‹‹ ሕወሓት እስከመጨረሻው ይደመሰሳል ፣ኢትዮጵያም የሰላም አገር ትሆናለች›› ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የደርግ አባል

የተወለዱት በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ተከታትለዋል። በ 1951 ዓ.ም ሐረር ወታደራዊ አካዳሚ እጩ መኮንንነት ትምህርት ቤት ገብተዋል። ከተመረቁ በኋላ ናዝሬት በሚገኘው የአየር ወለድ ክፍል ሁለት ዓመት አገልግለው ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተልከው የሕግ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በ1959 ዓ.ም በሐረር ወታደራዊ አካዳሚ መምህር ሆነዋል። በተማሩበት ሐረር ወታደራዊ አካዳሚ በመምህርነት አገልግለዋል። ደርግን የተቀላቀሉት የሕግ ኮሚቴ ሊቀመንበርና የወታደራዊ አካዳሚ ተወካይ በመሆን ነበር። በኋላ በ 1968 ዓ.ም ወደ ውጭጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊነት ከፍ ብለዋል። በዚህ ኃላፊነታቸውም በርካታ የአረብ አገሮችን ተዘዋውረው በማግባባት ታላቅ ስራን አከናውነዋል፤ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ።

በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት መጀመሪያ ላይ ሶቪዬት ኅብረት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የሰላም ድርድር ለማካሄድ በሞከረችበት ወቅት አገራቸውን ወክለው በድርድሩ ላይ ተገኝተዋል። በ1980 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጦር እስረኞች እንዲለዋወጡ ያመቻቸውን የኢትዮጵያ ልዑክ መርተዋል። የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር፣ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ የፖሊት ቢሮ አባል ፣ የተፈጥሮ አደጋ መከላከል መርጃ ኮሚቴ የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ ሊቀመንበር ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የመንግሥት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን አገራቸውን አግልግለዋል።

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ለ29 ዓመታት በጣሊያን ኢንባሲ ተጠግተው ቆይተዋል። በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል። በ 2003 ዓ.ም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በድጋሚ ታይቶ ወደ እድሜ ልክ እስራት ቢያሻሽልላቸውም ከተጠጉበት የጣሊያን ኢንባሲ ወጥተው የዕስር ቅጣቱን አልተወጡም። ከአንድ ዓመት በፊት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመክሮ እንዲለቀቁ ብይን በመስጠቱ እርሳቸው እና በጣሊያን ኢምባሲ ቅጥር ግቢ አብረዋቸው የነበሩት የደርግ መንግሥት ኢታማዦር ሹም ሌፍቴናንት ጄ/ል አዲስ ተድላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል። ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ከአምስት ወራት በፊት “ያልታሰበው፤ የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዪ” በሚል ርዕስ የሕይወት ታሪካቸውንና አብዮቱን የሚዳስስ በ700 ገጾች የተቀነበበ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ አሳትመዋል። ዘመን መጽሔት ከባለታሪኩ ጋር ግሩም ቆይታ አድርጋለች። እንደሚከተለው ይቀርባል።

 ዘመን፡- በመጀመሪያ ከፍጥረቱ ጀምሮ የመገንጠል ሐሳብ አቀንቃኝ የነበረው አሁን በሞቱ አፋፍ ላይ የሚገኘው አሸባሪው ሕወሓት ከሥልጣን ተወግዶ በመገናኘታችን ምን ተሰማዎ ?

ኮለኔል ብርሃኑ፡- በጣም ደስ ብሎኛል። አገር አጥፊ የሆነ ወንበዴ ቡድን ነው። እኛም ስንታገለው ነው የኖርነው። በመጨረሻ ስለተወገደና አሁን እንደምናየው እየተደመሰሰ ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኛል። ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ሰላሟ ይጠበቃል ፤ እድገቷ ብልጽግናዋ ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ። በነገራችን ላይ ዶክተር ዐቢይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪ ሆነው ብቅ ሲሉ በአጋጣሚ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ስለ እርሳቸው ጠይቆን ነበር። በወቅቱ እኔ መልስ የሰጠሁት ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያን ለማዳን ከላይ የተላከ ልዩ የሆነ ፍጡር ነው። እንደ እሱ ያሉ ሰዎች በመቶ ዓመት አንድ ጊዜ ነው የሚገኙት። ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ታድጋለች ትበለጽጋለች ሰላሟን ታገኛለች የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ ብዬ ነበር።

መን፡- ይህን አስተያየት ለመስጠት ያበቃዎት ምክንያት ምን ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡– ዶክተር ዐቢይ ሁኔታው ሁሉ የተለየ ነው። እንደ አንድነት ፓርክ ያሉ ፕሮጀክቶችንም መስራት ጀምሮ ነበር። አንድ ነገር አስቦ ወዲያው ተግባራዊ ያደርጋል። አንድነት ፓርክ ለዚህ ማሳያ ነው። ሔጄ ከጎበኘሁት በኋላ ደግሞ ይበልጥ አድንቄዋለሁ። ምክንያቱም በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ በጣም የሚገርም ነገር ነው የተሰራው።

ዘመን፡- የውትድርና ዓለም መነሻዎ ሐረር የጦር አካዳሚ ነው። አካዳሚው በወቅቱ ከነበረበት የብቃት ደረጃ እና ካፈራቸው መኮንኖች አንጻር እንዴት ይመዘናል ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- በጣም ትልቅ አካዳሚ ነበር። ያቋቋሙት ህንዶች ናቸው። የመጀመሪያዎቹ መኮንኖች የህንድ መከላከያ አካዳሚ ሠልጣኞች የነበሩ ናቸው። የመጀመሪው አዛዥ ኮሎኔል ራውል የሚባል ነበር ፤ በኋላ ጀነራል ሆኗል። እጅግ በጣም ብስል የነበረ ነው። ሌሎቹም አሠልጣኞች በጣም የበሰሉ ስለነበሩ አካዳሚውን ትልቅ አድርገውታል።

ዘመን፡- በመጽሐፍዎ ላይ እንደጠቀሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዎት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውይይቶችን እና ክርክሮችን በትኩረት ይከታተሉ ነበር። ከሁሉ በተለየ ግን የኃይሉ ገሞራው ግጥም በረከተ መርገም ሲቀርብ ፣ ለምን የተለየ ስሜት እንደፈጠረብዎ በወቅቱ ከነበረው ድባብ ጋር አያይዘው ቢገልጹልን ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለውጥ እፈልግ ነበር። ለውጥ እንደሚመጣም እርግጠኛ ነበርኩ። በወቅቱ ያ ግጥም ሲነበብ የነበረውን ስርዓት የሚያወግዝና ወደ ለውጥ የሚያማትር ስለነበር በጣም ተመስጬ ነበር

