ኢትዮጵያዊው ሠማዕት፡-አቡነ ጴጥሮስ

 የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ታላቅ ሠማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በቀድሞ አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በፍቼ ከተማ ተወለዱ። አቡነ ጴጥሮስ በሠማዕትነት እንደሚሞቱ መምህራቸው በትንቢት ነግሯቸውም ነበር። አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋር አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው ‹‹ሀይለማሪያም፣ አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚች አገር ላይ ይሰለጥናል። ታዲያ አንተ ያኔ በነፍስህ ሳትሳቀቅ በሠማዕትነት እለፍ። ሠማዕትነት ክፍልህ ነው። አደራ!›› ብለዋቸውም እንደነበር ይነገራል።

ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሠማዕትነት ለማለፍ በቅተዋል። አቡነ ጴጥሮስ የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ሀይለማሪያም ይባሉ ነበር። በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሀይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል። የቤተክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በዋሸራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈፅመው መምህርም ሆነዋል። የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር በመሄድ

 ተምረዋል። በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጽሐፍት ሚስጢር ይመግቡ ወደ ነበሩት ወደ ሊቁ አካለወልድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጽሐፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትን እና ሊቃውንትን በሚገባ አካሂደዋል።

ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አማራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለዘጠኝ ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ። በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈፀሙ። ከዚያም በመምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለስድስት ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረጽዮን ቅድስተ ማሪያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግስት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንስሀ አባትም ሆኑ።

ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆች እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት በሀይማኖታቸውና በስነምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ። ከዚህ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምስራቀ ኢትዮጵያ ተብለው ተሹመዋል። ቤተክርስቲያንንና አገራችንን በፀሎታቸው፤ ሕዝብን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነት አውጆ ሕዝቡንም በግፍ ይገድል ጀመር።

አቡነ ጴጥሮስ ይህንን ግፍ በማየታቸው ከአገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በፀሎታቸው ሊዋጉት ተነሱ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ተከትለው ወደ ማይጨው ዘመቱ። ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ ጋዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሳ የኢትዮጵያ ሠራዊት ቢበታተንም ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረሊባኖስ ሄደው ለሀገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሰላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል። በደብረሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረውን የእነ ደጅአዝማች አበራ ካሳ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረውን የእነ ፍቅረማሪያም አርበኛ ጦር እንዲሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባነብሶ ጦር ሶስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሃል አዲስ አበባ በመግባት አዲስ አበባ ላይ ሰፍሮ የነበረውን ፋሺስት ለመውጋት ታቅዶ የነበረውን እቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ።

መጀመሪያ የእነ ፍቅረማሪያም አርበኛ ጦር በኮተቤ አድርጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲደርስ ተመትቶ ተመለሰ። ይሄኛው እንዳለቀ የእነ አባነብሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድጋሚ ተመትቶ ተመለሰ። መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሳ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እሱም በጠላት ጦር ተመትቶ ተመለሰ። በዚህ አይነት ሁኔታ ሶስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደ መጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኞች ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም። ይልቁንም ብችል ጠላት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ እርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት ጠላት ላይ እንዲነሳ አደርጋለሁ። ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ። በማለት ከአርበኞቹ ተነጥለው አዲስ አበባ ቀሩ።

ይሁን እንጂ ጠላት በመላው ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አቡነ ጴጥሮስን እንዳሰቡት ሊያንቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር። በመሆኑም አቡነ ጴጥሮስ የሀገሬ ህዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሠማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑ። የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለነበረው ለራስ ኃይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡ። እሱም አቡነ ጴጥሮስን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. አሳልፎ ሰጣቸው። ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው።

አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሠማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት ኮሪየሬ ዲላ ሴራ የተባለ ጋዜጣ ወኪልና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፓጃሊ የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 በአዲስ አበባ በነበረበት ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈፀመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎት ነበር።

‹‹ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ። በዚህም ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ለእስክድርያው መንበረ ፓትሪያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት። አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስ ህይወትን ለማትረፍ አስበው ነበር። ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስን የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብፅ ከአዲስ አበባ ውጪ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን ውስጥ እንዲፈፀም መመሪያ አስተላለፈ።››

የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ ፓጃሊ የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን ሲገልጽ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረጅም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸውም ጠየም ያለ፣ አዋቂነታቸውና ትህትናቸው ከገፃቸው የሚነበብ ሲሆን በወቅቱ ለብሰውት የነበረው ልብስ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የቦካ ነበር።›› በማለት ይገልፀዋል።

በዚህ ሁኔታ ወደ ችሎት ቀረቡ። በችሎቱ የተሰየሙት ዳኞች ሶስት ሲሆኑ ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው። የመሃል ዳኛው ኮሎኔል ነበር። የቀረበባቸው ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛው ‹‹ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች፣ ሊቀጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ የጣሊያንን መንግስት ገዢነት አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ? ›› ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው። ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ አገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ›› አሉ።

በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ ‹‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሀይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፤ ስለውድ አገራችሁ፣ ስለቀናች ሀይማኖታችሁ ተከላከሉ። ነፃነታችሁን ከማርከስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ። የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪዪ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን›› ብለው አወገዙ።

ቀጥለውም አቡነ ጴጥሮስ ችሎቱ ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየፀለዩ ሕዝቡን ባረኩት። ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ አይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ። በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን አውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በወቅቱ ምንም ፍርሀት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረ ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሀትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር። የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ፀልይው በመስቀላቸው ባረኳቸው።

አቡነ ጴጥሮስ ሊገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሁ አስር ሜትር ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያው ተወሰዱ። ከገዳዮቻቸው አንዱ ‹‹ ፊትዎን መሸፈን ይፈልጋሉን ?›› ሲል ጠየቃቸው። ‹‹ይህ ያንተ ሥራ ነው›› ሲሉ መለሱለት። ወዲያው ቦታው እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ተደረጉ። ከዚያም ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ ተኩስ በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ነገር ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያ በኋላ አንድ ወታደር በሶስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው።

አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉበት ቦታ መሀል አዲስ አበባ ዛሬ መታሰቢያ ሀውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ፓጃሊ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል። በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ ? ሲል በወቅቱ አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነት ሲቀበሉ በቦታው በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉት የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ እለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘው የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለው በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውን ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩስ ገደሏቸው። ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ህዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ። ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‹በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ። ‹እንዴት? ›ብለው ‹አላየህም ሲያጨበጭብ !›አለኝ ‹ባታውቀው ነው እንጂ ሕዝቡ ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት። እንዴት ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት። ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና የኪሳቸውን ሰዓት አሳየኝ›› ብለዋል።

አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ ላይ የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸዋል። የእኚህን ታላቅና ቅዱስ ሠማዕት አባት ክብርና ተጋድሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ቅዱስ ሰማዕት ብሎ በማፅደቅ በስማቸው በቅድስና ማዕረግ በስማቸው ታቦት ተቀርፆ ቤተክርስቲያን እንዲሠራላቸው ወስኗል። ይህም በተወለዱበት በሰሜን ሸዋ ስላሴ ሀገረስብከት በፍቼ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኗል። ጉምቱ ባለቅኔ ፀጋዪ ገብረመድህን በግጥሙ ህያው አድርጓቸዋል። ይሁንና አፅማቸው የት እንደወደቀ ዛሬም ድረስ ሚስጢር እንደሆነ አለ። ደራሲ ፀሀይ መላኩ በአንድ ወቅት በኢቢኤስ ቴሌቭዥን ለብራና ልጆች ፕሮግራም በሰጠችው ቃለ ምልልስ የአቡነ ጴጥሮስ አስክሬን ፉሪ አካባቢ መኒሳ በምትባል ጉብታ ላይ ስለመቀበሩ የነገሯት አባት ስለመኖራቸው ተናግራለች።

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም መርጊያ አቡነ ጴጥሮስ ከህጻንነታቸው ጀምሮ ፆመኛና ፀሎተኛ እንደነበሩ እንዲሁም መንፈሳዊ ህይወት እንደሚታይባቸው፤ ዕድገታቸው በሀይማኖት ትምህርትና በመንፈሳዊ ህይወት የታጀበ እንደነበረ በመግለጽ ስለዕድገታቸው ያስረዳሉ። ከስጋዊው ይበልጥ መንፈሳዊው ህይወት ስለማረካቸው በፆም በጸሎት መወሰን ብቻ ሳይሆን፤ዓለም በቃኝ ብለው ምንኩስናን ተቀብለው በመምህርነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ በወቅቱ አልጋ ወራሽ በነበሩት በራስ ተፈሪ ተመርጠው ቅዱስ ቄርሎስ መጽሐፍን ወደ አማርኛ እንዲተረጉሙ ከተመረጡ አምስት ሊቃውንት መካከል አንዱ ሆነው መሥራታቸውን ይገልጻሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም አቡነ ጴጥሮስ ለጣልያን አገዛዝ ባለመሸነፍ በአደባበይ ሕዝብ በተሰበሰበበት በጥይት ተደብድበው መሞታቸው በመንፈሳዊው ዓለም ሠማዕት እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰው፤ በሠማዕትነታቸውም ፍቼ ከተማ ላይ በስማቸው የተሰየመ ካቴድራል መኖሩን እና በቅጥር ግቢው ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ያለውን የሚመስል ሀውልት በመታሰቢያነት የቆመላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በፍቼ ከተማ ላይ በከተማ አስተዳደሩ በሰላሌ ኦሮሞ ማዕከል ውስጥ በስማቸው የተሰየመ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳለም ይገልጻሉ።

የአቡነ ጴጥሮስ ተጋድሎ ከጥቅምና ከማዕረግ በላይ ኢትዮጵያን ማስቀደም እንደሚገባ እና አገርን ከጠላት ለመከላከል ሀይማኖትም ሆነ ብሔርን ወይም ሌላ ነገርን ማዕከል አድርጎ መነሳት እንደማያስፈልግ የሚያሳይ ነው በማለት ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም ያስረዳሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ፀጋዬ ዘለቀ የአቡነ ጴጥሮስ የሠማዕትነት ተግባር በወቅቱ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ መሞት ክብር እንደሆነ በማሳያነት የሚጠቅሱት መሆኑን እና የአርበኝነት ትግሉ እንዲፋፋም ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በወቅቱ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን የአሁኑም ሆነ የቀጣዩ ትውልድ የእሳቸውን ተግባር በማየት አገርን መውደድና ለአገር መቆም ምን እንደሚመስል ሊማርበት የሚያስችለው ነው ይላሉ።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም  

Recommended For You