ኢትዮጵያውያን የወያኔን ያህል የታገሱትና የተሸከሙት የፖለቲካ ኃይል በታሪክ ውስጥ ያለ አይመስለኝም። የመጀመሪያው ነጥብ የሶማሌ ክልሉ ሙስጠፌ … የተናገሩት ነው። ወያኔ ኢትዮጵያን እየጠላ ኢትዮጵያን ለመምራት የደፈረ ቡድን መሆኑ ነው። ወያኔ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ ኢትዮጵያን ሊዘክር፣ ሊያነብር፣ ሊያከብር የሚችል ሐሳብን፣ ቃልና ድርጊትን ሁሉ ከታሪክ ጓዳ እስከ ደረሰበት የጊዜ መደዳ ውስጥ ሁሉ ማጥፋት ላይ የሚያተኩር ቡድን ነው። ወያኔ የኢትዮጵያን ትናንት ይጠላዋል። የሚጠላው ግን፣ ለኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የተሻለ ሊያደርግላት በማሰብ አይደለም፤ የተሻለ መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ አንድነት፤ የተሻለ ነጻነትና ብልጽግና ሊያላብሳት አይደለም። ምስጢሩ ሌላ ነው፤ እንደ አገር የተሠራችበት ዋልታና ማገር በትናንት ውስጥ ፍንትው ብሎ ስለሚታየው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዕቅዱ እንደ ጥላ ስለሚከብደው ነው።
ወያኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከየትም ወገን የሆኑ ለኢትዮጵያ ስለ ኢትዮጵያ የኖሩ ነገሥታትን፣ ሊቃውንትን፣ ተቋማትን፣ የባህል እሴቶችን፣ ወርቃማ ማኅበራዊ ትስስሮችን ይጠላል። ስለዚህ ያንኳስሳል፣ ያራክሳል፣ ያስጠላል፣ ለማደብዘዝ፣ ትርጉማቸውን ለመለወጥ፣ ክብራቸውን ለማጉደፍ ያሴርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ትናንት ላይ ያሴራል። የሚያለያየውን ይሰብካል፤ የሚያስተሳስረውን ይሰውራል። አማራና ኦሮሞ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው በአንድነት ያገኙትን ወርቃማ ድል ለመንገር ይሽኮረመማል፤ በምኒልክ የማስገበር ዘመቻ የነበሩ ግጭቶችን ግን አጥንት ጉልጥምታቸውን እየፈለቀቀ ሐውልት ሊያቆምላቸው ይተጋል። በአማራና ትግራዋይን በያሬድ ዜማ በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተገኘውን መተሳሰር ብዙ ሊዘምርለት ሲገባ፣ የንጉሥ ዘርዓያዕቆብንና የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች ጋር የገባውን ግብ ግብ ደጋግሞ ሊያስጠና ይፈልጋል። የሙስሊም ክርስቲያኑን በአንድነት ለማቆም በወሎ ያለውን የሙስሊም ክርስቲያን ፍቅርና ትብብር ከሚነግረን ይልቅ በዐፄ ዮሐንስ እና በወሎ ሙስሊሞች መካከል የነበረውን ቅራኔ በስውር በዘረጋው መዋቅሩ በኩል እንዲሰበክ ማድረግን ይመርጣል…ኧረ ስንቱ?
ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከደቡብ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ ብሎ ሳይሆን፣ በትግራይ ምድር፣ ከትግራይ ማኅብረሰብ የመነጨ ኢትዮጵያዊነትን የሚያዳብር፣ የሚያጠነክር የሚሰብክ ዕሴት ጭምር ያጠፋል። ዐፄ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ አክሱም ጽዮን፣ ያሬድ… ወዘተ የሚሰጡት ገጽታ ከኢትዮጵያዊነት ያልተነጠለ፣ በዚያም ላይ የተመሠረተ ያንን የሚዘክር በመሆኑ ካልተገደደና ለራሱ የሴራ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ለማንሣት ይሽኮረመማል። የዓድዋ ድል ታሪክ ለወያኔ የእግር እሳቱ ነው። ‹‹እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነበት›› ዓይነት ነው። የትግራይ ሪፐብሊክ ሕልምና የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ መሠረትና እምብርትነትን የማመን ጉዳይ የወያኔ የዐሠርት ዓመታት ራስ ምታት ነበር። ትግራዋይ ሌላውን እንዲጠላ፣ ሌላውም ትግራዋይን እንዲጠላ ስንቱን ዳገት ወጣ! ስንቱን ቆላ ወረደ!…እስከ ደም ጎርፍ…አቤቱ!!!
ይህ ሁሉ ግን በኢትዮጵያውያን ዘንድ የታወቀ ነበር፤ እየታወቀ ግን ለወያኔ ያልተደረገለት አልነበረም። ውድ የሆነች ክብርት አገር በእጁ እንድትወድቅ ፈቅዶለታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ባርነት እየገባ መሆኑን እያወቀ ወያኔ ለደረሰው ‹‹የነጻነት መዝሙር››፣ ‹‹የነጻነት ሐውልት››፣ ‹‹የነጻነት ቀን በዓል›› ሁለመናውን ይሰጥ ነበር። ለዚህ ምስክሩ የ27 ዓመታት የግንቦት ሃያ ቀንና ሌሊቶች ናቸው። የዜግነት ክብሩን በየደቂቃና በየሰዓቱ እያጣ የነበረ ሕዝብ ‹‹የዜግነት ክብር›› ብሎ በሰቀቀን ዘምሯል። አገሩ በማፍያ ቡድን እየተዋረደች እያየ የነበረ ሕዝብ ‹‹ኢትዮጵያችን ኩሪ እኛም በአንቺ እንኩራ እያለ አዚሟል። ‹‹እያነቡ እስክስታ›› ይልሃል ይህ ነበር።
ወያኔ ከመቶ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በእውቀት፣ በመሣሪያ፣ በልምድ፣ በወኔ፣ በአገር ፍቅር ሲገነባ የኖረን ብሔራዊ ጦር ‹‹የደረግ ጦር›› ብሎ እንዳልነበር አድርጎ ሲበትን ኢትዮጵያን ለማሳነስ ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ያጤኑ ብዙዎች ነበሩ። ‹‹እኛ ብሔር ብሔረሰቦች ተፈቃቅደን አገር እንመሥርት፣ ባንዲራ እንትከል›› ብሎ በድፍረት ለምክክር ሲያቀርብ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በዘመን አጭር፣ በይዘት ተረት፣ በዋጋ ርካሽ አድርጎ ለራሷ ለዜጎቿ ሲናገር የማያፍር ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተደረገበት ምን አለ?! ልጆቹ በደካማ የትምህርት ፖሊሲ የደከሙበት፣ በሱስና ተስፋ መቁረጥ የተመቱበት፣ ከግብረገብ ውጪ ሆኖ ለራሱና ለአገሩ የማይተርፍ ብቻ ሳይሆን በአገሩ የሚያፍር፣ በአረብ አገር ስደት በባርነት የሚማቅቅ፣ በበረሃ የአራዊት፣ የአሸባሪና የወንበዴ ሲሳይ የተደረገ፣ በአገሩ ነጻነት፣ በስደት አገር ክብር ያጣ እንዲሆን የተደረገበት ጊዜ ነበር።
የወያኔ ባለሥልጣናትና የኔትዎርኩ ተንከባካቢዎች በአንድ ጠራራ ጀምበር ሚሊየነር ቢሊየነር የሚሆኑበት፣ ባንኩንም ታንኩንም በኪሱ ይዞ የሚዞር ግልጽ ማፊያ ነበር። የመንግሥት የኃይልና የሐብት ቁጥጥር ከአንድ ብሔር ወጥቶ፣ ከዚያውም ተመራርጦ በተደራጀና ከኢትዮጵያ ጠላቶችጋ ተመጋግቦ በሚሠራ ዓለም አቀፍ አደረጃጀት ‹‹ተጠርንፎ›› ቆየ።
ወያኔ የመራውን ሕዝብ ‹‹ወይኔ! ወይኔ!›› ሳያስብል የዋለበት ጊዜ አልነበረም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንቱን ቻለ፤ ከመቻሉ ደግሞ ማባበሉ። 27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመምራት ሰፊ ዕድል ሰጠው። የትግራይ ሕዝብ በሌላው እንዲጠላ እንዲለይ ለመነጠል በሥነልቦና የተዘጋጀ እንዲሆን ቢፈልግም ኢትዮጵያውያን ቻይነትና ጥበብ ግን ትግራዋይ ሁሉ በመላው ሀገሪቱ በሰላም ሠርተው እንዲበሉ፤ ነግደው እንዲያተርፉ፣ ዘርተው እንዲቅሙ ያለቅሬታ ተቀብሎ ኖረ።
