የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የክህደት ጥቃትን ተከትሎ ለስምንት ወራት በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠቃሽ ተሳትፎ ካደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ መከላከያ ከትግራይ ከወጣ በኋላም ከሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመውን መጠነ ሰፊ ወረራ ለመመከት እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። ዘመን መጽሔት በተለያዩ ግንባሮች በመገኘት ህዝብ የማንቃትና የማደራጀት ሥራ እየሰሩ ካሉት የንቅናቄው አመራሮች መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ የሱፍ ኢብራሒም ጋር በህልውና ዘመቻው እያደረጉ ያሉትን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ቆይታ አድርጋለች፤እንደሚከተለው ቀርቧል።
ዘመን ፡- በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ሆነው ተሹመዋል። ከመንግሥት ጋር ስልጣን ተጋርቶ መስራትን እንዴት አገኙት?
አቶ የሱፍ ፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካና ማህበራዊ ሁኔታ እጅግ በጣም ፈታኝ የሆነ ፤ በምስቅልቅል የተሞላ እና ቀደም ሲልም ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነው። ከውጭም ከውስጥም ያሉ ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች በቅንጅትና በሴራ በህዝብና በአገር ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽመዋል። እኛ እንደ አብን የአገራችን ችግር በአንድ አካል ብቻ እልባት የሚያገኝ አይደለም የሚል ጥቅል አቋም አለን። በጎ አገራዊ ኃይሎች በተናጠል በጥቃቅን ልዩነቶች የታጠረ ፖለቲካ ከመምራት ይልቅ ያለውን አገራዊ ችግርና አደጋ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተሻለ ትብብር ማድረግ አለባቸው።
ከመንግሥት ጋር መሰረታዊ የሚባሉ በርካታ ልዩነቶች እንደነበሩን ይታወቃል። ነገር ግን ኢትዮጵያን በተመለከተ የማያወላዳ አቋም አለን። እኛ ጉዳያችን የጥሬ ስልጣን ግብግብ አይደለም። ህዝባችንና አገራችን ከመዋቅራዊና ስርዓታዊ ችግር መላቀቅ አለባቸው የሚል አቋም ነው የምናራምደው። ከመንግሥት ጋር አብሮ መስራት በሚያስፈልግበት ሰዓት አብረን እንሰራለን። በምንለያይባቸው ጉዳዮች እንለያያለን ፤ በሰለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ ሀሳቦቻችንን ለህዝብ አቅርበን እንወዳደራለን። የፖለቲካ ምህዳሩ ለረጅም ጊዜ ችግር የነበረበት ከመሆኑ አንጻር በአንድ ወቅትና በአንድ ጀምበር ሊፈታ እንደማይችል ስለምንገነዘብ በጊዜ ሂደት የራሳችንን በጎ አስተዋጽኦ እያደረግን መቀጠል ነው የምንፈልገው።
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አብን ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ በክልልና በፌዴራል መንግሥቱ ውክልናዎችን አግኝቷል። ከመንግሥት ጋር አብሮ መስራት የሚለው ሀሳብ በእኛ ጥቅል አጀንዳ ውስጥ ስለነበረ ከምርጫ በኋላ መንግሥት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተወዳደሩና የህዝብ ድጋፍ ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብለናል። መደበኛ በሆነ መንገድ ባይሆንም ቀደም ሲልም ከመንግሥት ጋር ብዙ ነገሮችን በትብብር ስንሰራ ነበር። እኛ በትብብር ችግሮች እልባት ማግኘት አለባቸው ብለን ነው የምናምነው። ማን ሰራቸው የት ቦታ ሆነ የሚለው ለእኛ መሰረታዊ ነገር አይደለም። እኛ ቦታዎችን የምንፈልገውና አማራጮችን የምናቀርበው ቦታና ስልጣኑን ማግኘት ለአገርና ለህዝብ እስከ ጠቀመ ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ ከራሳችንም እሳቤ ጋር አብሮ ስለሚሄድ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ በጥቅሉ ተቀብለነዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታም የተሰጠንን ቦታ ተቀብለን እየሰራን ነው ያለነው።
ዘመን ፡- የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የገዢውን ፓርቲ ፕሮግራሞች የሚያስፈጽም ካቢኔ ውስጥ መካተታቸው ትርጉም የለውም ሲሉ የሚተቹ ወገኖች አሉ። የአብን ምላሽ ምንድ ነው?
አቶ የሱፍ ፡- ችግር የሚፈጥሩት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ማህበረ ፖለቲካ ግልብና ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መንገድ የሚያዩ ሰዎች ናቸው ። ይሄ እንደ አገር የነበረብንን ችግር ፣ የደረሰብንን ጉዳት እና ባሳለፍናቸው ሥርዓቶች በተለይም ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በትህነግ መር ሥርዓት የደረሰብንን አጠቃላይ ችግር የመርሳት አባዜ ነው። በአንድ ጊዜ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ማግኘት እንችላለን የሚል እጅግ በጣም ግብዝ የሆነ አስተሳሰብ አለ። ነባራዊ ሁኔታዎችን ተንትኖ የኃይል አሰላለፉን ተመልክቶ ግራና ቀኝ ያለውን ፍላጎትና አቅም ከግንዛቤ አስገብቶ በአንጻራዊነት የተሻለውን እና በጊዜ ሂደት የጋራ አጀንዳን እውን ለማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ በደንብ የማይፈትሹ አካላት ናቸው እንደዚህ የሚሉት።
እኛ ከመንግሥት ጋር የምንተባበረውና ስንተባበርም የቆየነው በሌላ ጎን ያለውን ኃይል ፍላጎትና አቅም ስለምናውቅ ነው። አገር ለማፍረስ ህዝብን ለመበተን ዘወትር ዝግጁ የሆኑ ለዚህም ጠብ መንጃውንም በጀቱንም ያዘጋጁ ኃይሎች በአንድ በኩል አሉ። በሌላ በኩል ማዕከላዊ መንግሥቱ እንዲጸና እና ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚፈልግ በውስጡ ሰርጎ ገቦችና ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ሰዎች ያሉበት ኃይል አለ። ከዚህ ኃይል ጋር አብረን መስራት አለብን የሚል አቋም አለን። ይህ ኃይል የአገር ሥርዓት ስለሆነ እየተሻሻለና እኛም በውስጡ ቦታ እየያዝን ተባብረን እየሰራን እንቀጥላለን። የምርጫ ስርዓቱ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘውን ብቻ የሚያሳልፍ በመሆኑ ነው እንጂ የተመጣጣኝ ውክልና የሚለው ስርዓት ቢሆን ኖሮ እኛ በርካታ ድምጽ ሊኖረን ይገባ ነበር። ዞሮ ዞሮ የበርካታ ማህበረሰብና የህዝብ ፍላጎት ከእኛ ጀርባ አለ። ስለዚህ ለዚህ ህዝብ ፍላጎት ዘላቂ ጥቅም እና ለኢትዮጵያዊነት ስኬት ለአገር ቀጣይነትና አንድነት ጠቃሚ ነው ያልነውን ሁሉ ነው የምንሰራው።
የተናጠል አንድ የፖለቲካ እሳቤ ሊኖር አይችልም። እኛ መንግሥትን ለመደገፍ አይደለም የምንሰራው። መንግሥት መተቸትና መሻሻል አለበት። ህዝብ ለሚፈልግበትና አደራ ለሰጠው ነገር ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ መልስ ሰጭ ደህንነቱን የሚያስከብር ተቋም እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሄ ግን በአንድ ጀንበር የሚሆን ነገር አይደለም። ድግሞም ከሌላ በይሁንታና በችሮታ ብቻ የሚሰራና በአንድ ወገን የሚከናወን ነው ብለን አናምንም። እኛ ራሳችን ባለድርሻ እንደመሆናችን መጠን በተለይም መንግሥት ያለንን የህዝብ ድጋፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀደም ብለን ስናቀርብ የነበረውን የትብብር ጥያቄ ተቀብሎት አብሮ የመስራት ፍላጎት ሲያሳይ አብረን የማንሰራበት ምንም ምክንያት የለም።
መንግሥት መር የሽግግር ጊዜ እንጂ የሽግግር መንግሥት አያስፈልግም ስንል የሽግግር መንግሥት ቢቋቋም እዚያ ውስጥ አብን የአማራን ህዝብ ወክሎ ሊመጣ እንደሚችል እናውቃለን። ግን ያ ተጨባጭና አዋጭ የሆነ አካሄድ አይደለም። ልክ እንደ 1983 ዓ.ም ህዝባችንን እና አገራችንን ለጽንፈኛ ኃይሎች አሳልፎ የሚሰጥና በጎ አገራዊ ኃይሉን ከጀርባ የሚወጉ ሴረኞችና በአሻጥር የተሞሉ ኃይሎች የሚሰባሰቡበት ማዕከል እንደሆነ ጠንቅቀን ስለምንረዳ በተቃራኒው መስመር መቆም ግድ ስለሆነ ነው።
የውጭ አገር ኃይሎች ከውስጥ ካሉት ጋር በመቀናጀት መንግሥትን ለማስወገድ ርብርብ ሲያደርጉ እኛ ከመንግሥት ባልተናነሰ ከኤምባሲዎችና ከዲፕሎማቲክ ተቋሞች ጋር እየተገናኘን መንግሥትን የምንከላከለው ችግር ስለሌለበትና ብቃት ስላለው ሳይሆን በዛ ደረጃ ኃላፊነት መውሰድ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። አገሪቱ በበጎ ኃይሎች ትብብር ስር መውደቅ አለባት የሚል እምነት ስላለን ነው። በስልጣን ላይ ያለ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ብቻውን ይሄንን አገር ማሻገር ይችላል ብለን አይደለም። በጎ ኃይሉ በተፎካካሪነት የሚሰራቸው ሥራዎች አሉ ፤ ጽኑ የሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ሲመጡ ደግሞ አብረን መስራት አለብን ብለን እናምናለን።
በመንግሥት ውስጥ ሆነን ስንሰራ አንደኛ በሕግ ነው ሁሉም ነገር የሚሰራው። ስልጣን ሲሰጠን በአዋጅ ነው። አዋጁ ደግሞ ደምብ አለው። ራሳችንም አብረን እየተሳተፍን የምናወጣው ነው። መመሪያውንም እዚያው ውስጥ የምናደርገው ነው። ልምድ ይገኝበታል። አብሮ መስራት መተማመንን ያተርፋል። የምናስባቸውን ሃሳቦች በቀጥታ መንግሥታዊ አጀንዳ የማድረግ ዕድልና መብት ይፈጥርልናል። ተቃውሞ ካለን እናስመዘግባለን፤ በአገራችን እና በስርዓታችን ጉዳይ ላይ ጽንፈኛ ሆነን አፍራሽ እርምጃ ሳንወስድ የራሳችንን በጎ ድርሻ እንወጣለን። ለመደበኛ ፖለቲካችንም መንግሥትን ይሄን አድርገሃል አላደረግህም ብለን ለመተቸት ይበልጥ ዕድል እናገኛለን። አኩራፊነትና ጠርዝ ወጥቶ ለአገርና ለህዝብ የማይጠቅም እንቅስቃሴ ማድረግ ተችሏል። በዚህም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በአካል ብቃትም ይሁን በአመለካከት ስራ መክቶ ማሸነፍ የሚችለው ኃይል ወደ ግንበር እየተመመ ነው ያለው። አሁን ከቀን ወደ ቀን የህወሓት ጀንበር እየጠለቀች የሚሸነፍበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። የኃይል ሚዛኑም ወደ ኢትዮጵያዊያን እያመዘነ ነው። በመካከል ግን የተሻሉ የቀውስ ጊዜ አመራሮችን በመስጠት ጉዳቱን መቀነስና አገራችን ላይ የተፈጸሙ ወከባዎችን ማስቀረት የምንችልባቸውን ዕድሎች መፍጠር እንችል ነበር የሚል እምነት አለኝ።
ዘመን፦ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እንገባለን እንዲሁም ከአማራ ጋር ሒሳብ እናወራርዳለን ሲል በአደባባይ ተናግሯል። የድርጅቱ አማራ እና ኢትዮጵያ ጠልነት ከየት መጣ ?
አቶ የሱፍ፦ ሕወሓት ከውሸት የተወለደ ኢትዮጵያዊ እሴት የሌለው ውሸታም ድርጅት ነው። ሲሰራ የቆየው በህዝቦች መካከል በጎ ድንበር ተሸጋሪ ግንኙነቶች እንዳይኖሩ ለማድረግና የነበሩትንም ለማፍረስ ነበር ። ሕወሓት የአማራን ህዝብ ጠላቱ ያደረገው የቅኝ ገዢ ኃይሎች ውላጅና ውርስ የሆነ ሀሳብን በመግዛት ነው። አንደኛ ተፈጥሯዊ በሆነው በመልክዓ ምድር አቀማመጡ የአማራው ቀጠና ወደ ማዕከል በመምጣት ስርዓቱን ለማፍረስ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቀላሉ አልፎት መሄድ የማይችለው ጎረቤት ክልል ስለሆነበት ነው። የአማራ ህዝብ ደግሞ በታሪኩ አገሩን ለማቆየት ከጠላት ፣ ከወረራና ከቅኝ ግዛት ለመከላከል ብዙ ዋጋ ከፍሏል። በየትኛውም የኢትዮጵያ ማዕዘን አጋሩ ወገኑ ሲጠቃ ይዘምታል ፤ መስዋዕትነት ይከፍላል። ይሄ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ የአማራ ህዝብ ጥቅል ማህበራዊ መገለጫው የሆነ ተግባሩ ነው ማለት ይቻላል። ብዙ ጉዳቶችን አስተናግዶ እዚህ ደርሷል። ስለዚህ አንደኛ ምክንያቱ እንደፈለግኩ ኢትዮጵያን አፍርሼ ለሌላ የውጭ አካልና የአገር ውስጥ የሽብር ቡድኖች ሲሳይ እንዳላደርጋት እንቅፋት ይሆንብኛል የሚለው የአማራን ህዝብ ነው።
‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራውንና ክርስትና እምነትን መምታት ነው›› የሚል ግልጽ አቋም ነበራቸው። ከሕወሓት ጋር በተመሳሳይ ዘመን የተመሠረቱ ድርጅቶችም ማኒፌስቷቸው እንዲሁ ነው። ኢትዮጵያን ከአንድ ብሔር ጋር ብቻ በማስተሳሰር ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለመጠበቅ በአርበኝነት በታሪክ የተመዘገቡ የሌሎችን ዜጎች ሚና ሁሉ በመካድ፣ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ ጽንፈኞችን በመፈልፈል ላይ የተመሰረተ ስምሪት ያለው ነው። ስለዚህ የአማራን ሕዝብ መምታት የሚፈልጉት የኢትዮጵያዊነት ወሳኝ አገናኝ ድልድይ ነው ብለው ለሚያመኑ ኃይሎች ስለሚሠሩ ነው። በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድም ልቦለዳዊ ቅራኔ በመፍጠር ማኅበራዊ ጭቆና በሕዝብ ደረጃ እንደነበረና እንዳለ አድርገው የውሸት ትርክት ያራምዱ ነበር።
ዋነኛ መዳረሻው ግን ኢትዮጵያን ማፍረስ ወይም ደግሞ ለዚህ ቡድን ብቻ የምታገለግል ፣ በጭቆናና በአምባገነንነት ቀንበር ውስጥ የምትገኝ እና በሯን ለውጭ ኃይሎች ከፍታ የምትተው ኢትዮጵያን በማበጀት የቀጣሪዎቹ ፍላጎት ለማስፈጸም መንቀሳቀስ ነው። አማራን የሚጠላው ኢትዮጵያን ለማፍረስና ሌሎች ፍላጎቶቿንም እንዳልፈጽም ዋነኛ ተገዳዳሪ ኃይል ይሆንብኛል ብሎ ስለሚያስብ ነው። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ ላይ ተኩስ በተከፈተበት ዕለት ዳንሻ ላይ አምስተኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ላይ ጥቃት በተሰነዘረ ጊዜ የአማራ ሕዝብ ከአርማጭሆና ከአካባቢው ማንም ነጋሪ ሳያስፈልገው መከላከያን ለመታደግ ዘምቷል። ሕወሓት ይህንን ቀድሞም ስለሚገነዘብ ነው አማራን የሚጠላው።
ዘመን፦ አብን በህልውና ዘመቻው እያደረገ ያለው ተሳትፎ ምን ይመስላል?
አቶ የሱፍ ፦ ሕወሓት የኢትዮጵያን መከላከያ በማጥቃት ጦርነት ሲከፍት አብን ግልጽ አቋሙን በመግለጫ አሳውቋል። ይሄ አገር ጠልና ወንጀለኛ ድርጅት ነው። አሁን የመጨረሻውን የአገር ክህደትና የባንዳነት ስሜቱን በተግባር አረጋግጧል። መከላከያን አጥቅቶ ሀገርን ለጠላት ተጋላጭ አድርጓል። ስለዚህ የመጨረሻውን ቀይ መስመር ስለተላለፈ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። በሕግ ጥላ ስር መዋል አለበት የሚል አቋም ነው የወሰደው። መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱ በሚወስደው ስምሪት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ እንዲቆም ሲጠይቅም አብንም በማንኛውም መንገድ በዘመቻው እንደሚሳተፍ አረጋግጦ ከመከላከያው ጎን ተሰልፏል።
አሁንም አባሎቻችን ከመከላከያ ሠራዊት ፣ ከፋኖ ፣ ከሚሊሻውና ከልዩ ኃይሉ ጋር ሆነው ሥራ እየሠሩ ነው። ወጣቶች መከላከያን እንዲቀላቀሉ የማንቃትና የማደራጀት እንዲሁም ማኅበረሰቡ ደጀን እንዲሆንና ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠር ደኅንቱን እንዲያስጠብቅ እና ማናቸውንም የመንግሥት አቅጣጫ እየተቀበለ ትብብር እንዲያደርግ እያስተባበርን እንገኛለን።
ዘመን፦ በወሎ ግንባር ተገኝተው ህዝብን የማደራጀት ሥራ ሲሰሩ ከነበሩት የአብን አመራሮች መካከል እርስዎ አንዱ ነበሩ። በወሎ የተደረገውን ተጋድሎና አሁናዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ የሱፍ ፦በወሎ የነበረው ሁኔታ ከባድ ነበር። ከራያ አላማጣ ጀምሮ ቆቦ ፣ ሮቢት፣ ወልዲያ፣ መርሳና ሌሎችም በዚያ አካባቢ በነበሩ ሕወሓት በወረራቸው አካባቢዎች የነበረው ሕዝብ በጅምላ ተፈናቅሎ፣ ተጠልሎ የነበረው ደሴ ከተማ ነበር። ስለዚህ ስደተኞችንም ያስተናግድ ነበር። የሕዝብ ፍሰቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴው እጅግ ከባድ ነበር። ነዋሪው ማኅበረሰብ ላይም የነበረው ጫና የትየለሌ ነበር። ሕወሓት ደግሞ ሰርጎ ገቦችን በማሰማራት ይታወቃል። በተጨማሪ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት በአብሮነት መንፈስ ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት ደሴና ከምቦልቻ ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችንም በመመልመል በሳይበርና በተለያዩ መንገዶች ስምሪት ሰጥቷል። የፕሮፓጋንዳ ኃይሎችን በመጠቀም አካባቢውን ሊቆጣጠር እንደደረሰና እንደተቆጣጠረም ያስነግር ነበር።
እኛ መሬት ላይ ያለውን እውነት በማጋለጥ በየጦር ግንባሩ ድረስ በመሄድ መከላከያ ሠራዊቱንና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ የሚያደርጋቸውን ትብብሮች በማሳለጥ ስንቅና ትጥቅ እንዲቀርብ ጥረት አድርገናል። የሕወሓት ኃይል የሚታይባቸውን ቀጠናዎች ሕዝቡ እንዲጠቁምና እንዲያጋልጥ በማድረግ ለወገን መረጃዎችን በማቀበል መንግሥትም እርምጃ እንዲወስድ ከመከላከያ አመራሮችም ጋር ጭምር ተናበን በመስራ ጠላት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዲደርስበት አድርገናል።
መከላከያ ጠላትን አሸንፎት ሐይቅና ኩታበር ላይ የወያኔ ኃይል እየሸሸ ነበር። በእነዚህ ቦታዎች ላይ የደረሰበት ጉዳት ደሴና ከምቦልቻን አልፎ ለመራመድ እንዳይችል አቅም አሳጥቶታል የሚል እምነት አለን። እዚያ አካባቢ የነበረው የመከላከያ ኃይል ትግል፣ የማኅበረሰቡም ደጀንነት በምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው። አንድ ቁልፍ ችግር ግን ነበር፤ ከሠላሳ እስከ አርባ ሺህ የሚገመቱ የትግራይ ተወላጆች በከተማ ውስጥ ይገኙ ነበር። የደሴና ኮምቦልቻ ሕዝብ አብረውን ኖረዋል ዝምድና ፈጥረናል በአንድ ዕድር በአንድ እምነት የምንኖር ነን ብሎ አምኗቸው የኖሩ ናቸው። እነዚህ ናቸው እንግዲህ እንደ አለመታደል ሆኖ እምነታቸውን በመብላት ከመሃል የደበቁትን ጠመንጃ በማውጣት መሐል ከተማ ላይ ሽብር በመንዛት ከተማዎቹን ከመሃል ያፈረሷቸው።
ደሴና ኮምቦልቻ በሚፈርሱበት ጊዜ ተዋጊው የሕወሓት ኃይል ከተማዎቹ ጫፍ እንኳን አልደረሰም። ሰርጎ ገቦቹ የልዩ ኃይሉ እና የመከላከያ ዩኒፎርምን አስገብተውላቸው ያንን እየለበሱ እያምታቱ ሠርተዋል። ይሄንን አጠቃላይ የክልሉና የከተማው የደኀንነት መዋቅር መቆጣጠር ነበረበት። ጊዜ አጠረን እንጂ ከመሃል የሚኖሩ ችግሮችን ካልተቆጣጠርን ችግር ይገጥመናል የሚል ማሳሰቢያም ሰጥተን ነበር። በጊዜው ባደረግናቸው ግምገማዎች ለምሳሌ በሐይቅ ከመከላከያ ጀርባ ገብተው በስንቅ አቀባይነትና በደጋፊነት አብረው ከሕዝቡ ጋር ተሰማርተው ‹‹በቦሩና በኩታበር ያለው መከላከያ እየፈረሰ ነው ፤ እናንተ ለምንድነው የምትለፉት!›› እያሉ ሽብር ሲነዙ የያዝናቸው የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። ያን ጊዜ ግን ትሕነግ ተመቶ እየሸሸ የነበረበት ወቅት እንጂ አንዳችም የመከላከያ ክፍል ቦታ ለቆ ያፈገፈገበትና የከዳበት አግባብ አልነበረም። እንዲሀ ባሉ መንገዶች በጣም በሚያስቆጭ ሁኔታ ያገኘነውን ድል አጥተነዋል።
አንዱ ጦር ወደ ሌላው የሚተኩስ በማስመሰል ከፊሎቹ የልዩ ኃይል ልብስ ከፊሎቹ የመከላከያ ልብስ ለብሰው ሳይመታቱ ግን እንደሚተኳኮሱ ዓይነት ድራማ ሠርተው ለከተማ ሕዝብ በማሳየት ለማሸበር ተንቀሳቅሰዋል። ይህን እንዳለ የሚወስዱ ጥራዝ ነጠቅ ሰዎች በጸጥታ ኃይሉ መካከል ቅራኔ ያለ አስመስለው ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት ሞክረው ነበር። ብዙ ሴራዎችን ነው ሲሠሩ የነበሩት። ገዳይ እስኳድ አስገብተው ስምሪት ላይ የነበርነውን አስተባባሪዎች ለማስገደል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ፋኖና የመከላከያ ሠራዊቱ በወሰዱት እርምጃ በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ። እኔ አርፍበት የነበረውን ሆቴል የክፍል ቁጥሩን ሁሉ በመለየት በከባድ መሣሪያ አፍርሰውታል። በአጋጣሚ እኛም በደኅንነት ጥንቃቄ እናደርግ ስለነበር እዚያ አልነበርንም። ሕዝቡ ደጀን እስከሆነ ድረስ ጠላት መደምሰስ እንደሚችል ስለምንገነዘብ የወገን ኃይል ማስተባበር ላይ አተኩረን ሠርተናል። እንቅስቃሴያችን ተጽእኖ አሳድሮባቸው ስለነበር በዘወትር ቃል አቀባያቸው በጌታቸው ረዳ ስማችንን እየጠቀሱ ዛቻና የማስፈራራት ሥራዎችንም ሠርተዋል።
ጠላት ሰተት ብዬ ወደ አዲስ አበባ እገባለሁ ብሎ ያቀደበትን አቅምና ዕቅድ በደሴና ኮምቦልቻ በተደረገ መከላከል በደረሰበት ጉዳት አጥቷል። አሁን በሁሉም ቀጠናዎች በከበባ ውስጥ ሆኖ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ያለው። የታፈነና የመሞቻ ጊዜውን ብቻ እየጠበቀ ያለ ወራሪ ኃይል ነው። አሁን ኮምቦልቻን አልፎ በደሴም መስመር በሸዋ ፣ ወደ አፋር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ፍላጎቱ በዚህ ፍጥነት እዚህ እደርሳለሁ ብሎ ለቀጣሪዎቹ የገባውን ቃልኪዳን ማስጠበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ አጠቃላይ ግብዓተ መሬቱን እየጠበቀ ነው።
ዘመን፦ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ህዝብ ለማደራጀት እያደረጋችሁ ያላችሁት ጥረት ምን ያህል ውጤታማ ነው?
አቶ የሱፍ ፦ በእኛ እምነት ትግሉ መጠናቀቅ ያለበት በማሸነፍ ብቻ ነው። አማራ ብቻ ሳይሆን ሌለውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማሸነፍ አለበት። ማእከላዊ ሥርዓቱ መጽናት አለበት። በውስጥም በውጭም የእኩያን ኃይሎች የተከፈተብንን ዘመቻ የመከላከል ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን። የእኛ ሕይወት መከላከያ፣ ፋኖ ወይም ልዩ ኃይል ውስጥ ካለው ሕይወት የበለጠ ዋጋ እንዳለው ማሰብ አይገባም። መስዋዕትነት መክፈል ካለብን ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል አለብን በሚል ቃል ኪዳን ገብተን ነው ስምሪት የወሰድነው። ደሴ ከተያዘና በአስቸጋሪ ሁኔታ ከወጣን በኋላ መኪናችንን ለመምታት የመጨረሻው ቀጠና ድረስ መድፍ እየተተኮሰብን ነበር።
የተሻለ ነገር ለማድረግ እኛ ወዲያው ኮምቦልቻ ከተማ ገባንና ደሴ ላይ የነበረውን ስሕተት ኮምቦልቻ ላይ በፍጥነት ማረም እንችላለን ወይ ብለን መዋቅራችንን ለማወያየት ብንሞክርም ወረራው ፈጣን ስለነበርና ከደሴም የወጣው ማኅበረሰብ መረጋጋት ስላልቻለና ለእንቅስቃሴም አመቺ ሁኔታ ስላልተፈጠረ ኮምቦልቻ ላይ መሥራት አልቻልንም። ወዲያውኑ ግን ቀጣዩ የጠላት እንቅስቃሴ ወዴት ሊሆን ይችላል የሚለውን የራሳችንን ትንተናዎች ወስደን ሥራችንን ቀጥልን።
አንድ ነገር ስላጣን እንደተሸነፍን ሳናስብ በቁጭት የጠላትን እንቅስቃሴ ማኮላሸት በሚያስችል ደረጃ ለመደራጀት የሄድነው ወደ ሸዋ ነው። እንደጠበቅነውም መረጃው ዝግጅቱም ያልነበረባቸው አካባቢዎች ነበሩ። ስለዚህ ወጣት አደረጃጀቶችን፣ ፋኖዎችን አስቀድመንም በተለያየ አግባብ እንገናኝ ስለነበር መኮይ ላይ ሄድን በዚያ አደርን። መተላለፊያ በዚህ ስለሚኖር ኬላ ይጠበቅ ፋኖ እና ሚሊሻ ዝግጁ ሆነው ቀጠናዎቹን ተቆጣጥረው እንዲጠብቁ አሳስበን ሄድን። ከዚያም መንዝ ግሼ ራቤል ሔድን መዋቅራችንን ሰብስበን ተገቢውን ሥራ ስንሠራ ቆየን። መሐል ሜዳ እንቅስቃሴዎች አሁኑኑ መደረግ እንዳለበትና ወደ መኮይ ፣ ማጀቴ አጣዬ አካባቢ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ለማስገንዘብ ጥረናል። በዚያም ሰርጎ ገቦች እንዳይኖሩ፣ ደሴና ኮምቦልቻ የተፈጸመው ስህተት እንዳይደገም ከመንግሥትም ከራሳችንም መዋቅር ጋር ተመካክረናል። ከአጠቃላይ የሸዋ ፋኖ መሪዎች ጋር ተወያይተናል። እኛ እዚያው ሆነን ውይይት እያደረግን ባለንበት ሰዓት የማኅበረሰቡ የጸጥታ እንቅስቃሴ ሲለወጥ በዓይናችን እናየው ነበር። በጣም ደስ የሚል ስ ምሪት ነበር።
በቀጣይ ቀናት ወደ ጃማ ወረኢሉ ከዚያም ቦረና መካነሰላም ገባን። እዚያም ከአካባቢው ሁሉ የተሰባሰቡ የወሎ ፋኖዎች ነበሩ። የልዩ ኃይል ባላትና የመከላከያ አባላትም ነበሩ። በዚያም ተደራጅተው ጠላትን መከላከል እንዲችሉ በማድረግ የሚጎድል ካለ ማህበረሰቡና ደጋፊዎቻችን ትብብር እንዲያደርጉ የማሳለጥ ሥራዎችን ሠራን። ከዚያም መርጡለ ማርያምና ሞጣ ሔደን ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረናል። በባህርዳርም ከክልሉ መንግሥት አመራሮች ጋር ተገናኝተን በቀጣይ መሠራት ስላለባቸው ነገሮች በስፋት ተነጋግረናል። ከዚያም ወደ ጎንደር ሄደን በደብረታቦር በኩል በጋሸና በታች በጋይንት ወዳሉት ግንባሮች በማቅናት ጠላትን እንዴት ማጥቃት እንዳለብን ተወያይተናል። በደቡብ ጎንደር ጋሳይ ፣ ክምር ድንጋይ፣ ደብረታቦርም የተሳኩ ሕዝባዊ ውይይቶችን አድርገናል። መዋጋት የሚችለው ኃይል ጠመንጃ ስላጣ ነው ፤ ስለዚህ አቅመ ደካሞች የዋስትና ፎርም እየተሞላ ጠመንጃችሁን ለሚዋጋው ኃይል ለፋኖ ስጡ የሚል ውይይት አድርገን እኛ እንኳን ባለንበት መድረክ በአንድ ቀን 240 ጠመንጃ ለወጣቶች የተሰጠበት ትዕይንት ነበር። እነዚያ ልጆች ግንባር ገብተዋል።
ሌላው ከክልሉ ጋር በነበረን ግብረ ኃይል ጎንደር ላይ ስብሰባ ነበረን። ወደ ልዩ ኃይልና መከላከያ ወጣቶች እንዲገቡ ቅስቀሳ ነበር። ወደ ማሠልጠኛ ከመግባታቸው በፊት የኢንዶክትሪኔሽን ስልጠናዎችን በትብብር ሰጥተናል። በማኅበረሰቡ ውስጥ የወጣቱ እንቅስቃሴ እጅግ የሚገርም ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ ሰፊ ነው። የወሎና የጎንደር ፋኖዎች የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ከመንግሥት ጋር በመነጋገርና ከየመዋቅሩም ጋር በማገናኘት እና ባለሀብቱ እንቅስቃሴ የሚያደርግበትንም መንገድ ለመቀየስ ጥረናል። በተወሰዱ ስምሪቶችም አመርቂ ውጤት እየተገኘ ነው። ይሄ አሁንም ይቀጥላል። ጠላትን ደምስሰን የአገራችንን ህልውና እናስጠብቃለን የሚል ጽኑ አቋም አለን። ለዚህም ሃያ አራት ሰዓታት ያለእረፍት እየሰራን ነው።
በዚህ ሳምንት የአብን መዋቅር ከጎንደር ሁሉንም ጠርተን ስምሪቶችን ሰጥተናል። በየግንባሩ መደረግ ስለሚገባው ነገር ግንዛቤ ሰጥተናል። ከራያ ቆቦ ጀምሮ በርካታ የአብን አመራሮች በትግሉ እየተዋደቁ ነው። እስከ አሁን ድረስ በተዋጊነትም በአመራርነትም የሚሳተፉ ለሕዝባቸው ቀናዒ ሆነው ታሪክ እየሠሩ ያሉ የአብን አባላት አሉ። እስከ መጨረሻው ድረስ የሚቀጥል ነው። እኛ የምንችለውን ፣ የምንፈልገውንና ትክክለኛ የሆነውን ነገር እያደረግን ነው። ተጠናክሮ ይቀጥላል። አሁን እየሠራን ባለነው ሥራ በተጨባጭና በፍጥነት እየመጣ ባለው ውጤት ኩራት ይሰማናል። የኢትዮጵያ ሕዝብና ታሪክ ለተሠራው ሥራ ምስክር ይሆናል።
ዘመን ፦ አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመው ወረራ መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ የሱፍ ፦ ይሄ አሸባሪ ድርጅት ተመቷል። የመጀመሪያው ነገር የሐሳብ ቅቡልነት የለውም፤ የነተበ ሐሳብ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው። ሰዎችን በሐሳብ አሸንፎ አሳምኖ የሚገዛበት በር ከተዘጋ ቆይቷል። አሁን በጉልበት ሐሳቤን አስፈጽማለሁ ብሎ መንቀሳቀሱ ነው። ብዙ ጥፋቶች አድርሷል። አሁንም ያለው ቀላል አይደለም ሊናቅ አይገባም። የወንጀል የሽብር ግብረአበሮች አሉት። የእነሱም ሚና መናቅ የለበትም። አሁን ያለው የኃይል አሰላለፍ ግን ሚዛን ላይ ከተቀመጠ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትሕነግ ተሸናፊ የመሆኑ ነገር እውን እየሆነ መጥቷል። ሕወሓት በአፋር ግንባር በግልጽ ተሸንፏል። በጀርባ በኩል ከወልዲያ እስከ አላማጣ ድረስ ያለውን የራያ ፋኖና ማኅበረሰቡ ዘግቶበታል። የዘረፈውን እንኳን ማስተላለፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ ነው። በደቡብ ወሎ በኩል በወረኢሉ በተላላ በኩል ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በሽንፈት ተገድበዋል። በከሚሴ በኩል ወደ ሸዋ ሮቢት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሌሎችም በባሰ ሁኔታ ተሸንፎ እንደውም በወገን ኃይል የማጥቃትና የጸረማጥቃት ሰፊ እንቅስቃሴ ምክንያት ባልተቋረጠ ሽሽት ውስጥ እንደወደቀ መረጃ አለኝ።
አሁን የወገን ኃይል እየተጠናከረ እየበዛ እያለ ሕወሓት በሕዝባዊ ማእበል ይዞት የመጣው ኃይል በየቦታው ሰረጎ እየተበተነ ሙት ፣ ቁስለኛና ተማራኪ እየሆነ ነው። ስለዚህ በእኔ ግምገማ ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል አይመስለኝም። መቆየትም የለበትም ብለን በብዙ ምክንያት እናምናለን። በሙሉ ከበባ ውስጥ ስለሆነ ዕድሉም የለውም። የተወሰነ መፈራገጥና ችግር መፍጠር ይፈልጋል፤ ለምሳሌ ዳውንት ላይ የዘር ጭፍጨፋ እንዳደረገ መረጃዎች ያሳያሉ። ያደረሰው ጥፋት ከድል በኋላ ሲመረመር ኢትዮጵያውያንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሊያስደነግጥ ይችላል። ድሉ ግን የኢትዮጵያውያን የመሆኑ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ዘመን ፦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁት ሕወሓትና ሸኔ ስለፈጠሩት ጥምረት አብን ምን ይላል?
አቶ የሱፍ ፦ የሕወሓትና የሸኔ ጥምረት ምንም አስደናቂ ነገር የለውም። ሸኔ ግልጽ የሆነ ዓላማ የለውም። ግቡ ከሕወሓት ጋር በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ ነው። ችግር እየፈጠረ የሚገኘው በራሱ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ነው። የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ስርዓት ማፍረስና የአማራን ሕዝብ ማጥቃት የሚል የሚጋሩት ሀሳብ አለ። ንፁሃንና ሴቶችን ኢላማ አድርጎ የፖለቲካ ትርፍ ማምጣት እችላለሁ የሚል የዘወትር ተሸናፊ ድርጅት ነው። በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ቦታ የለውም። በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችም የተገፋና ቦታ የሌለው ድርጅት ነው። ሕወሓት የውጭ ኃይሎች ቅጥረኛ ሲሆን፤ ሸኔ ደግሞ የሕወሓት ፈረስ ነው። ይህ ድርጅት በ1983 ዓ.ም ከሕወሓት ጋር በተወሰነ ደረጃ ጥምረት እንፈጥራለን ብሎ በአንድ ቀን ትዕዛዝ ሠራዊቱን የትም በትኖ የፈረጠጠ ነው። ረጅም ዘመን ከአገር ውጭ የተለያዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ቢሞክርም አልተሳካለትም። እንደውም ከገፋው የሕወሓት ስርዓት ጋር በጀርባ በማበር መረጃዎችን በመስጠት የኦሮሞ ወጣቶችን ለእስራት፣ ለእንግልትና ለሰቆቃ መዳረጉን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ።
በአጭሩ ሸኔ የሕወሓት እንቁላል ነው ማለት ይቻላል። በትርፍራፊ ገንዘብ በመናኛ ፍጆታ በጣም ለጨቋኙ ሕወሓት ቡድን ያደረ ነው። በጣም በሚያሳዝን መልኩ በታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ስም ተደራጅቻለሁ እያለ የኦሮሞን ሕዝብ ተነግሮ ለማያልቅ ሰቆቃ የዳረገውን ሕወሓት መራሹን አምባገነንና ዘረኛ ስርዓት እንደገና ወደ ማዕከል ለማምጣት የሚሠራ በፖለቲካ ሳይንስ ታይቶም የማይታወቅ ድርጅት ነው። በጦር ሜዳም ያን ያህል ልምድም ሆነ ገድል የለውም። ሰሞኑን በወሎና በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢ አንዳንድ የሽብር ሥራዎችን ከሕወሓት ጋር በጥምረት ለማከናወን ሙከራ አድርጎ ነበር። ነገር ግን የኦሮሞ ማህበረሰብ ራሱ አትወክለንም ለአገራችንም ለሕዝባችንም የማትሆን ድርጅት ስለሆንክ በእኛ እግር ስር ልትሆን አትችልም በሚል ከመከላከያ ፣ ከልዩ ኃይሉና ከፋኖ ጋር በመሆን እርምጃ ወስዶበታል።
ስለዚህ ሕዝብ የተጠየፈው ጥምረት ነው ማለት ነው። አሁን በአደባባይ ያወጡት እንጂ በወለጋ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ኦነግ ሸኔ ለሚፈጽማቸው የሽብር ተግባራት ሕወሓት የገንዘብና የመረጃ ድጋፍ ያደርጋል። የአሁኑ በቃል ከመገለጽ ውጭ የተለየ ትርጉም ያለው ነገር አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ይህንን ኃይል ፊት ለፊት እየተጋፈጠው ነው ያለው። ማህበረሰቡ እየተደራጀ ሰርጎ ገቦችንና ወንጀለኞችን አንገታቸውን እየያዘ ወደ ፍርድ አደባባይ እያወጣቸው ነው ያለው። የኦሮሞ ድርጅት ነኝ የሚለው ሸኔ የኦሮሞ ልጆች በማዕከላዊ ስርዓት ውስጥ በእኩልነትና በፍትሕ ለመተዳደር ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አብረው የሚሠሩበት መድረክ እየተፈጠረ ባለበት ሁኔታ ይሄን ለመዝጋትና ወደ ደም መፋሰስና ሽብርና አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ የመግባቱ እንቆቅልሽ ከሕወሓት ግብዓተ መሬት መፈጸም ጋር አብሮ የሚፈታ ይሆናል።
ዘመን ፦ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ሁሉንም አይነት ጦርነት ከፍተው በቅንጅት እየሰሩ ነው። ፍላጎታቸው ምንድን ነው?
አቶ የሱፍ፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነጻነት አርማ ፣ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት፣ ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከችና ያልገበረች አገር ስለሆነች ምዕራባውያኑ ታሪካችን አይመቻቸውም። በሰብዓዊነት፣ በነጻነትና በፍትሕ ሥም የመሸጉ አካላት የቅኝ ግዛት ውርስና ምልከታ አሁን ድረስ አለ። አሜሪካ ውስጥ ጥቁር ሕዝቡ የሚኖርበት የዘረኝነት ሁኔታ የምናውቀው ነው። የዘረኝነት ፖለቲካ የመጨረሻው የመንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያዊነትን መሠረት ሲያደርግና ነጻነቷንና ታሪኳን በቅጡ እውቅና እየሰጠ ሲሄድ ተረብሸዋል። በሕወሓት ስርዓት ወቅት ከፍተኛ መጎሳቆልና መጉደፍ የደረሰበት ኢትዮጵያዊነት ወደ ቦታው መመለሱ ፤ አርበኝነት ቦታውን መያዙ ፤ የነጻነት ፍላጎትና ጣልቃ ገብነትን መከላከል እምቢተኝነት መደራጀቱ ፤ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መሠረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የማንም ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት ሊሆን እንደማይችል እና የሌላ አገር ሕዝብም ይሁን መንግሥት ስርዓት ሊሆን እንደማይችል ተግባቦት ላይ እየተደረሰ መምጣቱ በጉልህ እየታየ መምጣቱ አልተመቻቸውም።
ኢትዮጵያ ጠንካራና የለማች በሕዝቧ ፍቃድና ይሁንታ የምትተዳደር አገር መሆን የለባትም የሚል የቆየ የውርስ ፖለቲካ አላቸው። ያንን አሁን በየቦታው እያጡት ሲመጡ ነው ተቃውሞ እያቀረቡ ያሉት። ሕወሓት ቀድሞም ተንበርካኪ ስለነበር በትጥቅ ፣ በመረጃና በገንዘብ የተወሰነ ድጋፍ ቢደረገለት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይችላል በሚል ነው አብረውት እየተሰለፉ ያሉት። ስለዚህ በአጠቃላይ ሰብዓዊ ድጋፍ ፣ የዜጎች መብት ፣ በሕግ የበላይነት ወዘተ. እየተባለ የሚወራው ሁሉ ፖለቲካ ነው። ሕወሓት ቀደም ሲል በፈጸማቸው ሰቆቃዎች ፣ ጅምላ ፍጅቶች ፣ አፈናዎች፣ እስራቶች፣ ግርፋቶች እና ግድያዎች ከእነዚህ የውጭ ኃይላት ጉልህ ድምጽ ተሰምቶ አያውቅም። አሁን በልዩ ሀኔታ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተንበርካኪ አገር ለመመስረት ባላቸው ፍላጎት ነው።
ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካዊ ይዞታዋ በጣም አስፈላጊ አገር ስለሆነች በራሷ እግር መቆም ከጀመረች ስጋት ትሆንብናለች ብለው ያስባሉ። ስለዚህ ለእነሱ ፍላጎት የሚጋለብና ተንበርካኪ የሆነ ፣ የአገርን ጥቅም ትቶ ለእነሱ ጥቅም ብቻ የሚሠራ ፣ ለቡድንና ለግለሰብ ጥቅም የሚንቀሳቀስ ኃይል ወደ ማዕከል ማምጣት ይፈልጋሉ።
ይህ የሆነው በእኛ አገር ብቻ አይደለም። ሊቢያና ሶሪያ ላይ እንዲሁም በርካታ አገራት ላይ ተፈጽሟል። የአሜሪካ መንግሥት በሕዝብ መካከል ፈንጂ የሚያፈነዱ የኮንትራት ሚሊሻዎችን በላቲን አሜሪካ እያሰማራ ፕሬዚዳንቶችን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን፣ አመራሮችን ሲያስገድልና ሲገድል የነበረ ስርዓት ነው። ይሄ በታሪክ ተመዝግቦ ያለ ጉዳይ ነው። ምዕራባውያኑ በአፍሪካ ውስጥ አምባገነንና ዘረኛ፣ የተወሰነ ቡድን ብቻ የሚወክሉ ስርዓቶችን በጦር መሳሪያ ፣ በገንዘብና በፕሮፖጋንዳ ሲደግፉ የኖሩ ናቸው። ይሄንን በተገቢው ተገንዝበን በልኩ መመከት ይኖርብናል።
ዘመን ፦ ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያኑን ጫና ተቋቁመው ሁኔታውን ለመቀልበስ ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
አቶ የሱፍ፦ ውለው ያደሩ በርካታ ችግሮች አሉብን። እነሱን ለመፍታት ስንንቀሳቀስ ሰቆቃ መጥቶብናል። ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነት ይሄንን ሁሉ ውጣ ውረድ ይቋቋማሉ። ከዚህም በኋላ ቀጣዩ ትውልድ ልጆቻችን እና የልጅ ልጆቻችን የተሻለ አገር ይወርሳሉ። ለዚህም ስኬት እኛ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልዩነቶቻችንን በጉያችን ይዘን ትብብሮችን በማድረግ ማሸነፍ መቻል አለብን። ይሄ የታሪክ ጥሪ ነው። የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ለታሪኩ ፍሰት ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ በተሠማራንበት ሁሉ በውስጥም በውጭም ርብርብ ማድረግ ይገባናል። አሁን ግንባር ቀደም ጉዳያችን የአገርንና የሕዝብን ህልውና አደጋ ላይ የጣለውን የሽብር ጥምረቱ በፈለገውና እየተንቀሳቀሰበት ባለው መንገድ በጠመንጃ ማንበርከክና ማሸነፍ ነው።
ከዚያ በኋላ ሕዝቡ እንደየፍላጎቱ ይወክሉኛል የሚላቸውን አደረጃጀቶች በማዋቀር አመራሮችን በመወከል ሰፊ አካታች ብሔራዊ ውይይትና ድርድር ይኖራል። አዲስ ማህበራዊ ውል ሊጻፍ ይችላል፤ ይጻፋልም። ያለፉ ችግሮቻችን እንዴት ፈተን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መውጣት አለብን የሚል ሥራ ይጠብቀናል። ምሁራኖቻችን፣ አመራሮቻችን፣ የፖለቲካ ኃላፊዎቻችን እና የሕዝባችን ተወካዮች ሁሉ የሚሳተፉባቸው በርካታ የተለያዩ መድረኮች ይፈጠራሉ። ዝርዝሩ ከዋናው ሂደት በፊት በውይይትም በስምምነትም የሚታይ ነው የሚሆነው። ከዋናው መድረክ በፊት ቅድመ ድርድሮች ይኖራሉ። ዞሮ ዞሮ መውጫ መንገዱን ሁላችንም በጋራ የምንተልመው ይሆናል። አሁን ግን በእንደዚህ አይነት ሰላማዊ ፣ ፍትሀዊ እና እኩል በሆነ መድረክ በሰለጠነ መንገድ መፍታት የማይፈልገው ኃይል ከፖለቲካ ማዕቀፉ በፈለገውና በመረጠው አግባብ ተገፍቶ መወገድና መሸነፍ አለበት።
በውስጥና በውጭ እኩያን ኃይሎች ጥምረት አገራችንን እና ሕዝባችንን ለማፍረስ የሚደረገውን ርብርብ በታሪክ አስመዝግበናቸው እንዳለፍናቸውና ነጻነታችንን አስጠብቀን እንደኖርንባቸው ድሎቻችን ዳግም ታሪክ የምንሠራበት ወቅት ነው የሚል መልዕክት አለኝ።
ዘመን፦ በቀጣይ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል?
አቶ የሱፍ፦ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶችና ስጋቶች ሁሉ በታሪክ እንደተሻገረቻቸው አሁንም ትሻገራለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ተሞክሮዎች አሉት ፤ ብዙ ሰቆቃዎችንና ጥቃቶችን አስተናግዷል። እንደ አገርና ሕዝብ ነጻነታችንን ያስከበርነው እንደሌሎች አገራት በውጭ ወይም በሶስተኛ ወገን ፍላጎትና ይሁንታ ሳይሆን መራር መስዋዕትነት በመክፈል ነው። ይህ ታሪክ ተመዝግቦ ያለ እውነት ነው። ከዚህ ተሞክሮና ልምድ እንወስዳለን። ታሪክ ተመዝግቦ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ተመሳክሮ ለተግባራዊ ስምሪት የሚውል ነው። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የአባቶቹንና የቅድመ አያቶቹን ገድል ለመፈፀም በማያወላዳ ሁኔታ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሷል።
ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ትወጣለች ለዚህ ምንም ጥያቄ የለም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲልና መሰባሰቢያ ማዕከል መሆኗ ይቀጥላል ፤ ተስፈኞቹም ይሸነፋሉ። እንደዚህ አይነት ስምሪት ዳግም እንዳይወሰድ ትምህርት ይሰጥበታል። እኛም አገር በመገንባቱ ሂደት የበኩላችንን ጥረት እያደረግን እንቀጥላለን። ይሄ በቅርቡ እውን የሚሆን ጉዳይ ነው። ዝም ብሎ መላምት ሳይሆን ተጨባጭ የሆኑ ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰጠ ትክክለኛ የሆነ አስተያየት ነው።
ዘመን ፦ የተጣበበ ጊዜዎትን መስዋዕት በማድረግ ሰፊ ጊዜ ወስደው የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን ከልብ እናመሰግናለን።
አቶ የሱፍ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
የትናየት ፈሩ
ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም