ለአገር ችግር መፍቻ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ ተሳትፎ

መግቢያ

ይህ ጽሑፍ በአገራችን ላይ ችግር በተከሰተ ቁጥር መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ በመተባበር ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አዲስ አለመሆኑን ለማመላከት፣ እንዲሁም አሁን ለተከሰተው ችግር ቀራፊ ፕሮግራሞች ለመጠቆም የተዘጋጀች ናት። ይዘቱ ቢለያይም፣ በታሪካችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮችን ለመፍታት ማህበረሰቡ በጋራ ሲሳተፍ እንደነበረ የሚያበስሩ በታሪክ የተመዘገቡ ተሳትፎዎች አሉ፣ ጥቂት እንደምሳሌነት የሚያገለግሉም ከታች ሰፍረዋል (ዓ.ም የሚል ካልታከለበት በስተቀር በዚህች ጽሑፍ ዘመን የሚጠቀሰው የግሪጎርያን አቆጣጠር ዘመን ነው)።

በእኛ ዘመን ከ1965 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ (ወሎ እና ትግራይ) በተከሰተው ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ጣምራ ችግር ለማለፍ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ (በዚያን ወቅት በኢትዮጵያ አንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነበር የነበረው) በራሱ ተነሳሽነት፣ ችግር መፍቻ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን ፈጽሟል።

ይህንን በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተነሳሽነት የተከናወነ ተሳትፎ፣ አሁን ለተከሰተው ችግር መፍቻ አቅጣጫ ሰጪ መስሎ ስለታየን፣ ዘርዘር ባለ መልክ እንደምሳሌነት በጽሑፉ መደምደሚያ አካባቢ እናቀርበዋለን። ከ1965 ዓ.ም ወዲህ በተደረጉ ጥረቶች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተሳትፎ የጎላ ነበር። በመንግሥት ፕሮገራም የተተገበሩትንም፣ በዘልማድ «የዕድገት በኅብረት ዘመቻ» በመባል የሚታወቀውን እና ከዚያም የ«መተከል እና የጋምቤላ» ዘመቻዎችንም እናወሳለን።

በ1977 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች አካባቢዎች፣ ረሃብ ተከስቶ ነበር። በዚህም ረሃብ መንስዔ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ለሕልፈት እንደተዳረጉ ይገመታል። ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺ ገደማ ቀያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደው ነበር (አራት መቶ ሺ ወደ ሱዳን፣ ሌሎቹ በአገር ቤት)። በዚህ ወቅት ሁለት መቶ ሺ ገደማ ሕፃናት ወላጅ አልባ ሆነው ነበር። ለዚህ ችግር መፍቻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አባላት (ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችች እና መምህራን) በመንግሥት በተዋቀረ ፕሮግራም በመተከል እና በጋምቤላ የሰፈራ ፕሮግራሙን ለማገዝ የዘመቱበት ዘመን ነበር።

ስለሆነም በዚህ ባህላዊ መሰል በሆነው ተግባራችን፣ አሁን በወቅቱ ለተከሰቱ ውስብስብ አንቃራዎችም በጋራ ከሠራን፣ ከችግሮቹ ዘልቀን የማናልፍበት ምክንያት አይኖርም።

ችግር መፍቻ ጥረቶች ከታሪክ አንፃር

በታሪክ እንደተመዘገበው በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት አገር አቀፍ ችግሮች (በተለይ ረሃብ እና ቸነፈር) ይከሰቱ ነበር። አንዳንዴ አገራችን ችግር ለመቅረፍም አቅም የለሽ የሆነችበት ዘመን ነበረ። በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ ችግር ሲከሰት፣ ችግሩን መፍታት ላይ ያተኮሩ ውጤት ያመጡ እንቅስቃሴዎች ተወስደው ነበር። በአንፃሩ፣ ችግር ለመፍታት የተተገበሩት ደግሞ፣ ከተሰማሩበት ተግባር በተጨማሪ (ከታለመው ውጪ)፣ የሌላ ጉዳይ ማስተናገጃ የሆኑባቸው ዘመናትም ነበሩ። ከላይ ለተጠቀሱት ለሁሉም ዓይነት ሁኔታዎች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ጥቂት ዘገባዎች እነሆ።

በአህመድ ኢብን ኢብራሂም (በተለምዶ «ግራኝ መሐመድ» በመባል የሚታወቀው መሪ) በ1535 የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ጦርነትን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ከፍተኛ ረሃብ እና ቸነፈር ተከስቶ ነበር። ለምሳሌ ጦሩ ወደ ትግራይ ሲገባ፣ በአማኻኝ እያንዳንዱ ጦረኛ ሃምሳ ያህል የጋማ ከብቶች ነበሩት። ጦሩ ከትግራይ ለቆ ሲወጣ ግን በአማካኝ ጦረኞቹ ከሁለት በላይ የጋማ ከብቶች አልነበሩዋቸውም። የጋማ ከብቶች እልቂት የተከሰተው የሚላስ፣የሚቀመስ መኖ ስላልነበረ እና በተጓዳኝ የጋማ ከብት በሽታ ተከስቶ ስለነበረ ነበር ይባላል። በዚህ ችግር መንስዔ ብዙ ሰውም አልቋል፣ ከሞቱት መኻልም የአህመድ ኢብን ኢብራሂም ልጅ፣ አህመድ አል ነጋሲ ይገኝበታል። በዚያን ዘመን ወራሪው ኃይል እንኳን ለተቸገሩት ድጋፍ ሊያበረክት፣ በጦሩም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ችግሩን ለመቅረፍ የመሞከርም አቅም አልነበረውም።

በ1611 በሱስኒዮስ ዘመን፣ «ምንን ትታ» (ምን ተረፈ እንደማለት ነው) ተብላ የተሰየመች ወረርሽኝ ገብታ ብዙ ሰው፣ በተለይ በደምብያ ለሞት ተዳረገ። በ 1625 ለዘመናት የዘለቀ ረሃብ ተከስቶ ነበር። በረሃቡ መንስዔ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን፣ በካቶሊክ መነኮሳት ድጋፍ ችግራቸውን መቅረፍ ችለው ነበረ። ከዚያም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር እየጨመሪ ሄዶ ነበር።

በ1702 ረሃብ / ጠኔ ያጎሳቆላቸው አርሶ አደሮች፣ ንጉሡን፣ አፄ እያሱን ካልረዳኸን በረሃብ እናልቃለን፣ እርዳን ብለው ተማጥነውት ነበር። ንጉሡም ችግራቸውን ተገንዝቦ፣ ማንንም ከማን ሳይለይ ነበር ድጋፍ ያበረከተው (ለምሳሌ ነፍሰ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ ቀማኞች፣ እርዳታ ተበርክቶላቸዋል)። የንጉሡን አርአያነት አጢነው መሳፍንቱም ችግረኞችን ከረሃብ ታድገዋቸው ነበር።

በ1789 በጎንደር ረሃብ በተከሰተ ጊዜ ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ በረሃብ የተጠቁትን ወገኖች በጠባቂነት አሰማርተው ድጋፍ አበረከተውላቸው ነበር። መኳንንቱም በደጃዝማች ኃይሉ አርአያነት ተመሳሳይ ድጋፍ ለተራቡ ወገኖቻቸው አበረክተው ነበር።

በአፄ ምኒልክ (1880-1984 ዓ.ም) ክፉ ቀን

 በመባል የሚታወቀው የመከራ ዘመን ትልቁ ረሃብ ተከሰተ፣ የችግሩ ዋና መንስዔ የቀንድ ከብትን ከሞላ ጎደል በሙሉ ለሕልፈት የዳረገው የደስታ (Rinderpest) ወረርሽኝ ነበር። በወረርሽኙ ምክንያት ለእርሻ ተግባር የሚያገለግል የቀንድ ከብት አልነበረም። ችግሩን ለማቅለል፣ አራሹ፣ በፈረስ፣ በበቅሎ እና በአህያ ማረስ ጀምሮ ነበር።

አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ እንደመዘገቡት፣ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት፣ አፄ ምኒልክ ከጳጳሱ ከአቡነ ማቴዎስ፣ እንዲሁም ከታላላቆች መኳንንት እና ሹማምንት ጋር ተመካክረው፣ አገር አቀፍ ምሕላና እግዚኦታ ተያዘ። የሃይማኖት ነገር በጣም የማይጫናቸው ምኒልክ፣ በእግዚኦታ ብቻ እህል ረድኤት እንደማይወርድ በማመን፣ እግዚኦታው ሳይቋረጥ፣ የእርሻ ከብት ቢያልቅ በቁፋሮ እህል መዝራትና ማምረት እንደሚቻል ለሕዝባቸው አስገነዘቡ። ራሳቸውም ምሳሌ በመሆን በእጃቸው ዶማ ይዘው እየቆፈሩ፣ ከላይ እስከታች በማናቸውም ደረጃ የሚገኘው ሁሉም (መኳንንቱን እና ሹማምንት ይጨምራል) እንዲቆፍረ አዘው፣ በዚያን ዓመት ታላቅ የቁፋሮ እና እህል መዝራት ተግባራት ተከናወነ። በተጨማሪም እህል ማደል ተግባራትም በሰፊው ተካሂዷል።

አለቃ ተክለሥላሴ የሚባሉ የጎጃም የአንድ ደብር አለቃ፣ ስለ እህል ማደል የሚከተለውን አትተዋል። «…ዳግማዊ ምኒልክ በጉዞው (በየአምራቹ ገበሬ) ቤት ወታደር ሰደደ። ለባለ እህሉ በነፍስ ወከፍ የአንድ ዓመት (እህል) እየተወለት ትርፉን በደብዳቤ አግብቶ (ደረሰኝ እየሰጠ) ተበድሮ ለደሃው ናኘው። ከዚህ በኋላ (የደበቀው ሁሉ) ወታደር ከሚዘርፈንስ ገበያ ብንሸምተው ይሻለናል እያለ ገበያ አወጣው። ይህን ጊዜ እህል በገበያ ተረፈ… » ።

«የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ»

በቅርብ ዘመን ከተካሄዱት የችግር መፍቻ ዘመቻዎች አንዱ «የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ» ነበር። በዚህ ፕሮግራም ሁለታችንም ተሳታፊዎች ነበርን (ያየህይራድ ቅጣው በዘመቻው ጠቅላይ መመሪያ በጤና ዘርፍ ኃላፊነት፣ ሽብሩ ተድላ የእንዳ ሥላሴ/ትግራይ/ ምድብ ጣቢያ የአስተዳደር ኃላፊ በመሆን አገልግለናል)።

«የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ» ጽንሰ ሃሳብ ለደርግ ያቀረበው በወቅቱ የደርግ ዕቅድ እና የምርምር ኮሚቴ ሰብሳቢ. የነበረው ብርሃኑ ባይህ (ሌ/ኮሎኔል) ነበር። «ያልታሰበው» በሚል ርዕስ በብርሃኑ ባይህ የተደረሰ መጽሐፍ እንደሰፈረው፣ ደርግ በተመሠረተ በወራት ውስጥ ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ እና ዋናው «የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ» ነበር። ደራሲው እንደነገረን ሀሳቡን ያቀረበው የደራሲው ታናሽ ወንድም ፍሥሃ ባይህ ነበር።

በዘመቻው የታቀዱት ሥራዎች ከሞላ ጎደል ትምህርት ነክ ነበሩ፣ «የኢትዮጵያ ትቅደምን» መመሪያ ማስተማር፣ መሠረተ ትምህርት ለገጠሩ ማህበረሰብ ማስተማር፣ ለገጠሩ ማህበረሰብ መሠረታዊ የጤና ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ስለ ተሻሻለ የኑሮ ዘዴ ማስተማር፣ የኅብረት ሥራ ማህበራትን ማደራጀት፣ ስለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስተማር፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን፣ድልድዮችን፣ የመጠጥ ውሃ «ኢንፍራሰተራከተር» መገንባት፣ ወዘተ ነበሩ።

የዕድገት በኅብረት ዘመቻ ማስተባበሪያ ቢሮ አምስት ኪሎ የቴክኖሎጂ ፋካልቲ ነበር። በዘመቻውም አስተዳደር መዋቅር ከወታደሮች በተጨማሪ ጥቂት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ነበሩ።

እቅዱ ወደ ተግባር ሲመነዘር፣ ዘመቻው ያካተተው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ የቴክኒካል ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በሙሉ ነበር። በተጨማሪ የእነዚህ የሁሉም ትምህርት ተቋማት መምህራን የዘመቻው ተሳታፊ ነበሩ።

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ዘመቻው ብዙ ዘርፎች ነበሩት። በወቅቱ አብዮታዊ ሁኔታ ጋር በተዛመደ መንስዔ ብዙ ውጣውረድ ቢኖርበትም፣ በዘመቻው ጥሩ ጥሩ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ያህል፡ በመሬት ይዞታ ፕሮግራም በኩል፣ አዋጁን በሰፊው ከማስተዋወቅ ጀምሮ፤ የገበሬ ማህበራትን በማቋቋም፣ ዘማቾች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በመሠረተ ትምህርት በኩል፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአሥራ አምስት ለማያንሱ ቋንቋዎች የማስተማሪያ መሣሪያዎች ተዘጋጅተው ተሰራጭተዋል። የተዘጋጁት ሰነዶች በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ የማህበረሰብ አባላት መማሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በኋላ ለተመሠረተው ‘የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ’ ጥሩ መነሻ ሆኖ አገልግሏል። በመሠረተ ልማት ፕሮግራም፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የጤና አገልግሎት ባልነበሩባቸው መቶ፣ ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ጤና ኬላዎች ተሠርተዋል።

በጤናው ፕሮግራም፣ የዘማቹን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር፤ ከየዘርፉ (ሕክምና፣ ነርስ፤ ፋርማሲ ወዘተ) የተውጣጡ ዘማች መምሀራንን በማስተባበር፣ ከዘመቻው ጠባይ ጋር የተዛማደ የማስተማሪያ ጽሑፎች ታትመው እና ተሰራጭተው፣ ዘማቹ በዘመተባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰብ አባላት የጤና ትምህርት እንዲበረከት አስችለዋል። እንዲሁም ወሳኝ ለሚባሉ በሽታዎች ክትባቶች ተሰጥተዋል። በባሀላዊ/አገር በቀል ሕክምና ላይ ዳሰሳዊ ጥናት ለማካሄድ እቅድ ወጥቶ በዛ ያሉ እጽዋት ተሰብሰበው፣ ለበለጠ ጥናት «ለኢንስቲትዩቱ ፓስተር» ተበርከተዋል።

አንድ ሺ የልምድ አዋላጆችን ለማሰልጠን እቅድ ተዘጋጀቶ፣ ብዙ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የማስተማሪያ መጽሐፍ ታትሞ፤ ከዩኒሴፍ አንደ ሺ የማዋለጃ ቋቶች (“ደሊቨሪ ኬትስ”) ተገኝተው፣ ስልጠናው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል እንዲከናወን ተደርገዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣አዲስ ለተሠሩት ጤና ኬላዎች፣ ከሁለት መቶ በላይ የጤና ረዳቶች ለማሰልጠን እቅድ ወጥቶ፤ መጽሐፍ ተዘጋጀቶ፣ ስልጠናው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ተጀምሮ ነበር።

ለምሳሌ ያህል የተጠቀሱት ተግባራት እንደሚያመለከቱት፣ የዩኒቨርሲቲው/የከፍተኛ ትምህርት ኅብረተሰብ በአግባቡ ከተንቀሳቀሰ፣ በትንሽ አስተባባሪ ኃይል፣ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ተግባር ማከናወን እንደሚችል አመልካች ነው። ለምሳሌ፣ የጤናው ፕሮግራም አስኳል አስተባባሪዎች አራት ብቻ [(ዶ/ር ያየህይራድ ቅጣው (ከህክምና ፋክልቲ፣ ኃላፊ)፤ ዶ/ር ሙላቱ ጆቴ (ከፋርማሲ ፋክልቲ፤ ኤርሚያስ ገ/እግዚአብሔር (ከጎንደርጤና ኮሌጅ)፤ ዶ/ር ተስፋየ ገ/አብ (የክሊኒክ ኃላፊ)] ነበሩ።

ሆኖም ዘመቻው አልጋ በአልጋ አልነበረም፣ ችግሮችም ተከስተው ነበር። በመጀመሪያ የዘመቻ ጥቂት ወራት በዘመቻ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይዘት ያለው እንቅስቃሴ አልነበረም። አንዳችን (ሽብሩ ተድላ) በዘመትንበት ጣቢያ በመጀመሪያ ሰሞን የተከሰቱት ችግሮች፣ ምቾት፣ ምግብ፣ የዘመድ ናፍቆት፣ ጤንነት፣ እና ተመሳሳይ ችግሮች ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ። ከወራት በኋላ

 ፖለቲካ ይዘት ያላቸው ተግባራት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። በትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ እንደ ሥላሴ አውራጃ፣ የትግራይ አንዳንድ ወጣቶች የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት በመቀላቀል፣ እንዲሁም ኤርትራውያን ሻብያን በመቀላቀል፣ ከዘመቻው ዓላማ ውጪ ተሰማሩ። በጣም ጎልቶ የመጣው ግን ኢሕአፓ በዘመቻ ጣቢያዎች የዘረጋው ፖለቲካ እንቅስቃሴ ነበር። በዘመቻው ወቅት በተለይ በደቡብ የአገራችን ክፍሎች፣ በመንግሥት እና በዘማቾች፣ አንዲሁም በዘማቾች እና በገጠር የመሬት ባለሀብቶች መኻል ግጭት በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ለብዙ ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኖ ነበር።

የመተከል እና የጋምቤላ ዘመቻዎች

በመንግሥት አስተባባሪነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች የጐጆ ቅለሳ ዘመቻ በጋምቤላ (የባሮ ግብረ ኃይል)፣ በመተከል (የዓባይ ግብረ ኃይል) የተሰማሩበት ዘመን ሲሆን፣ ዘመቻው የተካሄደው በ1977 ዓ.ም ክረምት ላይ ነበር። ስለ ዘመቻው የቀረቡ ሪፖርቶች እንደገለጡት (የዓባይ እና የባሮ ግብረ ኃይሎች) የዘመቻው ምክንያት በአጭሩ እንደሚከተለው ነበር።

«በአየር ንብረት መለወጥ ሰበብ፤ በእናት አገራችን ከፍተኛ እና አስከፊ ድርቅ ደረሰ፣ ድርቁ የአያሌ ወገኖቻችንን ሕይወት አጠፋ፤ በሕይወት የተረፉትም ከቤት-ንብረታቸው ተፈናቅለው ሰቆቃ የሞላበት ኑሮ እንዲኖሩ ተገደዱ። ለረጅም ዘመናት ሲያርሱ የኖሩት ለም የእርሻ መሬት አፈሩ ተሟጦ አለቀ፣ በየሜዳው ሲፈስሱ የነበሩ ጅረቶች እና ወንዞች የውኃ ይዘታቸው ቀነሰ፤ ለዘመናት ምድሩን ሸፍነውት የነበሩ ደኖች ተመንጥረው አለቁ፤ እንዲህ ባሉት አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ውጤቱ በጣም የከፋ ሆነ። በድርቅ በተመቱት አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ አርሶ አደሮች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ፣ በየሜዳው እንደቅጠል ረገፉ፤ በሕይወት ለመትረፍ የበቁትም ለዓመታት የኖሩባቸውን ቀበሌዎች እየለቀቁ እህል ፍለጋ ተሰደዱ፤ ሕፃናት፣ አዛውንት እና ወጣት ወገኖቻችን የሞቀ ከነበረ ቤት እና ንብረታቸው እየተፈናቀሉ፣ የሰቀቀን እንባ እያፈሰሱ የወገኖቻቸውን እርዳታ በመሻት ወደ አቅራቢያ ከተሞች ተጓዙ።

ይህን ተፈጥሮ ያስከተለውን ጉዳት ለመቋቋም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ እና አብዮታዊው መንግሥት ከፍተኛ እቅድ አውጥተዋል፤ መርሐ ግብርም ተቀይሷል፤ ይህም የሰፈራ መርሐ ግብር ነው። በብዙ ሺ የሚቆጠር ወገንን ከሞት አፋፍ መንጥቆ አዲስ ሕይወት እንዲመሠርት መልሶ የማቋቋም ሥራ ከፍ ያለ ጥረት የሚሻ፣ በየአቅጣጫው ርብርቦሽን የሚጠይቅ ነው። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር፣ የአብዮታዊ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የካቲት 2፣ 1977 ዓ.ም. ባደረጉት ብሔራዊ ጥሪ መሠረት የዩኒቨርሲቲው ኅብረተሰብ እንዲዘምት ተወስኗል» የሚል ነበር»።

በመንግሥት የተሰየመው የዘመቻው መዋቅር በጋምቤላ የባሮ ግብረ ኃይል፣ በመተከል የዓባይ ግብረ ኃይል ነበር። ይህችን ጽሑፍ ካቀረቡት አንዱ (ሽብሩ ተድላ) የዓባይ ግብረ ኃይል ሥራ አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበር። የኮሚቴው አባላትም የተለያዩ ድርጅቶች ወኪሎች ነበሩ፤ አዝማቾች ማንን ማንን እንደሚወክሉ በቅንፍ ተቀምጧል፣ ሽብሩ ተድላ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቱን/ ሰብሳቢ)፣ ታደለ ዓዳሙ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሠረታዊ ድርጅት አንደኛ ፀሐፊን)፣ ጆርጅ ተሰማ (የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽንን)፣ መኮንን ከበደ (የትምህርት ሚኒስቴርን)፣ አሰፋ ተፈሪ (የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን ማህበርን)፣ ግርማ ኤጀሬ (የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አብዮታዊ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበርን- የአኢወማ ኮሚቴ)፣ፍቅርተ አለማየሁ (የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሴቶች ኮሚቴን)፣ ዘሪሁን አስፋው (የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የውይይት ክበብ አመራርን)፣ ግርማ ሐለፎም (የግብረ ኃይል ኢንስፔክሽን ሰብሳቢ)፣ ፍስሐ ኃይሌ (የግብረ ኃይል የዘማቾች ጉዳይ ማስተባበሪያ) እና ጥላሁን ወርቅነህ (የግብረ ኃይል የመሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ሰብሳቢ) ሆነው ተሰይመው ነበር። ተመሳሳይ መዋቅር በጋምቤላም ተመሥርቶ ነበር።

በጋምቤላ እና በመተከል በተደረጉ የከፍተኛ ትምህርት አባላት ሊሠሯቸው የታሰቡ ቤቶች ስሌት የተመሰረተ (የስሌት መነሻ የሆነው) ቀደም ብሎ ባህር ዳር ከተማ ከነበረ የትምህርት ተቋም የዘመቱ ተማሪዎች እና መምህራን በመተከል አካባቢ በሠሩት ሥራ ውጤት ላይ ተመስርቶ ነበር። ሦስት መቶ ገደማ ሰዎች ዘምተው በሠሯቸው ጐጆዎች ቁጥር ላይ ተመስርቶ 10,000 ሰዎች ሊሠሩ የሚችሉት ተሰልቶ ነበር የተዘመተ።

በዚህ ስሌት ወደ መተከል የዘመቱት፣ ዘመቻው ሲጠናቀቅ፣ አርባ ሺ ጎጆዎች ሠርተው ያስረክባሉ ተብሎ ነበር፣ ሆኖም ዘመቻው ሲጠናቀቅ የዓባይ ግብረ ኃይል ዘማቾች ሠርተው ያስረከቡ አርባ ሺ ጐጆዎች ሳይሆን፣ 18,372 (አስራ ስምንት ሺ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት) ጐጆዎችን ብቻ ነበር። ጐጆዎችም ልዩ ስም ተሰጥቷቸው ነበር፤ «አትደገፉኝ» የሚል። ዘመቻው የተካሄደ በአማካኝ ከሰኔ 15 እስከ ነሐሴ 22፣ 1977 ዓም ድረስ ሲሆን፣ ለሁለት ወራት ያህል ነበር ማለት ይቻላል።

መተከል በነበሩ ጣቢያዎች አካባቢ መጀመሪያ ሰሞን ጐልተው የወጡ ከመኖሪያ ጋር ተያይዞ ለዘማቹ የድንኳን እጥረት፣ ጥበት፣ የዘማቾች የአጠቃላይ የሥነ ሥርዓት አልባነት፣ ተስፋ የመቁረጥ ዓይነት ግድየለሽነት፣ ሆኖ ተከሰተ። ችግሩ እየተለመደ ሲሄድ እዚያ ቦታ ከመገኘት ጋር የተቆራኜ የበሽታ፣ የአደጋ ክስተት እየጐላ መጥቶ ነበር።

የዘመቻው አሠራር በጠቅላላ ከዘማቾች፣ ከመደበኛ የሥራ ስምሪት በጣም የተለየ ስለነበረ፣ ዘማቾቹ ያካበቷቸው የሥራ ልምዶች እና የዘመቱበትን ሥራ ማጣጣም በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። በተጨማሪ ለመደበኛ ፍላጐቶች ማሟያ (ምግብ፣ መጠጥ፣ ወዘተ.) አቅርቦቶች ከፍተኛ እጥረት ነበረ። በጣም አፍጥጦ የመጣው ችግር

 በመጠጥ ውኃ ዙሪያ ነበር።

በመተከል ከውሃ ቀጥሎ ትልቅ ችግር የነበረው የዳቦ አቅርቦት ነበር፤ ከ10 ሺ ሰው በላይ በቀን ለእያንዳንዱ ቢያንስ ሦስት ዳቦ ማቅረብ ቀላል አልነበረም (የእንጀራ አቅርቦት አልነበረም)። መጀመሪያ በአውራ ጐዳና ካምፕ ዳቦ መጋገሪያ ቤት ቢጀመርም፤ ሰላሳ ሺ ዳቦ የሚበቃ ቡሆ በየቀኑ ማቡካት፣ ማዘጋጀት በነበረው መሰናዶ (ቅድመ ዝግጅት) የማይታለም ነበረ።

በመጀመሪያዎቹ የዘመቻ ቀናት አካባቢ ከሌላ አቅጣጫ ሌላ አዲስ ችግር ተከሰተ። የፓዊ ወጣት ዘማቾች፤ በተለይ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ (የቴክኖሎጂ ፋካልቲ) ተማሪዎች የነበሩ፣ ከእነሱም ውስጥ ከቤተሰባቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰንቀው የዘመቱ፣ ካቲካላ እንደ ለስላሳ መጠጥ መጠጣት ጀመሩ። በሁለት ሳምንት ውስጥ፣ ከስድስት ያላነሱ ህሊናቸውን እየሳቱ ክሊኒክ ተኙ፤ ሕይወት ማቆያ ምግብም በጉሉኮስ መልክ መስጠት ተጀመረ። ለአደጋ ጊዜ እንዲያገለግል የመጣው ጉሉኮስ፣ ካቲካላ የጐዳቸውን ተማሪዎች ማገገሚያ፣ ማቆያ፣ መሆኑ የዘመቻውን አላፊዎች ስጋት ላይ ነበር። እንዲሁም በመልስ ጉዞ አውቶቡስ ተገልብጦ ለብዙ ወጣቶች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆነ።

በዘመቻው ወቅት ብዙ ሰው ሆድ ብሶት ነበር። የመተከል የጐጆ ሥራ ዘመቻ፤ ብዙ ሰው የተማረረበት፣ ከሰውነትም በአካልም ሆነ በአስተሳሰብ ብዙ ፈተና የደረሰበት ነበር፤ ያልተሟላ ምግብ፣ የተበከለ መጸዳጃ፣ ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር፣ ከዝናብ የማያስጥል መጠለያ፣ በክረምት ከቦታ ቦታ ረጅም የእግር ጉዞ፣ ከሥራ ጋር ተደራርቦ ብዙ ችግር ያደረሰ ዘመቻ ነበር።

“ዩፍሮ”፣ በየዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተጠንስሶ ተግባር ላይ የዋለ ተሳተፎ

በ1965 ዓም በሰሜን ኢትዮጵያ ረሃብ ተከስቶ፣ ከ40 እሰከ 80 ሺ የሚገመት ሰው በረሃብ እንዳለቀ (ሞተ) ይገመታል። ይህን አሃዝ ከፍ ባለ መጠን የመዘገቡም የውጭ ዘጋቢዎች አልጠፉም። ይህ ረሃብ እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ በኢትዮጵያ የንጉሠ ነገሥት አገዛዝ አከተመ። ለዚያም ለችግር መቅረፊያ የሚሆን የዩኒቨርሲተ ማህበረሰብ ፕሮግራሞች ነድፎ፣ ተቋም መሥርቶ፣ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበረ።

አሁን ለተከሰተው አሳሳቢ እና ውስብብ የአገር ችግር በግርድፉም ቢሆን ለችግር መፍቻ በምሳሌነት የሚያገለግለው “ዩፍሮ” ነው። በ1965 ዓም በተከሰተው ችግር፣ በዘልማድ “የወሎ ረሃብ” በሚል የሚታወቀው በተከሰተ ወቅት፣ ከህዝባዊ እንቅስቃሴ ወዘተ በተያያዘ፣ በተማሪውና በመምህራን መካከል፣ በየቀኑ አዲስ ጉዳዮች ይከሰቱ ነበር። ሂደቱን ማውሳት አሁን ለገጠመን ዓይነት ችግር ቀራፊ ተሳትፎ ለልምድ መቅሰም ምሳሌነት ያገለግል ይሆናል ብልን አንናምናለን።

የወሎ ረሃብተኞች ለቀናት ተጉዘው አዲስ አባበ ሲደርሱ ወደ ከተማ እናደይገቡ በፖሊስ ታገቱ። ይህን ጉዳይ የሰሙ ሁለት የዩኒቨርሲቲው መምህራን (መስፍን ወልደ ማርያም እና አብርሃም ደመወዝ) ወደ ከተማው ሰሜን ምሥራቅ መግቢያ (ኮተቤ) ሄደው፣ የአገር ቤት ስደተኞችን ሁኔታ ተመለከቱ። ረሃብተኞቹን በጎበኙበት ጊዜ፣ ፖሊስ የመኪናቸውን ታርጋ ብቻ መዝግቦ ካለብዙ ውጣ ውረድ መምህራኑ ወደ ከተማ ሊመለሱ ቻሉ።

ከዚያም በጌታቸው ኃይሌ ጥያቄ፣ አብያተ ክርስቲያን ጉባዔ በተገኘ ድጋፍ፣ አንድ “ሴስና” አይሮፕላን ተከራይተው፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደመወዝ እና አሉላ አባተ (ሁሉም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ነበሩ) ወደ ኮመቦለቻ ተጓዙ። እዚያ ሲደርሱም ከቤተ ክህነት በተገኘ “ላንድሮቨር” መምህራኑ ሃይቅን፣ መርሳን. ወርጌሳን የወለድያ እና የባቲን አካባቢ ሁኔታ ተመልከተው ተመለሱ። በጉዞውም ላይ ብዙ ችግርን አመላካች የሆኑ ፎቶግራፎች አንስተው ነበር።

ከጉብኝቱ በኋላ፣ በጅኦግራፊ ትምህርት ክፍል አሰተባበሪነት፣ ፎቶግራፎቹ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እይታ ቀረቡ። ጉዳዩም በደጃዝማች ካሳ ወልደ ማርያም አማኻኝነት (በወቅቱ የግብርና ሚንስትር) ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም፣ የምክር ቤቱ አባል የነበሩት በተለያዩ ምክንያቶች ለችግሩ ትኩረት ሳይሰጡት ቀሩ። በተጓዳኝ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለችግረኞች ድጋፍ ሊያበረክቱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ጀመረ።

ተማሪዎች ለተቸገረው ወግነው ቁርሳቸውን አበረከቱ፤ መምህራን በበጎ ፈቃደኝነት ገንዘብ ማዋጣት ጀመሩ። በመጀመሪያ ዩኒቨርሲቲው በመምሀራን ማህበር አማካኝነት አሥር አሥር ብር እንዲዋጣ ተደርጎ፣ ብዙ መመህራን ይህንን ግዴታ ተወጡ። ከዚያም መምህራኑ ደመወዛቸውን በመቶ አሥር (10%) ለማዋጣት ቃል በገቡት መሠረት ገንዘብ መዋጣት ተጀመረ። ሆኖም በዚህ ተግባር ያልተሳተፉ መምህራን እንደነበሩም መዘንጋት የለበትም።

ገንዘብ ሰብሳቢ ኮሚቴ የተቋቋመው በሚያዚያ ወር 1965 ዓም ሲሆን፣ በዚያው ዓመት በሰኔ ወር ገደማ ኮሚቴው 80 ሺ ብር (ሰማኒያ ሺ ብር) ለመሰበሰብ ቻለ። የተማሪዎች ቁርስ በገንዘብ ተሰልቶ (ብር 41,974.80) እንደ ተማሪዎች መዋጮ ተወሰደ። ሂደቱ ውስብስብ እየሆነ ስለሄደ፣ ለፕሮግራሙ ቋሚ መዋቅር እንደሚያስፈልግ ታምኖበት፣ በሐምሌ 1965 ዓ.ም የዩኒቨረሲቲውን መምህራን፣ ተማሪዎች እና ሠራተኞችን ያካተተ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከተከሰተው ችግር መፍትሄ ላይ ያተኮረ አንድ ድርጅት ተቋቋመ። ያም ለረሃብተኞች ድጋፍ ሰጭ (University Famine Releief Committee/ UFRC) ሲሆን፣ በድርጅቱ አካባቢ የተሰባሰቡ መምህራን፣ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ፣ በራሳቸው ወጭ ድርጅቱን አገልግለዋል። የድርጅቱ ቢሮ ስድስት ኪሎ ግቢ፣ ሂሳብ ክፍል አጠገብ ነበር የሚገኘው።

 በዚህ ኮሚቴ፣ የኮሚቴው ሊቀመንበር አብርሃም ደመወዝ የነበረ ሲሆን፣መምህራኑ በመስፍን ወልደ ማርያም፣የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በካሣ ጋሻው በዛ (የዩነቨርሲቲው የሂሳብ ሹም)፣እና ተማሪዎች በገብረ እግዚአብሄር ሃብቱ ተወክለው ነበር።

በወቅቱ የተሰበሰበው ገንዝብ በሥርዓት እንዲተዳደር፣ በተማሪዎች፣ በአስተማሪዎች እና በዩነቨርሲቲው አስተዳደር ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ይሀም ሃሳብ በዩነቨርሲቲው አስተዳደር ተቀባይነት አግኝቶ፣ የባንክ ሂሳብ ለመክፈት ተቻለ፣ ስለሆነም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በሂሳብ ቁጥር 775 አንድ የባንክ ሂሳብ ተከፈተ። በአንፃሩ፣ ይህንኑ ሂሳብ በተመለከተ፣ ዩነቨርሲቲው ነጥሎ ለማስተናገድ እንዲችል፣ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሂሳብ ተከፈተለት (ሂሳብ ቁጥር 2327700000)።

ከዚያም የገንዘብ ሰብሳቢ አና የምግብ እህል ግዥ ኮሚቴ ተቋቋመ። የእህል ግዥው ኃላፊነት ለአቶ ከበደ ሥመኝ ተሰጠ። በከበደ ሥመኝ አስተባበሪነት፣ የመጀመሪያው የእህል መሸመት በብር 67,000.00 (ስድሳ ሰባት ሺ ብር) ተከናወነ። የዚህ ኮሚቴ አባላትም አየለ ትርፌ፣ መስፍን ወ/ማርያም፣ አብርሃም ደመወዝ (ሁሉም መምህራን)፣ ዬነቨርሲቲው ተወካይ እንዲሁም አሥር ተማሪዎች አባል ተደረገው ነበር። የተማሪዎች ተወካይ ከነበሩት አንዱ ታዬ አሰፋ ነበር (በወቅቱ የአንደኛ ዓመት የስድስት ኪሎ ተማሪ) የነበረ፣ እንዲሁም ከዘመናት በኋላ በኢሕአዴግ ተባረው ከነበሩት የዩኒቨርሲቲ መምህራን አንዱ የሆነው ምሁር ነው።

ከዚያም ዩኒቨርሲቲው ስለተዘጋ ችግር ተፈጠረ። ከምግብ ግዥ እና ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ በተጨማሪ፣ አንድ ሌላ ኮሚቴ ተቋቋመ። በዚያን ጊዜም ኮሚተውም መምህራንን የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ሠራተኞች ያካተተ ነበር። አባላቱም ንጉሤ አየለ፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደመወዝ፣ ያየህይራድ ቅጣው፣ ዓለማየሁ መላኩ፣ ኃይለ ገብረዔል ዳኜ፣ ፋሲል ገብረ ኪሮስ፣ አብደላ አብድልናስር፣ ናርዶስ ተሰማ፣ ፍቅሬ መርዕድ፣ ካሣ ጋሻው በዛ፣ ከበደ ስመኝ.፣ ሙሉጌታ ኢታፋ፣ መንግሥቴ እምሩ እና ይተጠቁ ነጋ ነበሩ።

ይኸም ኮሚቴ፣ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፎ ነበር። ባጭር ጊዜ መስተናገድ የነበረበት የምግብ እና የልብስ ጉዳይ ነበር፣ ከዚያም ለውሃ አቅርቦትና ለገጠር መንገድ ሥራ፣ የረጅም ጊዜው እቅድ ሕክምናን (ጤናን) ያካተተ ነበር።

ረሃብ ከመቅረፍ ባለፈ ይዘት፣ ችግሩን በተሻለ መንገድ ለመፍታት፣ በተጨባጭ ለመርዳት ወደ መደራጀት፣ ዝግጅት ተጀመረ። በዚህ ሂደት፣ ሁሉም ድርጅት/እንቅስቃሴ አሻራውን ለማሳረፍ ይጥር ነበር። በሂደቱ፣ ጎምቱዎቹ መምህራን (ለምሳሌ መስፍን ወ/ማርያም፤ አብረሃም ደመወዝ፣ ወዘተ) እርስበርስ ወዲህ ወዲያ መጓተት ጀመሩ። ከዚያም በሚያዚያ ወር 1966 ዓም ሁለት ዐቢይ ተግባራት ተከናወኑ። አንዱ የማህበሩ ስብስብ ስያሜ ነበር፣ ያም ረሃብ መታደግ ድርጅት (University Famine Relief Organization/ UFRO)፣ ወደ ረሃብ መታደግ እና መልሶ ማቋቋም ድርጅት (University Famine Rerelief and Rehabilitation Organizatio/ UFRRO) መቀየሩ ነበር።

ሁለተኛው ተግባር ወጣት መምህራንን ያካተተ፣ አዲስ ጠንከር ያለ ኮሚቴ ማቋቋም ነበር፣ ስለሆነም አዲስ ኮሚቴ ተቋቋመ። ያየህይራድ ቅጣው (የዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋካልቲ መምህር/ ሊቀመነበር)፣ ኤርምያስ ዳኜ (የዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋካልቲ የኬሚስተሪ መምህር/ ጸሐፊ)፣ታየ አበጋዝ (ሕዝብ ግንኙነት ተግባር)፣ እና ናርዶስ ተሰማ (ገንዘብ ያዥ) ሆነው ተሰየሙ። በተጨማሪ በጣም ለአጭር ጊዜ ፕሮፌሰር ስቬን ሩቢንሰን እና ዶ/ር ዴቪድ ቢር የኮሚቴው አባል ሆነው ተመርጠው ነበር።

ጠቅለል ብሎ ሲታይ፣ የድርጅቱ አላማ፣ የዩኒቨርሲቲዉን ህብረተሰብ (መምህር፤ተማሪ፣ወዘተ) በማስተባበር፤ ከህብረተሰቡና ከሌሎች በሚገኝ ጥሪት (ሪሶርስ)፣ በድርቅ/ረሃብ ለተጎዳዉ እርዳታ ማድረስ እና መልሶ ማቋቋም ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰው ተማሪው ከምግቡ፤ መምህሩ ከደመወዙ በመቀነስ፣ እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች (ለምስሌ ኦክስፋም) የማይናቅ ድጋፍ ተሰባስብዋል። ዋናው ግን፣ ለጥናት፤ ለማቀድ፤ ለመቀስቀስ/ማነሳሳት እና በተወሰነ ደረጃ ለመተግበር፣ በበጎ ፈቃደኛነት ለማሰማራት፣ የዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል መኖሩ ነበር። ኋላ ላይ፤ የዕድገት በህብረት ዘመቻ ሲጀመር፣ የተወሰኑ ዘማቾች ለድርጅቱ ስለተመደቡ፣ ተጠናከሮ መቀጠል ተችሏል።

በዚሀም፣ ከእለታዊ ደራሽ እርዳታ ባሻገር፣ ህዝቡን መለሶ የማቋቋምና የተወሰኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተክናውነዋል። ለምሳሌ፣ በወሎ፣ ዞብል ተራራን ተሻገሮ ወደ ቆላው (አፋር) የሚወስደው መንገድ የተቀየሰው እና ጥርጊያ መንገድ የተሠራለት፣ በዩፍሮ አስተባባሪነት፣ በምህንድስና ኮሌጅ ተማሪዎች እና መምህራን ነበር። በጎሊና፣ አፋር፣ ወንዙን በመጥለፍ (ጋቢዮን)፣ ሀብረተሰቡ በመስኖ ግብረና የማሳተፍ ውጤታማ ሥራ ተጀምሮ ነበር፣ ግን በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ተቋርጥዋል። በቦረና ብዙ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ለብዙ ዓመታት አርብቶ አደሩን ታድገዋል።

የቸነፈርን አስከፊነት በጥቂቱም ቢሆን ለማስገንዘብ ከዚህ ጽሑፍ አበርካቾች አንዱ (ሽብሩ ተድላ)፣በዩፍሮ (UFRRO) ተልእኮ በጥቅምት 1967 ዓ.ም ለሁለት ሳምንታት ያህል ወደ ወሎ ሄዶ፣ ድርቅ በደረሰባቸው አካባቢዎች፣ በሚሌ፣ ኤሉሃ፣ ዞብል፣ ፎኪሳ፣ ተኩለሽ፣ አላማጣ፣ ቆቦ፣ እየተዘዋወረ የሰማውን ያየውን በሪፖረት መልክ ለዩፍሮ ጽ/ቤት እቅርቦ ነበር። ያን ጊዜ የተገነዘበው እና የሰማው ሁሉ እንደ ህልም ነው አሁን የሚያስታውሰው። ከሪፖርቱ የተቀነጨበ

 ጽሑፍ ከታች ቀርቧል።

በመስከረም 1967 ዓ.ም በፎኪሳ አካባቢ (ወሎ) አንድ ወጣት እናት፣ ቤት ውስጥ የነበረ ተባይ እና የአይጥ መንጋ እንቅልፍ ሲነሳት፣ ሁለት ህፃን ልጆቿን (የሁለት እና አምስት አመት እድሜ) ይዛ፣ ከቤት ውጭ ለማደር ተገደደች። ሌሊት እግሯን ጅብ ሲነክሳት ነቃች፣ የአምስት ዓመት ልጇን ከአጠገቧ አጣችው፤ ጅብ ይዞባት እንደሄደ ተረዳች። ሲነጋ በአካባቢው የተገኘ የተበጣጠሰ የአምስት አመቱ ሕፃን አስከሬን ነበር። ይኸ በሆነ በሁለተኛ ቀን፣ ሌላ ሰፈር፣ ከቤት ውስጥ ጅብ ገብቶ፣ የሌላ ቤተሰብ የስድስት አመት ልጅ በላ ተባለ።

ጉዳዩን ከባዮሎጂ (ከስነሕይወት) አንፃር ሪፖርት አቅራቢው ተመልክቶ፣ ከረሃብ ተጨማሪ ሆኖ የተከሰተው ችግር፣ እንዴት ተከሰተ ለሚለው አስተያየት አስፍሮ ነበር። የድርቅ መንስዔ የዝናብ እጥረት ነው፤ የዝናብ እጥረት በሚከሰትበት ጊዜ፣ ማሳ ላይ ያለ ቡቃያ ምርት አይሰጥም፤ አዝመራው ማሳ ላይ እንዲሁ ምርት አልባ ሆኖ ይቀራል። ያ ምርት አልባ ማሳ በአካባቢ ለሚኖሩ የአይጥ ዘር እና የዝንጀሮ ዘር ዋና የምግብ አውድማ ይሆናል፤ ያም የአይጥን ብሎም የዝንጀሮ መራባትን ያስከትላል።

ድርቅ ሲኖር የከብት መሰማሪያዎች በቂ መኖ አይኖራቸውም፤ ከፍተኛ የውሃ እጥረትም ይከሰታል፤ ስለሆነም ትላልቅ የቀንድ ከብቶች በብዛት መሞት ይጀምራሉ፤ በመጀመሪያ ጥጆች ይሞታሉ፤ ከዚያም ላም በሬ። በዚህ ክስተት የሞተ ከብት ለጅብ በገፍ የቀረበ ድግስ/ምግብ ይሆናል፤ ብሎም ለጅቦች መራባት አመቺ ሁኔታን ያስከስታል፤ ጅቦችም ይራባሉ። አገራችን በብዛት የሚገኘው የጅብ ዘር እርግዝና የሚፈጀው ከአራት ወር ያነሰ ጊዜ ሲሆን፣ አንድ እናት ጅብ በዓመት ሁለት ጊዜ ልትወልድ ትችላለች፤ ያውም መንታ መንታ፣ ያ ሁኔታ የአካባቢውን የጅብ ቁጥር በጣም ከፍ ያደርገዋል።

እንግዲህ የድርቅ (የዝናብ እጥረት) መከሰት ለአይጥም ለጅብም ለዝንጅሮም ተመቸ (በጀ)፣ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም። ምክንያቱም ከዓመት በኋላ ለጅብም ቢሆን የሚላስ የሚቀመስ አይኖረውም፤ ለአይጥም ለዝንጀሮም እንዲሁ። በአይጥ ወደ ቤት ወደ ጐጆ ዘመቻ፣ በጅብ ሰው መብላት እና በቀን ማደን ለዚህ ይሆናል የተከሰተ፤ የምግብ ፍላጐት ለማሟላት በሚል ድምዳሜ ሪፖርት ቀርቦ ነበር። በተጨማሪ ጅብ የደከመ ሰው ያጠቃል፤ በቸነፈር ዘመን በጅብ መጠቃት የተለመደ ክስተት ነው። ማንኛውም አዳኝ ሆነ ቃራሚ (Scavenger) ደካማን ያጠቃል፤ የተራበ ሰው ደካማ ነው፤ ስለሆነም በጅብ ይጠቃል።

“በዩፍሮ” ጥረት የምግብ እህል የታደለባቸው ቦታዎች ወሎ ውስጥ ኮምቦልቻ፣ ጫለቃ፣ ወልድያ፣ ዶሮ ገበሬ፣ ቆቦ፣ አላማጣ እና መርሳ ነበሩ። በትግራይ ማይጨው ነበር። በነዚህ አካባቢዎች ለ33 378 ሰዎች 2970 ኩንታል እህል ታደለ።

የእህል መሸመቻ ገንዘብ የተገኘው ከላይ እንደተጠቀሰው ከዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር፣ “ከአፍሪካኒስት ኮንግረስ”፣ የኢትዮጵያ የሀኪሞች ማህበር፣ ከዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ግቢዎች (አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ ስድስት ኪሎ) ለመጽሐፍት ቤት ሠራተኞች፣ ከጎንደር ጤና ኮልጅ እና ሌሎች፣ ብር 44,439. 27 ተሰብስቦ ነበር።

“የዩፍሮ” የመዋቅሩ የበላይ አካል የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሲሆን፣ለማህበረሰቡ ተጠሪ የነበረው “ዩፍሮ” ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነበር። “ዩፍሮ” የኦዲት ቢሮ መሥርቶ፣ እንዲሁም የአስተዳደር ቋሚ ሠራተኞችም ቀጥሮ ነበር።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ማዕከላትን መሥርቶ ነበር፣ ዞብል ማዕከል (በማዕከሉ ሁለት ጣቢያዎች፣ ማለት ተኩለሽ እና ዞብል ላይ ተመሥርተው ነበር)፤ የሚሌ ማዕከል፣ የውጫሌ ማዕከል፣ እና በሲዳሞም አንድ የኩሬ ምሥረታ ፕሮጀክት ይካሄድ ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰው እነኝህን ተግባራት የሚመሩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር (የጤና ኮሚቴ፣ የገንዘብ ኮሚቴ እና የግብርና እና የተለያ ተግባራት ኮሚተዎች ያካትት ነበር)።

በነኝህና በመሳሰሉ ክንውኖች የዩኒቨርሲቲው ህብረተሰብ፣ እውቀቱን፣ ጊዜውን፣ጉልበቱን … ሳይቆጥብ ያደርግ የነበረው ተሳትፎ የሚያኮራ ነበር። የዩኒቨርሲቲዉን በጎ ስም በመጠቀም ከአገር ውስጥም ሆነ ውጭ፣ የማይናቅ ደጋፍ መሰበስብ ተችሎ ነበር። በእቅድ ከተሠራም፣ በቀጣይነት፣ የበለጠ ማሰባሰብ እንደሚቻል ብዙ አመልካቾች ነብሩ። “ዩፍሮም”፣ ከዚሀ አንፃር፣ ጽሕፈት ቤቱን

 በማጠናከር፣ የኢትዮጵያ/አፍሪካ “ኦክሰፋም” ለመሆን አቅዶ እንቅሰቃሴ ጀምሮ ነበር፤ ነገር ግን፣ በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋትና ሽኩቻዎች ምክንያት ያ ህልም ሳይሳካ ቀርቶ “ዩፍሮም” አክትሟል።

የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ ለወቅታዊ ችግር መፍቻ ጽንሰ ሃሳብ

አገራችን በአመዛኙ ሰው ሠራሽ የሆኑና ውስብስብና አዳጋች ችግሮች ገጥመዋታል። በሰሜኑ የአገራችን ክፍል፣ አሰከፊ ጦርንት ተቀስቅሶ ለብዙ ሕይወት እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችም በብዙ አካባቢዎች እየተከሰቱ ይገኛሉ።

በተጨማሪ ቀደም ሲል ይከሰቱ በነበሩ ችግሮች አምሳያ፣ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በሰሜን እና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በድርቅ እና በአንበጣ መንጋ ወረራ መንስዔ ችግር ተከስቷል። ከላይ የተወሳው ወቅታዊው የፀጥታ መናወጥም ችግሩን አባብሶታል። እነኝህ አገር አቀፍ ችግሮች፣ ነገ ዛሬ ሳይባል መቅረፍ ይገባል። ለወቅታዊ ችግሮች መፍቻ ምሳሌነት ተሞክሮ ይሆናል ተብሎ የታመነው “ዩፍሮ” እንደሆነ ከላይ ተወስቶ ነበር። ስለሆነም ጸሑፉ የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አመልካች ሲሆን፣ ይህንንም ችግር በዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ችግር ከተከሰተባቸው ማህበረሰቦች እና የመንግሥት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሊቀለብሱት ይችላሉ የሚል ግምት አለን።

ይህችን ጽሑፍ ወደ ሕትመት በምንልክበት ጊዜ፣ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋሙን እሳቤ መንግሥትም ሙሉ ግንዛቤ ወስዶ፣ የመንግሥት በጀት ክለሳ ማካሄድ ጀምሮ ነበር። የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ስለ መልሶ ማቋቋም ጉዳይ በሚዲያ በይፋ ማስተናገድ ጀምሮ ነበር። ስለሆነም ይህች ጽሑፍ በከፊልም ቢሆን ተቀባይነት ያሏቸው ሊተገበር የሚችሉ ጉዳዮች ታሳተናግድ ይሆናል የሚል እምነት አለን።

ጽሑፏ አመላካች አንጅ፣ የችግር መፍቻ ፕሮግራም አብሳሪ አይደለችም። ከላይ እንደተጠቀሰው በ1965 ዓ.ም ርሃብ በተከሰተ ጊዜ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በራሱ ተነሳሽነት የረሃቡን መጠን እና ስፋት፣ ለኢትዮጵያውያን በማሳወቅ ከፍተኛ ሚና ነበረው። ከዚያም ውስን የሆኑ የችግር መቅረፊያ ፕሮግራም ቀርጾ፣ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ፣ በተለያዩ ደረጃዎች ኮሚቴዎች አቋቁሞ ነበር። በሂደት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ጥረት አድርጓል። አሁን ለተከሰተው ውስብስብ የአገር ችግር መቅረፊያ የሚሆን፣ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ ተመሳሳይ ተግባር ሊፈጽም ይችላል፣ መፈጸምም አለበት ብለንን አናምናለን።

በመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ በበጎ ፈቃደኝነት በድርጅት መልክ መዋቀር ያስፈልገዋል። አደረጃጀቱ እና አወቃቀሩ ተጠንቶ፣ ፕሮግራሞች ተቀርጸው እና ከመዋቅሮች ጋር ተዛምደው፣ ተቀናጅተው መቅረብ ይኖርባቸዋል።ይህን የሚተገብር ቡድን ከዩኒቨርሲቲዎች ባለሙያዎች ሊውጣጣ ይችላል።

ለአወቃቀሩ ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሉት ብለን እናምናለን። ለሁሉም አማራጮች ቅድመ ሁኔታ፣ ፈቃደኛ የሆኑ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ አባል የሆኑ ባለሙያዎች ስብስብ፣ መቀነባበር አለበት (ስም፣ ሙያ/ክህሎት፣ ወዘተ)። ስብስቡም መንግሥታዊ ባለሆነ ድርጅት ሥር ተግባሩን ቢያከናውን ይመረጣል።

አማራጭ አንድ

የዩኒቨርሲተዎች ማህበረሰብ ከሙያ አንፃር ተደራጅቶ፣ ይህ የተደራጀ የባለሙያ ስብስብ፣ ችግሩን ለመፍታት ለተሰማሩ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሙያዊ አስተዋጽዖ ማበርከት ይሆናል።

አማራጭ ሁለት

የዩኒቨርሲተዎች ማህበረሰብ ራሱን የቻለ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አዋቅሮ፣ በተለያዩ ዘርፎች ቀጥተኛ ሙያዊ እስተዋጽኦ ማበርከት ነው።

አማራጭ ሦስተ

የዩኒቨርሲተዎች ማህበረሰብ ራሱን የቻለ አንድ መንግሥረታዊ ያለሆነ ድርጅት አዋቅሮ፣ በተለያዩ ዘርፎች ቀጥተኛ ሙያዊ እስተዋጽ ከማበርከት በተጨማሪ፣ድጋፍ እርዳታ ለሚፈልጉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላለሆኑ በተመሳሳይ ተግባር ላይ ለተሠማሩ ድርጅቶች የሰው ኃይል እርዳታ/ ድጋፍ ማበርከት ነው (የኣማራጭ አንድ እና አማራጭ ሁለት ጣመራ መሰል)።

አማራጭ ሁለት ዘርዘር ተብሎ ሲታይ

አማራጭ ሁለት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ራሱን የቻለ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አዋቅሮ፣ በተለያዩ ዘርፎች ቀጥተኛ ሙያዊ እስተዋጽ ማበርከት ነው። ይህም ለምሳሌነት ከወሰድነው “ከዩፍሮ” አወቃቀር ጋር ተመሳሳይነት ይኖረዋል።

  • የወቅቱን ፈታኝ ችግር የሚገመግም (የሚያጠና) አንድ ከባለሙያዎች የተውጣጣ ኮሚቴ እና አጋዥ የሆኑ ንዑስ ኮሚቴዎች መመሥረት እና ችግሮቹ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢወዎች ማሰማራት።
  • በተሰማሩት ባለሙያዎች አማኻኝነት በሚገኘው መረጃ ላይ መሥርቶ፣ ችግር ፈች ይሆናሉ ተብለው የሚታመኑ ፕሮግራሞችን መቅረጽ።
  • ፕሮግራሞችን ወደ ተግባር ይተረጉማሉ ተብለው ሲታመኑ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ አባላትን (ባለ ሙያዎችን) መመልመል፣ማሰባሰብ፣ማደራጀት።
  • ለፕሮግራሞች ተፈጻሚነት ቅደም ተከተል መንደፍ/ መተለም።
  • በቅደም ተከተሉ መሠረት፣ለፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚሆን ወጭ (በጀት)

 በባለሙያዎች ማስተመን።

  • የሕዝብ ግንኙነት እና የገንዘብ አሳባበሳቢ ኮሚቴዎች በተለያዩ ደረጃዎች ማዋቀር።
  • የገንዘብ ምንጮች ይሆናሉ ተብለው የተገመቱት ዋና ዋናዎች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰብ፣ አገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (በተለይ የድጋፍ ሰጭ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች)፣ እና የአገር ቤት ባለ ሃብቶች ናቸው።
  • የፕሮግራሞች አስፈጻሚ መዋቅር መመሥርት፣ ቢሮዎችን ማደራጀት፣ በተለያዩ አካባቢዎች (በተለይ ችግሮቹ በፀኑባቸው አካባቢዎች) ጣቢያዎች መመሥረት፣ ማዋቀር።ለጣቢያዎች ምሥረታ በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል።

ምንም እንኳን ይህ የተግባር ዝርዝር ከመስክ ጥናት በኋላ የሚወሰን ቢሆንም፣ ለጥቆማ ያህል ከፕሮግራሞች ውስጥ ትኩረት መሰጠት አለባቸው ብለን ያመንባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን አቅርበናል። እነሱም በየአካባቢዉ ከመንግሥት እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በማቀናጀት/ በመናበብ፡-

  • ፕሮግራሞች በሁሉም አካባቢዎች (ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ወዘተ.) ወደ ተግባር አንዲቀየሩ ለማድረግ ቅስቀሳ ማካሄድ።
  • ሐኪሞች በበጎ ፈቃደኝነት ስነልቦናዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መሞኮር፤የስነ ልቦና ቀውስ ማስታገስ ማረቅ፣ መፈወስ (ይህ ለረጅም ጊዜ የሚከናወን ተግባር ይሆናል)። ለማህበረሰቡም ስለዚህ ሥነ ልቦና ቀውስ በቂ ግንዛቤ ማበርከት (ለምሳሌ የተጎዱትን አንዳያገሉ፣ እንዲንከባከብ፣ እንዲቀበላቸው፣ የችግራቸው ተካፋይ እንዲሆኑ፣ ወዘተ ለማድረግ መሞከር)።
  • የሀሰት ትችቶችን (Fake News) መቀልበስ፣ የህዝብ ግንኙነት፣ ሚዲያ ተሳትፎ ማጠናከር።
  • ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የግል ቤቶችን እና የመንግሥት መ/ቤቶችን፣ መልሶ መገንባት፣ መጠገን።
  • ምግብ እና አልባሳት ማቅረብ።
  • የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሰናዶን መጠገን፣ መገንባት።
  • በሰው ጉልበት የሚሠሩ የገጠር መንገዶችን መመሥረት፣ ምንጮችን ማጎልበት፣ ወዘተ።
  • በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚረዱ ሁሉ ተግባራትን፣ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር፣ መፈጸም (በጋራ ተሳትፎ ሊዳብር ይችላል)። o የመዝናኛ ማዕከላትን መመሥረት፣
  • o የዕፅዋት መዕከላትን/ ፓርኮችን በጋራ መመሥረት፣
  • o የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በተደጋጋሚ ማካሄድ፣
  •  
  • የተከሰተውን ችግር መሰነድ (ሰነዶች ለወደፊት ችግር መፍቻ መረጃ ምንጮች ሆነው ያገለግላሉ ተብሎ ይታመናል)።
  • የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦችን (ዜጎችን) ማህበራዊ መግባበትን ማጠናከር። ለዚህ ተግባር የሚያገለግሉ ምሳሌዎች o የብሄራዊ ወታደራዊ አገልግሎት መመሥረት፣
  • o በተፈጥሯዊ አካባቢን ማገገሚያ ሥርዓት የሚሰማሩ ብሄራዊ አገልግሎት (ይህ ትምህርት፣ ማህበረሰባዊ አቅም ግንባታን፣ ልማትን ሊያካትት ይችላል) መመሥረት፣
  •  
  • አንድነትን እና ልዩነት በአግባቡ መገንዘብ፣ መቀበል እና ማክበር።

አሁን ከተሰተው ቀውስ በተጨማሪ፣ ከአገራችን ዋና ዋና ችግሮች የማህበራዊ ግንኙነቶች መዛባት እና የተፈጥሮ ሃብት መጎሳቀል ናቸው ተብሎ በብዙ ባለሙያዎች ይታመናል። ስለሆነም የረጅም ጊዜ ፕሮግራሞች ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለን የምናምነው፣ ለማህባራዊ መግባባት እና ለተፈጥሮ ሃብት በአግባባቡ አጠቃቀም እና እንክብካቤ ነው።

የማህበራዊ መግባባት በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ ተደጋጋሚ ውይይቶች፣ ማህበራት፣ እድሮች ወዘተ፣ እና በትምህርት ቤቶች የትምህርት ግብዓትነት ሊስተናገድ ይችላል። ተግባራቱም በፖሊሲ መደገፍ ይኖርባቸዋል።

የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና እንክብካቤም በትምህርት ቤቶች የትምህርት ግብዓትንት ሊስተናገድ ይችላል። በቅድሚያ በመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ (ለምግብ አዝመራዎች፣ ለፍራፍሬ፣ ለደኖች ምሥረታ / የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ደኖች፣ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ የሚያገለግለው መሬት/ አካባቢ ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል) ግብዓትነት ብዙ የተፈጥሮ ሃብት ተግዳሮቶች፣ችግሮች፣ ሊቀረፉ ይችላሉ። ሁሉም በቴክኖሎጂ ግብዓትነት መስተናገድ ይገባቸዋል። በተጨማሪ በክበቦች፣ በዕፅዋት አደባባዮች እና በፓሪኮች ምሥረታ እና ግንባታ በጋራ ተሳትፎ እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራት ግብዓትነት ሊታገዝ ይችላል።

በዚህች ጽሑፍ በግርድፉ የቀረበው ጽንሰ አሳብ፣ ተተችቶ፣ ዳብሮ፣ ወደ ተግባር ይተረጎም ይሆናል የሚል ጽኑ ምኞት አለን።

 ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ እና ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው

ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም

Recommended For You