በተለይ ደሴ፣ ሐዋሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ፣ ሎጊያና ሰመራ፣ አዳማና ቢሾፍቱ… ለትግራዋይ ምቹ ሆነው የኖሩ አካባቢዎች ናቸው። የትግራይ ሕዝብ ሌላውን አምኖ እንደሚኖረው ሌላውም ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ አምኖ አክሱም ጽዮን ወይም አልነጃሺ ብሎ ቀየውን አቋርጦ ይሄዳል። በወያኔዎች ‹‹የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው?›› ቢባልም ፊታውራሪ አመዴን የመሰሉ አገር ወዳዶች የአክሱምን ሐውልት ለማስመለስ እንቅልፍ ያጡ ነበር።
ወያኔ ስሙን እንኳን ሳቀይር ‹‹የትግራይ ነጻ አውጪ›› እየተባለ ኢትዮጵያን እንደሚመራ የሚያውቀው ሕዝብ የእኔ የግሌ ብሎ የሚጠራው ከትግራይ ክልል ‹‹ድንበር ተቆረሰ፣ ባድማ ተደፈረ›› ባለ ጊዜ ግን በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ቅጠል በረገፉበት ጦርነት ትግራይ አገሬ፣ ድንበሬ ወገኔ ብሎ ደሙን አፍሷል፤ የልጆቹን ሕይወት ገብሯል፤ ገንዘቡን አፍስሷል፤ እንቅልፉን አጥቷል። ፍቅሩን ገልጧል። በወቅቱ የመከላከያ አባል የነበሩት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ብዙዎች በጊዜው ትግራዋይ ወገኔ ነው ብለው በጦርነት ሰቀቀን ውስጥ አልፈዋል። ብዙዎች ልጆቻቸውን አጥተዋል፤ አካላቸው ተጎድቷል።
ሕዝብን ትምክህተኛ፣ ጠባብ እያለ ይሳደብ የነበረው ሕወሓት ሊቀመንበሩ መለስ ዜናዊ በሞተ ጊዜ መሪዬ፣ ወንድሜ፣ ወገኔ ብሎ ለሐዘን ወር የተቀመጠ ሕዝብ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወያኔ ያላደረገለት ምን አለ፤ ሰበርናችሁ ሲሉ ታግሷል፣ ምርጫ ሲጭበረበር ታግሷል፣ ዜጎች ሲገደሉ ሲሰቃዩ ታግሷል፣ ርስቱ ሲቀማ ታግሷል፤ እርስ በእርስ ሲያባሉት ታግሷል፤ ጠባብ ትምክህተኛ ሲሉት ታግሷል፤ ታሪክ ሲቆነጻጸል፣ ቅርስ ሲወድም ሲጠፋ፣ የውሸት የፖለቲካ ትርክት ሲጻፍ ታግሷል፤ አገር ያለወደብ ስትቀር፣ ያለምክር የግንጠላ ፈቃድ ሲሰጥ ታግሷል፤ ጳጳስና ሼክ ሲያሳድድ ታግሷል። ብሔራዊ ፕሮጀክትን ለጥፋት ሲዳርግ፣ ‹‹እኛ ብቻ እንብላ›› ሲል ታግሷል። በሕዝቡ ላይ ከተደረገበት ይልቅ ያልተደረገበትን መናገር ይቀላል።
እጅግ አስገራሚው ግን በታሪክ አጋጣሚ ግፉ በዝቶ፣ ጽዋው ሞልቶ ከ27 መራር ትዕግስት በኋላ በሕዝብ ቁጣ ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ድርሻቸው እንዲያንስ ሲደረግ፣ በቃችሁ ሲባሉ፣ የታገሳቸውን ብርቱ ሕዝብ እንደናቃቸው፣ እንደጠላቸው፣ እንደገፋቸው ቆጠሩ፤ ሰበኩ፤ አኮረፉ። ይቅርታ ሊጠየቅ የሚገባውን ሕዝብ መቀሌ ተሰብስበው ያጥላሉት ጀመር። ‹‹በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር›› የምትለው መርሕ ልትዋጥላቸው አልቻለችም። በተስፋ ያመናቸውን ካዱት፣ በትዕግስቱ የወደዳቸውን ሕዝብ ጠሉት።
‹‹ከእናንተ ይልቅ ሱዳኖች ይሻሉናል›› ብለው እንደ ባዕድ አቀለሉት። የደበቁትን አገር የመፍታት፣ ሕዝብ የማለያየት ድብቅ አጀንዳ ዐውዱን ተጠቅመው በይፋ ይነሰንሱት ጀመር። የትግራይን ወጣቶች ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ማሰዳደብ፣ ማጋጨት ቀጠሉ። ከአሐዳዊነት ወደ ፌዴራላዊነት የወሰድናትን አገር አሁን ደግሞ፣ ወደ ኮንፌዴሬሽን እናደርሳታለን፤ ዲፋክቶ ስቴት እንመሠርታለን… ወዘተ የሚሉ ፉከራዎች ቀጠሉ።
