በልጅነታቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በክረምት ወቅት ከሠፈር ልጆች ጋር ተሰባስበው እግር ኳስ ይጫወታሉ፤ ፈረስ ይጋልቡም ነበር።መኪና እና አውሮፕላን ሣያዩ ገመዶች የመጠላለፍ ዓይነት ጨዋታ ይወዱ ነበር።ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ መማራቸው ተቻችሎ መኖርን፣ ትዕዛዝ ማክበርን፣ ለፈለጉት ዓላማ ዋጋ መክፈልን፣ ወዘተ… ተለማምደውበታል።ማሻም ይሁን ጌጫ ሲማሩ ከወላጆቻቸው ተለይተው ነው።የኖሩባቸውን ዘመዶች የሚችሉትን ማንኛውንም ሥራ በመሥራት እያገዟቸው ነው የተማሩት።ከትምህርት መልስ ማታ… ማታ ባረፉበት የዘመድ ጠጅ ቤት ውስጥ ጠጅ በመቅዳት ያግዙ ነበር።የ13 ዓመት ልጅ ሆነው ሚዛን ተፈሪ ስምንተኛ ክፍልን ሲማሩም ከአንድ ልጅ ጋር አብረው በመኖር እንጀራ እየገዙ ሽሮ እየሠሩ ነበር የሚመገቡት።ብስክሌት ከሌሎች ተቀብለው ሃያ እና ሠላሳ ሣንቲም ለማግኘት ያከራዩ ነበር።
ሥራ ወዳዱና ታታሪው ሰለሞን በጎሬ ሚሽን ሆስቴል ውስጥ ወላጆቻቸው እየከፈሉላቸው ቢማሩም እሣቸው ግን በድርጅቱ ውስጥ እንደተቀጣሪ ሆነው ነበር የሚሠሩት።ፈረንጆቹን ያግዛሉ፣ ግቢውን ከማጽዳት እስከ መኪና ማጠብ ዓይነት ሥራዎችን በራሳቸው ተነሣሽነት ይሠሩም ነበር።የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳዎች 20 ሜትር በ700 እና በ800 ሜትር የሚሆን በበሬ በማረስ በኋላም ተሻሽሎ በዶማና በአካፋ ብቻቸውን ያስተካክሉ ነበር።የዚያን ጊዜ ከአውሮፕላን ጋር መተዋወቃቸው አሁን ላሉበት የሙያ ዘርፍ ውስጥ ለመግባት ሙሉ ለሙሉ በሩን ከፍቶላቸዋል።ሕልማቸውን ሁሉ በዚያ ዙሪያ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል።ጅማ አሥራ አንደኛ ክፍልን ሲማሩ ለተለያዩ ሚስዮን ጣቢያዎች ዕቃዎችን እየገዙ የመላክ ሥራ ይሠሩ ነበር፤ ለዚህም ተግባራቸው ይከፈላቸው ነበር።ባገኙት ገንዘብ ብስክሌት ገዝተው ከጓደኞቻቸው ጋር ይጠቀሙበት ነበር እንጂ ለአልባሌ ጉዳይ አያውሉም።ኮሌጅ ካገኙት እውቀት ባልተናነሰ ከእነዚያ ቦታዎች ያገኙት ተመክሮ ብዙ አስተምሮኛል ብለው ያስባሉ።
አሥራ አንደኛ ክፍል ሳሉ የደርግ ሥርዓት መጥቶ የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ታወጀ።ከዘመቻው መልስ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ያለው ፓለቲካዊ ሁኔታ አዳጋች ሆነባቸው።በወቅቱ በሀገር ደረጃ ትልቁ ነገር ላለመሞት ትግል ይደረግ ስለነበረ ለዚህ ትግል እንዲረዳቸው ቴፒ ይኖሩ የነበሩ እናታቸው የአንገት ሐብላቸውን ሸጠው እንዲጠቀሙበት በፓስታ አድርገው ልከውላቸዋል።ከዚያም አዲስ አበባ መጥተው ገነት ሆቴል አጠገብ ጋሽ ብሩ የሚባሉ ሰው ጋራዥ መሥራት ጀመሩ።ጋሽ ብሩም የሥራ ትጋታቸውንና ታማኝነታቸውን በማየት እምነት ሲጥሉባቸው ታክሲ እንዲነዱ መኪና ሰጧቸው።ታክሲ እየሠሩ ሕይወታቸውን በመምራት ላይ ሳሉ አዲስ አበባ ያለው ሁኔታ ደስ አልል ሲላቸው ሻሸመኔ ወንድማቸው ዘንድ ለመኖር ሄዱ።እዚያም የመኪና ሹፌር ሆነው ተቀጥረው ከሻሸመኔ ወንዶ ገነት፤ ከሻሸመኔ ደብረዘይት ሠሩ።በዚህ ጊዜ አሥራ ሁለተኛ ክፍልን የማታ ተማሩ።በኢህአፓ ወይም በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ላለመግባት ወስነው እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሣይገቡ በሕይወት ኖሮ ለመቀጠል ሲሉ ወደ ሦስት ዓመት አካባቢ ከትምህርት ውጭ ሆነው የተለያዩ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡
ሥደት
ቀደም ሲል የሚያውቋቸውን በወቅቱ አሜሪካ የነበሩትን ሚሲዮናውያንን ወደ ውጭ እንዲወስዷቸው ጠይቀው ፈቃደኛ ቢሆኑላቸውም ሀገር ውስጥ ያለው ሂደት ወደ ሦስት ዓመት አካባቢ ጊዜ ፈጅቶ መጋቢት 1972 ዓ.ም ተሳክቶ ወደ አሜሪካ ሄዱ።እዚያም ሄደው ሚስዮኖቹ ዘንድ ቆይተው መስከረም ላይ ስኮላርሽፕ አግኝተው ትምህርት ጀመሩ።የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ስኮላርሽፕ በመጠቀም ተማሩ።ሚስዮናውያኑ እሳቸውን ለማስተማር ገንዘብ ከተለያዩ ቦታዎች እያፈላለጉ እየከፈሉ እንደሚያስተምሯቸው በመረዳት ‹‹መሥራት እችላለሁ፤ ስለዚህ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሠርቼ ራሴን ማስተማር አለብኝ›› በማለት ወሰሠኑ።ኮሌጅ ውስጥ ሠሀን ማጠብ፣ ምግብ ማቅረብ፣ ሣር ማጨድ የመሣሰሉ ሥራዎችን በመሥራት ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ ገንዘብ በመክፈል ተምረዋል።በተጨማሪም አንድ ቦታ ሁለት ሠዓት፣ ሌላ ቦታ አራት ሠዓት፣ እንደገና ሌላ ቦታ ስምንት ሠዓት የትርፍ ጊዜ ሥራ በመሥራት ቅዳሜና እሁድ ሕልምና ምኞታቸው የነበረውን አውሮፕላን የማብረር ትምህርት ከፍለው በመማር የሥነ መለኮትና የቢዝነስ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት አጠናቀዋል።የጀመሩትንም ትምህርት አጠናቀው የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል።ከዚህ በኋላ ደግሞ ተፈላጊነታቸውን ለማስፋት በማሰብ አውቶብስ በመንዳት፣ ፋብሪካ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት በሚከፈላቸው ገንዘብ የአውሮፕላን ጥገና ትምህርት ከፍለው ተምረዋል።
አውሮፕላን ማብረር
የአውሮፕላን ጥገና ትምህርቱን ካጠናቀቁ በኋላ አሜሪካ በሚገኝ አየር መንገድ ውስጥ አውሮፕላን የማብረር ሥራ መሥራት ጀመሩ።በመቀጠል በልጅነታቸው ያዩት የነበረውን በሽተኞችን የመርዳትና የዕርዳታ በረራዎችን ሥራ ለመሥራት ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የጉልበት ሥራ ይሠሩበት የነበረው የበረራ ድርጅት ውስጥ በአብራሪነት እንዲቀጥሯቸው አመለከቱ።በድርጅቱ ለመቀጠር አውሮፕላን ማብረርና መጠገን እንደመሥፈርትነት ይቀመጥ ነበር፤ ባላቸው ብቃት ብዙ ፈረንጆችን በልጠው በመመረጣቸው ድርጅቱ ተቀብሏቸው መጀመሪያ ሃይቲ፣ በመቀጠል ዑጋንዳ ተልከው ሠርተዋል።በመጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት ተሣክቶ በ1989 ዓ.ም በሚሠሩበት አየር መንገድ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።በዚህም ሁለት ዓመት አካባቢ እንደሠሩ ድርጅቱ ከሀገር እንዲወጣ ስለተጠየቀ ወጣ።ለካፒቴን ሰለሞን ሌሎች ሦስት ሀገሮች ሄደው እንዲሠሩ በድርጅቱ እንደ አማራጭ ዕድሉ ቢሰጣቸውም እሣቸው ግን ከኢትዮጵያ መውጣት ስላልፈለጉ አልተቀበሉትም፡፡
የግል አውሮፕላን ባለቤት
የሚሠሩበት ድርጅት ከኢትዮጵያ ሲወጣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመሩ።ዑጋንዳ ለሥራ ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በጣም ይፈልጉ ነበር።ሀገሬ ሄጄ አንድ ቀን የግል አውሮፕላን ቢኖረኝ እያሉ ይመኙ ነበር።ወደ ኢትዮጵያ ለበረራ ሥራ መጥተው በሚሠሩበት ጊዜ በበረራ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለመመልከት ዕድል ተፈጠረላቸው።እነዚህን ክፍተቶች ከሞላ ጎደል ይሠሩበት የነበረው ድርጅት ይሸፍን ነበር።ድርጅቱ ሲወጣ ክፍተቶችን መሙላት ያስፈልግ ነበር።እሣቸው አውሮፕላን ያበራሉ፤ የጥገና አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፤ ያሉት ሀገራቸው ላይ ነው፤ ፍላጎቱ አላቸው።ታዲያ ‹‹ለምንድን ነው ራሴ ይህን ክፍተት የማልሞላው›› ብለው አሰቡ።99 በመቶ ችግሩ አውሮፕላን የላቸውም፤ የሚያገኙበትንም መንገድ አያውቁም።ከኢትዮጵያ የተባረረው ድርጅት ውስጥ 11 ዓመታት አገልግለዋል።ሥራቸውን ስለሚያደንቁ በየዓመቱ የማበረታቻ ሽልማት ተሸልመዋል።በግል የአውሮፕላን ማብረር ሥራ በኢትዮጵያ ለማቋቋም ሐሳቡ እንዳላቸው ድርጅቱን ሲያማክሩ ‹‹ፈቃድ ካገኘህ አውሮፕላን እንሰጥሃለን›› ተባሉ።በማይታመን መልኩ በሦስት ወር ውስጥ ፈቃዱን አወጡ።ለዚህም በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን አሁንም ወደፊትም በሕይወቴ እስካለሁ ድረስ አመሠግነዋለሁ ይላሉ።እሣቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከመንገዱ ወጥቶ ፎርም እንደዚህ ነው የሚሞላው፣ ይኼን እንደዚህ አድርግ፣ ይኼን በዚህ መልኩ አስተካክል ብሎ እጃቸውን ይዞ መንገዱን መራቸው።
ፍቃዱ ከተገኘ በኋላ አውሮፕላን የሚሰጧቸውን ሥርዓት ባለው ሁኔታ ማነጋገር ጀመሩ።አውሮፕላን ለማግኘት ባደረጉት እንቅስቃሴ ውስጥ በሕይወታቸው ትልቁ ተግዳሮትን ተጋፈጡ።ቀደም ሲል እንደብርቅ የሚያዩዋቸው፣ የሚያደንቋቸውና የሚያከብሯቸው ነጭ ፓይለቶችና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ‹‹እንዴት ለአንድ ጥቁር፣ አፍሪካዊ አውሮፕላን ይሰጣል? እሱ ምን ስለሆነ ነው?›› በሚል የቅናትና የምቀኝነት ጦርነት ተከፈተባቸው።በዚህም ሣቢያ አውሮፕላን ለማግኘት ግፋ ቢል ሁለት ወር ይፈጃል የተባለው ሂደት ስምንት ወር ገደማ ፈጅቶ ተጠናቀቀ።በሰባት ዓመት ተከፍሎ በሚያልቅ ብድር ውል ገብተው አሜሪካ ሥሪት የሆነ ሴሲና ካራቫን የሚባል ከ10 እስከ 12 ሰዎች የሚይዝ አውሮፕላን አዲስ አበባ በ1992 ዓ.ም አመጡ።
ውሉ በጣም አሣሪ ነበር፤ አሣሪነቱና የማያንቀሳቅስ መሆኑ ግን አላስከፋቸውም።እሥሩን ለመፍታት ሲሉ ተግተው መሥራት እንዳለባቸው ተገንዝበው በመተግበራቸው በሰባት ዓመት ማለቅ ያለበትን ብድር በአራት ዓመት ተኩል ከፍለው ዕዳቸውን አጠናቀቁ።በመሃል ሌሎች አውሮፕላኖችንም በብድር ገዙ።አሁን አቢሲኒያ በረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ የሚል ድርጅት በመክፈት ከፍተኛው እስከ አሥራ አራት ሰዎች የሚይዝ የ17 የተለያዩ አውሮፕላኖች ባለቤት ናቸው። የአገልግሎት አድማሣቸውን በማስፋት ከአራት የበረራ ሙያተኛ ከማሥመረቅ ተነስተው እስከ አሁን ከ150 በላይ ፕሮፌሽናል ፓይለቶችን አሥመርቀዋል። አብዛኞቹ ተመራቂዎች ኢትዮጵያውያን ይሁኑ እንጂ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ባለሙያዎች አሠልጥነው አሥመርቀዋል።የሱዳን፣ የሩዋንዳ፣ የየመን፣ የዩክሬን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የአሜሪካ እና የሌሎች አገራት ዜግነት ያላቸውን ተማሪዎች አሠልጥነዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ ሃምሣ የሚጠጉ ተማሪዎችን በአብራሪነት ሙያ እያሠለጠኑ ይገኛሉ፡፡
ከጉልበት ሥራ ተነስተው የ17 አውሮፕን ባለቤት መሆን ትልቅ ሥኬት መሆኑ አያጠራጥርም።እሣቸው ግን በዚህ አይረኩም።አሁን ላይ ሆነው የደረሱበትን ደረጃ ሲመለከቱ ሊያደርጉት ከሚያስቡትና መድረስ ከሚገባቸው ጋር ሲያወዳድሩ 20 በመቶ ወይም 25 በመቶ እንኳን አልሠራሁም ባይ ናቸው።በአሁን ጊዜ አሥር፣ አሥራ ሁለት እና አሥራ አራት ሰዎች የሚይዙ አውሮፕላኖች ብቻ ሣይሆን ቦይንግ አውሮፕላኖች ሊኖሩን ይገባ እንደነበር ያስባሉ።ካለው ገበያ፣ ካለው የሰው ኃይል፣ ሀገራችን ካላት መልክዓ ምድር አንጻር
ትልቅ ነገር መሥራት ይቻል እንደነበር ይቆጫሉ።
በሚገባቸው ልክ እንዳይሠሩ እጅና እግራቸውን አሥሮ የያዘው የጣሪያ መከለያ ያለው የአውሮፕላን መጠገኛ ቦታ (ሐንገር) አለማግኘታቸው ነው።ይህንን ለማግኘት ከአሥራ ስምንት ዓመት በላይ ጥረት አድርገው ሊያገኙ አልቻሉም።ጥገና ለማድረግ መካኒክ፣ መፍቻና ሌሎች ዕቃዎችን ይዘው የጣሪያ መከለያ ያለው ቦታ ለማግኘት ብቻ ኬንያ ድረስ ይሄዳሉ።ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ብቻ አውሮፕላን ይዞ ሲኬድና ሲመጣ የነዳጅ ወጪ፣ የሠራተኞች አበል፣ የጣሪያ አገልግሎት(ሐንገር) ክፍያ ወዘተ… የአቢሲኒያ ኪሣራ ብቻ ሣይሆን የሀገርም ኪሣራ ነው።ለአንድ አውሮፕላን ሀገር ውስጥ ቢሆን በሁለት ሺህ ዶላር መጠገን የሚቻለውን ናይሮቢ በመሄድ እስከ 20 ሺህ ዶላር ያወጣሉ።ለ17 አውሮፕላኖች በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ወጪዎች ሌሎች አውሮፕላኖችን አስመጥቶ ቢያንስ ከ50 እስከ 80 ለሚደርሱ ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መክፈት ይቻል ነበር።ለመንግሥትም ተጨማሪ ታክስ በመክፈል ሀገር ትጠቀም ነበር።አሁን ካሉበት ደረጃ ከፍ ባለ መልኩ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ቢሰለጥኑ ፕሮፌሽናሎች ሆነው ሀገር ውስጥም ሆነ በሌላው ሀገር በመሄድ ሠርተው ራሳቸውን የመጥቀም ዕድል ይፈጠርላቸዋል።ከስድስት ወር ወዲህ በትራንስፖርት ሚንስትሯ በኩል እየተሠሩ ያሉ አበረታች የሆኑ ጅምሮች እንዳሉ ካፒቴን ሰለሞን ይገልፃሉ።እነዚህ ጅምሮች ተጠናክረው ተግባራዊ ውጤት እንደሚያሣዩ ትልቅ ተሥፋ ሠንቀዋል፡፡
‹‹መንግሥት አሁን በያዘው አቅጣጫ የሚቀጥል ከሆነ ከግሉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጋር ቀርቦ ዘርፉ የበለጠ የሚያድግበትን ሁኔታ የሚመካከርና ስለ ሀገር ጥቅም የሚወያይ ከሆነ ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል።በእኛም ሆነ በሌሎች ድርጅቶች አራትና አምስት ትምህርት ቤቶች ተከፍተው በፋብሪካ ደረጃ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ማሠልጠን ይቻላል።ከአብራሪዎች በተጨማሪ የአቪዬሽን አስተናጋጅ፣ መካኒክ፣ አካውንታት፣ የሕግ ባለሙያ፣ ወዘተ… በሚል ወጣቶችን ብናሰለጥን ፕሮፌሽናሎች ስለሆኑ ሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ተለምነው የሚሠሩበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።እኛ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተግዳሮቶችን ተቋቁመን 21 ዓመት በመቀጠል “ይቻላል!” የሚለውን መንፈስ በተግባር ለማሣየት ሞክረናል።ቢዝነሱን በማየት ሠፈፉን ብቻ ልብላ ከተባለ አቪዬሽን በጣም አስቸጋሪ ነው።በፍቅርና በፍላጎት ተነሣስቶ መሥራት ያስፈልጋል።ልክ ልጅ እንደማሣደግ ዓይነት ሁኔታ ይፈልጋል።ያለበለዚያ በአቪዬሽን ሥራ መዝለቅ አዳጋች ይሆናል።በመንግሥት በኩል ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖር ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት ተሠጥቶት እየታሠበ ያለውና ወደ ተግባር ለመግባት ያለው ተነሣሽነትና እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታ ነው።ሠፋ ባለ መልኩ ለሀገር ጠቀሜታ እንዲኖረው በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የአቪዬሽን አማካሪ ያስፈልጋል፤ ምክር ቤት ያስፈልጋል።በአፍሪካ ደረጃ ብቻ ሣይሆን በዓለም ደረጃ ከፍተኛውን ሥፍራ ለመያዝ የሚያስችል ቁመና አለን።ያለን ብቃት እዚያ ድረስ ነው›› በማለት መንግሥት ቀረብ ብሎ በመነጋገርና በመመካከር የግል አቪዬሽን ዘርፉን ክፍተት የመደገፍ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሣስበዋል።
አቢሲኒያ
ካፒቴን ሰለሞን አቢሲኒያ በረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚን ከሌሎች አገራት መሠል ተቋማት ጋር ሲያወዳድሩት አቢሲኒያ በጣም በሚያሣፍር ደረጃ ላይ እንዳለ ይገልፃሉ።ይህንንም ለማለት ያስደፈራቸው ምክንያት አላቸው።የዛሬ አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ አንድ ትንሽ አውሮፕላን ገዝቶ ታንዛንያ ውስጥ የበረራ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ታንዛንያዊ ጓደኛቸው ትንንሹን ትተን አሁን 30 እና 40 ሰዎች የሚይዙ ትላልቅ አውሮፕላኖች አሉት።‹‹21 ዓመት ሠርቼ፣ ትናንሽ አውሮፕላኖች በመያዜ ትልቅ ነገር እንደሠራ ሰው ቃለ መጠይቅ እየተደረኩኝ ነው።እንደ አቢሲኒያ ብቻ ሣይሆን እንደ ሀገር ሊያሣፍረን ይገባል።ኢትዮጵያውያን ነበርን አፍሪካ ውስጥ የበላይነቱን መውሰድ የነበረብን።ከፈረንጆቹ ጋር ብዙም አንራራቅም 80 ዓመት የሚጠጋ የአቪዬሽን ልምድ አለን›› በማለት እንደ ግል የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መድረስ የሚገባን ደረጃ አለመድረሣችን ግን ያስቆጫቸዋል።
የአመራር ሥልት
ካፒቴን ሰለሞን አቢሲኒያ ውስጥ የሥራ ባልደረባ እንጂ ሠራተኛ የለም የሚል እምነት አላቸው።ለእሣቸው ከሥራ ኃላፊና ፓይለት፣ ከፓይለትና መካኒክ እንዲሁም ከቢሮና ከጽዳት ሠራተኛ መካከል ልዩነት የለም።ሁሉም እንደ አንድ ሠንሠለት ተያይዞ ካልሄደ የሆነ ቦታ ላይ ችግር ካለ ድርጅቱ ሊቀጥል ስለማይችልና ጉዳት ስለሚኖረው የሥራ ባልደረብነት እንጂ የአለቃና ምንዝር ሥርዓት የለም ባይ ናቸው።ይህም ውጤት እንዳመጣላቸው ያስረዳሉ።
ማህበራዊ ተሣትፎ
ስለማህበራዊ ተሣትፏቸው ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ‹‹ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ማህበራዊ ተሣትፏቸውን ለማሣየት ለተቸገሩ ልብስም ሆነ ገንዘብ ሲሰጡ የሚያሣይ በፌስ ቡክ (በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን) ላይ ሲለቁ በማይበት ጊዜ አዝናለሁ።ይህን የሚመስል ተግባር ማድረግ አልፈልግም፤ የምችለውን በአቅሜ ደረጃ አደርጋለሁ።አፌን ሞልቼ የምናገረው ግን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ማድረግ የምችለውን ነገር ሁሉ በተሣትፎም ይሁን በገንዘብ አደርጋለሁ።ከጊዜ ማነስና ከሌሎች ሁኔታዎች አንጻር በምችለው ሙያ በሹፌርነት አንድ ሁለት ሣምንት ግድቡ የሚገነባበት ቦታ ቆይቼ ገልባጭ መኪና በመንዳት መርዳት አለመቻሌና በዚህ መስክ አለመሣተፌ ይቆጨኛል›› በማለት ስለማህበራዊ ተሣትፏቸው ብዙ ማውራት እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።ስለ ማህበራዊ ተሣትፏቸው ለመግለጽ ፍቃደኛ ባይሆኑም በግልጽ ከሚታዩት ውስጥ ለመጥቀስ ያህል በሀይማኖት ሥም የሚነግዱና የሚያጭበረብሩ የሐሰተኛ አገልጋዮችን የአመጽ አካሄድ የሚያመላክትና የሚኮንን መዝሙር ደርሰው በምሥል በማስደገፍ ሠሚ ጆሮና ተመልካች ዓይን ላላቸው አገልጋዮችና ምዕመናን አበርክተዋል፡፡
የሕይወት ፍልሥፍናቸው “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለው እንደሆነ የሚያስረዱት እንግዳችን በጣም የምወዳትና ጓደኛ የሆነችኝ ባለቤት አለችኝ ይላሉ።የአራት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው። ለሰው እንዲገባው ነው እንጂ ልጆቼ ጓደኞቼ ናቸው ይላሉ። ልጆቼ እግዚአብሔርን ፈርተው ሰውን አክብረው እንዲኖሩ ነው የምፈልገው፤ ይህንን በተግባር እንዲያሣዩ እያደረኩ ነው የማሣድጋቸው በማለት ስለአስተዳደግ ሥልታቸው ይገልጻሉ።
ምሥክርነት
ካፒቴን አማረ ገብረሃና የአቢሲኒያ በረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ የነበሩና እስከ ሙሉ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱ ናቸው።ከአየር ኃይል በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተማሪ ሆነው ከመሥራታቸው ባሻገር በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም ሠርተዋል።እስካሁን ወደ 60 ዓመት በአቪዬሽን ውስጥ የሥራ ልምድ አላቸው።ካፒቴን ሰለሞንን የሚያውቋቸው ከ21 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የበረራ ደህንነት ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ነበር።ስለካፒቴን ሰለሞን የሚያውቁትን ሲናገሩ ‹‹ካፒቴን ሰለሞን ግዛውን ሣውቀው የግሉ የአቪዬሽን ዘርፍ ተሣትፎ ለብዙ ጊዜ ደካማ ሆኖ የቆየበት ሁኔታ ነበር።ሥራውን ለመጀመር ሲነሳ ምንም ዓይነት የግሉ ዘርፍ ተሣትፎ አልነበረም።የግሉን ዘርፍ እንደገና ለማበረታታት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች በሚደረጉበት ወቅት ካፒቴን ሰለሞን ግንባር ቀደም ሆኖ መጣ።መጠነኛ መበረታታት ተደርጎለት ፍቃድ አግኝቶ አንድ አውሮፕላን ይዞ መጥቶ ራሱ እያበረረ አንድ ቴክኒሻንና አንድ የቢሮ ሠራተኛ ይዞ በመጀመር በሂደት የ17 አውሮፕላን ባለቤት እንዲሁም ከ100 በላይ ሠራተኞች የሚሠሩበት ድርጅት አድርሷል።ለአቪዬሽን ባለው ቅርበትና ፍላጎት በየጊዜው የተፈጠሩትን ተግዳሮቶች እየተቋቋመ በእሱ ከፍተኛ ጥረት በግሉ ዘርፍ የተለያዩ አስተዋጽኦ ማድረጉና ምሣሌ ሆኖ የሚታይ ድርጅት በመያዝ እዚህ ደረጃ መድረሱ ቀላል አይደለም።ካሉ ተግዳሮቶች የተነሣ ማደግ የሚገባውን ያህል ደረጃ ግን አላደገም።የአመራር ሥልቱን በተመለከተ በአለቃና በሠራተኛ መካከል እንዳለ ግንኑኝነት ሣይሆን እንደቤተሠብ ነው የሚይዘው፤ አሣታፊ የሆነ የአመራር ሥልት ይከተላል።ውጤት የሚገኘው በሠራተኛው ነው ብሎ ስለሚያምን ሠራተኞችን ማዕከል አድሮጎ ሁሉንም በእኩል ዓይን በማየት ያከብራል።በኮቪድ 19 በሽታ ምክንያት ድርጅቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሲገባ ሠራተኛው ሣይፈናቀል እንዴት መቀጠል ይችላል? የሚለውን ለመመለስ በከፍተኛ ሁኔታ ይዞ ሲንቀሳቀስ ሁላችንም በተግባር የምናየው ነው።ፈሪሐ እግዚአብሔር የሆነ ባህሪ ስላለው ሰው በጣም መርዳት ይፈልጋል።ስፓንሰር እየሆነ በነጻ ያሥተምራል፤ እኛ ክርክር የምንፈጥርበት ጊዜ አለ።እሱ ግን ‹በጎነት ይከፍላል› በሚል የሚያደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ።በተለያየ ምክንያት ከበረራ ሙያቸውም ሆነ ከቴክኒሻንነት የተገለሉትን መልሶ አሠልጥኖ ወደነበሩበት ደረጃ አድርሶ በድርጅቱ ተቀጥረው ሙያቸውን የቀጠሉበት ሁኔታ አለ›› በማለት ምሥክርነታቸውን ሠጥተዋል።
ምክር ለወጣቶች
ለወጣቶች ይበጃል የሚሉትን ምክር አጽንኦት ሠጥተው ሲለግሱ፤ ለማብረር ፍላጎቱ ያላቸውን ወጣቶች የምመክረው ከፍላጎት በተጨማሪ ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል። ፍላጎቱና ዓላማው ያላቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥማቸውም ተሥፋ እንዳይቆርጡ፤ ነገ የተሻለ ጊዜና ዕድል ስለሚመጣ ዓላማቸውን ማሣካት እንደሚችሉ ተሥፋ እንዲያደርጉ ነው። ኬንያ ከትናንሽ አውሮፕላን ጀምሮ እስከ ትላልቅ ያላቸው ከ80 በላይ ድርጅቶች አሉ።እኛ ከዚያ በላይ ሊኖረን የሚችልበት ሁኔታ አለ።ይህ ምኞት ሣይሆን አስቻይ ሁኔታዎች ስላሉ ነው።በማብረር ሙያ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ደግሞ ሙያው አለሁ – አለሁ፣ ልታይ…ልታይ የሚባልበት ሣይሆን አብራሪነት የአገልግሎት መሥጫ መሣሪያ መሆኑን ተገንዝበው ሙያቸውን አክብረውና አስከብረው እንዲይዙ እመክራለሁ።ለኢትዮጵያ ወጣቶች አሁን ባለው ሁኔታ ምክር መስጠት በጣም ከባድ ነው።ወጣቶች በሙሉ ዘመኑን መዋጀት አለባቸው፤ ጊዜውን ማገናዘብ ይገባቸዋል።የራሣቸውን ሞሠብ ጠራርገው በልተው ጨርሰው የዚህን ዘመን ወጣት ትውልድ ሞሠብ ለራሣቸው የፓለቲካ ጥቅም ሲሉ የወጣቱን ደም እያጣቀሱ ለመብላት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ።ወጣቱ ቆም ብሎ ማሠብና ለምን? ብሎ መጠየቅ እንዲሁም ነቅቶ ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ ሀይማኖትን ሽፋን አድርገው ሀይማኖቱ ከሚፈቅደው ሥርዓት ውጭ ለግላቸው ጥቅም ብለው ከሚያጭበረብሩ፣ ከሚነግዱ፣ ከሚሠርቁ እንዲሁም ወጣቱ ሥራ እንዳይሠራና እንዲሠንፍ ብሎም የሀገር ፍቅር እንዳይኖረው ከሚያደርጉ አካላት አርቆ ራሱን መጠበቅ አለበት።በቲቮዞና በቡድን ማሠብን ማቆም አለበት።ወጣቱ በነገሮች ሁሉ ማማረር ሣይሆን በሚችለው አስተዋጽኦ አድርጎ ራሱንና ሀገርንም ሊጠቅም የሚችል ተግባር መፈፀም ይጠበቅበታል› በማለት አሣስበዋል፡፡