ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጪም እየተፈተነች ያለችበት ጊዜ ላይ ለመሆኗ እማኝ መፈለግ አያሻም። ፈተናው ከውስጥ፣ ሀገሩን ከከዳው የአሸባሪ ቡድን እና የቡድኑ አምላኪዎች ጋር ከውጭ ደግሞ፣ አሸባሪው ቀደም ሲል ከሀገር በዘረፈው ሀብት ካፈራቸው የጥፋት ቡድኖች እና አገር አፍራሽ አላማ ካነገቡ አገራት ጋር ነው። ይህ ፖለቲካዊ ሴራ ኢኮኖሚውንም ማናጋቱ አይቀሬ ነው። ከሀብት ማሸሽ ጀምሮ አሻጥር ከበዛበት የንግድ ስርዓት ጋር ተዳምሮ ህዝቡን ለማማረር ብዙ ርቀት ቢኬድም ህዝቡ ይህን ደባ ጠንቅቆ በመረዳቱ እጅጉን ተቋቁሞ አገርን ሊያፈርሱ የተደራጁና የተቀናጁ አካላትን በመፋለም ትግሉን አጠናክሯል።
ይሁን እንጂ፣ ወቅቱን የዋጀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው የፖሊሲና የስራ ባህል ለውጥ በማምጣጥ አለም አቀፉንም ሆነ አገር በቀሉን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በቅጡ ሊሰራባቸው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፤ ይታመናልም። ይህን ማዕከል ያደረገችው ዘመን መፅሔት ወቅታዊና ትኩረት የተቸራቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ከገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡-
የካፒታል ገበያ መፈጠር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያሳርፈው አዎንታዊ ነገር እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ኢዮብ፡- ኢኮኖሚው ውስጥ ከምንሰራቸው ማሻሻያዎች መካከል ስር ነቀል እና መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላሉ ብለን ከምናስባቸው ጉዳዮች ውስጥ የካፒታል ገበያ መቋቋም አንዱ ነው። በሀገራችን ዘላቂ የኢንቨስትመንት ባህል ብዙ አልነበረም። የንግድ ልምድ አለ፤ ነገር ግን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ዘላቂ ኢንቨስትመንት በማልማት ደረጃ ገና እየጀመርን ነው። ይህ የንግድ ልምድም ቢሆን የሚያሳትፈው ሰፊውን ህዝብ አይደለም።
የካፒታል ገበያ ትልቁ ልዩነት ምንድን ነው? ለሰፊው ህዝብ የኢንቨስትመንት እድል መፍጠር ነው። ይህ፣ የመከነና ስራ ላይ ያልዋለ ሀብት ኢንቨስትመንት ላይ ውሎ በአንድ በኩል ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችም የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም፣ ትላልቅ ኩባንያዎችን የሚያሳድግ የሼር ባህል አልነበረንም፤ ይህ በሚገባ እንዲፈጠር እና እንዲዳብር ይረዳል። ከዚህ በፊት ያቋቋምናቸው ስራዎች ጠንካራ አልነበሩም። የስኳር ሼር ኩባንያ በሚገባ ቁጥጥር ያልተደረገበት ነበር። የአሁኑ ግን ጠንካራ እና ተገቢው ቁጥጥር የተደረገበት ገበያ ነው። በመሆኑም የነበሩ ችግሮችን ቀርፎ ትልቅ የኢንቨስትመንት ሀብት በማሰባሰብ ረገድም ሆነ ለሰፊው ህዝብ የኢንቨስትመንት እድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ዘመን ፡- የካፒታል ገበያውን ተግባራዊ ለማድረግና ተገቢውን ካፒታል ከገበያው ለመውሰድ እንዲቻል የኩባንያዎች የመልካም አስተዳደር ዳራ ምን ያህል ምቹ እየሆነ ነው?
ዶክተር ኢዮብ ፡- ይህ በጣም ቁልፍ ጥያቄ ነው። በዚህ ረገድ የጀማመርናቸው ሁኔታዎች አሉ። እንደምታውቀው ‹አቤይ› የምንለው ሲቋቋም ትልቁ ውሳኔ ድርጅቶች አንድ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው። እኛ አገር በዚህ ጉዳይ ሲቀልዱ የሚሉት ነገር አለ። ‹‹ባለሀብቱ ለሚስቱ አንድ ሪፖርት፤ ለገቢዎች አንድ ሪፖርት፤ ለመንግስት ደግሞ ሌላ ሪፖርት ያቀርባል›› ተብሎ ይቀለዳል። ይህ ከቀልዱ ባለፈ ትልቅና ከባድ የተቋማት ችግር ነው። የተቋማትን የመልካም አስተዳደር ችግር በማስተካከል ረገድ ሪፖርት የሚያደርጉ ተቋማት ሂሳባቸውን በተገቢው መንገድ ሪፖርት እንዲያደርጉ ትልልቆቹ ወደ ‹አይ. ኤፍ. አር. ኤስ› እንዲገቡ ዓለም አቀፍ ተነባቢነት ያለው ወጥ የሆነ የሪፖርት ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ረገድ የጀመርነው ስራ አለ።
ሁለተኛ፣ በምክር ቤት ረገድ ብዙ አልተገፋበትም እንጂ፣ መልካም አስተዳደርን በማስተካከል ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ አምጥተናል። የድርጅቶቹን የአመራር ቦርድ ዳግም የማዋቀር ስራ፤ በርካታ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አስተካክለናል። ይህም ቢሆን ካፒታል ገበያ መቅረብ አለመቅረብ፤ ገብተህ ደግሞ ገበያን በሚገባ መምራትና መከታተል መቻል አለመቻልህ። ሌላ በጥምር የልማት ስራን ለማከናወን ከሚመጣ የውጭ ድርጅት ጋር አብሮ መስራት አለመስራት የሚለካው እነዚህ ነገሮች ላይ ግልፅ ስራ ሲሰራ በመሆኑ፣ ጎን ለጎን በሚገባ መስራት የሚኖርብን ትልቅ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። በዝርዝር የሚታወቁ ተቋማት ተቀባይነት ያለው ሂሳብ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ለካፒታል ገበያው ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ስርዓቱ ወሳኝ እና ጠቃሚ ጉዳይ ነው።
ዘመን፡- የመንግስት የልማት ድርጅ ቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ግል የማዛወሩን እቅድ መንግስት የት አድርሶታል? የድርጅቶቹ ቀጣይ እጣ ፈንታ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ኢዮብ፡- የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በማስተካከል ረገድ ከየት ተነስተን የት ደረስን? ብሎ ከመጠየቅ መጀመር አለበት። ድርጅቶቹን በሚመለከት የተዝረከረከ ሀብት ነበር። ስንት የልማት ድርጅት አለ? ምን እንደሚሰሩ ጭራሽ የማይታወቅበት ደረጃ ተደርሶ ነበር። በአጠቃላይ ውጥንቅጡ የወጣ ነበር። በመሆኑም እነዚህን ድርጅቶች በአንድ ላይ ሰብሰብ አድርገን በአንድ እይታ ስር መምራት መቻሉ አንድ ትልቅ ስኬት ነው። ሁለተኛ፣ ለሁሉም የልማት ድርጅቶች በጣም ጠበቅ ያለ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋትና ይህን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ባለፉት ሁለት አመታት የተሰራው ስራ ቀላል የሚባል አይደለም።
ሶስተኛ፣ የልማት ድርጅቶች ውስጥ የትኞቹ ናቸው የሚቆዩት፤ መንግስት ይዟቸው የሚቆዩትስ እነማንን ነው? በምን ያህል ጊዜ ነው ወደ ግል የሚዞሩት የሚለው መሰረታዊና በጣም ትልቅ ስራ ነው። በዚህ እሳቤ ድርጅቶቹን ወደ ግል በማዛወሩ ረገድ መጀመሪያ ትኩረት ያደረግነው ቁልፍ ቁልፍ የሆኑት ላይ ነው። በተለምዶው ሲደረግ የነበረው ወደ ግል የማዞሩ አሰራርና ስራ እንደቀጠለ አልሄደም። ትንንሾቹ ድሮም ቢሆን ወደ ግል እየዞሩ ቆይተዋል። ነገር ግን በሚገባ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነበር ማለት አይቻልም። በዚህም አሰራር፣ ተቋማቱ የሚገባቸውን ዋጋ እና ለውጥ አግኝተዋል ማለት አይቻልም። አንዳንዱ በትንሽ ኢንቨስትመንት የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ አለ፤ አሁን እየሰራን ያለው የሪፎርም ስራ እነዚህን ለማየት እድል ሰጥቶናል።
በተደጋጋሚ የማነሳው አንድ ጉዳይ አለ። የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት ዋናው ግብ ወደ ግል የማዞር ስራ አይደለም። እነዚህን ተቋማት ውጤታማ ማድረግ፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል ያለንን የሀገር ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል መቻል ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ አንጓ ድርጅቶቹን ወደ ግል ማዛወር መቻል ነው። መንግስት በእጁ የማያቆየው፤ ወደ ግል ቢዞር ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት የቱ ነው? የሚለውን በጥናት ጭምር እየመለስን ነው። ጥያቄህን ለመመለስ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ሄደናል። ደግሞም ብዙ ስራ ይቀረናል። ሂደቱንም ግልፅነት የተሞላበት እናድርግ ባልነው መሰረት ጊዜ ወስደን እያንዳንዱን ነገር በሚገባ ለማየት ሞክረናል።
በዚህ ረገድ ውጤቱና ሂደቱ በጣም ወሳኝና ጠቃሚ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብን በሚገባ የሚከታተለውና ምስክርነቱን የሚሰጥበት ነው። የቴሌኮም ሂደት ብናይ እጅግ በጣም ያስመሰገነ ነበር። ተወዳዳሪዎች ሳይቀሩ ‹‹እንዲህ አይነት አሰራር አፍሪካ ውስጥ ይኖራል ብለን አልጠበቅንም›› እስኪሉ ድረስ ነው ምስክርነቱን የሠጡት። ይህ እጅግ በጣም ትልቅ አገራዊ አቅም ነው። ይህ ደግሞ በራስ መተማመንን ያመጣል። በዚህ አይነት አካሄድ አብዛኞቹን እናከናውናለን። ቀጣይ ስራዎችም አሉ፤ በመሆኑም የመጣንበት መንገድ ብዙ ርቀት የተጓዝንበት ነው።
እዚህ ላይ በሰራነው ስራ ያሉንን የመንግስት የልማት ድርጅቶች አውቀናል። ሁሉም የተሻለ ኮርፖሬት አስተዳደር እንዲኖራቸው ተደርጓል፤ የተሻለ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸውም አድርገናል። ወደ ግል የሚተላለፉትን ለይተን የምዘና ስራ መስራት ጀምረናል። የስኳር እና የቴሌ የተሻለ ሁኔታ ላይ ያሉ ሲሆን፣ በቀጣይነት ደግሞ ሌሎቹን የምናይበት እድል ሰፊ ሆኗል። አንዳንዶቹ ከመሸጥ ይልቅ ሌላ ማስተካከያ ማድረግ ይመረጣል። ለምሳሌ ሎጂስቲክስ ላይ መሸጥ አያዋጣም። ዘርፉን ክፍት ማድረግና ለዚህ ደግሞ አጋር መፈለግ ነው። በመሆኑም ለእያንዳንዱ ዘርፍ የትኛው የተሻለ ነው? መሸጥ ወይስ ሌላ ማስተካከያ አድርጎ ትርፋማ ማድረግ የሚለውን በወሳኝነት እየተሰራበት ነው፤ ሁኔታው በአጠቃላይ በዚህ መልክ እየተጓዘ ነው።
ዘመን ፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እርዳታና ድጋፍ ላይ በመመርኮዙ ሳቢያ እንደ እነ አሜሪካ ያሉ አገራት ጭምር ፖሊሲያቸውን ሊያስፈጽሙበት እየሞከሩ ነው። ኢኮኖሚው ከዚህ ጫና የመላቀቁ ተስፋ ምን ድረስ ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- እውነት ነው ምንም ጥያቄ የለውም። አሁን ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የልማት አጋሮች ድጋፍ ያስፈልገዋል። ይህን ድጋፍ በአግባቡ ማሰባሰብ እና መምራት አንዱ የምንሰራው ስራ ነው። ነገር ግን በሪፎርሙ አመታት ያየነው አንዱ እና በብልፅግና ፍኖተ ካርታ ውስጥ ያካተትነው ነገር እንዴት አድርገን ነው በኢኮኖሚ ራሳችንን የምንችለው የሚለው ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል። የራሳችንን ወጪ በራሳችን ገቢ መሸፈን መቻል የሚል እሳቤ ትልቅ አቅም እና ሀይል ነው።
ሁለተኛ፣ ምርታማ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቀለበው ስንዴ ምርታማ እንዳይሆን መደረግ የለበትም የሚለው ነው። በዚህ ረገድ ሴፍቲኔት ወረዳዎች በሚባሉት ላይ ያመጣነው የአተያይ ለውጥ በጣም ስር ነቀል ነው። ሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበሩ ወረዳዎች ዛሬ በምግብ ራሳቸውን ችለዋል። ስንዴ አምርተው፤ ከራሳቸው ቀለብ ተርፎ ምርቱን ለገበያ ሲያቀርቡ ማየት ተችሏል። እነዚህ ነገሮች ተጠናክረው ከቀጠሉ በእርግጥ ይህ ለውጥ በአንድ አመት ውስጥ የምንጨርሰው አይደለም። ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ላይ የተንተራሰ በመሆኑ ለመለወጥ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ነገር ግን መሰረታዊ ስራዎችን መስራት በመጀመራችን መሰረታዊ የሆነ ለ ውጥ ማየት ጀምረናል።
ሌላው የአለም አቀፉ ጫና የጠቀመን የሚመስለኝ በሚገባ ወደ ውስጥ እንድናይ አስችሎናል። እንዴት ነው ጠንካራ እና ዘላቂ ኢኮኖሚ መገንባት የምንችለው የሚለውን እንድናይ አድርጎናል። በርከት ያሉ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጡ የፖሊሲ እርምጃዎች ተወስደዋል። ብዙ ቢቀረንም፤ የአለም አቀፉን ጫና መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ እየገነባን ነው። በቀጣይ በመንግስት የሚገለፁ ጉዳዮች በመሆናቸው አሁን ላነሳቸው የማልችላቸው ትልልቅ ኢኒሼቲቮች አሉ። በአዲሱ ዓመት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ፤ በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት የተደረገባቸው ትልልቅ የኢኮኖሚ ኢኒሼቲቮች አሉ።
ዘመን፡- ኢትዮጵያ በርከት የሚሉ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች። የዶላር ምንዛሬው ደግሞ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ሀገራችን ይህን እንዴት እየተቋቋመችው ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡ – የውጭ ምንዛሬ ተመኑን በሚመለከት ደጋግመን እንደምናነሳው እጅግ በጣም የተበላሸ ነው። ይህ ብልሽት ደግሞ በዋናነት የሚጎዳው ደሀውን የህብረተሰብ ክፍል ነው። ይህን ጉዳይ በጣም መገንዘብ ያስፈልጋል። የባንክ ሰራተኛው አሊያም ነጋዴው ስንጥቅ እያተረፈበትና የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እያገኘ ደሀው ላይ የሚፈጠረው ጫና በጣም ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ነው። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ ሊገልፀው አይገባም። ይህን ጉዳይ መቀየር አለብን ብለን ጀምረናል፤ ግን ደግሞ በአንድ ጀንበር የሚያልቅ አይደለም። ጊዜ ይፈልጋል። በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም አሉ።
አንዱ ቁልፍ ስራ የኤክስፖርት ምርቱን ማሳደግ ነው። በአንድ አመት ውስጥ 600 ሚሊየን ዶላር ኤክስፖርት የተደረገበት ሁኔታ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ሁለተኛው የአገር ውስጥ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ነው። በዚህም ረገድ ጥሩ ሂደት ላይ እንዳለን ማየት ትችላለህ። ከዘይት ጀምሮ ሌሎችንም ምርቶች እንዲሁ። ሰሞኑን ያወጣነው የታሪፍ መፅሐፍ ከስምንት ሺ በላይ የታሪፍ ዋጋ የተሻሻለበት ነው። ዋና ትኩረት የነበረው ለመጀመሪያ ጊዜ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪን እንዴት እንደግፍ የሚለው ነው። ይህ በጣም ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው።
ከዚህ በፊት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ነበር፣ ግን የትኛው ምርት ነው በአገር ውስጥ እንዲመረት የተፈቀደው፣ ለውጭ ገበያ የምናመርተውስ የትኛው ነው የሚለው የተናበበ ፖሊሲ አልነበረውም። ያን ማስተካከላችን ላሰብነው አጠቃላይ የሪፎርም ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ስለዚህ ገበያው ላይ ያለውን የተበላሸ የውጭ ምንዛሬ ማስተካከል ያስፈልጋል። እሱንም እየሰራንበት ነው፤ በቅርቡም የተወሰዱ እርምጃዎች አሉ።
አሁን በቅርብ የተፈጠረው የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ የኢኮኖሚው መሰረት የሚገልፀው አይደለም። ከአሻጥር ጋር የተገናኘ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ሀብት ለማሸሽ በሚደረግ ሩጫ ጭምር መሆኑን መገመት አያስቸግርም። ምክንያቱም ምንም የተቀየረ የኢኮኖሚ መሰረት የለም። ያም ሆነ ይህ ግን ባስቀመጥነው ጊዜ ውስጥ ገበያው ላይ ያለውን ችግር ፈትተን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ የማይገልፀው መሆኑን ማረጋገጥ በጣም ወሳኝ ነው።
ዘመን ፡- መንግሥት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የሚሰጡትን አስተያየትና ምክረ ሀሳብ ለማስተናገድ ያለው ዝግጁነት ምን ድረስ ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- እዚህ ላይ ምንም ጥያቄ የለውም የባለሙያዎችን አስተያየት እና ምክረ ሀሳብ ዋጋ ከመስጠት ባለፈ ገለልተኛ የአማካሪ ምክር ቤት አቋቁሟል። ከየትኛውም መስመር ለመጣ ሀሳብ በጣም ክፍት የሆነ ነው። ከዚህ በፊት እኔ ራሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እያለሁ መጀመሪያ ያደረኩት አሉ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ሀሳብን መጋራት ነው።
ገለልተኛ የአማካሪ ምክር ቤቱ ነፃ እና ሙያዊ የሆኑ ሀሳቦችን እንዲያቀርብ፤ እነዚህን ሀሳቦች ደግሞ መንግስት በጥንቃቄ ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ መቻል ነው። የባለሙያ ሀሳብን በሚመለከት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በማስመልከት ሰፊ የሆነ ገለልተኛ የባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ጥቅም ላይ ውሏል። ባለሙያዎችን ማማከር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ሁኔታው በሙሉ ካለፈው ስርዓትና አካሄድ በአሰራርም በዓይነትም የተለየ በመሆኑ አካታች የሆነ ኢኮኖሚ እየተገነባ ነው። መንግስት አሁንም ደግሞ ደጋግሞ አባካችሁ ሀሳባችሁን በደንብ አቅርቡልን ነው መልሱ።
ዘመን ፡- ከሀገር ሠላም ማጣት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች ባለሀብቱ እምነት ኖሮት ሀብቱን ኢንቨስትመንት ላይ እንዳያውል ተጽዕኖ አሳድረዋል። በመሆኑም ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ምን አይነት ዘዴ ዘይዷል?
ዶክተር ኢዮብ፡- በመጀመሪያ ኢንቨስትመ ንቱን የመራንበት መንገድ ትልቅ ችግር ነበረው፤ ምንም ጥያቄ የለውም። ‹‹ኢንቨስትመንት መጣብህ ሳይሆን መጣልህ›› መሆን ነበረበት። የምንሰራው ኢንቨስትመንት ለማህበረሰቡ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድል የሚፈጥር መሆን አለበት። በዚህ ረገድ የነበረውን ክፍተት ለማሻሻል ብዙ ስራ እየተሰራ ቆይቷል። ነገር ግን አጠቃላይ የፖለቲካ ኢኮኖሚውም ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም። ኢ-ፍትሀዊነት ነበር፤ ፍትሀዊነቱ አለመረጋገጡ ብቻውን ኢንቨስት መንቱን እንዲጠራጠር አድርጓል። አሁንም ህዝቡ የራሱን ማንነት አክብሮ ምርጫውን አከናውኗል።
ሰዎች የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል እና ዳራ አላቸው። በመሆኑም ለሁላችን የምትሆን አገር በመገንባት ረገድ በርካታ ስራዎች መስራት ይገባል። ኢንቨስትመንቱ ህብረተሰቡን ምን ያህል ጠቅሟል? የሚለውን በሚገባ መመልከት ይጠይቃል። በመሆኑም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በዚህ ልክ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒው ግን፣ የህዝቡን መሰረታዊ ችግር ያልተረዳ የብሔር ቁማር የሚጫወቱ ግለሰቦች፤ በህዝብ ስም የሚነግዱ የብሔር ነጋዴዎች በየቦታው አሉ። ነገር ግን ህዝቡ የተለያየ ባህል ያለው አብሮ መኖር የለመደ ነው። የጋራ ማንነት ያለው ህዝብ ነው። የህዝቡን በሰላም መኖር የማይፈልጉ ሆነው የህዝቡን የሰላም መሰረቶች የሚረብሹ አሉ። እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ትርክት ይዞ የመጣው መንግስት ነው። ትናንት የተለያየ አመጣጥ ነበረን፤ ነገር ግን ለሁላችንም የምትሆንና የምትጠቅም የጋራ አገር መገንባት ይቻላል፤ ያስፈልጋልም።