 የማዳምጠው። የተለየ ስሜት ወረረኝ። በውስጤ ያለው ነገር ሁሉ የተንፀባረቀበት ግጥም ነበር። ግጥሙ የቀረበው መጀመሪያ ኮሌጅ በነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በሚገኝ ሜዳ ላይ ነው። በርካታ ተማሪዎች ተገኝተው ነበር።

ዘመን፡- ደርግን ከመሠረቱት 108 አባላቱ መካከል እርስዎ አንዱ ነበሩ። ከሐረር የጦር አካዳሚ እንዴት ተመርጠው መጡ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እኔ ኤርትራ ነበርኩ። ተዘዋውሬ ሐረር የጦር አካዳሚ ከገባሁ ገና አንድ ዓመቴ ነበር። በሌለሁበት ነው የመረጡኝ። ሐረር የጦር አካዳሚ በነበርኩበት ወቅት የተደራረበ ሥራ ነበረኝ። አንደኛ እጩ መኮንኖችን ወታደራዊ ሕግ አስተምር ነበር። ሁለተኛ ከመላው ኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጎበዝ ተማሪዎች ተመርጠው ይመጡና መሰናዶ በሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመት ሠልጥነው ፈተና ተፈትነው በጥሩ ውጤት እያለፉ ወደ ጦር አካዳሚው እንዲገቡ ይደረግ ነበር። እኔ ከማስተማሩ በተጨማሪ የዚህ መሰናዶ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆንኩ። ዋና ስራዬ እነዚያን ተማሪዎች በደምብ አስተምሬና ተቆጣጥሬ ማሳለፍ ነው። አስተማሪዎቹ ህንዶች ነበሩ።

በአካዳሚው ሁልጊዜም አምስት ሰዓት ላይ ዋና ህንፃ ‹‹ሜን ቢዩልዲንግ›› በሚባል ቦታ የሚካሄድ የቡና ሰዓት ውይይት አለ። እኔ ብዙ ጊዜ በዚህ ስብሰባ ላይ አልገኝም ነበር። ሁልጊዜም በምትኖረኝ በዚህች ግማሽ ሰዓት ቤቴ ሄጄ ከባለቤቴ ጋር ቡና ጠጥቼ እየነዳሁ ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው የምሄደው። አንድ ዕለት ‹‹ሜን ቢዩልዲንግ›› የሚባለው ቦታ ጋር ስደርስ የወታደር ፖሊሶች አቁም አቁም አሉኝ። ምንድን ነው ብዬ ሳቆም በእግር በፈረስ ስንፈልግዎ ነበር አዛዥ ናቸው የጠሩዎ አሉኝ።

ስሄድ አዛዡ መደበኛ ወንበራቸውን ትተው ሶፋ ላይ ሆነው ከእርሳቸው ጋር ሌሎች የታወቁ መኮንኖች አብረዋቸው ቁጭ ብለዋል። የትምህርት መኮንኑ ደምሴ ቡልቶን (በኋላ ጀነራል) ጨምሮ ዋና ዋና የሚባሉ መኮንኖች እዚያ አሉ። በጣም ስንፈልግህ ነበረ ከአዲስ አበባ አራተኛ ክፍለ ጦር ቴሌግራም መጥቷል። ኮሚቴ እያቋቋምን ስለሆነ አባል የሚሆን አንድ መኮንን እና አንድ ባለማዕረግ መርጣችሁ ላኩ ስለተባለን ከመኮንኖች ተሰብስበን አንተን መርጠናል። ሕግም ስለተማርክ አንተ ትሻላለህ ብለን ነው አሉኝ። ብኖር ኖሮ ምርጫውን አልቀበልም ነበር። ቀድሞውንም እኔ የአስተዳደር ዝንባሌ አልነበረኝም። ኤልክትሪካል ኢንጂነር መሆን ነበር የምፈልገው ፤ የህይወት አጋጣሚ ነው ወደ ሌላ የወሰደኝ።

ሦስተኛ ክፍለ ጦር ሁላችሁም ተገኝታችሁ መመሪያ ይሰጣችኋል አሉኝ። ከፖሊስም ከመጡ ሰዎች ጋር እዚያ ስንሄድ ኤርትራ አብረን የነበርን ጥላሁን ቢሻኔ የሚባሉ ጀነራል ፣ የፖሊስ አዛዡ እና ከአካዳሚው ጀነራል ተፈሪ በንቲ ሆነው ቴሌ ግራም ብቻ ነው የደረሰን ምንም የምንሰጣችሁ መመሪያ የለም። የአንድ ሳምንት የውሎ አበል እንሰጣችኋለን ደርሳችሁ መጥታችሁ ሁኔታውን ታስረዱናላችሁ ብለውን ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሄድን።

ዘመን፡- ወደ አዲስ አበባ የመጣችሁት ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ጋር አብራችሁ ነው? ትውውቅስ ነበራችሁ ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ስንመጣ ከመንግስቱ ጋር ጎን ለጎን ነበር የተቀመጥነው። እኛ የኢትዮጵያን ህዝብ ዕድል ልንወስን መሆኑ በጣም ነው የሚገርመው አልኩት። ዝም አለኝ። ወደ አዲስ አበባ ከመሄዳችን በፊት ከክፍለ ጦራቸው ተጠርተው መከላከያ ሚኒስቴር ኢታማዦር ሹም ሆነው በተሾሙት ጄነራል ኃይሌ ባይቀጣኝ ሙስና ፈጽመዋል በሚል የቀረበ ውንጀላን ለማጣራት በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ ሁለታችንም አባል ነበርን። የጄነራሉን ጉዳይ ለማጣራት እዚያ ስንገናኝ ገና መኪናችንን እንዳቆምን እንደምን አለህ ሻለቃ ብርሃኑ አለኝ። እኔ ያውቀኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። መንግስቱ የመሳሪያ ግምጃ ቤት አዛዥ ሆኖ አንዳንድ ነገሮችን ስለ እርሱ እሰማ ነበረ።

ዘመን፡- ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ከመጣችሁ በኋላ በወቅቱ ሻለቃ የነበሩት መንግስቱ ኃይለማሪያም ሚናቸው ምን ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- መጀመሪያ መንግስቱ ምንም ሚና አልነበረውም። ኮሎኔል አጥናፉ ነበር ከአራተኛ ክፍለ ጦር ቴሌግራም የላከውና ያስተባብር የነበረው። በእርሱ ሰብሳቢነት ስብሰባው ሲካሄድ አባላት እርስ በእርስ እያወሩ አዳራሹ ድብልቅልቁ ይወጣል። ጎበዝ እባካችሁ ይላል ፤ ስብሰባ መምራት አይችልም። በዚህ ጊዜ መንግስቱ ይሄን ነገር እንደገና ማደራጀት አለብን ብሎ ሀሳብ አቀረበ። ምርጫ ሲደረግ ሻለቃ መንግስቱ ሃይለማሪያም ሊቀ መንበር፣ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ምክትል ሊቀ መንበር ሆኑ። እኔ ንጉሠ ነገሥቱ ወርደው ምን አይነት አስተዳደር ያለው መንግስት እናቋቁም የሚለውን የሚያጠና በአብዛኛው ጎበዝ የተባሉ መኮንንኖች ያሉበትን የእቅድ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኜ ጥናት ጀመርን። አንዳንድ ጊዜ በጣም አስፈላጊ ነገር ሲሆን መንግስቱን ጠርተነው ተሳትፎ ያደርጋል። አጥናፉን አንጠራውም ነበር። በዚህ ምክንያት አጥናፉ ለኮሚቴው ጥሩ አመለካከት አልነበረውም። እዚያ ተሰብስበው ምንድን ነው የሚሰሩት እኛንም ሊገለብጡ ይሆናል የሚመክሩት እያለ ይከሳል። በየጊዜው መጥተህ አስረዳ እባላለሁ። በኋላ ሲበዛ በእኔ እምነት ከሌላችሁ የመተማመኛ ድምጽ ካልተሰጠኝ በቀር አልቀጥልም አልኩ። መንግስቱ የመተማመኛ ድምጽ ሰጥተንሃል ቀጥል አለኝ። ከዚያ ስራዬን ቀጠልኩ ንጉሠ ነገሥቱ እንዴት እንደሚወርዱ ያቀድነው እኛ ነን።

ዘመን፡- አጼ ኃይለሥላሤ ከመውረዳቸው በፊት አንድ ደብዳቤ ይዛችሁ ቤተመንግስት ሄዳችሁ ፊት ለፊታቸው ተነቦላቸው ነበር። የደብዳቤው ይዘት ምን ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ደብዳቤው ዘጠኝ ያህል ነጥቦችን የያዘ ነው። እስረኞች እንዲፈቱ ፤ ውጭ አገር በስደት ላይ ያሉ እንዲመለሱ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ነበሩ የተነበቡላቸው። ትዝ እንደሚለኝ ሻምበል እንዳለ ነው ደብዳቤውን ያነበበው። ንጉሡ ለመሆኑ ከውጪ ይመለሱ እና ይፈቱ የምትሏቸው እነማን ናቸው አሉ። እኛ በወቅቱ እንዲሁ በድፍኑ ጥያቄውን አቀረብን እንጂ የተዘጋጀ መልስ አልነበረንም። ካባቸውን አወናጭፈው ዝም ብላችሁ ሳታጣሩ ነው የምትጠይቁት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት እንዳልካቸው መኮንን ቀረበው ግድ የለም እኛ እንጨርሰዋለን አሏቸው። በቃ ሂዱና እዚያ ጨርሱ አሉን። እስረኛና ስደተኛ ከሚሉት ውጪ ሌሎች ጥያቄዎች ላይ ተነጋገረን። አንድ ጋዜጠኛ ነበረ ተጠርቶ በሬዲያ ምን እንደሚነገር መመሪያ ተሰጠው።

ዘመን፡- ከዚያ ቆይቶ ደግሞ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ማረፊያ ተወሰዱ። አሟሟታቸው እንዴት ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- መንግስቱ ስብሰባ ላይ መጥቶ እኚህ ሽማግሌ አደገኛ ሆነዋል። አዳሀሪያን ከዚህ እንዲያመልጡ እረድተዋቸው እርሳቸውን እንደ መሪ አድርገው ችግር ሊፈጥሩብን ይችላሉ አለ። ከዚያ መልስ ሳይጠብቅ ስብሰባውን ጥሎ ሄደ። ጊዜ ቢሰጥ ኖሮ እኔ የ84 ዓመት ሽማግሌ ወጥቶ ምን ሊያደርግ ይችላል? የማይመስል ነገር ነው ብዪ እቃወም ነበር። ከዚያ ሞታቸው ተነገረ። ዋናው መነጋገሪያ የቀብራቸው ጉዳይ ነበር። ቅድስት ሥላሤ ቤተ ክርስቲያን ከሆነ በክብር ሊቀበሩ ነው። የት መቀበር እንዳለባቸው ስንነጋገር መንግስቱ ግድ የለም በዚህ ጊዜ አናጥፋ ይሄን ለእኛ ተዉት አለ። ወዲያውኑ የግል ሐኪማቸው በወቅቱ ነጻ በነበረው ሬዲዮ ላይ ቀርቦ ‹‹እኔ በፍጹም አላየኋቸውም፣ አላከምኳቸውም ስለመሞታቸው አላውቅም›› አለ። ይሄ ትንሽ ሁኔታውን የሚያጋልጥ ሆነ።

 ዘመን፡- ለበርካታ ዓመታት አብሮ እንደሰራ ባልደረባ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ማን ናቸው ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ትንሽ ጨካኝ ነው፤ በመግደል ያምናል። እዚህ ላይ በጣም ተሳስቷል። ለአገር የሚያስብ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበር። ነገር ግን ሁሉን ነገር በኃይል ለመፍታት ይፈልጋል።

ዘመን፡- ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ አገርን መምራት የጀመረው ደርግ ብዙም ሳይቆይ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም 60ዎቹን የአጼ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት ሲገድል የደርግ አባላት ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ብዙ ጊዜ ጠዋት ልጆቼን ትምህርት ቤታቸው ባለቤቴን ደግሞ ወደ ስራዋ አድርሼ በጊዜ ነው ስራ የምገባው። ያን ዕለት ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል እዚያ ስደርስ በወቅቱ ሻለቃ የነበረውን ኮሎኔል አጥናፉን በረንዳ ላይ አገኘሁት። ሻለቃ ብርሃኑ ዛሬ እነዚህን ሰዎች አንድ ነገር ማድረግ አለብን አለኝ። ጦሩ በቴሌ ግራም ተላልኮ ጉዳዩን ጨርሷል። እነዚህ ሰዎች ሲበዘብዙ የኖሩት አንሶ አሁን ደግሞ ደርግ ሰብስቦ ሊቀልባቸው አይገባም እያለ ነው። ጠባቂዎች እነርሱ ስለሆኑ ገብተው ሊፈጇቸው ይችላሉ ፤ እነርሱን ከፈጇቸው ደግሞ እኛንም አይምሩንም ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ አለብን አለኝ። ኧረ ባክህ አልኩት።

ሁልጊዜ ችግር ሲፈጠር የምናደርገው እንደ አየር ኃይል ፣ አየር ወለድ ፣ መደበኛው ጦር ሠራዊት ፣ ታንከኛ ካሉ ክፍሎች የሚዋቀር የተለያየ መለዮ ያላቸውን አባላት የሚይዝ ቡድን እንፈጥራለን። ይህ ቡድን ህብረታችንን ስለሚያሳይ ለምሳሌ ጦር ሲያስቸግር ልከነው አነጋግረን ነገሩን አብርደን ፈትተን እንመለሳለን። ስለዚህ አሁንም ከየክፍሉ የተወጣጣ ቡድን ፈጥረን ልከን ጦሩን ልናሳምን እንችላለን አልኩ ፣ ነገር ግን ተቀባይነት አላገኘም። እኔ ስናገር አንዳንድ ሰዎች ተነስተው ልክ ነው ይላሉ ፤ ተቃዋሚውም ደግሞ ሲናገር እንደዚሁ እየተባለ ነበር። በኋላ የሕግ ኮሚቴ ሊቀመንብር ተብዬ ስለነበር በመጨረሻ የተናገርኩት በህግ ኮሚቴ ሊቀመንበርነቴ የማስረዳው ነገር አለ ብዬ ነው። በሕጉ መሰረት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነስርዓት አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ሲመሰረትበት ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ ምስክር ቆጥሮ ነጻ ሊወጣ ይችላል። የጥፋተኝነት ውሳኔ ቢተላለፍበት እንኳን ቢያንስ ሁለት የይግባኝ መብት አለው። ይሄ ሁሉ ስርዓት ሳይከናወን ያለፍርድ ሰው ከገደልን እኛ ነብሰ ገዳዮች እንሆናለን። አንድ ቀን ደግሞ እኛም ነፍሰ ገዳዮች ተብለን እንረሸናለን። በተጨማሪም የሞት ፍርድ ከባድ ውሳኔ ስለሆነ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ካልተደገፈ መጽደቅ የለበትም አልኩ።

ቀደም ብሎ የተቋቋመው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የሚመሩት መርማሪ ኮሚሽን ያቀረበው ነው በሚል አንድ ሰነድ መጣ። ነገር ግን የኮሚሽኑን ሰነድ ሳይሆን ሌላ ወረቀት ነበር ያቀረቡት። እስረኞቹን ከ15 ዓመት ፣ ከ10 ዓመት በፊት እና በመጨረሻ የተያዙ በሚል በተያዙበት ጊዜ በሦስት ዝርዝር ከፍሎ ነው የሚያስቀምጠው። እኔ ቀደም ብዬ ተመልክቼው ስለነበረ ይሄ የወንጀለኛነታቸውን ደረጃ የሚገልጽ አይደለም። በወንጀለኛነትማ ቢሆን ኖሮ መጨረሻ የተያዙት ነበሩ በአንደኛ ደረጃ መጠየቅ የነበረባቸው ስል ወዲያው ተሻረ።

በዚህ ጊዜ መንግስቱ ዝርዝራቸውን አምጡልን እና አንድ በአንድ እኛ እንወስናለን አለ። ዝርዝራቸው መጣ። አንድ በአንድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጀምሮ ስም እየተጠራ ድምጽ እየተሰጠ ከሁለት ሶስተኛ ከበለጠ እንዲገደል ካልሞላ እንዲተርፍ ተወሰነ። ይህች ሁለት ሶስተኛ የተባለች ነገር ብዙ ሰው አዳነች። ሌላው መትረፊያ መንገድ የነበረው አለመታወቅ ነው። አለመታወቅ ጥሩ ነገር ነው። ካልታወቅክ በጎም ሆነ መጥፎ ታሪክ ስለማይነሳብህ ትታለፋለህ። በዚህ የተረፉ ብዙ አሉ። ሌላ ደግሞ በጥሩ የምናውቃቸው ሰዎች ሲሆኑ እንናገር ነበር። እኔም እየተነሳሁ ተራማጅ ነበር ጸረ ፊዩዳል ነበር እንዲህ እንዲህ አድርጓል እያልኩ ለብዙ ሰው ተናግሬያለሁ። ለምሳሌ አንድ ትዝ የሚሉኝ ታምራት ይገዙ የሚባሉ (ማዕረጋቸውን አላስታውሰውም) ስማቸው ሲጠራ ተነሳሁና እኚህ ሰውዬ ድሃ የሚወዱ በጣም ጥሩ ሰው ናቸው። እንደሰማሁት ግርማሜ ነዋይ ጅግጅጋ እያለ ሲያደርግ እንደነበረው ሴት እንስራ ተሸክማ ስትሄድ በመኪና ጭነው ወደ ምትፈልግበት ያደርሳሉ እየተባሉ የሚመሰገኑ ናቸው አልኩኝ። መንግስቱ አሄሄ እልም ያለ ፊውዳል ነው አለና አለቀላቸው። በዚህ አይነት ያዳንናቸውም ብዙ ሰዎች አሉ።

ዘመን፡- የደርግ አባላት እውቀቱ እና ልምዱ ሳይኖራቸው ድንገት መጥተው የኢትዮጵያውያን ህዝብ 17 ዓመታት በመምራታቸው ከእስር ያለፈ ነገር ይገባቸው ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እኔ እስር ወይም ሌላ ነገር ይገባን ነበር አልልም። ምክንያቱም እኛ ባለን ችሎታ የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ ጥረናል። ያን ጊዜ ዋናው ጦርነት ኤርትራን ለመገንጠል ነበር። ኤርትራ እንዳትገነጠል እየተዋጋንም በሰላምም ለመፍታት ብዙ የተቻለንን ነገር ስናደርግ ቆይተናል። ለምሳሌ አንድ ጊዜ የሰላም ጉባዔ የሚባል ተቋቁሞ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገናቸው የነበሩት ልጅ ሚካኤል እምሩ የሚመሩት እኔም ያለሁበት ቡድን ተገንጣዮችን የሚደግፉትና በዩኒቨርሲቲዎቻቸው የሚያስተምሯቸው አረቦች ስለነበሩ ሳውዲ አረቢያ ስትቀር ኩዌይት ፣ ኢራቅ ፣ ሶሪያ ፣ ቤሩት እና ሌሎች አረብ አገራት ተጉዘን የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት ድጋፋቸውን እንዲያቋርጡ የማግባባት ስራ ሰርተናል።

ዘመን፡- ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም የኤርትራን መገንጠል ይደግፉ ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እርሳቸው መገንጠልን አይደግፉም። እንደውም እርሳቸው ያሉትን ብንከተል ኖሮ ይሄ ሁሉ ነገር አይደርስም ነበር። ሊቀመንበር አድርገን እንደመረጥናቸው ወደ ኤርትራ ሄደው ጉብኘት አደረጉ። ሕዝቡን በስታዲየም ሰብስበው አነጋገሩ። ከተመለሱ በኋላ የኤርትራን ችግር መፍታት ቀላል ነው ፤ ፌዴሬሽኑን መመለስ ብቻ ነው አሉ። እነርሱ የሚጠይቁት ፌዴሬሽኑ እንዲመለስ ነው። ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብለው የታገሉ ሰዎች ስለሆኑ ፌዴሬሽኑ ከተመለሰላቸው ችግሩ ይፈታል ሲሉ ፣ መንግስቱ ራሱን ጨበጠ። ፌዴሬሽን ማለት ለመገንጠል የመጀመሪያ እርምጃ ነው አለና በዚህ ቀረ። ፌዴሬሽኑ ቢመለስላቸው ኖሮ ኤርትራ

 አትገነጠልም ነበር።

ዘመን፡- ባለንብት ታህሳስ ወር በ1967 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ብሔራዊ የእድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ መነሻ ሀሳብ እንዴት መጣ ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- መነሻ ሀሳቡ የመጣው ከእኔ ወንድም ነው። ፍስሃ ባይህ ይባላል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የትብብር ማህበር መሪ ነበር። እኔ ከሐረር መጥቼ እርሱ ጋር ነበር ያረፍኩት። በፊት ብሔራዊ አግልግሎት የሚባል ነገር ነበር። ከየኮሌጁ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት የቀራቸው ተማሪዎች በየጠቅላይ ግዛቱ ወደሚገኙ ገጠሮች ተልከው ለአንድ ዓመት በአስተማሪነት እያገለገሉ ይመለሳሉ። ወንድሜም ጎጃም ተልኮ አስተምሮ መጥቷል። አንድ ቀን ከብሔራዊ አገልግሎት በተለየ መልኩ ተማሪዎችን ወደ ገጠር በመላክ ገበሬውን እንዲያነቁትና እንዲያገለግሉት ማድረግ ያስፈልጋል አለኝ። ይሄ ሊሆን የሚችል ነገር አይደልም የት አርፈው የት እየኖሩ ብዬ ተከራከርኩት። ለተማሪዎቹ ገንዘብ በመስጠት ከገበሬው ጋር እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል። ይህ ገበሬውንም መርዳት ነው። በዚህ መንገድ ገበሬውን ማንቃትና ማስተማር ይቻላል አለኝ።

አራት አምስት ቀን ከተከራከርን በኋላ እሺ አልኩና እኔም ለደርግ አቀረብኩ። ተቀባይነት አገኘና ጥናት እንዲደረግ ተባለ። ጥናቱ ተጠናቆ ሲቀርብ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው ሀሳብ ተተንትኖ ማብራሪያ ይቅረብለት ተባለ። ዶክተር አብይ ክፍሌና ዶክተር ገብረ እግዚአብሔር የሚባሉ ከእኛ ጋር የዊንጌት ተማሪዎች የነበሩ እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ጉዳዩን እንዲያጠኑ ተመረጠው በደንብ አድርገው ተንትነው አምጥተው ጸደቀ።

የዕድገት በህብረት ዓላማው ምንድን ነው ሲባል አንደኛ የኢትዮጵያ ትቅደምን ዓላማ ለገበሬው ለማስረዳት። ሁለተኛ የግብርና እና ሌሎች ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ ተብሎ እንደ እርሻ ኮሌጅ ካሉ የሙያ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ነው ተማሪዎች እንዲዘምቱ የተወሰነው። ከዚያ በጃን ሜዳ ትልቅ ሰልፍ ተደረገ። አስታውሳለሁ ጀነራል ተፈሪ መሃል መንግስቱና አጥናፉ ግራና ቀኝ ሆነው በጂፕ ሲዞሩ ቪቫ መንግስቱ ተባለ። በአስቸኳይ ተሰፍቶላቸው ዩኒፎርም ለብሰው ነበር። ፕሮቶኮሎች ለመሪዎቹ እንጂ ለእኔ ትኩረት ስላልሰጡኝ ከሕዝቡ ጋር አንድ ደረጃ ላይ ነበር ቁጭ ያልኩት። ተማሪዎቹ ከጃንሜዳ ሲወጡ እየዘመሩና እየጨፈሩ ብዙ ዞሩ።

ዘመን፡- አሸባሪውን ሕወሓት ከውልደቱ ጀምሮ ያውቁታል። መጨረሻው ምን የሚሆን ይመስሎታል ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ሕወሓት አልቆለታል። መጨረሻው መደምሰስ ነው። እኔ እንደውም መቀሌ ሳይገቡ ማቆማቸው ደስ አላለኝም። የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ የገባን እንደሆነ ይወነጅሉናል ምን እንዳጠመዱብን አናውቅም ብሎ የተናገረው ለእኔ አልተዋጠልኝም። እንደ እኔ እዚያው ድረስ ገብቶ ፋብሪካ እያፈራረሱ በደንብ በሰለጠነ ባለሙያ እየነቀሉ የወሰዱትን ንብረት ሁሉ ማስመለስ አለበት። አመራሩንም ደግሞ ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ይገባል እንጂ ደርሶ ከቦ መቀመጥ አልተዋጠልኝም።

ዘመን፡- ሕወሓት በጦር ሜዳ የሚሞቱ አመራሮቹን አንገት ቆርጦ በመውሰድ እንዲሁም በአማራ እና አፋር ክልል ነዋሪዎች ላይ የከፋ በደል በመፈጸም ያሳየውን የጭካኔ ደረጃ እንዴት ይመለከቱታል ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡-አረመኔዎች ናቸው። አንድ ሰው ሲገልጻቸው ሰዎች አይደሉም፤ ሰይጣንም አይደሉም ምክንያቱም ከሰይጣንም የባሱ ናቸው ብሏል። ይሄ ነው እነርሱን ሊገልጻቸው የሚችለው። አረመኔዎች ናቸው። ማውደም ፣ ማጥፋት ፣ መዝረፍ እና መግደል ነው ስራቸው። ከተፈጥሯቸው ጀምሮ ወንበዴዎች ናቸው። ውንብድናው ቀደም ብሎ የተጀመረ ነው። አሁን ያለው ትውልዳቸው በውንብድና ተፈጥሮ በውንብድና ያደገ ስለሆነ መግደልና ማጥፋት እንጂ ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም። ሕውሓትን እስከመጨረሻው መደምሰስ ነው ፤ ደግሞም ይደመሰሳሉ። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ የሰላም አገር ትሆናለች።

ዘመን፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ እንዳገለገለ አንድ ሰው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕወሓት የሚፈፅመውን ይሄን ሁሉ ግፍ እንዳላየ ማለፉ ከምን የመነጨ ይመስሎታል ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ጥላቻ ነዋ! ኢትዮጵያ ለእነርሱ ያልተንበረከከች በነጻነት የኖረች እና ለሌሎች ነጻነት የታገለች ምሳሌ የሆነች አገር ስለሆነች አምርረው ይጠሏታል። ስለዚህ እያወቁ እንዳላወቁ በመሆን እውነቱን እየገለበጡ በሌላ መንገድ ያቀርቡታል።

ዘመን፡- ሕወሓት ደርግን አሸንፏል ማለት ይቻላል ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ሕወሓትን ሻቢያ ነው አዝሎ ወደ አዲስ አበባ ያመጣው። ስለዚህ ሕወሓት ደርግን አሸንፏል አልልም።

ዘመን፡- ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም ከአገር ሸሽተው ወደ ዚምቧቤ መሄዳቸውን በምን ሁኔታ ነው የሰሙት ? ከአገር ይሸሻሉ ብለወ ገምተው ነበር ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- አዎ ገምቻለሁ። አንደኛ ከብዙ ወራት አስቀድሞ አንድ ወንድሙ እንደሆነ የሚነገር ነገር ግን አጎቱ የሆነ አስራት የሚባል ሞስኮ አምባሳደር የነበረን ሰው ቀደም ብሎ ወደ ዚምቧቤ አዘዋውሮት የእርሻ መሬት እንዲገዛ እንዳደረገው ስሰማ መጠራጠር ጀምሬ ነበር። ከዚያም ልጆቹን ወደዚያው ላከ ይሄም ምልክት ነበር። በመቀጠል ከዙምባብዌ አንድ መልክተኛ መጥቶ ፕሬዚዳንቱን ባነጋገረ በማግስቱ መንግሥቱ ገመቹ እና ተስፋዬ ወልደስላሴ መጥተው እኛን እንዲሁም ዋናዎቹን የመንግሥት ባለሥልጣን ሚኒስትሮችን እና ሌሎችንም ጠርተው ሰብስበው ‹‹ይሄ ጦርነት እንዳይቆም ያደረገው ሊቀመንበሩ ነው በማለት ሕዝቡ እየተማረረ ስለሆነ በዚህ ምክንያት ፕሬዚዳንቱ ‹ሄጃለው› ብለውን ሸኝተናቸው መጣን›› ብለው ነገሩን።

ዘመን፦ ለሕዝብ ከመነገሩ በፊት ነው ይህን የሰማችሁት ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- አዎ! ከዚያም ከውጭ ወሬው ሳይሰማ ስድስት ሰዓት ከመድረሱ በፊት መግለጫ ይዘጋጅ ተብሎ እኔ የምመራው ቡድን ተመረጠ። በሰማነው መልኩ ነው ወይ መግለጫው የሚወጣው ብዬ ጠይቄ አዎ ተባልኩኝ። እኔ እንኳን ጠፍቶና ፈርጥጦ እንደሄደ እንዲገለጽ ነበር የፈለኩት። በተባለው መልኩ መግለጫው ተዘጋጀ፤ በስድስት ሰዓት ተገለጸ። ማታ ደግሞ ፈረጠጠ ተብሎ ተሻሽሎ ተነገረ።

ዘመን፦ እርስዎ በወቅቱ በግልዎ ምን አደረጉ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ወንበዴው አዲስ አበባን እየከበበ አምቦ እና የተለያዩ አካባቢዎች ደርሷል። ይሄ ሲሆን እኔ ቤተሰቦቼን በተለይ ልጆቼ በወንበዴ እንዳይዋረዱና ሞራላቸው እንዳይነካ በማለት ቀደም አድርጌ ሁለት ሳምንት፣ ሶስት ሳምንት አጎታቸው ዘንድ አሜሪካ ልኬአቸዋለሁ። ባለቤቴ ደግሞ በዚህ ሁኔታ እንዴት ትቼህ እሄዳለሁ ብላ መሄድ አልፈልግም ብላ አስቸግራ ነበር። ተቆጥቼ ነው በግድ በመጨረሻው አውሮፕላን እያለቀሰች የሄደችው። ፓይለቱ ሲመጣ መሄዷን ስጠይቀው እኔ ከሃዲ ነኝ፤ በዚህ ጊዜ ጥዪው የምሄድ እያሉ ሰውን ሁሉ እያስለቀሱ፤ በነርስና በሲስተር እየተደገፉ ነው ተሸክመው ያገቧቸው ብሎ ነገረኝ።

ዘመን፦ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ እንዴት ገቡ ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- በዚያ ወቅት እኔ ወስኛለሁ። ወንበዴ ሲገባ ቢሮዬ ከሆንኩኝ ወንበሬ ላይ ቁጭ እንዳልኩኝ ሱፍ ልብስ እንደለበስኩኝ በጥይት ጭንቅላቴን እመታለሁ። መኝታ ቤቴ እያለሁ ከሆነ አልጋ ላይ እያለሁ ራሴን እገላለሁ። ከሁሉም የምመርጠው አራት ኪሎ የነጻነት ሃውልት ስር ሆኜ ራሴን ብገድል ብዬ ወስኛለሁ። ማታ ወደ ቤቴ ሲሄድ ልጆቼ የሉ፤ ባለቤቴ የለች፤ ከሠራተኛ በቀር ብቻዬን ሆንኩኝ። ማታ ላይ ወንዱ ልጄ ደውሎ ‹‹ሰው ሁሉ እነዚህ ሰዎች እስከ አሁን ታገሉ፣ ታገሉ፤ አሁን መጨረሻው እንዲህ ሲሆን ለምን ከንቱ ይሞታሉ እያለ ነውና ለምን አትወጡም? ›› አለኝ።

እኔ እዚህ እሞታለሁ እንጂ አገሬን ጥዬ አልሄድም። እስከ አሁን ያስተዳደርነውን ሕዝብ ጥዬ አልሄድም፤ ሕዝቡ የሆነውን እሆናለሁ ብዬ አልኩት። ከዚያም ሴቷ ልጄ እነማን እነማን አሉ ብላ አነጋገረችኝ። ጄነራል አዲስ፤ ጄነራል ተስፋዬ እንዲሁም ሌሎችም አሉ ስላት እነሱ ካሉማ አብሮ መሆን ነው እንጂ ክህደት ነው በማለት

 አበረታታችኝ። ጠዋት ተመልሼ ወደ ቢሮዬ ስሄድ ስርዓት የለም፤ ወታደሩ ግማሹ ተኝቷል፣ ሌላው በየፊናው ይንቀሳቀሳል። ቢሮ ስገባ ፀሐፊዎቼ፣ ረዳቴ ሁሉ የሉም። እየደወልኩ ጠራሁኝ፤ መጡ። እንዴት ጥላችሁ ትሄዳላችሁ አልኳቸው። መድፍ ሲጠመድ አይተዋል፤ እኔም በመስኮት ሲጠመድ አይቻለሁ። ሌላው ደግሞ ይዘርፋል፤ አንዳንዱ ዱቄት የመሳሰሉትን ተሸክሞ መኪና ላይ ሲጭን አያለሁ። ገንዘብ ሲዘርፉ ተጋድለዋል የሚባልም አለ። ይህን የመሳሰሉ ድርጊት እየተፈፀመ ስለነበረ እንሂድ ብዬ ወደ ቤቴ መንገድ ጀመርን። ከዚያም ከኋላ ክላክስ ተነፋ፤ ምንድን ነው ስል ከጀነራል ተስፋዬ ጋር አልተነጋገራችሁም ወይ አለኝ። ጣሊያን ኤንባሲ እንግባ ሲል ነበር አልኩኝ። ለማንኛውም ወደ ቤት ከመሄድ ጣሊያን ኤንባሲ እንጠይቅ ብለውኝ ሄድን። ኤንባሲው ጋ ስንደርስ ጠባቂዬን ጠይቅ ብዬ ላኩት። ጣሊያን ኤንባሲ ገብተዋል ብሎ ነገረኝ፤ ክላሽኮቭ ጠበንጃ፣ ሽጉጥ እና የጦር ሜዳ መነጽር እንደያዝኩኝ ገባሁ። ሁሉም መሳሪያ አሁን ስወጣ ኤንባሲው ውስጥ ነው የቀረው። በኋላ ላይ ሳጣራ ጀነራል ተስፋዬ አልገባም ነበር። የነገረኝ ሰው ዋሽቶኛል፤ ወይም ለእሱ የነገረው ሰው ዋሽቶታል።

ዘመን፦ ‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የነበረዎትን የሕይወት ተሞክሮ በሚገባ ገልጸውታል። ከደርግ ምስረታ ጀምሮ አባላት እንዴት እንደተገዳደሉና እንደተበላሉ ፊልም በሚመስል መልክ ተርከዋል። ነገር ግን የኢንባሲ ቆይታዎት ብዙ ዓመታት ሆኖ ሳለ ጥቂት ገፆች ብቻ በመስጠት ነው ያለፉት ይህ ለምን ሆነ? የእነ ጀነራል ተስፋዪ ገብረኪዳንን አሟሟት ላለማንሳት ይሆን?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እስከ ገባሁበት ድረስ ነው የገለጽኩት፤ታሪኩ እዛ ላይ አበቃ። ኢንባሲ ውስጥ ያለውን ኑሮ አልገለጽኩትም። ከአሁን በፊትም ብዙ ሰዎች ይሄን ጥያቄ አንስተዋል። ለምሳሌ ሰዎች ሞተዋል፤ ኃይሉ ይመኑ ሞቷል፣ ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ሞቷል። ፋሲካ ሲደልል እና ሌሎችም ኢንባሲው ውስጥ ገብተው ነበር፤ በማግስቱ ወጡ። የወጡበት ምክንያት የጣሊያን ወታደሮች አቶማቲክ መሳሪያ ታጥቀው መጥተው በማስፈራራታቸው ነው። አዚህ መግባታችሁ ታውቆ ጋዜጠኞች መጥተው እየጠበቁ ነውና ውጡ ብለውም ነበር። እኔ ከፈለጋችሁ ግደሉኝ፤ አልወጣም ብዬ አልኩኝ። ማምረሬን ሲያዩ መስማማት ጀመሩ። በወቅቱ ኃይሉ ይመኑ ሁኔታው ስላልተመቸው ጤነኛ አልነበረም፤ አልተዋጠለትም። ልብስ አይለብስም፤ በቢጃማ ብቻ ይንቀሳቀስ ነበር።

ወታደሩ መጥቶ አስጠንቅቆና ፎክሮ ከሄደ በኋላ ሽንት ቤት ገብቶ ቆለፈ። ከቆይታ በኋላ ኃይሉ ጋር ሄጄ እኔ ነኝ ክፈትልኝ እኔም ራሴን ማጥፋት እፈልጋለሁ አልኩት፤ ከፈተልኝ። ከፍቼ ስገባ ፊቱን ወደ ባኞ አድርጎ ሽጉጡን ጭንቅላቱ ላይ ደግኖ ቆሟል። ለምን ትቸኩላለህ? አትቸኩል፤ ለማስፈራራት ነው እንጂ ምንም አያደርጉንም፤ አያስወጡንም። ምክንያቱም ሕግ ስለማይፈቅድላቸው አይችሉም። ቀደም ሲልም ወያኔ ጠይቆ የሞት ፍርድ ላለበት አገር አሳልፈን አንሰጥም ፤ ሕገ መንግሥታችን አይፈቅድም ብለውታል። ይሄ ስለሆነ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለምና አትቸኩል አልኩት። እሱ ወደ ባኞ ፊቱን አዝሮ እንደቆመ ግው የሚል የመሳሪያ ድምፅ ሰማሁ። ዞር ስል ዱብ ብሎ ደሙ በጆሮ ግንዱ ነው የመጣው፤ በዚህ ሁኔታ ሕይወቱ አለፈ። እኔም የኃይሉ ይመኑን ሽጉጥ እንደምንም ብዬ ፈልቅቄ ወስጄ ወደ ጭንቅላቴ ሳደርግ ጣሊያኖቹ ብርሃኑ ራስህን እንዳትገድል፤ መውጣታችሁ ቀርቷል እያሉ እየሮጡ መጡ፤ ራሴን ማጥፋቱን ተውኩት።

የጄነራል ተስፋዬ አሟሟት ደግሞ ኤንባሲው ውስጥ ብዙ ጊዜ አብረን ከቆየን በኋላ ኤንባሲው መቀለቡን አቁሞ ቤተሰቦቻችን እንዲቀልቡን አደረገ። ስለሆነም የተወሰነ ገንዘብ እያዋጣን አንድ አንድ ወር በሠራተኛ እናዘጋጃለን። በዚህ ጊዜ አለመግባባት ስለተፈጠረ የየራሳችንን እናድርግ ተባለ። የማይሠራ ነገር ነው ግን ተሞከረ። ጀኔራል ተስፋዬ አንድ ቀን ይህ ሁኔታ በዚህ የሚቀጥል ይመስልሃል አለኝ። ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል ብዬ መለስኩለት። እሱም ልንገዳደል እንችላለን አለኝ። እኔ አንተን አልገድልህም ፤ እገድላለሁ ብዬም አላስብም፤ አንተ እገላለሁ ካልክ ሞክር። እንኳን ከፎከረ ከወረወረ ያድናል እንደሚባለው ምንም አያሳስበኝም አልኩት። ይሄን ባልኩት በወሩ አካባቢ ጣሊያኖች ግብዣ አዘጋጅተው ስለነበረ የጣሊያኖች ጠባቂ ወታደር እኔና ጀነራል አዲስ ወክ እያደረግን እያለን ነገ እንዳትወጡ ብሎ ነገረን። እኔም የነገረንን ሰው እግባባው ስለነበረ እንደቀልድ ነገ እኔ እወጣለሁ አልኩት።

ጄነራል ተስፋዬ ከእኔ ጋር ከተቃቃርን በኋላ ብቻውን ወክ ስለሚያደርግ የተነጋገርነውን ስላልሰማ የድግሱ ቀን ጠዋት ወክ ሊያደርግ ሲሞክር ትናንት አትውጡ ብለን አልነበረም እንዴ ይሉታል። እኛ አልወጣንም ነበር። እኔና ጄነራል አዲስ አጠገብ ለአጠገብ ሆነን ቁርስ እየበላን ጄነራል ተስፋዬ እሳት ጎርሶ፣ እሳት ለብሶ መጣና ለጄነራል አዲስ ትናንት እንዳትወጡ ተብሎ ተነግሯችሁ ነበር ወይ ብሎ ጠየቀው። እሱም እንደትዕዛዝ ሳይሆን እንደቀልድ ነው ብሎ ስለመለሰለት ሄደ። ጄነራል ተስፋዬ ተመልሶ ይበልጥ ተናዶ መጣና አንተስ ብርሃኑ? ብሎ ጠየቀኝ፤ አዎ! ተነግሮኝ ነበር ብዬ መለስኩለት። ታዲያ ለምን አልነገርከኝም አለና የፕላስቲክ ጠርሙስ ወረወረ፤ በመቀጠል በቦክስ ለመምታት ሲሞክር ብድግ አልኩኝና ሁለት እጁን አንድ ላይ ያዝኩት። ቆዳ ጫማ አድርጎ ስለነበረ ወደ ኋላ አንሸራቶት መስታወቱን ሰበረው።

ቀኑ ቢደርስ ነው እንጂ ብረቱን ቢመታው መስታወቱን አይሰብረውም ነበር። መስታወቱን ከሰበረው በኋላ ታጣፊ ጠረጴዛ ላይ ደገፍ አለ፤ ጠረጴዛው እጥፍ ሲል ወደ ተሰበረው መስታወት ሲወድቅ ሹሉ ከማጅራቱ በላይ ያለውን የጭንቅላት ክፍል ይቀደዋል። ከዚያም ስንያያዝ ሠራተኛዋ ጮኸች፤ ዘበኛው ሰምቶ መጣ። ተያይዘን መጀመሪያ ጠረጴዛ ላይ ወደቅን፤ በመቀጠል ጄነራል አዲስ ተነስቶ ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ ጠረጴዛው ስለተንሸራተተ መሬት ላይ እኔ ከላይ እሱ ከታች ሆነን ወደቅን። ዘበኛው እጄን እየጎተተኝ ሳለ ጄነራል ተስፋዬ አፍንጫዬ ላይ በቦክስ በቀለበቱ ስለመታኝ ደማሁ፤ ነጭ ልብስ ነበር የለበስኩት ልብሱ ደም በደም ሆነ። ከወደኩበት ከተነሳሁ በኋላ እንደገና በካልቾ ብልቴ ላይ ሊመታኝ ሲል እግሩን ያዝኩትና ወደ ላይ ሳደርገው መስታወቱን ሰብሮ ተያይዘን ወደቅን። ከዚያም ዘበኛው እንዳነሳን እሱ ሽንት ቤት ሲገባ የኤንባሲው ሀኪሞች ከግብዣው ተጠርተው መጡ። ሀኪሙ ማድረግ የነበረበት ከቻለ ራሱ መስፋት፤ ካልቻለ ወስዶ ማሰፋት ነበረበት። ከግብዣው ላይ ተነስቶ ስለመጣ ቸኩሏል። በፋሻ ጠምጥሞ፣ ጠምጥሞ እንዲተኛ አድርጎ ይሄዳል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይጮሃል፤ ጄነራል አዲስ ሲሄድ ሽንት ቤት ውሰደኝ ይለዋል። በእግሩ መሄድ አልቻለም በዊልቸር እየገፋ ሽንት ቤት አድርሶት ከተመለሰ በኋላ ይተኛል። ከዚያም ሚኒሊክ ሆስፒታል ሄደ ተባለ፤ ሞተ።

ዘመን፦ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ምንድን ነው ?

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፡ – የማስተላልፈው መልዕክት አንደኛ ሕዝቡ ህብረቱን ጠብቆ አንድ እንዲሆን ነው። በዘርም ሆነ በሌላ ነገር መከፋፈል ፍፁም ቀርቶ አንድነቱን እንዲያጠናክርና ለዕድገትና ለብልጽግና መስራት ይገባዋል። ሁለተኛ የሰላም ጠንቅ የሆነውን ወያኔን እስከመጨረሻ ደምስሶ ሙሉ ሰላም አስፍኖ ተስፋውን ማለምለም ይጠበቅበታል። ሌላው አሁን ያለው የክልሎች አከፋፈል ስያሜ አማራ፣ ኦሮሞ፣ትግራይ ወዘተ. የሚለው የዘር አከፋፈልም መለወጥ አለበት እላለሁ። በተለይ አማራ የሚለው ክልል መጠሪያን ስሰማ ቅር ይለኛል። አማራ ከማለት ወይም እንደድሮው ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወዘተ. መባል አለበት እንጂ አማራ በሚለው መጠራቱ በፍጹም ደስ አይለኝም። አማራ የኢትዮጵያዊነት ዋና መሰረቱ ነው። ሁልጊዜም ኢትዮጵያዊነትን ሲያቀነቅን የኖረና የሚያቀነቅን ነው።

ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ሳሙኤል ይትባረክ እና የትናየት ፈሩ

ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም

Recommended For You