ብያኔ
‹‹ግብረ ገብ›› የቃሉ ምንጭ የግዕዝ ቋንቋ ሲሆን፣ ገብረ ሠራ ከሚለው ሥርወ ግሥ የተገኘ ነው። ትርጉሙም ተግባር ያልተለየው መልካም ኅሊና የሚል ትርጉም ይሰጠናል። በአመዛኙ በሃይማኖት ዓለም ሰው ለፈጣሪው ወይም ለባልንጀራው ያለውን መልካም አመለካከትና በሥራ የተገለጸ ፍቅርና አክብሮት የሚያመለክት ሆኖ ይተነተናል።
በፍልስፍናው ዓለም ያለውን ብያኔ መነሻ አድርግን ማየቱ ደግሞ የበለጠ ምንነቱን ለመረዳት ይጠቅማል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ጠና ደዎ ስለግብረ ገብ ምንነት ሲገልጹ ‹‹እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎችና ከራሱ ሕይወት፣ ዕድገት መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት፣ ክብርና ዓላማ አንጻር ማድረግ የሚገባው ወይም ማድረግ የማይገባው ድርጊት፣ መሆን የሚገባው ጠባይ ወይም መሆን የማይገባው ጠባይ የሚገለጽባቸው፣ የሚደነገግባቸው ወይም ብይን የሚሰጥባቸው ጽንሰ ሐሳቦች አሉት። በሁሉም ግላዊ፣ ሙያዊና ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ባለው የሰው ድርጊትና ጠባይ ላይ የሚያተኩር ነው።›› ይላሉ። /ጠና ደዎ። ሰው፣ ግብረ ገብና ሥነምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/ገጽ 38/
የግብረ ገብ ፍልስፍና መነሻም በሰው ውስጥ ያለ በዚህ ዓለም በጋራ ሲኖር ሊቀበልና ሊሰጥ ስለሚችለው ዕሴት ባሰበ ጊዜ /አስፈላጊ መሆኑን በተረዳ ጊዜ እየቀረጸው፣ እያከበረው፣ እያዳበረው የሚሄድ ነው። ዶክተር ጠና፣ ይህንን አጉልተው ሲያሳዩ ‹‹ግብረ ገብ እያንዳንዱ ሰው ‹ምን ሳደርግ ነው ራሴን ለመጥቀም ሌሎችን የምጎዳው፣ ወይም ራሴን ጎድቼ ሌሎችን የምጠቅመው? ምን ጊዜ ነው ድርጊቴ ማንንም ሳይጎዳ ሁሉንም ሊጠቅም የሚችለው?› በማለት ራሱን መፈተሽ እንዳለበት ይመክራል›› ይላሉ። የማህበረሰቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአኗኗር ዘዴ የሚያመላክት፣ የማህበረሰቡን አባላት ማንነትና የአካባቢያዊ መስተጋብሮችን ጨምሮ ባህልና ወጉን የሚገልጽበት፣ በጋራ ተግባቦት ላይ የተመሠረተ የመግባቢያ ቋንቋ ወይም ተለምዷዊ ሕግ ወይም ሥርዓት በግብረገብ ውስጥ ይገነባል ማለት ነው።
የሰው ልጅ ያለ ማኅበራዊ ትስስር ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ መኖር አይችልም የሚሉት ዶክተር ጠና በዚህ ፍላጎት ውስጥ የፍላጎት አንድነትና ልዩነት እንደሚኖር፣ አንድነቱ እንደሚያስተሳስር ልዩነቱ እንደሚያጋጭ ይህንን ግጭት ግን ማስታረቅና ማረቅ የሚያስችል የማህበራዊ ትስስር ጉልበት የሚሆን ግብረ ገብ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ስለዚህ እውነተኛ ዕርቅ፣ ስምምነት፣ መስተጋብር እንዲኖር ልባዊ የሆነ የሚገዛ ዕሴት አስፈላጊ ነው፤ እርሱ ግብረገብ ነው። የሰው ሕይወቱ የሚመራው በውስጡ ነው፤ ስለዚህ ግብረ ገብም የሚገዛው ውስጥን ነው። ስለዚህ ሰውን የሚመራው የግብረ ገብ እሴት ምክንያታዊ ሆኖ የተሰደረ ከሆነ ኃያልና ተፈጻሚነት ያለው ይሆናል።
ዶክተር ጠና፣ ሰዎች የሚቸገሩት በየትኛው ሕግ ለመገዛት እየጣሩ ነው? የሚለው ጥያቄ በሚፈጠረው ምላሽ ነው ይላሉ። ውስጥን በሚገዛ ግብረ ገባዊ ሕግ ወይስ በሚታወጁ የፖለቲካ ሕግጋት? ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም ‹‹በእርግጠኝነት ሕግ ሁሉም ቦታ ተገኝቶ ሁሉንም ሰውና ድርጊት መቆጣጠር አይችልም፤ ግብረገብ ግን ሕግ በሌለበትና በማይኖርበት ቦታና ጊዜ ውስጥ ራሱ ሰውን አግባብቶና አቻችሎ የማኖር አቅም አለው›› ይላሉ።
ግብረ ገባዊ እሴቶች በዚህ ደረጃ አስፈላጊ መሆናቸው የታወቀ ከሆነ፤ የሚቀረጹበት፣ ዕውቅና የሚያገኙበት፣ ተፈጻሚ የሚሆኑበት፣ ክፉ ደግ፣ ክብር ነውር፣ ትክክል ስሕትት ወዘተ እየተባሉ የሚበየኑበት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰርጹበት መንገድና ተቋማት ሊኖሩ የግድ ነው።
አንደ መስኩ ምሁራን እምነት ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት ልዩ ልዩ ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። ቤተሰብ የመጀመሪያው የበጎም ይሁን የመጥፎ ዕሴቶች መማሪያ በመሆኑ፣ መንግሥት ተቋማት የአገር ደኅንነት፣ ክብር፣ ፍላጎት ሁሉ በአግባቡ የሚመራባቸው የፖለቲካ ተቋማት እንደሆኑ ስለሚታሰብ፣ የትምህርት ተቋማት/በሁሉም ዓይነትና ደረጃ ያሉ/ ግብረ ገብ በትምህርት የሚስፋፋ የሚዳብር ዕሴት ከመሆኑ አንጻር እንደ ትምህርት ተቋምነታቸው ወሳኝ ሚና ስላላቸው፣ የሃይማኖት ተቋማት እኩይ/ኃጢአትን/ የማስወገድ፣ ሠናይን /ጽድቅን/ የማጎልበት ዓላማ ያላቸው ተቋማት በመሆናቸው ለግብረ ገብ ህልውና የማይተካ ሚና ይጫወታሉ።
የግብረ ገብ ተጽእኖው ከፍ ያለ በመሆኑም በዓለም ላይ የራሱ የሆነ ግብረ ገባዊ ዕሴት የሌለው ማኅበረሰብ የለም፤ ከዚያም በመነጨ የግብረ ገባዊ
እሳቤዎችንና የግብረ ገባዊ ሕይወታችንን ተፈላጊ ገጽታዎች የሚያጠና የግብረገብ ፍልስፍና /Moral philosophy/ በዓለም ላይ የታወቀ ሆኖ ቆይቷል። ኢማኑኤል ካንት፣ ቶማስ አኲነስ፣ ዴቪድ ሁም፣ ጆን ሎክ፣ ፕሌቶ፣ አርስቶትል፣ ኮንፊሺየስ የመሳሰሉ ፈላስፎች በዚህ ረገድ ስም ያላቸው ነበሩ። ስለዚህም እንደ አንድ ሳይንስ በዓለም ላይ እየዳበረ መጥቶ፣ በሥነ ዜጋና በሥነምግባር መልክ የመደበኛ ትምህርት ቅርጽ ይዞ ይሰጣል።
ግብረ ገባዊነት በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በፈጣሪ አምኖ የሚኖር፣ የበርካታ ቤተእምነቶች የመስፋፋት ታሪክ ሲነሳ እምነቶችን ፈጥኖ በመቀበል የሚታወቅ ማኅበረሰብ ከመሆኑ አንጻር ከዚያ የመነጩ በርካታ ግብረገባዊ ዕሴቶች ሲዳብሩበት የኖር ሕዝብ ነው። በእምነትና ልዩ ልዩ ባህላዊ ተቋማት ውስጥም እሴቶቹ ሲዳብሩ ሲጠበቁና ሲስፋፉ ኖረዋል። የዘመናዊ ትምህርት መጀመሩን ተከትሎም ግብረ ገብ የትምህርት ሥርዓቱ አካል እንዲሆን ጥረት ሲደረግ ነበር። ዘመናዊው ትምህርት በኢትዮጵያ ተስፋፋ ከሚባልበት ጊዜ አንሥቶ የግብረ ገብ ትምህርት በልዩ ልዩ ስምና ቅርጽ እየተሰጠ መሆኑ ቢነገርም፣ ከጊዜ ጊዜ ግን የግብረ ገብ ዕሴቶች ስለመሸርሸራቸው እንጂ ስለመገንባታቸው አይወራም፤ በተግባርም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከግብረ ገብ ያፈነገጡ ልዩ ልዩ የጥላቻና ጭካኔ ሥራዎች እየታዩ በመምጣታቸው ትምህርቱ ምን አጋጥሞት ነው የሚል ጥያቄ ብዙዎች ያነሣሉ። ይህንን በተመለከተም The Role of Civic and Ethical Education in Democratization Process of Ethiopia: Challenges and Prospects በሚል ርዕስ ተጠንቶ በሳይንስ ፐብሊሺንግ ግሩፕ በጥናት መጽሔት የወጣው ጽሑፍ ትምህርቱ በየዘመኑ ውስንነቶች እንደነበሩበት ደምድሟል።
