“ጊዮን አባ ለጋስ”

ኢትዮጵያ ከሚገኙት ወንዞች ሁሉ ትልቁ ዓባይ ነው። ይህ ወንዝ የባህላዊ እና ታሪካዊ ይዘቶች ባለቤት ሲሆን፣ ከሃይማኖት አንፃር ዓባይ ከገነት ከሚፈልቁ አራት ቅዱሳን ወንዞች አንዱ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አንፃር ስያሜውም “ጊዮን” (the Ghion) ሲሆን፣ ሌሎቹ ፒሾን (the Pishon)፣ ቲገሪሰ (the Tigris)፣ እና ኤፍራቲስ (the Euphrates) ናቸው። ስለሆነም ዓባይ የጠበልነት ባህርይ እንዳለው እና በሽታ/ ተውሳክ እንደሚፈውስ ስለሚታመን፣ ከብዙ አካባቢዎች ወደዚህ ቦታ እየመጡ በምንጩ ውሃ ይጠመቃሉ።

የዓባይ መነሻ የጣና ሃይቅ ሳይሆን፣ የጮቄ ተራራ ሰንሰለት አካል ከሆነው ከደንገዛ ተራራ ሥር፣ ከባህር ወለል በላይ 2750 ሜትር ላይ ነው የሚገኘው፣ ስያሜውም “ግሽ ዓባይ” ምንጭ ነው። ምንጩ ፈለገ ጊዮን በመባል ሲታወቅ፣ ነጠላ ምንጭ ሳይሆን በሃያ ሜትር ርቀት የሚገኙ ሦስት ምንጮችን ያካተተ ነው። ከምንጩ አጠገብ፣ አንድ መቶ ሜትር ርቀት ገደማ የአቡነ ዘራብሩክ ገዳም ይገኛል። ገዳሙም ለዘመናት በአካባቢው በጣም ከታወቁ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነበር። ቅድስናውን የሚያዳብረው፣ ቅድስት ማርያም በስደት ጉዞ ልጇን ክርስቶስን ይዛ በጣና ውስጥ ከምትገኝ አንዲት ደሴት ውስጥ አርፋ አንደነበረ በአፈ ታሪክ መወሳቱ ነው። ዓባይ “ግሽ ዓባይ” ምንጭ ፈልቆ፣ ግልገል ዓባይ ተብሎ፣ ጣናን ይቀላቀላል። ከጣና የሚወጣው ወንዝ ዓባይ በመባል ይታወቃል።

የዓባይ ሸለቆ ቆላ፣ በዘልማድ በርሃ ይባላል፣ አካባቢውም የጀግኖች መዋያ፣ ማደሪያ እንደሆነ የሚያመለክቱ ስንኞች አሉ፣ ምሳሌዎች እነሆ።

ቀረርቶ፡

ቢገድልም ገደለ፣ ባይገድለም ገደለ፤

ዓባይ ከበረኻው ብቻውን ከዋለ።

ዓባይ የዘፈን ስንኞችም መንስዔ

ነው፤ ምሳሌ-

አሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፣

የሥጋ ወጥማ ከወዴት አባቴ።

ዓባይም ሞላልሽ፣ ሞላልሽ፤

ያሰብሽው ሆኖልሽ።

በዓለም ላይ ያለው ውሃ መጠን፣ ባህርይ እና ለሰው ልጆች የሚያበረክተው ጥቅም

ከዓባይ ውሃ ላይ የተመሠረቱ ጥቅማ ጥቅሞች ለሰው ልጆች ይበረከታሉ። ጥቅማ ጥቅሞቹም ከውሃ ባህርይ ጋር ቁርኝት ስላላቸው፣ የውሃን ባህርዮች በመጠኑም ቢሆን መገንዘብ ይበጃል። እንዲሁም የዓባይን ውሃ ፖለቲካ ከመዳሰሳችን በፊት፣ ስለውሃ ተፈጥሯዊ ይዘት ማውሳቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ። በውሃ መንስዔ የሚከሰቱ ውዝግቦች በውሃ መጠን ክፍፍል መንስዔ ስለሆነ፣ የሰው ልጅ ቀጥታውን ሊጠቀምበት የሚችለውን፣ በዓለም ላይ ያለውን የውሃ መጠን መገንዘብ ያሻል ብየ ስለማምን፣ ስለ ውሃ መጠንም በጥቂቱ አወሳለሁ።

በመጀመሪያ ውሃ (የኦክስጅን እና የሃይድሮጅን ኬሚካዊ ውሑድ) ብቻ ነው። በምድራችን በአንድ ጊዜ ሦስቱንም የቁስ ባህርያት ተጎናፅፎ፣ ማለት “በጋዝ” (እንፋሎት)”በፈሳሽ” (ውሃ) እና “በጠጣር” (በረዶ) ይዘት በምድራችን ላይ የሚገኘው (ሌሎች ቁሶች በምድር ላይ በእንድ አካባቢ የፈሳሽነትም፣ የጠጣርነትም ባህርይን አይጎናፀፍም)።

የሰው ልጅ ቀጥታውን የሚጠቀምበት የውሃ መጠን በጣም ውስን ነው። በዓለማችን ያለው ውሃ፣ ዘጠና ሰባት በመቶ (97%) በላይ ቀጥታውን ልንጠቀምበት የማንችል ጨዋማ ሲሆን፣ ቀጥታውን ለሰው ልጅ ፍጆታ ሊውል የሚችለው የተቀረው በመቶ ሦስት (3%) እጁ ብቻ፣ “ጨው-አልባ” ውሃ ነው ። ይህም “ጨው- አልባ” ውሃ በፈሳሽ መልክ (0.75%) እና ቀሪው (1.75-2%) በጠጣር በረዶ ይዘት፣ በመሬት ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ዋልታዎች አካባቢ (አርክቲክ እና አንታርክቲክ አካባቢዎች) የሚገኝ ሲሆን፣ የሰው ልጅ በነዚህ በረዶ ክምሮችም ቀጥታውን አይጠቀምባቸውም። በአፈር ውስጥ እና በከርሰ ምድር ያለው ውሃ በጣም ውስን ነው (0.01%)። ስለሆነም በአጠቃላይ ስንመለከት፣ ለአገልግሎት ቀጥታውን ልንጠቀምበት የምንችል “ጨው- አልባ” ውሃ፣ በጠቅላላ በምድራችን ከሚገኘው ጋር ሲነፃፀር በጣም ውስን ነው። በዓለማችን ከሚገኘው ውሃ 97% ጨዋማ ውሃ ሲሆን 3% ጨው አልባ ውሃ ነው። ከዚህ ሦስት በመቶ (3%) ጨው አልባ ውሃ 69%በጠጣር በረዶ ይዘት በመሬት ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ዋልታዎች አካባቢ (አርክቲክ እና አንታርክቲክ አካባቢዎች) የሚገኝ ሲሆን የቀረው 30% ከመሬት በታች (በከርሰ ምድር) በወንዞች፣ በሃይቆች እና በረግረጋማ ቦታዎች የሚገኝ ውሃ አንድ በመቶ (1%) ብቻ ነው።

በምድራችን በሃይቅ እና በረግረግ መልክ ተንጣሎ፣ ወይም በወንዝ መልክ ሲፈስ ከሚታየው “ጨው-አልባ” ውሃ፣ በዛ ያለው በሃይቅ መልክ (87%) የሚገኝ ነው። የሃይቆችም ውሃ፣ ሃያ ዘጠኝ በመቶ (29%) በአፍሪካ ሃይቆች (ቪክቶሪያ፣ ማላዊ፣ ታንጋኒካ. ወዘተ) ሲገኝ፣ በሩስያ የሚገኘው “የባይካል” ሃይቅ ብቻውን ሃያ አንድ በመቶ (21%) የምድራችንን ጨው አልባ ይዟል፤ ቀሪው “ጨው-አልባ” (14 %) በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ሃይቆች ድርሻ ሲሆን፣ በጣም ጥቂቱ (1%) ሌሎች አካባቢዎች የሚገኝ ነው።

ከላይ እንደተወሳው በዓለማችን ውስጥ ያለው በቀጥታ ልንጠቀምበት የምንችል ውሃ በጣም ውስን ነው። በተጨማሪ የሕዝብ ቁጥር በጨመረ መጠን የውሃ ፍላጎትም አብሮ ይንራል፣ ነገር ግን በዓለማችን ያለው ውሃ ውስን ስለሆነ፣ ስለማይጨመር፣ ከፍተኛ “የጨው-አልባ” ውሃ እጦት ይከሰታል። መፍትሄ ካልተበጀለት፣ ችግሩም ወደፊት በጣም እየባሰ እንደሚሄድ ይገመታል።

እንዲሁም በዓለማችን ላይ ያንዣበበው የአየር ቅጥ ለውጥ ከውሃ አንፃር ሲፈተሽ፣ ሦስት ችግሮችን ያስከትላል፣ ችግሮቹም የውሃ ጥራት (Water quality) መጓደል፣ የውሃ እጥረት (water availability) ፣ የዝናብ ነባር ወቅቶች መቀያየር ናቸው። የዝናብ ወቅት መቀያር የሚገለጠው፣ በኃይል በመዝነብ እና ጎርፍ በማስከተል፣ ወይም በውሃ እጥረት መንስዔ ድርቅ መከሰት ነው።

ከዚህ አንፃር በተደጋጋሚ ድርቅ፤ ወይም መጠነ ብዙ ዝናብ (ወይ ከባድ ዝናብ፣ ወይ ዝናብ አልባ ክረምት ተከስተው) የተቸገረ፣ አንድ የመንዝ ገበሬ አለ የተባለውን ማውሳቱ ይበጃል። ገበሬው አምላኩን አማርሮ፣

ወይ ዝናብ፣ ወይ ዝናብ፣

ወይ ጠሃይ፣ ወይ ጠሃይ፣

ሁሉም የልህ የልህ፤

ትዘራው እንደሆን ቅብቃቡ

(ማሳ) ያውልህ።

ብሎ ቡና ለቀማ ወደ ጅማ

ተሰደደ ይባላል።

ውሃን ከሕያው ጋር አዛምደን ከሌላ አንፃር ስንፈትሽ፣ ውሃ ለሕያው ሕልውና አረጋጋጭ የሆነ አንድ ልዩ ባህርይ አለው፤ ያም የውሃ “ሞሎኪዩሎች” የመሳብም ሆነ የመገፍተር እቅም መኖር፣ እንዲሁም ቢኖሩም ኃይላቸው ውስን መሆኑ ነው። የመገፍተሩ ወይም የመሳቡ አቅም ውስን በጣም ቢሆንም፣ ውሃ ባህርዩ ከሌሎች ኬሚካላዊ ውሑዶችን ቀላል ትስስር መሥርቶ፣ በሚፈለግበት ጊዜ ቀለል ባለ ሁኔታ ከኬሚካላዊ ውሑዶች መላቀቅ ይችላል።

ይህም ባህርይ በሳይንስ ሕግ የሚገዛ ነው። ውሃ በአንድ አቅጣጫ አዎንታዊ ሙል (+)፣ በሌላ በኩል አሉታዊ ሙል (-) ስላለው፣ በመጀመሪያው ባህርይ፣ ከአሉታዊ ሙል (-) ጋር ለመሳሳብ ብሎም ለመጣበቅ፣ እንዲሁም በሁለተኛው ባህርይ፣ አዎንታዊ ሙል (+) ካላቸው ጋር ለመሳሳብ፣ ብሎም ለመጣበቅ ይችላል። ስለዚህ ውሃ በሕያው አካላት ውስጥ ካሉ “ሞሎኪዩሎች” ጋር እየተሳሰረ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል፤ የምግብን “ሞሎኪዩሎች” ከሚፈለግበት ቦታ ያደርሳል፤ እንዲሁም የቆሻሻን “ሞሎኪዩሎች” ለማስወገድ ይችላል። በዚህም ባህርይው መንስዔ ውሃ ብዙ ኬሚካሎችን ለማሟሟት በመቻሉ፣ «ሁለገብ አሟሚ» (universal solvent) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

እንዲሁም ሌላው የውሃ ልዩ ባህርይ ወደ ጠጣርነት ሲቀየር (ወደ በረዶነት ሲቀየር) “ዴንሲቲው” (Density) መቀነሱ ሲሆን፣ በዚህም መንስዔ ወደ ታች በመዝቀጥ ፈንታ ወደ ላይ (ውሃው ላይ) ይንሳፈፋል። ስለሆነም፣ ወደ በረዶነት ያልተቀየረ ውሃ ከስር ስለሚኖር፣ በውሃ ውስጥ ያሉ ሕያው በቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወት አልባ እንዳይሆኑ ይታደጋል። በአንፃሩ ሌሎች ፈሳሾች ወደ ጠጣርነት ሲቀየሩ “ዴንሲቲዎቻቸው” ይጨምራሉ (ከፍ ይ ላሉ)።

ሕያው ካለ ውሃ ይኖራሉ ተብሎ አይታሰብም፣ አይታለምም። በጠፈር ምርምር አንዱ ዓቢይ ተግባር፣ ውሃ በጠፈር መኖር አለመኖሩን መረዳት ነው። ውሃ ካለ እንደ ሕይወት መኖር አመልካች ሆኖ ስለሚወሰድ፣ ሕያውም ሊኖሩ ይችላሉ ከሚል እሳቤ ላይ ይደረሳል። በአማካኝ የሕያው ገላ ክብደት ሰባ አምስት በመቶው (75%) የውሃ ድርሻ ነው።

የሕያውን ሕልውና ከማረጋገጥ በዘለለ፣ ውሃ ለሰው ልጆች ሌሎች በርከት ያሉ አገልግሎቶችን ያበረክታል። የጨው አልባ ውሃ ዋና ጥቅሞች ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ማገልገ ላቸው ሲሆን፣ ውሃ በአጠቃላይ (ጨዋማ ውሃንም ያካትታል)፣ ለትራንስፖርት፣ ለኃይል ማመንጫነት፣ እንዲሁም የመዝናኛ መድረክ በመሆን ናቸው።

በውሃ የተለያዩ አገልግሎቶች መንስዔ በጣም ብዙ የዓለም ታላላቅ ከተማዎች የተመሠረቱት ወንዞች ዳር ነው። ወንዞቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ የውሃ ፍጆታ በተጨማሪ፣ በውሃ ላይ ትራንስፖርት አመች ስለሚሆኑ ነው ተብሎ ይታመናል። ከሃምሳ በላይ ወንዝ ዳር ላይ ከተመሠረቱት ታላላቅ ከተማዎች፣ በጣም የታወቁትን ጥቂቶቹን “ቶክዮ”፣ “ሻንጋሃይ”፣ “ባንኮክ”፣ “ባግዳድ”፣ “ካቡል”፣ “አንክራ”፣ “ካርቱም”፣ “ካይሮ”፣ “ሞስኮ”፣ “ፕራግ”፣ “ቪያና”፣ “ቡዳፔስት”፣ “በርሊን”፣ “ሊዝቦን”፣ “ፓሪስ”፣ “ሮም”፣ “ደብሊን”፣ “ሮተርዳም”፣ “አምስተረዳም”፣ “ኦትዋ”፣ “ለንደን”፣ “ዋሽንግቶን ዲሲ”፣ እና “ኒው ዮርክ” ብሎ መጥቀስ ይቻላል።

ዓባይ እና ገባሮቹ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የውሃ ማማ በመባል ትታወቃለች፣ ይህም ያለምክንያት አይደለም። ከአፍሪካ ክፍለ ዓለም ከሁለት ሺ ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያለው አካባቢ ሰባ በመቶ (70%) ኢትዮጵያ ነው የሚገኘው። በተጨማሪ ከሦስት ሺ ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያሉ ብዙ አካባቢዎችም አሉ። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያን ተራራማ አካባቢዎች ዓመታዊ የዝናብ መጠን ክፍተኛ ያደርገዋል። ዝናቡ በከፊል ወደ ከርሰምድር ሰርጎ ገብቶ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መጠንን ያጎለብታል፣ ብሎም የወንዞች ፍሰት መጠንም እንዲሁ አብሮ ይጎለብታል። ስለሆነም ነው ኢትዮጵያ የውሃ ማማ በመባል የምትታወቀው። ይህ ሁኔታ ግን ለአገር ልማት ያበረከተው አስተዋፅዖ በጣም ውስን ነው።

የኢትዮጵያ ምድር ገጽታ ወደ ምዕራብ ያጋደለ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ወንዞች አብዛኞቹ የሚፈሱት ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ነው፣ ዓባይም ከነሱ አንዱ ነው። የዓባይ ዋና ዋና ገባሮች ከመቅደላ አጠገብ (ወሎ) የሚነሳው “በሽሎ”፣ ከአንኮበር (ሸዋ) የሚነሳው “ጀማ”፣ አዲስ አበባ አጠገብ የሚነሳው “ሙገር”፣ ከከፋ የሚነሳው እና በውሃ መጠን ከገባሮች ሁሉ የሚልቀው “ዲዴሳ”፣ ከወለጋ የሚነሳው “ዳቡስ”፣ ከምዕራብ ጎጃም የሚነሳው “በለስ” ናቸው። ምንም በነጠላ ሲታዩ ትናንሽ ወንዞች ቢሆኑም፣ ከጮቄ ተራራ ሰንሰለት (መኻል ጎጃም) የሚነሱና ተደምረው ለዓባይ ብዙ እስተዋፅዖ የሚያደርጉ ብዙ ወንዞች አሉ። እነሱም “ሃናዳሳ”፣ “ጠል”፣ “ዓባያ”፣ “ሰዴ”፣ “ተሜ”፣ “ጭዬ”፣ “ጠዛ”፣ “ሱሃ”፣ “ሙጋ”፣ “በጨት”፣ “ጨሞጋ”፣ “ተምጫ”፣ “ጉላ”፣ “ብር”፣ “ላህ”፣ ወዘተ ናቸው። ከጮቄ ተራራ ሰንሰለት የሚፈልቁ ወንዞች የተዘገበበት ዋና ምክንያት ወደ ኋላ ስለ ዓባይ ተፋሰስ ማገገም በምናወሳበት ጊዜ፣ የጮቄ ተራራ ሰንሰለት እንዲያገግም የተወሰዱ ተግባራት ስለሚወሱ ነው። ለዓባይ በእጅ አዙር የሚገብሩም (ወደ ጣና የሚገቡ) ብዙ ወንዞች አሉ፣ ዋናዋናዎቹ “ግልገል ዓባይ” (ጎጃም) እና ከቤጌምድር የሚነሱት “መገጭ”፣ “ጉመራ”፣ እና “ርብ” ናቸው።

ምንም በሰሜን አካባቢ ያለው የዓባይ ሸለቆ ተፋሰስ የተራቆተ (እልባስ አልባ) ቢሆንም፣ በሰሜን ወለጋ እና በደቡብ ጎጃም በኩል ያለው አሁንም በከፊል በዕፅዋት የተሸፈነ እና ብዙ የዱር እንስሳት የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ይህም ለዱር እንስሳት ጥበቃ ሊውል የሚችል፣ በከፊል አደን እንዲሁም ለገበያ የሚቀርቡ የዱር እንስሳት ርቢ ተግባር ሊውል የሚችል አካባቢ ነው። የዓባይ ፏፏቴ አሁንም የቱሪስት መስህብ ሆኖ እያገለገለ ነው። “ግሽ ዓባይም” (የዓባይ ምንጭ) አካባቢ በቅርብ ከሚገኘው የፋሲል ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ እና “ከጉደራ ሃይቅ” ጋር ተደምሮ፣ የአካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እየሆነ ነው።

ዓባይ ወንዝ ውስጥ ብዙ እንስሳት ይኖራሉ፣ ጥቂቶቹ ትላልቆች ናቸው፣ ለምሳሌ ከአጥቢዎች ጉማሬ፣ ከገበሎ አስተኔዎች አዞ፣ አርጃኖ እባብ እንዲሁም በተጨማሪ ብዙ የአሳ ዝርያዎችን ያካትታል። በዓባይ ተፋሰስ ከአርባ በላይ የአሳ ዝርያዎች ይገኛሉ፣ ከነሱም እብዛኞቹ ዝርያ መጠነ ግዙፍ እና ቢመረቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የፕሮቲን የምግብ ግብዓት አለኝታ ሊሆኑ ይችላሉ፣ አንዱም “የናይል ፐርች” (Nile Perch/ Lates nilolticus) ነው።

ዓባይ “ከነጭ ናይል” (White Nile/ እኛ “ነጭ ዓባይ” ብለን ከሰየምነው) ጋር ካርቱም ከተማ ላይ ከመቀላቀሉ በፊት፣ ከጣና ተነስቶ አንድ ሺ እምስት መቶ ኪሎሜትር ይጓዛል። አብዛኛው ጉዞ በጠባብ ጥልቅ ሸለቆዎች ውስጥ ነው የሚከናወነው። ዓባይ የኢትዮጵያን ምድር ለቆ ከመውጣቱ በፊት ካለው ሰፊ የዓባይ ተፋሰስ እስከ 1.0 (አንድ) ሚሊዮን ሄክታር (master plan study) ሊለማ የሚችል መሬት እንዳላት ይገመታል። ከዚህም ውስጥ ከመቶ አንድ እጁ ብቻ (1%) እንደለማ ይገመታል፣ ዘጠና ዘጠኝ በመቶው (99%) ገና ልማት የሚጠባበቅ መሬት ነው ማለት ነው።

ከኢትዮጵያ ወደ “ናይል” የሚፈሱ ወንዞች

እስከ ሃያኛው ምዕተ ዓመት ድረስ “ናይል” ከብሩንዲ ተራራዎች፣ ከምድር ወገብ ከሚገኙ ሃይቆች፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ማለት ከብዙ ገባሮች የተጠራቀመ መሆኑ አይታወቅም ነበር። ጉዳዩ ሲደረስበት ግን፣ “ናይል” ከኢትዮጵያ ብዙ ውሃ እንደሚበረከትለት ታወቀ።

ከዓባይ ለግብፅ የሚደርሰው ውሃ ግብፅ ከምታገኘው ሃምሳ ስድስት በመቶ (56%) ብቻ ነው። ሆኖም ከሌሎች ከኢትዮጵያ ተራራዎች የሚነሱ ወንዞች ከተከዜ ባሮ አኮቦ ዲንዲርና ራሃድ ከአትበራ ከምታገኘው ጋር ተደምሮ፣ ግብፅ ከኢትዮጵያ የምታገኘው አስዋን ላይ ሲለካ በአማካይ ሰማኒያ ስድስት በመቶ (86%) የውሃ መጠን ነው። በተጨማሪ ከምታገኘው ደለል ሁሉ፣ ዘጠና ስድስት በመቶውን (96%) ከኢትዮጵያ ነው የምታገኘው።

ዓባይ ስናር በርሃ (ሱዳን) ሲደርስ አዲስ ስም ተጎናጽፎ፣ “ጥቁር ናይል” (Blue Nile/ Bahr-el-Azark) ተብሎ ካርቱም ሲደርስ “ከነጭ ናይል” (White Nile/ Bahr-al-Abyad) ተቀላቅሎ፣የሁለቱ ወንዞች ውሃ ተደምሮ፣ “ናይል” (Nile) ተብሎ ፍሰቱ ወደ ግብፅ ይቀጥላል። “ ነጭ ናይል” (White Nile) ከደቡብ እቅጣጫ ተነስቶ ሱዳን ሲገባ፣ ሱዳን ውስጥ “ባህር አል ጀባል” (Bahr al Jabal/ “Mountain River”) በመባል ነው የሚታወቀው። ከጋምቤላ ተነስተው “ከነጭ ናይል” የሚቀላቀሉ፣ ሁለት ታላላቅ ወንዞች አሉ፣ እነሱም ፒዮር (አኮቦ እና ጊሎ ከተቀላቁ በኋላ) እና ባሮ ናቸው። ወንዞቹ (ፒዮር እና ባሮ) ሱዳን ከገቡ በኋላ፣ የሁለቱ ድምር “ሶባት” (Sobat) ተብሎ፣ “ከነጭ ናይል” ጋር “ማላካል” (Malakal) ላይ ይቀላቀላል። ያም ቦታ “ነጭ ናይል” ካርቱም ላይ “ከጥቁር ናይል” ጋር ከሚቀላቀልበት ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ወደ ደቡብ አቅጣጫ ነው የሚገኝ። ከዚያም “አትበራ” (ሌላው ስሙ ቀይ ናይል/ Red Nile ነው)፣ “ናይልን” (Nile) ሱዳን ውስጥ ይቀላቀላል።

በሱዳን እና በግብፅ የተገነቡ ግድቦች

ሱዳን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት እና ለተለያዩ ተግባራት፣ ማለት ለጎርፍ መከላከል፣ ለመስኖ፣ እንዲሁም ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት፣ ጣምራም ሆነ ነጠላ አገልግሎት ለማበርከት፣ የተገደቡ ስድስት ግድቦች አሉ። እነሱም “ነጭ ናይል” (White Nile) ላይ “ጀበል አውልያ” ግድብ (Jebel Aulia Dam)፣ “አትበራ” ላይ “ካሽም ኤል ጊርባ” ግድብ (Khashm el-Girba Dam)፣ “ናይል” (Nile) ላይ “መረዌ” ግድብ (Merowe Dam)፣ “በጥቁር ናይል” (Blue Nile/ ዓባይ) ላይ “ሮሲየርስ እና ሰናር” ግድቦች (Roseires and Sennar dams)፣ እና ሰሜን “አትበራ” እና “ሰቲት” አካባቢ “ጥምረት ግድቦች” (Upper Atbara, Setit Dam Complex ) ናቸው። ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅማ ጥቅሞች በተጨማሪ፣ ግድቦቹ ለአሳ እርባታም ለትራንስፖርት አገልግሎት ይውላሉ።

ሱዳን የምትጠቀምበት ውሃ፣ በጠቅላላ ማለት ይቻላል፣ ከወንዞች የሚገኝ ነው። እነዚህ ወንዞች “ከነጭ ናይል” በቀር ከኢትዮጵያ የሚነሱ ናቸው። ከከርሰ ምድር ካላት የውሃ ሃብት የምትጠቀምበት የውሃ መጠን በጣም ውስን ነው፣ ያም የሚያገለግለው ለመጠጥ ብቻ ነው። ሱዳን ለመስኖ የምትጠቀመው ከወንዞች ውሃ ብቻ ነው።

ግብፅ ብዙ ትናንሽ ግድቦች አሏት፣ ዋናዎቹ ግድቦች ግን ሁለት ናቸው፣ እነሱም በ 1902 የተገነባው “ታችኛው አስዋን” ግድብ (Aswan Low Dam) በመባል የሚታወቀው እና በ1970 ግንባታው የተጠናቀቀው “ላይኛው አስዋን” ግድብ (Aswan High Dam) በመባል የሚታወቀው ናቸው። ግድቦቹ በዋናነት የሚያገለግሉት ለኃይል ማመንጫነት እና ለመስኖ ተግባር ነው። “ላይኛው አስዋን” ግድብ ያቆረው ውሃ የናስር ሃይቅ (Lake Nasser) በመባል ይታወቃል፣ ሃይቁም 162 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይዘት ሲኖረው አንድ መቶ ሃያ አምስት ኪሎ ሜትር ወደ ሱዳን መሬት ይዘልቃል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

የአባይ ተፋሰስ የቆዳ ስፋት 172,250 ኪሎ ሜትር ካሪ እንደሆነ ይገመታል፣ ይህም የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት አስራ አምስት በመቶ (15%) ያህል ያካተተ ነው። የተፋሰሱ አብዛኛው አካባቢ፣ ዕፅዋቱ ተከልተው የተራቆተ ነው። በግድቡ መንስዔ የሚቋተው የሃይቅ ስፋት 1,874 ኪሎሜትር ካሪ ሲሆን፣ ይህም የጣና ሃይቅ ከሚሸፍነው ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ገደማ ነው። ሆኖም የግድቡ ሃይቅ ጥልቀት ስላለው፣ የሚያቁተው የውሃ መጠን (ግድቡ ሲሞላ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይዘት ይኖረዋል) ፣ ጣና ከሚያቁረው የውሃ መጠን ከሁለት እጅ በላይ ይልቃል። የግድቡ ውሃ (ሃይቁ) ወንዙን ተከትሎ ወደ ኋላ 245 ኪሎ ሜትር ድረስ ይዘልቃል።

ይህ ግድብ ለሱዳን የሚያበረክተው ጥቅም ከፍተኛ ነው። ከግድቡ የሚወጣው ውሃ በነባር ተፋሰሱ ወደ ሱዳን ይገባል፣ ይህም ፍሰቱ የማስተጓጎል፣ የማይቋረጥ መጠኑ የታወቀ ውሃ ያበረክታል። በተጨማሪ፤ ከፍተኛ ዝናብ ሲኖር ሱዳን በጎርፍ እንድትጠቃ ያደርጋል። ለግብፅም የማይቋረጥ መጠኑ የታወቀ ውሃ ያበረክታል። ይህም ሆኖ ሁለቱ የታችኛው የተፋሰስ አገሮች፣ ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ መንስዔ ብዙ ውዝግብ እያስነሱ ይገኛሉ።

እያንዳዱ “የናይል” ተፋሰስ አገር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የውሃ ተጠቃሚ መሆን ይገባዋል። በነባር ሁኔታ ይቀጥል ማለት ከከንቱ ምኞት የዘለቀ አይሆንም። የውሃው ተጠቃሚ አገሮች ሁሉ ይህን ጉዳይ በጥሞና ማጤን እና መረዳት ይገባቸዋል። ለዚህም ተግባር የተፋሰሱ አገሮች በጠቅላላ የተስማሙበት አዲስ ውል መመሥረት ይገባል። ያ፤ ባይደረግ ተጎጂ የሚሆኑት የውሃ አመንጭዎች ሳይሆኑ፣ ታች ያሉ ብቻ (የውሃው ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች) ናቸው።

ነባራዊው የናይል ፖለቲካ

ከ12ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት የግብፅን ገዥዎች የዓባይን ወንዝ ፍሰት አቅጣጫ እንቀይረዋለን እያሉ ያንገራግሯቸው እንደነበረ ይወሳል። የዓባይ ፍሰት በቀነሰ ቁጥር በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ ማህበረሰቦች ለችግር ይጋለጡ እነደነበረ ይወሳል፣ በእንደዚያ ባለ ወቅት ውሃ አመንጭዎችም (የላይኛው ተፋሰስ አገሮች) ተጎጂዎች እንደነበሩ አያጠራጥርም። ከክርስቶስ ልደት 1740 ዓመት በፊት በግብፅ የተከሰተው የሰባት ዓመታት ርሃብ በዓባይ ፍሰት መቀነስ እንደነበረ ይገመታል።

የኢትዮጵያ እና የግብፅ ባህላዊ ሃይማኖታዊ ግንኙነት የተመሠረተው ንጉሥ ኢዛና በ330 አካባቢ ከነገሠ በኋላ ነበር (ዘመን ሲጠቀስ “ዓም” የሚል ካልታከለበት፣የግሪጎሪዎስ ዘመን አቆጣጠር ነው)። ለአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት ገደማ ለኢትዮጵያ ጳጳሳት የሚላኩላት ከእስክንድርያ (ግብፅ) ነበር። በዕውቀቱ ሥዩም ያለምክንያት አይደለም “ዓባይን ወስደው አባሆይን ላኩልን” ብሎ ሁኔታውን የተቸው። ለኢትዮጵያ የሚላኩት ጳጳሳትም የሚሾሙት በግብፅ ነገሥታት ነበር።

ዘመናዊው የናይል ፖለቲካ

“የናይል” ዘመናዊ ፖለቲካ ከቅኝ ገዢዎች ጥቅማ ጥቅም ጋር የተቆራኘ ነበር። “ከኢንዱስትሪ አብዮት” ማግስት፣ የብሪታንያ መንግሥት ግዙፍ የሆኑ የጨረቃ ጨርቅ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በሊቨርፑል እና በማንቸስተር ከተማዎች ገንብታ፣ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ዕቃ ግብዓት ስላስፈለጋት እና ዋናው ጥሬ እቃ ጥጥ ስለነበረ፣ ሱዳን እና ግብፅን የጥጥ ማምረቻ ማእከላት አደረገቻቸው። በዚያ በበርሃ አካባቢ ያለ ውሃ ግብዓትን ጥጥም ሆነ ሌላ ሰብል ማምረት አይቻልም። በዚያ አካባቢ ያለው የውሃ ቋትም “የናይል” ወንዝ ስለሆነ፣ ብሪታንያ ወንዙን ከነምንጩ መቆጣጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ አገኘችው። ቅኝ ገዥዎች “የናይል” ወንዝ መፍለቂያን ለመቆጣጠር ፉክክር ጀመሩ፣ አንዱም ደቡብ ሱዳን ላይ ተከስቶ የነበረው የፈረንሳይ እና የብሪታኒያ ፍጥጫ ነበር።

ቀደም ሲል በታሪክ “የናይልን” መነሻ (The source of the Nile) ለማወቅ የተመኙ ብዙ ናቸው። ለዘመናት “የናይል” ዋና መነሻ በምድር ወገብ አካባቢ ያሉ የአፍሪካ ሃይቆች እንደሆኑ ይታመን ነበር። ከዘመናት በኋላ ነበር፣ “ናይል” የሁለት ወንዞች ድምር መሆኑ እና አንዱ፣ “ነጭ ናይል” የሚባለው፣ ከቪክቶርያ ሃይቅ አካባቢ የሚነሳው እና ሁለተኛው ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚነሳው ዓባይ መሆናቸው ግንዛቤ የተገኘው። ግንዛቤውንም ካዳበሩት አንዱ ኢትዮጵያን በ1770 የጎበኘው እና በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየው “ጄምስ ብሩስ” (James Bruce) ሲሆን፣ እሱም በጉብኝቱ ወቅት የዓባይን መፍለቂያ እንዳገኘው ለአውሮፓውያን አስታውቆ ነበር።

በ19ኛው ምዕተ ዓመት የዚያን አካባቢ በመቆጣጠር የእስያን ሃብት መዛቅ እንደሚያስችል ስለታመነበት፣ አካባቢውን መቆጣጠር የአውሮፓውያን ዋና ዓላማ ነበር። በዚያም መንስዔ በብሪታንያ (Britain) እና በፈረንሳይ መንግሥታት መኻል ከፍተኛ ፉክክር ተከስቶ ነበር። ያም የፋሾዳ መፋጠጥ የሚባለው በብሪታንያ የበላይነት ተቋጨ። ከዚያም በስምምነት ፈረንሳይ የኮንጎ ወንዝን (Congo River) እንድትቆጣጠር፣ ብሪታንያ ደግሞ “የናይል” ወንዝን እንድትቆጣጠር በሁለቱ መኻል ስምምነት ተደረሰ።

የፈረንሳይ መንግሥት ከምዕራብ አፍሪካ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ቦታ (አፍሪካን ከምዕራብ ጠረፍ እስከ ምሥራቅ ጠረፍ) ተቆጣጥራ ነበር፣ ይህም ሴኔጋልን (Senegal)፣ ማሊን (Mali)፣ ኒጀርን (Niger) እና ቻድን (Chad) ያካትታል። የምሥራቁም መዳረሻ ቀይ ባህር ዳራ ላይ ያለችው ጅቡቲ (Djibouti) ፣ ወይም የፈረንሳይ “ሶማሌ ምድር” (French Somaliland) ነበረች።

ዋናው ዓላማ “በኒጀር” ወንዝ (Niger River) እና “በናይል” ወንዝ (Nile) የግንኙነት ሰንሰለት መሥርቶ፣ የአካባቢውን፣ በሳሃራ በርሃ የሚያልፈውን የንግድ መስመር (caravan routes)፣ እንዲሁም “ነጭ ዓባይን” (White Nile) ከምንጩ አካባቢ መቆጣጠር ነበር። በዚያን ዘመን ብዙ ውሃ አበርካቹ “ነጭ አባይ” እንደነበረ ይገመት ነበር። ዋናው የናይል ገባር “ጥቁር ዓባይ” (Blue Nile) መሆኑ ቢታወቅ ኖሮ፣ ምናልባት የኢትዮጵያ ታሪክም አቅጣጫ ሊቀየር የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር ብሎ መገመት ይቻላል።

ብሪታንያ “የናይልን” ተፋሰስ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንድትችል፣ ብሎም የፈረንሳይን ተመሳሳይ ፍላጎት ለማክሸፍ ተነስታ፣ የፈረንሳይ መንግሥት እና ብሪታንያ ለግጭት ተቃርበው ነበር። ይህም በ1898 የተከሰተው ሁኔታ “የፋሾዳ ፍጥጫ” (The Fashoda Incident) በመባል ሲታወቅ፣ ፍጥጫው በሰላማዊ መንገድ፣ ያለ ጦር መማዘዝ ተቋጨ፣ ተደመደመ። ፈረንሳዮች በዓድዋ ጦርነት በጣሊያን ጦር ላይ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ (1896) ድል የተጎናጸፈውን ምኒልክን፣ በነሱ ወገን ሆኖ የዚህ ፍጥጫ ተካፋይ እንዲሆን በጣም ገፋፍተውት ነበር፣ ሆኖም ጥረታቸው አልተሳካም። ምኒልክ “በፋሾዳ ፍጥጫ” ባለመሳተፉ፣ ኢትዮጵያን በብሪታንያ ሊደርስባት ከሚችል ጫና እንደታደጋት ይታመናል። ከ”የፋሾዳ ፍጥጫ” በኋላ እንደማካካሻ፣ ዓላማው ያልተሳካለት የፈረንሳይ ጦር በአዲስ አበባ በኩል ወደ ጅቡቲ ሲያቀና፣ በምኒልክ ግቢ ከፍተኛ ግብዣ እና ሽኝት ተደርጎለት ነበር።

ሆኖም ከዚያ በኋላ የናይልን ውሃ አጠቃቀም ስምምነት እንደሚያስፈልግ ቅኝ ገዥዎች ስላመኑ፣ “የናይል” ብቸኛ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ብለው፣ ሱዳን (ቀደም ሲል በቅኝ ገዥዎች ተወክላ፣ ነፃ ከወጣች በኋላ ራሷ) እና ግብፅ በውሃ አጠቃቀም ስምምነቶች እንዲፈጽሙ ወሰኑ።

የ “ናይል” (Nile) ውሃ

አጠቃቀም ስምምነቶች

ስለ “ናይል” (Nile) ውሃ አጠቃቀም ሁሉንም የተፋሰሱን አገሮች ያካተተ/ ያሳተፈ አንድም ስምምነት የለም። ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱት ሱዳን ወይም ቅኝ ገዥዋ የነበረችው ብሪታንያ እና ግብፅ በ1929 እና በ1959፣ የደረሱባቸው ስምምነቶች ናቸው። እነኝህ ስምምነቶች ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች የማይመለከቱ ናቸው። በተጨማሪ ስለ ኢትዮጵያ ሲወሳ፣ በ1902 ከብሪታንያ መንግሥት ጋር የነበረ የስምምነት ሰነድ ረቂቅ ይወሳል። የስምምነት ሰነዱ በመሠረቱ የሱዳን እና የኢትዮጵያን ድንበር ለመከለል የተዘጋጀ ሲሆን፣ እግረ መንገዱን ስለ ውሃ አጠቃቀም ያወሳል (አንቀጽ ሦስት)። የዚህን ሰነድ ይዘት ለመገንዘብ ይረዳ ዘንድ፣ በእንግሊዝኛ የተፃፈውን እንዳለ በቅንፍ ማስፈሩ ይረዳል የሚል እምነት ስላለኝ፣ እነሆ፡

(On May 15, 1902, the United Kingdom of Great Britain and Ethiopia…, Article III of the Treaty ….…. provided: “His Majesty the Emperor Menelik II, King of kings of Ethiopia, engages himself towards the Government of His Britannic Majesty not to construct or allow to be constructed, any works across the Blue Nile, Lake Tsana or the Sobat, which would arrest the flow of their waters into the Nile except in agreement with his Britannic Majesty’s Government and the Government of the Sudan”.)

ሰነዱ ቁልጭ አድርጎ እንዳሰፈረው፣ ፍሰቱን “የሚያግድ” እንጅ “የሚገድብ” ጉዳይ አይደለም፤ ስምምነት ላይ በቅድሚያ መደረስ ያለበት የሚሻ፣ ያም ቢሆን ከብርታንያ ጋር እንጅ ከሱዳን ወይም ከግብፅ ጋር አይደለም። በስምምነቶችም ሰማኒያ በመቶ (80%) “የናይል” ውሃ ለግብፅ፣ ሃያ በመቶ (20%) ለሱዳን ድርሻ ነው ተባለ። ለውሃ አመንጭ አገሮች ምንም ድርሻ አልታሰበላቸውም፣ ከዚህ የባሰ ግድ አልባነት የት ይገኛል።

ግብፅ ከናይል ተፋሰስ ውጭ ካቀደቻቸው ፕሮጀክቶች አንዱ

ግብፅ የናይልን ውሃ ከተፋሰሱ ውጭ ቀልብሳ እየወሰደች፣ ለልማት በማዋል ሙከራ ብዙ ውሃ በትነት ታባክናለች፣ ለምሳሌ ያህል “የቶሽካን” ፕሮጀክት (Toshika Project) ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ1964 በዚያን ዘመን የግብፅ ፕሬዚዳንት በነበረው በጋማል አብደል ናስር ነበር። ለመገንባት ዘመናት(1964-1968) የፈጀው የአስዋን ግድብ (የናስር ሃይቅ በመባል ይታወቃል) ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በ1978 “የሳዳት ቦይ” (Sadat Canal) በሚታወቅ የውሃ መስመር ከናስር ሃይቅ “ከቶሽካ” አካባቢ ጠልፎ ወደ ምዕራባዊ የግብፅ በርሃ ለመውሰድ ተጀመረ። ይህ ፕሮጀክት በ1964 ቢታቀድም እንደገና ነፍስ የዘራው፣ በ1997 በሁስኒ ሙባረክ (የግብፅ ፕሬዚዳንት) ዘመን ነበር። ውሃ “ከናይል” ተጠልፎ “በሳዳት ቦይ” ወደ ምዕራብ ግብፅ በረሃ እንዲፈስ ነበር። ቦዮቹ በአካባቢው ከሚገኙ “ለምጌዎች” (ኦኤስስ/Oasis) ጋር እየተገናኘ፣ መጠነኛ ሃይቆች እየመሠረተ፣ በሃይቆች ሰንሰለት እንዲፈስ ነበር የታሰበው። ቦዮቹ 310 ኪሜ ይጓዛሉ፣ ሃይቆቹ በድምሩ 1300 ኪሎ ሜትር ካሬ ይሸፍናሉ። ጠቅለል ብሎ ሲታይ ይህ ፕሮጀክት በመሠረቱ ከናስር ሃይቅ ውሃ በሰፋፊ ቦዮች ተጠልፎ፣ የናይልን በመቶ አሥር (10%) ውሃ ወስዶ፣ የግብፅን ምዕራባዊ በርሃ ለማልማት የታቀደ ፕሮጀክት ነበር።

የናይል ወንዝ የሚወሰደው፣ ከተፈጥሮ ፍሰቱ ውጭ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በዚህ በርሃ፣ ውሃ ከሃይቁ ተጠልፎ 310 ኪሜ ሲጓዝ፣ በሂደት በዓመት ሦስት ቢሊዮን ሜትር ውሃ ከቦዮች ሲተን፣ ከናስር ሃይቅ ብቻ ከ10 እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ይተናል። ፕሮጀክቱ ከመነሻው ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩበት።

አንዱ እና ዋና ምዕራባዊ በርሃ በመስኖ ለማልማት ቢሞከርም፣ በአጭር ጊዜ አፈሩ ጨዋማ ስለሚሆን መሬቱ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በክፍት ቦይ በበርሃ በረጅም ርቀት የሚፈሰው ውሃ በትነት ይባክናል። በ2010 ይህ ፕሮጀክት ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ገደማ ለማልማት እንዳስቻለ ይወሳል። በተጨማሪ መሬቱ ዋልካ ቀመስ ስለሆነ፣ ባለበት አካባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስተናገድ በጣም አስቸጋሪ (መኪናዎች ወዘተ በጭቃ ይያዛሉ) ነው። “የቶሽካ” ፕሮጀክት የናይል ተፋሰስ አገሮች ሁኔታ (ድርሻ) ያላከተተ ነበር፣ ይህ ፕሮጀክት የተመሠረተው የናይል ተፋሰስ አገራት እንደሌሉ ተቆጥረው ነበር።

በተፋሰስ አገሮች በውሃ ፍጆታ መንስዔ ለተከሰቱ ችግሮች

መፍትሄ ጥቆማ

በግብፅ “ናይል” ውሃ ላይ የተመሠረተ ግብርና ውሃ በጣም አባካኝ ነው። በአንድ ወቅት ግብፅ በአማካሪነት፣ ካይሮ ከሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ “የበርሃ ጥናት ማዕከል” (American University of Cairo –Desert Studies Centre) ጋር በመተባበር ተሰማርቼ ከሁለት ዓመታት በላይ እየተመላለስኩ በጥናት ተሠማርቼ ነበር። ያም በካናዳ መንግሥት የምርምር ተቋም የተደገፈ ጥናት፣ በግብፅ የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር ግምገማ [Assessment of Water Users Associations in Egypt for the International Development Research Centre (IDRC) Canada] ያተኮረ ተግባር ነበር። በጥናቱ ወቅት የተገነዘብኩት እነሆ። “ከናይል ወንዝ” በፓምፓ (Pump) ውሃ ተስቦ፣ ከሁለት ሜትር ስፋት ባለው ቦይ ውስጥ ይለቀቃል፣ ያም አንደኛ ቦይ (Primary Canal) በመባል ይታወቃል። ውሃ ከዚህ ቦይ እየተቀነሰ ለሁለተኛ ደረጃ ቦዮች (Secondary Canal) ይከፋፈላል። ከሁለተኛ ደረጃ ቦዮች ደግሞ እንዲሁ ውሃ እየተቀነሰ ለሦስተኛ ደረጃ ቦዮች (Tertiary Canal) ይከፋፈላል። ከዚህ በኋላ ነው ውሃ ማሳ ላይ የሚደርሰው። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ቦዮች አስተዳደር ሃላፊነት የመንግሥት ሲሆን፣ ማሳ ላይ የሚደርሰው የሦስተኛ ደረጃ ቦዮች አስተዳደር ግን የውሃ ተጠቃሚ ማህበራት ሃላፊነት ነበር። የግለሰቦች የውሃ አጠቃቀም የሚተዳደረው በማህበራቱ የውሃ አጠቃቀም ህግጋት ነበር።

ግብፅ በብዛት ከሚመረቱት ሰብሎች አንዱ እና ዋናው ሩዝ ነው። አንድ ኪሎ ሩዝ ለማምረት 1400 ሊተር ውሃ ያስፈልጋል፣ ይህም ሰባ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀን የሚጠቀሙበትን የውሃ መጠን ነው። ግብፅ በግብርና ላይ ተሠማርታ ለውጭ ንግድ (ሽያጭ) ብዙ ዓይነት ምርቶች ለገበያ ታቀርባለች፣ ዋናዋናዎቹ ሩዝ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ አበባ፣ ወዘተ ሲሆኑ፣ ሁሉም ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚሹ አዝመራዎች ናቸው። ግብፅ ይህን የምታስተናግደው በርሃ ውስጥ ሆና ነው።

መንግሥት ቢያንስ አንደኛው (ዋናው) ከተቻለ በአንደኛ እና ሁለተኛ ቦይ ውስጥ የሚፈሰውን ውሃ በዝግ ቱቦ ውስጥ እንዲያልፍ ብታደርግ፣ በትነት የሚባክነውን ተገትቶ፣ ብዙ ውሃ ለጥቅም ለማዋል በተቻለ ነበር። እንዲሁም ሰብል አምራቾች (ገበሬዎች) የሚጠቀሙበትን ውሃ፣ በክፍት ቦይ ፋንታ፣ ውሃ በሚረጭ ቴክኖሎጂ (sprinkler) ቢጠቀሙ፣ የውሃ ሃብቱን በአግባብ ለመጠቀም ያስችል ነበር። ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት ቢያስተናግዱ፣ በአጠቃላይ ብክነቱ በግማሽ ሊቀነስ እንደሚችል ይገመታል። በተጨማሪም በከርሰ- ምድር በተቋተ መጠነ ብዙ ውሃ መጠቀም ይችላሉ።

በአገራችን ብዙ የመረጃ ውስንነት ይስተዋላል። ያም በአጠቃላይ ከኢኮኖሚ እድገታ ችን ጋር የተቆራኘ ነው። ባንፃሩ ግብፅ በጣም ብዙ ጥናት ላይ የተሰማሩ ምሁራን አፍርታለች። እኔ የጥናቴን ውጤት በአንድ ስብሰባ አንድ አዳራሽ ውስጥ ሳቀርብ፣ በውሃ የትምህርት ዘርፍ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ከሦስት መቶ በላይ ምሁራን ተሰብስበው ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው የውሃ ትነት መቀነስ ተግባር ሱዳን ውስጥም መካሄድ ይኖርበታል። አንድ ጥናት ላይ ተመሥርቶ፣ በ2020 በተደረገ ስሌት፣ በሦስት የተፋሰሱ አገሮች፣ ማለት በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ እያንዳንዱ ግለሰብ በየቀኑ የሚጠቀምበት የውሃ መጠን ተገምቶ ነበር፡ ያም በኢትዮጵያ 279 ሊትር፣ በሱዳን 2087 ሊትር እና በግብፅ 2202 ሊትር ነበር። ይህ ኩነት የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው ያስብላል።

የዓባይ ተፋሰስ ክብካቤ በኢትዮጵያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዐሊ አነሳሽነት እና መሪነት አካባቢያችንን “አረንጓዴ” የማድረግ ተግባር ተጀምሯል፣ ይበል፣ ይበል ሚያሰኝ ነው። ይህም ተግባር ለዓባይ ተፋሰስ ማገገም ከፍተኛ ተስፋን የሚያበስር ነው። ሆኖም እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥቅም ያለው እንቅሰቃሴ፣ ብሎም የሃገር ህልውናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ግብዓት የሆነ ተግባር ሲከናወን በዘመቻ መልክ ብቻ ባይሆን ይመረጣል። እንቅስቃሴውን ዘላቂ ለማድረግ አንድ ቋሚ ሥርዓት ቢመሠረት ተግባሩን ያጠናክራል የሚል እምነት አለኝ። ከተጀመረው እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ በብሔራዊ አገልግሎት መልክ ቋሚ ተግባር ሆኖ በወጣቱ ትውልድ መተግበር ይገባዋል የሚል እሳቤ አለኝ። በተጨማሪ የአካባቢ ክብካቤን ባህል ለማዳበር ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባል፣ ያም በቋሚ መልክ በየትምህርት ቤቶች ሁሉ መስተናገድ ይገባዋል። ይህንን ጉዳይ ለማስተናገድ ሰፋ ያለ ትንታኔ ስለሚጠይቅ፣ አንድ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ማዘጋጀት ያሻል።

ከአካባቢ (የተፋሰስ ክብካቤ ጋር ተያይዞ) በዓባይ ዋና ተፋሰስ ላይ ያነጣጠረ የጮቄ ተራራ ሰንሰለት ልማት እና የአካባቢ ምኅዳር ማገገሚያ በሚል ርዕስ (Choke Mountain Range Development and Ecosystem Rehabilitation) አንድ ፕሮጀክት አለ። የፕሮጀክቱ ግርድፍ እቅድ ፣ “ከወደ አነጀኒ ምን ይሰማል?” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ከተነሱ የአካባቢ ክብካቤ ጉዳዮች ጋር በቅርብ የተዛመደ ነበር። እቅዱም ከ2008 ጀምሮ ሥራ ላይ እየዋለ ነው።

ከጊዜ በኋላ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዋና ተዋናዮች. የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ሆኑ። ለዚህም ሂደት ወሳኝ ሚና የነበረው፣ አሁንም ያለው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አባል የሆነው ፕሮፌሰር በላይ ስማኒ ነው። በፕሮፌሰር በላይ ስማኒ መሪነት፣ አሜሪካን አገር ካሉ ሁለት አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች (ማለት”የዊስኮንስን እና የጆንስ ሆፕኪንስ” (University of Wisconsin/ Johns Hopkins University) የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች በመደረግ፣ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሳይንሳዊ እና ማህበራዊ መረጃዎች አበርክተዋል፣ እያበረከቱም ይገኛሉ። መረጃዎች በዋናነት የተሰበሰቡት በድህረ ምረቃ ምርምሮች (ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፎች ሲሆን፣ ከአርባ በላይ የመመረቂያ ጽሑፎች ለጮቄ አካባቢ መረጃ አበርክተዋል።

የእንቅስቃሴው ዋና ዓላማ ማህበረሰቡ ስለ ተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ያለውን ግንዛቤ ማዳበር ነው። ስለ አካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት እና ስለ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች በዛ ያሉ መረጃዎች መሰብሰብ ተችሏል። የተሰበሰቡት መረጃዎች ለፕሮጀክቶች ቀረፃ እንዲሁም፣ ለልማት ግብዓትነት እያገለገሉ ናቸው። በሂደት የጉዳዩን ባለድርሻዎች ሁሉ በዓውደ ጥናቶች ላይ ማወያየት፣ ወዘተ. መረጃ ማካፈል ብሎም ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መጣር አንዱ ዓቢይ ተግባር ነው። የዚህ ጥረት አንዱ ዋና ውጤት “ለጮቄ አናት” ክብካቤ የሚያገለግል ደምብ በአማራ ክልላዊ መንግሥት መደንገጉ ነው።

“ደምብ ቁጥር 184/2011 ዓም፡ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ዳር ድንበር አከላለንና አስተዳደር መወሰኛ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት ደምብ” በሚል ርዕስ ደምብ ወጥቷል። ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፣ ሌላው የልማት ተግባር እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ።

በዓባይ ሸለቆ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ “ጣና በለስ” ጣቢያን መሥርታለች። “ታላቁ የሕዳሴ ግድብ” እየገነባች ትገኛለች። ወደፊት “በካራዶቢ”፣ “በቤኮአቦ”፣ እና “በመንዲያ” የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለመመሥረትም አቅዳለች። የዓባይን ውሃ ልማት ተግባር መጠቀም ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ከድህነት መላቀቂያ ተግባር ነው፣ የህልውና ጉዳይ ነው።

Recommended For You