የማሰብ ችግር የብዙኀኑ የህወሓት ጁንታ ዓይነተኛ መገለጫ ነው። ሂሳብ ለብዙዎች የሚያስቸግር ትምህርት እንደሆነ ቢታወቅም ለወያኔ አመራር ደግሞ በራስ ዳሸን ላይ የመሮጥ ያህል ከባድ ነው።
የመጀመሪያው የማሰብ ችግር መገለጫው ትልቅና ትንሽን ያለማወቅ ነው። የወያኔ አመራር ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር መሆኗን ሳይረዳ የመገንጠል ትግል መጀመሩ ነው። ደርግን አሸንፎ ምኒልክ ቤተመንግሥት ሲደርስ ኢትዮጵያን ሲለካት ሲመዝናት ትልቅ ሀገር ሆነችበት። ብቻውን የሚሸከማት ሀገር አልሆን አለች። ጨነቀው… ስለዚህ ብዙና ትልቅ መሆኗ ዘግይቶ የገባው ኃይል ይህቺን የተደመረች ሀገር ልቀንሳት ብሎ አለመ፤ ዛሬ ሉዐላዊ ሀገር መሆኗን የምንረዳላት ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር የሆነችው ስለፈለገች ብቻ ሳይሆን ስለተገፋችም እንደሆነ አስባለሁ። ወያኔ አላፈረ፣ አልተደራደረ፤ እንደ አሮጌ ቁና አውጥቶ ሲጥላት ምን እንኳን እንደሚጎድልበት፣ ምን እንደሚመጣበት አላሰበም፤ ሂሳብ የለማ!
እንዴት ያለ የጽድቅ ሥራ ነው፤ ከሌላት ሰጠች የተባለችውን መበለት መሰለ! ደሃይቱስ አስባ ነው፤ ከሌላት ላይ ሰጥታለችና ኑሮዋን ትዳሯን ሰጠች ተባለ፤ እንዲህ ያለ በሚሊዮኖች ኑሮ ላይ ቸርነት ያሳየ የፖለቲካ ቡድን የሂሳብ ችግር ያለበት እንጂ የቸርነቱ ልዕልና አይደለም።
የተቀነሰው ሀገር ግን ስንት ዋጋ ይዞ እንደተቀነሰ አላሰበም። ዕዳ ከሜዳ! ሳይቸገር ዕዳ ገባ፤ ሳይበደር ዕዳ ከፋይ ሆነ። ወደብን የሚያህል መውጫ መግቢያ ‹‹ይብሉት!›› ብሎ ሲቀንስ ለጂቡቲ ግን ይደምርላት ያዘ። ይህ ከባላንስ ውጪ የሆነ ሂሳብ ነው። ወያኔ ወጪ ገቢን ማመጣጠን አያውቅም። ማመጣጠን የሂሳብ ነገር ነዋ! ‹‹ሳይኖራት አበደረች፤ ሳትቀበል ሞተች›› ካሉ አይቀር ለወያኔ የተስማማ ነው።
ጉዴ! ምን ይሄ ብቻ፤ ‹‹ላለው ይጨመርለታል ከሌለው ያው ያለው ይወሰድበታል›› የተባለውስ ነገር፤ ወያኔ ኤርትራን ሰጥቶ ሲያበቃ ‹‹ባድመ ይቅርልን›› ብሎ 80 ሺህ ሰው ከአፈር የቀላቀለበት ታሪክስ ሂሳብ ያለማወቅ ያመጣው ጣጣ አይደል!
ኤርትራውያንስ ካገኙት ሀገርነት በላይ ሊደሰቱ የሚገባቸው በዚህ የማያስብ ኃይል ከመመራት በመትረፋቸው ነው። እኔና ቤቴ ግን በዚህ መዳፍ ተይዘን ቀጠልን።
ወያኔ ግን አሁንም ኢትዮጵያ ከብዳዋለች፤ አሁንም ግን ጨነቀው፤ የሀገሪቱ ኪሎና እና ቁጥር በዛበት፤ እንዲህ የተጃመለችን ሀገር እንዴት በችርቻሮ ልያዛት ብሎ አሰበ። በብሔር ብሔረሰቦች ስም የተዘጋጀ የከፋፍለህ ግዛው ማስፈጸሚያ ሕገመንግሥት አመጣ። በአንድ ባሕር የነበረ ሕዝብ በተለያየ ገንዳ አስቀምጦ ‹‹ዋኝ!›› ይለው ጀመር። አንድ ትልቅ የነበረውን ብዙ ትንንሽ አደረገው። ትልቅ መሆን ምን እንደሆነ አልገባውም። ትንሽነትን ያፈቅራል፤ ትልቅ ነገር ይጨንቀዋል። የመሸከምም አቅም የለውም።
የትልቁን ሀገር መሸከሚያ የምኒልክን ቤተመንግሥት ግን ጨምድዶ ይዟል። ትንሽ ትከሻ ትልቅ ሀገር ተሸክሞ እንዴት አይጨንቀው። ብዙና ትልቅ ነገር ማሰሪያ፣ መሰብሰቢያ፣ ማስማሚያ ካልያዝክ ልትሸከመው አትችልም። ይዝረከረክብሃል። ለወያኔ አመራር ግን መደመር አይሆንለትም፤ የሚቀለው መቀነስ ብቻ ነው። ሲቀነስ ሐሳብ ይቀልልናል፤ ሂሳቡም ይቀለኛል ብሎ ያምናል። መሸከሚያ ትከሻውን ማስፋት አይፈልግም፤ ኢትዮጵያዊነትን አይወድም። ትልቋን ኢትዮጵያን መቸርቸር ይመርጣል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከመቸርቸር በወጣች ጊዜ ትከሻው መሸከም እንደማይችል፤ ትልቅ ልትሆን ስታስብ የእርሱ ጠባብ ትከሻ ሊሸከማት እንደማይችል፤ አለመመጣጠኑ እንደሚደፈጥጠው አላሰበም። ይሄ በእውነት ሂሳብ አለማወቅ ነው።
ስለዚህ ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከችርቻሮ የመውጣት ፍላጎት በድንገት ስታሳይ ከትከሻው ወረደች። እንደ ትልቅነቷ ወደሚሸከማት ትከሻ ከፍ ብላ ወጣች። የእነሱ ትከሻ ደቀቀ፤ ከጉዳታቸው ብዛት እግርና እጃቸው ሁሉ ተያዘ፤ ስለዚህም ቆላ ተንቤን ተሸጉጠው፣ ተኝተው ከረሙ።
ሂሳብ የማያውቅ ግን የደረሰበትንም ጉዳት መጠን ለማሰብ ይቸገራልና፤ ስንት አለን? ስንት ቀረን ማለት አልቻለም። ጆሮው ሲሰማ ዓይኑ የሚያይ፣ እጁ ሲዘረጋ እግሩም የሚሄድ ይመስለዋል። የቱ እንደተፈወሰ የቱ ላያገግም እንደደቀቀ አያውቅም። ሰው እንዴት የሕመሙን ልክ እንኳን አያስብም። ማሰብ የጁንታው መሠረታዊ ችግር ነው።
የጁንታው አፍ ጌታቸው ረዳ አዕምሮው በእጅጉ ርዶ ሳለ ስለሂሳብ ማወራረድ መናገሩን በሰማን ጊዜ ደግሞ በእጅጉ አዘንን። ‹‹ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን›› ብሎ ሲናገር ሂሳብ የሚያውቅ ይመስላል። ሂሳብ ቢያውቅ ከምኒልክ ቤተመንግሥት ባልወጣ ነበር። ሂሳብ የሚያውቅ ግምትም ያውቃል። ባልገመቱት ጊዜ ካልገመቱት ቦታ መገኘትን የመሰለ የሂሳብ አለማወቅ ማሳያ አለ? ከአራት ኪሎ ቆላ ተንቤን ስንት ኪሎሜትር ነበር?
ጋሽ ጌች! የሚወራረድ ሂሳብ ምን እንደሆነ አልገባውም። የሚያወራርድ የተጠቀመ ነው። የተፈቀደለትን ያህል መጠቀም አለመጠቀሙን ለመለየት ተጠቅመህ የከፈልክበትን ደረሰኝ ይዘህ ማወራረድ የሂሳብ ሙያ የሚያዘው ነው። የተፈቀደልህን ያህል መጠቀምህንም ለማሳየት ቢሆን ያልተጭበረበረ ደረሰኝ ይዘህ መገኘት አለብህ። እነ ጌች ባለዕዳ መሆናቸውን ቢያወራርዱ የሚርዱ መሆናቸውን እያወቁ ስለሂሳብ ማውራታቸው የአዕምሯቸው መቀሰፍ ጉልህ ማሳያ ነው።
በወታደራዊ አመራሩ ስንት የወያኔ ጀነራል ነበር፤ የተፈቀደልህን ያህል ተጠቅመሃል ወይስ ትርፍ!? የተፈቀደልህን ወሰን ይዘሃል ወይስ ትርፍ ነጥቀህ ከልለሃል!? የተፈቀደልህን ያህል በጀት ተጠቅመሃል ወይስ ትርፍ አጋብሰሃል!? የተፈቀደልህን ያህል ሥልጣን ተጋርተሃል ወይስ ትርፍ ኃይል አዳብረሃል!? በተፈቀደልህ የሞራል ሁኔታ ተመላልሰሃል ወይስ ትርፍ አመል አምጥተህ ሀገር በድለሃል፤ …..ማወራረድ ይሄንን ነው። ሜቴክ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ኤፈርት የተጠቀሙት የተፈቀደላቸውን ወይስ ትርፍ?
ጌች ረዳ ነገሩን ተረዳ! የሚያወራርደው የገዛ ነው፤ በአምስት ምርጫዎች ወግ የተያዘው ሥልጣን የተፈቀደ ወይስ በማጭብርብር የተያዘ ትርፍ፤ የሚያወራርደው ሃያ ሰባት ዓመት የገዛ ወያኔ ወይስ ተገዢው!?
መግዛትስ ቢሉህ መግዛት ነው! ቀጥቅጦ መግዛት ማለትስ እንዲህ ቀላል ነው!? እናት የልጇ ሬሳ ላይ አስቀምጠህ፣ በመኪና ገጭተህ፣ በጨለማ አስራችሁ፣ አካል ቆራርጣችሁ፣ ደም በደም አድርጋችሁ የገዛችሁ እናንተ! ታዲያ ያልገዛ እንዴት ያወራርዳል? አይይ… ሂሳብ አለማወቅ!
ጌች ረዳ ነገሩን ተረዳ! የሚያወራርደው ያከ ማቸ ነው። ወያኔ ስንቱን ነገር ያለ ደረሰኝ ወስዶ አከማቸ… ያለ ውድድር፣ ያለ ክርክር፤ ያለ ጨረታ፣ ያለ ይሉኝታ ስንቱን ቢዝነስ አከማቸ፤ ስንቱ ከሀገር ወዲህ ስንቱ ከሀገር ወዲያ ተወስዶ ተከማቸ፤ ማወራረድማ ይሄንን ነው!
ጋሽ ጌች! የምታውቃትን የኤፈርት ዘፈን ትንሽ ባዜምልህ ሂሳቡ ይገባህ ይሆናል። አጭብጭብ!
ምን አለ አልመዳ ምን አለ…… መከላከያን
ፖሊስን ሁሉ ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ሜጋ ምን አለ…. ትምህርት
ሴክተሩን ኅትመት ሴክተሩን ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ መሶቦ ምን አለ… ታላቁን
ግድብ፣ ኮንዶሚኒየሙን ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ትራንስ ምን አለ… መንገዱን
ሁሉ ወደቡን ሁሉ ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ሕይወት ምን አለ… ግብርናን
ሁሉ መስኖውን ሁሉ ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ጉና ምን አለ….. ንግዱንም
ሁሉ ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ሱርስ ምን አለ……. ግንባታን
ሁሉ ይዣለሁ አለ፤
ምን አለ ኢዛና ምን አለ….. ማዕድን ሁሉ
በእጄ ነው አለ፤
ምን አለ ኤፈርት ምን ምን አለ…
ቢዝነሴን ለሰው አልሰጥም አለ።
– ታዲያ እኛስ ምን እንበል ክምችቱ
– የት ነው? ታዲያ! የሚያወራርደው
-ማን ነው?
ጌች ረዳ ነገሩን ተረዳ! የሚያወራርድ የበላ ነው። ስንቱ ትርፍ ጠጥቶ ሰከረ፤ ስንቱ ተጠምቶ ተዘረረ፤ መተሳሰብ እዚህጋ ነው! ስንቱ ጠግቦ ተፋ፣ ስንቱ ተርቦ ተከፋ፤ የሚያወራርደው ትርፍ ያከማቸ ነው!
አይይ… ሂሳብ አለማወቅ!
ቶኩማ ሮባ