በመላው አገሪቱ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባሉ ግጭቶችን ሲያቀጣጥሉ ቆዩ። አቦሉን ጠጥተው እፍታውን በልተው እንዲመሩት 27 ዓመት የፈቀደላቸው ሕዝብ የፖለቲካ መሪና ፖሊሲ ለመቀየር አንፍቅድልህም አሉት። ምኞትና ዛቻቸውንም ለመፈጸም እንሞትለታለን ይሉት የነበረውን ሕገ መንግሥት ሳይቀር ለመጣስ ደፈሩ። ለማዕከላዊ መንግሥት አንታዘዝም አሉ። ጦርና የጦርንም ወሬ ማውራት ቀጠሉ፤ ካለእኛ ጀግና፣ ካለኛ የጦር አዋቂ፣ ካለኛ አሸናፊ የለም እያሉ የትግራይን ወጣቶችና ሕፃናት በፕሮፓጋንዳ አሰከሩ።
የእነርሱን ዕብሪት መታገስ የለመደው ሕዝብ በከፍተኛ ትዕግስት ሁኔታዎችን ተከታተለ፤ ማዕከላዊ መንግሥት የአገር ውስጥና የአገር ውጪ ሽማግሌዎችን እያፈራረቀ ሰላምን ለመነ። የሕወሓት የሽብር ቡድን ግን የንቀቱን ጥግ የጭካኔውንም ወሰን እስከምን እንደሆነ ጥቅምት 24/2013 ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳየ። ኢትዮጵያ በከፍተኛ አንጡራ ሐብት ስትገነባው የቆየችውን ሠራዊት ለሁለተኛ ጊዜ ለማፍረስ እርምጃ ወሰደ። ጀሌዎቹ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የመከራ ዶፍ አወረዱ። ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ ቀውስ ይዘዋት ገቡ።
የኢትዮጵያን ጥንተ ጠላቶች ሁሉ ከጎናቸው አሰልፈው፤ በዓለም አቀፍ ፈርጣማ ሚዲያዎችና በኃያላን መንግሥታት ዲፕሎማሲ ተደግፈው ያደረገችላቸውን አገር አደረጉባት። ከፍተኛ የዘር ጭፍጨፋ፣ የንብረት ውድመት፣ የመፈናቀል አደጋ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ውድመት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስከተሉ።
የወያኔ ጀሌዎች በኢትዮጵያ ላይ ተሳለቁ፤ ከንቱ የሚዲያ ሰዎቻቸው ‹‹ኢትዮጵያ ስትፈርስ ትውልዳችን በማየቱ ዕድለኞች ነን›› አሉ። መነኮሳቶቻቸው ከእነቆባቸው ወጥተው ‹‹ኖ ሞር ኢትዮጵያ››ን ዘመሩ። ወታደራዊ ጁንታው በአማራና አፋር ላይ ያለ የሌለ የጭካኔ ክንዱን አሳረፈ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንደሚወርዱ ፖለቲከኞቻቸው ደነፉ።
ይህ ሁሉ የሆነው በማያውቁት ሕዝብ ላይ አይደለም፤ መርተውት፣ አስተዳድረውት በማያውቁት ሕዝብ ላይ አይደለም። በሌሎች ኃይሎች ባርነት ሥር ለሚማቅቅ ሕዝብ አይደለም። ራሳቸው ሲቀጠቅጡት፣ ሲገዙት በነበሩት በሚያውቁት በሚያውቃቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው። የመከራን ሀ፣ሁ ሲያስቆጥሩት በነበረ ሕዝብ ላይ ነው። አሁን ግን ወደ ነጻነት ሀ፣ሁ.. የመራመጃው…የመከራ ሰንኮፍ የመንቀያው ጊዜ ሆነ፤ ሃሌ ሉያ። አላህ ዋአክበር።
ቶኩማ ሮባ
ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም