መምህር፣ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂው ደራሲ

መምህር እና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል በሰሜን ሸዋ ማጀቴ ከተማ ተወልዶ፣ ኮምቦልቻና አስመራ አድጓል። አስመራ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የቀን ሥራ ሠርቷል፤ በመምህርነትም አገልግሏል። የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ለመብታቸው ተሟግቷል። በደርግ ሥርዓት በኢህአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ ሲታገል በደርግ መንግሥት ተይዞ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ ተፈቷል። ከተፈታ በኋላ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ በኋላ “የወዲያነሽ” በሚል ርዕስ ያሳተመው ተወዳጅ መጽሐፉን ይጽፍ ነበር።

በ1976 ዓ.ም. በሚኖርበት አካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መጀመሪያ ጋራዥ ውስጥ ሰርቷል ፤ ቀጥሎም በመምህርነት አገልግሏል። በመምህርነት ለ33 ዓመታት ያገለገለ ሲሆን “የወዲያነሽ” እና “ጉንጉን” የሚባሉ የልቦለድ መጽሐፍ እንዲሁም “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክንም ጽፎ አሳትሟል።

በትግሪኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ” ቲያትርን ተርጉሞ በ2005 ዓ.ም. ከማሳተሙ በተጨማሪ ሌሎች ቲያትሮችም ጽፎ ለሕትመት ዝግጁ አድርጎል። የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት ወደ ቲያትር በመቀየር በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። በጋዜጠኝነት ከመሥራቱ በተጨማሪ “እረኛዬ” በተሰኘ ተከታታይ ድራማ ላይ ተውኗል። የብዙ ወጣቶችን ድርሰት የአርትኦት ሥራ በመሥራት አስተምሯል፤ አግዟል። በተለያዩ ፕሮግራዎች ላይ አስተማሪና አዝናኝ ንግግሮች በማድረግ ወግ አዋቂነቱንም አስመስክሯል። የዚህ መምህር፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂ ሕይወት ብዙዎችን ያስተምራል ብለን በማመን እንግዳችን አድርገነዋል። መልካም ንባብ!

ውልደትና ዕድገት

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣የጣልያኖችን የግፍ አገዛዝ በመሸሽ በ1926 ዓ.ም. ከአስመራ ወደ መሃል አገር ከመጡት አቶ መዋዕል መሐሪ እና ማጀቴ ተወልደው ካደጉት ከወይዘሮ ሙላቷ ሀብተሚካኤል በሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ገምዛ ወረዳ ሰኔ 16 ቀን 1943 ዓ.ም. ማጀቴ ከተማ ደይ-ምድር መንደር ተወለደ። ኃይለመለኮት ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ፣ ለአባቱ ደግሞ ሰባተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው። የአራት ዓመት ሕጻን ሳለ ወላጆቹ በመለያየታቸውና አባቱ ለሥራ ኮምቦልቻ ተቀይረው ስለሄዱ አጎቱ ቤት ጌሾ፣ጥጃ እና ማሽላ እየጠበቀ አደገ። ከአጎቱ ቤት በመቀጠል አያቶቹ ዘንድ አድጓል። አያቶቹ ከፍተኛ ፍቅር ቢያሳዩትም ከአባትና እናት ጋር በመሆን የሚገኝን ልዩ የወላጅ ፍቅርን ሳያገኝ እንዳደገ ይናገራል።

አያቶቹ ዘንድ እያደገ ሳለ አባቱ የቴሌኮሚኒክሽን ሥራ ከሚሠሩበት ከኮምቦልቻ በመምጣት ወደ ሥራ ቦታቸው ይዘውት ሄዱ። ያን ጊዜ የኮምቦልቻ ከተማ ሃያ እና ሰላሳ ቤቶች ብቻ የነበሩባት በመሆኗ በሆያ ሆዬ የሚዳረሱ ነበሩ በማለት ይገልጸዋል። ኮምቦልቻ ከሄደ በኋላ የመጀመሪያዋ እንጀራ እናቱ ክፉ ስለነበሩ ከእሳቸው ጋር አብሮ መኖሩ አሰልቺ ሆነበት። ከእንጀራ እናቱ ጋር ሲኖር በድሮው ፋሽኮ ጠርሙስ ውሃ ለመቅዳት ይዞ ወጥቶ ሳለ አዳልጦት ወድቆ ጠርሙሱ ስለተሰበረ ወደ ቤት መሄድ ፈርቶ ዛፍ ላይ ያደረበትን ቀን አሁን ድረስ በኀዘን ያስታውሳል። እኚህ እንጀራ እናቱ ከአባቱ ጋር ተጣልተው ከሄዱ በኋላ ወደ አራት እንጀራ እናት አይቷል። ኮምቦልቻ የቄስ ትምህርት መማር እንደጀመረ ዘመናዊ ትምህርት በስፍራው ስለተከፈተ አንደኛ ክፍል ገብቶ በእጥፍ (ደብል እየመታ) እያለፈ እስከ አራተኛ ክፍል ተምሯል።

