‹‹የበደለኝ ሥርዓት እንጂ አገሬ ወይም ሕዝብ አይደለም›› – ዶክተር ፍቅሩ ማሩ

የዚህ እትም የፈለግ ዓምድ እንግዳችን ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ናቸው። ሥራ የጀመሩት በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዋጊ ጀት አብራሪ በመሆን ነው። በደርግ ዘመን በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ለስደት ተዳርገው ለበርካታ ዓመታት በውጭ አገር ኖረዋል። በዘመነ ኢህአዴግ ወደ አገራቸው ተመልሰው በሕክምና ሙያ ኢትዮጵያን ለማገዝ ብዙ ጥረት አድርገዋል። የነበረው ሥርዓት በኋላ በነጻ የተሰናበቱባቸውን ሁለት ክሶች መስርቶባቸው አምስት ዓመታትን በወህኒ ቤት አሳልፈዋል። ከእስር እንደተፈቱ ወደ ውጭ አገር ያመሩት ዶክተር ፍቅሩ ፣ ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ‹‹የበደለኝ ሥርዓት እንጂ አገሬ ወይም ሕዝብ አይደለም›› በማለት ከፍተኛ የልብ ስፔሻሊስቶችን የያዘ ቡድን እየመሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ኢትዮጵያውያን የልብ ታካሚዎች ሕክምና እንዲያገኙ አድርገዋል። ከእኒህ አገር ወዳድ ጋር ሕይወታቸውን እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!

ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኘው ጉራራ የተባለ ቦታ በ1943 ዓ.ም. ተወለዱ። ለቤተሰባቸው አምስተኛ ልጅ ናቸው። የክቡር ዘበኛ ሳጅን የነበሩት አባታቸው ኮሪያ ዘምተዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀ.ኃ.ስ) በአሁኑ ኮከበ ጽባሕ እስከ ሰባተኛ ክፍል ተከታትለዋል። ከሰባተኛ ክፍል በኋላ ታላቅ ወንድማቸው ለሥራ ወደ አሰላ ሲሄዱ ወንድማቸውን ተከትለው በመሄድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ አሰላ ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ተምረዋል።

አሰላ እያሉ ጀት በሰማይ ላይ ሲበር ሲመለከቱ በጣም ይማረኩ ስለነበረ የጀት አውሮፕላን ማብረር ምኞት ነበረቸው። ምኞቸውን እውን ለማድረግ በ1962 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀት አውሮፕላን ለማብረር ስልጠና ለመውሰድ ከተመለመሉ 27 ወጣቶች አንዱ መሆን ችለዋል። ስልጠናው ከባድ ስለነበረ ከሃያ ሰባት ሰልጣኞች እሳቸውን ጨምሮ አምስቱ ብቻ አጠናቀው በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ተመርቀዋል። በአየር ኃይሉ ኃላፊዎች ያላቸው ብቃት ታይቶ ከድምጽ ፍጥነት አንድ ነጥብ ስድስት በላይ የሚፈጥነውንና በወቅቱ ከፍተኛ የነበረውን የሱፐር ሶኒክ F-5 የጦር ጀት ለማብረር ሰልጥነው በአግባቡ በማጠናቀቃቸው ከአስተማሪዎቻቸው ጋር አብረው እስከማብረር ደርሰዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ስለኢትዮጵያ አየር ኃይል ሲናገሩ ብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት አየር ኃይል ከማቋቋማቸው በፊት በ1936 ዓ.ም. የተቋቋመና በወቅቱ በዓለም ላይ የተደነቀ ተቋም እንደነበረ ይናገራሉ። ከውጭ አገራት ከምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም ናይጄሪያን ከመሳሰሉ አገራት ሰልጣኞች ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል በመምጣት ይሰለጥኑ እንደነበረም ያስታውሳሉ።

በንጉሱ የመጨረሻ ዘመን መቶ አለቃ የነበሩት የጦር ጀት አብራሪ እንግዳችን በአየር ኃይል ውስጥ የተነሳውን አመጽ (አብዮት) ካነሳሱት ውስጥ አንዱ ነበሩ። በኋላም አራት ኪሎ በነበረው ደርግ እና በአየር ኃይሉ መካከል አገናኝ በነበረው ንዑስ ደርግ ውስጥ በአገናኝነት አስተባብረዋል። በዚህ ወቅት ሶማሊያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ክፍተት በመጠቀም የስለላ አውሮፕላን በመላክ በኢትዮጵያ አየር ክልል ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረጓን ተከትሎ ሁለት ጀቶች ተነስተው አውሮፕላኑን በማስገደድ ኢትዮጵያ መሬት ላይ እንዲያርፍና በቁጥጥር ሥር እንዲውል ካስተባበሩት ሰዎች አንዱ ነበሩ። በየትኛውም ጊዜ የውስጥ ክፍተት ሲኖር የውጭ ኃይሎች ሊያጠቁን መሞከራቸው አይቀርም ፤ ስለሆነም በማንኛውም ጊዜ በውስጣችን የሚኖረውን ክፍተት በተቻለ መጠን በውይይት መፍታት ብልህነት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ።

በአየር ኃይል ንዑስ ደርግ ውስጥ የአስተባባሪነት ሚና የነበራቸው በወቅቱ መቶ አለቃ የነበሩት እንግዳችን ወታደር ሥልጣኑን መያዝ የለበትም ሕዝባዊ መንግስት መቋቋም አለበት የሚል አቋም ነበራቸው። እሳቸው የወሰዱትን አቋም የሚያራምዱ ጓደኞቻቸውን ደርግ ሲያስር እንዲሁም በአደባባይ ሲረሽን ሲመለከቱ በጎንደር በኩል ጠፍተው በሱዳን አድርገው ሲውድን ገቡ።

በሱዳን የስደት ቆይታቸው ጋራዥ ውስጥ የመኪና ጠጋኝ በመሆን ዘጠኝ ወራት ከሠሩ በኋላ በውጭ አገር ሰዎች እገዛ ወደ ስዊድን አምርተዋል። ስዊድን ከሄዱ በኋላ ፖስታ ቤት ሠርተዋል፤ ካፍቴሪያ ከፍተው ሠርተዋል፤ አዛውንቶችን ተንከባክበዋል እንዲሁም ሬሳ መሸከም እና ሌሎች ሥራዎችንም ሠርተዋል። ሐኪም ብሆን የተለያዩ አገራት በመሄድ ልሠራ እችላለሁ ፣ የሥራ ዋስትናም አገኛለሁ በሚል ሀሳብ በመጨረሻ የሕክምና ትምህርት ተምረዋል። የሕክምና ትምህርት ሲማሩ ትዳር መስርተው ስለነበረ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነትም ነበረባቸው። ተደራራቢ ኃላፊነት ስለነበረባቸው በወቅቱ ከባድ ጊዜ አሳልፈዋል። ይሁን እንጂ ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ በመማር ማጠናቀቅ ችለዋል። ከመጀመሪያው የአጠቃላይ ሕክምና ትምህርት በኋላም በትምህርታቸው ገፍተው የውስጥ ደዌ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የልብ ስፔሻሊስት መሆን ችለዋል።

የሁለት ዘርፍ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ፍቅሩ ትዳር የመሠረቱት የሕክምና ባለሙያ ከሆኑት ዶክተር መሠረት መንግሥቱ ጋር ነበር። ጥንዶቹ ዶክተሮች ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። ፍቅርተ ፍቅሩ የአይቲ ኢንጅነር ስትሆን ሌላኛዋ ልጃቸው ሠላማዊት ፍቅሩ የአጠቃላይ ሕክምና ትምህርቷን ጨርሳ ዶክተር ሆናለች። በአሁኑ ወቅትም የአባቷን ፈለግ በመከተል የውስጥ ደዌና የልብ ስፔሻሊስት ለመሆን እየሠራች ነው። ሁለቱም ልጆቻቸው ትዳር መሥርተው እያንዳንዳቸው ሁለት ልጆችን ወልደው የአራት ልጆች አያት አድርገዋቸዋል።

ዶክተር ፍቅሩ በስደት ሱዳን ከገቡ በኋላ ደርግን በመቃወም የተለያዩ ሥራዎች ሠርተዋል። በስዊድንም በኢሕአፓ አመራር ውስጥ ገብተው በአውሮፓ ደረጃ በፖለቲካው ተሳትፈዋል። በመጀመሪያ በተማሪዎች ማህበር ቀጥሎም ኢሕአፓ ራሱን ይፋ ባወጣበት ወቅት በፓርቲው የአውሮፓ ክንፍ ተሳታፊ ነበሩ። ከገጠር ወደ ከተማ የሚለውን የትግሉን አካሄድ ይደግፉ ስለነበር የኢሕአፓ ወታደራዊ ክንፍ በመደገፍ አብዮቱን ለማስቀጠል ጥረት አድርገዋል።

ከወያኔ ጋር በነበረ የትጥቅ ትግል ሻቢያ ወያኔን በመደገፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሰራዊትን በኃይል ስላጠቁት በሕይወት የተረፉት ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን በኃዘንና በቁጭት ያስታውሳሉ። ዶክተር ፍቅሩ ስለነበረው ትግል ሲያስረዱ ‹‹ የደርግን ሥርዓት እንደምንቃወመውና እንደምንታገለው ያህል የመገንጠል ሀሳብ የሚያራምዱትንም እንቃወም ነበር። ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝም አገሪቷን ወደብ አልባ ማድረጉን አምርረን ስንቃወምና ስንታገል ነበር። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሶስተኛ ዜጋ ነው የሆነው። ሻቢያና ወያኔ ናቸው አገሪቷን እንዳሻቸው ሲያስተዳድሩ የነበሩት። ሁለቱ አካላት በፈጠሩት ልዩነት ጦርነት ተጀምሮ በወያኔ አሸናፊነት ሲገባደድ ያን ጊዜ ነው ኢትዮጵያውያን ወደ ሁለተኛ ዜግነት የመጣነው ›› ይላሉ።

ዶክተር ፍቅሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኤች አይ ቪ ኤድስ ኮንፍረንስ በ1991 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲደረግ ከስዊድን መጥተው ነበር። በኢትዮጵያ ያለውን የሕክምና ሁኔታ ሲመለከቱ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የልብና ልብ ነክ ሐኪም አንድ ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ። በዚህ ጊዜ በፖለቲካው በኩል ታግለው የሚያታግሉና የተሻለ ሥራ የሚሠሩ ብዙ ሰዎች ስላሉ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማቆም በሙያቸው ኢትዮጵያን መርዳት እንደሚገባቸው በማመን የጥቁር አንበሳ ወዳጆች ማህበርን አቋቁመው የተለያዩ ቁሳቁሶች ከስዊድን አገር በመላክ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን መርዳት ጀመሩ።

በመቀጠልም የዛሬ አስራ ሰባት ዓመት 85 በመቶ የውጭ ኢንቨስትመንት በማምጣት 15 በመቶ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማሳተፍ አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከልን በአዲስ አበባ በመመሥረት የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። የሕክምና ማዕከሉ የተመሰረተበት ዋና ዓላማ ፈረንጆች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በእርዳታም ሆነ በሌላ መንገድ ከፍተኛ የልብ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ እንዲቀር ለማድረግ በሚል ነው። እስካሁን ሰባት ሐኪሞች በከፍተኛ ደረጃ ሰልጥነዋል ፤ ወደ ፊትም ሌሎችን ለማሰልጠን ዕቅድ ተይዟል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ቦታ የማይሰጡ ሕክምናዎች በማዕከሉ ብቻ ይሰጣሉ። ይህ በቂ እንዳልሆነና ከዚህም በላይ መሥራት እንደሚቻል ዶክተር ፍቅሩ ይናገራሉ። በኪራይ ቤት ውስጥ ሆነው በማያፈናፍን ሁኔታ የልብ ሕክምናው እንደሚሠራም ይገልጻሉ። ይህን የተጣበበ አሠራር የሚያሻሽል ከሃያ እስከ ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፕሮጀክት በመቅረጽ ሀብትና ዕውቀት አሰባስበው የጨረሱ ቢሆንም መሬት ለማግኘት ያደረጉት ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጥረት እስከ አሁን ፍሬ እንዳላፈራ በኃዘን ይናገራሉ። የመሥራት ችሎታ እያለ በተጣበበ ሁኔታ ሕክምናውን መስጠት ስለማይቻል ፤ ሰፋ ለማድረግ ሲባል ከኪራይ ቤት ወደ ኪራይ ቤት ለመሄድ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት ያላቸውን ትልቅ ህልም እውን ለማድረግ ሀብትና ዕውቀት አሰባስበው የሚቀራቸው ተደራሽ የሆነ መሬት አዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት ነው። ልብ ለአራት ደቂቃ በተለያየ ምክንያት ከቆመ አንድ ሰው ይሞታል። አንድ ሰው ልቡን ታሞ በአንድና በሁለት ሰዓት ውስጥ ወደ ማዕከሉ ካልደረሰ የመዳን ዕድሉ በ80 በመቶ ዝቅ ይላል። አንድ ታማሚ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከመጣ 95 በመቶ የመዳን ዕድል አለው። የልብ ሕመም ጊዜ የማይሰጥ በሽታ ስለሆነ ለማዳን እንዲሁም ዘላቂ የሆነ የሕመምና በሽታ ይዞ እንዳይሄድ ለማድረግ ተደራሽ የሆነ ቦታ ማግኘት ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ፍቅሩ ይሄን ለማስገንዘብ ያደረጉትን ጥረት ሲናገሩ ‹‹የሚመለከታቸውን ለማስረዳት በተደጋጋሚ

 ሞክረናል ፤ ውጤት ግን አላገኘንም። አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከል አሁን ያለው አቋም በሰለጠኑ ሐኪሞችና በዘመናዊ መሣሪያዎቹ የሚሰጣቸው ሕክምናዎች በአውሮፓ ደረጃ እንደሚሰጡት ደህንነታቸውና ስታንደርዳቸውን የጠበቁ ናቸው። ሁለት የአፍሪካ አገሮች ይሄን የተደራጀ ተቋም አይተው ‹50 በመቶ ኢንቨስትመንቱን ሸፍነን ተደራሽ የሆነ መሬት በነጻ እንሰጣለን› በማለት ከኢትዮጵያ ተነቅሎ እንዲሄድ በስዊድን መንግሥት በኩል ጥያቄ አቅርበዋል።

እኔ አገሬን አልበድልም በማለት ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ እየለፋሁና እየታገልኩኝ እገኛለሁ። አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ የሚያገለግለው ይህ ተቋም ከእጃችን እንዳይወጣ መሬት የሚሰጡ ተቋማት ሁኔታውን ተገንዝበው ዐይናቸውን እና ጆራቸውን ከፍተው ያድምጡ እላለሁ። ሌሎችም ሁኔታው የሚፈቅድላቸው አካላት ከአቅማችን በላይ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሮ ተቋሙ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ መሬት ለሚሰጡት ተቋማት ያስረዱልን›› በማለት ሆስፒታሉን ለመሥራት ተደራሽ መሬት የሚገኝበት መንገድ እንዲመቻችላቸው አጥብቀው ይጠይቃሉ።

ዶክተር ፍቅሩ በዘመነ ኢህአዴግ አምስት ዓመት ታስረዋል። ለእስር የዳረጋቸው ጉዳይ ቀረጥ ያልተከፈለበት የሕክምና ቁሳቁስ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚል ነበር። ቁሳቁሶቹ ለልብ ሕክምና እገዛ ለማድረግ የመጡ ጓንትና ፕላስቲኮች መሆናቸውን በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለነበሩት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቀርበው አስረድተዋል። ዶክተር ቴዎድሮስም ለእነ አቶ መላኩ ፈንታ ነግረውላቸው ክሳቸው ተቋርጧል። ከዓመታት በኋላ “ክሱ የተቋረጠው ለእነ አቶ መላኩ ጉቦ በመክፈል ነው” በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ለእስር ተዳርገዋል።

