ማደሪያ ያገኘው አባይ

ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ባለፈው ዓመት ክረምት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዙ ይታወሳል:: በዘንድሮው ክረምት ደግሞ በታቀደው መጠን ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል። ግድቡ ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚይዝም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ አሁን በሰዓት 13 ሺ ጊጋ ዋት ኃይልን ማመንጨት ትችላለች።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ምርት መስጠት በሚጀምርበት ጊዜ በሰዓት 15 ሺ 700 ጊጋ ዋት ማመንጨት ይችላል። ይህም አሁን በሀገራችን እየመነጨ ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን የሚልቅ ነው።

ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳዩ ወደ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ተጽዕኖ ይፈጥሩልናል ወደ አሏቸው አገራት በመውሰድ የቅኝ ግዛት ዘመን የአባይ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀምን ለማስጠበቅ ቢፍጨረጨሩም ኢትዮጵያ በግድቡ ቴክኒካልም ሆነ ህጋዊ መንገዶች ዙሪያ ግልፅ መርህ ማስቀመጧን እወቁልኝ ብላለች። በግድቡ ዙሪያ ያለው አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይፈታል የሚል ጽኑ እምነቷን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህም አፍሪካ በራሷ ጥበብ ችግሮቿን ሁሉ መሻገር ትችላለች የሚል እምነት እንዳላት ለዓለም አሳይታለች። ይህ ጥረቷ ፍሬ አፍርቶም የጸጥታው ምክር ቤት በኒውዮርክ ባካሄደው ስብሰባ ግድቡን የተመለከተው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መታየቱን ደግፏል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት በተጎናጸፈችው ዲፕሎማሲያዊ ድል የታጀበው ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት መጠናቀቁ ዜናውን በጉጉት ለሚጠብቁት ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ይፋ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት መጠናቀቁን ሲያበስሩ ባደረጉት ንግግር “የሁለተኛውን ዓመት የህዳሴ ግድብ ሙሌት ተገባዶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ፈሷል። ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም እንኳን ደስ አላችሁ።

ይህ ውጤት ሁለት ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ያገኘንበት ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ በዘንድሮው ዓመት መጠነ ሰፊ ስራ ሰርተናል። በቀጣይ ሁለቱ ተርባይኖች ማደሪያ ያገኘው አባይ ኃይል እንዲያመነጩ ብርቱ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ስራውን በቅርብ ወራት በማጠናቀቅ የልፋታችንን ውጤት ላይ እናደርሳለን። ” ብለዋል።

በዚህ ጽሑፍ የሁለተኛው ሙሌት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ፣ ለቀሪዎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገራትና ለግብጽና ሱዳን ያለው ትርጉም፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሙሌት በማሳካቷ የምታገኛቸው ጥቅሞች ፣ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሚደረገው ቀጣይ ድርድር የሚኖረው መልክ እና በቀጣይ የኢትዮጵያ አካሄድ ምን መምሰል አለበት የሚሉት ጉዳዮች ተዳሰዋል።

 ለዚህም በዘርፉ የማማከር ስራ የሚሰሩ ፣ ምርምር የሚያካሂዱና ኢትዮጵያን በመወከል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ምሁራንን አናጋግረናል ፤ እንደሚከተለው ይቀርባል። በናይል ቤዝ የትብብር መድረክ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትና አሁን በውሃ ሀብት አስተዳደር የግል አማካሪ በመሆን እየሰሩ የሚገኙት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገነባው በሉዓላዊ ድንበራችን ውስጥ ነው።

በኢትዮጵያ ወንዝ ላይ ነው። የሚሞላውም በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ ድርሻ ነው። ምንም እንኳን በአንድ በኩል ግብጽና ሱዳን በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኃያላን አገራት ጫና ቢፈጥሩም ሙሌቱ መካሄዱ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ የማትደራደርና ምን ጊዜም መብቷን ከማስከበር ወደ ኋላ የማትል ሀገር መሆኗን የሚያሳይ መልዕክት ያስተላልፋል ይላሉ።

የናይል ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ አገራት እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገራትና እንደ ኢጋድ ያሉት ቀጠናዊ ድርጅቶች ሙሌቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት መሆኑን ይቀበላሉ የሚሉት አቶ ፈቅአህምድ ፣ በተለይ የናይል ተፋሰስ አገራት ግድቡ መገንባቱንም ሆነ በመርሐ ግብሩ መሰረት መሞላቱን እንደ ፈር ቀዳጅ እርምጃ ይወስዱታል።

በሌላ መልኩ ግን ግድቡ ውሃ እንዳይዝ ሚዛን የማይደፋ ምክንያትን እያነሱ ችግር እየፈጠሩ ላሉት ወገኖች ደግሞ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ የማትደራደር አገር ስለመሆኗ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ይገልጻሉ። አያይዘውም “የውሃው ከፍታ እየጨመረ ሲሄድና ኃይል የማመንጨት ስራሲጀመር ለኢትዮጵያ የመደራደር አቅሟን ከፍ ያደርግላታል። የመደራደር ኃይል ከሚባሉት ውስጥ አንደኛው መሰረተ ልማት ነው። ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ካሉና እነዚህ መሰረተ ልማቶች ደግሞ ውሃውን የማረጋጋት ስራ የሚሰሩ ከሆነ የመደራደርን አቅም ይጨምራሉ። ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ሁለተኛው ሙሌት ተካሂዷል ብለው ቀጣይ ሙሌቶች እንዳይካሄዱና ወደ ፊትም ግድቡ በሰላም እንዳይሰራ ላይ ታች ከማለት አያርፉም። ጭቅጭቁና ፍጥጫው ይቀጥላል። የኢትዮጵያ የመደራደር አቅምም ያድጋል። በተለይ ደግሞ ሁለተኛው ሙሌት በተካሄደበት ወቅት ግብጽና ሱዳኖች እያናፈሱ ያሉት ጉልህ ጉዳት አለመድረሱ በመታየቱ ለሚለቁት ውዥንብር ስህተት መሆኑን የዓለም ማህበረሰብ ይረዳል ” ይላሉ።

ከሁለተኛው ሙሌት በኋላ በኢትዮጵያና በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት መካከል የሚኖረው ድርድር ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል ሲገልጹም “የግብጽና ሱዳን ጩኸት የህዳሴ ግድብ በእኛ ላይ ጉዳት ያደርሳል ከሚል የሚነሳ አይደለም። ዋናው ዓላማቸው በግድቡ ሙሌትና የውሃ አለቃቅ ድርድር መካከል ውዥንብር ፈጥረው አለን ለሚሉት ታሪካዊ የውሃ ድርሻ እስካሁን ከኢትዮጵያ አግኝተው የማያውቁትን እውቅና ማግኘት ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወደፊት ሌሎች ግድቦችን እንዳትሰራ ከወዲሁ ለመገደብ መከራ የማሳየትና ተስፋ የማስቆረጥ ስራ ነው የሚሰራው። ግድቡ ጉዳት እንደማያደርስባቸው እነሱም ያውቃሉ እኛም እናውቃለን፤ የዓለም ማህበረሰብም ያውቃል። ስለዚህ ይህ አስተሳሰብና እምነት እስካለ ድረስ ግድቡ ከሞላ በኋላም ከድርጊታቸው ይታቀባሉ ብዬ አላስብም” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ከዚህ ቀደም በግብጽ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰሩት አቶ ፈቅአህመድ ግብጽ በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምታደርገው እንቅስቃሴ በረጅሙ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ የነበረ ነገር መሆኑን ሲገልጹ ፤ “ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት የገባችባቸው ዓለም አቀፍ ፣ አህጉራዊ እና ከጎረቤት አገር ጋር የተደረጉ ጦርነቶች እንዲሁም የውስጥ ግጭቶች ውስጥ ሁልጊዜም የግብጽ እጅ መኖሩ ይታወቃል። ይህ በሰነድ የተረጋገጠ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁላችንም እንደምናውቀው እ.አ.አ. ሰኔ ሦስት ቀን 2013 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢንተርናሽናል ኤክስፐርቶች ፓናል ሪፖርት ለግብጽ መንግሥት ቀርቦ በነጋታው በወቅቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ የራሳቸውን ካቢኒ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮች ሰብስበው በቀጥታ ለዓለም መሪዎች በተላለፈ አሳፋሪ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የዓባይ ውሃን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን ባለ ሰባት ነጥብ ስትራቴጂያቸውን አስቀምጠው ነበር። እነዚህን ስትራቴጂዎቻቸውን ስናይ በአብዛኛው ኢትዮጵያን ማዳከም ፣ ማተራማስ ፣ ብሔርን ከብሔር ጋር ማጋጨት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ላይ እንዲነሱ ማድረግ እና ከጎረቤት አገራት ጋር ግጭት ውስጥ እንድንገባ መስራት የሚሉ ነገሮችን ነው ሲናገሩ የነበሩት። ይሄ በቀጥታ ለዓለም ማህበረሰብ በቴሌቪዥን የተላለፈ ስለሆነ የሚደበቅ ምስጢር አይደለም። ለረጅም ጊዜም ሲተገብሩት የነበረ ስልታቸው ነው” በማለት ግብጽ ለኢትዮጵያ የማትተኛ አገር መሆኗን ያስረዳሉ።

ይህ አካሄዳቸው የሚዳከመው ኢትዮጵያ የውሃ አጠቃቀሟን ስታሳድግና የውሃ አጠቃቀሙ ተመጣጣኝ ሆኖ በእነሱ ላይ ጉዳት አለማድረሱን በተግባር ሲገነዘቡ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ፈቅአህምድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጎ ፣ መረጋጋት ሰፍኖ ፣ አገራዊ አንድነት ተፈጥሮ አቅማችን ካደገ ወደ ድርድር መምጣታቸው የማይቀር በመሆኑ ያኔ እየቀነሰ ይመጣል ይላሉ።

ሁለተኛው ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵውያን የሚኖረውን ፋይዳ ሲገልጹም “ለረጅም ጊዜ በናይል ተፋሰስ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ግብጽ ነች። ራሷን እንደ ካቦ አድርጋ ሾማ አጀንዳዎችን የማስቀመጥና የማስወሰን ፣ በፈለገችው አቅጣጫ የፈለገችውን ወገን ማስፈራራት እንዲሁም ጫና እና ደባ የመፍጠር ስራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። ይሁን እንጂ ይህ ግድብ መጀመሩና ወደ መጠናቀቁ መምጣቱ የነበራትን የካቦነት ውሳኔ የመስጠት አቅሟን ይቀንስባታል ተብሎ ይታመናል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውሃውን በተወሰነ ደረጃ መቆጣጠር ከቻለች የመደራደር አቅሟ በጣም ከፍ ይላል። አጀንዳ የማስቀመጥና የማስወሰን አቅሟ በጉልህ ይጨምራል። ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ተምሳሌትነት መከተላቸው የማይቀር ስለሆነ የግብጽ ተሰሚነት እየቀነሰ ስለሚሄድ የውሃ ፖለቲካ አሰላለፉ ይቀየራል። አሁን እያነሳን ያለነው ስለውሃ ጉዳይ ስለሆነ ነው እንጂ በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ይጨምራል። የአቅም እድገት ማለት መሰረተ ልማት ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ፣ ወታደራዊ ብቃትን ፣ የዲፕሎማሲ እድገትንና ሌሎች አገራት ላይ ጫና የመፍጠርና ከጎን የማሰለፍ አቅምን ሁሉ የሚያካትት ነው” ይላሉ።

አያይዘውም “መንግሥት ለህዝቡ የገባውን ቃል ማክበሩ ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት ያጠናክራል የሚል እምነት አለኝ። ሌላኛው ሁለተኛው ሙሌት በመከወኑ ወደ ግድቡ ተጨማሪ ውሃ ስለሚገባ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይቻላል። ውሃው ከተያዘ በኋላ ወደ እነሱ የሚሄደው ውሃ በቂ ስለሆነ የሱዳን ህዝብ ግድቡን በተመለከተ ሲቀርብለት የነበረው ማስፈራሪያ ውሸት መሆኑን ይረዳል። ስለዚህ ፖለቲከኞቻቸው የሱዳንን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዘብ ጋር ለማጋጨት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሆኑን ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ። ለላይኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት ደግሞ ግድቡ ትልቅ ተምሳሌትነት ስላለው ዲፕሎማሲያዊ ስራ ከተሰራ ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፉበት ሁኔታ ያመቻቻል” ሲሉ የሁለተኛውን ሙሌት ጠቀሜታዎች ይጠቅሳሉ።

የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የግድቡ ግንባታና ኮንስትራክሽኑ፣ ሙሌቱ እንዲሁም የኃይል ማመንጨቱ ተጣምረው ነው የሚሄዱት። ዘንድሮ የተካሄደው ሁለተኛው ሙሌት ሁለቱን ተርባይኖችና የሚገቡትን ተጨማሪ ተርባይኖች ወደስራ ለማስገባት ወሳኝ የሆነ የስራ ሂደት ነው። ይሄ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ቋታችን ለማስገባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሌላው ደግሞ ህዝባችን በጉጉት የሚጠብቀውን የግድቡን የመጀመሪያ እሸት ፍሬ እንድናገኝ ይረዳናል የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ መሀንዲስ ፕሮፌሰርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ ናቸው።

የዓባይ ጉዳይ የውሃ አጠቃቀሙ በአስራ አንዱ የተፋሰሱ አገራት መካከል በአግባቡ ስላልተሰራና የታችኞቹ አገሮች ደግሞ ውሃው የኛ ብቻ ነው የሚል ስስታዊ አስተሳሰብ ስላላቸው የመጣ ክርክርና ፍጥጫ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ፤ “በተለይ የሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በፍጹም እዚህ የሚያደርስ ነገር የለውም። እኛ የምንገነባው ግድብ ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ጎርፍ ከመከላከል አንስቶ ኢኮኖሚያቸው ውስጥ ተጨማሪ ኢነርጂ በመክተት በብዙ መንገድ የሚሰጠው ተጨማሪ ጥቅም አለ። ነገር ግን ክርክሩ ስለ ኃይል ማመንጨቱ ሳይሆን ውሃውን ከመጠቀምና ካለመጠቀም ጋር የሚያያዝና እኛ ሳንፈቅድላችሁ እንዴት ትጠቀማላችሁ የሚለው ላይ ተንጠልጥሎ ነው እንጂ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም። ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ጉዳዩን እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ጎትተው ወስደው የንትርክ አጀንዳ አድርገውታል” ይላሉ።

ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከተከናወነ በኋለ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሚኖረው ድርድር ምንም አይነት ለውጥ እንደማይኖረው ሲያስረግጡም “በእኛ በኩል የምንፈልገውንና ያቀድነውን ኤሌክትሪክ ማመንጨታችንን እንጀምራለን። ሙሌቱን ለማከናወን ሁሉንም ውሃ መያዝ ብንችልም ከእነሱ ጋር በተወሰነ መልኩ መግባባት ላይ ደርሰን የገባነውን ቃል ጠብቀን ሙሌታችንን እያካሄድን ኤሌክትሪክ ማመንጨታችንን እንቀጥላለን። ስለዚህ በኛ በኩል ስራችንን ነው የምንሰራው በእነሱ በኩል ግን ምንም ለውጥ አያመጡም። እነሱ ሙሌቱ አይደለም ጉዳያቸው። ስለ ህዳሴው ግድብ አይደለም ጉዳያቸው ውሃውን እኛን ሳታስፈቅዱ ለምን ትጠቀማላችሁ ነው የሚሉን። እኛ ደግሞ ከእናንተ ፈቃድ አንፈልግም በመብታችን ነው የምንሰራው እያልን ስለሆነ ክርክሩ ውጥረቱ ይቀንሳል ብዬ አላስብም። ምናልባት ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያም የውሃ ድርሻ አላት የምትሞላውም በራሷ ድርሻ ነው። ወደፊትም ውሃውን የመጠቀም መብት አላት ተነጋግረን እነሱም ሳይጎዱ እኛም ሳንጎዳ እንዴት አድርገን እንጠቀም ካሉና ወዳጆቻቸውም የያዛችሁት መንገድ አያዋጣችሁም ብለው በጥብቅ መክረዋቸው ሀሳብ ከቀየሩ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። በተረፈ ግን ክርክሩ ይቀጥላል ምንም ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። ክርክሩ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች እኛን እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ በመክተት ሰላም እንዳናገኝ በማድረግ ኢኮኖሚያችንን መጉዳቱን በዓለም አቀፍና በአካባቢያዊ ፎረሞች እንዲሁም በግላቸውም ይቀጥሉበታል። ታክቲካቸው ይሄ ስለሆነ ንትርኩ አይቆምም” በማለት በኢትዮጵያ በኩል ጠንክሮ መገኘት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

በግድቡ ዙሪያ ጦርነት እንደማይጀምር የሚገልጹት ፕሮፌሰር ይልማ “እነሱ የእኛን ግድብ አይመቱም እኛም የእነሱን ግድብ አንደበድብም። በውሃ ጦርነት አትገባም በዓለም ላይ ተደርጎም አይታወቅም። ግድቡ ባለበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የዓባይ ውሃ የትም ቦታ ያለ ነው። በውሃ በቀጥታ ወደ ጦርነት ከገቡ ገባሮቹን በመያዝ ቋሚ ጥቃት ነው የምናደርስባቸው። እነሱም ፊትለፊት በመምጣት ይህን አያደርጉትም። በሌሎች ችግሮች አስታከው በጀርባ ነው የሚመጡት ለምሳሌ የትግራይ ችግር አለ ሌላም የውስጥ ችግር ሊፈጥሩብን ይችላሉ። አመጣጣቸው በጓሮ በር ነው። አሁን እያደረጉ ያሉትም ያንን ነው። አሜሪካኖቹ የህዳሴ ግድብ ላይ እናንተ ተነጋገሩ ይላሉ እንጂ በጀርባ ሌላ ችግር ፈጥረውብን እኛን በማዳከም ኢኮኖሚያችንን ዜሮ በማድረግ ሰላም በማሳጣት ዞሮ ዞሮ ወደፊት በውሃው የመጠቀም አቅማችንን እንድናጣ እየረዷቸው ነው ። ከግብጾቹ ምን እንደሚያገኙ እግዚአብሔር ይወቅ” ሲሉ እየተደረገ ያለው የሸፍጥ ስራ መሆኑን ያስረዳሉ።

አያይዘውም “የአንድን ሀገር ውሃ ለመቆጣጠር መንግሥቱን ወይም ሀገሩን ነው መቆጣጠር ያለብህ። ሀገሩን መቆጣጠር አይችሉም ስለዚህ የእነሱን ፍላጎት የሚያስጠብቅ መንግሥት ማስቀመጥ አሊያም ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖር ማድረግን ግልጽ እስትራቴጂ አድርገው ይዘውታል። ጠንካራ መንግሥት ከሌለ እንኳን ግድብን ልትሰራና ልታስተዳድር ቀርቶ ገብተህ መውጣትና ማረስም ትቸገራለህ ፤ እንደምናየው ትግራይ ውስጥ ማረስ አልተቻለም። እኛ እየጠነከርን እንመጣለን። የታችኞቹን አገራት ሳንጎዳ ግድቦች ገድበን ለመጠጥ ፣ ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የመጠቀም መብት አለን። ከአንድ መቶ በላይ ግድቦችን እንገነባለን የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በተለየ መንገድ የሚተረጉሙት ኢትዮጵያ ይሄን ለማድረግ መብት የላትም ብለው የሚያስቡት ወገኖች ናቸው። ሰላማችንን አስጠብቀን ይህንን ማድረግ ግድ ነው። ቻይና ከሃምሳ ሺህ በላይ ፣ አሜሪካ ከሃያ ሺህ በላይ ሩሲያም በተመሳሳይ ብዙ ግድቦች አሏቸው። የግድቦችን ዝርዝር ብትመለከት በዓለም ላይ አገራት በርካታ ግድቦች አሏቸው። እኛ ደግሞ እግዚአብሔር ሰጥቶናል መገደቢያ ቦታ አለ ፤ ዝናቡም አለ ፤ የሚታረሰውም መሬት አለ እንዲሁም ኤሌክትሪክ ማመንጨትም እንችላለን። ስለዚህ ከድህነት ለመውጣትና በልቶ ለማደር የተፈጥሮ ሀብታችንን መጠቀም አለብን” ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ሁለተኛውን ሙሌት ተከትሎ ድርድሩ የሚቀጥልበትን ሁኔታ በተመለከተ ሲናገሩ “በነገራችን ላይ ግብጾች የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ማመንጨት መዋሉን አልተቃወሙም። ግድቡ መሰራት የለበትም ብለው መጀመሪያ ነው የተቃወሙት በኋላ ተቀብለውታል። አሁን ባሉበት ደረጃ ኢትዮጵያ ለኤክትሪክ ማመንጫ ዓባይን አትጠቀም አላሉም። ሙሌቱም ድረስ ተስማምተናል። ይሄ ግልጽ መሆን አለበት። ጥያቄው ስለወደፊቱ የውሃ አጠቃቀም ነው። የወደፊቱን ትውልድ መብት የሚገፍ ስምምነት እንድንፈርም እየጠየቁን ነው ያሉት። ለዚህም አሜሪካኖች ተባባሪ ሆነዋል። አጀንዳው የውሃ አጠቃቀም ነው። የጸጥታው ምክር ቤት ሰብሳቢ የፈረንሳዩ አምባሳደር እኛ የውሃ ኮታ በሌለበት ምንም ማድረግ አንችልም ሦስቱ አገሮች ችግራቸውን ይፍቱ ብለው በግልጽ አስቀምጠውታል። ግብጾች አያወሩትም እንጂ ጭብጡ ይሄ ነው። እኛ እያልን ያለነው የውሃ ኮታችን ይሰራና የዛሬ ሃምሳ ዓመት የዛሬ መቶ ዓመት ምን ያህል ውሃ እንደምንለቅላችሁ ከታወቀ በኋላ ተስማምተን እንፈርማለን ነው ። ሱዳኖች አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ አፍ አውጥተው የውሃ ኮታማ ድጋሚ አንፈርምም ብለው እምቢ ይላሉ። ግብጾችማ ጨርሶ ቃሉንም አያነሱትም ፤ ኦፕሬሽን በሚል የማጭበርበሪያ ቋንቋ ውስጥ ተደብቀው ይሳለቃሉ” በማለት በግብጽና ሱዳን በኩል መሰረታዊ የሆነ የአካሄድ ለውጥ እንደማይጠበቅ ይጠቁማሉ።

ሁለተኛው ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የዓላማ ጽናታችንን በጉልህ ስለሚያሳይ በቀጠናው ያለንን ተሰሚነት ይጨምርልናል የሚሉት ተደራዳሪው ፤ “ይህንን ጽናታችንን ግን ተከታታይ ማድረግ አለብን። በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ከፍተኛ የፖለቲካ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን የራስን ኢኮኖሚ በራስ የመቻል መሰረታዊ ነገሮቹ ላይ ከፍተኛ እርምጃ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ከፍተኛ ብሔራዊ ጦር ማዘጋጀት ያስፈልጋል። አሁን የፖለቲካ ጡዘቱ ወደ ጫፍ እየደረሰ ስለሆነ ጊዜ የሚኖር አይመስለኝም። ብዙ ነገሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ዝግጅት ይጠይቃል። የሁለተኛው ሙሌት መከናወን ግን ጥንካሬያችንን ስለሚያሳይ ድሉን ወደ ፊት ይወስደዋል” ይላሉ።

ሌላኛው የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፣ ግብጽና ሱዳን እ.አ.አ በ2015 በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን ካርቱም የህዳሴ ግድቡን ድርድር አስመልክቶ የመርሆች ስምምነት መፈረማቸውን በማስታወስ የመርህ ስምምነቱ አስር አንቀጾችን ያካተተና የሶስቱንም አገሮች ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ያወሳሉ። ኢትዮጵያ ፣ ግብጽና ሱዳን በፈረሙት በዚህ የመርህ ስምምነት መሰረት ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት መካሄዱንም ይገልጻሉ።

በመርሆ ስምምነቱ መሠረት የግድቡን ውሃ ሙሌት የተመለከቱ አንቀጾች በግብፅና ሱዳን የውሃ ባለሙያዎች የሚታወቁና ስምምነት የተደረሰባቸው መሆኑን የሚገልጹት ተደራዳሪው ፤ በመርህ ስምምነቱ አንቀጽ 9 ላይ ድርድሩ የእያንዳንዱን አገር ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ መካሄድ እንዳለበት መገለጹን ይጠቅሳሉ። ግብጽና ሱዳን ግን ይህን በመጣስ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ወቀሳና ትችት እየሰነዘሩ መሆናቸውን በማንሳትም ፤ ይህ ድርጊታቸው የተዛባ መረጃ በመስጠት ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ከማሳሳት ውጭ ለድርድር ፋይዳ አይኖረውም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግብጽና ሱዳን የግድቡን ውሃ ሙሌት በተመለከተ የሚሰጡትን የተዛባ መረጃ ሊመረምር ይገባል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ ባለፈ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባትና የተለያዩ የመስኖ ስራዎችን ለመስራት ያቀደችባቸው ግዙፍ ምቹ መሬቶች አሏት። ለእነዚህ ሰፋፊ ስራዎችም ገባሪ የሚሆኑ 13 ያህል ወንዞች አሉን። ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ እነዚህን ገባሪ ወንዞች እንዳትጠቀም የሚያደርግ አሳሪ ውል እንድትፈርም ይፈልጋሉ። የሚያቀርቡት ውል ላይ ከዚህ ቀደም በሦስቱ አገራት የተፈረመውን ስምምነት የሚጻረሩ ድንጋጌዎች በመስፈራቸው ምክንያት ኢትዮጵያ አልፈርምም ብላለች የሚሉት ኢንጂነር ጌዲዮን ፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2015 የተፈረመውን ስምምነት መሰረት በማድረግ የግድቡን የግንባታ ደረጃ ተከትላ የውሃ ሙሌቱን ማከናወኗን ትቀጥላለች። በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም በያዝነው ክረምት በታቀደው መጠን ውሃ ሙሌት ይጠናቀቅ እንጂ አጠቃላይ የግድቡ ሙሌት አልተጠናቀቀም ሲሉ ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታትም ባስቀመጠችው የጊዜ ሰሌዳ ሙሌቶችን ማከናወኗን እንደምትቀጥል ይገልጻሉ።

አክለውም የሁለቱ ተርባይኖች ሙሉ የማመንጨት አቅም 750 ሜጋ ዋት ነው። ነገር ግን ግድቡ አሁን ባለው ቁመት ግን ማመንጨት የሚችሉት 400 ሜጋ ዋት ነው። ከሆለታ እስከ ሕዳሴ ግድብ ያለው 650 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ዋና የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከግድቡ የሚመነጨውን ኃይል ወዲያውኑ ወደ ማዕከላዊ ቋት ለማስገባት ያስችላል ሲሉ ኢትዮጵያ ግዙፉን ግንባታ የመጀመሪያ እሸት ለማጣጣም ጫፍ መድረሷን ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ ሲታይ ሦስቱም ከፍተኛ ምሁራንና ተደራዳሪዎች የግብጽን ኢፍትሐዊ አካሄድ የማያዋጣ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ደግሞ የዚህ ኢፍትሃዊ አካሄድ መዳረሻ ኪሣራ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመውበታል።

የትናየት ፈሩ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You