አባቱ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ኤርትራ ሲሄዱ ከኮምቦልቻ ወደ አስመራ በትሬንታ ኳትሮ የጭነት መኪና ከአባቱ ጋር ተሳፍሮ ሄደ። በመቀጠልም ከአስመራ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ወደምተርቀው ወክድባ መንደር በመሄድ መኖር ጀመረ። በዚያን ወቅት እዚያ መንደር አማርኛ መናገር የሚችሉት እሱና አባቱ ብቻ ስለነበሩ ትምህርት ለመቀጠል ተቸገረ። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጭ ትምህርት የሚሰጠው በትግርኛ ስለሆነ አንድ ዓመት ቆይቶ እንዲመጣ በአስተማሪዎች ስለተነገረው በመንደሩ ውስጥ ያለትምህርት ትግርኛ ቋንቋ እየለመደ ቤተሰቡን ሲያገለግል ቆየ።

በመቀጠል አስመራ ከተማ ሐዲሽ ዓዲ ሰፈር አክስቱ ጋር ሆኖ በመማር አክሪያ ትምህርት ቤት ከ5- 8 ክፍል፣ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ከ9- 12 ክፍል ተምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። አስመራ እየተማረ ሳለ ዕዳጋ ዓርቢ በሚባል የገበያ ቦታ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ተልባ እና ቆሎ ከአክስቱ ጋር ይዞ በመሄድ ሸጧል። አክስቱ ዶሮ ያረቡ ስለነበረ የዶሮዎቹ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግሏል፤ በከተማው ውስጥ በመዘዋወርም እንቁላልና ዶሮ ይሸጥ ነበር። ክረምት- ክረምት ደግሞ ክብሪትና ጆንያ ፋብሪካ በቀን አርባ ሳንቲምና ከዚያ በታች እየተከፈለው የጉልበት ሠራተኛ በመሆን ሠርቷል።

አሥራ ሁለተኛ ከፍል ከጨረሰ በኋላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ባለማምጣቱ ወክድባ በመሄድ ቤተሰቡን አገልግሏል። ከዚያም አዲስ አባባ በ1962 ዓ.ም. በመምጣት መጀመሪያ በግንባታ ሥራ ውስጥ በጉልበት ሠራተኝነት በቀን ሰባ አምስት ሳንቲም እየተከፈለው ሠርቷል። በመቀጠልም በ19 ዓመቱ ዓለም ማያ በሚባል በግል ትምህርት ቤት በወር ሠላሳ ስምንት ብር እየተከፈለው በመምህርነት ተቀጠረ። በጊዜ ሂደት ደግሞ ክረምት- ክረምት (1967- 68ዓ.ም) በመማር በመምህርነት መጠነኛ ስልጠና አገኘ። ኮልፌ መሠረተ ዕድገት ትምህርት ቤት በኋላም እድገት ጎልማሶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስተምሯል። በመሃል በተለያዩ ምክንያቶች እያቋረጠ እንደገና እየጀመረ በአጠቃላይ በመምህርነት 33 ዓመታት አገልግሏል።

የንባብና ድርሰት ጅማሮ

የድርሰት ሥራ ጅማሮው አስመራ ከተማ ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የቤት ሥራውን ስለግመል ጽፎ የመጣው ነበር። በወቅቱ እስኪርቢቶ አምስት ሳንቲም በሚሸጥበት ጊዜ የአምስት ብር ፓርከር በጻፈው ድርሰት ምክንያት ከአማርኛ አስተማሪው ከመምህር ጌታቸው ተሸልሟል። መምህር ጌታቸው የንባብ ዓለምን ያስተዋወቁት የንባብ አባቱ ናቸው(መምህር ጌታቸው በኋላ አዲስ አበባ የኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል)። ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበው መጽሐፍ “ገልጠን ብናየው” የሚል በቤካ ነሞ የተጻፈውን ነበር። ከዚያ በኋላ በአማርኛም በእንግሊዝኛም የተጻፉ መጻሕፍትን አስመራ በሚገኙ ቤተመጻሕፍት በመግባት አንብቧል።

ዘጠነኛ ክፍል እያለ አንድ ጊዜ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲሄድ ለሚያያት ልጅ አንዴ ስለእግሯ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለፀጉሯ፣ ወዘተ. በትግሪኛ ግጥም በመጻፍ ለመስጠት ፈልጎ ሲተወው፤ በነጋታው ሌላ ሲጽፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ ሌላ ጊዜ ተጨማሪ በመጻፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ በመጨረሻ አንዱንም ሳይሰጣት ተወው። ለጓደኛው የተሻለ የሚለውን ግጥም ሲያሳየው አምጣ ብሎ ለራሱ የሴት ጓደኛ ሰጣት። የሴት ጓደኛው ደግሞ ለጋሽ ኃይለመለኮት ጎረቤቱ ስለነበረች ምላሽ ጻፍልኝ በማለቷ የሁለቱን የጽሑፍ ምልልስ በመፃፍ የመጻፍ ችሎታውን አሻሽሏል። ችሎታውንም ለማሳየት አንዳንድ ጽሑፎቹን የቤተክህነት ትምህርት ዕውቀት ላላቸውና አንባቢ ለሆኑት አባቱ በማንበብ ያቀርብ ነበር። ከእሳቸውም አድናቆት ተችሮታል።

የእኔ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጽሐፍ ወመዘክር ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ቤቱ የሆነ ያክል የተጠቀመበት ሥፍራ ነው። ጠዋት ለንባብ ገብቶ ምሳውን እዚያው አካባቢ ከበላ በኋላ ተመልሶ ለንባብ ገብቶ ማታ የሚወጣባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው። አክስቱ ጋር በነበረባቸው ጊዜያት ለአራት ዓመት ከስድስት ወር በተከታታይ የተወሰኑ ቀናትን ሥራ ለመሥራት ከቀረባቸው ጊዜያት ውጭ ወመዘክር ገብቶ አንብቧል። አንድ ጊዜ ወመዘክር ያነበበው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ የተባለ ደራሲ የጻፈውን መጽሐፍ አሮጌ መጽሐፍ መሸጫ ሥፍራ ያይና ገዝቶ የራሱ ለማድረግ ስንት እንደሆነ ይጠይቃል። ሻጩ ሦስት ብር እንደሆነ ሲነግረው ሦስት ብር ስላልነበረው በጣም ያዝናል። ትንሽ ቆይቶ ግን አንድ ሐሳብ መጣለት፤ ሦስት ብር ባይኖረውም ሦስት ሱሪ ስላለው አንዱን ሸጦ መጽሐፉን መግዛት። አላወላወለም፤ ሌላ ሰው ቀድሞት መጥቶ መጽሐፉን እንዳይወስድበት በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄዶ ሱሪውን ገበያ ውስጥ ሸጦ መጽሐፉን እጁ አስገባ። አሁን ድረስ መጽሐፉ እሱ ዘንድ ይገኛል። መጽሐፉን የሸጠለት ደግሞ ያን ጊዜ መጽሐፍ ሻጭ የነበረው ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ህሩይ ሚናስ) ነበር።

ወመዘክር የሕይወቴ አቅጣጫ መለወጫ እና ዕውቀት የገነባሁበት ቦታ ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ካነበባቸው መጻሕፍት ውስጥ “ጫት እንደበላ ሰው ያመረቀነኝ” የሚለው የፀጋዬ ገብረመድሕን “ኦቴሎ” የሚለው መጽሐፍ ነበር። የሼክስፒርን እንግሊዘኛ መጽሐፍና የፀጋዬን አማርኛ መጽሐፍ በመያዝ በ1963 ዓ.ም. “ኦቴሎ”ን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። “ፀላም መቀነት” (ጥቁር መቀነት)፣ “ጋሕሲ ስቃይ” (የስቃይ መቃብር) የሚል ርዕስ ያላቸው ቲያትሮች በትግርኛ ቋንቋ ጽፏል። የቲያትር ጽሑፎቹን ለደራሲ ፀጋዬ ገብረመድህን ተርኮለት ታሪኩ ጥሩ ነው፤ ቲያትር በመድረክ ላይ በተግባር የሚታይ፣ የሰውን ኅሊና መመሰጥ የሚችል ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርከውን ታሪክ በሙሉ የሚያጤንልህ ስለሌለ በዚህ መልኩ ጻፈው ብሎ ምሳሌ በመስጠት አስተያየት ሰጥቶታል። በተጨማሪም በቲያትር መድረክ ላይ ብቻ አይደለም መቅረት ያለብህ በሰፊው መሄድ የምትችለው ልቦለድ (ኖቭል) በመጻፍ ነው በማለት መክሮታል። አስተያየቱን ተቀብሎ አስተካክሏል፤ ልቦለድ በመጻፍም የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርጓል።

