በማሕበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድኅን ተቋም ውስጥ አባል ለሆኑ ግለሰቦች ከዚህ በፊት በመንግሥት ህክምና ተቋማት በሀኪም በታዘዘው መሠረት የአባልነት መታወቂያቸውን እያሳዩ በከነማ ፋርማሲዎች መድኃኒቶች ይወስዱ ነበር። በተለይ በ2014 ዓ.ም. የተለያዩ መድኃኒቶችን የከነማ ፋርማሲዎች ‹‹አትስጡ ስለተባልን ከፈለጋችሁ በገንዘብ ግዙ ብለውናል፤ለምን ስንል ተገቢ ምላሽ የሚሰጠን አላገኘንም›› የሚል ቅሬታ በተጠቃሚ አባላት ሲነሳ ይሰማል። ይህን ለማጣራት ወደ ከነማ መድኃኒት ቤት በመሄድ የቅሬታ አቅራቢን ሀሳብ፣ የቅርንጫፍ መድኃኒት ቤቱን ኃላፊ እንዲሁም የከነማ መድኃኒት ቤቶች ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ከከነማ መድኃኒት ቤት ጋር ውል የገባውን ክፍለ ከተማ በማናገር ምላሽ አቅርበናል።
ቅሬታ ፦ ወይዘሮ አይናለም ገብረፃዲቅ ልጃቸው ስለታመመችባቸው ከየካቲት 12 ሆስፒታል የተሰጣቸውን የመድኃኒት ማዘዣ ይዘው አንበሳ ግቢ ከሚገኘው የከነማ መድኃኒት ቤት ለመውሰድ ልጃቸውን አዝለዋት መጥተው አግኝተናቸዋል። የአባልነት መታወቂያቸውን እና የመድኃኒት ማዘዣውን አያይዘው ለባለሙያዋ ሲሰጧት ‹‹ይህ መድኃኒት በነጻ አይሰጥም፤ከፈለግሽ በገንዘብ መግዛት ትችያለሽ። ይህ የተሰጠን ትዕዛዝ ነው›› መባላቸውን ይገልጻሉ። ከልጄ በላይ የሚሆን የለም በማለት የተጠየቁትን 381.60(ሶስት መቶ ሰማንያ አንድ ብር ከስልሳ ሳንቲም) ሲከፍሉም ተመልክተናል። ‹‹አይሰጥም ከተባለ ማንን እጠይቃለሁ? ምላሽ የምታገኙ ከሆነ እናንተ ጠይቁ›› በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የአንበሳ ግቢ ከነማ መድኃኒት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሌ፦ ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማት ሀኪም ከታዘዘ እንዲሁም በተቋማቱ ውስጥ መድኃኒቱ አለመኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ ይዘው እስከመጡ ድረስ አባል ለሆኑ ግለሰቦች በከነማ መድኃኒት ቤት ያለውን መድኃኒት ያለልዩነት እንሰጥ ነበር። አሁን ግን “ብራንድ” የሆኑ መድኃኒቶች እንዳይሰጡ “በጀነሪክ”(በጽንስ ስም) እንዲሰጥ የሚል ከዋናው መሥሪያ ቤት በደብዳቤ ደርሶናል። ለአባላቶቹ በጀነሪክ የታዘዙትን በነጻ እንሰጣለን፤በብራንድ የታዘዙትን በነጻ አንሰጥም። ግለሰቦቹ ከፈለጉ በገንዘብ እንዲወስዱ እናደርጋለን።
የከነማ መድኃኒት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምስጋናው ከበደ ፦ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በክፍለ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ደረጃ ከሚያስተባብረው አካል ጋር መድኃኒት የምንሰጥበትን ስርዓት በተመለከተ ውል ገብተን ለአባላት በከነማ መድኃኒት ቤት ውስጥ ያሉትን ማንኛውንም መድኃኒት ስንሰጥ ቆይተናል። ለአባላት የሰጠናቸውን መድኃኒቶች ማስረጃ በማቅረብ ገንዘቡን ከሶስት ወር በኋላ ከየክፍለ ከተሞቹ እንቀበላለን። አሁን ግን መድኃኒቶች መሰጠት ያለባቸው በጀነሪክ ስማቸው ነው፤ በብራንድ ስማቸው እንዳይሰጥ የሚል ደብዳቤ ከሁሉም ክፍለ ከተሞችና ጤና ቢሮ ተሰጥቶናል። ስለሆነም ለአባላቱ በጀነሪክ ስም ብቻ የታዘዙትን ነው እየሰጠን ያለነው። ብራንድ መድኃኒቶች ደግሞ በባህሪያቸው ውድ ናቸው። ለአባላቶቹ የምንሰጣቸው መድኃኒቶች ቀደም ሲል እንደነበረው በወቅቱ እየተከፈለን አይደለም። በአጠቃላይ ከአርባ ሚሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ገንዘብ አለን። ለዚህም የሚሰጡን ምክንያት በካዝናችን ውስጥ ገንዘብ ስለሌለ ታገሱን የሚል ነው።
የአራዳ ክፍለ ከተማ የማሕበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድኅን ሥራዎች አስተባባሪ አቶ እስጢፋኖስ ነጋሽ፡- በብራንድ ስም የሚሰጡ መድኃኒቶች ዋጋቸው ውድ ስለሆነ በከነማ መድኃኒት ቤቶች እንዳይሰጡ ደብዳቤ መሰጠቱን ገልጸው ይህም የሆነው ከደረሰ ከፍተኛ የበጀት እጥረትና ውልን መስመር ለማስያዝ ሲባል መሆኑን አስረድተዋል። ሀኪሞች ለአባላት በብራንድ መድኃኒት እንዳያዙ ለሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ደብዳቤ ስለተሰጠ በአባላትና በከነማ መድኃኒት ቤቶች መካከል ይከሰት የነበው ውዝግብ መፍትሔ እንደሚያገኝም ተናግረዋል።
ስሜነህ ደስታ
ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም