ከረፈደ ጀምረው ቀድመው የደረሱት አባት

 የዛሬው የፈለግ አምድ እንግዳ ኡስታዝ ካሚል አሊዪ ይባላሉ፤ ትምህርት የጀመሩት ልጃቸውን ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ በሄዱበት ጊዜ ነበር። ዛሬ በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም በመሆን ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፤ የትምህርት ጊዜዬ አልፏል ሳይሉ መማር ጀምረው ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸውም ባሻገር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይና የልብ ጓደኛቸውን አባ ጥበቡንም ለዕውቀት አይረፍድም በማለት ትምህርት ቤት አስጀምረው፣ የትምህርት ቁሶችን እያሟሉ፣ ተከታትለው አስመርቀዋቸዋል። ከእኚህ፣ የሕይወት ጉዟቸው ለብዙዎች ትምህርት ከሚሆን አባት ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡-

ውልደትና እድገት

ኡስታዝ ካሚል አልዪ፣ ከአርሶ አደር አባታቸው ከአቶ አልዪ ቃሲምና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጀሚላ አብዱልቃድር በኦሮሚያ ክልል፣ በባሌ ጋሰራ ዞን በ1959ዓ.ም ነሐሴ ወር ተወለዱ። አባታቸው ለነጻነት ትግል ወደ ባሌ ጫካ ሲገቡ፣ እርሳቸውም በባሌ ዞን በምትገኘው፣ ድሬ ሼክ ሁሴን በምትባል ታሪካዊ ቦታ አደጉ። በሶስት ወንድሞችና አምስት እህቶች መካከል የተወለዱት ኡስታዝ ካሚል ለቤተሰባቸው አራተኛ ልጅ ናቸው። በልጅነታቸው ኳስ ጨዋታ ይወዱና ያዘወትሩ ነበር። ለቤተሰባቸውና ለአካባቢያቸው ሰው በታዛዥነትና ተግባቢ በመሆናቸው ይታወቃሉ። ለቀለም እውቀት የነበራቸው ፍላጎት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነበር።

ትምህርት

ከእኩዮቻቸው ጋር ትምህርት መጀመር ያልቻሉት ኡስታዝ ካሚል፣ ትዳር መሥርተው ሁለት ልጆች ካፈሩ በኋላ፣ በ1990ዎቹ፣ የመጀመሪያ ልጃቸው እድሜው ለትምህርት ደርሶ እርሱን ለማስመዝገብ በሄዱ ጊዜ ራሳቸውም ለመመዝገብና ከልጃቸው ጋር ትምህርት ለመጀመር ወሰኑ።

በወቅቱ፣ ልጃቸውን ለትምህርት አስመዝግበው፣ እኔንም መዝግቡኝ ያሏቸው የትምህርት ቤቱ አስተዳደሮች ለመማር መምጣታቸውን አላመኗቸውም ነበር፤ ይህንም፡ – “የመጀመሪያ ቀን ለመመዝገብ ትምህርት ቤት ስገባ ማንም አላመነኝም፣ እንዲያውም፣ መዝግበኝ ያልኩት መምህር “ኡስታዝ እባክዎ ጊዜ አያጥፉብኝ” ብሎኝ ነበር። እኔ ደግሞ፣ አንተ ዝም ብለህ መዝግበኝ እስክርቢቶው እምቢ ይበል አልኩት፣ ካልክ ብሎ ተመዝግቤ ወደ ክፍል ሄድኩ፣ ወደ መማሪያ ክፍል ስሄድ ደግሞ፣ አስተማሪው “ልጁን ይዘህ መጣህ ኡስታዝ” አለኝ፣ ልጄንም አመጣሁ፣ እኔም መጣሁ ስለው፣ ቀድሞም ትውውቅ ስለነበረን፣ አይይ አታሹፍ ባክህ፣ ጊዜም አታባክን በኋላ ካፌ ተገናኝተን ቡና እንጠጣለን አለኝ፣ አይይ ተው እስቲ ልግባ፣ አስገባኝ አልኩትና ወደ ክፍል የተመራሁበትን ወረቀቱን ሰጥቼው ገባሁ፤ በክፍል ውስጥ የነበሩ ልጆች ሲያዩኝ በኦሮምኛ “እንደምን አደሩ መምህር” በማለት ሠላምታ ሰጥተውኝ ነበር። እኔም መምህር አልነበርኩምና መልሱንም አላወኩም ዝም ብዬ ገብቼ መጨረሻ ወንበር ላይከተቀመጠ ረጅም ልጅ ጎን ተቀመጥኩ፣ በጊዜው ልጆቹ ሁሉ እኔን እኔን እያዩ ክፍለ ጊዜውን ሳይማሩ ነበር ያሳለፉት” በማለት ያስታውሳሉ።

ኡስታዝ ካሚል ቁጭ ብለው እንኳ በቁመት ከሚበልጧቸው ህጻናት ጋር ቁጭ ብሎ መማር፣ በስፖርት ክፍለ ጊዜ አብሮ መስራትና ረብሻቸውን መቋቋሙ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። ቢሆንም፣

 ከፍተኛ የሆነ የመማር ጉጉት ስለነበራቸውና ራሳቸውንም ስላሳመኑ ከትምህርታቸው ወደኋላ አላስቀራቸውም።

የአባትና የልጅ የትምህርት ቤት ቆይታ

ከልጃቸው ጋር አብረው ትምህርት ቤት ይገባሉ፤ አብረው ይወጣሉ። አንደኛ ደረጃን በቱሉዲምቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን በጎባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ፕሪፓራቶሪን ደግሞ ጎባ መሰናዶ ተምረዋል። ከልጃቸው ጋር ተፎካካሪ ተማሪዎችም ነበሩ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከበድ ብሏቸው የነበሩት ኡስታዝ፣ ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ ይበልጥ እየጣፈጣቸው መጣ። ትምህርት ቤት የቀሩበትን አንድም ቀን አያስታውሱም፣ ሰዓትም አያረፍዱም፣ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስርዓትንም በሚገባ ያከብራሉ።

የ10ኛ ክፍል ማትሪክን ከልጃቸው ጋር አብረው ወሰዱ፣ ከዚያም “እኔ ማኅበራዊ ሳይንስ ልግባ፣ አንተ ደግሞ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ግባ” በሚል ከልጃቸው ጋር መክረው፣ እርሳቸው ማኅበራዊ ሳይንስን መርጠው ገቡ። እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱም ደስታቸው ከፍ ያለ ሆነ። የመሰናዶ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፣ አስደሳች በሚሉት የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ቆይታ በሶስት አመት በማኔጅመንት፣ በዲግሪ ተመረቁ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ሞራልና ፍቅር ይሰጣቸው የነበረው የአካባቢው ህዝብና ዩኒቨርሲቲው በደማቅ ሁኔታ ነበር ያስመረቃቸው፣ ትጋትና አቅማቸውን የተመለከተው ዩኒቨርሲቲም የማስተርስ እድል ሰጣቸው፤ አብረው ትምህርት የጀመሩት ልጃቸው፣ የመረጠው የትምህርት መስክ የአምስት አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታን የሚጠይቅ ነበረና፣ በ2010ዓ.ም እርሱ ዲግሪውን ሲይዝ እርሳቸው ደግሞ፣ ማስተርሳቸውን ጨረሱ። በአሁኑ ሰዓትም በተማሩበት የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት እያስተማሩ ይገኛሉ።

ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ሕይወት

የአራት ወንዶችና፣ ሶስት ሴቶች ልጆች አባት የሆኑት ኡስታዝ ካሚል፣ ከባለቤታቸው ዘሐራ ሙሀመድ ጋር ከ30 ዓመታት በላይ በትዳር ኖረዋል፤ ኡስታዝ ካሚል ባለቤታቸውንም ትምህርት አስጀምረው የተወሰነ መንገድ ከሄዱ በኋላ ወደኋላ እንደቀሩባቸው ነግረውናል፤ ለዚህ ደረጃ የመብቃቴ ምክንያት ባለቤቴ ናት ያሉን ኡስታዝ ካሚል፣ ባለቤታቸው ምንም እንኳ እርሳቸው እንዳሰቡት በትምህርት ረጅም መንገድ ባይሄዱላቸውም ለእርሳቸውና ለልጆቻቸው የእውቀት መንገድ መቃናት የኢኮኖሚና በሞራል አቅም በመሆን፣ ለዚህ ደረጃ መብቃት መሰላል ሆነዋቸዋል። ኡስታዝ ካሚል፣ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት አላቸው። ልጆቻቸውም አባታቸውን የሚመለከቱት እንደ ወንድምና እንደ እኩያ ጓደኛቸው ነው።

ኡስታዝ ካሚል፣ በማኅበራዊ ሕይወትም የነቃ ተሳትፎ አላቸው። የቀለም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊትም ሆነ፣ በትምህርት ባሳለፉበት ጊዜ፣ አሁንም ባሉበት ደረጃ በጠንካራ የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፏቸው ይታወቃሉ። አስታራቂ፣ የመፍትሔ ሰው፣ መካሪም ናቸው። ወላጅ አብሮነታቸውን ላልፈቀደላቸው፣ ዓላማ ላላቸውና ለተፈቃቀዱ ጥንዶች “ከተዋደዱ ፍቀዱላቸው፤ ሰርተው ይለወጣሉ” በማለት ብዙዎችን ከቤተሰብ አሸማግለዋል፤ ድረዋልም።

በጓደኝነትም ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ ከሁሉ ጋር ወዳጅ፤ ከሁሉ ጋር ሠላም ናቸው። በተለይ ትምህርት ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም ማንም ሰው ሳይማር እንዳይቀር፤ ከጀመረም እንዲገፋበት አጥብቀው ይመክራሉ። እርሳቸው ያዩትን የቀለም እውቀት ብርሃን ሌሎችም እንዲያዩት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ፣ የልብ ወዳጃቸው ለሆኑት ለአባ ጥበቡ ቁምላቸው “ትምህርት መጀመር አለብዎት” የሚል ጥያቄ፤ “የማይጀምሩ ከሆነ ወዳጅነታችን ይቋረጣል” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር አቀረቡላቸው። አባ ጥበቡም፣ የወዳጅነታቸውን መልካም ምክር በዋዛ አላለፉትም ነበር።

ኡስታዝ ካሚልና አባ ጥበቡ

አባ ጥበቡ ትውልዳቸው ጎንደር ነው። ወደ ባሌ ጎባ መጥተው፣ በጎባ ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን ያገለግላሉ። ኡስታዝ ካሚል፣ ወዳጃቸው አባ ጥበቡን ትምህርት መማር አለብህ በሚል ምክር ብቻ አልተዋቸውም፣ ይልቁኑ፣ ቦርሳ፣ ደብተር፣ እስክርቢቶና ሌሎችም የትምህርት መርጃዎችን አሟልተው አስመዘገቧቸው። አስመዝግበው ብቻም አልቀሩም፣ በየጊዜው እየተከታተሉ፤ በትምህርም ሆነ በሚችሉት ሁሉ እያገዙ በደረጃ አራት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስመረቋቸው፤ ኡስታዝ ካሚል፣ አባ ጥበቡ ሲመረቁ፣ የጎባን፣ ሮቤ፣ ጋሰና እና አርጋርፋ ወረዳዎችን በማስተባበርና ጥሪ በማድረግ በደማቅ ሁኔታ ነበር ያስመረቋቸው። አባ ጥበቡ በአሁኑ ሰዓት በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማኔጅመንት ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

“ከጓደኝነት ውጪ ስለ ሃይማኖታችን ተነጋግረን አናውቅም፣ እኛ የምንተያየው እንደ ሰው ልጅ ነው፣ ዓላማችንም መለወጥ፤ መንገዳችንም መከባበርና መፈቃቀር ነው በማለት ኡስታዝ ካሚል፣ ከአባ ጥበቡ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ሰውነትን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

ከአባ ጥበቡ ጋር ያላቸውን ወዳጅነቱ የሚመለከቱ አንዳንድ ሙስሊም ጓደኞቻቸው፣ በዚህ በኩል የመስኪድ ኢማም ሆነህ በዛ በኩል ደግሞ ከእርሳቸው ጋር ወዳጅነት ገጥመሃል፤ ለምን ታበላሸናለህ ብለዋቸው እንደነበረና፣ አባ ጥበቡንም በአንድ ወቅት ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን አንተ ከመስኪድ ደመወዝ እየተቀበልክ ነው ብለው እንደከሰሷቸው ያልሸሸጉት ኡስታዝ፣ ሰው ፈጣሪውን በትክክል ካመነ፣ ትክክለኛ ሰውም ከሆነ አብሮ የሚኖር፣ አብሮ የሚበላ የሚፋቀር እንጂ መለያየትን መገፋፋትን የሚሰብክ መሆን የለብትም፣ የእምነት መጽሐፎችም የሚሉት ይህንኑ ነው ብለዋል።

አባ ጥበቡስ ምን ይላሉ?

የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑትና ኑሯቸውንና አገልግሎታቸውን በባሌ ጎባ ያደረጉት አባ ጥበቡ፣ ኡስታዝ ካሚልን “አባቴ፣ የሀገር አባት፣ የፍቅር አባት” በማለት ይጠሯቸዋል፤ አስተምረው ትልቅ ደረጃ ያደረሱኝ፣ አሁንም ተከታትለው ዲግሪዬን ያስጀመሩኝ አባቴ ናቸው፤ እኔና እርሳቸውን የሚለየን ሞት ብቻ ነው ይላሉ። ሼክ ኡስታዝ ካሚል ፍፁም ሀገር ወዳድ፣ ህዝብ አክባሪ፤ ለደሃ ደራሽ፣ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ህዝብ ሁሉ የሚወዳቸውና የሚያከብራቸው ትልቅ አባት መሆናቸውን አባ ጥበቡ ይመሰክራሉ።

በእኛ እቅድ ሳይሆን በፈጣሪ ፈቃድ ነው የተገናኘነው የሚሉት አባ ጥበቡ፣ ከኡስታዝ ካሚል ጋር ከሀገር ፍቅር ውጪ፤ ከትምህርት ውጪ አንድም ቀን የእኔ ሐይማኖት እንዲህ ነው የአንተ እንዲያ ነው፤ የእኔን ውሰድ ተባብለው እንደማያውቁ ነግረውናል።

አባ ጥበቡ እንዳጫወቱን፣ 12 አመታትን የተሻገረው ጓደኝነታቸው አንድም ቀን ንፋስ ገብቶት አያውቅም፣ አብሮነታቸውንና መተጋገዛቸውን የሚያውቁ ሁሉ በምሳሌነት ይጠቅሷቸዋል፤ ከሕይወት ልምዳቸው ያካፍሉ፣ ሠላምና ፍቅርን ይሰብኩ ዘንድም በየመድረኩ ይጋበዛሉ። ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ አለመግባባቶች በሚፈጠሩ ጊዜም ሼክ ኡስታዝ ካሚልና አባ ጥበቡን አታዩም እንዴ በማለት አለመግባባት እንዲረግብ ምክንያት ሆነዋል።

ገጠመኝ

ኡስታዝ ካሚል አባ ጥበቡ ተጫዋች ሰው እንደሆኑ ይናገራሉ፤ አንድ ቀን ኡስታዝ፣ አባ ጥበቡን ለማየትና የቸገራቸው ነገር ካለም ለማገዝ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ድረስ ሄደው አጠገባቸው ቁጭ ብለው ደብተራቸውን እያዩና እየተጫወቱ ሳሉ፣ አንዲትን ተማሪ እግሯን ረገጥ ያደርጋሉ፤ በዚህን ጊዜ የደነገጡት ኡስታዝ ፣ አረ አባ ጥበቡ ምንድነው የሠሩት ሲሏቸው “ታዲያ እንዲህ ካልረበሽኩ ተማሪ መሆኔ በምን ይታወቃል” ብለው እንዳሳቋቸው፣ በፈገግታ ያስታውሳሉ።

ትምህርታቸው ላይ ቀልድ የማያውቁትና ወጥረው የሚሠሩት ኡስታዝ ካሚል፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በአንድ የፈተና ሰሞን የገጠማቸውንም እንዲህ ሲሉ “እኔ ካፌ ሰቃይ ነበርኩ፤ ይህን የማደርገው ጊዜ ለመሻማት ነው፤ ፈተና የደረሰ ሰሞን፣ አንድ ቀን፣ ፈጥኜ ካፌ ገብቼ ከበላሁና ከጠጣሁ በኋላ፣ የበላሁበትን ሰሃንና ስኒ እዛው ካፌ በተዘጋጀ አስቀምጬ መውጣት ሲገባኝ፣ በእጄ እንደያዝኩ ዶርም ድረስ ሄጄ አውቃለሁ፣ በወቅቱ ከነሰሀኔ ዶርም የተመለከቱኝ ልጆች “ሼኪ ሼኪ ምነው” ያሉኝን አልረሳውም” በማለት አጫውተውናል።

የፓርላማው ጉዞና ቆይታ

ኡስታዝ ካሚል ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ሲጀምሩ ሚኒስትር እሆናለሁ ብለው ነበር፤ ከድሮም “ለሀገሬና ለህዝቤ የበኩሌን ድርሻ ማበርከት አለብኝ” የሚል አቋም ነበራቸውና ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲወዳደሩ ጥያቄ ሲቀርብላቸው በቀረችኝ እድሜ ለሀገሬ አስተዋጽዖ ማበርከት አለብኝ በሚል ጥያቄውን በይሁንታ ተቀብለው ተወዳደሩ፤ ከፍተኛ ማኅበራዊ ተቀባይነት ነበራቸውና የመደወላቡ ህዝብ ደምፁን አልነፈጋቸውም።

ህዝብ ድምፁን የሰጠን መድኃኒት እንድንሆንለት ነው የሚሉት ኡስታዝ ካሚል፤ የተወካዮች ምክር ቤት ከገቡ አምስት ወራትን አስቆጥረዋል። ቆይታቸውንም በጣም ደስ የሚል በማለት ይገልፁታል። ወደ ምክር ቤቱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለፅ አንችል ይሆን የሚል ስጋት እንደነበራቸውም አልሸሸጉም። ነገር ግን የፈራሁት ሳይሆን፣ የትኛውም የምክር ቤቱ አባል ለኢትዮጵያ ይበጃል ብሎ ያሰበውን በነጻነት የሚገልጽበት ሆኖ አግኝቼዋለው ብለውናል።

ምክር

ተከባብሮና ተፋቅሮ፤ አንድነትን ጠብቆ በመኖርና ለትምህርት አልረፈደም ብሎ በመነሳት ከግብ በመድረስ ምሳሌ ለሆኑት ኡስታዝ ካሚል፣ ለወጣቱ ትውልድ ምን ይመክራሉ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ “ምክር የሚያሻው ወጣቱ ብቻ አይደለም” በማለት፣ ለአዛውንቱም፣ መምህሩም፣ ተማሪውም፣ ነጋዴውም፣ የእምነት አባቶችም፣ የእምነት ተከታዮችም ለሙስሊሙም ክርስቲያኑም ይህቺ ሀገር እንኳን ለኛ፣ ሌላውም ቢመጣ ለሁላችን የምትበቃ ናትና መገፋፋቱን ትተን ተዋደን እንኑር፤ ቁርዓንም ሆነ መፅሐፍ ቅዱስ የሚያስምሩት ፍቅርንና ህብረትን ነው ብለዋል።

በዚህ ዘመን፣ ሙስሊምም ይህቺ ምድር ለእርሱ ብቻ እንደተፈጠረች አድርጎ፣ ክርስቲያኑም የራሱ ብቻ አድርጎ በማሰብ፣ አጠገቤ ማንም አይኑር የሚል ጫፍ የያዘ አመለካከት መኖሩን ጠቅሰው፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የምንኖርባት ይህች ሀገር፣ ሌላም የእኛኑ ያህል ብትጨምር እንኳ ትበቃናለች፤ ለልጆቻችን ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መከባበርን እንጂ ጥፋትንና መገፋፋትን አውርሰን አንሂድ ይላሉ። አያይዘውም፣ የትኛውም እምነት ጥላቻን አይሰብክም፤ ትክክለኛ አማኝ ከሰው ጋር አብሮ መኖር የሚችል ነው፤ የድሮ እናቶችና አባቶች እንዴት አብረው ኖሩ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፤ ሰው ስለመለያየትና መገፋፋት እንዲያስብ የሚያደርገው ሌላ የሚያስበው ነገር ሳይኖረው ሲቀር ነው፣ ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ መማርና መሥራት ነው በማለት ይናገራሉ።

“መማር ይለውጣል ከድንቁርና ያወጣል” ያሉት ኡስታዝ ካሚል፣ እርሳቸው ትምህርት ሲጀምሩ ዓላማቸው የነበረው ለማወቅና ለመቀየር እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ ግን ራሴን ከመቻልም አልፌ፣ ቤተሰቤን እንዳስተዳድር፣ ልጆቼን እንዳስተምር፣ ለሀገሬ የድርሻዬን እንዳበረክት አድርጎኛል ይላሉ፤ በቀጣይም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የመጀመር እቅድም የያዙት ኡስታዝ ካሚል ሰው የሆነ ፍጥረት ሁሉ መማር አለበት፤ የመማር ቀዳሚ ዓላማ አስተሳሰብን መለወጥ እንጂ ገንዘብ ማግኘት መሆን የለበትም ብለው ይመክራሉ።

“እኔ ፈተና አለ በተባለ ጊዜ፣ ፀሐይን እንኳ ለማየት ከክፍሌ አልወጣም” ያሉን ኡስታዝ ካሚል፣ መማር ማለት ዩኒፎርም ለብሶ ትምህርት ቤት መመላለስ አይደለም በማለት ከዘንድሮ ተማሪ የታዘቡትን “ተማሪ ሆኜ አውቃለሁ፤ አሁን ደግሞ እያስተማርኩ ነው፣ የአሁን ተማሪዎች እንደ ድሮ አይደሉም፣ ዩኒፎርማቸው ሳይቀደድ ገና በአዲስነቱ የሚቀዱ አሉ በማለት ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የተማሪ ውበቱ በደብተር አያያዙ፣ በአለባበሱ፤ በሰዓት አክባሪነቱ፣ ለዓላማ በመኖሩ የሚታይ ነው ያሉት ኡስታዝ ካሚል፣ ተማሪ የመጀመሪያ አያያዙ ካላማረ፤ የመማርን ጥቅምም ሳይረዳ እንዲሁ ለይስሙላ ትምህርት ቤት ስለተመላለሰ ብቻ ራሱን መቀየር አይችልም፤ ስለዚህ በዚህ ዘመን ያሉ ተማሪዎች ለመለወጥና ያሰቡበት ለመድረስ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በሚገባ ሊጠቀሙበት ይገባል በማለት መክረዋል።

በተለይ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ትዳር የሚሮጡ ታዳጊ ሴቶች ለትምህርታችሁ ቅድሚያ ስጡ፣ ትዳርም ልጅም ከትምህርት በኋላ ይደረስበታል፤ ቤተሰባችሁን የምታስተዳድሩበትን እውቀት ይዛችሁ ቤተሰብ መስርቱ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

እርሳቸው እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያውያን የሥራ ባህላችን መታረም ያለበት ነው። ወጣቱ አጠገቡ ያለውን እድል ትቶ ንብረቱን ሸጦ፣ ወይ የቤተሰቡን ንብረት አሽጦ፣ ወይ ተበድሮ፣ በአጠቃላይ ብዙ ዋጋ ከፍሎ ይሰደዳል፤ መድረስ የቻለው እዚህ የናቀውን ስራ፣ በሰው ሀገር ይሰራል፣ መድረስ ያልቻለው ደግሞ፣ ከንብረትና ከገንዘብ ኪሳራ በላይ የሕይወት መስዋዕትነትን ይከፍላል ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት፣ ለሥራ ያለን አመለከካት፤ ለሀገራችን የሰጠናት ዋጋ ጤናማ አለመሆኑ ነው። “ሀገራችን ገና ብዙ ያልሰራንባት ያልተነካች መሆኗን ተረድተን፣ መሥረቅ እንጂ መሥራት አያሳፍርም ብለን ከትንሽ እንነሳ፣ ብንማርና ስንፍናችንን ገፍፈን ወደ ሥራ ብንሰማራ ለመገፋፋትና ለመናቆር የሚሆን ጊዜም አይኖረንም” የሚለው የመጨረሻ ምክራቸው ነው።

የሕይወት መርሕ

ኡስታዝ ካሚል፣ በትምህርት ያሳለፉትን ጊዜ፣ የአንድ ሳምንት እንኳ መስሎ አይታየኝም በማለት ይገልጹታል፤ እንዲህ እንዲሰማኝ ያደረገኝ፣ ግብ አስቀምጬ፣ በዓላማና በፅናት በመማሬ ነው ይላሉ፤ ይህንን መነሻ አድርገው “የሰው ልጅ ምንጊዜም፣ መስራት እችላለሁ ብሎ ራሱን ካሳመነ፣ ሊሰራ ካሰበው፤ ሊደርስበው ካለመው ወደኋላ ሊጎትተው የሚችል ኃይል የለም” የሚለው የሕይወት መርሃቸው እንደሆነ ነግረውናል።

Recommended For You