በመሆኑም፣ መንግሥት ይህን የሚያስተካክል አዲስ ትርክትና እይታ ይዞ መጥቷል። ይህ በእርግጥ ብዙ ርቀት ያስኬደናል። ነገር ግን ባለፈው ስርዓት የነበረው ትርክት ሰዎችን ከሰዎች የሚያጋጭ፣ ብሄር ብሄረሰቦችን እንዲሁ የሚያጋጭ ነበር። ይህ በእርግጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጠባሳው ታይቷል። ይህ ደግሞ በአንድ ምሽት የሚለቅ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይህን እንደማይፈልገው በሚገባ በምርጫው አሳይቷል። በሚገባ እንሰራበታለን።
ዘመን፡- ከስራ አድል አኳያስ ግለሰቦች ወደሚፈለጉት ቦታ/ክልል በመሄድ እንደ ቀድሞው ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ካፒታል ድንበር የለውም። መንቀሳቀስ አለበት። እንደ አንድ አብሮ እንደሚኖር ህዝብ የተሳሰረ ኢኮኖሚ ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ ጎጃም ያለ የዘይት ፋብሪካ ከጎጃም ጀምሮ እስከ ግማሽ ወለጋ ድረስ ሰሊጥና ሌሎች ግብዓቶችን አምርቶ ትስስሩን የበለጠ ማጠናከር አለበት። ከአንድ ክልል የሚመጣ አንድ ወሳኝ ግብዓት ሌላ ክልል ላለ ኢንዱስትሪ ወሳኝ አቅም ይሆናል። በዚህ ረገድ የነበረው የተንሸዋረረ አተያይ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንቱ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሯል።
በመሆኑም ዛሬ ይህን ትስስር መጠበቅ ግድ ይላል። አሁን እየዘረጋን ያለነው ስርዓት እንደ ትናንቱ አፈናቃይ ሳይሆን ሰዎችን አካቶ የሚሰራ መሆን አለበት። ይህ ቁልፍ ነገር ነው። በዚህ ረገድ በተለይ የማዕድን ልማት ላይ በትኩረት እየሰራን ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው የኢንቨስትመንት አስተዳደሩ አይኑ የጠፋ ነበር። ዛሬም ብዙ ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉት። የመሬትና የኢንቨስትመንት ፍቃዶች ወራት ነው የሚፈጁት። ቀላል አይደሉም፤ አሰልቺ ናቸው። ካነሳኸው ቁልፍ ችግር ጀምሮ እነዚህን ነገሮች በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ማስወገድ ትልቁ ስራችን ነው። ይስተካከላል የሚል እምነት ይዘን እየሰራን ነው። ይህ ቢዝነስን የማቅለል ስራ ብዙ ርቀት የተጓዘ ነው። ይህ ይሁን እንጂ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ። በተለይ ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ ብልፅግና ይዞት የመጣው መንገድ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት ተይዞ እየተሰራ ነው።
ዘመን ፡- የመንግስት የበጀት ጉድለትን ለማሟላት በሚደረግ ትግልና በገበያ ውስጥ ያለው የገንዘብ አቅርቦት በመጠን እንዳደገና ይህም ለዋጋ ግሽበት እንደዳረገ ባለሙያዎች ይናገራሉ። መንግስት ይህን አስተያየት እንዴት ይመዝነዋል?
ዶክተር ኢዮብ፡- ታሪኩን በሚገባ ካየኸው ትክክል ነው። የዋጋ ግሽበቱ በአማካይ 15 በመቶ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ወጪ ነበረ። ይህ ደግሞ ከኢኮኖሚው በመነጨ ሳይሆን ከፖለቲካው ክንድ የመነጨ ነው። በወቅቱ መንግስት ወጪውን ከብሔራዊ ባንክ ያሟላ ነበር። በዚህ ረገድ ዛሬ የለውጥ መንግስቱ ትልቅ ለውጥ ነው ያመጣው። በሪፎርሙ የተሰራው ትልቅ ስራ ገንዘብ ሚኒስቴር በፈለገበት ሰዓት ብሔራዊ ባንክ ካዝና እየሄደ የሚጠይቅ ሳይሆን ወጪውን ካለው ገቢ እና አዋጭ ስራዎች አኳያ በበጀተው ልክ የሚራመድ ነው።
አንደኛ፣ ከብሔራዊ ባንክ ስትወስድ ወጪው ያሳስብሀል ገንዘቡን ከፍለህ ነው የምታመጣው። ሁለተኛ፣ መንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ገንዘብ ነው የሚጠቀመው እንጂ እንዲሁ ከባንክ የሚወስድ አይደለም። በዚህ ረገድ በ20 እና 25 እንጀምራለን ብለን ወደ 120 ቢሊየን በላይ ነው ቢል የገዛነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ስራ ተሰርቷል። የተሰራው ስራ መመስገን የሚችል ነው። እንዲህ ማለት ግን ጎዶሎነት ስላለው ዛሬ አሊያም አምና የሰራኸው የፖሊሲ ለውጥ ለውጡ ዘግይቶ የምታየው፤ ቀስ ብሎ ነው የሚመጣው። የዘርፉ ባህሪ ችግሩ የሰራኸውን ስራ ወይም ለውጥ በአጭር ጊዜ አታይም።
ዘመን ፡- የመንግሥት የገንዘብ ቁጥጥር የላላ ነው በሚለው የባለሙያዎች አስተያየት ላይስ የእርስዎ ሐሳብ ምንድነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- እውነቱን ለመናገር የገንዘብ ቁጥጥሩን በሚመለከት ክፍተት አለው። በዚህ አመት የግል ባንኮች የገንዘብ ብድር 65 እስከ 70 በመቶ ጨምሯል። ይህ ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ አቅም አለው። በአንድ በኩል ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመፍጠሩ እንዳልከው የዋጋ ንረት ሊኖረው ይችላል። እንደዚህም ሆኖ ዘንድሮ የብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ ተጠባባቂ ገንዘብ እድገት በጣም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ይሄንን ጠበቅ አድርገን መያዝ ያስፈልጋል።
ነገር ግን ይህን ትልቅ ችግር ነው ብለን እንሰራለን ማለት ነው። በዚህ ረገድ መንግስት የፖሊሲ ለውጥ አድርጎ ነው ያሻሻለው። አጠቃላይ የገበያ ስርዓቱ ላይ ያለው ችግር እና የምርትና ምርታማነት ጉዳይ ግን መሰረታዊ ነገር እንደሆነ በሚገባ ትመለከታለህ። ይሄም አሁን በያዝነው አያያዝ እያሻሻልን ችግሩን ትርጉም ባለው መልኩ እንቀይራለን በሚል ፅኑ እምነት እና ቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
ዘመን ፡- መንግሥት የግል ዘርፉን በገበያ አሳታፊ በማድረግና እንደ ሀገር ወጪን በመቀነስ ረገድ እየሄደበት ያለው ሂደት ምን ይመስላል? ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ኢዮብ፡- የግል ዘርፉ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ብዙ ለውጦች አሉት። እንዲያውም ምጣኔው የተገላቢጦሽ ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም ¾ የሚሆነውን ብድር መንግስት ይጠቀመው ነበር። አሁን 3/4ኛ ብድር እየወሰደ ያለው የግሉ ዘርፍ ነው። እናም አሁን ምጣኔው የተገላበጠ እንደሆነ ትረዳለለህ። ይህም ተሰርቶ፤ የፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ የመጣ ነው። በሪፎርሙ ከተሰራው ትልቅ ስራ ውስጥ አንዱ የግል ባለሀብቱ በኢኮኖመው ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ ማሳደግ መቻል ነው። በመሆኑም በጥልቅ ስታየው የግሉ ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተነቃቃ ነው።
በየትኛውም ሁኔታ መንግስት አስፈላጊውን አቅጣጫ ያስቀምጣል። የገበያ ጉድለት ያለበት ቦታ ላይ ደግሞ ይገባል። ነገር ግን እንደ ከዚህ በፊቱ ‹‹አባካኝ ሆኜ ልጓዝ›› የሚል አይደለም፤ አይችልምም። ለዚህም ነው መንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ እጁን እያወጣ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እያተኮረ አቅጣጫ የሚያሣየው። በዚህም የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የተሻለ ተሳታፊ እንዲሆን እድል ተከፍቷል። ነገር ግን፣ የግል ዘርፉ የማይተካቸው አሉ። በጀት ላይ የግል ዘርፉ የሚተካው ነገር የለም። መንገድ እና ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች የመንግስት ስራዎች ናቸው። ማህበራዊ ጉዳዮችም በመንግስት የሚሰሩ ስራዎች ናቸው። ዩኒቨርሲቲዎችን ማስፋፋት እና ሌሎች የጤናው ዘርፍ ስራዎች የመንግስት ግዴታ ስራዎች ናቸው። እነዚህን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው።
በሁለተኛነት ያነሳኸው ወጪን የመቀነስ ጉዳይ ትልቅ ስራ ነው። ይሄ ትልቅ ስራ እና ማሻሻያ የሚፈልግ ነው። ወጪን በሚመለከት እንደ ባህል መፈጠር ያለበት የሚያስፈልገንን ብቻ መሸመት መቻል ነው። እውነት ነው በግዥ ብቻ የሚያመልኩ አንዳንድ ተቋማት አክሳሪ ነበሩ። ይሄ መስተካከል አለበት በሚል ብዙ ስራ ተሰርቷል። ሌላው የመንግስት የግዥ ስርዓት በጣም ትልቅ ችግር ያለበት ነው። ለዚህ ሲባል በእርግጥ አዲስ የግዥ ስርአት አዘጋጅተናል። ይህ እንዲፀድቅልን ለምክር ቤቱ አቅርበናል።
ይህ የሚድበሰበስ ጉዳይ ሳይሆን ስር ነቀል የሆነ ተግባር የሚጠይቅ ነው። በዚህ ረገድ የተነሳው ሀሳብ ትክክል ነው ልንሰራበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ መግለፅ በቂ ይመስለኛል። እስካሁን የተጀመሩ ስራዎች እንጂ ለውጥ ያመጣ ስራ አልተሰራም። ፕሮጀክት ላይ ያለ አፈጻፀም፣ ጊዜና ወጪን ያልቆጠበ ስራ እጅግ አደገኛ ነው በሚል በኢኮኖሚው ላይ አጠቃላይ ሪፎርም እየተደረገ ነው ያለው። በዚህ ረገድም ከጅምሩ እንደምንገነዘበው ለውጥ የሚያመጣ አካሄድ ላይ ነን። ልነግርህ የምችለው ትልቁ ሀሳብ እነዚህ ባለሙያዎች ያነሱት ሀሳብ ትክክለኛ መሆኑን ነው።
ዘመን ፡- በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ግብርና በዝቅተኛ ግብዓት፣ ምርትና ኢንቨስትመንት እየተጓዘ መጥቷል። ይህን ለመለወጥ ምን እየተሠራ ይገኛል?
ዶክተር እዮብ፡- ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ድርሻ ትልቅ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ግብርና የተወራለትን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም ያልንበት አንዱ ምክንያት በሁለት እና ሶስት አመታት የጀመርናቸው ስራዎች በጣም የሚገርም ለውጥ ሲያመጡ ስታይ ይህን ዘርፍበአግባቡ እንደግፈው፤ ተገቢውን ኢንቨስትመንት እናድር ግለትና ምርታማነቱን እንዲጨምር ብናደርግ ምን ያህል መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል አሳይቶናል።
ስንዴ ላይ ለምሳሌ ብዙ ስራ ተሰርቷል። መሬቶቹ እኮ አዲስ አይደሉም፤ ትናንት የነበረ ነው። መሬት ጥሩ ነው ስለተባለ ብቻ በአንድ አመት ብቻ የሚታረስ መሬት ውስጥ ተካተው በተሰራው ስራ ዘንድሮ 15 ሚሊየን ኩንታል ተጨማሪ የስንዴ ምርት ማግኘት መቻሉ ግብርናው ላይ ምን ቢሰራ ምን ሊመጣ ይችላል የሚለውን በግልፅ ያሣየ ነው። ይህ ማለት ከውጭ በዓመት የምንገዛውን 17 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በአጭር ጊዜ መሸፈን ቻልን ማለት ነው።
በዚህ ረገድ፣ ሁሉንም የውሀ ሀብት ያለምንም ምክንያት ለልማት ማዋል መቻል ትልቁ እየተሰራበት ያለ ስራ ነው፤ ከወንዝ ጠለፋ ጀምሮ ውሀ ማቆርና ተያያዥ የግድብ ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው። ይሄ በግብርና ምርታማነት ላይ አዲስ እሳቤ ይዞ የመጣ ነው። በመሆኑም ግብርና የሰጠኸውን ስለሚሰጥህ በትኩረትና በጥረትህ ልክ ታተርፍበታለህ። በደንብ ኢንቨስት ካደረክ እና ከመራኸው ወጤታማ ነህ። ነገር ግን፣ እንደ ከዚህ በፊቱ ግብርናውን በስም እያቆለጳጰስከው ከተጓዝክ ፍሬ አልባ ሆኖ ታገኘዋለህ። እውነት ነው ዘርፉ ተጨማሪ ስራ ይፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በመስኖ እና በአጠቃላይ ግብርና ላይ ብዙ እየሰራን ብዙ መዋዕለ ንዋይም እየተመደበለት ነው። ብዙ ከሰጠኸው ብዙ ሊሰጥ እንደሚችል ስለሚታወቅ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። በዚህ ረገድ የግሉን ዘርፍ አቀናጅቶ በፖሊሲ አደራጅቶ በመስራት የበለጠ ማነቃቃት ይቻላል።
ዘመን፡- በአገራችን ‹ግብርና መር› እየተባለ የተመጣበት ጉዞ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዳይስፋፋ ማነቆ ሆኗል ሲሉ ባለሙያዎች ይወቅሳሉ። በዚህ ላይ እርስዎ ምን አስተያየት አሎት?
ዶክተር ኢዮብ፡- ይሄ ትክክለኛ አስተያየት ነው። ‹የእንትን መር፤ እንትን መር› የሚል አባዜ ነበረብን። ይህን ስህተት መቀበል ያለብን ጉዳይ ነው። ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ተናበው መሄድ አለባቸው። ለአብነት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ብትመለከት ከአካባቢህ ዝም ብለህ ከምታያቸው ተነስተህ፣ እነዚህ ነገሮች ለምንድን ነው ወደ ፊት ያልመጡት? የሚለውን ስትመለከት ‹‹እዚህ ማምረት አንችልም ነበር ወይ?›› ብለህ የምትጠይቃቸው ብዙ ናቸው። ለዚህ ጉዳይ ቀደም ሲል ያነሳሁትን የታሪፍ ማሻሻያዎች ለማየት ትገደዳለህ።
በመሆኑም፣ የታሪፍ መዋቅሩ እዚህ አገር ውስጥ እንዳይመረቱ የሚከለክል እና የማያበረታታ ነው። የገቢ ንግድን የሚደግፍ ሆኖ ብቻ ነው የተቀረፀው። ስለ ግብርና ብቻ ሳይሆን ማኑፋክቸሪንግ ላይ የፈለገ ብታወራ በፖሊሲ ካልደገፍከው ለውጥ አይመጣም። አሁን ያቀረብነው የታሪፍ ማሻሻያው መስረታዊ ለውጥ ያመጣል ያልኩህ ለዚህ ነው። በሁሉም ዘርፎች ላይ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ማተኮር አለብን። አሁን ይህ የታሪፍ ማሻሻያው ሲፀድቅ ብዝሀ ዘርፍ ያለው ሆኖ ለኢኮኖሚው የእድገት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚቸነከር አይሆንም። ያም ሆነ ይህ ግን፣ በትኩረት መያዝ ያለበት መንግስት ብቻውን የሚሰራው ጉዳይ አለመሆኑን ነው። በዚህ ረገድ ሪፎርሙ ሁለት መልክ አለው። አንዱ ሰፋ ታደርግና አንተ ያላሰብከው አዲስ ነገር እንዲመጣ ለግል ባለሀብቱ እድል ትፈጥራለህ። ከዚያም ደግሞ የለየሀቸውን ዘርፎች በፖሊሲ እየደገፍክ እንደ ማዕድን ያሉ ዘርፎችን ደግሞ ልዩ ትኩረት እየቸርክ የኢኮኖሚ እድገቱ እንዲበረታታ ታደርጋለህ።
አሁን ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ወደፊት ትልቅ ኢንዱስትሪ ሊሆኑ የሚችሉ አነስተኛ ተቋማት አሉ። እነዚህን በሚገባ በመደገፍ መጓዝ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ባለፈው አመት ልማት ባንክ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የብድር አገልግሎት አቅርቧል። በየቦታው የምታያቸው ዳቦ ቤቶች፤ አነስተኛ ማኑፋክቸሪንጎች፣ ግብርና ስራዎችን አሳድገው ሰፊ ቦታ ኖሯቸው ብዙ ሊሰሩና ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። እነዚህን ማብዛትና መደገፍ ያስፈልጋል።
ሌላው አገልግሎት እና ኢንደስትሪ ያለው ግንኙነት ነው። በኢንዱስትሪውና በግብርናው መካከል ያለው ግንኙነት ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስታስብ ፓርኩ ውስጥ ያለውን ስራ ብቻ አይደለም። በዚህ ዙሪያ በርካታ የአገልግሎት ስራ አለ። ግብዓት የሚያቀርብ አለ፤ ምርት የሚያወጣ አለ፤ ምግብ የሚያቀርብ አለ፤ ቤት የሚያቀርብ አለ፤ ተፈጠረ የምትለው ስራ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የፈጠረው አገልግሎት አንድ ላይ በድምር ታይቶ መሆን አለበት። አንድ ላይ ማየቱ በጣም ጠቃሚ ነው።
ዘመን ፡- ማህበረሰቡ በዋጋ ንረት እጅግ እየተማረረ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በቀጣዩ አዲስ አመትም ተባብሶ እንዳይቀጥል ከብልጽግና ፓርቲ ምን ይጠበቃል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ኢዮብ፡- ህዝቡ የብልፅግና ፓርቲን የመረጠው ወደፊት ለሚሰራው ስራ ነው የሚል እምነት አለኝ። ህዝብ የመግቢያ ፍቃድ ሰጥቶታል ብሎ መውሰድ ይቻላል። በሚቀጥለው አምስት አመት እድል እንስጥህ፤ አገልግለን ብሎታል። ይህ የሚከብድ ኃላፊነት ነው። በዚህ ደረጃ ህዝብ ለሰዓታት ቆሞ ሲመርጥህ የሚጥልብህ የቤት ስራ ትልቅ ነው። እውነት ነው ብዙ ስራ መስራት አለብን።
ኑሮን ከማሻሻል፣ የስራ እድል ከመፍጠር፣ አገልግሎት ከማሻሻል መንግስት ለህዝብ አቅም የሚሆንበትን ለመፍጠር ብዙ ይሰራል። የኑሮ ውድነቱ እንደ አጋጣሚ ተደራራቢ ችግር የነበረበት ነው። የፀጥታ ችግር አለ፤ ዓለም ላይ የኮቪድ ክስተት አለ፤ በዚህም የብዙ ነገር ዋጋ ጨምሯል። በዚህም ሸቀጦች 100 ፐርሰንት የጨመሩበት ነው። ይህ በሁሉም ነገሮች ላይ የታየ ነው። ይህ በድምሩ ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው። ይህንን ጫና ለመቀነስና የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ወገባችንን ጠበቅ አድርገን መስራት አለብን። ህዝብም የመረጠን እንድናገለግለው በመሆኑ እንሰራለን። በመሆኑም ህዝቡን ሰርቶ መካስ ያስፈልጋል። በጥቅሉ ኑሮን ብቻ ሳይሆን በርካታ ጥያቄዎቹን በስራ ለመካስ አቅደን እየሠራን ነው። አንዳንዱ በቀጣይ ለህዝብ የሚገለፅ ይሆናል በአጠቃላይ ችግሩን በሚገባ እንፈታለን።
ዘመን፡- ብልፅግና እንደ መንግስት በ2014 ዓ.ም ይፈተንባቸዋል ተብሎ የሚታ ሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ኢዮብ፡- እውነት ነው የምንፈተንባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። አንዱ ምንም ጥያቄ የሌለው የዋጋ ግሽበት ነው። ይህ ብዙ ከፈታናቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ በሚገባ የምንሰራበት ጭምር ነው። ይሄ እንሰራለን ብለን ያሰብነው ትልቅ ጉዳይ ነው። መፈታት ያለበት ከባድ የማይክሮ ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። በሁለተኛነት ፈተና የሆነው እና እየሆነ ያለው አገልግሎት አሰጣጣችን ነው። ህብረተሰቡ መታወቂያ ለማውጣት ጉቦ መክፈል የለበትም። ለአንድ አጭር አገልግሎት በርካታ ሰዓታትን ማጥፋትም የለበትም። አሁን ያለው ሀቅ ግን እንግልት ነው። ይህን ከመሰረቱ መፍታት ይገባል። ህዝብን ከሚያማርሩ ነገሮች አንዱ አገልግሎት ዘርፉ ላይ ያለው ችግር ነው። በሶስተኛነት አለም አቀፍ ጫናውን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ነው። በዚህ ሶስት አመት ውስጥ በኤክስፖርት፣ በገቢ ከፍተኛ ውጤት ያየንበት ነው። አሁንም ችግርን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መሆኑን ማሳየት አለብን ብለን ተገቢውን ስራ እየሰራን ነው።
ዘመን ፡- የግል ባለሀብቱ በቀጣይ ጊዜያት በኢኮኖሚው ዘርፍ ዋና ተዋናይ እንዲሆን ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?
ዶክተር ኢዮብ፡- የሀገር ልማት የጋራ ስራ ነው። አጠቃላይ ሀገራዊ ልማት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ድምር ነው። ልማት ሊመጣ የሚችለው ሁሉም የድርሻውን መወጣት ሲችል ነው። በዚህ ረገድ መንግስት የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት ላይ በጣም ሰርቷል። በዚህ መሰረት መንግስት አቅጣጫ አስቀምጧል። መንግስት የግል ባለሀብቱ በኢኮኖሚው በስፋት እንዲሳተፍ ያለውን ቁርጠኝነት በሚገባ ተረድቶ ዘላቂ አገራዊ ልማት ላይ መሰማራት አለበት። በዚህ ረገድ መንግስት ባመቻቸው መስመር በመጓዝ ማንንም ሳይጠብቅ አገሩን ማልማት አለበት።
ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መል ዕክት ካለ?
ዶክተር ኢዮብ፡- የማስተላልፈው መልዕክት የተሻለች እና የበለፀገች ኢትዮጵያ፤ ሰላሟና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመርነውን ጉዞ ከአመታት በኋላ ዞር ብለህ ስታየው በትክክልም ጉዞውን ጀምረናል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ሁሉም ባለድርሻ ከልጅ እስከ አዋቂ ከመንግስት እስከ ግለሰብ ሁኔታውን ተረድቶ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ አደራ እላለሁ፣ ጥሪም አቀርባለሁ።
ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር እዮብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ሀብታሙ ስጦታው
ዘመን መጽሔት ነሐሴ 2013 ዓ.ም