ኃይለመለኮት የጽሕፈት ሥራውን በመቀጠል የውጭ ጸሐፍት ሥራዎችን መገሻ ዓሻ (የቂል ጉዞ)፣ ሩፋኤል ጸበል፣ የደንከል ዱቄት፣ በሚል በትግርኛ እና በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ በመጨረስ የድርሰት ችሎታውን ይበልጥ በማሻሻል “የወዲያነሽ” የሚለውን ልቦለድ በአማርኛ መጻፍ ጀምሯል።

የትግል ሕይወት

በ1965 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ወመዘክር ቤተመጽሐፍ ያገኘው አንድ መምህር፣ ቡና እና ሻይ ሕንጻ አጠገብ ኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ውይይት ስላለ እንድትገኝ ብሎ ሁለት- ሦስት ጊዜ ዓለም ማያ ትምህርት ቤት ድረስ መጥቶ ጋበዘው፤ ኃይለመለኮት ጊዜውን በማንበብ ለማሳለፍ ስለፈለገ አልሄደም። መምህሩ ባለመሰልቸት መጋበዙን በመቀጠሉ በመጨረሻ በውይይቱ ላይ ተገኘ። የሄደበት ስፍራ ስለመበዝበዝ፣ ስለመጨቆን እና ስለመደራጀት አለመቻል በሁለት የማኅበሩ መሪዎች ትምህርት ከመሰጠቱ በላይ፣ ውይይት ተደርጎ ስለነበረ ለሕልሙ ፈውስ ያገኘ መሰለው። ከዚያ በኋላ የትምህርቱና ውይይቱ ዋና ተከታታይሆነ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁለቱ የማኅበሩ መሪዎች ሌላ ሥራ አግኝተው መሪነቱን ስለለቀቁ ማኅበሩን በፈቃደኝነት የሚመራ ሰው አልተገኘም። ኃይለመለኮት ማኅበሩ መፍረስ የለበትም በሚል ቁጭት ተመራጭ አመራር እስኪሰየም ድረስ በፈቃደኝነት እንደሚመራ መድረክ ላይ ወጥቶ ተናገረ። ሌላም ሰው ሊያግዘው ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩም ከመፍረስ ዳነ።

ሁለት ወር ያህል በመሪነት እንደሠራ ምርጫ ሲካሄድ የግል ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ። ከ1965 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. የማኅበሩ መሪ በመሆን ከመቶ በላይ ለሆኑ በደል ለደረሰባቸው መምህራንና ሠራተኞች ከሌሎች የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር በመተባበር ፍርድ ቤት በመቅረብ ስለደረሰባቸው በደል ተከራክሯል። በዚህ ጊዜ ባደረገው እንቅስቃሴ በየካቲት 1966 ዓ.ም. በንጉሡ ጊዜ ለአምስት ቀን ታስሮ ክስ ተመስርቶበት፣ በደርግ ጊዜ በ1967 ዓ.ም. ሃምሳ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተበይኖበት ከፍሏል።

የማኅበሩ መሪ ሆኖ ሳለ የወዲያነሽን ከአጠገቡ ገሸሽ አደረገ፤ ልቦለድ ድርሰት መጻፉንም አቋረጠ። በቤተመጽሐፍ ስለሙያ ማኅበራት የሚተርኩ መጻሕፍትን አብዝቶ አነበበ፤ የሶሻሊዝም ርዕዮት ተከታይም ሆነ። ጋዜጣ ላይ በብዕር ስም ሲጽፍ የነበረውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች በመተው ስለሠራተኛው መደብ መጨቆን እና ስለመደራጀት መጻፍ ጀመረ። በዚህ ሂደት በኢሕአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ እየታገለ ሳለ በደርግ መንግሥት ተይዞ በቅድሚያ ሶስት ወር በታላቁ ቤተመንግሥት (በወቅቱ ደርግ ጽ/ቤት በነበረው) ታስሯል። ከሦስት ወር በኋላ ደግሞ በዝውውር ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሯል። በአጠቃላይ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ በ1972 ዓ.ም. ተፈታ።

ስለእስር ቤት ሕይወቱ ሲናገር ‹‹እስር ቤቱ እጅግ በጣም የስቃይ ቦታ ነው። አንድ ሰው ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ ሲጨንቀው ራሱ ውስጥ የሚቀርበት ሥፍራ ነው። በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የመጀመሪያው 10 ካሬ ሜትር ሁለተኛው 12 ካሬ ሜትር በሆነ መስኮት በሌላቸው ቤት ውስጥ 46 እስረኞች ታስረን ነበር። በመኝታ ጊዜ አስቸጋሪ ስለሆነ እግራችን በግራና በቀኝ ተላልፎ ቁልፍልፎሽ ነው የምንተኛው። በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ በዚያን ጊዜ የነበረው የስቃይ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ሳይቀረፍ ዘልቆ መቀጠሉ ነው። ሲገረፍ የነበረው ሰው ገራፊ ይሆናል ብዬ አላስብም ነበር፤ በተግባር ያየሁት ግን ብሶበት መገኘቱን ነው›› ይላል።

ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ውስጥ የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት አብሮት የታሰረው ዮሐንስ ክፍሌ ከእንግሊዝኛው መጽሐፍ ወደ አማርኛ ሲተረጉም፣ ኃይለመለኮት የአርትኦት ሥራውን እየተከታተለ ከአሳሪዎቹ ተደብቆ አከናውኖ ጨርሷል። አርትኦቱን ከጨረሰ በኋላ ደግሞ አሳሪዎቹ እንዳያውቁበት ሌሊት ከስድስት ሰዓት በኋላ እየጻፈ ደግሞ “እናት” መጽሐፍን ብቻውን ወደ ቲያትር በመለወጥ በአማርኛ ጽፏል። ጽሑፉን ሲጽፍ የደብተር ሉክን አንዷን መስመር ለሁለት በመክፈል ነበር። የጻፈበትን አንድ መቶ ሰባት ገጽ ደብተር ከእስር ቤት እንዲወጣ ያደረገው ደግሞ በፔርሙስ ቂጥ ሥር አስገብቶ በመደበቅ አምስት ስድስት ሉክ በማስቀመጥ ለወንድሙ በመላክ ነበር። በዚያ ደብተር የተጻፈው ጽሑፍ አሁን የአርትኦት ሥራው ተጠናቆ ለሕትመት ዝግጁ ሆኖ አልቋል። አሳታሚ ቢያገኝ ለማሳተም ፈቃደኛ ነው።

ወደ ስነጽሑፍ ሥራ መመለስ

እንግዳችን ሁለት ዓመት ከአስር ወር ታስሮ ከተፈታ በኋላ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦት የነበረውን የወዲያነሽን ድርሰት አውጥቶ መጻፍ ቀጠለ። ትንሽ ቆይቶ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር በ1973 ዓ.ም. ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ የወዲያነሽ ድርሰትን ካቆመበት መጻፉን ተያያዘው። በ1976 ዓ.ም. ደግሞ በአካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ከማጀቴ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ አንድ ዓመት ያህል ጋራዥ ሠራ። ጋራዡ አካባቢ ለሚሠራ ጓደኛው ለሆነ አቶ ዘለቀ ብሩ ለሚባል ሰው የወዲያነሽን ረቂቅ እንዲያነበው ሲሰጠው፣ ለሦስት ቀን ያህል ካነበበ በኋላ ድርሰቱን አድንቆ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲያትምለት መስጠት እንደሚችል ይነግረዋል።

ከአቶ ዘለቀ ጋር አብረው በመሄድ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ረቂቁን ይሰጣሉ። ከአስር ወር በኋላ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ቦርድ እንዲታተም መፍቀዱ ተነገረው። መስፍን ሀብተማርያም ደግሞ የአርትኦት ሥራ እንዲሠራለት ተመደበ። መስፍን መጽሐፉን በአድናቆት እየካበ ከነገረው በኋላ ማስተካከል የሚገባውን አንድ ነገር ነገረው። ባሻ ያየህይራድ ጨቋኝ ስለሆኑ፣ በደል ስለፈጸሙ፣ ጊዜው ሶሻሊዝም ስለሆነ መሞት ስላለባቸው ግደላቸው ተብሏል አለው። እሱም ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ገደላቸው። “የወዲያነሽ” በ1978 ዓ.ም. ታተመ። የመጀመሪያ መጽሐፉ ሲታተም ኮልፌ መሠረተ ዕድገት የሚባል ትምህርት ቤት ያስተምር ነበር። እጅግ በጣም ደስተኛ ከሆነባቸው ቀኖች አንዱ እንዲታተምልህ ተፈቅዷል ተብሎ የተነገረው ቀን እንደሆነ ይናገራል።

“የወዲያነሽ” ታትሞ በወጣ በሃያ ቀኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ መጽሐፉን በመተቸት ወቀሳ አዘል አስተያየት ሰጡ። ኃይለመለኮት ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ‹‹እኔ እሳቸው በጻፉት መጽሐፍ ተምሬ ያደኩኝ ስለሆነ ምላሽ መስጠት አልችልም›› አለ። መምህር፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ጽጌ ግን ‹‹“የወዲያነሽ” እንደዚህ አይደለችም›› ብሎ ለጽሑፉ ምላሽ ሰጠ። ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹ባለአደራ ይጣራል ከጋራ›› በሚል በድጋሚ ጻፉ። እንኳን ባለአደራነት ደረጃ ሊዳረሱ ኃይለመለኮትና ደምሴ በወቅቱ በአካል የሚተዋወቁ ሰዎች አልነበሩም። በመጨረሻ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ የሚባሉ እውቅ ጸሐፊ ማሞ ውድነህን ነቅፈው ኃይለመለኮትን ደግፈው ጻፉ። በዚህ ሂደት “የወዲያነሽ” ታዋቂና ተነባቢ መጽሐፍ ሆነ። በኢትዮጵያ ሬድዮ “የመጽሐፍ ዓለም” በሚል ፕሮግራም ላይ በ1979 ዓ.ም. በተፈሪ ዓለሙ ለመተረክም በቃ። ከኢትዮጵያ ሬድዮ በተጨማሪ በአሜሪካና በጀርመን አገር በማኅበረሰብ ሬዲዮ ተተርኳል።

በሠዓሊ ጥበበ ተርፋ እና በአውግቸው ተረፈ መኖሪያ ቤት ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ አልአዛር ሳሙኤል፣ ሥዩም ተፈራ፣ መስፍን ዓለማየሁ፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደምሴ ጽጌ ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ቅድስት ክፍለዮሐንስ እና የቤቱ ባለቤቶች ቅዳሜ – ቅዳሜ እየተገናኙ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን እያቀረቡ እርስ በእርስ በነፃነት አስተያየት ይሰጣጡ ነበር። ተሳታፊዎቹ የሚሰጡት አስተያየት ጸሐፊውን የሚገነባ፣ የተሻለ እንዲሆን ጥረት ያደርጉ ነበር። ከተጠቀሱት ዋነኛ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በጊዜያዊነት ሌሎች ባለሙያዎችም እየመጡ ተሳትፈዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ኃይለመለኮት በዋነኛነት የሚሳተፉትን አባላት ሲገልጻቸው‹‹በየግሉ አንብቦ የመጣ፤ ሰው ማክበር ራስን ማክበር እንደሆነ የተረዳ፣ ለሥነጽሑፍ (ጥበብ) ከፍተኛ ፍቅር ያለው፣ አንብቦና አድምጦ የማይጠግብ፤ አንዱ የሌላውን ነፃነት የሚጠብቅ ስብስብ ነበር›› ይላል።

በዚህ የስነጽሑፍ ስብስብ ውስጥ የ“ጉንጉን” መጽሐፍ በማጀቴ አነጋገር ዘይቤ መጻፍ ተጀምሮ ተጠናቋል። መጀመሪያ ኃይለመለኮት ህዳር ወር 1980 ዓ.ም. አስራ ስምንት ገጽ ጽፎ አነበበ፤ ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ካዳመጠ በኋላ ‹‹ለእኔ ክላሲክ ሥራ ነው›› አለ። በቡድኑ አስተያየት እየተሰጠበት በየጊዜው ጋሽ ኃይለመለኮት ሲጽፍ፣ ሲያነበብ እንዲሁም አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቶ ነሐሴ ወር 1980 ዓ.ም. ተጽፎ ተጠናቀቀ። በ1981 ዓ.ም. ደግሞ የአካባቢውን ስያሜዎች ትክክለኛነት ለማጣራት ማጀቴ ድረስ በመሄድ በየመንደሩ በመዘዋወር አረጋግጧል። በመጨረሻ በ1982 ዓ.ም. ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን ሳይጠይቅ ድርጅቱ ራሱ ኃይለመለኮት በግሉ በማሳተም ላይ እንዳለ አውቆ ጥያቄ አቅርቦ “ጉንጉን” ታተመ። ከታተመ በኋላ በሸገር ሬዲዮ ለሁለት ጊዜ ተተርኳል። ከሸገር ሬድዮ በተጨማሪ በጀርመን አገር በማህበረሰብ ሬዲዮ ለመተረክ በቅቷል።

ከ“የወዲያነሽ”ና ከ“ጉንጉን” በተጨማሪ በ2005 ዓ.ም. “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ አሳትሟል፤ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም. የዶክተር ተወልደ እና ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ታላቅ ወንድምን የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። በትግርኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ”ን በ2005 ዓ.ም. አሳትሟል። “ኦቴሎ” በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ተማሪዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች በመድረክ ቀርቦ ታይቷል። ከጎቴ የባህል ማዕከል ጋር በመተባበርም ወደ ስምንት የሚሆኑ የሕጻናት መጽሐፍ ተርጉሞ ታትመዋል።

ዶክተር እንዳለጌታ ስለ አንጋፋው የስነ ጽሁፍ ሰው ሲናገር ‹‹ድንቅ መምህርና ደራሲ ብቻ ሳይሆን ድንቅ ወግ አዋቂ ነው›› በማለት ይገልጸዋል። በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ጽሑፎች በማቅረብ እየተሳተፈ ታትሞለታል። በጋዜጠኝነት “እፎይታ” መጽሔት ላይ ምክትል አዘጋጅ በመሆን ከመሥራቱ በተጨማሪ “ፈርጥ” መጽሔት ላይ የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በ“እረኛዬ” ተከታታይ ድራማ ላይ ተዋናይ በመሆንም ሠርቷል። ጋሽ ኃይለመለኮት በድራማው ላይ የተሳተፈው በአጋጣሚ መሆኑን ይናገራል። የፊልሙ ደራሲ ከሆኑት ውስጥ አንዷ የሆነችው አዜብ ወርቁ በአጋጣሚ ታገኘውና ከአንተ ሕይወት ጋር የሚሄድ አንድ ድራማ ስላለ ትተውናለህ በማለት ትጠይቀዋለች። እሱ መጀመሪያ አይሆንልኝም ብሎ ቢያንገራግርም በመጨረሻ እንደሚችል ታግባባውና ለፊልሙ ታሪክ መነሻ የሚሆን ሥራ በማቅረብ አብዬ በቃሉን ወክሎ ሲተውን ታይቷል።

ሌሎች የሕይወት ገጾች

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ላበረከተው አስተዋጽኦ የተለያዩ እውቅናዎችን አግኝቷል። በኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት በ1976 ዓ.ም. እና በ1977 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ደረጃ ምስጉን መምህር በሚል ተሸላሚ ሆኗል። በ1979 ዓ.ም. ደግሞ ከአዲስ አበባ ብቸኛ ተመራጭ በመሆን በኢትዮጵያ ደረጃ ምስጉን የትምህርት ባለሙያ ተብሎ የነሐስ ሜዳልያ ተሸልሟል። በወቅቱ በአገር ደረጃ የተሸለሙት መምህራን ሃያ አንድ ነበሩ። ኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት ያስተማራቸው ተማሪዎቹ ደግሞ በመምህርነት ላደረክልን ሁሉ እናመሰግንሀለን በማለት በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ውስጥ በአካባቢው ሕዝብ ፊት ዕውቅና በመስጠት ልዩ ተሸላሚ በማድረግ ካባ አልብሰውታል፤ ገንዘብም ሰጥተውታል።በሽልማቱ ሥነሥርዓት ላይ ግን ሌላ ጊዜ ለመናገር የማይቸገረው አንደበቱ በደስታ ብዛት ተሳስሮበት እንደነበረ ያስታውሳል። በደራሲነቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ደግሞ “ኢትዮጵያ ታመሰግናለች” ተብሎ ከሌሎች የሥነጥበባት ሰዎች ጋር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሜዳልያ ተበርክቶለታል።

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ከወረዳ 24 የምርጫ ጣቢያ በ1987 ዓ.ም. አንደኛ በመሆን ተመርጦ በሥራ አስፈጻሚነት በማኅበራዊ ዘርፍ ቢሮ ተሰጥቶት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሠርቷል። በዚህ ወቅት የቢሮክራሲው አስተዳደር ልምድ ስላልነበረው መንፈሱ የተጨነቀበትና በመምህርነት ሲያገኝ የነበረው ነጻነቱን ያጣበት ጊዜ መሆኑን ይናገራል። ስለሆነም ነፃነቱን ወደሚያገኝበት መምህርነት ሥራ ተመልሷል።

በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ስድስት ዓመት ሙሉ አባትህ ኤርትራዊ ነው በሚል ሰበብ ያለቀበሌ መታወቂያ ቆይቷል። በወቅቱ እናታቸው ወይም አባታቸው ኤርትራዊ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሥልጣን ሆነው እያስተዳደሩ ባሉበት አገር፣ እሱ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ መታወቂያ መከልከሉ እጅጉን አበሳጭቶታል፤ አሳዝኖታል። ባንክ ቤት የራሱን ገንዘብ ለማውጣት ሄዶ “የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ከሌለህ አትስተናገድም” የተባለበትን ቀን አሁን ድረስ በሀዘን ያስታውሰዋል። በዚሁ ሰበብ ከሚያስተምርበት ት/ቤት እንዲባረር ሲመከርበት እንደነበረና በመጨረሻ እንዳልተባረረ ይናገራል።

የይፍራታ ተወላጅ የሆኑት ባለቤቱ ወይዘሮ ጽዱ ጌታቸው የቤት እመቤት ሲሆኑ የድርሰት ሥራውን ሲሠራ ቋንቋውን ከማስተካከል በተጨማሪ የማጀቴ አካባቢ ቃላት ሲጠፋው በማስታወስ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንዲሆንም አድርገውታል። ባለቤቱ የቤተሰብ ጉዳይን ጠቅልለው ስለሚሠሩ እሱ ጊዜ ኖሮት መሥራት የሚፈልገውን እንዲሠራ ጊዜ አግኝቷል።

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ለፍትሕ የሚቆምን ሰው ያደንቃል። ሰው አደርገዋለሁ ባለው ጉዳይ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም፤ዋናው ተስፋ አለመቁረጥና አለመንበርከክ ነው። ተስፋ ላለመቁረጥና ላለመንበርከክ የሚያግዘው ደግሞ ማንበብና የተግባር ሰው መሆን ነው የሚል ፍልስፍና የሚከተል መሆኑን የሚናገረው እንግዳችን የአርትኦት ሥራ አስተማሪዎቼ አረፍአይኔ ሃጎስ እና ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ናቸው ይላል። የሰማንያ ሰዎችን መጽሐፍ በነጻም በክፍያም የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በአርትኦት ሥራ የሰጠውን አገልግሎት በጣም እንደሚደሰትበትና ብዙ ወጣቶችን እንዳስተማረበትና እንደረዳበት በኩራት ይናገራል። በዚህም ምክንያት የራሱን የድርሰት ሥራ አጠናቆ ለማውጣት እንዳዘገየበት ይጠቅሳል። ለጸሐፊዎች ምክር ሲሰጥ፤ ሀሳባችሁን ለማውረድ ፍጠኑ፣ ያለማቋረጥ ጻፉ፣ ደጋግማችሁ አንብቡና አስተካክሉ፣ የጽሞና ጊዜ እየሰጣችሁ አርሙ፣ ሥራችሁ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ችሎታችሁን በንባብ አበልጽጉ፣ ያነበበ ሰው ብዙ የእውቀት ምንጮች ይኖሩታልና አንብቡ- አንብቡ፣ ከሰዎች ጋር በቅንነት ስለሥራችሁ ተወያዩ፣ በአጭር ጊዜ ጥሩ ደራሲ መሆን አይቻልምና አትቸኩሉ ይላል።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

Recommended For You