የግብረ ገብ ዕሴቶችን በማኅበረሰብ ውስጥ የማበልጸግ፣ የማስረጽ፣ የመጠበቅ፣ የማስተማር ልምዶች ከአንዱ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ ሌላው በሚደረግ ሽግግር ምክንያት ልዩ ልዩ መልክ ይዞ ቆይቷል። የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተብሎ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ የትምህርት ዓለም ውስጥ ተካቶ ያለው ትምህርት በመደበኛ ትምህርትነት መሰጠት የጀመረበት ታሪክ የሚጀምረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ነበር። በዚያን ወቅት ግብረ ገብ “Moral Education” በሚል ስም የሚሰጠው ትምህርት በሂደት ግን ልዩ ልዩ ስም እየተሰጠው በይዘትና ቅርጽ እየተለወጠ መምጣቱን ጥናቱ ያመለክታል።
በንጉሡ ዘመን የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት ይዞታው በአመዛኙ የተቀዳው ሃይማኖታዊ ከሆነው ሥነምግባር ትምህርት በመሆኑ በአንድ በኩል ለአንድ ሃይማኖት ያደላ ይዞታ አለው የሚለው እሳቤ፣ በሌላ በኩል የሥነ ዜጋ ትምህርቶችን ያቀፈ አይደለም፤ የዴሞክራሲ ባህል በአገር እንዲገነባ አያበረታታም በሚል ከትችት ያመለጠ አልነበረም። የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የነጻነት እና የመሳሰሉትን እሳቤዎች አያንጸባርቅም። በአመዛኙም ወጣቶች ለንጉሣዊው ሥርዓት ተገዢ እንዲሆኑ ማግባቢያ ተድርጎ ይወሰድ ስለነበርም በጊዜው ለመወለድ አሰፍስፎ በነበረው አብዮት ውስጥ ሰለባ ሆኗል ማለት ይቻላል።
ጥናቱ እንደሚያመለክተው ደርግ በ1967 ዓ.ም በአብዮቱ ምክንያት ሥልጣን ሲይዝ ይከተለው የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍና ማርክሲዝም ሌኒንዝም ስለነበር፣ በሶሻሊዝም እሳቤ የተለያዩ መንግሥታዊ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ተገዷል። በዚያም መሠረት የትምህርት ፖሊሲው ከዚህ መውጣት የሚችል አልሆነም። ስለዚህ በንጉሡ ዘመን የነበረውን ንጉሥ አስከባሪ፣ የሃይማኖት እሳቤ የጎላበት የተባለውን ግብረ ገብ ትምህርት ለመሸሽ ሲባል የተተከለው ትምህርት ፖለቲካ “political education” የተባለ ትምህርት ነበር። ትምህርቱ እንደ ሥነ ዜጋ ትምህርት ታስቦ ነገር ግን፣ ለአንድ ርዕዮት ብቻ ሰባኪ ሆኖ ትውልዱን በዚያ ቀንብቦ ለማሳደግ የተዘጋጀ ትምህርት ነበር። በጊዜው ሶሻሊዝም የሚባለውንና ዓለም አቀፋዊ ወዛደራዊነት የሚለውን እሳቤ ለማስረጽ የሚጠቅም ነበር። ከንጉሡ ዘመን የሚለዩት መሠረታዊ መነሻም ትምህርቱን ዓለማዊ መልክ ይዞ መቅረቡ እንጂ ሥርዓትን ማገልገያቱ ቀጥሏል በሚለው ጥናት አቅራቢዎች ይስማማሉ። የተሟላ ሆኖ የግብረገብ እሴቶችን ያልያዘ፣ የፖለቲካ ይዞታውም ዴሞክራሲያዊና የዴሞክራሲያዊነት መልክ የሚያስተዋውቅ ሥነ ዜጋ ትምህርት አልነበረም። /SciencePG፣ Volume 7, Issue 2, March 2019/
ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲረከብ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ሲቀርጽ በይዘት፣ በሥነ ዘዴ፣ በዓላማ ከቀደሙት የተለየ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ሥርዓት መትከሉን ተናገረ። በዚያም መሠረት የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት የመሳሰሉትን እሳቤዎች በየደረጃው ላሉ ተማሪዎች ለመስጠት ጀመረ። ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ ሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ረገድ ውጤታማ እንዳልሆነ ምሁራን ያነሣሉ።
በትምህርት ሥርዓቱ ቆይቶብን ስለነበረው የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ያለበትን ውስንነት በዝርዝር ያስረዱን ለረጅም ጊዜ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት የቆዩትና አሁን በባልህና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስትራቴጂ ኤክስፐርት ሆነው እየሠሩ ያሉት ዶክተር ታደለ ፈንታው ናቸው። ‹‹ትምህርቱ የተወሰኑ ወገኖችን ፍላጎት ለማጉላት እና በሌላው ላይ ለመጫን በዘዴ የተዘጋጀ ነበር። ሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር በተግባር እና በንድፈ ሐሳብ መካከል የነበረው ርቀት የተራራ ያህል የገዘፈ ነው። አገር በቀል የሆኑ ሥነ ዜጋዊ ጉዳዮችን የዘነጋ እና የሌሎችን/ባዕዳን/ ተሞክሮ አብነት ያደረገ ነው። የትምህርት አሰጣጥ ዘዴውም ትኩረት የተነፈገው፣ ሥነ ምግባር በጎደላቸው፣ አብነት ሊሆኑ በማይችሉ፣ ራሳቸው ሥነ ዜጋ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ባልተረዱ መምህራን ጭምር የሚሰጥ ነበር። ከክልል ክልል ወጥ እና አንድ ዓይነት የሆነ ትምህርት አይሰጥም ነበር።
ዛሬ ላጋጠመን ጦስ በሚዳርግ መንገድ በጨቋኝ እና ተጨቋኝ ትርክት ላይ የሚያተኩር ከንድፈ አሳባዊነቱ ይልቅ አሳባዊነቱ የሚልቅ፤ ተረት ተረትነቱ የሚያጋድል፤ የፈጠራ ድርሰት የታከለበት በዘዴ አገር ለመበታተን ታልሞ ታቅዶ በበጀት ተደግፎ የሚሠራበት ነበር። ሆን ብሎ የተሳሳተ ትምህርት ማስተማር (ዲስቶርሽን) እና መረጃ ማዛባት የበዛበት ሕዝቦችን በጠላትነት የሚፈርጅ፣ አግላይ፣ አንዱ ሕዝብ ወዳጅ ሌላውን ሕዝብ ጠላት የሚል ነበር።›› ብለዋል።
የዕሴቶች መዝቀጥና የጊዜያችን ምስቅልቅል
በርካቶች ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ላጋጠማት የሰላም እጦት መነሻው የግብረ ገብ ዕሴቶች መዝቀጥ መሆኑን ያነሣሉ። በዚህ ረገድ ጽኑ አቋም ያላቸው የሥነልቡና፣ የሥነ መለኮት እና ሕክምና ምሁርና ባለሙያው ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ ‹‹የትኛውም ማኅበረሰብ ያለበት ደረጃ የሚታወቀው በዕሴቶቹ ነው። ሠልጥኗል፣ ገናና ሕዝብ ነው የሚባለው በሚጠብቃቸው ዕሴቶች የተነሣ ነው። የኢትዮጵያ ከዚህ የተለየ አይደለም። የተከበርን ሕዝቦች እንድንሆን ያደረገን የጠበቅነው ግብረገባዊ ዕሴትም ነው። እንግዳ ተቀባይነታችን መተሳሰባችን፣ ፍቅርና መከባበራችን አስከብሮን ቆይቷል ብዬ ነው የማምነው። አሁን የተፈጠረው ምስቅልቅል ግን እነዚህ እሴቶች በተወሰነው ማኅበረሰብ ዘንድ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ነው የሚያሳየው። ነገሩን የግብረ ገብ ዝቅጠት ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን።›› ይላሉ።
ዶክተር ወዳጄነህ የግብረ ገብ ዕሴቶች መዝቀጣቸው ላይ ጥያቄ እንደሌለ አንሥተው ምክንያቱ ምንድነው የሚለው ግን አነጋጋሪ መሆኑን ያወሳሉ። ዶክተር ወዳጄነህ ስለዚህ ሲናገሩ ‹‹የዝቅጠቱ ምክንያት አለው፤ ያንን መፈተሽ አለብን፤ እኛ በጣም ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነን። የምንታወቀው አጥብቀን ፈጣሪን የምንፈራ ሕዝብ በመሆናችን ነው። እዚህ መሃል ግን ችግር እንዲገባብን በተለያየ መንገድ የሆነ የሚዘራ ተንኮል አለ። ምክንያቱም ሃይማኖተኛ ማኅበረሰብ በቀላሉ አሁን በገጠመን ዓይነት አስቸጋሪ ምስቅልቅል ውስጥ ለመግባት ይቸገራል፤ ስለዚህ የሆነ ተንኮል የተዘራበት መሆኑን ትረዳለህ። ምክንያቱም ሁሉም ሃይማኖቶች ግድያን ዝርፊያን፣ የሴቶች ጥቃትን ወዘተ ይከለክላሉ። ምናልባም የውጭ እጆች በመካከላችን እየረጩት ያለ መርዝ አለ ብዬ አስባለሁ።›› ብለውናል።
ይሄንን ሐሳብ በጥብቅ የሚጋሩት ዶክተር ታደለ ፈንታው ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ሥርዓቱ መሆኑን ይጠቁማሉ ‹‹በመጀመሪያ የሥነ ምግባር እና ሥነ ዜጋ ትምህርት መሠረታዊ ፋይዳው ዜጎች መልካም ባሕርያትን የተላበሱ፣ አገራቸውን የሚወዱ፣ በልማት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ እና ኢትዮጵያ እገነባዋለሁ ብላ የምታስበውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ ሆነው እንዲሠሩ ማስቻል ነው። በዚህ ረገድ ካየነው የትምህርት ተቋማት ሚና ሰፊ ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በተግባር ስንፈትሸው በመጀመሪያ የትምህርት ሥርዓታችን የተኮረጀ ነው። እኛን፣ እኛን አይሸትም። ሌሎች የሰለጠኑ አገሮች የደረሱበት ደረጃ በአጭር ጊዜ ለመድረስ የሌሎችን መኮረጅ ጥሩ ነው። ስንኮርጅ ግን፣ በጎ በጎውን እንጂ እንቶ ፈንቶውንና ኮተቱን ሁሉ አይደለም። ለምሳሌ ሠለጠኑ የሚባሉ ፈረንጀች ሲዝናኑ፣ መኪና ሲነዱ፣ ጁስ ሲጠጡ፣ ፍራፍሬ ሲመገቡ እንመለከታለን እንጂ የስኬታቸውን ምስጢር አይነግሩንም። እንዴት እዚያ ደረጃ ለመድረስ አፈር ግጠው 24 ሰዓት እንደሚሠሩ አይነገረንም። ስለዚህ የኮረጅነው ግማሽ ኩረጃ ነው ማለት ነው። ጨረቃ ላይ መውጣትን፣ ሱፐር ሶኒክ ጀቶችን ማብረርን፣ አኅጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን የመሥራትን ጥበብ አይነግሩንም። በትምህርት ስም መለያየትን ይሰብኩናል፣ ጭቆናን ያጎላሉ። ብዝበዛ የደረሰብን መሆኑን አጉልተው ይነግሩናል። የሚገርመው አንዳችን የሌሎቻችን ጠባቂ መሆናችን ተረስቶ፣ አንዳችን ሌላችንን በጠላትነት እንድንሥል ያስተምሩናል። ስለዚህ ሥርዓተ ትምህርታችን በእኛ ዘንድ ያሉ በጎ በጎ እሴቶቻችንን ቆፍሮ የማውጣት፣ ማልማት፣ መጠበቅ፣ ማስተማር ትውልድን መቅረጽ ይኖርበታል።›› ይላሉ።
ግብረ ገባዊ እሴቶችን ያከበረ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ሥርዓቱና የትምህርት ተቋማቱ ሚና እንዳላቸው ሁሉም ወገኖች ቢያምኑም፣ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸው ሚናም ቁልፍ ነው በዚያ ረገድ ተቋማቱ እየሠሩ ያለው ሥራ በቂ አይደለም፤ በስፋት መንቀሳቀስ አለባቸው የሚሉ አሉ። ዶክተር ወዳጄነህ ይሄንን ሲያሳስቡ ‹‹ግብረገባዊ ዕሴቶች እንዲጠበቁም፣ የወደቁትም እንዲያገግሙ በዋናነት ሚና ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። ከዚያም የአገር ሽማግሌዎች፣ የታወቁና ሕዝብ የሚያከብራቸው ሰዎች ናቸው። ከየትኞቹም ተቋማት በላይ የሃይማኖት ተቋማት ግብረ ገብን መልሶ ለመገንባት ኃላፊነት፣ ችሎታም አላቸው ብዬ አስባለሁ። ዕሴቶቹ መልሰው ማገገማቸው አይቀርም የምፈራውና የምሰጋው
ግን ከብዙ ዘርፈ ብዙ/ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የግብረ ገብ/ ድቀት በኋላ እንዳይሆን ነው። በኋላ መመለሱ ላይቀር ጉዳትን ለመቀነስ ግን መፍጠን ያስፈልጋል።›› ብለውናል።
ይሄንኑ አስመልክተን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑትን ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስተያየት እንዲሰጡ በጋበዝናቸው ጊዜ ‹‹የእምነት ተቋማት አስተምህሮን መሠረት በማድረግ በግብረ ገብ ጉዳይ ለዘመናት ሲሠሩ እንደነበር ይታወቃል፤ አሁን እየሠሩ ነው። ዋነኛ የተቋማቱም ተልእኮ እሱ ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህም ትውልድ ይቀረጽበታል የሚል እምነት አለኝ። እናት አባትህን አክብር፣ ለመሪዎች ተገዛ፣ ታላላቆችህን አክብር፣ በጎውን ሁሉ አድርግ፤ ክፉውን ተቃወም የሚለው ነገር ሁሉ ሁልጊዜ በሚያስተምሩት የትምህርት ሂደት ውስጥ ሁሉ እየተመላለሰ የሚኖር ነው። ከእምነት ተቋማት ቀድሞ በዚህ ረገድ ተጠሪ ሊሆን የሚችል አይኖርም›› ይላሉ።
ቀሲስ ታጋይ ባሉት ደረጃ ተቋማቱ ሚና ካላቸው አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሁኔታ በቀላሉ ለመግራት አልተቻለም የሚል ጥያቄ ሊያስነሣ እንደሚችል በጠቆምናቸው ጊዜ ‹‹የሃይማኖት ተቋማት አልሠሩም ብሎ መናገር ያለጥናት አይቻልም፤ ይሁን እንጂ ለአገራት የቀውስ ምክንያት የሚሆነው የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና በግብረ ገብ እሴቶች መዳከም የመጣ መሆኑን እረዳለሁ፤ ለዚህ ሁሉ ግን፣ የእምነት ተቋማትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም።›› ካሉ በኋላ የእምነት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አልሠሩም ከማለት ይልቅ እንዳይሠሩ ስለገጠማቸው ተግዳሮት ማንሣት እንደሚበጅ ያመለክታሉ። ቀሲስ ታጋይ ስለዚሁ ሲያብራሩ ‹‹ሕዝቡም ውስጥ እኮ! የሚነሣ ነገር አለ፤ ከሃምሳ ከአርባ ዓመት ወዲህ ችግር አለ ይልሃል፤ ለምን እንዲህ ይላል ስትል የደርግም ሥርዓት ሃይማኖት ጠል ሥርዐት ነበር። ለቤተእምነቶች ክብር የማይሰጥ የሚያዋርድም ነበር፤ ከዚያ በኋላ የተተካው ደግሞ ዴሞክራሲን አሰፋናለሁ በሚል ሽፋን ሃይማኖቶችን በማጋጨት፣ በማለያየት ትውልድን በግብረ ገብ እንዳያንፁ ከማድረግ አኳያ አሉታዊ ሚና ይጫወት ነበር። ፖለቲካው ተጽእኖ ነበረው፣ ቤተ እምነቶች እንዳይንቀሳቀሱ ሽባ ከማድረግ አኳያ ሚና ነበረው። የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ለመክፈል ያደረጉት ተግባር እንደ ምሳሌ አይረሳም፤ በጎን የሚያስቡ ሁሉ ይታሠራሉ፤ ይሰደዳሉ። የሥርዓቱ ብሉሽነት ቤተ እምነቶች በሚፈልጉት ልክ እንዳይሠሩ አድርጓል።›› ብለዋል።
ቀሲስ ታጋይ የጠቀሱትን የፖለቲካ ሥርዓቱ ቀና አለመሆን በግብረገብ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን በተመለከተ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁርና ተመራማሪው አቶ ፋንታሁን ዋቄም ይስማሙበታል። አቶ ፋንታሁን፣ የመንግሥት ፖሊሲ ወይም የፖለቲካ ሥርዓቱ ቀና አለመሆን፣ ለግብረ ገብ እሴቶች መዳበር ከመሠረቱ ለመሥራት ቁልፍ ሚና ባለው የቤተሰብ አኗኗር ላይ ጭምር ተፅዕኖ ነበረው ይላሉ። አቶ ፋንታሁን ይሄንኑ ሲያብራሩ ‹‹ግብረ ገብ የሆነ ትውልድ ለማሳደግ የባህልና የሃይማኖት ተቋማት ሁለንተናዊ ተሳትፎን በማመቻቸት፣ በመጀመሪያ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለምን በመምረጥ፣ በማመንጨትና ለአገራዊ የማኅበረሰብ አመራር ፖሊሲ፣ ለትምሕርት ሥርዓቱ ይዘትና አቀራረብ፣ ለቤተሰብ አስተዳደር፣ ለሚዲያ መልእክታት ይዘት ላይ ተፅእኖ የሚሳርፉ፣ ወይንም ገደብ በማበጀት ረገድ ዋነኞቹ በአገር ደረጃ ሚና የሚጫወቱ አካላት ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ የመልካም ሰብእና መገለጫ የሆነው ግብረ ገብ ትውልድ የሚገኘው ወላጆች የሚፈጥሩትና የሚኖሩት የማኅበረሰብ እሴት፣ እሴቶቹን በሕይወት እንዲከበሩ የሚጠብቁና የሚያስጠብቁ ተቋማት ጥንካሬ ደረጃና ከአገር የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና በቤተሰብና በማኅበረሰብ ባህላዊ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ወይም ተባብሮ የመሥራት ድንበርን በመወሰን ደረጃ ያላቸው የመደራደር ጥንካሬ ነው።
ከእነዚህ ሁለት አካላት አንፃር አዎንታዊ የሆነ ትብብርና ሁኔታ ሲኖር በአገር ደረጃ ቤተሰብ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ፣ የቤተሰብ አስተዋጽኦ እጅግ የተገደበ ይሆናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ1966 የኮሚኒዝም መተዋወቅ በኋላ የተነሳው ትውልድ የፈጠረው ከባቢ የቤተሰብ ሚናን እጅግ ያዳከመ ነው። ቤተሰቦች ዘመናዊውና በተውሶ ውጭ ገብ ትምህርት የታነፀው ትውልድ እንኳንስ ቤተሰቡን ንጉሥና ጳጳስን የሚገድሉ የፖለቲካ ልሂቃን ያፈራ ነው። መሪዎቹ የአገሪቱን መሠረታዊ ፍልስፍናና እምነት በሚያዋርዱበት ዐውድ ውስጥ ትምህርት ቤቶችና መገናኛ ብዙኃን የወላጆችን ክብርና ተሰሚነት ለመሸርሸር ተግተው ስለሚሠሩ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ ሊሆን አልቻለም። ወደፊትም በፖለቲካና በእውቀት ላይ የተመሠረተ የወላጆችን ሚና የማሳደግ ሥራ ካልተሠራ በአንደበት ከመናገር የሚያልፍ ለውጥ አይመጣም።
መንግሥት የሕፃናት፣ የሴት፣ የቤተሰብ፣ ወዘተ በሚል ማርክሳዊና ምዕራባዊ እሳቤ ፖሊሲ ቀርጾ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሲመሠርት የቤተሰብ ሚናን የሚወስኑ የእምነትና የባህል አስምህሮዎች ሚናቸው አልቦ ነው። ይህን ከመሠረቱ አገራዊ እሴትና አገር በቀል ጠቃሚ እውቀቶች በሚመሩት ዐውድ በማዋቀር የቤተሰብን የሥነ ምግባር ግንባታ አስተዋጽኦ የትውልድ ቀረፃ ስሌት አካል ማድረግ ያስቻላል፤ አሁን ግን የለም።›› ይላሉ።
አቶ ፋንታሁን እንደሚሉት ሃይማኖታዊ መሠረት ላላቸውና ነባር ግብረ ገባዊ ዕሴቶች ደካማ ዋጋ የሚሰጠው የመንግሥት ፖሊሲ በመደበኛ ትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ በሚዲያና ኪነጥበብም በሚሠሩ ፕሮግራሞች አገር በአግባቡ የሚረክብ ትውልድ ሳይፈጥር መቆየቱን ያወሳሉ። በተለይ በሚዲያ በኩል ስለነበረው ድክመት አቶ ፋንታሁን ብቻ ሳይሆኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት እና የኮሚዩኒኬሽን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ሐሳባቸውን በመጋራት እንዲህ ይላሉ ‹‹ግብረ ገብ እሴቶችን በማስተማርና በማስተዋወቅ ሚዲያዎች ብዙ ይጠበቅባቸው ነበር፤ አሁንም ይጠበቅባቸዋል፤ የማስተማር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።
ለምሳሌ፡- ትምህርት በሬድዩ ግብረ ገብን ለማስተማር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በተለይ የማህበረሰብ ሬድዮኖች ትኩረት ቢያደርጉ ብዙ ለውጥ ያመጣሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ የሚዲያ አካላት ከግብረ ገብ ውጪ ነበሩ። ግብረ ገብ የሌለው ግብረ ገብ አያስተምርም። ‹አይሬ ፕሮግራም ደረሰ› እየተባለ ወደ ጫት ቤት መሮጥ እንደነበር ይታወሳል። የፕሮግራም ግዴታም አልነበረባቸውም። ስለዚህ ለወደፊቱ ቋሚና የተጠና የግብረገብ ፕሮግራም ያስፈልጋል። የሚዲያ ባለስልጣን ይህን ማስፈፀም አለበት።›› በማለት አብራርተዋል።
