት እና ስለአንድነት ሲያወራ መቼም ለሕዝቡ ሁሉ ስሜት የሰጠ ነው። አሁንም ዓላማው እንደዚህ ነው ብዪ እገምታለሁ። የዘር ነገር ቀርቶ ስለኢትየጵያ አንድነት ማውሳት ያስፈልጋል። ይሄ ማለት እያንዳንዱ ስለብሔረሰቡ አይቆርቆር ወይም ደግሞ መብት አይከራከር ማለት አይደለም። ዋናው የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ነው። እንደዚህ ማድረግ አለባቸው ብዬ ነው የማምነው።

ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።

ሌተናል ጄነራል አዲስ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም

Recommended For You