ዶክተር ቴዎድሮስ ክሱ የተቋረጠው በእሳቸው አሳሳቢነት እንደሆነ እያወቁ ለሕሊናቸው ሲሉ እውነቱን ያልመሰከሩላቸው ‹‹በመሰረታዊነት በጣም ጨካኝና ክፉ ሰው ስለሆኑ ነው›› ብለው ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ላቅ ያለ የሕክምና ስፔሻሊስቶች ለኢትዮጵያ አያስፈልጓትም፤ በጤና ጣቢያ ደረጃ ያሉት ይበቋታል በሚል ለስፔሻሊስት ሐኪሞች ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው ይገልጻሉ። ይሄ አስተሳሰብ ደግሞ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚፈልጉት የነጮች አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም ጥቁሮች ላቅ ያለ ትምህርት አያስፈልጋትም የሚለውን የነጮች አስተሳሰብን ለማስፈጸም ተግቶ የሚሠራ ነው በማለት ያስረዳሉ።

አያይዘውም ‹‹አሁን ያለበትን የዓለም የጤና ድርጅት መሪነት ቦታን ከፀባዩና ከተስማሚነቱ አንጻር ማግኘት አልነበረበትም። እንኳን ይህ ከፍተኛ ቦታ ከዚያም በታች ቢሆን የሚገባው ሰው አይደለም። የነጮቹን አስተሳሰብ አራማጅ ስለሆነ ነው ቦታውን ሊያገኝ የቻለው። ለ27 ዓመት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወያኔ ጋር ሲያሰቃይ መኖሩ ሳይበቃው ፣ 50 ዓመት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ጎትቶ ያደኸየውን አሸባሪውን ወያኔን መልሶ ለማምጣት ያለበትን የኃላፊነት ደረጃና ተቋም በመጠቀም የሚያደርገው ተግባር የድሮ ሥራውን የሚያጠናክር ነው። ወደ ውስጥ ብዙ አልገባም እንጂ በሚያደርገው ተግባር እንደ ኢትዮጵያዊ የማፍርበት ሰው ነው›› በማለት ይገልጻሉ።

ዶክተር ቴዎድሮስ የሚደግፉት አሸባሪው ወያኔ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የከፈተው ጥቃት፣ እንዲሁም በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ ሆነ ሌላው አካባቢ የሚያደርሰው ስቃይና እንግልት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ዶክተር ፍቅሩ ይናገራሉ። አሁን በጅምላ አደረገው እንጂ ቀደም ሲል ጫካ በትጥቅ ትግል በነበረበት ጊዜ ጀምሮ በራሱ ሕዝብ ላይ እንዲሁም አብረው ለትግል የተሳተፉትን አባላቶቹን በጭካኔ ጫካ ውስጥ ከአንገታቸው በታች እየቀበረ የማሰቃየትና የመግደል ታሪክ እንዳለው ይገልጻሉ።

ሲመሠረት ጀምሮ ተኮትኩቶ ያደገውም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ስለሆነ ማሰቃየትና መግደልን መፍትሔ አድርጎ የሚጠቀም ቡድን መሆኑን ያስታውሳሉ። አሁን እያደረጉ ያሉት አሰቃቂ ድርጊት የናዚዎችንም ሆነ የሌሎችን አሰቃቂ ታሪክ ያነበቡ ቢሆንም የአሸባሪው ወያኔ አሰቃቂ ድርጊት ግን የሚያህል ተፈልጎ እንደማይገኝ፤ ይህም ከአፈጣጠራቸውና ከባህሪያቸው እንደሚመነጭ እንዲሁም ከጥፋትና ከጭካኔ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን በትግል ወቅት ከሚያውቁት ባህሪያቸው በመነሳት ያስረዳሉ።

አሁን ስላለው ሁኔታ ሲናገሩም ‹‹ቀደም ሲል የነበሩትን የወታደራዊ አሰላለፍ ሁኔታዎች በማየት አሁን ያሉትን ነገሮች ተመልክቼ እንደወታደር ስገመግመው ዶክተር ዐቢይ የወያኔን እንቅስቃሴ ገተው አሁን ለተደረሰው ደረጃ ማድረሳቸው በጣም የሚደነቅ ተግባር ነው። ወደ ፊት ደግሞ ዛሬ የሞቱት እና የታሰሩት እንዳሉ ሆነው እነ ጌታቸውና ደብረጽዮን መያዛቸውና መደምሰሳቸው የማይቀር ነው። እነሱ ከተደመሰሱ በኋላ ይግባውም፣ አይግባውም አስተሳሰባቸውን ተቀብሎ የሚከተላቸው ሕብረተሰብን እንዴት መቀየር እንደሚገባ በውጭ ያሉ ወገኖች ሀገር ውስጥ ካሉት ጋር በመቀናጀት የሌሎችንም አገሮች ተሞክሮ በመመልከት ትምህርት በመውሰድ ከፍተኛ ጥናት በማድረግ መፍትሔ ሊደረግለት የሚገባ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር ሳንቸኩል በትዕግስት በመጠበቅ ሁላችንም ተረድተን ልናግዝ ይገባል። ምክንያቱም ሙሉ መረጃ ያለው መከላከያ ጋር ነው። እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው ወይም በሌላ መንገድ ብዙ ጥፋት ሳይደርስ እጅ እንዲሰጡ የማድረግ ዘዴም ይኖራል። ንግስት ጣይቱ ከጣሊያን ጋር በነበረ ጦርነት በአንድ ወቅት ‹ውጊያ ከማድረግ ይልቅ ከብቦ በመያዝ ግንኙነት በማቋረጥ ውሃ እንዳያገኙ ማድረግ› የሚል ምክር አቅርበው ተግባራዊ ሆኖ የተገኘው ድል የሚታወቅ ነው። ስለሆነም መንግሥትንም ሆነ መከላከያን ለመውቀስ መቸኮል አይገባም›› በማለት ሀሳባቸውን ከሰጡ በኋላ የአካሄድ አቅጣጫ ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም ትዕግስት በማድረግ የመንግሥትና የመከላከያን ተግባር መከታተል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ከ45 ዓመታት በላይ ከነጮች ጋር ኖረዋል። ስለ አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን ባህሪ በሕክምና ማህበር ውስጥ በተግባር በመሳተፍ ጠንቅቀው ያወቃሉ። ስለባህሪያቸው ሲናገሩ በአንደኛ ደረጃ የአፍሪካ አህጉር ሁል ጊዜ ለእነሱ ተግባር የሚሆን ግብዓትና ጥሬ እቃ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚፈልጉ ይጠቅሳሉ። ሁለተኛ ፍላጎታቸው አፍሪካውያንን ከሌሎች ኃያላን መንግሥታት ጋር በሚያደርጉት ፉክክር ታዛዥ በማድረግ በቁጥጥራቸው ስር ውስጥ ለማዋልና ለማስተዳደር ይተጋሉ። ስለሆነም እነዚህን ሁለት ዓላማዎች የሚያስፈጽምላቸው ተባባሪ መንግሥት እስካገኙ ድረስ ይደግፋሉ በማለት ዋነኛ የሚባሉትን ባህሪዎቻቸውን ያስቀምጣሉ። በመቀጠልም፤ ‹‹ዶክተር ዐቢይ በኖቤል ሽልማት ላይ ያደረጉትን ንግግር በማዳመጥ ሽልማቱን የምትሰጠው ተወካይ ‹የምናገረው ነገር አሳጣኸኝ!› ነው ያለችው። ይሄ ሁሉ አድናቆት በእኛ ጭን ላይ አስቀምጠን የፈለግነውን ጉዳይ ሊያስፈጽምልን ይችላል የሚል ከፍተኛ እምነት የተካሄደ ነው።

ዶክተር ዐቢይ ግን ነጮች ያላሰቡትን እና የማይፈልጉት ነገር ነው ያደረጉት። ‹ከማንም የውጭ ተጽዕኖ በመላቀቅ በነጻነት ሕዝቤን አምኜ የአገሬን ጥቅም ከሚያስጠብቅልኝ መንግሥት ይሁን ተቋም ጋር እተባበራለሁ፤ የማያስጠብቅ ከሆነ አልተባበርም› በማለት በተግባር መፈጸም ጀመሩ። ይህን በማድረጋቸውም አክርረውና አምረው ጠሏቸው። አሁንም ‹እርዳታ እናቆመዋለን፣ ማዕቀብ እንጥላለን› ብለው ማስፈራሪያና ዛቻ የሚያደርጉት ዶክተር ዐቢይን አብዛኛው ሕዝብ ስለደገፋቸው ፍላጎታቸው እንዲፈጸም ሊያስገድዱ የሚችሉት የመጨረሻ አማራጫቸው አሸባሪው ወያኔን አዲስ አበባ ማምጣት ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ቡድን መደራደሪያ እንዲሆን ማቆም ነው። ይሄን ተግባር ለማስፈጸምና የኢትዮጵያን መንግሥት ለማንበርከክ የሚችሉትን ያህል ያደርጋሉ፤ እስከ ደም ጠብታ ድረስም ይታገላሉ። ይሄን ለመግታት ኢትዮጵያውያን ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል›› በማለት ነጮች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም በሰብዓዊ እርዳታ ሥም ብዙ ነገር ለማድረግ እንደሚጥሩ ያሳስባሉ።

ነጮቹ በሚያደርጉት ዛቻ መደናገጥ እንደማይገባ ሲያስረዱ፣ አንዱ ዛቻቸው “የኢኮኖሚ እቀባ እናደርጋለን” የሚል መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ስለምታስፈልጋቸው ላያደርጉት እንደሚችሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ቢያደርጉትም ይሄን ያህል የኢትዮጵያን ሁኔታ እንደማያናጋ ምሳሌ በመስጠት ሲያስረዱ የአሜሪካ እርዳታ ሰጪ ኃላፊ ስትናገር “የኢትዮጵያን ሰባት በመቶ ሕዝብ የምንመግበው እኛ ነን ብላለች” በማለት ጠቅሰው እሷ ያለችውን ይዘው መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ነን ብለን ብንል አስር ሰው ለአንድ ሰው እርዳታ ቢያደርግ የአሜሪካ ምጽዋት አያስፈልገንም። ይሄን በተግባር ማሳየት ብንጀምር ኢትዮጵያን ማጣት የማይፈልጉበት ምክንያቶች ብዙ ስለሆኑ ጥንካሬያችንን እና ችግራችንን በራሳችን መፍታት መጀመራችንን ዐይተው ተመልሰው ወደ እኛ እንደሚመጡ ከባህሪያቸው በመነሳት እርግጠኛ ናቸው።

የራስን ችግር በራስ ለመፍታት በሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ በቅንጅት ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሱት ዶክተር ፍቅሩ የዲያስፖራው ማሕበረሰብ እየሠራ ያለው ሥራ ቢኖርም በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የዲያስፖራው አባላት ሊያደርጉ የሚገባውን ተግባራት ሲገልጹ ‹‹ሶስት ሚሊዮን ዲያስፖራ አለ ይባላል። እያንዳንዱ አንድ መቶ ዶላር በወር ቢያዋጣ ሶስት መቶ ሚሊዮን ዶላር አገር ውስጥ ይገባል። ከሶስት ሚሊዮን ዲያስፖራ አንድ ሚሊዮኑ ብቻ አንድ መቶ ዶላር በወር ቢያዋጣ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር አገር ውስጥ ይገባል። ገንዘቡ አገር ውስጥ ሲገባ ብዙ ነገር ይሠራል። ይሄን ለማስፈጸም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በቅንጅት ማድረግ ይጠይቃል። ሁለትና ሶስት ዓመት ሊርበን ይችላል፤ እንደ አገር መቶ ዓመት ከመራብ ሶስት ዓመት ተርበን ዘጠና ሰባት ዓመት ለዘላቂነት ጠግበን ብንኖር ይሻላል። በደንብ ተቀናጅተን ከሠራን ተባብረን ይሄን የመከራና የችግር ጊዜ በዘላቂነት እንወጠዋለን›› በማለት ያስረዳሉ።

በገንዘብ የሚደረግ ድጋፍ ዋነኛው እንደሆነ ጠቅሰው ሌላው ድጋፍ ሁለተኛና ሶስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ፍላጎቱና ዓላማውን ተከትሎ ተነሳሽነቱ ከመጣ የህዳሴ ግድቡን በዲያስፖራ አባላት ብቻ ማጠናቀቅ ይቻላል ብለው ያምናሉ። ግድቡ ከድህነት ለመውጣት ከሚረዱ ነገሮች አንዱ መሆኑን፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚመጣ እንዲሁም ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው ግብጽ አምርራ ግድቡ እንዳይሠራ የምትታገለን አንዱ ምክንያት እሷ የምትሸጠውን የኤሌትሪክ ኃይል ኢትዮጵያ መሸጥ ስለምትጀምር በኢኮኖሚ ዝቅ እንደምትል ስምታውቀው መሆኑን ይናገራ ሉ።

ዶክተር ፍቅሩ የውጭ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት መሪዎች ላይ ብቻ ማተኮር እንደማይገባ፣ የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ መሪዎች የሕዝባቸውን ድምጽ (ቁጣ) የሚሰሙ ስለሆነ ትኩረታችን ታክስ ከፋዩ ሕዝብ ላይም መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ። ታክስ ለሚከፍለው ሕዝብ ያለውን በደል በማሳወቅና በማስረዳት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ መንግሥታቸውን እንዲያሳስቡና ጫና እንዲፈጥሩ ማድረግ አንደኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንደሚገባው ይገልጻሉ። በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት በእሳቸው ላይ ተደራራቢ በደል ሲደርስ ስዊድን አገር ስለተከናወነው እንቅስቃሴ ሲናገሩ ‹‹በእኔ መታሰር ጉዳይ ላይ ታክስ የሚከፍለው ሕዝብ ባደረገው መነሳሳትና ተጋድሎ መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር የስዊድን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በመነጋገር ብዙ ነገር ሊደረግ ችሏል። እንዲህ አይነት ተግባራት ለማከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያውን እና የደህንነት ተቋሙን በተሻለ መልኩ በአዲስ መልክ አጥርቶ እንዳደራጀው ሁሉ ዲፕሎማሲው ውስጥ ተሰግስገው ያሉትን የአሸባሪው ወያኔ ደጋፊዎችን ከሕዝቡ ጋር በመመካከር ማጥራት ይኖርበታል›› በማለት የዲፕሎማሲው ተቋም ሊፈተሸና ሊስተካከል እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያን የሶስት ዓመቱን የለውጥ አጀማመርና ሂደትን ሲያስረዱ ምናልባት ቻይና ውስጥ ታይቶ ሊሆን ይችላል እንጂ ሌላ ቦታ ታይቶ እንደማያውቅ ይናገራሉ። ይህ የለውጥ ሂደት እመርታ ያሳያል እንጂ አንዳችም መቀልበስ ይደርስበታል ብለው እንደማያስቡና አንዳንድ ቦታ ከተገቢው በላይ የፈጠነበት ሁኔታ እንዳለ ይገልጻሉ። በአጠቃላይ የለውጡ ሂደት ሲታይ የሚፈለገውን ያህል በቂ እንዳልሆነ ፣ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች እንዳሉም ያሳስባሉ። ለእነዚህ ጉድለቶች ምክንያቶቹ ሲነሱ ክህሎቱና አቅሙ ሁሉ የተዘጋጀ ነበር ወይ ? ብሎ በመጠየቅ በአግባቡ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ማጉላትና ማናፈስ ሳይሆን ከሚመለከተው ተቋም ጋር በመሆን ዕውቀት ባለው ሁኔታ ማስረዳትና እንዲስተካከል መታገል ከሁሉም ዜጋ እንሚጠበቅ ያስገነዝባሉ።

ዶክተር ፍቅሩ ስለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹ምርጫው ከዲሞክራሲያዊነቱ አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርጎ የማይታወቅ ነው። አውሮፓም አሜሪካም ውስጥ ምርጫን በተመለከተ ተከታትያለሁ። እነሱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተደረገ ብለው ከሚያወድሷቸው አገሮች ጋር አሁን በኢትዮጵያ የተደረገው ምርጫ ባይበልጥ እንኳን አይተናነስም። እንደእኔ አረዳድ በግልጽ ለመነጋገር ሕዝቡ የብልጽግናን ፓርቲ መረጠ አልልም። ብዙ ሰዎች ጠይቄአለሁ ‹ዶክተር ዐቢይን መርጬ መጣሁ› ነው የሚሉት። እኔ እስር ቤት ሆኜ ዶክተር ዐቢይ ፓርላማ ያደረጉትን የመጀመሪያ ንግግር አድምጬ እግዚአብሔር ሙሴን ለእስራኤል እንደላከው ሁሉ ዶክተር ዐቢይን ለኢትዮጵያ ልኮላታል ብዬ ጮክ ብዬ ተናግሬአለሁ።

በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር በዚህ አጭር ጊዜ ብዙ ሥራ በመሥራት አሳይተዋል። በሚሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል፤ እንደማንኛውም ሰው ሊሳሳቱ ይችላሉ። የሚያስተካክሉበትን መንገድ ማሳየትና ማገዝ ከሁላችንም ይጠበቃል። የብልጽግና ፓርቲ አባላት ደግሞ የዶክተር ዐቢይ ደጋፊና ረዳት መሆን አለባቸው። ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል ብሎ መሞኘት አይገባም። የፓርቲ ነገር ቢሆን ኖሮ በተፎካካሪነት ያሉት ብዙ ድምጽ ያገኙ ነበር። ሕዝቡ ዶክተር ዐቢይ ላይ እምነት አለው። ብልጽግና ፓርቲ የሚሠራው ስህተት ሁሉ መስተካከል ካልታየበት ‹ዶክተር ዐቢይ ነው የሠሩት› ብሎ በመቀየም ዛሬ እንደመረጠው ሁሉ ነገ ሕዝቡ ሊቀጣ ይችላል። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ አመራር በከፍተኛ ደረጃ አስበው መምራትና ማስተዳደር ይገባቸዋል›› በማለት ያሳስባሉ።

ዶክተር ፍቅሩ አዲስ የተመረጠው መንግሥት ይሠራቸዋል ብለው የሚጠብቁት ዋና ተግባራትን ሲናገሩ ‹‹ከዚህ መንግሥት የምጠብቀው አንዱ ትልቅ ጉዳይ የኢኮኖሚ ተግዳሮት የሚባሉትን ጉምሩክ፣ ገቢዎች እና የታክስ ስርዓቱ እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች ያሉት ማነቆዎች እንዲፈታ ነው። ምክንያቱም የኢኮኖሚ ተግዳሮት ካልተፈታ የኢኮኖሚ እድገት የሚባለው አይመጣም። ኢኮኖሚው ካላደገ ደግሞ ፖለቲካውን ተሸክሞ መሄድ አይኖርም። ሌላው የምጠብቀው ትልቅ ጉዳይ ለሃያ እና ሰላሳ ዓመታት በዘቀጠ የትምህርት ሥርዓት ስለታለፈ በተለይ ወጣቱን በትምህርትና ስልጠና ትኩረት ሰጥቶ የማደስ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሌላው ትልቅ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነቱ መጠበቅ አለበት። በአሸባሪው ወያኔ ጊዜ እንደነበረው የቡድን መብት ወይም የፓርቲ መብት እየተባለ የሚሄድ ከሆነ የግለሰብ መብት እስከተረገጠ ድረስ ደኅንነት አይኖርም። መንግሥት የግል መብት ሳያረጋግጥ የቡድን መብት ያረጋግጣል ከተባለ መፈናፈኛ አይኖርም። ስለዚህ እያንዳንዱ የዜግነት መብቱ እንዲጠበቅለት በማድረግ ግለሰቡም መብቱን እንዲያስጠብቅ ተባባሪ ማድረግ ይገባል። የፍትሕ አካላት ደግሞ መብቱ እንዲከበርለት አጋዦች ይሆናሉ›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እንግዳችን ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በሰሜን በኩል ያለው ስቃይና እንግልት እንዲሁም ጥፋት መቆም አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። የሰሜኑ ችግር ሲቀረፍ በሌሎች አካባቢም ያሉ ችግሮች አብረው እንደሚቀረፉ ይገልጻሉ። ስለሆነም የአሸባሪው ወያኔ ጉዳይ በወታደራዊም ሆነ በሌላ መልኩ በአጭር ጊዜ ከተጠናቀቀ በእሱ ድጋፍ የሚተነፍሱና የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔ አይነቶቹ ምንጫቸው ስለሚደርቅና ስለሚዘጋ የእነሱም ጉዳይ በዚያው እንደሚጠናቀቅ ይገልጻሉ። በመንግሥት ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ለአሸባሪው ወያኔ የሚደግፉትም መጋረጃው ስለሚገለጥ መጋለጣቸው እንደማይቀር ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከሰጠችው ከቀረጥ ነጻ ንግድ ማበረታቻ ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድትወጣ ግፊት ለሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን አስተያየት ሲሰጡ በእስር በነበሩ ጊዜ ተደጋጋሚ በደል ቢፈጸምባቸውም (በቅድሚያ ከተከሰሱበት በተጨማሪ እሳቸው ሆስፒታል ተኝተው በነበሩበት ወቅት እስር ቤቱ በመቃጠሉ እሳቸው ቃጠሎውን አስተባብረዋል በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶባቸው በዚህም በደል ደርሶባቸው ነበር) እሳቸው ላይ በደረሰው በደል የተነሳ የስዊድን መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ አንድም ሳንቲም ቢሆን እንዳያቋርጥ በልጃቸው በኩል በተደጋጋሚ ሲጠይቁና ሲያሳስቡ እንደነበረ በማስታወስ ይጀምራሉ።

በመቀጠልም ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ዕርዳታ በተለይ ውጪ ያሉት ዲያስፖራዎች ለመንግሥት ባለስሥልጣናት የሚደርስ ይመስላቸዋል ፤ ዕርዳታ ሲቀር የሚራበው፣ የሚሰቃየው፣ እንዲሁም ችግሩን የሚሸከመው ዕርዳታው የሚደርሰው ወገን ነው። ስለዚህ ዕርዳታ እንዲቀር የሚደረግ የትግል ዘዴ መንግሥት ከያዘው አቋም አንድ ሴንቲሜትር ወደ ኋላ የሚያደርገው እንዳልሆነ ይናገራሉ። አጎዋን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት የፈቀደው ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ትናንሽ አምራቾች እንዲጠቀሙ ታስቦ አብዛኛውን መካከለኛና ደሃ ሕዝቦች የሚጠቀሙበት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዶክተር ዐቢይ ወይም ሚኒስትሮች የሚጠቀሙበት አይደለም። ስለሆነም አጎዋ ቢቀር መንግሥትን የሚጎዳ እንዳልሆነ ተገንዝበን በተለይ ውጭ ያሉ ዲያስፖራዎች ዜግነታቸውን ተጠቅመው ለአሜሪካ ሕዝብ፣ ለሴኔት እና ለኮንግረስ ሰዎች ድሃው ሕዝብ ተጎጂ እንደሚሆን ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ‹‹የበደለኝ ሥርዓት እንጂ አገሬ ወይም ሕዝብ አይደለም›› በማለት ከሁለት ሳምንት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ እሳቸው የተሳተፉበት ከፍተኛ የልብ ስፔሻሊስቶች ቡድን እየመሩ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢትዮጵያውያን የልብ ሕመምተኞች እገዛ እንዲያገኙ አድርገዋል። እሳቸው የዚህን ያህል ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም በተለይ ዩቲዩብ ከፍተው ተደራጅተው ሰበር ዜና እያሉ የኢትዮጵያ ሕዝብን መከራ እንዲቀጥል የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስ አስተያየት ሲሰጡ ‹‹ለኢትዮጵያውያን በጣም አበክሬ የምናገረው እባካችሁ የእነዚህን አካላት ዩቲዩብ ምንም አይነት ሰበር ዜና አለ ቢሉ አትክፈቱ። የምትከፍቱ ከሆነ የእነሱን ተመልካች ቁጥር ስለምታበዙ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው አካል ብዙ ሰው ይከታተላቸዋል በሚል ገንዘብ ስለሚሰጣቸው ወሬ እየፈጠሩ ይቀጥላሉ። በመክፈት አናብዛቸው፤ ዝም በማለት እንቅጣቸው እላለሁ። ስለኢትዮጵያ በጎ የሚያስቡትን በመከታታል መርጦ መረጃ ማግኘት ይቻላል›› በማለት ስለሚዲያ አጠቃቀም የሚታየው ልምድ መስተካከል እንደሚገባው አበክረው ይመክራሉ።

በእስር ላይ በነበሩ ጊዜ በድብቅ ማስታወሻ እያስወጡ እንዲቀመጥ ሲያስደርጉ ቆይተው ከእስር ከተፈቱ በኋላ ስዊድን ከሚገኝ ጋዜጠኛ ጋር በመተባበር በስዊድን ቋንቋ “አምስት ዓመት በእስር” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አሳትመዋል። ብዙ አንባቢ ስላገኘ ወደ ፊልም ሊቀየር እንደሆነ እንዲሁም ወደ እንግሊዘኛና አማርኛ ተተርጉሞ በቅርቡ አንባቢ እጅ እንደሚደርስ ነግረውናል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከልና እህት ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ልብና ልብነክ የሆኑ በሽታዎችን ከማገዝ አንጻር ምን አይነት አገልግሎት እንደሰጡ እንዲሁም ሐኪሞች እንዴት እንደሰለጠኑ በመጽሐፍና በፊልም የማሳየት ዕቅድ አላቸው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ብለው ለተነሱት ዕድሜና ጤና እንዲሰጣቸው በመመኘት ስለኢትዮጵያ የሚታያቸው ተስፋ ብቻ አለመሆኑን እና ሕዝቡ ከዚህ አስቸጋሪ ኑሮ ወጥቶ አገሩን ጠንካራ የአፍሪካ መሪ አገር እንደሚያደርጋት እርግጠኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ‹‹ከሕዝቡም ሆነ ከሌላው ወገን የማየው ከእነጉድለቱ እየተሄደበት ያለው አካሄድ በትክክለኛው መስመር ላይ እንደሆነና ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን እንዳይ አድርጎኛል። ለዚህ መስመር ቀጣይነት ከእነቤተሰቤ በዕውቀትም ሆነ በገንዘብ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ›› ሲሉም ለኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሆነ ይናገራሉ።

 ስሜነህ ደስታ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You