መፍትሔ
ከላይ በተጠቀሱ የአካሔዶች ድክመት አሁን በኢትዮጵያ ዓይነተ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። ስለዚህ ችግሩን ከመቅረፍና ትውልዱን ከማነጽ አንጻር መንግሥት የግብረ ገብ ትምህርትን በትምህርት ሥርዓቱ አስገብቶ ለማስተማር እየተንቀሳቀሰ ነው። ከዚህ ባሻግር ግን፣ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ምሁራኑና የሚመለከታቸው ሥራ ኃላፊዎች ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ይህንን አበክረው ሲያስረዱ ‹‹ዘላቂ መፍትሔን ከማምጣት አኳያ ሁሉም ሚና አለው፤ አገር መገንባት ብዙ ተዋንያን አሉት፤ አንድ ቤት ሢሠራ ልዩ ልዩ ሙያተኞች እንደሚሳተፉበት፤ ልክ እንዲሁ አገርም ሲገነባ የብዙዎች ጥረትና ጥበብ ያስፈልጋል።
ከግብረ ገብ አንጻር የመጀመሪያውና ከፍተኛውን ድርሻ ወሳጅ የእምነት ተቋማት ናቸው። ከሕፃንነት ጀምሮ ግብረ ገባዊ፣ አገር ወዳድ፣ ቤተሰቡን መሪውን የሃይማኖት አባቶችን አክባሪ እንዲሆኑ የቤተ እምነቶች ሚና መጉላት አለበት። ሌላው ድርሻ የቤተሰብ ነው፤ ልጆችን በደንብ መቅረጽ ያለበት ወላጅ ነው፤ ውሏቸውን መከታተል አለባቸው። በሦስተኛ ደረጃ፣ የትምህርት ተቋማትና መምህራን ሥርዓተ ትምህርት ስለተዘጋጀና ስላልተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አጋጣሚዎች ተማሪዎቻቸው ግብረ ገባዊ እንዲሆኑ መትጋት አለባቸው።
‹ላልወለድኩት ልጅ ምን አገባኝ› ማለት አይገባቸውም። አገር ይፈርሳል። መልሶ መምህሩ ራሱ ተጎጂ ይሆናል። በአራተኛ ደረጃ መንግሥትም ወሳኝ ድርሻ አለው። ግብረ ገባዊ ትውልድ ለመገንባት ካልተጋ የሚዋረደው መንግሥታዊ ሥርዐቱም ነው። አገር መሪዋን ትመስላለች እንዲሉ፣ መሪዎች በተለይ፣ አርአያ መሆን አለባቸው። ስለዚህ ኳሱን እዚህ ወይም እዚያ ከመወርወር ይልቅ ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።›› ይላሉ።
አቶ ፋንታሁን ዋቄም ለወደፊቱ በተለይ የቤተሰብን ሚና የሚወስኑ አገራዊ ሁኔታዎችን መርምሮ በማስተካከል ግብረ ገብ ትውልድ በመፍጠር ላይ አስዋጽኦአቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ ‹‹ግብረ ገብነት ያለው ሰብእናን ለመገንባት አንድ ቤተሰብ በነባር ባህሉ፣ በእምነቱና በታሪኩ ፋይዳ ላይ ያለውን መተማመን የሚሸረሽር የመደበኛ ትምህርት፣ የመንግሥት ሕጎች፣ ርእዮተ ዓለማዊ ቅድመ ብያኔ የተሰጠባቸው ውጭ ገብ አስተምህሮዎችን፣ ተቃራኒ መልዕክት ያላቸው የመገናኛ ብዙኃንና የኪነ ጥበብ ውጤቶችን ከአገር ሊቃውንት ጋር ሳይወያዩ በአገር ውስጥ በትውልዱ ላይ አለመጫን ያስፈልጋል። መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ የተለያዩ የሕዝብ ጀግኖች የሚባሉ ሰዎች ከቤተሰብ እሴት ጋር የሚኖረን አርአያነት ሲያሳዩ የሚገሰፁበትና ልጆች ለወላጆቻቸው ምክርና አስተምህሮ ዋጋ እንዲሰጡ ተገዳዳሪ መልእክት የሚያስተላልፉትን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ሲታይ ግብረ ገብ በኢትዮጵያ አንሠራርቶ አገርም እንድታንሠራራ ሁሉም ድርሻ ያለው መሆኑና በተለይ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ፣ በተለይ የትምህርት ሥርዐቱ፣ ሚዲያና ኪነጥብብ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተመልክቷል።
ማለደ ዋስይሁን
ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም