ሀብታሙ ስጦታው
ኢትዮጵያ አምስት አገራዊ ምርጫዎችን አከናውናለች። ምርጫዎቹ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ይወልዳሉ የሚል ምኞት ቢኖርም የዜጎችን ነብስ ከመንጠቅ ባለፈ ከሽፈው ቀርተዋል። ምርጫ በአገር ደረጃ ዘላቂ ሰላም ያመጣል የሚል መግባባቶች ቢኖሩም ያለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች የሰላም እጦት መንስኤ ሆነው ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዜጎች በተለይ ደግሞ ከሕዝቡ የተሻለ ሀሳብ አለን የሚሉት ፓርቲዎች ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንደሚጠናቀቅ ሙሉ እምነት ቢኖራቸውም ከእነሱ የሚጠበቀውን ተወጥተዋል ወይ? ስትል ዘመን ትጠይቃለች።
ሰላምን ርዕሰ ጉዳይ አድርጋ ያነጋገረቻቸው የብልፅግና፣ የኦነግ፣ የኢዜማ እና የመድረክ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአገሪቱ ከሚሳተፉባቸው የምርጫ ጣቢያዎችን በማመላከት ምርጫ 2013 ሰላማዊ ሆኖ እንደሚጠናቀቅ ተስፋቸው ሙሉ ቢሆንም የዴሞክራሲ ስርዓት ውልደቱ የተሳካ እንዴሆን ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያሏቸውን ሳንካዎች ከእነ ምክረ ሀሳባቸው እንዴህ ተሰናስኗል።
የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ዛዴግ አብርሃ እንደሚገልፁት ፓርቲው ገዥ ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በርካታ ኃላፊነቶች ቢኖሩበትም በምርጫው ከመሳተፍ ባለፈ ዴሞክራሲ በአገሪቱ እውን እንዴሆን በእጁ ያለውን እድል አያባክንም። በመሆኑም በወቅታዊ የሕግ ማስከበር ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ከማይካሄድባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ውጭ በመላ አገሪቱ ይሳተፋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዳስታወቁት በመላው አገሪቱ ባሉ በ450 የምርጫ ጣቢያዎች ይሳተፋል። ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ከነበረው የሕግ ማስከበር ተግባር ጋር ተያያዞ በአስቸኳይ የነብስ አድን ስራው ምክንያት የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከሁሉም ክልሎች እኩል አይከናወንም። በመሆኑም ኢዜማ ቢሮ ከመክፈት ያለፈ ስራ እንደማይኖረው አመልክተዋል። ኢዜማ በምርጫ ወረዳ ደረጃ መዘጋጀቱን ያስታወሱት አቶ የሽዋስ ወደ አስር የሚደርሱ ንቅናቄዎች እና ፓርቲዎች እንደ አንድ ፓርቲ ሆነው ለውድድር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዴና በበኩላቸው ፓርቲያቸው በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ አዴስ አበባ፣ አፋር፣ ደቡብ በተለይ ሲዳማ ላይ የመወዳደር ፍላጎት አለው። ነገር ግን የሰላም እጦቱ ወቅቱን የምርጫ አላስመሰለውም ብለዋል። ‹‹በመድረክ ውስጥ አራት ፓርቲዎች አሁንም አለን፤ አፋር ፓርቲ ወጥቻለሁ እያለ ነው። አረና ትግራይ፣ ሲዳማ አርነት ንቅናቄ እና ኦፌኮ አለን። ‹ትብብር› ከሚባል ፓርቲ ጋር አብረን ልንሰራ ተፈራርመን ምርጫ ቦርድ አስገብተናል። በዚህ ውስጥ እነ ኦነግ፣የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር፣ የአገው ንቅናቄ እና ሌሎች አምስት ስድስት የሚደርሱ ፓርቲዎች ይገኛሉ። በአጠቃላይ አስር ከሚደርሱ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት እየተዘጋጀን ነው፤›› ብለዋል።
‹‹ስሙ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/ ይሁን እንጂ አገራዊ ፓርቲ ነው። ሆኖም ግን በአብዛኛው ኦሮሚያ ይወዳደራል። ኦሮሚያ ባላት መቀመጫ ልክ በፌደራልም በክልልም እንወዳደራለን። ከዚህ ባለፈ በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎችን በማካለል፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣በሐረሪ፣ አዴስ አበባ እና በደቡብ ክልል ይወዳደራል፤›› ሲሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር / ኦነግ/ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ አመልክተዋል።
ቅድመ ግምገማ
አንድ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዴጠናቀቅ ከሚነሱ በርካታ ምክንያቶች ውስጥ የመጀመሪያው የፓርቲ የውስጥ ዝግጅት ነው ያሉት አቶ ዛዴግ የውስጠ ፓርቲ ስነምግባር ደንብ ከማዘጋጀት ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብን መላው አባላት አክብረው እንዴገኙ በማስተማር ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ፓርቲው በምርጫው ሕግጋቶች አክብሮ በመንቀሳቀስ፤ ቢያሸነፍ ፕሮግራሙን በሚገባ ሊፈፅም፤ ቢሸነፍም ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች በመቁጠር ውጤቱን በፀጋ ይቀበላል፤ለአሸነፈውም አካል ሥልጣኑን ያስረክባል ብለዋል።
በአገሪቱ ዴሞክራሲን የማዋለዱ ተስፋ ከትናንት በተሻለ እድሉ አለ። ይህ ግን ስጋቶችንም አብሮ እንደያዘ መዘንጋት የለበትም። ነገር ግን «ተስፋ ከቆረጡ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ »የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ «ተስፋ ያስቆረጠኝ ጉዳይ ብሔራዊ መግባባት ላይ የነበረን ተስፋ መሟጠጡ ነው። የእስረኞች ጉዳይ፣ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆን፣ የቢሮዎች መዘጋት ጉዳይ፣ እነዚህ በሙሉ ችግሮች ሰላም ይፈጥራሉ ተብለው በሁሉም የምርጫ ምዕራፎች ያሉ እንከኖች እየተቀረፉ አይደለም። ስለዚህ ገዥው ፓርቲ የራሱን ፍኖተ ካርታ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ሊመቸው ይችላል። መድረክን የመሰሉ በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዴሰፍን የሚጥሩ ፓርቲዎች የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ግምት አልተሰጣቸውም፤» ሲሉ ወቅሰዋል።
ኦነግ አንድን አገራዊ ምርጫ ለማከናወን ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ናቸው ብሎ ያምናል ሲሉ አቶ ቀጀላ ይገልፃሉ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰላም መደፍረሶች በተለይ ግጭቶች መኖራቸውን የፓርቲው ግምገማ ያመለክታል። እነዚህ ግጭቶች መወገድ አለባቸው። በተለይ በፓርቲ- ፓርቲ፤በመንግስት- ፓርቲ መካከል ባሉ ችግሮች የፖለቲካ አለመረጋጋት ተወልደዋል። እነዚህ የተጠራቀሙ ችግሮች ከምርጫው በፊት እልባት ሊያገኙ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ቀጀላ አስታውቀዋል። ለመፍትሄው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ፓርቲዎችም በትኩረት ሊሰሩ ይገባል። ፓርቲዎች በግጭት ካለመሳተፍ ጀምሮ መፍትሔዎችን በማመቻቸት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ የሽዋስ ገለፃ በአገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። ይህን ጉዳይ ኢዜማ ብቻ ሳይሆን በርካታ ፓርቲዎች እና ህብረተሰቡ ካለፉት ዓመታት በተሻለ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩን በንፅፅር እየገለፁ ይገኛል። በመሆኑም ምርጫ 2013 ሰላማዊ ሆኖ እንዴከናወን በሚሰሩ ስራዎች ላይ የሚወሰን ቢሆንም ሁኔታው የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን ፅኑ እምነት አስቀምጠዋል፡
ምርጫ 2013ን ሰላማዊ በማድረግ ረገድ ገዥው ፓርቲ /ብልፅግና/ ትንሹ የሚጠበቅበትን ሕገመንግስታዊ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል። ምርጫውን ሰላማዊ ከማድረግ አኳያ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም ሕዝብ እና የመገናኛ ብዙሀንም ከመንግስት ያልተናነሰ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል አቶ የሽዋስ። ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ አክቲቪስቶች የሚሰነዘሩ ሀሳቦች በተለይ መርዛማ መልዕክቶችን ሳያላምጥ መውሰድ የለበትም። ህብረተሰቡ ከእነዚህ አካላት በተሻለ የተረጋጋ እና ሚዛናዊ በመሆን ፀረ-ሰላም እና ፀረ- ኢትዮጵያ አመለካከቶችን እስከ ድምፅ የመንፈግ እርምጃ በመውሰድ ሊያስተምራቸው ይገባል ሲሉ ለጉዳዩ አፅንኦት ይሰጣሉ።
በመሆኑም ግራ የሚያጋቡና የሚያደናግሩ መረጃዎችን የማጥራት እና ትክክለኛ መልካቸውን በሚገባ በመፈተሸ ትክክለኛውን ለሕዝብ የማቅረብ የመገናኛ ብዙሀን ተግባር አሁን ካለው በበለጠ በዘንድሮው ምርጫ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። በዚህ ረገድ የተበላሸ መረጃን የሚያስተላልፉ ፓርቲዎችና ጋዜጠኞችም ሥራቸውን በጥንቃቄ ሊያከናውኑ ይገባል ሲሉ የፓርቲያቸውን ቅድመ ግምገማ አ ስቀምጠዋል።
ከዚህ በበለጠ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶች መንግሥትም ጭምር ከሕዝቡ ጋር በተለየ ጥምረት የሚሰሩት ስራ አገሪቱ ያገኘችው እድል ወሳኝ መሆኑን አምነውና ተገንዝበው ሊሆን ይገባል። የዘንድሮ ምርጫ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማዋለድ አንዱ ትልቅ ስር በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። በፓርቲው ግምገማ ላለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ሙከራዎች ተደርገዋል፤ነገር ግን የዴሞክራሲ ስርዓት ምኞት ብቻ ሆኖ ተጨናገፈ ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል፤ አቶ የሽዋስ። እነዚህ ምርጫዎች ከሽፈዋል ተብለው የሚታለፉ አይደሉም፤ አገር እና ሕዝብን ችግር ውስጥ ከተው አልፈዋል። በመሆኑም የዘንድሮው ምርጫ እንደ ኢዜማ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚወጣው መሆኑ የፓርቲው አቋም ነው። በመሆኑም ሁሉም የአገሪቱ ሕዝብ በየትኛውም ሙያ እና የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በአገሩ ጉዳይ እኩል ባለድርሻ ስለሆነ የሚጠበቅበትን ሊያደርግ ይገባል ባይ ናቸው። ያም ሆኖ ይህ ግን ለምርጫው ሰላማዊነት የህወሓት መጥፋት እና የኦነግ ሸኔ እጅጉን መዳከም እና መጥፋት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስቀምጠዋል።
ተስፋና ስጋቶች
ከዚህ ምርጫ የሚጠበቀው ዋናው ውጤት በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ማስፈን ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ በተለይ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዴወለድ ማስቻል አለበት ብለዋል።ነገር ግን መሰረታዊ በሆነ መንገድ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረው ብሔራዊ መግባባት የትም አለመድረስ መንግስት ለጉዳዩ ምንም ትኩረት አለመስጠቱ ለምርጫው ሰላማዊነት አሉታዊ ጫና ይኖረዋል ሲሉ አመልክተዋል።
የህወሓት መወገድ እና የኦነግ ሸኔ መዳከም ብቻውን የምርጫ 2013ን ሰላማዊነት አልጋ በአልጋ ያደርገዋል ብሎ በየዋህነት መናገር እንደማይቻል የሚገልፁት አቶ የሽዋስ የተለያዩ ፈተናዎች ይኖራሉ የሚለውን ስጋታቸውን በማስቀደም ነው። ጥራዝ ነጠቅ እና ፅንፍ የወጣ አስተሳሰብን ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ በተለይ በዘር እና በሃይማኖት ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ፈተናው ይከብዳል። በብሔረሰብ ፣በሃይማኖት፣ በጎሳ እንዴሁም በአካባቢ ተቧድኖ የነበረን የፖለቲካ አስተሳሰብ ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ቁልፍ ፈተና ነው ብለዋል።
‹‹ዴያስፖራ ሆኖ ከአገር ውጭ የነበረ፤ ግማሹ ጠመንጃ ታጥቆ በረሀ የወረደ፤ እኛን ጨምሮ ገሚሱ እስር ቤት የቆየ በመሆኑ ይህን አስተሳሰብ በአንድ ከተማ በተለይ በአንድ ጠረጴዛ አስቀምጠህ በሀሳብ እንድንፋጭ ማድረግ ትልቅ ስራ ነው፤›› ሲሉ አቶ የሽዋስ ይናገራሉ። ይህ ሁኔታ በአገሪቱ ካለው ድህነት እና ኋላቀርነት ጋር ተዳምሮ ፈተናውን የበረታ ያደርገዋል ብለዋል። የኢኮኖሚው ግሽበት እና የስራ አጥነት ቁጥር መብዛት በምርጫ 2013 ሰላማዊነት ላይ የራሱን ክንድ ያሳርፋል። ወጣቱ ስራ እንደልብ ማግኘት አለመቻሉ እና ለኑሮው የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ግብዓቶች አለማግኘቱ ካለው የፖለቲካ ደንቃራ ጋር ተዳምሮ የምርጫውን አጠቃላይ ሰላም እንዳያውክ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ ክፉኛ እየተገዳደረው የሚገኘው የማህበራዊ ሚዴያ ተደማሪ ፈተና እንደሚሆን አቶ የሽዋስ ይናገራሉ። በጣም በተለየ እና ሁሉም ሰው የፈለገውን በሚተፋበትና በሚወረውርበት ይህ ሜዳ ለምርጫው ፈተና ነው ብሎ ኢዜማ ያመለክታል። ፍፁም ተጠያቂነት የሌላቸው ሀገር ሊያፈርስ የሚያስችል አጥፊ መረጃ የሚያመላልሱ የበዙበት ሜዳ በመሆኑ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል። ማህበራዊ ሚዴያ ሀገር እስከማፍረስ የሚደርስባቸው በርካታ መልኮች እንዳሉት የሚጠቁሙት አቶ የሽዋስ ጉዳዩ ከእንጀራ ጋር ሁሉ የተያያዘ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገኙበትም ነው። እነዚህ ዜጎች ምስሉንም ሆነ ፅሁፍ /Like/ ድጋፍ በመቁጠር እንጀራ የሚበሉበት መንገድ በመሆኑ ከህልውና ጋር ተያይዟል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። አንድ ቤተሰብ የበላው የጠጣው ሳይቀር የተነጋገረው ጉዳይ ማህበራዊ ሚዴያ ላይ ተዝረክርኮ ስምህ የሚጠፋበት፤ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ሆኖ ዜጎች በተለይ ንፁሀን ዳግመኛ እንዳይነሱ የሚመቱበት ሆኖ በተግባር ታይቷል። ይህ ሁኔታ በተለይ በምርጫ ወቅት ከእሳት በላይ ይለበልባል ብለዋል።
ፓርቲዎች ሀሳብ ላይ የሚንጠለጠሉ ከሆነ ሀሳቦች መቀራረብ ይችላሉ፤ ወጣቱ ህይወት ላይ ለመንጠልጠል ከሆነ ደግሞ ሕዝብ ሌላ ዋጋ መክፈል የለበትም ሲሉ የኢዜማ ሊቀመንበር አፅንኦት ይሰጣሉ። ፓርቲዎች በወጣቱ ህይወት ላይ ሲንጠለጠሉ የምርጫውን ሰላማዊነት በማደናቀፍ ራሳቸው ፈተና ይሆናሉ። ፓርቲዎች /ኢዜማን ጨምሮ/ አዴስ የዴሞክራሲ ሥርዓትን በአገሪቱ ለማዋለድ መስራት ላይ ብቻ ትኩረታቸው ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። በመሆኑም ሀሳብ ለመሸጥ የመጣ ተወዳዳሪ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ሕዝብን ላለማስጨረስ አስቀድሞ ቃል መግባት ይጠበቅበታል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በውስጥ ችግር እየተናጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቀጀላ ለምርጫው ዝግጅትም ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። ምናልባትም በምርጫው ላይሳተፉ እንደሚችሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በውስጥ አሰራር ያጋጠማቸው ችግር በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደሪያ ሕግ የማይፈቀዱ ሁኔታዎች ተወጥሯል ሲሉም ጉዳዩን አስረድተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊ ስላለው በአገሪቱ ምርጫ ላይ አንድ ፈተና ሊሆን ይችላል የአቶ ቀጀላ ሀሳብ ነው። ኦነግ ውስጥ በአንድ በኩል ለችግሩ መንግሥትን ጥፋተኛ የሚያደርግ አካል ያለበት፤ በሌላ በኩል ዋናው የውስጥ ችግር ሳቢያ ፓርቲው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።
ምርጫ 2013 ሰላማዊ ሆኖ እንዳይከናወን ትልቁ ፈተና እየተፈፀሙ ያሉ እስሮች ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ለምርጫ በምንሳተፍባቸው አብዛኛው ኦሮሚያ ውስጥ ገዥው ፓርቲ ቢሮዎችን ዘግቷል። ብዛት ያላቸው አባላት በተለይ ፓርቲያችን ለበርካታ የምርጫ ስራዎች የመደባቸው አባሎች ሳይቀሩ ያለበቂ ምክንያት መታሰራቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ኦነግን ጨምሮ ከመንግሥት ጋር የተወሰኑ ምክክሮች ነበሩ። እሱም አልተፈታም። የኦነግ ችግር ከእኛ የባሰ ነው፤ ብ ዙ አባላት ታስረውባቸዋል። ቢሮዎቻቸው ከአዴስ አበባ ጀምሮ በአብዛኛዎቹ ተዘግተዋል። ብሔራዊ መግባባት የምንለው ታጣቂዎችን፣ የታሰሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አንድ መጥተው ፍትሐዊ ምርጫ እናድርግ፤ይሄም ይቻላል ነው የምንለው፤››ሲሉ ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
ኢዜማ እንደ ፓርቲ በበርካታ ክልሎች የአባላት እስር እና የቢሮ መዘጋት እንዳጋጠመው አቶ የሽዋስ አስታውቀው ፓርቲው በመላ አገሪቱ ስለሚወዳደር ጥቃቱ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም ይላሉ። ችግሩ ከመንግስት እና አካባቢው ‹‹የእኛ ነው›› ከሚሉ የሰፈር ጎረምሶች በሁለት መንገድ የሚከሰት ነው። በኦሮሚያ፣ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ችግሮች ነበሩ፤ የተሻለ የነበረው በደቡብ ክልል እና አዴስ አበባ ነው። በመሆኑም ኢዜማ ችግሮች ቢኖሩበትም እነዚህን ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
‹‹ኦሮሚያ ውስጥ ቢሮ ይዘጋብናል፤ ትግራይ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተዘጋብን በቅርቡ ነው የከፈትነው። ትግራይ ውስጥ ለአብነት ዘጠኝ ወረዳ ውስጥ የነበረንን ቢሮ ወደ ሁለት ሶስት ዝቅ ብሎ አባሎቻችን እየተሳቀቁ ነበር የሚሰሩት። ከሕግ ማስከበሩ በኋላ ብልፅግናን ጨምሮ ፓርቲዎች ቢሯቸውን እየከፈቱ ነው›› ሲሉ አቶ የሽዋስ ይገልፃሉ።
ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚፈልገው የፓርቲ አባላትን በማሰር አሊያም ቢሮዎችን በመዝጋት አይደለም ሲሉ ሀሳባቸውን ያቀረቡት አቶ ዛዴግ ይሄ አካሄድ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ሀሳብ የሌላቸው አካላት የሚጠቀሙት አካሄድ ነው። ብልፅግና በአገሪቱ ሰላም ፣ዴሞክራሲና እድገት ሊያመጡ ይችላሉ ያላቸውን ሀሳቦች ለሕዝብ አቅርቦ ሕዝብም አምኖበት እንዴመርጠው ነው በሀቅ እየሰራ ያለው። በራሱ አሊያም ሕግን ጥሶ የታሰረን አካል በሕግ አግባብ መጠየቅ እንጂ ለመወነጃጀል የሚውል መሆን የለበትም፤ ተገቢም አይደለም ብለዋል።
ማንም ፓርቲ እንዳይወዳደር ታግዶ፤ ቢሮ ተዘግቶበት በምርጫ እንዴሳተፍ ብልፅግና አይፈልግም። ሙሉ በሙሉ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ በምርጫው አሸናፊ መሆን ይፈልጋል። ሁሉም ነገር ተሰርቶ ቅሬታ ቢኖር ባለው ሥርዓት በመነጋገር ይስተካከላል። በፓርቲ ደረጃም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲኖራቸው ምርጫ ቦርድ እየሰበሰበ ችግሩ የሚፈታበት የሶስትዮሽ ተጨማሪ ሥርዓት አለ። ይህ በኦሮሚያ፣ቤኒሻንጉል እና ሌሎች አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በአጠቃላይ ችግር የደረሰባቸው ፓርቲዎች በምርጫ በሚሳተፉበት የትኛውም ቦታ ያጋጠማቸውን ችግር በተዘረጉ መድረኮች አቅርበውት ሊፈታ ይገባል። ብልፅግና ሁሉም ፓርቲ በምርጫው እንዴሳተፍ ይፈልጋል። ፓርቲዎች የሚያጋጥማቸው ችግር ካለም ተረዳድቶ አንድም ፓርቲ ሳይቀር የአቅሙን እንዴወዳደር በዘመቻው ተሳትፎ ሕዝብም ሀሳቡን ተረድቶ እንዴዳኘው እንፈልጋለን።
ምርጫ ቦርድ
‹‹የምርጫ ቦርድ መዋቅር እያስደነገጠን ነው። መዋቅሩ ወደታች ሲዘረጋ በየዞኑና ወረዳው ምርጫውን ያስፈፅማሉ ተብለው ተመልምለው የተመደቡ አስፈጻሚዎች የማይመጥኑ ናቸው። የሕግ እና የፖለቲካ ሳይንስ ሌላው ቢቀር የሶሻል ሳይንስ እውቀት እንኳ ያላቸው ሳይሆኑ ዝም ብሎ የተመደቡ ናቸው። ኤሌክትሪሺያን፣ እንጨት አውራጅ፣ተላላኪ ቢልም ቦታው የምርጫ ጉዳይ በመሆኑ እነዚህን ሙያዎች አይመጥንም፤›› ሲሉ መድረክ በሊቀመንበሩ በኩል ወቅሷል።
ከዚህ ቀደም አስፈጻሚዎች የሚታሙት በሌብነት ነው፤ የአሁኖቹ ደግሞ ምርጫን በማስፈፀም እውቀት ችግር ነው። በመሆኑም የበለጠ ሊበጠብጡና ምናልባትም ያልተጠበቁ ችግሮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለው ሁኔታውን ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ መናገራቸውን ጠቁመው ነገር ግን በጉዳዩ ላይ በቂ ምላሽ አልተሰጠም ባይ ናቸው። ‹‹በአጠቃላይ በምርጫ አስፈፃሚዎቹ እምነት እንደሌለን ለምርጫ ቦርዱ ፅፈን አስገብተናል። ምንም መልስ አልተሰጠንም። ምርጫ ቦርድ ግን ጨዋታውን ቀጥሏል። በእነዚህ ጥቅል ጉዳዮች በምርጫ ቦርዱም ምንም እምነት የለንም።›› ሲሉ ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ በሰው ኃይል፣ በመዋቅርም ሆነ በሕግ ማቋቋሚያም ገና እየተፈጠረ ያለ ተቋም ነው። በመሆኑም በለውጥ ሂደት ላይ ያለ ተቋም ነው። አሁን ምርጫ ቦርድ ላይ የሚሰጠው አስተያየት ‹አንድ ህፃን ተወልዶ፤ ወዴያው እሩጥ› እንደ ማለት ነው ሲሉ አቶ የሽዋስ የፕሮፌሰርን ሀሳብ ይቃወማሉ። ተቋሙ እየተፈጠረ ያለ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምስረታው ምርጫ እንዴያስፈፅም ሌላ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
ምርጫ ቦርድ አሁን ያለበት ሁኔታ ይህን ይመስላል ማለት ከዚህ በፊት ችግር የለበትም፤ ቅዱስ ነበር እየተባለም አይደለም። ከዚህ በፊት የነበረው መዋቅር ስልጠና አግኝቶና ተሻሽሎ ካልመጣ ወይዘሪት ብርቱካንን እና የቦርድ አባላትን በመምረጥ የሚመጣ ለውጥ የለም። አሁን ያሉት መሪዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ያላቸውን ፍላጎት እና ቀናኢነት ማየት ያስፈልጋል። በወይዘሪት ብርቱካንም ሆነች በዶክተር አብይ ዙሪያ ያሉ መሪዎች ሁኔታውን በሚገባ ተረድተው እንዴሰሩ ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደተያዘ በግልፅ የሚታይ ነው ብለዋል፤ አቶ የሺዋስ።
እንደ አቶ የሺዋስ ገለፃ ይህን ሁኔታ በደንብ ተረድቶ የሚፈጠሩ ችግሮችን አብሮ በጋራ መፍታት እንጂ ‹‹እምነት አጥተናል›› ማለት መፍትሔ አይደለም። በዚህም ሁኔታ ‹ወደቀ ሲባል ተሰበረ› እያልን ተቋም መመስረት አንችልም፤ ሰላማዊ ምርጫ ለማከናወን ስለሚያዳግት አገራችንን ወደምንፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሻገር አንችልም። የሚፈጠር ችግርም ቢሆን የእኛው ጉድ ስለሚሆን አብረን መስራት ነው የሚገባን። ነገር ግን ሁኔታው የማያሰራ እና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከሌለው እንጂ ሙያ ነክ ጉዳዮችን በጋራ ቁጭ ብሎ መፍታት አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት የቤት ሥራ ነው።
ምርጫ ቦርድ ላይ ሶስት ነገሮች ተለውጠዋል። አንዱ የሰው ኃይል ነው፤ የሰው ለውጥ ሲደረግ ባልተለመደ ሁኔታ ሁሉም የፓርቲ አመራር ‘እከሌ ቢሆን እከሌ ቢሆን’ የሚል አስተያየት ሰጥቷል። የመዋቅር ለውጥ ታች ድረስ ሊደረግ ሲል ፓርቲዎች በእያንዳንዱ ሰው ላይ ግልፅ አስተያየት እንዴሰጥ እድሉ ተመቻችቷል። ይህ በሁሉም ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈፀመ ነው። ችግር አይኖርም ባይባልም ችግሩ የጋራ ነው ብሎ በጋራ የመፍታት ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ችግር ሲከሰት የምንወራወረው ጉዳይ መሆን የለበትም። ስለሆነም ችግር ሲፈጠር የአሜሪካ አሊያም የሌላ ወዳጅ አገር ምርጫ ቦርድ የሚያስፈፅምልን አይደለም። ስለዚህ ችግሩን መረዳትና መፍታት ያስፈልጋል።
አለመሳተፍና መሳተፍ
ለምን ስጋት ይሆናሉ?
በምርጫ ወቅት ከውጤት ጋር ተያይዞ ፓርቲዎች የማሸነፍ ዕድላቸውን በግልፅና ምክንያታዊ በመሆን ገምተው መግባት አለባቸው የሚሉት አቶ የሺዋስ አንድ ፓርቲ የማሸነፍ እድሉ 50 በመቶ ሲሆን፤ የመሸነፍ እድሉም ተመሳሳይ ነው። ኢዜማ ሊያሸንፍ አሊያም ሊሸነፍ እንደሚችል አምኖ ነው የሚገባው። ካሸነፈ ያሸነፈውን ክልልም ይሁን ዞን፣ወረዳም ይሁን ቀበሌ ያስተዳድራል። በመሆኑም ሕዝብ የሰጠውን አደራ ለመቀበል ዝግጁ ነው። ከተሸነፈ ደግሞ ውጤቱን ተቀብሎ ስህተቱን አሻሽሎ ለቀጣይ ይዘጋጃል። ለአንድ ጊዜ ምርጫ ብቻ የሚደረግ ዝግጅት የለም።
ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲ በዚህ ልክ መዘጋጀት አለበት። ነገር ግን በማህበራዊ ሚዴያ ላይ ድጋፍን ቆጥሮ ‹‹አሸንፌያለሁ፤ አልቋል ነገሩ፤ ምርጫ ቦርድ የሚለውን ውጤት ተቀበል›› የሚል ፓርቲ ካለ ጨዋታው ሌላ ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም በማህበራዊ ሚዴያው ላይ /ላይክ/ ድጋፍ የሚሰጠው ሰው አሜሪካ አሊያም አውሮፓ ሆኖ እንጂ አገር ውስጥ አይደለም። ‹‹መራጩ ደግሞ የእኛ ወረዳ ሕዝብ ነው። የወረዳው ሕዝባችን ደግሞ አንዱም ማህበራዊ ሚዴያ ላይጠቀም ይችላል፤ በመሆኑም የማህበራዊ ሚዴያው ጩኸት ሀቁን አያሳይም።›› ያሉት የኢዜም ሊቀመንበር ለምርጫ የሚኖር ስነልቦና ሀቅ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው።
ስለሆነም ከተሸነፉ ውጤቱን ለመቀበል መዘጋጀት ይገባል። በማስፈራራት፣ ‹‹እንዴህ አደርጋለሁ›› ማለት ፍፁም አይሰራም። በዚህ ቅኝት ውስጥ መጓዝ እንጂ ‹የአንዱ ደረት ከብረት፤ የሌላው ከካርቶን› የተሰራ አድርጎ በማሰብ በጉልበት ውጤትን መጠበቅ አይገባም። ‹‹እኛ ወንድማማቾች ነን፤ ለምን እንጠፋፋለን? ነገር ግን የውድድር ሜዳውን በሚያሳምነን ልክ የእኛ እናድርገው፤ ለዚህ የተከበረ ሕዝብ ደግሞ በታሪካችን የሚፈልገውን መሪ እንዴመርጥ አቅም እንሁን›› ሲሉ አቶ የሺዋስ ጦረኛነት አያስፈልግም፤ አይገባምም ብለዋል።
ፕሮፌሰር መረራ በአቶ የሺዋስ ሀሳብ በመስማማት ሲገልፁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሸነፉም ቢያሸንፉም በሀቅ የሚደረግ የምርጫ ውድድር ውስጥ መግባት አለባቸው። ፓርቲዎች ቢሸነፉም ችግራቸውን ሁሉ ወደ ገዥው ፓርቲ ማጣበቅ የለባቸውም ብለው ፓርቲዎች የራሳቸውን ስጋትና ጭንቀት ወደ ገዥው ፓርቲ መውሰድ አይገባም።
ኦነግ በምርጫ 2013 የማይሳተፍ ከሆነ የአገሪቱ የምርጫ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ትልቅ ችግር ይፈጥራል የሚሉት አቶ ቀጀላ ፓርቲው ከምርጫው የሚገለልበት ጠንከር ያሉ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም ተጠያቂው የድርጅቱ ሊቀመንበር ነው። በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ አስተዳደራዊ ካልሆነ በስተቀር ሕጋዊ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም ብለዋል። ኦነግ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ወደ ምርጫው የማይገቡ ከሆነ የሰላም መደፍረስ ሊያስከትል ይችላል።
አቶ የሺዋስ በአቶ ቀጀላ ሀሳብ አይስማሙም። የትኛውም ፓርቲ በውስጥ ችግሩ ምክንያት በምርጫው ስለማይሳተፍ ሰላም አይኖርም ማለትም ሆነ በምርጫው ተሸንፎ ሲያበቃ አልቀ በልም ‹‹እኔ አሸንፌያለሁ›› ማለቱ በዴሞክራሲ ሥርዓት ልኬት ስታየው ‹‹ሕዝቡ የእኔን ሀሳብ ብቻ ነው የሚጠብቀው ሌላ ሀሳብ የለም፤›› የሚል ያልሰለጠነ መልክ ውስጥ ተገባ ማለት ነው። ይህ ለራስ፣ ለፓርቲም ሆነ ለአገር አይጠቅምም፤ አያስፈልግም።
እንደ አቶ የሺዋስ ገለፃ ለሀገር አቀፍ አስር ሺ፤ የክልል አራት ሺ አስፈርሙ ተባለ። የተሟላ መዋቅር ስላለን ለእኛ ቀላል ነበር። ለአንዳንድ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ችግር አልነበረባቸውም፤ በተሳካ ሁኔታ አስፈርመዋል። አንዳንዶቹ ግን የሚጠበቅባቸውን ማስፈረም ሳይችሉ 40 ሰው አባል ሳይኖራቸው ‹‹እኛ የተሰረዝን እንደሆን ሰማይ እና ምድር ነው የሚጣበቀው›› አሉ። ነገር ግን ምንም የሕዝብ ድጋፍም ሆነ የሚፈለግ የአባላት ብዛት አላሟሉም፤ አልተመዘገቡም፤ በዚህም ከፉከራቸው ውጭ የመጣ ነገር የለም።
በዚህ ምርጫ ከሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲ የሚጠበቀው የተቀመጠውን ሕግና ሥርዓት አክብሮ መስራት እንጂ አለመመዝገባቸውን የሀገር ችግር አድርገው ማምጣት አይገባቸውም። ራሳቸውን የአለም ፍጻሜ አድርገው የተናገሩ ሰዎች እኮ አለፉ፤ ከእነዚህ ሰዎች እንዴት አንማርም። ይህ እኮ ከዚህ በኋላ አይሰራም። ‹‹አሁን አልተዘጋጀሁም፤ ለቀጣይ በሁሉም ረገድ ተዘጋጅቼ እመጣለሁ›› ማለት ይሻላል። ነገር ግን የሕዝብ ወኪል ሳይሆኑ፤ ሕዝብ ሳይመርጣቸው ራሳቸውን ‹‹ወኪል ነን›› ብለው መቅረብ አይገባም የአቶ የሺዋስ አስተያየት ነው።
ምን ይሰራ?
ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ እድል ሆኖ 51 በመቶ የሚባል ብሔረሰብ የለም። በጣም ብዙ ነኝ የሚለው እንኳ 20 ወይም 25 በመቶ ነው። የጋራ አገር እንጂ ማንም ጠፍቶ ማንም መኖር እንደማይችል የሚያሳይ ነው፤ በቅርብ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ40 እስከ 45 በመቶ የሚደርሱ ዜጎች ውህድ ማንነት ያላቸው ናቸው። በመሆኑም መጪው ሁኔታ የተለየና የተሻለ ነው።
እንደ አቶ የሺዋስ ሀሳብ አሁን በአገሪቱ ያለውን ይህን እውነታ በቅጡ መረዳት በቅድሚያ ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው፤ በመሆኑም ትልቁ እድል ብልፅግና ፓርቲ እጅ ነው፤ በተለይ ደግሞ ዶክተር አብይ። ዋናው የመንግሥት ሥራ ሕግ ማስከበር ነው። የፖሊስ ተቋም፣የደህንነት ተቋም፣ የመከላከያ ተቋም፣ የሰላም የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማት «የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፋ፤ አልሰፋ» እያሉ መናገር አይገባቸውም፤አይመለከታቸውም። በእርግጥ እነዚህ ተቋማት የማያልፏቸው መስመሮች አሉ፤ እነዚህን ለይቶ መስራት ይገባቸዋል።
ሀገረ መንግሥቱ እንዴቀጥል ሕግ መከበር አለበት። ምክንያቱም ከአገር በተቃራኒው መቆም አይቻልም። በቅርቡ በአሜሪካ ምርጫ የታየው ሀቅ ስንመለከት ከሥልጣን የተወገዱት ትራምፕ እንደ ግለሰብ የፈለገውን ሊሆን ቻለ፤ ነገር ግን ከአሜሪካ በተቃራኒው መቆም እንደማይችል የፍትሕ ስርዓቱ/ተቋማት/ ዓለምን ጭምር አስተማሩበት።
ፕሮፌሰር መረራ ሕግ ማስከበር ላይ «የተለየ አስተያየት አለኝ» ይላሉ። ጠዋትና ማታ የሕግ የበላይነት እየተባለ እስኪሰለች ድረስ ይነገራል። ማን ነው በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን የሚጥሰው? የሚለው በአግባቡ አይመለስም። ፍርድ ቤት ሁለት ሶስት ጊዜ ፈቶት፣ ፖሊስ ደግሞ ደጋግሞ ያስርብናል። ስለዚህ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሕግና እና ሕዝብን ማክበር አለባቸው የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትም ቢሆኑ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ። ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ካላንቀሳቀሳቸው ምንም አይሰሩም። ብቻቸውን መስራት እንደማይችሉ ብዙ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል ሲሉ ይመክራሉ።
«ሕግን ማክበር እና ማስከበር የብልፅግና ፓርቲ መለያው ነው። ያለ ምንም ድርድር አገራዊ የሕግ ማስከበር ሕገመንግሥታዊ ግዴታውን ለሚፈለገው የዴሞክራሲ ሰርዓት ግንባታ ትዕግስት በተሞላበት አካሄድ እየፈፀመ ነው፤ ዜጎችም እንዴፈጽሙት እያደረገ ይገኛል። በአጠቃላይ ፓርቲው በአገሪቱ ያሉ የጫወታ ሕጎችን በማክበር ወደ ምርጫው የገባበት ሁኔታ የመጀመሪያው ተግባሩ ነው፤» ሲሉ አቶ ዛዴግ የሕግ ማስከበሩን ጉዳይ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሁለተኛው ጉዳይ ብልፅግና ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ሌላ ተጨማሪ ድርብ ኃላፊነት አለበት። ይህ ኃላፊነት የዜጎች ደህንነት የተሟላ እንዴሆን ወደ ምርጫ ጣቢያ ከመሄድ ጀምሮ ዜጎች ደህንነት እንዴሰማቸው ያደርጋል። በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የራቁ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዴመለሱ የሚያስችል ሰላም የማስከበር ሥራ በሚገባ ማከናወን እንደሚጠበቅበት አቶ ዛዴግ ይገነዘባሉ።
ገዥው ፓርቲ የፀጥታ ተቋማትን በማስተባበር ምርጫ ቦርድም ያለበት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል። ይህ ኮሚቴ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል። ስለዚህ ግጭት ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የሚያስችል ሥራ እየሰራ ነው ብሎ ያምናል ያሉት አቶ ዛዴግ መንግሥት ግጭትን ለማስወገድ የሚያስችል ቁመና ላይ ከመኖሩ በተጨማሪ ችግር ሲያጋጥም የሚፈታበትን ሥርዓት በመዘርጋቱ የትኛውም ፓርቲ አለ የሚለውን ችግር ወይም ቅሬታ አቅርቦ ይፈታል የሚል እምነት ተይዟል። ‹አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም› እንደሚባለው ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ምርጫው በአገሪቱ ታሪክ ዴሞክራሲን በሚገባ ለማዋለድ መሆኑን ተገንዝበው በምርጫው ሰላማዊነት ላይ የጋራ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
ስለዚህ በአገር ላይ ሕግ ማስከበር ምን ማለት ነው? ሕገ መንግሥቱን በሥርዓት እስከምንቀይረው ድረስ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው፣ መዝሙሩ፣ ብሔረሰቦች፤ ሃይማኖ ቶችን መንካት ወይም እንዴጋጩ ማድረግ ለማንም መፈቀድ የለበትም። በምርጫ ክርክር ወቅትም እነዚህን መጠለያ ማድረግ አይገባም የአቶ የሺዋስ ምክረ ሀሳብ ነው። ይህን ሥርዓት ማስከበር ደግሞ የመንግሥት ነው። ዶክተር አብይ አገሪቱን ወደሚፈለገው ደረጃ አሸጋግረው በታሪክ እንደ ማንዴላ ሊነሱ የሚችሉበት እድል አለ ሲሉ ጠቁመዋል፡
«ማንዴላ ከ27 ዓመት እስር በኋላ አራት ዓመት ነው የመሩት፤ ነገር ግን ዛሬ ድረስ ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የሁልጊዜ መሪ ናቸው። ከእርሳቸው በኋላ ብዙ መሪዎች ተቀያይረዋል። ማንዴላ ግን እነዚህን ሁሉ ተሻግረው ስማቸው የሚጠራ መሪ ናቸው። ስለዚህ በኢትዮጵያም ዶክተር አብይ ይህን የመሰለ እድል በእጃቸው አለ። በመሆኑም ይህን ፕሮጀክት በትክክል ማጠናቀቅ ከቻሉ ስማቸውን ይተከላል ብለዋል» አቶ የሺዋስ።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ ተበላሸ፤አበላሸ›› እየተባለ ሲናገሩ ይታያል ያሉት አቶ የሺዋስ ዛሬም እንደትናንቱ በእጃችን ያለውን የአሁኑን ትውልድ እንዳናበላሸው በተለይ ምርጫውን በጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ማከናወን ይገባል፤ ይጠበቃልም። ይህ እድል እንዳለፉት የ60ዎቹ የሚበላሽ ከሆነ እከሌ ፓርቲ አበላሸው አይባልም ፤’ይህ ትውልድ አበላሸው’ ነው የሚባለው። ስለዚህ ተወቃሽ ትውልድ ላለመሆን ጭምር መሥራት ይገባል። በተወዳዳሪነትም ሆነ በመራጭነት የሚሳተፈው የትኛውም ዜጋ ኃላፊነት ወስዶ ሊሰራ ይገባል።
በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት እድሉ አለ ሲባል አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታው የተሻሻለ መሆኑ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ወዳጅ አገራትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲንቀሳቀሱ ይታያል። የአገር ሽማግሌዎች አባገዳዎች እና ትላልቅ የሃይማኖት አባቶች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ያለውን ቁርጠኝነት በሚገባ ይዞ ከዘለቀ በእርግጥም ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሊወለድ ይችላል የሚል ተስፋ አለ። ተስፋዬ ከገዥው ፓርቲ በተለይ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችና ልምዶችን በሚገባ ከወሰድን ዴሞክራሲ እውን ይሆናል።
‹‹ከምርጫ በኋላ አገር አለች፤ ትቀጥላለች። ለሥልጣን ሁላችንም እንፎካከራለን ነገር ግን ምርጫን እንደ አንድ የዓለም ፍፃሜ አድርገን ከምርጫው በኋላ የአገርን ቀጣይነት ሳናስብ ወደ ምርጫ መገባት የለበትም ፓርቲያችን ወደ ምርጫ ዘመቻ ሲገባ የሚፎካከራቸው ፓርቲዎች እንዳሉ በመገንዘብ በወንድማማችነት መንፈስ ነው። ለሥልጣን እየተፎካከርን ሕዝብና አገርን ማሰብ ይገባል።›› የአቶ ዛዴግ መልዕክት ነው።