አሸባሪው ሕወሓትን ድባቅ በመምታት የለኮሰውን አውዳሚ ጦርነት በድል በማጠናቀቅ ላይ አንገኛለን። ይሁን እንጂ በጦርነቱ ሂደት የደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ግን ለዓመታት ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ስለዚህም የድሉ ባለቤት ለሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ከደረሰው ሰብአዊ ጉዳት የመጽናናት፣ ቁሳዊ ጉዳቱን የመመለስ ብርቱ የመልሶ ግንባታ ትግል ይጠብቃቸዋል።
በተለይ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎች ወገኖቻቸውን በአሸባሪው ቡድን ሰይፍ አጥተዋል፤ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ በሚያዋርድ የሽብር ቡድኑ ድርጊቶች የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህ ሁሉ ወገኖቻችንን የማጽናናት፣ የማሳከም፣ የማበረታታት የቤት ሥራ አለብን። በርካቶች ሀብታቸውን ንብረቶቻቸውን አጥተዋል፤ ተቃጥሏል ወይም ተዘርፏል። የጋራ የሆኑ የጤና፣ የትምህርት፣ የመሳሰሉት መገልገያዎች በቡድኑ የምቀኝነት መንፈስ ሆን ተብሎ እንዲወድሙ፣ እንዲዘረፉ ተደርጓል። እነዚህም ፈጣን የመልሶ ግንባታ ምላሽ የሚፈልጉ የቤት ሥራዎቻችን ናቸው።
መንግሥት የመልሶ ግንባታ ሴክሬቴሪያት በማቋቋም ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ የማስተባበርና ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ ወደ ተግባር የመግባት ግዴታ አለበት። የመልሶ ግንባታ ምላሽ የሚፈልጉ አንዳንዱ ጉዳዮች በጊዜው ምላሽ ካላገኙ የበለጠ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ሊያወሳስቡ እንደሚችሉ ከግምት በማስገባት አጣዳፊና ስልታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ለይቶ ምላሽ መስጠት ብልህነት ነው።
ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልገው የገንዘብ ወጪ በብዙ አማራጮች የማሰባሰብ ሥራው መፍጠን አለበት። የወዳጅ አገራትን፣ የክልሎችን ወንድማዊ ትብብሮች፣ የዲያስፖራውን ድጋፍ፣ አቅም ያላቸውን መላውን የአገራችን ዜጎች ሁለንተናዊ ለወገን ደራሽነት ሁሉ ማቀናጀት በፍጥነት ሊሠራ ይገባዋል። የተማሪዎች የትምህርት፣ የበልግ እርሻ፣ የቀጣዩ መኸር የእርሻ ጊዜን ታሳቢ ተደርጎ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ የመግሥትንም ሆነ የህዝብን የመልሶ ግንባታ ጫና እያቀለለ ሊሄድ እንደሚችል እናምናለን። ለእነዚህ ተግባራት የሚያስፈልግ ግብዓትን በተቻለ ፍጥነት ማቅረብ ቢቻል በርካቶችን በቀላሉ በአንድ ዓይነት ጊዜ ውስጥ የህልውና ስጋቶቻቸውን መቅረፍ ይቻላል። ከስደትና ምሬት ገላግሎም ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረግ ይቻላል። የወደሙ የጤና ተቋማት ጉዳት ባልደረሰባቸው ሌሎች የአገራችን ተቋማት በቁሳቁስና በሰው ኃይል የሚደገፉበት፣ በመላው ዓለም ያሉ በጤና መስክ የሚሠሩ ደጋፊና ረጂ አካላትን ሁሉ በር በማንኳኳት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት መሞከር ያስፈልጋል።
የመልሶ ግንባታውን በፍጥነት ጀምሮ በአዎንታዊ ሁኔታ ማስኬድ የሽብር ቡድኑንና የሚደግፉትን እኩይ ኃይላት ሁሉ ቅስም የሚሰብርና ከአገራችን ላይ እጃቸውን እንዲያነሡ ግፊት የሚያሳድርም ይሆናል። ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ሕወሓትን ለመቅብር አስገራሚ አገራዊ አንድነት ተፈጥሯል። ውጤትም ተመዝግቧል። አሁን ደግሞ የተፈጠረውን አገራዊ አንድነት የሕወሓትን የክፋት ሕዋስ ከማጥፋት ጎን ለጎን ለመልሶ ግንባታውም እናውለው እንላለን።
ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም